ታሪክ ማንበብ ያልኖሩበትን ዘመን ያስኖራል›› ይባላል።ይህ ማለት እኛ ባልነበርንበት ዘመን የነበረውን ሁነት ይነግረናል ማለት ነው።አዲስ ዘመን ጋዜጣ የተለያዩ ዘመናት የየዕለት ሁነት ሰንዶ ያስቀመጠ የ81 ዓመታት ታሪክ ነው።
ጋዜጣው በሰነዳቸው መረጃዎቹ ያልነበርንበትን ዘመን እንድንኖረው ያደርገናል።በዚያ ዘመን፤ የመንግስት አስተዳደር እና የማህበረሰቡ ሥነ ልቦና ምን ይመስል እንደነበር፣ ምን ነውር ምንስ አስገራሚ እንደሚሆን፣ በዘመኑ የነበሩ ህግና ደንቦች፣ የኑሮ ሁኔታ እና የመሳሰሉትን ያሳየናል።
በማስታወቂያዎች፤ በዘመኑ የነበረውን የገበያ፣ የቅጥር፣ የሚከለከሉና የሚፈቀዱ ነገሮችን ይጠቁመናል።በዜናዎች ደግሞ የዘመኑን ክስተቶች ያሳየናል።
እዚህ ላይ አንድ ነገር ልብ እንበል።በዘመኑ ጋዜጣ ላይ ይወጡ የነበሩ ዘገባዎችን፣ ማስታወቂያዎችን፣ ወዘተ. ዛሬ ላይ ሆነን ስናነባቸውና ስንመለከታቸው ‹‹አሁን ይሄ ዜና ይሆን ነበር? ጋዜጣ ላይ መውጣት ነበረበት?›› የሚያሰኙ ነገሮችን እናገኛለን።ይህ ሲያጋጥመን ልብ ማለት ያለብን የዘመኑን ባህሪ ነው።ያኔ እንደዛሬው የማህበራዊ መገናኛ አውታሮች እንዲሁም ተፎካካሪ ጋዜጦችና መጽሔቶች አልነበሩም፡፡
እናም ከአፋልጉኝ ማስታወቂያ ጀምሮ የጠጅ ቤት እና የአረቄ ቤት ወሬዎች ሳይቀር በጋዜጣው ላይ ልናገኝ እንችላለን።ምክንያቱም በወቅቱ አስገራሚ ከነበሩ ከዚህ ጋዜጣ ውጭ ሌላ መታያ አማራጭ አልነበራቸውም።ይህን ታሳቢ አድርገን በተለያየ ዓመታት የወጡ የአዲስ ዘመን ጋዜጣን ጽሑፎችን እናስነብባችኋለን። እንደተለመደው ጽሑፉን እንደወረደ እናስቀምጣለን።
ማስታወቂያ
በተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት ገብተው ለመማር ለሚፈልጉ ልጆች ሁሉ ተማሪ ቤት ከመግባታቸው በፊት ጤናቸውን መመርመር ፈንጣጣ መከተብና ማናቸውንም የተማሪ ቤቱን ደንብ ፈጽመው በተማሪ ቤቱ መዝገብ እንዲጻፉ የሚያስፈልጋቸው ስለሆነ ይህንኑ ለመፈጸም ከሚመጣው ማክሰኞ ጥቅምት 11 ቀን ጀምሮ እስከ ጥቅምት 18 ቀን ድረስ ጧት ከ3 ሰዓት እስከ 7 ሰዓት እንዲሁም ከ9 ሰዓት እስከ 11 ሰዓት ከተፈሪ መኮንን ተማሪ ቤት ድረስ እንዲሰበሰቡ የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት መንግስት የትምህርትና የጥበብ ሚኒስቴር ያስታውቃል፡፡
ጥቅምት 8 ቀን 1934 ዓ.ም
ከላይ ያስቀመጥንላችሁ የማስታወቂያ ጽሑፍ ሙሉውን አንድ አረፍተ ነገር ነው።ነጠላ ሰረዝም ሆነ ድርብ ሰረዝ መግባት ያለባቸው ቦታዎች ላይ አልገቡም።አራት ነጥብ ያለው መጨረሻ ላይ ብቻ ነው።ከዚህም ከ80 ዓመታት በፊት የነበረውን የጋዜጠኝነት አጻጻፍ እንረዳለን፡፡
የእስረኞች ሱቅ የሰረቀው በእስራት ተቀጣ
የግቢ አውራጃ ወህኒ ቤት ባልደረባ የነበረው ተሾመ አያና የወህኒ ቤቱ የህግ እስረኞች ዕቃ የሚሸጡበት ሱቅ ውስጥ ሌሊት ገብቶ ከሁለት ሺ 232 ብር በላይ መስረቁ ስለተረጋገጠበት በሰባት ዓመት ጽኑ እስራት እንዲቀጣ የአውራጃው ፍርድ ቤት ባለፈው ሳምንት ውስጥ
በዋለው ችሎት በይኖበታል።
በተያያዘም በጋሞ ጎፋ ክፍለ ሀገር የጎፋ አውራጃ የርዳታ ማስተባበሪያና ማቋቋሚያ ኮሚሽን ቅርንጫፍ መስሪያ ቤት ባልደረባ የሆነው አሰግድ አስፋው በተፈጥሮና ሰው ሰራሽ አደጋ ለተጎዱ ወገኖች ዘላቂ መፍትሔ ማካሄጃ እንዲውል በኃላፊነት ከተሰጠው ገንዘብ ውስጥ ሶስት ሺ 147 ብር ከ45 ሳንቲም አጉድሎ ለግል ጥቅሙ አውሏል በመባል ተከሶ አድራጎቱ በማስረጃ ስለተረጋገጠበት ሰሞኑን በአምስት ዓመት ጽኑ እስራት እንዲቀጣ የጎፋ አውራጃ ፍርድ ቤት ወስኖበታል።
ጥቅምት 10 ቀን 1972 ዓ.ም
ፋንቱ ያለሰፈሯ ሌሊት ስትዞር ተይዛ ታሰረች
ወይዘሮ ፋንቱ ወንደማርያም የተባለች በንፋስ ስልክ አካባቢ የምትኖር ሴት ያለሰፈሯ ከሌሊቱ በ10 ሰዓት በየካቲት 12 አደባባይ ስትዘዋወር በመገኘቷ ተይዛ የሶስተኛ ወረዳ ፍርድ ቤት የአንድ ወር እስራት የቀጣት መሆኑን አስታውቋል።ስትዘዋወር መገኘቷንና ተላላፊ መኪናዎችንም አድርሱኝ በማለት ማስቸገሯን ፖሊሶች መመስከራቸውን አስታውቋል።
ተከሳሿም ፍርድ ቤት ቀርባ በተጠየቀች ጊዜ በአድራጎቷ ጥፋተኛ መሆኗን ስላመነች ፍርዱ ተሻሽሎላት በ30 ብር መቀጫ ወይም በአንድ ወር እስራት እንድትቀጣ ተደርጎ መቀጫውን መክፈል ስላልቻለች አንድ ወር እንድትታሰር ወደ ወህኒ ወርዳለች ሲል ከአንደኛ ፖሊስ ጣቢያ የተገኘ ዜና ያስረዳል።
ጥቅምት 7 ቀን 1963 ዓ.ም
ልሰርቅ ሔጄ ጠጅ
አስክሮኝ አስያዘኝ
አባዲ ተስፋዬ መስከረም 10 ቀን 1959 ዓ.ም
ከሌሊቱ አምስት ሰዓት ላይ ከሁለት ጓደኞቹ ጋር ሆኖ የአቶ ካህሳይን ቤት ለመስረቅ ሄዶ ከዚያም ሲደርሱ በሩ ስለተዘጋባቸው በዕድሜና በሰውነት ያነሰው አባዲ በአጥር ተንጠልጥሎ ገባ።
አባዲ የቤቱን በር ከፍቶ እንደገባ እያማረጠ ለመስረቅ ጥሩ ጊዜ ሆነለት።በዚህ ሁኔታ የተሰረቀውን ዕቃ እያማረጠ እያጋዘ በማመላለስ እውጭ ካስቀመጠ በኋላ ጠጅ ጠጅ ሸተተው።ወደኋላው መለስ ቢል ጠጅ የሞላው በርሜል አየ።ጎንበስ ቢል የውሃ መቅጃ ቆርቆሮ አገኘ።ከዚህ በኋላ ምን ይጠየቃል ራሱን በራሱ ጋባዥ ሆነ።ከዚያ በኋላ ስካር ተጫጭኖት ስለተሸነፈ አባዲ ከወደቀበት ሥፍራ ሳይነሳ በዚያው ተኝቶ አደረ፡፡
በማግስቱ ጠዋት ባለቤቶቹ ከእንቅልፋቸው ተነስተው ቤት ሊጠርጉ ሲሉ አባዲ ተጋድሞ አገኙት።ወዲያው በፖሊስ አስያዙት።ከዚያም ወደ ማረፊያ ቤት ተወስዶ በወታደር ደስታ በቃኸኝ አማካኝነት ቃሉን ሲሰጥ ከላይ እንደተገለጠው ‹‹ለመስረቅ ሔጄ ጠጅ አስክሮኝ በዚያው ተኛሁ›› ሲል አረጋግጧል ብለው ሻለቃ ጌራ ወርቅ ገልጠዋል።
በትግሬ ግዛት የኢትዮጵያ የወሬ ምንጭ
ጥቅምት 10 ቀን 1959 ዓ.ም
በመግቢያ ላይ እንደገለጽንላችሁ ጽሑፎችን የምናስቀምጠው እንደወረደ ስለሆነ አንዳንድ ቦታ ላይ ‹‹ይሄ ደግሞ ምን ማለት ይሆን?›› የሚል ሊያጋጥማችሁ ይችላል።እንዲህ አይነቶቹን ከዘመኑ ዓውድ መረዳት ነው።ጽሑፎችም ከዘመን ዘመን የተለያየ ቅርጽ አላቸው።ለምሳሌ በ1930ዎቹ የነበሩትና ከ1960ዎቹና 70ዎቹ በኋላ ያሉት አረፍተ ነገሮችና የሥርዓተ ነጥብ አጠቃቀሞች ይለያያሉ።
ሳምንት ሌሎች ጽሑፎችን እናስናብባችኋለን፤ መልካም ሳምንት!
ዋለልኝ አየለ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 2/2014