ቤተሰብ ዘመድ አዝማድ በከፍተኛ ተሰባስቦ ከሚያከብራቸው በዓላት አንዱ የመስቀል በዓል ነው:: በተለያዩ አካባቢዎች የሚኖር ማህበረሰብ / በሀገር ውስጥም በውጪ ሀገርም/ ለመስቀል በዓል ወደ ትውልድ አካባቢውና ቤተሰቡ ይሄዳል:: በዚህም መደጋገፉ፣ አብሮ መብላት መጠጣቱ፣ መጫወቱ በስፋት ይስተዋላል:: በወቅቱ የማይነሳ የማይጣል የለም:: በበዓሉ ሰሞን የማይደረግም የለም::
በየማህበራዊ ሚዲያው የተመለከትኳቸው የዘንድሮው የመስቀል በዓል መረጃዎችም ይህንኑ ያመለክታሉ:: የበዓሉ ታዳሚዎች ቁርጥ ሲቆርጡ፤ ጠጅ ሲያንቆረቁሩ፤ ክትፎ ሲጎራረሱ፤ ወዘተ… በየማህበራዊ ሚዲያቸው አሳይተውናል፤ ደስ ይላል፤ የበዓል ስሜትን በመስል አጋርተውናል:: የምግቡ ማማር፤ የቤቶቹ ማማር፤ የመልክአ ምድሩ ማማር፤ የሰው ማማር … ደስ ይላል:: እንኳንም ኢትዮጵያዊ ሆንኩ ያስብላል::
እኔ ግን መሰል በዓላትን ሳስብ አንድ ነገር ቅሬታ ያጭርብኛል:: ወደሱው ልግባ:: መቼም የሰው ልጅ ትናንት በብዙ መልኩ ያስፈልገዋል:: በእርግጥ ትናንቱን ሳይዝ ነገውን የሚያስብ ሰው ቤቱን በአሸዋ ላይ እንደሚገነባው ሰነፍ ነው:: ሰንብቶም ቢሆን መፍረሱ አይቀርምና:: ምንም ያህል ቢረቅቅ እና ቢመጥቅ ትናንቱ ወደኋላ ይጎትተዋል:: እናም የሰው ልጅ ሁልጊዜ ወደፊት የሚዘረጋውን ያህል ወደኋላም ይመለሳል:: ትናንትን ይናፍቃል::
ልጅነቱን፤ የእናቱን ክብካቤ፤ የአባቱን ቤት ሙቀት፤ ጓደኞቹን፤ የመንደሩን ሰዎች፤ የወጣባቸውን ኮረብቶች፤ የዋኘባቸውን ወንዞች፤ የተጫወተባቸውን መስኮች፤ የተማረባቸውን ትምህርት ቤቶች ወዘተ. ያስታውሳል:: ስለዚህም ወደኋላ የመመለስ እድል ሲያገኝ አያባክነውም:: ለዚህም ጥሩ ማሳያ የሚሆነው አውሮፓ እና አሜሪካ ገብቶ የሞቀ ህይወት ከገነባ በኋላ የእናቱ ደሳሳ ጎጆ እየናፈቀው ወደ ሀገር ቤት በየጊዜው የሚመላለሰው ኢትዮጵያዊ ነው::
በተመሳሳይም እንዲህ አይነት የትናንት ማንነት ገመድ ሆኖ ያሰራቸው የሀገር ውስጥ ዲያስፖራዎችም እንደ መስቀል እና ጥምቀት የመሳሰሉ በዓላትን ተገን እያደረጉ ወደ ሀገር ቤት ይመጣሉ:: ብዙዎቹ ግን ወደ ሀገር ቤት ሲመለሱ ከብዙ ዓመት በፊት እነሱ ከሀገራቸው ሲወጡ የነበረው ሰፈር እና ከተማ አርጅቶ እና ወዳድቆ ሲያዩት እንኳን አይደነግጡም:: አንዳንዶቹማ እንኳን ሰፈሩ እና ከተማው ያደጉበት ቤት እነሱ ትተውት እንደሄዱት እንዲያገኙት ይፈልጋሉ:: ይህ አይነቱ የትናንት ናፍቆት ግን የጤና ተደርጎ መወሰድ የለበትም::
የሳሩ ጎጆ የሳር እንደሆነ፤ እናት አሁንም በጭስ እየተጨናበሰች እንጀራ የምትጋግርበት ምጣድ ቦታውን ሳይለቅ፤ ሰውና ከብት አብረው አንድ ቤት እያደሩ፤ መደብ በአልጋ ሳይቀየር፤ ሶፋም ሳይታወቅ ቤታቸው እንደነበረው እንዲቆይ ይፈልጋሉ::
እንዲህ አይነቶቹ ሰዎች ጥቂት አይደሉም፤ እነሱ የተማሩበት ትምህርት ቤት አርጅቶ እና ወዳድቆ ፤ ያስተማሯቸው መምህራን አርጅተው እና ተጎሳቁለው፤ የተመላለሱበት መንገድ ከእድሜ ብዛት ተፈነቃቅሎ፤ የተወለዱበት ክሊኒክ ቀለም እንኳን ሳይቀይር ፤ የህዝቡ ኑሮ ከነበረበት አንዲት ስንዝር እልፍ ሳይል ሁሉም ባለበት ሆኖ ሲያዩት ደንገጥ እንኳን አይሉም:: እንዲያውም እነሱ አእምሮ ውስጥ እንደተቀረጸው ሆኖ ምንም ነገር ቦታውን ሳይቀይር ስለጠበቃቸው ደስ ይላቸዋል::ጋሽ እገሌ አረጁ፤ እገሊት አደገች ፤ እገሌ ምን ሆኖ ነው እንዲህ የከሳው ፤ እገሊትስ መች አገባች ፤ ወዘተ. እንጂ ይሄ መንገድ ከዓመት ዓመት ለምንድን ነው እየተበላሸ የሚጠብቀኝ ብሎ መጠየቅ የለም::
ይሄ ስህተት ነው:: ለውጥ የሰው ልጅ ሁሉ ፍላጎት ነው:: የሰው ልጅ ምንም ያህል የእነዚህን ነገሮች ትዝታ ቢወድደው የሚያኖረው ግን ተስፋው ነው:: ያ ተስፋ ደግሞ የለውጥ ተስፋ ነው:: ዛሬ ከትናንት የተሻለ ነው ፣ ነገ ደግሞ ከዛሬ የተሻለ ይሆናል የሚል ተስፋ ነው የሰውን ልጅ የሚያኖረው::
ይህ በየትኛውም የዓለም ክፍል የሚኖር ሰው ባህሪ ነው:: በገጠሪቱ የኢትዮጵያ ክፍል የሚኖረውም ሰው ከዚህ የተለየ እሳቤ የለውም:: ለውጥን ይፈልጋል:: ለለውጥም የአቅሙን ይሞክራል:: ነገር ግን ሁልጊዜም ቢሆን የአቅም እጥረት አስሮ ይይዘዋል:: ስለዚህም ለዚህ የለውጥ ምኞቱ አጋዥ የሚሆነውን ሀይል ይፈልጋል:: ለዚህ ደግሞ ከራሱ ልጆች ፣ ወንድሞች እና እህቶችና ዘመዶች የተሻለ ማን ሰው ይገኛል? ማንም::
ችግሩ እሱ ተስፋ ያደረገባቸው ዘመዶቹ በእሱ ውስጥ ያለውን የለውጥ ሀሳብ አለመገንዘባቸው እና በተቃራኒው ያለው እና የነበረው ነገር እንዲቀጥል መፈለጋቸው ነው:: አንዱ ወደፊት ሲመኝ፣ አንዱ ወደኋላ ይናፍቃል:: አልተገናኝቶም::
እዚህ ጋር ልብ ሊባል የሚገባው አንድ ነገር አለ:: ይህም ሁሉም ከከተማ ወደ ገጠር የሚሄድ ሰው የሚሄድበት ቦታ እንደነበረ እንዲጠብቀው ይፈልጋል ማለት አይደለም:: በተቃራኒው እንዲያውም አንዳንድ ልባሞች የትውልድ መንደራቸውን ለማልማት ሲደክሙ ነው የሚውሉት:: የትውልድ ስፍራቸው በልማት ወደኋላ መቅረት አንገብግቧቸው ተሰባስበው ትምህርት ቤት፤ ክሊኒክ፤ መንገድ ወዘተ የገነቡ ጀግኖች ጥቂት አይደሉም::
ችግሩ እንደዚህ አይነቶቹ ሰዎች ብዙ አለመሆናቸው ላይ ነውም:: በተቃራኒው አንዳንዶች ከተማ ላይ ሲሆኑ የምንትስ ተወላጆች ማህበር፤ የምንትስ አብሮ አደጎች ህብረት ወዘተ የሚል ስብስብ ፈጥረው አንድም የረባ ነገር ሳይፈጽሙ፤ እንዲያውም ለልማት የተነሳሱ ሰዎችን ሲያጣጥሉ የሚውሉ ሆነው ይገኛሉ:: አንዳንዶቹ ደግሞ የሀገር ልጅ ህብረት ብለው ፈጥረው ከዓመት ዓመት እየተሰባበሰቡ ሲደግሱ፤ ሲበሉ እና ሲጠጡ ውለው ይበተናሉ::
በዓመት አንድ ቀን ወይም አንድ ሳምንት ሀገር ቤት ገብቶ አካባቢዋ ወይም ከተማዋ ከምትችለው በላይ የመዝናኛ ድግስ በማድረግ የሚቀየር ነገር የለም:: እርግጥ በዚያ ሰሞን ከከተማ ወደ ገጠር የሚኖረው የሀብት ፍሰት ከተማዋን ሊጠቅም ይችላል:: ነገር ግን የአንድ ቀን ኢንቨስትመንት መሰረታዊ ለውጥ አያመጣም::
ለውጥ የሚያመጣ ድጋፍ ያስፈልጋል:: ይህም አንድም በረዥም ጊዜ ትርፍ የሚያመጡ ኢንቨስትመንቶችን በማድረግ ነው:: ይህም ማለት ለምሳሌ ያህል አዲስ አበባ ላይ ሆቴል ያለው ሰው በትውልድ ከተማው ላይ አንድ ደህና ሬስቶራንት እንኳ ቢሰራ ብዙ ጥቅም ይሰጣል:: ያ ሬስቶራንት በፍጥነት አትራፊ እንደማይሆን ቢያውቅም እንኳ ለከተማው እድገት ሲል ከትርፍ በላይ ማህበራዊ ፋይዳውን በመገንዘብ ታግሶ ስራውን ከቀጠለ የስራ እድል ይፈጥራል ፤ ለከተማዋ ኢኮኖሚም አስተዋጽኦ ያደርጋል::
በሌላ መልኩ የሀገር ልጆች ተባብረው መንገድ ወይም ትምህርት ቤት ወይም ጤና ጣቢያ ወይም ሌላ ነገር መገንባት ይችላሉ:: በዚህ መልኩ ሀገር ቤት የቀረ ህዝባቸው ትምህርት ያገኛል ፤ ጤናው ይጠበቃል ፤ ለእንቅስቃሴ ምቹ የሆነ የተስተካከለ መንገድ ይኖረዋል ወዘተ…:: ከዚህም ባለፈ መንግስትም ለእነዚህ ነገሮች የያዘው በጀት ካለ ሌሎች አገልግሎቶችን በማዳረስ ላይ እንዲያውል ያግዘዋል::
ከዚያ ባለፈ ግን በዓመት አንድ ቀን በሚደረግ ድግስ ለውጥ አይመጣም:: ዘመድ አዝማድ ከገጠር ወደ ከተማ እንዲፈልስ በማድረግ መሰረታዊ ልዩነት መፍጠር አይቻልም:: ለውጥ የሚመጣው ራሱ ቦታውን በመቀየር ነው እንጂ፤ ወደ ተቀየረ ቦታ በመፍለስ አይደለም:: ለውጥ የሚመጣው ትናንትን ባለበት አቁሞ ነገርን በማሯሯጥ አይደለም::
እኛ ወደፊት ስንራመድ ትናንታችንም አብሮን መራመድ አለበት:: እኛ ስንቀየር ያሳደግን መንደር እና ከተማ ፤ የተወለድንበት ቤት፤ የተማርንበት ትምህርት ቤት ፤ የተጓዝንበት ጎዳና አብሮን ካልተቀየረ እኛ እያደግን፣ ከእነዚህ የማንነታችን መሰረቶች ግን እየተነጠልን እንሄዳለን:: ስለዚህ የማንነታችን መሰረታ የሆኑ ነገሮች እንዲቀየሩ እንበርታ! እናም አንዳንዴ ይቆጨን::
(አቤል ገ/ኪዳን)
አዲስ ዘመን መስከረም 26/2014