ገና እየነጋ ነው… ሁለት አይነት የብርሃን ቀለም በበሯ ሽንቁር ይታያታል። በመኝታዋ ግርጌ ካለው የግራር ዛፍ ላይ ወፎች ሲንጫጩ ይሰማታል። የጎረቤቷ የእማማ ስህን አውራ ዶሮ በማን አለብኝነት ሲጮህ ይሄም ይሰማታል። ማለዳዋ እንዲህ ነው በወፎች ንትርክና በአውራ ዶሮ ድንፋታ የተሞላ። ባልመሸና ባልነጋ ሁለት አይነት ዓለም ውስጥ ሆኖ ስለ ነገ የሚያስጨንቅ።
ማለዳ ትወዳለች፤ ማለዳ የነፍሷ ውብ ስዕል ነው። በትናንት በዛሬዋና በነገዋ ውስጥ የተቀለመ። ራሷን ሙሉ ሆና የምታገኘው በአራስ ጀምበር ፊት ነው። ንጋት የህይወቷ መጀመሪያና መጨረሻ ነው። ጀንበር ምስራቅ አድማስ ላይ ስታቅላላ፣ ሰማይ በቀይና በጥቁር ሁለት መልክ ብርሃን ሲያሸበርቅ መኖር ደስ ይላታል። ምድር በአራስ ጀምበር ስትረሰርስ፣ ቀዬው የእንቁላል አስኳል ሲመስል ያኔ ሌላ ናት። ራሷን ፈልጋ የምታገኘው በዚህ እውነት ውስጥ ነው። በዚህ እውነት ውስጥ መኖር የምንጊዜም ምኞቷ ነው።
የነፍሷን ውብ ስዕል ንጋትን ሽታ ከነለሊት ልብሷ ወደ መስኮቱ ተራመደች። መሬት የሚልስ ረጅም ልብሷን በእጆቿ አንቃ። ጸጉሯ ከለሊት ልብሱ አፈንግጦ ጀርባዋ ላይ ይዘናፈላል፤ እናቷን በሚያስታውሳት መልኩ ተጎንጉኖ። ጸጉሯ የእናቷ ማስታወሻ ነው፤ በወር አንድ ጊዜ አብረሃም እንደሚወደው ካልተሰራች በስተቀር ሁሌም ሹሩባ ነው።
አብረሃም የልጅነት ፍቅረኛዋ ነው። አሁን የት እንዳለ አታውቅም። ድንገት ነው እንዲህ እንደ አሁኑ ማለዳን ሽታ በቆመችበት ወጥቶ የቀረው። በነፍሷ የሁለት ሰዎች ንብረት ናት፤ የእናቷና የአብረሃም።
እናቷ የአእምሮ ህመምተኛ ናቸው፤ አማኑኤል ሆስፒታል ነው የሚገኙት። ሁሌ ጠዋትና ማታ ከሹሩባዋ ጋር እየሄደች እቅፋቸው ውስጥ ትወድቃለች። እስከ አስራ ስምንት ዓመቷ ድረስ ጸጉሯን የሚሰሯት እሳቸው ነበሩ። ያንን ሁሉ ዘመን ከሹሩባ ሌላ ሰርተዋት አያውቁም። ከነሹሩባዋ እናቷ ፊት መቆም ደስ ይላታል፤ እናቷን ከህመም የሚያሽርላት፣ ትናንትን የሚመልስላት ይመስላታል።
አብረሃም በነፍሷ ላይ ሳይሞት የሚኖር ነፍስ ነው። ጠይም ነው፤ እንደ መስቀል ደመራ እንጨት ዘለግ ያለ። እንደ እናቷ የሳለችው በህይወቷ ውስጥ ዳግም እንዲፈጠር የምትሻው አንድ እውነቷ ነው። ንጋትን ያስለመዳት፣ ማለዳን ያስወደዳት እሱ ነው። ሁሌ እንዲህ እንደ አሁኑ በሚነጋ ሰማይ ፊት እሷን አጠገቡ አድርጎ ‹እኔና አንቺ ጀምበርና ሰማይ አንድ አይነቶች ነን። አንዳችን ያላንዳችን ስፍራ የለንም። ሰማይ ለጀምበር መድመቂያዋ ነው። ጀምበር ለሰማይ ውበቱ ናት። እኔና አንቺም እንዲሁ ነን፤ እንደዚህ ንጋት ይላት ነበር።
ሊነጋ ያለን ሰማይ እንደማየት ደስታ የላትም። ከደመና ለመውጣት የምትተናነቅን ጀንበር እንደማየት ፍሰሀ የላትም። ብርሃን ከጨለማ ውስጥ ሲወጣን የመሰለ ድንቅ ተፈጥሮ አታውቅም። በብርሃን የተሳለን ድንቅ ተፈጥሮ ቆሞ እንደማየት ጥበብ አታውቅም። በጎጆአቸው ውስጥ ሆነው የሚያንሾካሹኩ ወፎችን እንደመስማት፣ በቤታቸው ውስጥ ሆነው ንጋት አብሳሪ አውራ ዶሮዎችን እንደማድመጥ ጥኡም ሙዚቃ አታውቅም። በጋጣቸው ውስጥ ሆነው፣ በጉሬአቸው ውስጥ ተደብቀው የሚቁነጠነጡ ነፍሳትን እንደመስማት ዓለም የላትም። ግን ብዙ ናፍቆት አለባት… ብዙ ትዝታ። በህይወቷ ውስጥ እንዲመለሱ፣ ዳግም እንዲፈጠሩ የምትፈልጋቸው ትኛንትናዎች አሉ። ትኖራቸው ይሆን? አታውቅም።
መስኮቱን ከፈተችው… እንዳሰበችው ሆነላት። ጠይም ምድር፣ ጠይም ሰማይ፣ ጠይም ተፈጥሮ ፊቷ ላይ ተጋረጠ። ብርሃንና ጨለማን የቀላቀለ ጅብማ ዓለም ተቀበላት። ደስ አላት፤ ሰማያዊ ደስታ። እንዲህ ደስ የሚላት ከእለታት አንድ ቀን ነው እና እንዲህ እንደ አሁኑ ሊነጋ ባለ ሰማይ ስር ስትቆም። እንዲህ ደስ የሚላት በመኝታዋ ግርጌ ካለው የግራር ዛፍ ላይ ያሉ ወፎች ሲንጫጩ፣ የእማማ ስህን አውራ ዶሮ ሲጮህና እናቷ ፊት ስትቆም… አብረሃም ትዝ ሲላት።
ጎረምሳ ንፋስ አጠናፈራት። ደረቷን አላግቶ፣ የለሊት ልብሷን አወናጭፎ ወደ ሳሎኗ ሲገባ አላስተዋለችውም ነበር። ወደ ሰማይ አየች፤ ቀይ ጥቁር፣ ቡናማና አመዳማ የብርሃን ሽርጥ አሸርጧል። ወደ ምስራቅ ቀና አለች፤ ምስራቅ አድማስ በብርሃን ለሀጭ ተዝረክርኳል።
ልጃገረድ ኮረዳ ጀምበር ማርያም… ማርያም በሚሉ ወዳጆች ታጅባ ንጋትን ለመውለድ ስታምጥ ይታያታል። በዙሪያዋ ሽር ጉድ የሚሉ ጠይምና ቀይዳማ የብርሃን መልኮች ከበዋታል። የእግዜር እውነት ይገርማታል። በመኝታዋ ግርጌ ዋርካው ላይ የሰፈሩት አእዋፋት ማለዳን ሲያበስሩ ይገርማታል። የጎረቤታቸው የእማማ ስህን አውራ ዶሮ እኩለ ለሊትን ለመነገር ነፍስ ማወቁ ይሄም ያስደንቃታል። የእግዜር እውነት ይገርማታል። በብርሃን ውስጥ ጨለማ፣ በጨለማ ውስጥ ብርሃን ማኖሩ፣ በትናንት ውስጥ ዛሬን፣ በዛሬ ውስጥ ነገር መደበቁ ያስደንቃታል።
ወደ ጀንበር አየች፤ ምጥ ላይ ናት፤ ብርሃንን ለመገላገል። እዬዬዋ ይሰማታል፤ ልጇን ወልዳ ለመሳም ያላት ጉጉትም። የሰው ልጅ ያልደረሰበት የተፈጥሮ እውነት ንጋት ውስጥ ያለ መሰላት። በመኖር ውስጥ ያለው ስውር እውነት መሽቶ መንጋት፣ ነግቶ መምሸት ነው ስትል አሰበች። በንጋት ስር መቆም፣ በንጋት ስር ተፈጥሮን መቃኘት ደስታዋ ባለፈ የእውነቷ መገኛ ስፍራ ነው። የጠፋባትን እውነት በንጋት ጉያ ውስጥ ነው የምታገኘው። እንዲመለሱ የምትሻቸውን ትናትናዎች በመስኮቱ አሻግራ ሰማዩ እርቃን ላይ ነው የምታያቸው። ከቀይና ከጥቁሩ የብርሃን ጓል እያጠቀሰች ራሷን ሳለችው። እየነጋች፤ እየፈካች ራሷን አገኘችው።
ኮቴ ሰማች…
በንጋት ትካዜ ውስጥ ናት። የጀምበርን ምጥ እያማጠች… ጭንቀቷን እየተጨነቀች። በትካዜዋ ውስጥ ሳለች አንድ ሰው ውልብ አለባት፤ ከጨለማው ጋር የተመሳሰለ አንድ ሰው። እንደ መስቀል ደመራ ዘለግ ያለ።
ወደምትናፍቀው እውነት እየቀረበች እንደሆነ አላስተዋለችም። እምነቷን ከጀምበሯ መገላገል በኋላ ወዳለው አዲስ ዓለም አድርጋ ጠበቀች። እንደዛሬ የሆነ ንጋት ያየች አይመስላትም። በጀምበር ጉያ ውስጥ ይሄ ነው የማትለው የሆነ እውነት ይታያታል። ወደ እሷ የተዘረጋ እውነት።
በቆመችበት ምድር ወገግ አለች። ለመጨረሻ ጊዜ ወደ ሰማይ ቀና አለች፤ ጀምበር ወልዳ፣ ምስራቅ አድማስ በብርሃን አቅላልቶ አየች። የምትጠበቀው እውነት ይሄ ነበር። ልትደርስበት የምትሻው ሀቅ ይሄ ነበር፣ ሳቀች በነፍሷ።
እለተ ማክሰኞ ፤ወገግ ሲል ከመስኮቱ ጋ ፈቀቅ አለች። ወደ እናቷ ጋ ልትሄድ ወደ ኋላዋ ስትዞርና በሩ ሲቆረቆር አንድ ሆነ።
በሩን ከፈተችው።
ያየችውን ማመን አልቻለችም፤ እንደ መስቀል ደመራ እንጨት ዘለግ ያለ አንድ ሰው በር ላይ ቆሟል፤ አብረሃም።
በትረ ሙሴ (መልከ ኢትዮጵ)
አዲስ ዘመን መስከረም 21/2014