አመልካቹ በጫት መሬታቸው ይገባኛል ምክንያት የተለያዩ ፍርድ ቤቶችን ረግጠዋል።ከዓመታት በፊት በአደራ ‹‹ሰጠሁት›› የሚሉት ሰፊ መሬት እንዲለቀቅላቸው ያልሞከሩት የለም። ይህ ስድስት ሄክታር መሬት ከዓመት እስከ ዓመት በረከት እንደያዘ ነው።ለምለም ጫትን ያስታቅፋል።
ለአካባቢው ሰዎች ፍላጎት የሚውለው የጫት ተክል ጥቅምና ፍላጎቱ የበዛ ነው። ዘወትር የሚሹት ተጠቃሚዎች በየቀኑ ቢያገኙት ይወዳሉ። ይህን ጠንቅቀው የሚያውቁ ባለመሬቶች የጫት ቅጠልን በሰፊው ያመርታሉ።ጫቱ ለተጠቃሚዎች የዕለት ፍላጎት ወሳኝና አስፈላጊ ነው።
በምዕራብ ሀረርጌና አካባቢው በጫት ንግድ የሚተዳደሩ ብዙዎች ህይወታቸውን፣ ቤተሰባቸውን በሚያገኙት ገቢ ይመራሉ። አመልካቹ አቶ ሙየዲን የኑስም በአካባቢው ተመሳሳይ ህይወትን አሳልፈዋል። በሰፊው መሬታቸው ላይ ከዓመት እስከ ዓመት የሚበቅለው የጫት ምርት ለእሳቸውና ለቤተሰቦቻቸው ህልውና መድህን ሆኖ ቆይቷል።
አቶ ሙየዲን ከቀናት በአንዱ ዕለት ይህን ሰፊ የጫት መሬት አንደኛ ተከሳሽ ናቸው ለሚሏቸው ግለሰብ በአደራ ይዘው እንዲጠቀሙበት፣ እንዲያስተዳድሩት መስጠታቸውን ይናገራሉ። እሳቸው እንደሚሉት ግለሰቡ ከአቶ ሙየዲን የተረከቡትን የአደራ መሬት ለዓመታት ተጠቀሙበት ።
መሬቱ የጫት ምርትን የሚያሳፍስና የልብን የሚሞላ ነው። በሰፊው ይዞታ የተንጣለለው ጫት እርሳቸውን ጨምሮ መላ ቤተሰባቸውን ሲጠቅም ቆይቷል።አቶ ሙየዲን መሬቱን ከሰጡ በኋላ ግለሰቡ ከሚስቱ ጋር ሲገለገልበት እንደቆየ አውቃለሁ ይላሉ።
ይዞታው ጥቅም ሲሰጥ ከቆየ በኋላ ሙየዲን መልሰው መሬቱን መረከብ ፈለጉ። ይህን ሲያስቡ አደራ ተቀባዩን በወግና ደንቡ አስጠርተው ጠየቁ፣ አስጠየቁ።እንዲህ ከሆነ ጥቂት ቀናት በኋላ ግን ባለጫት ይዞታው ሰፊ መሬታቸውን ለሌላ ሰው በሽያጭ ስለመተላለፉ አረጋገጡ ።
ሙየዲን የመሬቱን መሸጥ ባወቁ ጊዜ ድንጋጤ ገባቸው። ‹‹አለኝ›› የሚሉት ሰፊ ይዞታ ያለምንም ጥቅም በዋዛ ከእጃቸው መውጣቱ ሲያስተክዝ፣ ሲያሳስባቸው ከረመ። ጥቂት ቀናትን ቆይተው ሙየዲን ዘመድ አዝማድ አማከሩ። ያማከሯቸው በርካቶች ጉዳዩን በዝምታ ከማለፍ በህግ ሊጠይቁ እንደሚገባ አሳሰቧቸው።
ሙየዲን መለስ ብለው ከራሳቸው መከሩ። ውስጣቸውን ከሌሎች ሀሳብ አጣምረውም ያዋጣኛል ባሉት የህግ አግባብ መብታቸውን ሊጠይቁ ዶሴያቸውን አዘጋጁ።የህግ ሰዎችን አማክረው፣ እንደሳቸው በጉዳዩ ያለፉትን ጠይቀው ከፍርድ ቤት ደጃፍ ሲደርሱ ለሆነባቸው አግባብ ያልሆነ ድርጊት ሁሉ ህግ እንደሚክሳቸው በማሰብ ነበር።
በክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ክስ የተመሰረተባቸው ሁለት ሰዎች የጫት መሬቱ ሻጭና ገዥ በመሆናቸው በተጠሪነት ቀረቡ።‹‹ተበድያለሁ፣ ፍትህ እሻለሁ ›› ያሉት አቶ ሙየዲን ከሳሽ ሆነው ሲቀርቡ ‹‹አለኝ›› የሚሏቸውን ማስረጃዎች ከእማኞች ምስክርነት ጋር በማያያዝ ሆነ።
አቶ ሙየዲን ለፍርድ ቤቱ ባቀረቡት የክስ አቤቱታ ሁለቱ ግለሰቦች ስድስት ሄክታር መሬት የሆነ የጫት ይዞታቸውን ሻጭና ገዥ በመሆን ተጠቃሚ ሆነዋል። መሬቱን በመግዛትና መሸጥ የተደረገው የውል ስምምነትም ከእሳቸው ፈቃድና እውቅና ውጭ የተካሄደ ነው።አመልካች ይህን አቤቱታ ለፍርድ ቤቱ ሲያቀርቡ በሻጭና ገዢ መካከል የተደረገው ውል እንዲፈርስና ከእጃቸው የወጣው የጫት መሬትም በአግባቡ እንዲመለስላቸው በመጠየቅ ሆነ።
ፍርድ ቤቱ የአመልካችን አቤቱታ መሰረት አድርጎ ስለጉዳዩ በዝርዝር እንዲያስረዱ ዕድል ሰጠ።አመልካቹ ክርክር የተነሳበትን የጫት መሬት በሚመለከት ለሚጠየቁት ሁሉ ምላሻቸውን አቀረቡ። አንደኛው ተጠሪ ከአመልካቹ እጅ መሬቱን ለመቀበል ምክንያት የሆነው በወቅቱ አደራ በመቀበሉ መሆኑን በዝርዝር አስረዱ።
ተጠሪው እያደር ኑሮ ሲከብደውና ለውጥ ሲፈልግ በአደራ የተቀበለውን መሬት ለሁለተኛው ተጠሪ በኪራይ መልክ ማስተላለፉን አቶ ሙየዲን አስረዱ።በወቅቱ የነበረው የመሬት ኪራይም አንድ ሺህ ብር እንደነበር ማስረጃው እንዳላቸው አስረግጠው ተናገሩ።
ፍርድ ቤቱ በዕለተ ቀጠሮው አንደኛና ሁለተኛ ተጠሪ ሆነው በችሎቱ የቀረቡትን ሁለት ሰዎች ስለጉዳዩ እንዲያብራሩለት ጠየቀ። በመሬቱ ጉዳይ ተከሳሽ ሆነው የተጠሩት አንደኛና ሁለተኛ ተከሳሾች የቀረበባቸውን ክስ አድምጠው ተገቢ ነው የሚሉትን ም ላሽ ሰጡ።
አንደኛ ተጠሪው ለፍርድ ቤቱ በሰጠው ምላሽ የጫት መሬቱን ከአመልካች ከተረከበ በኋላ ለሁለተኛው ተጠሪ መልሶ በአደራ መልክ ሰጥቶት እንደቆየ አስረዳ። የአደራው ቆይታ ጥቂት እንዳለፈ ግን መሬቱን በኪራይ ሲጠቀምበት እንደቆየና ክፍያውንም ከግለሰቡ ሲወስድ እንደነበር ገለጸ።
ሁለተኛ ተጠሪ ይዞታው በተፈለገ ጊዜ ለአንደኛ ተጠሪ ለመመለስ ፈቃደኛ እንዳልሆነ የተናገረው አስረጂ ይህም ቃል ትክከለኛና ሀሰት የሌለበት ስለመሆኑ አረጋገጠ። ፍርድ ቤቱ የአንደኛ ተጠሪን ቃል አድምጦ በጉዳዩ ላይ ሁለተኛ ተጠሪ ምላሽና ማብራሪያ እንዲሰጥበት ጠየቀ።
ሁለተኛው ተጠሪ ፍርድ ቤቱ በሰጠው ዕድል ‹‹አለኝ›› የሚለውን ምላሽ መስጠት ጀመረ።ግለሰቡ ከዓመታት በፊት ከአንደኛው ተጠሪ መሬቱን የወሰደው በአደራ ሳይሆን በሽያጭ ውል እንደሆነ ተናገረ።ሽያጩ ሲከናወንም አንደኛ ተጠሪ ከህጋዊ ባለቤቱ ጋር በመሆን እንደፈጸመውና በወቅቱ ሽያጭም ብር አንድ ሺህ አራት መቶ ብር እንደተቀበሉት በዝርዝር አስረዳ ።
ተጠሪው ከዚሁ አያይዞ ባሰማው ክርክርም በ1988 ዓ.ም የተፈጸመው የመሬት ሽያጭ ውልና የተነሳው ክስ በይርጋ እንደሚታገድ ነበር። በመሆኑም ይዞታውን ለመመለስ እንደማይገደድና ይህን ማድረግ ፈጽሞ ተገቢ እንደማይሆን በመግለጽ ክሱ እንዲነሳለት ፍርድ ቤቱን ጠየቀ።
ጉዳዩን የተመለከተው የኦሮሚያ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ለክርክሩ መነሻ የሆነው የጫት መሬት የባለቤትነት መብት የማን እንደሆነ ለማወቅ የራሱን ማጣራት አደረገ።ፍርድ ቤቱ ተጣ ርተው የቀረቡትን ሪፖርቶችም አንድ በአንድ እየለየ በአግባቡ መረመረ።
ለምዕራብ ሀረርጌ ዞን ከፍተኛው ፍርድ ቤት በቀረበው መረጃ መሰረት ክርክሩን ያስነሳው መሬት የአንደኛ ተጠሪ ሚስት አባት መሆኑን ፍርድ ቤቱ አረጋገጠ። የአንደኛ ተጠሪ ሚስት ክርክር ያስነሳውንና በውርስ ከአባቷ የተላለፈላትን መሬት ለሁለተኛ ተጠሪ የሸጠች ሲሆን ይህ የክርክር ቦታም የአመልካች ይዞታ አለመሆኑን ለመረዳት ተችሏል።
በኦሮሚያ የመሬት ንብረት አጠቃቀም አዋጅ መሰረት ቋሚ የሚባል የንብረት ሽያጭ የሚከለከል ነው ።ያም ቢሆን የመሬት ሽያጭ ውሉ እንዲፈርስ የሚጠይቀው ወገን ከውሉ መፍረስ የተነሳ ጥቅም ያለው ሰው ብቻ እንደሆነ በፍትሐብሔር ቁጥር 1808 ንዑስ አንቀጽ 2 ይደነግጋል።
በዚህ አዋጅ መነሻ መሰረትም አመልካች የመሬት ሽያጭ ውሉ እንዲፈርስ መጠየቅ አይችልም ስለመባሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ከዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ካገኘው መዝገብ ለመረዳት ችሏል። ፍርድ ቤቱ መዝገቡን አመልካች ካቀረቡት የክስ አቤቱታ ጋር አዛምዶ መረመረ።
ጉዳዩን በአግባቡ የተመለከተው ፍርድ ቤት ክርክር የተነሳበት የመሬት ይዞታ የአንደኛ ተጠሪ ሚስት ለሁለተኛው ተጠሪ በሽያጭ ያስተላለፈች ስለመሆኑ ተረድቷል። ተጠሪው የመሬት ሽያጭ ውሉ መፍረስ እንደማይገባው መሞገቱ አመልካች ከውሉ መፍረስ የሚገኙትን ጥቅም አላረጋገጡም በሚል ምክንያት ይሆናል።
አመልካቹ አቶ ሙየዲን በፍርድ ቤቶቹ የተላለፈውንና ቆይቶም ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ያጸደቀውን ውሳኔ ለመቀበል አልፈቀዱም።ሴት ልጃቸውን ጨምሮ መሬቱን በሽያጭና ግዢ የተረካከቡት ይዞታ ፈጽሞ ወደእነሱ ሊያልፍ እንደማይገባ አምነውበታል።
ሙየዲን የይዞታ መሬቱ በፍርድ ቤት ውሳኔ መሰረት አይገባዎትም መባሉ ዘወትር ሲያሳስባቸው ከረመ። መሬታቸው እንደዋዛ ከእጃቸው ወጥቶ የሌሎች ሰዎች መጠቀሚያ መሆኑ አስቆጫቸው።ጠዋት ማታ ለቀጣዩ መፍትሄ መላና ዘዴ መፈለጋቸው አልቀረም።
በመሬቱ ተጠቃሚ አለመሆናቸውን ሲያስቡ፣ ያለ አግባብ ተወስዶብኛል የሚሉት የጫት መሬት ውል ይላቸዋል። ይህን እያሰቡ አርቀው ያስባሉ። በፍርድ ቤቱ የተላለፈው ውሳኔ የመጨረሻ እንደማይሆን ሲገባቸው ጉዳዩን እንደአዲስ ለመጀመር ያስባሉ።እያሰቡ አዲስ ውጥንና፣ ተጨማሪ ዕቅድ ይነድፋሉ።
ዳግም አቤቱታ…
አቶ ሙየዲን ያሰቡት አልቀረም። ክሳቸውን አጠናክረው አቤቱታቸውን መቀጠል ፈለጉ።ይህን ለማድረግ ቀድሞ አቤቱታ ወዳቀረቡባቸው ፍርድ ቤቶች መመለስ አላስፈላጋቸውም። ይግባኝ በማለት መጠየቅም አላሻቸውም። ሙየዲን በፍርድ ቤቶቹ የተላለፉትን የይዞታው አይገባህም የውሳኔ ግልባጭ ይዘው ተንቀ ሳቀሱ።
ሙየዲን ለሕገ መንግስት ጉዳዮች አጣሪ ጉባኤ ባስገቡት አቤቱታ ጉዳያቸው ዳግም እንዲታይላቸው አቤት አሉ። አቤቱታው የሕገ መንግስት ትርጉም እንዲሰጠው ያቀረቡት ማመልከቻ በመሆኑ ጉባኤው ትርጉም የሚያስፈልገው መሆኑን በአግባቡ መርምሮ በትክክል ትርጉም እንደሚያስፈልገው አረጋገጠ።
አመልካች ሙየዲን ነሐሴ 26 ቀን 2006 ዓ.ም በተጻፈ ማመልከቻ ባቀረቡት አቤቱታ ለተጠሪዎች የሰጡት የመሬት ይዞታ እንዲለቀቅላቸው ጠይቀዋል። የማመልከቻቸው ይዘት በግልጽ እንደሚያስረዳው ከዚህ ቀደም ይዞታው እንዲለቀቅላቸው በፍርድ ቤቶች መጠየቃቸውን ይጠቁማል።
ፍርድ ቤቶቹ ጉዳዩን አጣርተው ይዞታውን ማስለቀቅ ሲገባቸው ለተጠሪዎቹ መወሰናቸው አግባብ አለመሆኑን የጠቆሙት አመልካች ከዚሁ ተያይዞ የግል ንብረታቸው የሆነው ስድስት ሄክታር የጫት መሬት ‹‹አይገባህም›› መባሉ የህግ ጥሰት መፈጸሙን ያመላክታል ብለዋል።
አመልካቹ ይህን አቤቱታ ለጉባኤው ሲያቀርቡ ከሕገ መንግስቱ አንቀጽ 37 እና አንቀጽ 40 ጋር ይቃረናል በማለት ሲሆን ይህን እውነታ በመንተራስም የሕገ መንግስት ትርጉም ይሰጠኝ በማለት ጉባኤውን ጠይቀዋል።
መዝገቡን አመልካች ካቀረቡት አቤቱታ ጋር አጣምሮ የመረመረው ጉባኤ የፍርድ ቤቱ ውሳኔ በሕገ መንግስቱ አንቀጽ 40 ላይ በተጠቀሰው መሰረት ከንብረት መብታቸው ጋር የሚቃረን መሆኑን አጣቅሰው የጠቆሙትን ፍሬ ሀሳብ ጭምር መርምሯል። ቀድሞ በተሰጠው ውሳኔ መሰረትም አመልካች እንዲመለስላቸው የሚጠይቁት የገጠር መሬት የአንደኛ ተጠሪ ሚስት ለሁለተኛው ተጠሪ የሸጠች መሆኑ ቢታወቅም ግለሰቡ በይዞታው ላይ መብት ያላቸው ስለመሆኑ አላስረዱም በሚል መስፈሩን ከመዝገቡ ላይ ለማረጋገጥ ተችሏል።
ጉባኤው የፍርድ ቤቶቹን ውሳኔ ለመርመር እንደሞከረው ይዞታውን የአንደኛ ተጠሪ ሚስት ለሁለተኛው ተጠሪ በሽያጭ ስለማስተላለፏ በትክክል አረጋግጧል።የሕገ መንግስቱ አንቀጽ 40/3/ ላይ የሰፈረው አንቀጽ እንደሚያስረዳው ግን በገጠርም ሆነ በከተማ የመሬትና የተፈጥሮ ሀብት ባለቤትነት መብት የመንግስትና የሕዝብ ብቻ ስለመሆኑ ብቻ ነው።
መሬት የማይሸጥ፣ የማይለወጥ፣ የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች የጋራ ንብረት ስለመሆኑ የሚደነግገው አንቀጽ ሲመረመርም በአንደኛና በሁለተኛ ተጠሪዎች መካከል የተካሄደው የመሬት ሽያጭ ውል መሬት እንዳይሸጥ፣ እንዳይለወጥ ከሚከለክለው የሕገ መንግስቱ ድንጋጌ ጋር የሚቃረን መሆኑ አስረጂ አያስፈልገውም።ይሁን እንጂ ይህን ተቃርኖ በሚጣረስ መልኩ አመልካች ከመሬት ሽያጭ ውሉ መፍረስ የሚያገኙትን ጥቅም አላረጋገጡም በሚል የመሬት ሽያጭ ውሉ ሳይፈርስ እንዲቀጥል መወሰኑ አግባብ አለመሆኑ ተረጋግጧል።
ይህ ውሳኔም በሕገ መንግስቱ አንቀጽ 40/3/ ላይ የሰፈረውን ድንጋጌ የሚቃረን ስለመሆኑ ጉባኤው በትክክል መርምሮ በሙሉ ድምጽ ያጸደቀ ሲሆን የዚህ ውሳኔ ሀሳብ ለመጨረሻ ውሳኔ ለፌዴሬሽን ምክር ቤት እንዲተላለፍ በማለት የሕገ መንግስት ጉዳዮች አጣሪ ጉባኤ በአንድ ድምጽ ተስማምቷል።
ውሳኔ
የኢፌዴሪ ፌዴሬሽን ምክር ቤት የሕገ መንግስት ጉዳዮች አጣሪ ጉባኤ የውሳኔ ሀሳብን መሰረት በማድረግ የአመልካቹን አቤቱታ በማየት የሕገ መንግስት ትርጉምና የማንነት ገዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ያቀረበውን የውሳኔ ሀሳብ በጥልቀት መርምሯል፡፡
በዚህም መሰረት ክርክር የተነሳበት የይዞታ መሬት የአመልካቹ ሳይሆን የአንደኛ ተጠሪ ሚስት ከአባቷ በውርስ የተላለፈላት መሆኑን አረጋግጧል።ይዞታው በሽያጭ ከተላለፈ በኋላም ውሉ ሳይፈርስ መታለፉ በሕግ አግባብ ተገቢ አለመሆኑ ተረጋግጧል።ከዚህ አኳያም ጉዳዩ የሕገ መንግስት ትርጉም የሚያስፈልገው ስለመሆኑ ምክር ቤቱ በሙሉ ድምጽ ወስኗል፡፡
ከዚሁ ጋር ተያይዞ ምክር ቤቱ ባሳለፈው የመጨረሻ ውሳኔም ጉዳዩን የተመለከተው የዶባ ወረዳ ፍርድ ቤትና በየደረጃው በሚገኙ ፍርድ ቤቶች የጸናው ውሳኔ የሕገ መንግስቱን አንቀጽ 40/3/ የሚቃረን በመሆኑ በሕገ መንግስቱ አንቀጽ 9 /1/ ድንጋጌ መሰረት ተፈጻሚ ሊሆን አይገባውም ሲል ወስኗል፡፡
የመሬት ይዞታው የአንደኛ ተጠሪ ሚስት ቢሆንም ባለመብቷ በህገወጥ የሽያጭ ውል የተላለፈው መሬት እንዲለቀቅላቸው በህግ አልጠየቁም።በዚህም ምክንያት ሁለተኛው ተጠሪ በህገወጥ ግዢ በያዙት መሬት ተጠቃሚ ሊሆኑ አይገባም።በመሆኑም መሬቱን ህጋዊ መብት አለኝ የሚል ወገን አስኪረከበው ይዞታው በሚመለከተው የመሬት አስተዳደር ቁጥጥር ስር እንዲቆይ በማለት ምክር ቤቱ የመጨረሻውን ውሳኔ አስተላልፏል፡፡
መልካምስራ አፈወርቅ
አዲስ ዘመን መስከረም 29/2014