በቀጣዩ የፈረንጆቹ ዓመት መጀመሪያ በአፍሪካ ታላቁ የእግር ኳስ ውድድር የሆነው የአፍሪካ ዋንጫ ለ33ኛ ጊዜ ይካሄዳል፡፡ ይህንን ውድድር የምታስተናግደው ካሜሮንም ዝግጅቷን በማጠቃለል ላይ ትገኛለች፡፡
ለሁለት ዓመታት በኮቪድ 19 ወረርሽኝና ሌላ ምክንያት የተራዘመው ውድድሩ ከጥቂት ወራት በኋላ 24 ሀገራትን በማሳተፍ ይደረጋል፡፡ ይህንን ተከትሎም የውድድሩ አዘጋጅ የሆነው የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን ከስፖንሰሩ ጋር በመሆን የቅድመ ውድድር ስራዎችን በመስራት ላይ ይገኛል።
ከስራዎቹ መካከል አንዱ የሆነውም ዋንጫውን በተለያዩ ሀገራት በማዞር እንዲጎበኝ ማድረግ ነው። ከሰሞኑም በአህጉር አቀፍ ደረጃ ትልቁ በሆነው ውድድር ለአሸናፊዎች የሚሰጠው ይህ የአፍሪካ ዋንጫ ወደ ኢትዮጵያ መጥቶ ተጎብኝቷል፡፡ ታሪካዊው ዋንጫ ኢትዮጵያን ጨምሮ 18 ሀገራት በውድድሩ ስፖንሰር ቶታል ኢነርጂስ አማካኝነት ለእይታ የሚቀርብ ይሆናል፡፡
ከረጅም ዓመታት በኋላ ወደ መሰረተችው ውድድር የተመለሰችው ኢትዮጵያ የዋንጫው መዳረሻ ከሆኑት ሀገራት መካከል አንዷ ስትሆን፤ ዋንጫውም የሀገሪቷ ርዕሰ ከተማ እንዲሁም የአፍሪካ መዲና በሆነችው አዲስ አበባ ለአምስት ቀናትም ቆይታ የሚያደርግ ይሆናል፡፡
ዋንጫው ከትናንት በስቲያ ከሰዓት ኢትዮጵያ ሲደርስም የቶታል ኢነርጂስ የኢትዮጵያ ማርኬቲንግ ማኔጀር እና ሶፊ፣ የድርጅቱ ብራንድ አምባሳደር ኃይሌ ገብረስላሴ እንዲሁም የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ተወካይ ሰለሞን ገብረስላሴ አቀባበል ማድረጋቸውን የሶከር ኢትዮጵያ መረጃ ይጠቁማል። አንጋፋው አትሌትና የቶታል ኢነርጂስ በኢትዮጵያ አምባሳደር ኃይሌ በወቅቱ ዋንጫው በመምጣቱ የተሰማውን ደስታ ገልጾ፤ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በመድረኩ መልካም ውጤት እንዲያስመዘግብም ተመኝቷል፡፡
ዋንጫው በሚኖረው የአም ስት ቀናት ቆይታም በቦሌ እና ሜክሲኮ በሚገኙት የቶታል ኢነ ርጂስ አገልግሎት መስጫዎች በይፋ የሚቀመጥ ሲሆን፤ የእ ግር ኳስ ደጋፊዎች በነጻ ፎቶ እንዲነሱ እድል ተመቻችቷል። ነገ ደግሞ በሃያት ሪጀንሲ ሆቴል በሚዘጋጀው መድረክ ላይ የሀገሪቷ ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች ተገኝተው እንዲመለከቱት ለማ ድረግ ታቅዷል፡፡ በመርሃ ግብሩ ላይም የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አመራሮች፣ የብሄራዊ ቡድን አባላት እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገ ኙበት በኢትዮጵያ የሚኖረው ጉብኝት የሚጠናቀቅ መሆኑም ተጠቁሟል፡፡
እአአ በ1957 የተመሰረተው የአፍሪካ ዋንጫ ሶስት ሀገራትን (ኢትዮጵያ፣ ግብጽ እና ሱዳን) ብቻ ነበር በአባልነት ያቀፈው፡፡ በሂደትም የሀገራቱን ቁጥር በማሳደግ ከሶስት ወራት በኋላ የሚካሄደው የአፍሪካ ዋንጫ 24 ሀገራትን የሚያሳትፍ ይሆናል፡፡
ወደ ኢትዮጵያ የመጣውና በሌሎች ሀገራትም ጉብኝት የሚያደርገው ዋንጫው ለውድድሩ አሸናፊዎች መስጠት የጀመረው እአአ በ1978 ሲሆን፤ ጋና ደግሞ የታሪካዊው ዋንጫ ባለቤት በመሆን ቀዳሚዋ ናት፡፡ በወቅቱ የአፍሪካ አንድነት ዋንጫ በሚል ይታወቅ የነበረው ዋንጫው፤ እአአ ከ2002 ወዲህ ስያሜውን በመቀየር የአፍሪካ ዋንጫ በሚል ይጠራል፡፡
ዋናውን የአፍሪካ ዋንጫ የሚያነሱ ሀገራት ሶስት ጊዜ ማሸነፍ የቻሉት ሲሆን፤ እአአ በ19 84፣ 19 88 እና 2000 አሸናፊ የሆነችው ካሜሩን ለመጀመሪያ ጊዜ የግሏ ለማድረግ ችላለች፡፡ የአፍሪካ ዋንጫ መካሄድ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ ለውድድሩ የሚሆነው የዋንጫ ዲዛይን ለሶስት ጊዜያት ተቀያይሯል፡፡
አሁን ለአሸናፊዎች የሚበረከተው ዋንጫ እአአ በ2001 የወርቅ ቅብ ሆኖ በጣሊያናዊ ባለሙያ ሊዘጋጅ ችሏል፡፡ አንድ ጊዜ አሸናፊ የሚሆን ቡድን ከዋናው ዋንጫ ጋር ተመሳሳይ ሆኖ የተሰራው ዋንጫ ሲበረከትለት፤ ሶስቴ አሸናፊ የሚሆነው ዋናውን ዋንጫ በክብር ይረከባል፡፡ ግብጽ እአአ በ2006፣ 2008 እና 2010 በተከታታይ አሸናፊ መሆኗን ተከትሎ ዋናውን ዋንጫ ወስዳለች፡፡ ይሁን እንጂ ያለፈው ዓመት ዋንጫዎቹ ከሚቀመጡበት የሀገሪቷ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ዋና ጽህፈት ቤት መሰረቁ ተሰምቷል፡፡
የአፍሪካ ዋንጫ መስራቿ ኢትዮጵያ እአአ በ1962፣ 1968 እና 1978 ለሶስት ጊዜያት የዋንጫ ባለቤት ለመሆን ችላለች፡፡ በጊዜ ሂደት በዋንጫው መሳተፍ አዳጋች ቢሆንባትም ከዓመታት በኋላ በመጪው የካሜሩን አፍሪካ ዋንጫ ዳግሞ በመድረኩ ተሳታፊ ትሆናለች፡፡
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 3/2014