ወወክማ «ወጣት ወንዶች ክርስቲያናዊ ማህበር» ከተመሰረተ አንድ መቶ ሰባ ስድስት ዓመት ሆኖታል። የተመሰረተው በእንግሊዝ ሀገር ሲሆን በአሁኑ ወቅት በበርካታ ሀገራት ስራውን እየሰራ ይገኛል። ማህበሩ በኢትዮጵያ ስራውን የጀመረው ደግሞ በአጼ ሃይለ ስላሴ ዘመነ መንግስት በ1942 ዓ.ም. ነው። በኢትዮጵያ የወወክማ ዋና ዳይሬክተር የሆኑትን አቶ ዳግማዊ ሰላምሳ አነጋግረን የሚከተለውን ይዘን ቀርበናል።
ዋና ዳይሬክተሩ እንደሚያብራሩት የማህበሩ ዋና ዓላማ ወጣቶችን ሁለንተናዊ እድገት እንዲኖራቸው ማስቻል ነው። የማህበሩን እንቅስቃሴ ማህበሩ በጅምሩ ወቅት በአብዛኛው ይሰራ የነበረው አራት ኪሎ አካባቢ የቤት ውስጥ ስፖርት በማስጀመርና በማስፋፋት ነበር። በዚህ ሁኔታ የጀመረውን ስራ እያስፋፋም በርካታ ሰዎችን ለቁም ነገር ለማድረስ በቅቷል። ከእነዚህም መካከል በኪነ ጥበብ ዘርፍ «ስፖርት ለጤንነት ለምርት ተወዳጅነት…» ዘፈንን ያዘጋጁት አቶ ተስፋዩ ገብሬ፤ አርቲስት ፍቃዱ ተክለማርያም ሎሬት ጸጋዬ ገብረ መድህንን ሌሎችንም በስሩ ባሉ ፕሮግራሞች ያሳትፍ ነበር። በዚህ ሁኔታ ለሃያ አራት ዓመታት ያህል ከቆየ በኋላ በ1967 ለውጡን ተከትሎ ተቋሙ እንዲዘጋ ተደርጎ ቆይቶ በ1984 ዓ.ም በድጋሚ ስራውን ለመጀመር በቅቷል።
በአሁኑ ወቅት በአማራ በኦሮሚያ በደቡብና በትግራይ በአስር የዞን አስተዳደሮች ስር ባሉት ቅርንጫፎች እየሰራ ይገኛል። በስሩም ከሰላሳ ሺ በላይ አባላትን በተለያየ መልኩ የያዘ ሲሆን ከነዚህም መካከል ሶስት ሺ አምስት መቶ የሚደርሱት በቋሚነት ዓመታዊ ክፍያቸውን እየከፈሉ እየተሳተፉ ያሉ ናቸው። ማህበሩ ከግማሽ ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎችን ተደራሽ የሚያደርጉ አራት ፕሮግራሞችን እየተገበረ ሲሆን ከ2012 እስከ 2017 ዓ.ም በርካታ ወጣቶች ሁለንተናዊ አድገት እንዲያስመዘግቡ እየሰራ ይገኛል።
ማህበሩ እየተገበራቸው ካሉ ፕሮግራሞች የመጀመሪያው የወጣቶችን ተጠቃሚነትን ለማረጋጋጥ ተሳትፏቸውን ለማዳበር የህይወት ክህሎታቸውን ሙሉ በሆነ መንገድ በሥነ ምግባር በመገንባት ለሃላፊነት እንዲበቁ ማስቻል ነው። በአሁኑ ወቅት ያለው ከኢትዮጵያ ህዝብ ብዛት ከሰባ በመቶ በላይ እድሜያቸው ከሰላሳ ዓመት በታች የሆኑ ናቸው። እነዚህ የሀገር ተረካቢዎች ነገ አድገው ሀገራቸውን ቤተሰባቸውንና አካባቢያቸውን እንዲንከባከቡ ለማብቃት ከስር ሲያድጉ ጀምሮ መሰራት ያለባቸው በርካታ ስራዎች አሉ።
በተለይ ሀገር መውደድ ምንድን ነው ሃላፊነት መውሰድስ ምን ማለት ነው የሚሉትንና ሌሎችንም በሚገባ ሊረዱና ሊገነዘቡ ይገባል። ለዚህም የሀገር ውስጥ ተሞክሮን ብቻ ሳይሆን የሌሎች ሀገራትና ህዝብን ተሞክሮ መሰረት በማድረግ ካሪኩለም ተዘጋጅቶ ከችግር ወደ መፍትሄ በሚል ፕሮግራም እየተተገበረ ይገኛል። ይህ ፕሮግራም በመላው አፍሪካ የወወክማ ቅርንጫፎች እየተተገበረ የሚገኝ ነው።
ከወጣትነት ጋር በተያያዘ የባህሪ ችግር፤ ስራ አጥነት፤ ስደተኝነትና የመሳሰሉት ጉዳዮች ይነሳሉ። በአንጻሩ ወጣቶች ሀገር የሚረከቡም ናቸው። ሀገር መምራትና ሃላፊነት መቀበል የሚችሉም መሆናቸውን ለራሳቸው ግንዛቤ ለማስጨበት ማህበሩ አስራ ሁለት የህይወት ክህሎቶች እንዲጨብጡ እያደረገ ይገኛል። ከእነዚህም ዋናው እየተሰራበት ያለው በጎ ፈቃደኝነት አገልግሎት ነው። የበጎ ፈቃደኝነት አገልግሎት በሀገሪቱ ተፈጥሯዊና ሰው ሰራሽ ችግሮች ሲከሰቱ በርካታ ወገኖች ለችግር ይጋለጣሉ። በዚህ ወቅት ወጣቶች ማህበረሰቡ ውስጥ በመግባት ድጋፍ ያሰባስባሉ ለተጎጂዎች ያደርሳሉ። ወጣቶች የሰላም ባለቤት የችግር መፍትሄ አመላካች እንዲሆኑም በየአካባቢያቸው የማሳተፍ ስራ እየተሰራ ይገኛል።
በሌላ በኩል ማህበራዊ ሚዲያው በዓለም ላይ ከፍተኛ ተጽእኖ እያሳደረ እንደሚገኝ ይታወቃል። በመሆኑም ስልካቸውንና ሌሎች ቴክኖሎጂዎችን ሲጠቀሙ ህዝብን በሚጠቅም ወገንን በማያጋጭ፤ በማያጣላና በማያራርቅ እንዲሆን በሚዲያ አጠቃቀም የላቁ ወጣቶችን ማፍራት የሚል ፕሮግራምም ቀርጾ እየሰራ ይገኛል። ይህን ሃሳብ የሰላም ሚኒስትር በሀገር አቀፍ የበጎ ፈቃደኞች አገልግሎት ላይ አንዱ ካሪኩለም አድርጎ እንዲጠቀምበት እየተሰራ ሲሆን ከሌሎች አጋሮች ጋር በመሆን እስካሁንም አስር ሺ የሚደርሱ ሰዎች እንዲሰለጥኑ ተደርጓል።
ሌላው ፕሮግራም የኢኮኖሚ ኢምፓወርመንት ነው። ወጣቶች አምራች ዜጋ መሆን መቻል አለባቸው። በአሁኑ ወቅት በየዓመቱ ከሁለት ሚሊዮን በላይ ወጣቶች እድሜያቸው ለስራ ደርሶ ወደ አዲስ ስራ ይገባሉ ተብሎ ይገመታል። ከግማሽ ሚሊዮን በላይ የሚሆኑት በተለያዩ የትምህርት መስኮች ትምህርታቸውን ተከታትለው የሚመረቁና ስራ የሚፈልጉ ናቸው። ቀሪዎቹ መደበኛ ባልሆነው የስራ መስክ የሚሳተፉ ናቸው። እነዚህን ወጣቶች በአግባቡ መጠቀም ከተቻለ የልማት ሀብት ማድረግ ይቻላል። በመሆኑም ወወክማ በዚህ ረገድ አራት ፕሮግራሞችን በመቅረጽ እየሰራ ይገኛል።
ከእነዚህም አንደኛው በቴክኒካልና ቮኬሽናል ፕሮግራም ከአንድ ሺ ሁለት መቶ በላይ ተማሪዎችን አስተምሮ ያስመርቃል። ከእነዚህ ውስጥ አብዛኞቹ አዲስ አበባ ላይ የሚገኙ ሲሆን የሜታል፤ የአልሙኒየም ማሰልጠኛ የምግብ የኮምፒዩተር ግራፊክስ የልብስ ስፌትና የመሳሰሉትን ከገበያና ቢዝነስና እንዲሁም የህይወት ክህሎት ጋር በማጣመር ስልጠናዎች እየሰጠ ይገኛል። ይህም ወጣቶች በሀገራቸው ስራ ፈጣሪ ሆነው ስደትን ከመመኘት ተቆጥበው ራሳቸውን ቤተሰባቸውንና ማህበረሰቡን ብሎም ሀገራቸውን እየጠቀሙ እንዲኖሩ ለማስቻል ነው። እነዚህኑ ሰልጣኞች ከሌሎች አጋሮች ጋር በመሆን በሌሎች ፕሮግራሞችም ስራ ለመጀመር የመነሻ ካፒታል ማግኘት የሚችሉበትን ሁኔታ እንዲመቻች ማህበሩ የሚሰራቸው ስራዎች አሉ።
ሁለተኛው ደግሞ ስማርት አፕ የሚባል ከሌላ ዓለም አቀፍ ድርጅት ጋር በጋራ የሚሰራው ፕሮግራም ነው። ፕሮግራሙ ላለፉት አራት ዓመታት ሲሰራበት የነበረም ነው። በዲጅታል በቴክኖሎጂ በመጠቀም ከጥቃቅን እስከ ከፍተኛ ስራ የመፍጠር እንቅስቃሴ ነው። ለዚህም ወጣቶች እንዴት ቴክኖሎጂን መጠቀም እንዳለባቸው አዲስ አበባ መርካቶ አብነት አካባቢ ባለው የማህበሩ ቅርንጫፍ በስፋት እየተሰራ ይገኛል። በውስጡም የቴክኖሎጂ፤ የአመራር፤ የቋንቋ የስራ ፈጠራ የገበያ ትስስር ስልጠናዎችን በከፍተኛ ልምድ ባላቸው ባለሙያዎች እየሰጠ ይገኛል። ፕሮግራሙ እድሜያቸው ከአስራ ሰባት እስከ ሃያ ስድስት ያሉ በተለይ ትምህርታቸውን ያቋረጡና አዲስ ተመራቂ የሆኑ አካል ጉዳተኞችንም የሚያካትት ነው። አራተኛ ዓመቱን የያዘ ሲሆን በሌላ ተጨማሪ ፕሮግራም ለሚቀጥሉት አምስት ዓመታት ለመቀጠልም ዝግጅት እየተደረገ ይገኛል።
ከዚሁ ጋር በተያያዘ ሌላው አጫጭር የቢዝነስ ስልጠናዎችን ኢመደበኛ የስራ እንቅስቀሴ ውስጥ ያሉት ላይ በማተኮር እየሰጠ ይገኛል። በሀገሪቱ ያለው የቢዝነስ እንቅስቃሴ ከስልሳ እስከ ሰባ በመቶ የሚሆነው ኢመደበኛ ነው። በዚህ መስክ የተሰማሩትን ወጣቶች በስልጠናና በልምድ ብሎም በቁሳቁስ በመደገፍና በማሟላት ማብቃት ሲሆን እየተተገበረ ያለውም በአራዳ ክፍለ ከተማ ሶስት ወረዳዎች ወረዳ ስድስት፤ ሰባትና አስር ላይ ነው። በተጨማሪ ለወጣቶች ከሚያደርገውም ድጋፍ በዘለለ አቅመ ደካማ እናቶችን በራስ አገዝ በማደራጀት ቁጥባ አስቀምጠው ራሳቸው እንዲበደሩ ስሞል ማይክሮ ፋይናንስ በሟቋቋም እየሰራ ይገኛል።
በሶስተኛ ደረጃ ማህበሩ ተደራሽ እያደረገ ያለው የጤና ፕሮግራም ነው። የጤና ፕሮግራም በዋናነት ከወጣቶች የሥነ ተዋልዶ ጤና ጋር የሚያያዝ ሲሆን በሁሉም ቅርንጫፎች እየተተገበረ የሚገኝ ነው። ይህም በህይወት ክህሎት ላይ ትኩረት በማድረግ ወጣቶች ሊያጋጥማቸው ከሚችለው የሥነ ተዋልዶ ሳንካ ያልተፈተለገ እርግዝና ውርጃ ኤች አችአይቪና የመሳሰሉት የሚያስከትሏቸውን ችግሮች መታደግ ነው። እነዚህ ችግሮች ከተከሰቱ በአብዛኛው የወጣቶቹ ህይወት የተመሰቃቀለ ይሆናል። በመሆኑም ይህ ነገር እንዳይከሰት ማህበሩ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎችን የሚሰራ ይሆናል። በተጨማሪ በዚህ ዓመት ደግሞ ከአእምሮ ህመም ጋር በተያያዘ መነሻዎቹን በመለየት ህክምና መስጠት ሳይሆን መነሻ ጉዳዮቹን ለማስቀረት መስራት ጀምሯል።
በዚህ ፕሮግራምም ምንም እንኳን ዋናው ዓላማ መከላከል ላይ ቢሆንም በችግሩ የተጠቃ ከተገኘ ህክምና እንዲያገኝ ሁኔታዎች የሚመቻቹለት ይሆናል። ከዚው ውስጥ በቀዳሚነት ወጣቶች ወደ ሱስ እንዳይገቡየመከላከል እንቅስቃሴ አንዱ ነው። ለዚህም አንደኛው መንገድ በግለሰብ ደረጃ ስፖርት እንዲያዘወትሩ የህይወት ክህሎት ስልጠና መስጠትና ሁኔታዎችን ማመቻቸት ሲሆን በሌላ በኩል በማህበረሰቡም ዘንድ የግንዛቤ ፈጠራ ስራ እየተሰራ ይገኛል። ከዚህ ውስጥ በተለይ በተዘጋጁ የስፖርት ማዘውተሪያዎች በአዲስ አበባ አዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ፤ ባህር ዳር ደብረ ማርቆስ ወላይታ ላይ በስፋት የማስ ስፖርት ዳርት ጠረጴዛ ቴኒስ ባስኬት ቦል ቦክስና ሰርከስ የመሳሰሉትን እንስቃሴዎች እንዲያዘወትሩ እየተደረገ ይገኛል። ይህ በወጣቶች ላይ ብቻ ሳይሆን እድሜያቸው እስከ ስልሳና ስልሳ አምስት ዓመት የሆናቸውንም በስፋት የሚያካትት ነው።
የማህበሩ አራተኛ ፕሮግራም ማህበረሰቡ ችግር ሲገጥመው ያለውን የመቋቋም አቅም ማዳበርና ችግር ሲከሰት ሊሰጥ የሚችለውን የሚገባውን ምላሽ ተገቢ እንዲሆን ማስቻል ነው። አንዳንድ ችግሮች ሳይጠበቁ በድንገት የሚከሰቱ ናቸው። ከእነዚህም መካከል እንደ ጎርፍ ድርቅ የመሳሰሉትን ማንሳት ይቻላል።
እ.አ.አ በ2016 በአማራና ትግራይ ክልሎች ከፍተኛ ድርቅ ተከስቶ ነበር፡፡ የአምበጣ መንጋ ያደረሰው ጉዳትና በአሁኑ ወቅት ያለው ኮሮና ተጠቃሽ ናቸው። በዚህ ረገድ ወወክማ ከሚመለከታቸው ጋር በመሆን በርካታ ድጋፎችን ሲያደርግ ቆይቷል። በተለይ በተለያዩ ግጭቶች የተፈናቀሉ ዜጎችንም ላለፉት ሁለት ዓመታት በተለያያ መልኩ ሲደግፍ ቆይቷል። በአሁኑ ወቅትም በወሎ በደረሰው ችግር በደብረ ማርቆስና ባህር ዳር ቅርንጫፎች በኩል አንድ መቶ ሰማንያ ሰባት ለሚደርሱ ሰዎች የቤት ውስጥ ቁሳቁስ አርባ አምስት ለሚደርሱት ደግሞ የምግብ ድጋፍ አድርጓል።
በትግራይም መንግስት የተናጥል ተኩስ አቁም ከማድረጉና ከመውጣቱ በፊት ከተለያዩ ቦታዎች የተሰባሰበ ከአንድ ነጥብ ሁለት ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት የቁሳቁስ ድጋፍ አድርጓል። በኮቪድ ወረርሽኝ ወቅትም ወወክማ በርካታ ስራዎችን ሲሰራ የነበረ ሲሆን ከእነዚህም ውስጥ አንደኛ የተቋቋመውን ግብረ ሃይል በመደገፍ በምግብ ማሰባሰብ በህብረተሰብ የማንቃትና ስርጭቱን የመከላከል ስራዎች ተጠቃሽ ናቸው።
ባጠቃላይ ማህበሩ ዜጎች በተለይ ወጣቱ የአእምሮ የመንፈስና የአካል ብቃት እንዲኖረው ሁለገብ ድጋፍ እየሰጠ ይገኛል። አካሄዱም በዋናነት ችግሮች እንዳይከሰቱ በመከላከል ላይ ትኩረት በማድረግ ሲሆን ችግሮች ሲደርሱ ደግሞ ጣልቃ በመግባትና ድጋፍ በማድረግ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት የሚንቀሳቀስ ማህበር ነው።
ይህም ሆኖ ማህበሩ ባባለፉት ሶስስት አስር ዓመታት የተለያዩ ተግዳሮቶችንም ሲያስተናግድ ነበር። ከእነዚህም መካከል ቀዳሚው የሚተገብራቸውን ፕሮግራሞች ወደ መሬት ለማውረድ የገጠመው የቦታ ችግር አንዱ ነው። ወወክማ ከሌሎች አንጻር ሲታይ በተሻለ ሁኔታ ላይ የሚገኝ ቢሆንም ሊሳካ ከሚፈልገው አንጻር ግን ብዙ ይቀረዋል።
በአሁኑ ወቅት የወጣቶች የስራ ዝግጁነት ማእከል ለመገንባት እቅድ አለው። ለዚህም የስራ ማስታወቂያ መለጠፊያዎች በተለያዩ ቦታዎች እንዲሆኑ ለማንበብ እንዲመቻቸው እንዲሁም የኢንተርኔት አገልግሎት እንዲያገኙ ለመስራት እቅድ የያዘ ቢሆንም የገጠመው የቦታ ችግር እንዳይንቀሳቀስ አድርጎታል።
በተጨማሪ የጀመራቸውን ፕሮግራሞችን አጠናክሮ ለመቀጠል የዲጅታል ቴክኖሎጂና ስራ ፈጠራ ከስራ ዝግጁነት ጋር አጣምሮ ለወጣቶች ተደራሽ ለማድረግ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል። ለዚህም አንድ ማእከል ለማዘጋጀት እቅድ የያዘ ሲሆን በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት ከግማሽ ሚሊዮን በላይ ዜጎችን ተጠቃሚ ለማድረግ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል። በዚህም በመንግስት ጫንቃ ላይ ብቻ የተጫነውን የስራ ፈጠራ ሸክም ከሌሎች አጋሮች ጋር በመሆን የማቅለል ራእይ አለው።
በተጨማሪ በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት ማህበሩ ከውጭ ጥገኝነት በመላቀቅ በገቢ ራሱን ለመቻል የሚሰራቸው ስራዎችም አሉት። በዚህም በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ባለው ሰባት መቶ ሃምሳ ካሬ ሜትር ቦታ ላይ ባለ አራት ወለል ህንጻ ለመስራት እቅድ ይዟል።
ህንጻው ተገንብቶ አገልግሎት መስጠት ሲጀምር ከገቢ ማስገኛነቱ ባሻገር ለወጣቶች መዋያ ቤተመጻህፍትና የመሳሰሉትም የሚኖሩት ነው። በተጨማሪ እስካሁን ተደራሽ ባልሆነባቸው የሀገሪቱ ክፍሎች ማለትም ቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ ጋምቤላ፣ በሀረርና ድሬዳዋ ቅርንጫፍ ለመክፈት የሚሰራም መሆኑንም ዋና ዳይሬክተሩ ጠቁመዋል።
ራስወርቅ ሙሉጌታ
አዲስ ዘመን መስከረም 21/2014