በሀረር ከተማ ደከር ሶፊ ወረዳ ማርያም ቤተክርስቲያን አካባቢ በሚገኘው ሰፊና በዛፎች በተሞላው ግቢ ነፋሻማውን አየር እየተመገቡ የሚንቀሳቀሱ በርከት ያሉ አረጋውያን ከወዲህ ወዲያ ሲንቀሳቀሱ ይታያሉ። በሌላው አቅጣጫ ደግሞ ሰብሰብ ብለው በተደረደረ ነጫጭ ኩባያዎች ውስጥ ጠጠር እየጣሉ የሚጫወቱም አሉ። በአንደኛው ጥግ የአትክልት ስፍራ አንድ እድሜያቸው የገፋ፤ ከትከሻቸው ጎንበስ ያሉና ብልጣብልጥ አይኖች ያሏቸውን አዛውንት አትክልት እየኮተኮቱ አገኘናቸው። ማን እንደሆኑና እንዴት እዚህ እንደተገኙ ስንጠይቃቸው በትዝታ ወደ ኋላ በመመለስ አጠር አድርገው የሰባ ሁለት ዓመት ህይወታቸውን እንደሚከተለው አወጉን።
ጋዜጠኛ እንደሻው እጅጉ እባላለሁ። እስከ ስምንተኛ ክፍል ተወልጄ ባደኩበት ይርጋለም ከተማ አካባቢ በምትገኝ አንዲት የገጠር ከተማ የተማርኩ ሲሆን፤ ከዛ ቀጥሎ በይርጋለም አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቴን ተከታትያለሁ። ከዚያም ቀጥሎ በአሁኑ ኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት በወቅቱ ስያሜው ማስታወቂያ ሚኒስቴር ዘጋቢ በመሆንም ተቀጥሬ ከአስራ ዘጠኝ ስልሳ ዓመተ ምህረት ጀምሮ እሰራ ነበር።
በስራ ባሳለፍኩባቸው ዓመታትም ከተቀጠርኩበት አዲስ አበባ ከሚገኘው ዋናው መስሪያ ቤት ጀምሮ፤ በኢሉባቡር ጎሬ ለሰባት ዓመት፤ ከዚያም አምቦ ለሶስት ዓመታት፤ እንዲሁም ባሌ ለረጀም ዓመት ስሰራ ቆይቻለሁ። ከዚያ በኋላ በአፋር የነበረ አንድ ጓደኛችን የሆነ ዘጋቢ በመኪና አደጋ ምክንያት ህይወቱ በማለፉ እሱን የሚተካ ሰው በማስፈለጉ እኔ ተመድቤ ለአራት ዓመታት ስሰራ ቆየሁ። ከዛም በኦጋዴን፤ ቀብሪ ደሀርና ደጋ ሀቡር በመመላለስ ለስድስት ዓመት ስሰራ ከቆየሁ በኋላ ወደ ሀረር በመዛወር ለሃያ ዓመታት አገልግዬ እድሜዬ ለጡረታ በመድረሱ በክብር ተሰናብቻለሁ።
የጋዜጠኝነት ስራ ከቦታ ቦታ ለመንቀሳቀስ የሚያስገድድና አረፍት የሚነሳ ነው። በዛ ላይ እኛ በምንሰራበት ወቅት የነበረው ደመወዝም ሆነ ውሎ አበል ከእለት ጉርስ አልፎ ጥሪት ለመቋጠር የሚበቃ አልነበረም። በተጨማሪ ጎበዝ ስለነበርኩ እሱ ነው የሚችለው እየተባልኩ ቶሎ ቶሎ በየቦታው እንድዛወር ይደረግ ነበር። እኔም ሀገርና የህዝብ አኗናር የማወቅ ጉጉት ስለነበረኝ በየተመደብኩበት ያለማመንታት ደስ እያለኝ እየሄድኩ እሰራ ነበር።
በሌላ በኩል እኔ ብቻ ሳልሆን ብዙዎቻችን ከአዋሽ በታች ህይወት መመስረትም ዘላቂ ሆኖ መኖርም እንዴት ይታሰባል የሚል አመለካካት ነበረን። እናም በእነዚህ ምክንያቶች ትዳር ለመጀመርም ሆነ ልጆች ለማፍራትና ቤተሰብ ለመመስረት አልበቃሁም ነበር። በዚህ ሁኔታ ውስጥ እያለሁ ደግሞ በጣም ትንሽ በሚባል ክፍያ ጡረታ ለመውጣት በቃሁ። የኔ የጡረታ ክፍያ ለውጥ ሳያመጣ ነግቶ በጠባ የሚጨምረው የኑሮ ወድነት ሁሉንም ነገር እያወሳሰበብኝ መምጣት ጀመረ። በዚህ ሁኔታ ውስጥ እያለሁ ደግሞ የኮሮና ቫይረስ መከሰት ሁሉንም ነገር አስቸጋሪ ያደርግብኝ ስለጀመር አንዳች አማራጭ ማግኘት እንዳለብኝ ለራሴ ነግሬ አካባቢዬን ማማተር ጀመርኩ።
በሀረር ከተማ ረጅም ዘመን የኖርኩ ቢሆንም ስለአብርሃ በሃታ የማውቀው ነገር አልነበረም። ከዓመት በፊት አቅመ ደካሞችን እንደሚደግፍና አገልግሎቱን ማግኘት የሚፈልጉ ካሉ መቅረብ እንደሚችሉ በሬዲዮ ማስታወቂያ ሲነገር ሰማሁና በራሴ ፍላጎት እስኪ ልይ ብዬ ወደ ግቢው መጣሁ። በግቢው ከደረስኩ ጀምሮ ያየሁት ነግር እየሳበኝና እስካሁንም አለማወቄ ያስቆጨኝ ጀመር። እኔም ያለፈው አልፏል ብዬ ፈቃደኝነቴን ተናግሬ ግቢውን ተቀላቀልኩ። በግቢው በነበረኝም ቆይታ ለዓመታት በመንግስት ሰራተኝነት ሳገለግል ያላየሁትን ለማግኘት በቅቻለሁ።
ግቢው ምቹ ነው በቀን ሶስት ግዜ ያለ ሀሳብ እንበላለን ቤታችን ይጸዳል ተንከባከካቢም አለን ቢያመን የፈለግንበት ወስደው ያሳክሙናል። ይህንን እድል ከዚህ ቤት ውጪ ብንሆን ማንኛችንም ልናገኘው የምንችለው አይደለም። እኔ በግሌ እየተሰማኝ ያለው በልጅነቴ ቤተሰቤ ጋር ያለሁ ያህል ነው የሚሰማን ይላሉ አቶ እንደሻው።
በሀረሪ የመቄዶንያ ቅርንጫፍ ማዕከል ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ዳንኤል መኩሪያን ለመሆኑ የቀድሞው አብርሃ በሃታ- የዛሬው መቄዶንያ ማእከል ማነው? ስንል ጠይቅናቸው። ዋና ስራ አስኪያጁ አቶ ዳንኤልም በሚከተለው መልኩ የማእከሉን ታሪክ አጫወቱን።
አብርሃ በሃታ የአረጋውያን መንከባከቢያ ማዕከል በአስራ ዘጠኝ ሀምሳ ስምንት ዓ.ም የተመሰረተ ነው። በወቅቱ ሀብትና ንብረታቸውን በመለገስና ለመመስረት የሚያስፈልገውን ገንዘብም በማውጣት በሀረርናበድሬዳዋ ያሉ አለሁ ባይ አባቶችና እናቶች እንዲጦሩበት ያስጀመሩትም አብርሃ በሃታ በሚባሉ በድሬዳዋ ከተማ የሚኖሩ በጎ አድራጊ የቡና ነጋዴ ኤርትራዊ ናቸው።
ማእከሉ እኚህ በጎ አድራጊ ባሟሉለት መሰረትም በአስራ ዘጠኝ ሀምሳ ዘጠኝ ዓ.ም ስራውን ከጀመረበት ግዜ አንስቶ ላለፉት ሀምሳ አራት ዓመታት በርካታ አረጋውያን የህይወት ዘመናቸውን ያለ ሀሳብ በእንክብካቤ እንዲያሳልፉ ሲያደርግ ቆይቷል። በወቅቱ የነበረው ስምም አብርሃ በሃታ የድኩማን መርጃ ይሰኝ ነበር። በዚያን ወቅትም በማእከሉ ለነበሩ አቅመ ደካሞች በየቀኑ ያለመቋረጥ የሚቀርበውን ወተት ጨምሮ ለኑሮ የሚያስፈልጓቸው ነገሮች በሙሉ ይሟሉላቸው ነበር። በዘመነ ደርግም ማእከሉ በመንግስት ስር በመሆን በርካቶችን ለመታደግና ሰው ያጡ ችግረኞችን እንባ ለማበስ የበቃ ነበር።
በወቅቱም ከድጎማ አልፎ አዲስ ራእይ በመሰነቅ በምስራቅ እዝ ጦር ሰራዊት አባላት መዋጮ የእደ ጥበባት ማስልጠኛ፤ ሰው ሰራሽ አካል ማምረቻና የከብት እርባታ በማቋቋም ገቢ በማመንጨት ራሱን የሚደግፍና ህዝብን የሚያገለግል ማእከል ለመሆን በቅቶ ነበር። ከግዜ በኋላ ግን በተለያዩ ምክንያቶች ማእከሉ በጀመረው ፍጥነት መቀጠል ሳይችል ይቀርና የነበረውንም የተጧሪ ቁጥር፤ ይሰራ የነበራቸውም ስራዎች እየተቀዛቀዙ መምጣት ይጀምራሉ።
በዚህ ሁኔታ ውስጥ እያለ ነበር መቄዶንያ ሰኔ አንድ ቀን 2012 ዓ.ም በታሪካዊው በአንጋፋው የሀረር አብርሃ በሃታ የአረጋውያን መንከባከቢያ ስራውን የጀመረው። በወቅቱ የኮሮና ቫይረስ በሀገሪቱ ተከስቶ በመስፋፋት ላይ ስለነበር በተለይ በጎዳና ላይ ያሉትን አረጋውያን ለመታደግ በተባበሩት መንግስታት በተያዘና በመቄዶንያ ስር በተያዘ የሁለት ዓመት ፕሮጀክት ነው። ፕሮጀክቱ ከፌደራልና ከሀረሪ ክልል ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ጋር በመዋዋል የተጀመረ ነው።
መቄዶንያ የተመሰረተበት ዋና አላማ የሀገር ባለውለታ የሆኑ በተለያየ የህይወት ውጣ ውረድ አለፈው ዛሬ አለሁ ባይ ጧሪ ቀባሪ ላጡ አረጋውያንን በመንከባከብ በመጦርና ፍቅር በመስጠት የህይወታቸውን መጨረሻ ለማሳመር ነው። ዛሬ ልበ ሩህሩሁ የክብር ዶክተር ቢንያም በለጠ «ሰውን ለመርዳት ሰው መሆን በቂ ነው» ከመጀመሩ በፊት አቶ አብርሃ በሃታም በሀረር ከተማ በተመሳሳይ ሀሳብና ርዕይ መስርተውት ነበር። እናም በዘመን የተለያዩት ሁለቱ የሀገር ባለውለታ ባለራእዮች በተግባር ለመገናኘት በቁ።
በአሁኑ ወቅት አብርሃ በሃታ -መቄዶንያ በቂ መጠለያና የእለት ጉርስ ሳይኖራቸው በየጎዳናው ህይወታቸውን የሚመሩትን በመለየትና ይህንን መስፈርት ያሟሉትንና ፈቃደኛ የሆኑት እያስገባ በመንከባከብ ላይ ይገኛል። እነዚህ አረጋውያን ማዕከሉን ከተቀላቀሉበት ግዜ አንስቶም በቅድሚያ ለዚሁ ጉዳይ በተዘጋጀ ልዩ ማቆያ የኮቪድ ምርምራ ተደርጎላቸው ነጻ መሆናቸው ከተረጋገጠ በኋላ ከሌሎቹ ጋር እንዲቀላቀሉና በመደበኛው ቤታቸው እንዲኖሩ ይደረጋል። በዚህ ሂደት ባጋጣሚ የኮሮና ቫይረስ የተገኘበት ሰው ካለም ለዚሁ በተዘጋጀ ቦታ አስፈላጊው እንክብካቤ እየተደረገለት እንዲቆይ የሚደረግ ይሆናል።
በተጨማሪ አረጋውያኑ ወደ ማእከሉ በሚገቡበት ግዜ በቅድሚያ የጸጉር ማስተካከል የገላ ማጠብና መሰል የቅድመ ጤና እንክብካቤ ስራዎች ይሰራሉ። የአልባሳት የመተኛና ሌሎች አስፈላጊ ቁሳቁሶችም እንዲሟሉላቸው በማድረግ በፍቅርና በእንክብካቤ የማዕከሉ ቤተሰብ እንዲሆኑ ይደረጋል። በማዕከሉ በሚኖራቸው ቆይታም በቂ ስልጠና በወሰዱና ተነሳሽነትና ፍቅር ባላቸው ሞግዚቶች ከሚደረግላቸው የእለት ከእለት እንክብካቤ ባለፈ በህክምና ባለሙያዎችም የጤና ጥበቃና የስነልቦና ድጋፍ የሚደረግላቸው ይሆናል። በአጠቃላይ የሚሰራው ሁሉ አንድ አዛውንት ወይንም እናት በቤተሰብ ውስጥ እያሉ ሊኖራቸው የሚችለውን ፍቅር እንዲያገኙ ማድረግ ነው። በጎዳና አረጋውያኑ ህይወታቸው የተጎዱ በመሆናቸውም አስፈላጊው አልሚ ምግብ በሳምንት ሁለት ቀን ስጋን ጨምሮ እየቀረበላቸው ይገኛል።
የኮሮና ወረርሽኝ ተከስቶ ማዕከሉ እንዳዲስ በመቄዶንያ ስር መተዳዳር በጀመረበት ወቅት በቂ ሊባል የሚችል መሰረተ ልማት የነበረው ቢሆንም ሲመሰረትና ለረጅም ዓመታት ከነበረበት የተወሰኑ መቀዛቀዞች የነበሩበት ነበር። በግቢው የነበሩትም ሃያ አምስት አረጋውያን ብቻ ነበሩ ግቢው ጫካ ስለነበር እሱን የመመንጠርና የማስተካከል፤ ቤቶችንም ለአረጋውያን በሚመች መልኩ የማደስ ስራም ተሰርቷል። እንዲሁም በየመኝታ ክፍሉ በመአድ ቤትና በጤና ክፍሉ መሟላት የነበረባቸው ግብአቶች እንዳዲስ እንዲሟሉ ተደርጓል።
በዚህ ሁኔታ እንዳዲስ ከተዋቀረ በኋላ እስከ አሁን ድረስ በአጠቃለይ አንድ መቶ አርባ አረጋውያን ማዕከሉን የተቀላቀሉ ሲሆን፤ ሃያ አንድ አረጋውያን በእድሜ ምክንያት አርፈዋል፤ ሰላሳ አምስት የሚሆኑ እስከ ስድስት ወር ያህል በማዕከሉ ቆይተው ከዚህ በኋላ አቅማችን በመደርጀቱ ሰርተን መለወጥ እንችላለን በማለት አመልክተው በፈቃድ የሄዱ ሲሆን በአሁኑ ወቅት ሰማንያ ዘጠኝ አረጋውያን አገልግሎቱን እያገኙ ናቸው።
በማዕከሉ የተለያዩ ብሄር ብሄረሰቦች እንዲሁም የተለያየ ሃይማኖት ያላቸው አረጋውያን አሉ። በትምህርት ዝግጅትም ኢንጂነሮችን ጨምሮ ከፍተኛ ደረጃ የደረሱ የተለያዩ የሙያ ባለቤቶች የሆኑ አረጋውያን ያሉበት ነው። አብዛኛዎቹ አረጋውያን ማእከሉን ሲቀላቀሉ በከፍተኛ የጉስቁልና ሁኔታ ውስጥ የነበሩ ሲሆን አንዳንዶቹ ራሳቸውን ከማንቀሳቀስ ጀምሮ ምንም ማድረግ የማይችሉ ዳይበር ተጠቃሚና በሞግዚት የሚንቀሳቀሱ ናቸው። ከእነዚህም መካከል እስካሁንም በማእከሉ የሚገኙና ሙሉ ለሙሉ በሞግዚቶቻቸው ትብብር ብቻ የሚንቀሳቀሱ ከአልጋ የማይነሱ ይገኛሉ። በአጠቃለይ ሁሉም ሊባል በሚችል ደረጃ ቢያንስ አንድ እንደ ስኳር ደም ማነስና ግፊት ወይንም የእይታ መጋረድና ነርቭና የመሳሰሉት የጤና እክል የገጠማቸው ናቸው።
ይህም ሆኖ ከመንግስት እየተደረገልን ያለው ድጋፍ ለአረጋውያኑ ተገቢውን እንክብካቤ እንድንሰጥ አስችሎናል ብለዋል ዋና ስራ አስኪያጁ አቶ ዳንኤል። በጤና ረገድ የክልሉ ጤና ቢሮ ድጋፍ፤ በአካባቢው የውሃ ችግር ያለ በመሆኑ የክልሉ ውሃና ፍሳሽ አገልግሎት ትብብር እያደረገልን ይገኛል ይላሉ።
በተመሳሳይ የአለማያ ዩኒቨርሲቲ የጤና ሳይንስ ፋኩሊቲ ዲን ዶክተር ለታ የነበረብንን የማገዶ ችግር በማየት ሀምሳ ሜትር ኪዩብ እንጨት ድጋፍ አድርገውልናል። ህብረተሰቡም ልደት ተስካርና የመሳሰሉትን ታሳቢ በማድረግ አረጋውያንን እየደገፉ በዓላትንም አብረውም እያሳለፉ ይገኛል። ከሁሉም በላይ የክልሉ ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ድጋፍ ብቻ ሳይሆን የቅርብ ክትትልም እያደረገ ከእኛው ጋር በመስራት ላይ የሚገኝ በመሆኑ የሚገጥሙንን ተግዳሮቶች በቀላሉ ለመሻገር አስችሎናል። ይህም ሆኖ ከኑሮ ውድነትና በየቀኑ ከሚፈጠሩ ከአረጋውያኑ ጋር የተያያዙ ሁኔታዎች አኳያ ደግሞ ብዙ መስራት የሚጠበቅብንም ነገር አለ።
ከእነዚህም መካከል ቶሎ ቶሎ የመታመም ነገር ስለሚደጋገም በቋሚነት የጤና አገልግሎት የሚሰጠን ተቋም ያስፈልገናል፡፡ በዚህ ረገድ በሀያ አስራ አራት ቃል የተገባ ቢሆንም እስካሁን የጤና መድን ሽፋን የለንም። በተጨማሪ አብዛኛዎቹ በተለያዩ ሱሶች በዋናነት ጫት ተጠቃሚ የነበሩ በመሆናቸው የተለየ ከፍተኛ ትእግስት የሚጠይቅ ጥበቃና ክትትል የሚያስፈልጋቸው ናቸው። በአሁኑ ወቅት ያሉት ሞግዚቶች በትልቅ ተነሳሽነትና በቤተሰባዊ ፍቅር እየሰሩ ቢሆንም ከበጀት ውስንነት የተነሳ የልዩ ክትትል የሚያስፈልጋቸውም በመኖራቸው በቂ አይደሉም።
ችግሮችን በተወሰነ ደረጃ ለመቅረፍ በቅርቡ የሀረሪ ክልል ብልጽግና ፓርቲ የየወረዳ ሴት አመራሮች ጋር ውይይት ተደርጎ ጉብኝትም አድርገው ትብብራቸው እንደማይለየን ነግረውናል። በቀጣይ ከትምህርት ተቋማትም ጋር በጋራ ለመስራት የያዘነው እቅድ አለ።
በሌላ በኩል አሁንም እኛ እየሰጠነው ያለውንም ድጋፍ ያላገኙ በርካታ አረጋውያን በሀረር ከተማ አሉ። ስለሆነም የምንከባከባቸውን አረጋውያን ቁጥር ለመጨመር በቤተክርስቲያንና በመስጊድ አካባቢዎች በመሄድ የማነሳሳት ስራ እየሰራን እንገኛለን።
በተጨማሪ በሀረር ከተማ ውስጥ ላሉት ስድስት ወረዳዎችና በአጎራባች በሚገኙት ሶስት ወረዳዎች በኩል ለመመልመልም በርካታ ስራዎች ተከናውነዋል። ነገር ግን በአካባቢው ከፍተኛ የጫት ተጠቃሚ ያለ በመሆኑ ይህንን ነገር አጥቶ በማቆያው ከመቀመጥ ይልቅ ሱሳቸውን አግኝተው ሌላውን ችግር መጋፈጥ የሚመርጡት ያመዝናሉ። በመሆኑም የምንፈልገውን ያህል ማስገባት አልቻልንም። ይህም ሆኖ ማእከሉ በቂ ቦታ ያለው በመሆኑ ተጨማሪ የመተኛ ክፍሎችን በማስገንባት ከአራት መቶ በላይ አረጋውያንን ለመታደግ ዝግጅት እንዳለውም አቶ ዳንኤል ጠቁመዋል።
የጥንቱ አብርሃ በሃታ የዛሬው መቄዶንያ አሁንም በሀረር ከተሞች ጎዳናዎች ላይ ላሉ አረጋውያን ብቻ ሳይሆን በተለያየ ሱስ ለተያዙ ወጣቶችም ማገገሚያ በመሆን የሀገር ባለውለታነቱን ማስቀጠል ይቻላል። ለዚህ ደግሞ የሀረሪ ክልላዊ መንግስት እያደረገ ያለውን ሁለንተናዊ ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ተስፋ አለን። ወደ ሀረር ብቅ የምትሉ ዜጎችና የከተማዋ ነዋሪዎችም አብርሃ በሃታ -መቄዶንያን በመጎብኘት የተለመደ ትብብራችሁን አትንፈጉን ሲሉ አቶ ዳንኤል መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።
ራስወርቅ ሙሉጌታ
አዲስ ዘመን መስከረም 28/2014