ሁሌም አዲስ ዓመት በመጣ ቁጥር “አዲስ” ሆነው ከተፍ ከሚሉት ሁነቶች አንድ ከሁለት እስከ ሶስት ወራት ተዘግተው የነበሩ ትምህርት ቤቶች መከፈት ሲሆን፤ ይህም ሚሊዮኖችን የሚመለከት ዐቢይ አገራዊ ጉዳይ ከመሆኑ አኳያ በየዓመቱ የብዙዎችን ትኩረት እንደሳበና ተግባሩም ከፍተኛ ዝግጅትን እየጠየቀ ኖሯል፤ ይቀጥላልም።
ትውልድን ያለ ትምህርት ማሰብ አዳጋች ብቻ ሳይሆን፤ በተለይ በዚህ በ21ኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽ ላይ ሆኖ ላገናዘበው ሁለቱ ያንድ ሳንቲም ሁለት መልኮች መሆናቸውን በቀላሉ ይረዳል። ለዚህ ደግሞ “የተማረ ትውልድ”፣ “ያልተማረ ትውልድ”፤ “የሰለጠነው ዓለም”፣ “ያልሰለጠነው ዓለም”፤ “ያደጉ”፣ “ያላደጉ”፣ “ደሀ”፣ “ሀብታም” … አገራት፤ “የጨለማው”፣ “የአብርሆት” … ዘመን ወዘተ ከሚሉት እድሜ ጠገብ አገላለጾች በላይ ማረጋገጫ የለም። እጓለ ዮሐንስም ሆኑ ሌሎች ሳያሰልሱ “ለሁሉም ነገር ትምህርት፣ ትምህርት፣ ትምህርት” ማለታቸውም ከላይ ካልናቸው በላይ ገላጭ ነውና የትምህርትን ጉዳይ በዚሁ አልፈነው ወደ ርእሰ ጉዳያችን እንሂድ።
አዲሱን የትምህርት ዘመን መከፈት ወይም መጀመር አስመልክቶ ዝግጅቱም ሆነ የሚዘጋጀው አካል በጣም ብዙ ነው። ባጭሩ፣ የትምህርት ጉዳይ የማህበረሰቡ ጉዳይ ነውና ባለድርሻ አካላቱ ከግለሰቡ(ቧ) ተማሪ ጀምሮ እስከ ዋናው ባለድርሻ አካል የሆነው መንግስት፤ እንዲሁም ተባባሪዎቹ ድረስ ይዘልቃል። በግለሰቡ(ቧ) ተማሪና ግዙፉ ባለድርሻ በሆነው መንግስት መካከል በርካታ ባለድርሻ አካላት ያሉ ሲሆን ለጋሽ አገራትና ድርጅቶችም ይገኙበታል። “የቻይና መንግሥት”፣ “ፓንዳ ፋውንዴሽ” እና “አሊባባ ፋውንዴሽን” የዛሬው የትኩረታችን ማእከል ናቸው።
በ1989 (እአአ) በ”መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት” (NGO) ስም የተቋቋመውና አላማው ድህነትን ማስወገድ የሆነው የቻይና ፋውንዴሽን (CFPA)፤ በኢትዮጵያ ህጋዊ እውቅናን በማግኘት በ2019 በ”የአገር ውስጥ መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት” (INGO) በመሆን “CFPA Ethiopioa” በሚል ስያሜ ከተቋቋመ ጀምሮ በኢትዮጵያ በርካታ ስራዎችን ሰርቷል፤ ግምቱ $4.6 ሚሊዮን በሆነ ወጪም 130ሺህ ዜጎች ተጠቃሚ እንዲሆኑ አድርጓል።
ለትርፍ ያልተቋቋመው ይህ ድርጅት ከተቋቋመበት አላማ አኳያ “አሳካቸዋለሁ” ብሎ የነደፋቸው ስምንት ግቦች ያሉት ሲሆን፤ ከስምንቱ አንዱ (ተ.ቁ 4) “የትምህርት ጥራትን ማረጋገጥ” ነው።
በዚሁ መሰረት “ሲኤፍፒኤ ኢትዮጵያ” (CFPAE) የትምህርት ጥራትን ከማስጠበቅም ሆነ ተያያዥ ጉዳዮችን ተግባራዊ ከማድረግ አኳያ ርቆ በመሄድ ላይ ሲሆን፤ ከእነዚህም መካከል ከተቋቋመበት (2019) ጊዜ ጀምሮ በ”ፓንዳ ፓክ ፕሮጀክት” (PPP) ጥላ ስር ተግባራዊ ሲያደርገው የነበረውና በእቅዱ መሰረት ዘንድሮ (2021) የተጠናቀቀው ለአንደኛ ደረጃ ተማሪዎች የትምህርት ቤት የጀርባ ቦርሳ (School Panda Packs) ድጋፍ ፕሮግራም ነው።
ባለፈው ረብዕ (መስከረም 19) በትምህርት ሚኒስቴር ቅጥር ግቢ ውስጥ በአንድ ጠባብ መድረክ የተዘጋጀ ልዩ ፕሮግራም ነበር። ፕሮግራሙም እዚህ በተጠቀምንበት ሎጎ ላይ እንደሚታየው አዲሱን የትምህርት ዘመን አስመልክቶ ከላይ ከጠቀስናቸው ለጋሽና ተባባሪ አካላት ወደ ትምህርት ቤት ለሚገቡና ስጦታው ለሚያስፈልጋቸው ተማሪዎች ዘመናዊ የትምህርት ቁሶች የሚበረከቱበት ፕሮግራም ነበር።
ይህ እንደ አውሮፓዊያን አቆጣጠር ከ2019 ጀምሮ በመከናወን ላይ ያለውና ሶስተኛ ዙሩን በያዘው የድጋፍና እርዳታ ተግባር በእነዚህ አመታት ውስጥ በርካታ የእገዛና እደላ ፕሮግራሞች የተከናወኑ ሲሆን፤ ይህ የዘንድሮው 20ሺህ ዘመናዊ የተማሪ የጀርባ ቦርሳዎችን ለትምህርት ሚኒስቴር በማስረከብ የተከናወነ፤ የአዲሱ ዓመት ትምህርት ዘመን መጀመሪያ ቅድመ ዝግጅት ነበር። (ይህንን ድጋፍ ድጋፍ ሰጪዎቹ የራሳቸው የሆነ ስያሜን የሰጡት ሲሆን እሱም ቻይናንና ልዩ መታወቂያዋ የሆነውን ፓንዳ እንስሳን በማስተሳሰር “ከፓንዳ ምድር የቀረበ ስጦታ” (The Gift From Panda Land) የሚል ነው።)
ይህ በ”ኢትዮጵያ ፓንዳ ፓክ ፕሮጀክት” የታቀፈና ላለፉት ሶስት ዙሮች ተግባራዊ ሲደረግ ቆይቶ የተጠናቀቀ ፕሮግራም በድምሩ 118ሺህ የተማሪ ቦርሳዎችን ያደለ ሲሆን፤ በ2019 43ሺህ፣ በ2020 55ሺህ፤ እንዲሁም ዘንድሮ (2021) 20ሺ ዘመናዊ፣ የቻይናንና የኢትዮጵያን ባህል ባስተሳሰሩ የፊት ለፊት ምስሎች የተጌጡ፤ የተማሪዎችን የመማር ፍላጎት የሚቀሰቅሱ ቦርሳዎችን በትምህርት ሚኒስቴር በኩል ለተጠቃሚ ተማሪዎች እንዲደርስ አድርጓል።
በፕሮግራሙ ላይ በሁለቱም ወገኖች፣ በትምህርት ሚኒስቴርና በቻይና ኤምባሲ፤ እንዲሁም የ”ቻይና ፋውንዴሽን ፎር ፖቨርቲ አሊቬሽን ኢትዮጵያ” ቅርንጫፍ ቢሮ የስራ ሀላፊዎች በኩል ያሉና ጥሪ የተደረገላቸው አካላት የተገኙ ሲሆን፤ በድጋፍ የተሰጡት የትምህርት ቁሶችን የሚረከቡ የየክልሉ ትምህርት ቢሮ ሃላፊዎችም (የአዲስ አበባና የኦሮሚያ) በስፍራው ተገኝተው ርክክቡን ፈፅመዋል።
ይህ በቻይና ኤምባሲ በኩል ለትምህርት ሚኒስቴር፤ በትምህርት ሚኒስቴር በኩል ለክልሎች የተደረገው አበርክቶት በአይነቱም ሆነ በአገልግሎቱ እጅግ ዘመናዊ መሆኑ፤ በተለይም የኮቪድ-19ን ፕሮቶኮል ታሳቢ ማድረጉ በሁለቱም፣ አስረካቢና ተረካቢዎች በኩል ባሉ ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች ተገልጿል።
የትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ዶ/ር ኢንጂነር ጌታሁን መኩሪያ ይህ በቻይና መንግስት አማካኝነት ከአሊባባ ፋውንዴሽን፣ ከቻይና ፋውንድሽንና ከመሳሰሉት ጋር አብሮ የመስራቱ፣ የመደጋገፉና መረዳዳቱ ጉዳይ የቆየ ሲሆን ተጠናክሮም ይቀጥላል። በተለይ ኮቪድ ያስከተለው ከባድ ፈተና እስከሚወገድ ድረስ እንደነዚህ አይነቶቹ መደጋገፎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ።
ሚኒስትር ጌታሁን መኩሪያ እንደተናገሩት ኮቪድ-19ን ከመከላከል ጋር በተያያዘ ከቻይና መንግስት በርካታ ድጋፎች ሲደረጉ የነበሩ ሲሆን በዚህ ዓመት ትምህርት ከመጀመሩ በፊት መምህራንና ሰራተኞች ክትባት እንዲወስዱ በተወሰነው መሰረት የቻይና መንግስት ከ3000ሺህ በላይ ለሚሆኑ መምህራን የክትባት መድኃኒቱን በማምረት ድጋፍ ያደረገ ሲሆን፤ ከንፅህና መጠበቂያ (ከማስክና ሳኒታይዘር) ጀምሮ ያለማቋረጥ ሲያግዝ ነበር።
ለቻይና መንግስት፣ ለፋውንዴሽኖቹና ለሚመለከታቸው ሁሉ ምስጋና ያቀረቡት ሚኒስትሩ ቁሶቹ በቅርብ ግዜ ውስጥ ለክልሎች እንደሚታደሉና ተማሪዎች እጅ እንደሚገቡ ተናግረዋል፤ በእለቱ በአካል ለተገኙት የኦሮሚያና የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ ተወካዮችም የየክልሎቹን ድርሻ አስረክበዋል። በኢትዮጵያ የካንትርኦፊስ ዳይሬክተር ኢማ ዢኦሽን ሁዋንግ፣ በኢትዮጵያ የቻይና ኤምባሲ አምባሳደር አማካሪ፣ እና ሌሎችም በቅደም ተከተል ንግግር ያደረጉ ሲሆን በሁለቱ አገራት መካከል ያለው ሁሉን አቀፍ ድጋፍና ትብብር፤ እንዲሁም ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ተናግረዋል።
በእርዳታ የተገኙት የተማሪዎች ቁሶችም ዘመናዊ መሆናቸው ከመገለፁም በላይ ለእይታ የቀረቡ ሲሆን እያንዳንዱ የተማሪዎች የጀርባ ቦርሳ 27 አይነት ዋና ዋና (በንኡስ ክፍሎቹ ውስጥ ያሉትን ስንጨምር ጠቅላላ 146 ይሆናሉ) የውስጥ ክፍሎች ያሉትና ለእያንዳንዱ የትምህርት መገልገያ ቁስ (ምሳና ውሀን ጨምሮ) የራሱና ልዩ ስፍራ እንዲኖረው ተደርጎ፣ በበቂ ጥናትና ምርምር ላይ ተመስርቶ የተሰራ መሆኑ ተገልጾ ማብራሪያ ተሰጥቷል።
በፕሮግራሙ ላይ በመገኘት “ቻይና ከድህነት ወጥታ በዓለም በኢኮኖሚ መሪ ከሆኑ አገራት ተርታ የተሰለፈችው ለትምህርት ልዩ ትኩረት በመስጠቷ ነው” ያሉት በኢትዮጵያ የቻይና አምባሳደር ዋና ፀሀፊ ኬ ሊዮ ቻይና ለኢትዮጵያ በርካታ የውጭ ነፃ የትምህርት እድል (ስኮላርሺፕ) ስትሰጥ መቆየቷንና አሁንም በርካታ የሁለተኛና የሶስተኛ ዲግሪ ተማሪዎች በቻይና ልዩ ልዩ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ውስጥ ትምህርታቸውን እንደሚከታተሉ ተናግረዋል። ይህም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል። “ኢትዮጵያ በትምህርት ዘርፍ በምትሰራቸው ማናቸውም ስራዎች ድጋፏን አጠናክራ ትቀጥላለችም” ብለዋል።
የቻይና ፋውንዴሽን ከአሊባባ ፋውንዴሽን ጋር በመተባበር ድጋፍ የተደረገው ይህ 20ሺህ የተማሪዎች ቦርሳ ቃል ከተገባው 118ሺህ ቦርሳዎች ውስጥ የመጨረሻው ዙር እንደሆነም ከፕሮግራሙ መረዳት ተችሏል።
ይህ ፕሮግራም በርካታ አገራትን የሚያዳርስ ሲሆን፣ የቻይና ጎረቤት አገራትን፣ ወዳጅ አገራትን፣ እርዳታው የሚያስፈልጋቸውን፤ እንዲሁም በቻይና እየተገነባ ያለው የ”ቀለበት” መንገድ (Road and Belt) ፕሮጀክት ተባባሪዎችን ሁሉ የሚያካትት መሆኑን በወቅቱ ከተሰራጨው ጽሑፍ መረዳት ተችሏል።
ሚኒስትር ጌታሁን እንደተናገሩት የቻይና መንግስት የኮቪድ ወረርሽኝ ከተከሰተበት ጊዜ ጀምሮ የህክምና ባለሙያዎችን ከመላክ ጀምሮ እስከ ክትባት ድረስ የዘለቀ ከፍተኛ ድጋፍ ሲያደርግ ከመቆየቱም ባለፈ በትምህርት ጥራትና በመሳሰሉት ላይም አስፈላጊውን እገዛ በማድረግ ከፍተኛ አስተዋፅኦ እያደረገ ይገኛል። ይህ በወዳጅነትና አጋርነት ላይ የተመሰረተ ጠንካራ ግንኙነትም በሁሉም መስክ ተጠናክሮ ይዘልቃል።
ባለፈው፣ መስከረም 18 ቀን 2014 በኢትዮጵያ የቻይና አምባሳደር ዛሆ ዡዩዋን የቻይና ሪፐብሊክ 72ኛ ዓመት የምስረታ ክብረ በዓልን አስመልክቶ በተካሄደ ኮንፈረንስ/ውይይት ላይ ባደረጉት የቪዲዮ ንግግራቸው “ኢትዮጵያ የጀመረችው የሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ወደ ብልጽግና የሚወስዳት ነው። በተለያዩ ዘርፎች እየተደረገ ያለው ስር ነቀል ለውጥም ለቻይናና ለኢትዮጵያ ትብብር አዲስ ተስፋዎችን ከፍቷል።” ማለታቸው የሚታወስ ሲሆን፤ በሁለቱ አገራት መካከል ያለው የቆየና በሁሉም ዘርፍ ያለው ትብብር ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ተናግረዋል።
ባለፈው ሰኞ መስከረም 24 ቀን 2014 ዓ.ም የአዲሱ መንግስት ምስረታና የበዓለ ሲመቱ ስነ ስርአት በተካሄደበት እለት የኢፌዲሪ ፕሬዝዳንት ክብርት ሣህለወርቅ ዘውዴ የመጪውን አንድ ዓመት የመንግስት እቅድ በተወካዮች ምክር ቤት ቀርበው በንባብ ያሰሙ ሲሆን፤ ከእቅዶቹም አንዱ የትምህርት ጉዳይ ነበር።
ፕሬዝዳንት ሣህለወርቅ እንዳሉት ከሆነ በትምህርት ዘርፍ በሁሉም የትምህርት ደረጃዎች በገጠር፣ በከተማ፣ በጾታ፣ በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዳራ፣ በአካል ጉዳተኝነት፣ በስጦታና ተሰጥኦ እና በመሳሰሉት ምንም አይነት ልዩነት ሳይፈጠር ለሁሉም ዜጎች ፍትሀዊ የትምህርት ተደራሽነትን፣ ጥራትን፣ ተገቢነትን ማረጋገጥ፤ እንደዚሁም በሁሉም የትምህርት ደረጃዎች ሁሉም ህፃናትና ወጣቶች ሙሉ አቅማቸውን እንዲጠቀሙ የማድረግ ስራ ይሰራል። ከዚህም በተጨማሪ ስርአተ ትምህርቱ ከገበያው ፍላጎት ጋር የተጣጣመ እንዲሆን ይደረጋል።
ይህንን በክብርት ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ የቀረበውን የመንግስት እቅድ ወደ ተግባር ከመለወጥ አኳያ ከላይ የጠቀስናቸውን አይነት ፋውንዴሽኖች አስፈላጊነት ከጥያቄ ምልክት ስር ሊወድቅ የሚችል አይደለም። በመሆኑም “የቻይና መንግሥት”፣ “ፓንዳ ፋውንዴሽን” እና “አሊባባ ፋውንዴሽን”ና የመሳሰሉት ሁሉ የትምህርት ጥራትን ከማምጣትም ሆነ አገር ተረካቢ ትውልድን ከመፍጠር አኳያ ሚናቸው ከዚህ በመለስ ሊባል የሚችል አይደለምና የወደፊቱ የትምህርትና ተማሪዎች አጠቃላይ ሁኔታ ተስፋ ሰጪ ነው ብሎ ማጠቃለል ይቻላል። ከተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲ ወገን የሆኑትና በትምህርት ሚስትርነት የተሰየሙት ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋም ዘርፉን ወደ ተሻለ ደረጃ ያሻግሩታል ተብሎም ተስፋ መጣሉም ከዚሁ ጋር በተጓዳኝ ሊታሰብ የሚገባው መሰረታዊ ጉዳይ ነው።
ግርማ መንግሥቴ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 1/2014