የመጀመሪያው የአውሮፓ ኅብረት እና የአረብ ሊግ የጋራ ጉባዔ (EU-Arab League Summit) ሰሞኑን በቀይ ባሕር ዳርቻ ላይ በምትገኘው የግብጿ ሻርም አል-ሼክ ከተማ ተካሂዷል፡፡ የአረቡ ዓለም በእርስ በእርስ ጦርነቶች፤ በባህረ ሰላጤው ፖለቲካዊ ፍጥጫና በሌሎች ማኅበረ-ኢኮኖሚያዊ ችግሮች፤ እንዲሁም አውሮፓ ደግሞ በ‹‹ብሪኤግዚት (Brexit)››፤ በስደተኞችና በምጣኔ ሀብት ቀውስ ጉዳዮች ተወጥረው ባሉበት ወቅት ለሁለት ቀናት የተካሄደው የጋራ ጉባዔ፣ የአውሮፓንና የአረቡን ዓለም ትብብር ለማጠናከር ታስቦ የተካሄደ እንደሆነ የአውሮፓ ኅብረት ባወጣው መግለጫ ላይ ተመልክቷል፡፡
ከ40 አገራት የመጡ መሪዎችና ከፍተኛ የመንግሥት ባለስልጣናት በታደሙበት የሻርም አል-ሸኩ ጉባዔ ላይ የመካከለኛው ምስራቅ ሰላምና የስደተኞች ጉዳይ፤ የሶሪያ፤ የየመንና የሊቢያ የእርስ በእርስ ጦርነቶች፤ እንዲሁም የምጣኔ ሀብት ቀውስ ዋነኛ የመነጋገሪያ አጀንዳዎች እንደነበሩ ተዘግቧል፡፡
የግብፁ ፕሬዚዳንት አብደል ፋታህ ኤል-ሲሲ እና የአውሮፓ ካውንስል ፕሬዚዳንት ዶናልድ ተስክ በጋራ በመሩት በዚህ ጉባዔ ላይ ከታደሙት የአውሮፓና የዓረቡ ዓለም አገራት መሪዎች መካከል የጀርመኗ መራሂተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል፤ የጣሊያኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ጁሴፔ ኮንቴ፤ የብሪታኒያዋ ጠቅላይ ሚኒስትር ቴሬዛ ሜይ፤ እንዲሁም የሳዑዲ አረቢያና የኩዌት ነገሥታት ተጠቃሾች ናቸው፡፡
ይሁን እንጂ፤ ‹‹ጉባዔው ተሰብስበን መከርን›› ብሎ ከማውራት የዘለለ ፍሬ የሚያፈራ ሊሆን እንደማይችል የፖለቲካ ተንታኞች እየገለፁ ነው፡፡ መቀመጫውን ዶሃ ባደረገው የአረብ ፖሊሲ ጥናትና ምርምር ማዕከል ተመራማሪ የሆኑት ሶርያዊው ማርዋን ካባላን፤ ከጉባዔው ፍሬ ያለው ነገር እንደማይጠብቁ ይናራሉ፡፡ ‹‹እኔ በግሌ ከጉባዔው ትርጉም ያለው ነገር አልጠብቅም፡፡ መሪዎቹ ለውይይት በቀረቡት ሁሉም አጀንዳዎች ላይ መስማማት እጅግ ያዳግታቸዋል›› ይላሉ፡፡
እርሳቸው እንደሚሉት፣ ጉባዔው ፕሬዚዳንት አል-ሲሲ ስልጣናቸውን የሚጋፋቸውን ማንኛውንም ድርጊት ለመቆ ጣጠር ሲሉ የሚወስዷቸው ርምጃዎች አወዛጋቢ ቢሆኑም፤ ሰውየው በቀጣናው ተፅዕኖ ፈጣሪ መሪ እንደሆኑ ለማሳየት እድል ይፈጥርላቸዋል::
ባለፈው ሳምንት የግብፅ ባለስልጣናት በቀድሞው የአገሪቱ ዓቃቤ ሕግ ሂሻም ባራካት ግድያ የተጠረጠሩ ዘጠኝ የሙስሊም ወንድማማችነት (Muslim Brotherhood) ፓርቲ አባላትን በሞት መቅጣታቸው ይታወሳል፡፡ እ.አ.አ በ2015 ለተፈፀመው የባራካት ግድያ ኃላፊነት የወሰደ አካል ባይኖርም፤ የግብፅ ባለስጣናት ግን ድርጊቱን በሕግ በተወገዘውና የቀድሞው የአገሪቱ ፕሬዚዳንት መሐመድ ሙርሲ ፓርቲ በሆነው በሙስሊም ወንድማማችነት ላይ አመካኝተዋል፡፡
በዚህ ወር መጀመሪያ ላይ ደግሞ፤ የግብፅ ፓርላማ አብደል ፋታህ አል-ሲሲ እስከ 2034 (እ.ኤ.አ) በስልጣን ላይ ለመቆየት እድል የሚሰጣቸውንና የአገሪቱ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ክፉኛ የኮነኑትን ሕግ አፅድቋል፡፡
ማህጁብ ዝዌሪ የተባሉ ዮርዳኖሳዊ የመካከለኛው ምስራቅ ፖለቲካ ተንታኝ፤ ግብፃውያን የአረብ ሊግን የሚፈልጉት በቀጣናው ያላቸውን የበላይት ለማሳየት ብቻ እንደሆነ ያስረዳሉ፡፡ ተንታኙ እንደሚሉት፤ ግብፅ ያለ አረብ ሊግ በአካባቢው ተፅዕኖ መፍጠር አትችልም፡፡ ሊጉ ግብፃውያን በአረቡ ዓለም መሪና ኃያል ሆነው እንዲታዩ ትልቅ ሚና አለው፡፡
ተንታኞቹ እንደሚገልፁት፤ በጉባዔው ላይ የተሳተፉት የአውሮፓ አገራት መሪዎች ትኩረት መስጠት የሚፈልጉት ከሰሜን አፍሪካና ከሶሪያ ወደ አውሮፓ ስለሚገቡ ስደተኞች ጉዳይና ስለሽብርተኝት ነው፡፡ የአውሮፓ መሪዎች የአረቡን ዓለም ቀጣና የሽብርተኞችና የታጣቂ ቡድኖች መፈልፈያና የስደተኞች መነሻ አድርገው ስለሚቆጥሩት ችግሩን ለመፍታት የአረብ አገራት መሪዎችን ድጋፍና ትብብር ይሻሉ፡፡
ካላባን ‹‹የአውሮፓ አገራት የችግሮቹን ገፈት እየቀመሱ ቢሆንም የችግሮቹ ምንጮች በሆነው አካባቢ ዘላቂ ለውጥ እንዲመጣ ጠንከር ያለ ርምጃ ሲወስዱ አይታዩም፡፡ ይባስ ብለው የአውሮፓ አገራት የአረብ አምባገነኖችን ሲደግፉ ይስተዋላል፤›› ይላሉ፡፡
የአረብ አገራት መሪዎች ባለፈው ወር ቤይሩት ወስጥ በተካሄደው የአረብ ኢኮኖሚ ጉባዔ ላይ ሊባኖስ ውስጥ ስላለው የስደተኞች ቀውስ ሳይነጋገሩ ቀርተዋል፡፡ በሶሪያ የእርስ በእርስ ጦርነት ምክንያት ከተሰደዱ ከስድስት ሚሊዮን ሶሪያውያን መካከል ከአንድ ሚሊዮን የሚበልጡት ሊባኖስ ውስጥ ተጠልለለው ይገኛሉ፡፡ በጉባዔው የሊባኖስ ፓርላማ አፈ ጉባዔ ናቢህ ቤሪ ለስደተኞች ችግር እልባት ለመስጠትና ሶሪያን መልሶ ለማቋቋም የሶሪያ ተሳትፎና ትብብር ወሳኝ እንደሆነ ተናግረው ነበር፡፡
ሃምዛ አል-መስጠፋ የተባሉ ሶርያዊ የጥናትና ምርምር ባለሙያ በበኩላቸው የሻርም አል-ሼኩ ጉባዔ ልክ ቤይሩት ውስጥ እንደተካሄደው የምጣኔ ሀብት ጉባዔ ወሳኝ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ያተኩራል የሚል እምነት የላቸውም፡፡ የአረብ ሊግ ከሚያሳልፋቸው ውሳኔዎች መካከል ብዙዎቹ ተፈፃሚ እንደማይሆኑ የሚጠቅሱት ሃምዛ አል-መስጠፋ፣ በአውሮፓ ኅብረትና በአረብ ሊግ ጉባዔ የተደረሱ ስምምነቶች ተፈፃሚነት አጠራጣሪ ነው ሲሉ ይናገራሉ፡፡ ከዚህ በተጨማሪም፤ አሜሪካን በተመለከተ በሚነሱ ጉዳዮች ላይ ከወገንተኝነት የፀዳ አቋም ከመያዝና ወሳኔ ከማሳለፍ ይልቅ ሁለቱም ማኅበራት የአሜሪካን መንገድ መምረጥ ይቀናቸዋል፡፡
የፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር አሜሪካ በመካከለኛው ምስራቅ ያላት ፖሊሲ ግልፅ እንዳይሆን አድርጓል፡፡ ፕሬዚዳንቱ ከፍልስጤም የሰላም ስምምነት እስከ ሶሪያ ወታደራዊ ዘመቻ ያሳዩት አቋም አሜሪካ ለበርካታ ዓመታት በመካከለኛው ምስራቅ ላይ ስታራምደው የቆየችውን ስትራቴጂ የገለባበጠ ሆኗል፡፡
በእርግጥ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በሶሪያ የሚገኙ የአሜሪካ ወታደሮች ከሶሪያ እንደሚወጡ ይፋ ሲያደርጉ ውሳኔው ራሱን ‹‹እስላማዊ መንግሥት (Islamic State)›› እያለ የሚጠራው ቡድን ተመልሶ እንዲያንሰራራ በማድረግ በቀጣናው ተጨማሪ የፀጥታ ስጋትና የስደተኞች ቀውስ እንዲፈጠር ያደርጋል በማለት የአውሮፓ ኅብረትና የአረብ ሊግ የፕሬዚዳንቱን ውሳኔ መቃወማቸው ሁለቱ ማኅበራት የፕሬዚዳንቱን ውሳኔ ለማስቀልበስ አጋጣሚ እንደሚያገኙ አል-ሙስጠፋ ያስረዳሉ፡፡
እስላማዊ መንግሥት በሶሪያ ውስጥ በጠቅላላ ሽንፈት አፋፍ ላይ መገኘቱ የቡድኑ ተዋጊዎች ወደ አውሮፓ ሊሸሹ ይችላሉ የሚል ስጋት ያደረባቸው የአውሮፓ አገራት መሪዎች፤ የአሜሪካ ወታደሮች ከሶሪያ ይወጣሉ የሚለውን ውሳኔ ከመቃወምም አልፈው በፕሬዚዳንት ትራምፕ ላይ ከረር ያለ ትችት እንዲሰነዝሩ ምክንያት ሆኗቸዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም፤ ፕሬዚዳንት ትራምፕ በአሜሪካ በሚደገፈው የኩርድ ታጣቂ ቡድን የተማረኩትን አንድ ሺህ የአሸባሪው ቡድን አባላት የመልቀቅ እቅድ አላቸው መባሉም ዜጎቻቸው ቡድኑን የተቀላቀሉ የአውሮፓ መሪዎችን ክፉኛ አስደንግጧል፡፡
በጉባዔው የተገኙ የአረብ አገራት መሪዎችም ከአውሮፓውያኑ ጋር ስለሚነጋገሩባቸው ጉዳዮች ስምምነት ላይ ሳይደርሱ ወደጉባዔው እንደገቡ ሲገለፅ ነበር፡፡ ዝዌሪ እንደሚሉት አብዛኞቹ የአረብ አገራት ከአውሮፓ አገራት ጋር ያሏቸውን ጉዳዮች በጋራ በሚያደርጓቸው የሁለትዮሽ ስምምነቶች በኩል መጨረስ ይፈልጋሉ፡፡ ‹‹ላለፉት 20 ዓመታት የተካሄዱ መሰል ጉባዔዎች አንዳችም ለውጥ አላመጡም:: የአውሮፓ አገራት የአረቡን ዓለም ችግሮች ለመፍታት ልባዊ ቁርጠኛት የላቸውም›› ይላሉ::
ከጉባዔው አጀንዳዎች መካከል አንዱ እንደነበር የተነገረለት የእስራኤል-ፍልስጤም የሰላም ድርድር የአውሮፓንና የአረቡን ዓለም ሰዎች በቀላሉ ያስማማል ተብሎ አይታሰብም፡፡ ካባላን እንደሚሉት፤ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ እየሩሳሌም የእስራኤል ዋና ከተማ ናት ብለው እውቅና ከሰጡ ወዲህ ክፉኛ የተበሳጩት አረቦቹና በሰላም ድርድሩ ተስፋ የቆረጡት የሚመስሉት አውሮፓውያኑ በጉዳዩ ላይ ተቀራርቦና ተስማምቶ ለመስራት ይቸገራሉ፡፡
‹‹አል ሻባካ (Al Shabaka)›› የተባለው የፍልስጤም የፖሊሲ ማዕከል ዳይሬክተር ናዲያ ሂጃብ፤ የአውሮፓ ኅብረት ባሳየው ቸልተኝነትና አቅመ ቢስነት ምክንያት የፍልስጤማውያን መብት ጥሰት ጉዳይ ተቀብሮ እንዲቀር ተደርጓል›› በማለት ለአልጀዚራ ተናግረዋል፡፡
በአጠቃላይ ለሁለት ቀናት በግብፅ ሻርም አል-ሼክ የመከሩት የአውሮፓና የአረቡ ዓለም አገራት መሪዎች ፍሬ ላለው ነገር እንዳልተሰበሰቡ የፖለቲካ ተንታኞቹ ያስረዳሉ፡፡
በእርግጥስ ጉባዔው እንደተባለው ‹‹የታይታ ብቻ ሆኖ ይቀራል ወይ?›› ለሚለው ጥያቄ ጊዜ እውነተኛውን ምላሽ ይሰጣል፡፡
አዲስ ዘመን የካቲት 20/2011
በአንተነህ ቸሬ