የአርሲ ክፍለ አገር አሰላ ከተማ፣ ኢትዮጵያ በዓለም መድረክ ላይ ዜጎች አንገታቸውን ቀና እንዲያደርጉ የኩራት ምንጭ የሆኑ ውድ ልጆቿ የሚፈሩባት የኢትዮጵያ ክፍል ነች። በተለይ በአትሌቲክስ ስፖርት ሻለቃ ሃይሌ ገብረስላሴ፣ ደራርቱ ቱሉ፣ ቀነኒሳ በቀለ፣ ጥሩነሽ ዲባባ የመሳሰሉ ፈርጦችን ማህፀኗ ከማይነጥፈው አሰላ የወጡ ብርቅዬዎች ናቸው። በእግር ኳሱም ቢሆን አንዷለም ንጉሴ (አቤጋን) መጥቀስ ይቻላል።
አስደንቃን የማታበቃው ማህፀነ ለምለሟ የአሰላ ከተማ፣ ዛሬም አገራቸውን በልዩ ልዩ ዘርፎች የሚያገለግሉ ብርቅዬዎችን እያስተዋወቀችን ነው። ከነዚህ ውድ ልጆቿ መካከል ደግሞ በርካታ መሰናክሎች አልፋ የትራንስፖርት ዘርፉ ላይ “አብዮት” ያስነሳች፣ ስኬታማ የፈጠራ ባለሙያና የጠንካራ ሴቶች ምሳሌ የሆነች ፈርጥ ሰጥታናለች። በበርካታ ችግር ተተብትቦ የቆየውን አገልግሎት በፈጠራ ቴክኖሎጂ በማገዝ ቀልጣፋ፣ በጥራት የታገዘ፣ ግዜንና ጉልበትን የቆጠበ አንዲሆን የዚህች ብርቱ ሰው ትጋት ጉልህ ድርሻ ይወስዳል።
ተገልጋዮች በቀላሉ ስልካቸውን ተጠቅመው ከአቅራቢያቸው የትራንስፖርት አገልግሎት እንዲያገኙ፣ የሚደርስባቸውን እንግልት፣ ዘረፋና ትንኮሳ የሚያስቀር፣ ከየአስተዳደር ሰራተኞችን ጨምሮ 38 ሺህ በላይ አሽከርካሪዎችና የመኪና ባለንብረቶች ስራ እንዲፈጠርላቸው፣ እንዲሁም አዲስና ዘመናዊ ሥርዓት እንዲዘረጋ በማስቻል የዘርፉ ተጨማሪ ሃይልና ጉልበት ሆናለች። የዛሬው የስኬት አምድ እንግዳችን የሆነችው “የሃይብሪድ ዲዛይንስ ኤንድ ራይድ” መስራችና ስራ አስፈፃሚ ሳምራዊት ፍቅሩ።
ወደ ስኬት ግስጋሴ
ተወልዳ ያደገችው በአርሲ አሰላ ከተማ ውስጥ ነው። ዛሬ ላይ በቴክኖሎጂና በስልክ መተግበሪያ የሚሰራ ፈጣን የትራንስፖርት አገልግሎት መስርታ ስኬታማ ትሁን እንጂ፤ የልጅነት ህልሟና ልትደርስበት የምትፈልገው ግብ እርሱ አልነበረም። ይልቁንም በሳይንሱ ዘርፍ ለባዮሎጂ ትምህርት ከፍተኛ ፍቅር ነበራት። የአሰላ ብርቅዬ አትሌቶችን ፈለግ ለመከተል አትሌት የመሆን ተጨማሪ ፍላጎት የነበራት ቢሆንም በአባቷ ክልከላ ምክንያት ወደ ትምህርቱ እንድታዘነብል ሆናለች። “በትምህርቱም በአትሌቲክሱም ውጤታማ ነበርኩ አባቴ ግን ይበልጥ ትምህርቱ ላይ እንዳዘነብል ገፋፋኝ” በማለትም የህይወት መስመሯ እንዴት ወደ ሳይንሱና ቴክኖሎጂው ዘርፍ ሊያዘነብል እንደቻለ ትናገራለች።
ሳምራዊት በልጅነቷ ብዙ ከቤት መውጣት አይፈቀድላትም ነበር። ይሁን እንጂ በትርፍ ጊዜዋ አትክልቶችን በጊቢ ውስጥ (በተለይ አዲስ የሆነና አይታው የማታውቀውን አይነት) በመትከል አጋዥ መፅሃፍትን በብዛት በማንበብ ታሳልፍ ነበር። ጓደኞቿ እቤት በሚመጡበት ጊዜም አዳዲስ ሃሳቦችን መወያየትና መጫወትን ታዘወትር ነበር። ሁሌም አዳዲስ ነገሮችን የመፍጠር ጉጉቷ የመጣውም ከዚያ የሚመነጭና አብሯት ያደገ ነው።
“ኮምፒውተር 12ተኛ ክፍል ሆኜ ነው ለመጀመሪያ ጊዜ ያየሁት” የምትለው ሳምራዊት የቴክኖሎጂ እቃዎችን፣ የሙዚቃ መሳሪያዎችን አሊያም መሰል ከቴክኖሎጂ ጋር የተያያዙ ቁሳቁሶችን በምትኖርበት አካባቢ የማግኘት እድል እንዳልነበራት ትገልፃለች። በአጋጣሚ ግን በአንድ የስልጠና ማእከል ውስጥ ያየችው ኮምፒውተር ሙሉ ለሙሉ አመለካከቷንና የትምህርት አቅጣጫዋን ቀየረው። ቴክኖሎጂውን ለማወቅ በጣም በመጓጓቷም በወንድሟ አማካኝነት አዲስ አበባ ለእረፍት ስትመጣ ስለ “ኮምፒውተር ምንነት” መረዳት፣ ኢንተርኔት ቤት ማዘውተርና በግሏ ማንበብን ተያያዘችው።
“መጀመሪያ ላይ የባይሎጂ ትምህርት ላይ ጎበዝ ስለነበርኩ ፍላጎቴ የሜዲካል ዶክተር መሆን ነበር” የምትለው ሳምራዊት፤ ለመጀመሪያ ጊዜ ኮምፒውተር ስታይና ጥቅምና አገልግሎቱን በደንብ ስትለይ ግን የዚህ ሙያ ባለቤት ለመሆንና ለመወሰን ጊዜ አልወሰደባትም ነበር። ወዲያው ቤተሰቦቿን በተለየ ደግሞ የኤሌክትሪካል ኢንጂነር የባለሙያ የነበረውን ወንድሟን በማሳመን “ማክሮሊንክ ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ኮሌጅ” ገብታ በሶፍትዌር ኢንጅነሪንግ ዲፕሎማዋን ያዘች።
ወዲያው እንደወጣች ስራ ለማግኘት አልተቸገረችም ነበር። በሲስተም አናሊስስ በአንድ ድርጅት ውስጥ ተቀጠረች። ብዙም ሳትቆይ ዲግሪዋን ሂልኮ የኮምፕዩተርሳይንስና ቴክኖሎጂ ኮሌጅ በመግባት ጀመረች። በተጨማሪ በአንድ ሙዚቃ ቤት ውስጥ የሽያጭ ሰራተኛ በመሆን ሁለት ስራና በአንድ ተምህርት እራሷን ጠምዳ ወደ ህይወት ግቧ መገስገሱን ተያያዘችው።
አዲስ የሽያጭ መዝገብ ሶፍትዌር ፈጠራ
የራይድ ትራንስፖርት መስራች ሳምራዊት ለመጀመሪያ ጊዜ በተቀጠረችበት የሙዚቃ ሽያጭ ቤት ውስጥ “መረጃ መዝግቦ የሚይዝ” የሽያጭ ሲስተም በመስራት ለባለቤቱ እዚያው መስራት ቻለች። ይሄን የፈጠራ ስራ ለመስራት ያነሳሳት እጅግ አድካሚ የሆነ ጊዜና ጉልበት የሚወስድ የአሰራር ሥርዓት በመመልከቷና ያንን ችግር መፍታት ስለፈለገች ነበር። የቤቱ ባለቤትም የፈጠራ ስራዋ ስላስደሰተው ሊገዛት ችሏል።
በዚህ ሳታበቃም ለሌሎች ተመሳሳይ ችግር ላለባቸው የንግድ ተቋማት የፈጠረችውን ሲስተም በተወሰነ መልኩ መሸጥ ቻለች። ይሄን ጊዜ ነበር ተቀጥሮ ከመስራት ይልቅ በራሷ ፕሮጀክቶች በመንደፍ ስራዎችን የመስራት አስፈላጊነት ላይ ይበልጥ ማተኮር የጀመረችው። ሲኒየር የሶፍትዌር ባለሙያ በመሆን በሌላ ድርጅት ውስጥ ተቀጥራ ክህሎቷን በደንብ ማሳደግ ጀመረች። በድርጅቶች ውስጥ የመስራት ፍላጎቷ ዋንኛ ምክንያት የነበረው በግሏ መስራት ስትጀምር ልምድ እንዲኖራት ነበር።
በአገር ውስጥ ካሉ ድርጅቶች ሌላም በካሜሮን አገር ሲኒየር የሳይበር ሶፍትዌር ባለሙያ ሆና ሰርታለች። የነዚህ ሁሉ መነሻ ደግሞ አሁን ላይ በእጀጉ በስኬታማነቱ በአገርው ውስጥ ካሉ ካምፓኒዎች መካከል የሚጠቀሰው “የራይድ የትራንስፖርት አገልግሎት” እንድትፈጥር ትልቁን መንገድ የከፈተላት ነበር።
የትራንስፖርት ዘርፉን ያነቃቃ የፈጠራ ስራ
ሳምራዊት ጠንካራ ህልምና እምነት አላት። ላመነችበት ነገር እስከመጨረሻው ትታገላለች። የጀመረችውን በስኬት ለመጨረስ ተቸግራ አታውቅም። ይሄ ትጋቷ ደግሞ በግል የመስራት ፍላጎቷን ይበልጥ አነሳሳው። የሽያጭ መተግበሪያ ሶፍትዌርና ሌሎች መተግበሪያዎች የሰራች ቢሆንም ዋነኛ ግቧ ግን ያ ብቻ አልነበረም። የማህበረሰቧን ችግር የሚፈታ ትልቅ ፕሮጀክት ማውጠንጠን ጀመረች።
በግል ቢሮዋን ከፍታ እራሷው የሽያጭ ባለሙያ፣ እሷው ስራ አስኪያጅ እንዲሁም የሶፍትዌር ዴቨሎፐር በመሆን በአንድ ኮምፒውተር፣ ጠረጴዛና ወንበር ጀምራ ህልሟን መከተል ጀመረች። አምሽታ ትሰራለች። ፕሮጀክቶችን ትነድፋለች። እኩለ ሊሊት ሲሆን ወደ ቤቷ ትሄዳለች። የዚህን ጊዜ ነበር ከስጋት ነፃ የሆነ፣ ዋጋው በቴክኖሎጂ የሚታገዝና ጭቅጭቅ የሌለበት ለተሳፋሪውም ሆነ ለአሽከርካሪው አደጋን የሚቀንስ በስልክ መተግበሪያ የሚሰራ የትራንስፖርት አገልግሎት ለመመስረት ያቀደችው።
ብዙ ጊዜ ተገልጋዮች በውድ ዋጋ እራሳቸውን ለአደጋ አጋልጠው ጭምር በሌሊት ትራንስፖርት ለመያዝ መገደዳቸው ፈጠራዋን ይበልጥ እንድታስብበት አደረጋት። በተለይ እሷ ከቢሮዋ አምሽታ መውጣቷ ይህን ስጋትና ችግር እንድትገነዘበው አድርጓት ነበር።
የራይድ መጠንሰስ፣ ተግዳሮትና ስኬት
በአንድ ኮምፒውተር፣ ሰርቨርና የግል ክህሎቷን ብቻ ይዛ “ከስጋት ነፃ” የሆነ የተሳፋሪን፣ የአሽከርካሪውን ማንነት የሚያሳውቅና ተመጣጣኝ ክፍያን የሚጠይቅ መተግበሪያሰራች። ይሄ ትልቅ ስኬት ነበር። ይሁን እንጂ ስራውን ስትጀምረው በርካታ ፈተና ገጠማት። የመጀመሪያው “የፈጠራ ውጤቷን” ገበያው ላይ ለማስተዋወቅና ለማስፋፋት “ፋይናንስ” የሚያደርጋት ማግኘት አለመቻሏ ነበር። ይህን እንቅፋት ለማለፍ፣ ብድሮችን ለማግኘትና የሚያግዛት አካል ለመፈለግ በርካታ ባንኮችና የማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት ዞራለች። ግን ሁሉም ስጋታቸውን ብቻ በመግለፅ ፍቃደኛ መሆን አልቻሉም። ከብዙ ልፋትና ስራዋን ለኢንቨስተሮች የማስተዋወቅ ትጋት በኋላ ግን የሚደግፋት አካል አገኘች።
ሆኖም የሳምራዊት አዲስ የትራንስፖርት “አብዮት” የሚፈጥር የሞባይል መተግበሪያ ሌላ ፈተና ከመንግስት አካላት ገጠመው። ዋናው ምክንያት ደግሞ “እንደዚህ አይነት ሥርዓት ማስተናገድ የሚችል የህግ ማእቀፍ፣ መመሪያ የለንም። ስራውን ማቆም ይኖርብሻል” የሚል ተደጋጋሚና ተስፋ አስቆራጭ ሙከራዎች ተደረጉባት። ችግሩ እያለ መፍትሄ የሚሰጥ “የስራ ፈጠራ ውጤት” በጥቂት ባለስልጣናት አለማወቅ ተደጋጋሚ መታሸግና የስራ ክልከላ ተደረገበት። ይሁን እንጂ በፍርድ ቤት እግድ እየሰራች ለሶስት ዓመት ተከራክራ በመጨረሻ መፍትሄ አገኘ። ስራዋን ስኬታማ እንዲሆን ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ፣ የቀድሞው የአዲስ አበባ ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ኡማ ትልቅ እገዛ አደረጉላት።
“ራይድ የተነሳው ከችግር ነው። የማህበረሰቡን የትራንስፖርት ፈተናና ተያይዞ የሚመጡ ስጋቶችን ለመቅረፍ ነበር የተነሳነው” የምትለው ሳምራዊት ስትጀምረው ብቻዋን በ40 ሺህ ብር ካፒታል የነበረ ሲሆን፤ በአሁኑ ሰዓት ግን ስድስት የአክሲዮን አባላትን በባለድርሻነት ይሳተፉበታል። መተግበሪያውን ለመሥራት አራት ወር ወስዶባታል። አሁን ላይ ይህ ግዙፍ የከተማችን በኢንተርኔት፣ በስማርት ስልክና በትራንስፖርት ሰጪ አሽከርካሪዎች የሚሰራ፣ 37 ሺ አሽከርካሪዎችና የመኪና ባለቤቶች የሚሳተፉበት፣ ከ500 በላይ ቋሚ ሰራተኞችና በኮንትራት የሚሰሩ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰራተኞችን ያቀፈ “የትራንስፖርት አብዮት” የፈጠረ ድርጅት ሆኗል።
የራይድ መስራችና ስራ አስፈፃሚ ሳምራዊት አሁን ላይ በክልሎች አገልግሎቱን ለማስፋት እየተንቀሳቀሰች እንደሆነ ትናገራለች። ወጣቱና የስራ ፈጣሪው አዲሱ ትውልድ ምንም አይነት ፈተናዎች ከፊት ለፊቱ ቢጋረጡ ተስፋ መቁረጥ እንደሌለበትና ህልሙ ወደ ተግባር ለመቀየር መትጋት እንዳለበት ትናገራለች። በተለይ ሴቶች “ከጭምተኝነትና እራሳቸውን ከመቆጠብ” ወጥተው ህልማቸውን እንዲኖሩ እንደምትሻ ትመክራለች። ለዚህ ደግሞ በእርግጥም ከእርሷ የተሻለ ምሳሌ አይገኝም።
ራይድ ከአንድ ኮምፒውተርና ከ40 ሺ ብር ካፒታል ተነስቶ የሚሊዮን ብሮች ካፒታልና ግዙፍ ተፅኖ ፈጣሪ መሆን ችሏል። ዛሬ የሃይብሪድ ዲዛይንስ ኤንድ ራይድ መስራች እና ሥራ አስኪያጅ ሳምራዊት ፍቅሩ የአፍሪካዊ ቢዝነስ ባለ ራዕይ ሽልማት አሸናፊ ሆናለች። በየዓመቱ የሚዘጋጀው የአፍሪካ ኦፕን ቢዝነስ አዋርድ ሳምራዊት ፍቅሩን ለበርካቶች የሥራ እድል በመፍጠር ምርጥ አፍሪካዊ የቢዝነስ ባለ ራዕይ (Best African Business Visionary) ብሎ የ2021 ተሸላሚ አድርጓታል።
ይህ ብቻ አይደለም ራይድ ከምንም በላይ በኢትዮጵያውያን የስራ ፈጣሪዎች፣ ተገልጋዮች ዘንድ ከፍተኛ አድናቆት አለው። የቀድሞው የአሜሪካን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ማይክ ፖምፒዮ፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይን ጨምሮ ግዙፍ አገልግሎት ሰጪ የመጪው ትውልድ የቴክኖሎጂና የስልጣኔ አርማ መሆኑን መስክረውለታል።
”የአትሌት ሃይሌ ገብረስላሴ አድናቂ ነኝ”
ሳምራዊት በ40 ሺህ ብር የመሰረተችው “ራይድ” አሁን ላይ ለመንግስት ብቻ አሽከርካሪዎቹን ጨምሮ እስከ 347 ሚሊዮን ብር በዓመት የገቢ ግብር እየከፈለ ነው። ከምንም በላይ ግን የትራንስፖርት ዘርፉ እንዲዘምን ጉልህ ድርሻ አበርክታለች። በዚህ ትልቅ ስኬታማና ለወጣቱ “አርአያ መሆን የምትችል የስራ ፈጣሪ ሆናለች።
እሷ ለሌሎች አርአያ የሚሆን ስራ ትስራ እንጂ በግሏ ግን በጥንካሬውና በትጋቱ “ አትሌት ሻለቃ ሃይሌ ገብረስላሴን በጣም ነው የማደንቀውና የማከብረው” ትላለች። አገሩን በስፖርቱ በዓለም መድረክ ላይ ከማስተዋወቁም በላይ በንግድ ስራ ላይ ተሰማርቶ ለብዙዎች የስራ እድል መፍጠሩን አንስታ “የሁላችንም ጀግና ነው። እስካሁን እድሉ ባይፈጠርም በቅርቡ ላገኘውና ምስጋናዬን ላቀርብለት እወዳለሁ” ብላለች።
ዳግም ከበደ
አዲስ ዘመን መስከረም 22/2014