ወጣትነት አፍላነት ነው።እሳቱ ከቀዝቃዛው የማይለይበት።ለመንፈሳዊም ሆነ ለሌላ ነገር በቀላሉ መጋል እና በቀላሉ መቀዝቀዝም ነው። ካለማስተዋል የተነሳ ውሳኔን አስር ጊዜ መቀያየር፣ በቀላሉ መደሰትና በቀላሉ ማዘን ያለበት፣ በቀላሉ ወደ ፍቅር መግባትና በቀላሉ ወደ ጥላቻ የሚኬድበት ትኩስ እድሜ ነው።ወጣትነት በህይወት ውስጥ የጥሩም ሆነ የክፉ መሰረት የሚጣልበት፤ የተዘበራረቀ የስሜት አይነት የሚታይበትና ለቀጣይ ነጋችን ስንል የምንሰራበት የእድሜ ክልል መሆኑን መገንዘብ አለብን።
ከዚህ ጋር በተያያዘ ለዛሬ የ‹‹ወጣቶች›› አምድ ለወጣቶች አርአያ ይሆን ዘንድ የአምቦ ዩኒቨርሲቲውን የማዕረግ ተመራቂ ዳኜ ቤክሲሳ አቦምሳን ይዞላችሁ ቀርቧል።ዳኜ ከማዕረግ ተመራቂነቱ ሌላ ስለ ወጣትነትም ብዙ ነገር ብሎናልና ከእርሱ ልምድ እንድትወስዱ በማሰብ ትከታተሉት ዘንድ ጋብዘናችኋል።
ዳኜ ተወልዶ ያደገው በምዕራብ ሸዋ ዞን ቶኬውዳዮ ወረዳ ላሉ ሀሩ ቀበሌ ውስጥ ነው። በጣም ገጠር ውስጥ ያለች ቀበሌ በመሆኗ ምንም አይነት መሰረተ ልማት አልተሟላባትም። በተለይም ለተማሪ የሚያስፈልገው መብራት የለም።ስለዚህም ዳኜና መሰሎቹ በኩራዝ ብቻ ሳይሆን በጨረቃ ጭምር ማንበብ ካልቻሉ ውጤታማ ለመሆን ይከብዳቸዋል።በዚያ ላይ ዳኜ የቤተሰብ የኑሮ ሁኔታም ይፈትነዋል።
እናት አባቱ በመለያየታቸው የተነሳ በቀላሉ ሊማር የሚችልበት እድል አልነበረውም።እናቱን እየረዳ ጭምር እንዲማር ጫና ያረፈበት ወጣት ነው።የኑሮ ውድነቱም እንዲሁ አቅሙን ተፈታትኖት እንደነበር አይረሳውም።ግን አንድም ቀን ከጉብዝናው አስተጓጉሎት አያውቅም።የደረጃ ተማሪ ሆኖም እስከመጨረሻው ትምህርቱን ተከታትሏል።እስካሁን ወያኔን በመታገሉ ለእስር የተዳረገበት ወቅት ከመኖሩ ሌላ ያጋጠመው ፈተና አልነበረም ነው።
እንደእርሱ አገላለጽ ወጣትነት ስሜታዊነት የሚያይልበት እድሜ እንጂ ወጣት ስለሆነ ብቻ ስሜታዊ የሚኮንበት እድሜ አይደለም።ምክንያቱም በሁሉም ወጣቶች ላይ የሚኖር አንድ የሆነ ባህሪ ቢኖርም፤ በዚህ በወጣትነት እድሜ ከእኛ ውጭ ሰው የለም፣ ከእኛ ውጭ ጉልበተኛም የለም ሊባል ይችላል።ነገር ግን በስነ ምግባር ይህ ነገር ይሰበራል፤ በችግር ብዛትም ራስን ለማኖር በሚደረግ መፍጨርጨር ይጠፋል።ይህንን ደግሞ በህይወቱ አጋጥሞት እንደነበር ይናገራል።
ወጣትነት በሰው ልጅ የህይወት ዘመን ውስጥ ወርቃማው የዕድሜ ክልል ነው። ምክንያቱም ይህ እድሜ የወርቃማ እድል ጊዜ ነው።ብዙ አቅም፣ ብዙ ፈጠራ፣ ብዙ ሥራ የሚሰራበት ነው።ጉልበት ያለበትና ከተንቀሳቀሱ ነገን መወሰን የሚቻልበትም ነው።በዚህም ስሜታዊ የምንሆባቸው ነገሮች ቢኖሩም ከፊት ለሚጠብቀን ጊዜ ለመዘጋጀት ብለን ከስሜታችን ወጥተን ከተጠቀምንበት የተሻለ ነገን ማየት እንችላለን።ለዚህም እኔ ዛሬን ያየሁት ጥሩ ማሳያ ነው ብዬ አስባለሁም ይላል በማዕረግ ተመራቂው ዳኜ።ዛሬ በወጣትነት ላይ ሆኜ በብዙ ፈተናዎች ውስጥ አልፌ ወርቁንና ዋንጫውን መለቃቀሜ ከምንም የመነጨ አይደለም ሲልም ይናገራል።
ነገን ማሰብ ማለት ወጣትነትን ለነገ ማስቀመጥ ወይም መቆጠብ ማለት ነው የሚለው ዳኜ፤ ዛሬ የፈለግነውን ነገር ክፉም ሆነ በጎ በቀላሉ መከወን እንድንችል ነገን ማሰብ ያስፈልገናል።ነገር ግን ይህ ወርቃማ የእድሜ ክልል ካለፈ ነገሮች በእኛ ላይ ይሰለጥናሉ።ነገ የምንሆነው ዛሬ የሰራነውን ነው።የሰው ልጅ ዛሬን ወደ ትላንት ነገን ወደ ዛሬ እየቀያየረ፤ አዳዲስና የተሻሉ ተግባራትን እየጨመረ የሚሄድ ፍጡር ነው።በዚህም በእያንዳንዱ ቀናት ውስጥ የተለያዩ ክስተቶችን ያስተናግዳል።ይህ ደግሞ ራሱን፣ ቤተሰቡንና ሀገሩን የሚያድን ወይም የሚያጠፋ ሊሆን ይችላል።እናም ይህንን እያሰቡ መንቀሳቀስ ከምንም በላይ ለዛሬው ወጣት አስፈላጊ እንደሆነ ይመክራል።
ህወሓት በሚመራበት ጊዜ የወጣቶች መብት ታጋይ ሲሆን፤ በሱማሌ ክልል ለሁለት ዓመት ታስሯል፤ ብዙም በደል ደርሶበታል።በአይኑ ላይ የእይታ ችግር እስከማጋጠም ድረስ የደረሰው በዚህ ምክንያት ነው።በዚህም ብዙ ሰዓት ወስዶ ማንበብ አይችልም።ይሁን እንጂ ተስፋ መቁረጥ በእርሱ ዘንድ ቦታ የለውምና በጥሩ ውጤት የ12ኛ ክፍል ትምህርቱን ማጠናቀቅ ችሏል።ይህ ደግሞ ወጣትነት ላይ ያለው አስተሳሰብ የተገራ በመሆኑ ምክንያት የመጣ እንደሆነ ይናገራል።ለዚህ ደግሞ መሰረቱ ከእናቱ ቀጥሎ መምህራን እንደሆኑም ያስረዳል።በተለይ ሁለቱን መምህራኖቹን “የህይወቴ መሪና ተስፋ ሰጪዬ ናቸው” ይላቸዋል።በማስተማር ብቃታቸው ብቻ ሳይሆን በምክራቸውና በሚሰጡት ድጋፍ ጭምር ለዛሬ ቆሞ እንዲሄድ አድርገውታልና ያመሰግናቸዋል።
ወጣትነት ስነልቦናዊ፣ አካላዊ፣ ማህበራዊና አዕምሯዊ ለውጦች የሚከናወኑበት ጊዜ ነው።በወጣትነት ወቅት ከውስጣዊ ፈተና በተጨማሪ ውጫዊ ፈተና የራሱ የሆነ ተጽኖ የሚፈጠርበት ዘመን ነው።በዚህ ወቅት በደንብ የተኮተኮተ ወጣት በሚደርስበት ፈተና አይወድቅም።ለዚህም አንድ ምሳሌ ከህይወቴ ማንሳት እችላለሁ።አባት የሌለው ልጅ በአብዛኛው በሀገራችን ማህበረሰብ ዘንድ በጥሩ ሁኔታ አይታይም።በዚህም ብዙ ፈተና ያሳልፋል።ይህ ደግሞ ትምህርቱ ላይ ጭምር ጫና ይፈጥርበታል።የሚሰጠው ቦታም ቢሆን ከሌሎች ልጆች ያነሰ ነው።እናም ከስነልቦና ባለፈም አካላዊ ጫናው ቀላል አይደለም።ይህንን ደግሞ ሆኜ አይቸዋለሁ ይላል ዳኜ።
ራዕዩ ትልቅ ኑሮ ግን ፈተና ቢሆንበትም ግቡን ለማሳካት ሩቁን ጉዞ የያዘ አይሸነፍም የሚለው ወጣት ዳኜ፤ በዚህ የእድሜ ክልል ሰው እውነተኛ ፀባዩን፣ ባህሪውንና ተግባሩን የሚገነባበት፤ ላይመለስ የሚያልፈው ደቂቃው እንዳያመልጠው የሚታትርበት ጊዜ ነው።ስለዚህም እኔ እየተጠቀምኩበት ነውና ሌሎችም እንዲጠቀሙበት እመክራለሁ ብሏል።
ሌላው ዳኜ ያነሳው ትልቅ ቁምነገር ወጣትነት ለውጥ ናፋቂነት መሆኑን ነው። ለዚህም “ትንሽ ሥራ አልሰራም” በሚል ብዙ ፈተናን ተጋፍጧል።ከዩኒቨርሲቲው እስከ ትምህርት ክፍሉ ድረስ በፍላጎቱ የመረጠውን ያገኘውም በዚህ የተነሳ ነው።በኢኮኖሚክስ ትምህርት ውጤታማ በሆነ መልኩ አጠናቆ (ሰቅሎ)ም በመቅረቱ ያሰበውን ለመስራት ያስቻለው ይህ ተስፋ አለመቁረጡ መሆኑንም ይናገራል።
የአንድ ሀገር ቀጣይነት ያለው እድገት የሚለካው በአለው ሃብትና ንብረት ብቻ ሳይሆን ያንን ተረክቦ በአደራነት የሚሰራ፣ ለትውልድ የሚተላለፍ ተግባር ሲኖር ጭምር ነው።ያ ደግሞ ወጣቱ ትውልድ መሆኑን ማንም ያውቀዋል።እናም ሀገርን በጊዜና በዘመን ለመረከብ፣ ለማስረከብና ለመጠበቅ ትልቅ ሀላፊነት ያለበት ወጣቱ መሆኑን መገንዘብ ይገባዋል።ከዚህ አንጻር ወጣቱ ለሀገሩ በማህበራዊ፤ በሥነ ምጣኔ ሃብታዊና በፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ መፍጠር አለበት።
እርሱም እንደግለሰብ በዩኒቨርሲቲው ውስጥ የመቅረትና የመስራት እድሉ ስላለው አሁን ሀገሩን በቻለው ሁሉ ለማገዝ ዝግጁ መሆኑን አጫውቶናል።በተለይም እርሱን መሰል ተማሪዎችን የማገልገሉ ሀላፊነት የእርሱ እንደሆነም ያስባል።ምክንያቱም ለሀገር ብሎ መንቀሳቀስ ብዙ መስዋዕትነትን እንደሚያስከፍል ከእርሱ በላይ ያየ የለም ብሎ ያምናልና ነው።ለዚህም በአብነት የሚያነሳው ለለውጥ ብሎ በመታገሉ የደረሰበትን ስቃይ ነው።ግን ውጤቱ የእርሱን አሻራ በለውጡ እንዲያይ ስላደረገው ደስተኛ ነው።ከዚያም በላይ ደግሞ በሽልማቱ ለዚህ እድል በመብቃቱ የልፋቱ ዋጋ የትም እንዳልቀረ ዓይቷል።እናም ወጣቶች ለእውነት መታገል ጉልበትና ኃይል እንደሆነ ተናግሯል።
ትምህርት በእውቀት የበሰሉ ወጣቶችን የሚያመርት ኢንዱስትሪ ነው።ለእውቀት ብቻ ሳይሆን ለስነልቦናም ይሰራል።ከዚያም በላይ ደግሞ ሀገር ወዳድነትን ይገነባል።ለዚህ ግን ጥሩ ተማሪ መሆንንና መምህር ማግኘትን ይጠይቃል።ስለሆነም ወደፊት በዚህ ላይ መስራት እንደሚፈልግም ነግሮናል።ከሁሉም በላይ ግን ኢኮኖሚው የሚያንሰራራበትን መርህ ከፖሊሲ ጀምሮ ባለው ሥራ ላይ በመሳተፍ አሻራውን ማኖርም ይፈልጋል።ምክንያቱም ሀገር ባለሙያ ስለሌላት ሳይሆን እየተጎዳች ያለችው “የውጪው ይበልጣል” በማለት የራሷን ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ፖሊሲ ሳታካትት በመስራቷ ነው ብሎ ያምናልና ይህንን ከማረምና የራስን እሴት ከማየት አንጻር ብዙ ስራዎችን ለመስራት ማሰቡን አጫውቶናል።
ወጣቱ ጤናውንና ደህንነቱን ለመጠበቅ ብቻ የሰውን ሀገር ያማትራል።በሀገሩ ላይ ሰርቶ እንዲያልፍለትም አይፈልግም።ምክንያቱ ደግሞ የሚሰጠው ተስፋ ዝቅተኛ መሆን ነው።የሚወቅሰው እንጂ የሚደግፈው የለም።በዚህም የሚበረታታበትን መንገድም መፍጠር ላይ እሰራለሁ ያለን ወጣት ዳኜ፤ በሀገሩ ተረጋግቶ እንዳይቀመጥ፣ ወደ ጸብ ጭምር መግባትን በማስቀረቱ ዙሪያ እያንዳንዱ የድርሻውን ቢወጣ ብዙ ነገሮችን መታደግ ይቻላል።ስለሆነም እንደ እኛ አይነት የግለሰብ ተነሳሽነት ያለውን በመጨመር እንደ ሀገር በወጣቱ ላይ መንግስት መስራት ይኖርበታልም ብሏል።በተለይም የሰራውን አይቶ ማበረታታት ላይ ትልቅ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል ባይ ነው።
ትውልዱ የሚሰራ አይደለም፤ ሀገሩን አይወድም ወዘተ ማለት የትም አያደርስም።ይልቁንም የወጣቱን ሞራል ይሰብረዋል።እናም ማህበረሰቡ ጭምር ታዳጊውን ማበረታታትና ማስተማር ከምንም በላይ ያስፈልገዋል።እንደ መንግስትም የሥራ እድል ፈጠራው ላይ በስፋት ማሰብ ይጠበቅበታል።በሀገራችን ሥራ የሚባለው ትልልቁ ብቻ ነው።ነገር ግን ብዙ ያልታዩ፣ ሊፈጠሩ የሚችሉና ታሪካችን ባህላችን የሆኑ ሥራዎች ብዙ ናቸውና እነርሱን አይቶ ማሳየትና ወደ ስራው ማስገባት ላይም መረባረብ ያስፈልጋል።
በግብርናው ሥራ ትልቅ አቅም መፍጠር እንደሚቻል ማየቱ ለሀገራችን እድገትና በወጣቱ ስነልቦና ለውጥ ወሳኝ እንደሆነ የሚያነሳው ወጣት ዳኜ፤ ስለ ስራ ምንነት ወጣቱን ማስረዳት ይገባል።ትልቅ ማለም እንዳለ ሆኖ ትንሽ የሚባል ሥራ እንደሌለ ማስገንዘብም ያስፈልጋል።በተለይም ይህ መሆን ያለበት በመንግስት በኩል ነው።መንግስት ሲቀየር ፖለቲካውና የዘልማድ ሥራው ሳይሆን የሚቀየረው ባህልና ታሪክ ሆኗል።ይህ ደግሞ ያልታሰበውን ጭምር ወጣቱ እንዲያስብ አድርጎታል።አመራሩም ቢሆን በተባለውና በተለመደው ብቻ እንዲጓዝ አስገድዶታል።ስለሆነም ይህንን ማስተዋልና ወጣቱን ማስተማር ብቻ ሳይሆን መቅጠርና እንዲሰራ ማድረግ ላይ ሊሰራ ይገባል።ከስልጣን በላይ ሰው መስራት ላይ መታተር ያስፈልጋልም ይላል።
በአንዳንድ የአደጉ አገራት ላይ ስልጣን ለመያዝ ብዙም ፍላጎት የለም።ምክንያቱም ስልጣኑ ልፋት እንጂ ብልጠት አይደለም።ሥራ እንጂ የራስን ጥቅም ማደላደል አይሆንም።ለዚህ ደግሞ መሰረቱ ጠያቂ ህዝብ መኖሩ ነው።እኛ ጋር ግን የሚታየው ለመብላት ስለሆነ ስልጣንን በያዝኩት እንጂ በለቀኩት አይባልም።ከዚህም በላይ ደግሞ አሳዛኙ ነገር መልካም ነገሮችን አጠናክሮ ከመቀጠል ይልቅ የዚያኛው መንግስት ሥራ ነው በሚል ማጥፋት ማልማት መምሰሉ ነው።ህዝብም ቢሆን ጠያቂ የሚሆንበት እድል አልተመቻቸለትም።በዚህም ብዙ ጎዶሎዎች እንዲኖሩን አድርጓል።እናም እንደ መንግስት እነዚህ ነገሮች ትኩረት ሊሰጣቸው እንደሚገባም አበክሮ ይናገራል።
አፍርሶ ሌላ ማምጣት ለተጨማሪ ውድቀት ያጋልጣል።የሀገሪቱን ኢኮኖሚ ዳግም ውድመት ውስጥ ይከታልም።የሰው ሀይልንም ጭምር በብዙ መንገድ እንድናጣ ያደርጋል።ከምንም በላይ ደግሞ በጎሳ ተከፋፍሎ በጸጥታ ችግር ብዙ የሰው ህይወት እየጠፋና ንብረት እየወደመ ነው።ስለዚህም እነዚህ ነገሮች አሁን በሚመሰረተው መንግስት መታደስ አለባቸው የሚለውም ሀሳቡ ነው።ህወሓትንም ሆነ ሸኔን የሚቀላቀለው ወጣት ያለ ምክንያት አይደለም።በብዙ መልኩ ስለተበደለና መኖር ስላለበት ነው።ሥራ ከምፈታ እየተከፈለኝ ራሴን ላቆይ በሚል ይቀላቀላል።እናም ወጣቱን ከእነዚህና መሰል ወቀሳዎችና ችግሮች ለማውጣት ሁሉም የበኩሉን ማበርከት አለበት በማለት ሀሳቡን አሳርጓል።እኛም ምክሩን ለህይወታችሁ አድርጉት በማለት ለዛሬ ሀሳባችንን በዚህ ቋጨን።ሰላም!
ጽጌረዳ ጫንያለው
አዲስ ዘመን መስከረም 28/2014