በመጪው ዓመት በሚካሄደው የኳታር ዓለም ዋንጫ በመላው ዓለም የሚገኙ ብሄራዊ ቡድኖች የማጣሪያ ጨዋታቸውን እያደረጉ ይገኛሉ።የአፍሪካ ሀገሮች ብሄራዊ ቡድኖችም በተመሳሳይ ለዓለም ዋንጫው ለማለፍ የማጣሪያ ውድድሮችን እያደረጉ ናቸው።ከእነዚህ መካከል አንዱ የሆነው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድንም (ዋሊያዎቹ)ሰሞኑን ከደቡብ አፍሪካ አቻው ጋር በባህር ዳር መጫወቱ ይታወሳል።የመልስ ጨዋታቸውን ደግሞ ዛሬ በደቡብ አፍሪካ ኬፕታውን ያደርጋል።
እአአ 2022 የኳታር ዓለም ዋንጫ ተሳታፊ ለመሆን የሚያስችለውን እድል ለማግኘት በሚደረገው የማጣሪያ ውድድር ዛሬም በርካታ ጨዋታዎች ይካሄዳሉ።ጨዋታ ከሚደረግባቸው ምድቦች መካከል አንዱ የሆነውና ኢትዮጵያ የተደለደለችበት ምድብ ሰባትም ሁለት ጨዋታዎችን ያካሂዳል።ዋሊያዎቹ ከደቡብ አፍሪካ ብሄራዊ ቡድን ጋር ከሜዳቸው ውጪ ሲጫወቱ፤ ዜምቧቡዌ እና ጋናም ይገናኛሉ።
ከቀናት በፊት በዚሁ ምድብ ጨዋታዎች ሲካሄዱ ዋሊያዎቹ ለመጀመሪያ ጊዜ ዓለም አቀፍ እውቅና ባገኘው የባህርዳር ስታዲየም ሽንፈትን እንደደረሰባቸው ይታወሳል።በዚህም ቡድኑ በምድቡ ዚምቧቡዌን ብቻ ከማሸነፍ በቀር ሁለት ሽንፈቶች ደርሶውበት ለአራተኛው የምድቡ ጨዋታ ዛሬ ይሰለፋል።ባለመሸነፍ ጉዞ ላይ ያሉት ባፋና ባፋናዎቹ ዛሬ በጆሃንስበርግ በሚደረገው ጨዋታ ኢትዮጵያን ሲያስተናግዱ፤ እንዳለፈው ሁሉ አሁንም ጠንካራ ፉክክር እንደሚያደርጉ ይጠበቃል።
በዓለም ዋንጫው ተካፋይ ለመሆን እየጣሩ የሚገኙት ዋሊያዎቹ በባህርዳሩ ጨዋታ ማግስት ነበር ወደ ጆሃንስበርግያቀኑት።23 ተጫዋቾች እንዲሁም የአሠልጣኝ ቡድን አባላት በአጠቃላይ 35 ልኡክ ወደ ደቡብ አፍሪካ ሲጓዝ፤ በዛብህ መለዮ ከቡድኑ ውጪ ሆኗል።የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን (ዋሊያዎቹ) ከጆሀንስበርግ ከተማ ወጣ ብሎ በሚገኘው የደቡብ አፍሪካ እግር ኳስ ማህበር ቴክኒክ አካዳሚ ሜዳ ልምምዳቸውን እየሰሩ መሆኑንም የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በድረ ገጹ አስነብቧል።
ከባህርዳሩ ጨዋታ በኋላ ደቡብ አፍሪካ ነጥቧን ወደ ሰባት ከፍ በማድረግ በማጣሪያው ምድብ ሰባትን መምራቷን ቀጥላለች፤ ኢትዮጵያ ደግሞ በሶስት ነጥቦች ሦስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች። በሜዳቸው በደቡብ አፍሪካ የተሸነፉት ዋሊያዎቹ ከአንዱ ጨዋታ በቀር የዛሬውን ጨምሮ ሁሉኑም ጨዋታ ከሜዳቸው ውጪ የሚያደርጉ መሆናቸው ጫና ሊፈጥርባቸው እንደሚችል እሙን ነው።ባህርዳር ላይዋጋ ያስከፈላቸውን ደካማ ጎን በማረም የዛሬውን ጨዋታ እንደሚያካሂዱ ይጠበቃል።
ዛሬ ዚምቧቡዌ እና ጋናም በተመሳሳይ የምድቡን አራተኛ ጨዋታ ያደርጋሉ።ባለው ስድስት ነጥብ ከደቡብ አፍሪካ ቀጥሎ በምድቡ ሁለተኛ ስፍራ ላይ የተቀመጠው የጋና ብሄራዊ ቡድን፤ በአንድ ነጥብ የመጨረሻውን ስፍራ ከያዘችው ዚምቧቡዌ ጋር ይጫወታል።
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 2/2014