ወጣት ተስፋ አለባቸው ይባለል ተወልዶ ያደገው በሀረር ከተማ ነው፤ ሀረር የሀገር ልጅ በጎ አድራጎት ማህበር መስራችና ሊቀመንበርም ነው። ተስፋ ወላጅ አባቱን የማያውቀው ሲሆን እናቱንም በሞት የተነጠቀው ገና የሰባት ዓመት ታዳጊ ልጅ እያለ ነበር። በዚህም የተነሳ የልጅነት ጊዜው ለእሱ አስደሳች ትዝታ ያሳለፈበት አልነበረም። በእነዚህ ጊዜያትም በርካታ አስቸጋሪ ህይወቶችን ለማሳለፍ ተገዷል።
ገና በለጋ እድሜው ውሃ እየቀዳ ቆሻሻ እየተሸከመና የመላላክ ስራዎችን እየሰራ ነበር በጨዋታ ሊያሳልፈው የሚገባውን የልጅነት ጊዜውን ካለ አቅሙ፣ ካለ አድሜው በስራ ለማሳለፍ የተገደደው። ይህም ሆኖ ትምህርቱን እንዳያቋርጥ በርካታ የአካባቢው ነዋሪዎች የተለያዩ ድጋፎችን ያደርጉለት ነበር። አቦከር አንደኛ ደረጃ ትምህርት በሚማርበት ጊዜም በትምህርት ቤቱ የነበረው የበጎ አድራጎት ክበብ ተማሪዎች ከሚሰጡት አንድ ብርና ሁለት ብር እየተሰበሰበ ደብተርና ዩኒፎርም እያሟላለት ትምህርቱን እንዲከታተል ሲያደርገው ቆይቷል።
በዚህ ሁኔታ ያደገው ተስፋ ከፍ እያለ ሲመጣና ነገሮችን በተለያየ አቅጣጫ መመልከት ሲጀምር እናት አባቱን አጥቶ ብቻውን በነበረበት ወቅት ተንከባክቦ ላሳደገው ማህበረሰብ ለውለታው ምላሽ አንድ ነገር ማድረግ እንዳለበት ይወስናል። እናም ወዲያው በአእምሮው የመጣለት እሱም በተራው በአቅሙ ለችግር የተጋለጡን የመርዳትና የመንከባከብ ስራ መስራት ነበር። እናም ውሎ ሳያድር በጎዳና ላይ የሚኖሩ እናትም አባትም የሌላቸው እንዲሁም የኔ የሚሉት የሚያስጠጋ ዘመድም ሆነ ወዳጅ የሌላቸውን ህጻናትን ሰብስቦ ለማሳደግ ይወስንና ወደ ተግባር ይሸጋገራል።
በወቅቱ ግን ይህን ሃሳቡን በተግባርም ሆነ በሃሳብ በቋሚነት የሚደግፈው አንድም አካል አልነበረም። በራሱም በኩል ቢሆን ተቀንሶ ለሰው የሚቸር ሀብትም አልነበረውም። ነገር ግን ይህንን ነገር ደፍሬ ከጀመርኩት ትናንት አቅፎ ያሳደገኝ ማህበረሰብ ዝም አይለኝም ይተባበረኛል አያሳፍረኝም በሚል እሳቤ ብቻ ነበር።
እናም በ2008 ዓ.ም አርባ ህጻናትን ከጎዳና በመያዝ በሀረር ከተማ ዳርቻ ቤት በመከራየት ረጅሙን የተቸገሩትን የመጎብኘትና የአለሁ ባይነት ጉዞ ይጀምራል። ነገር ግን ማህበሩን በ2008 ዓ.ም ጥቅምት ሃያ አንድ ቀን ነበር በይፋ በህጋዊ መንገድ ከመመስረቱም በፊት በበጎ ፈቃደኝነት ይሰራ ነበር። እናም እነዚህን አርባ ህጻናት ጠዋት ጠዋት ከሰው በሚለምነው ቁርሳቸውን አብልቶ ትምህርት ቤት የሚልካቸው ሲሆን ቀን ከትምህርት ቤት ሲመለሱ ደግሞ ከየሆቴሉ የተራረፈ ምግብ በባሊ በመሰብሰብ እንዲመገቡ ያደርጋል።
የቀረውን ጊዜ ልጆቹ በየከተማው በመሽከርከር የመሰላቸውን የራሳቸውን ህይወት ይመሩበት ነበር። ማስቲሽ የሚስበው ይስባል፤ የሚጠጣው ይጠጣል፤ የሚያጨሰው የሚቅመው ብቻ ሁሉም የመሰለውን ሲያደርግ ይውላል። ተስፋ ነገን በተስፋ ስላስቅመጣት የመጀመሪያ ዓላማው ልጆቹ በትምህርት ገበታ ላይ እንዲገኙ ማድረግ ብቻ ነበር።
ከስራው በተጓዳኝም እያደረገ ያለውን ነገር ለህብረተሰቡ ማሳየቱን ማስተዋወቁን ቀጠለበት። ይህም ሆኖ በርካታ ሰዎች እጃቸውን ለመዘርጋት ፈቃደኝነቱ ቢኖራቸውም የቀጣይነቱ ጉዳይ አልዋጥ ስላላቸው ለመደገፍ ፈቃደኛ አልነበሩም። እሱም ያገኘውን እያቃመሰ በዓላማው በመጽናት አርባውንም ልጆች አንዱን ዓመት ትምህርታቸውን ተምረው እንዲጨርሱ ያደርጋቸዋል።
በዚህ ሁኔታ ውስጥ እያለ እንቅስቃሴውን የተመለከተው የሀረሪ ክልል ሴቶችና ህጻናት ቢሮ በመስከረም ወር 2009 ዓ.ም አርባ ፍራሽ፤ አርባ አንሶላ፤ አርባ ትራስ እና አርባ ብርድ ልብስ ይለግሰዋል። ተስፋም በፍጥነት በከተማ ዳርቻ ሁለት ክፍል ቤት በመከራየት በአንዱ አስራ ስምንት በአንዱ ሀያ ሁለት ልጆችን በመያዝ ማኖር ይጀምራል። ይህ ቤት በቂ ባይሆንም ከጎዳና ስለሚሻልና ልጆቹ የትምህርት ቁሳቁሶቻቸውን ለማስቀመጫ ቦታ ስለሚያገኙበትም በወቅቱ ትልቅ እፎይታን የፈጠረ ነበር።
በዚህን ጊዜ ስራውን የተመለከቱና ነገሩ የወረት አለመሆኑን የተገነዘቡ አንዳንድ በከተማዋ ያሉ በጎ አድራጊዎች አለሁ ማለት ይጀምራሉ። በዚህም የተለያዩ ድጋፎችን ሲያደርጉለት ወደ ከተማ በመምጣት ራስ መኮንን ትምህርት ቤት አካባቢ ቀበሌ አስር አንድ ሰፊ ጊቢ ለመከራየት ይበቃል። ለመጀመሪያ ጊዜም ለልጆቹ በቂ መጠለያ በማግኘቱ ተስፋ ትልቅ እፎይታ ይሰማው ይጀምራል።
የመጠለያው ችግር በዚህ አይነት ቢቀረፍም ሌሎቹ ጉዳዮች ግን አልተነኩም ነበር። በመሆኑም ለልጆቹ የሚሆኑ አልባሳትን ከትምህርት ቤቶች ከሃይማኖት ተቋማት እየሰበሰበ ያሟላላቸው ይጀምራል። ለምግባቸውም በከተማዋ ያሉ ሆቴሎችን እየዞረ በማነጋገር በርካታ ሆቴሎች እንደ አቅማቸው አንዳንዱ ለአንድና ለሁለት፤ አንዳንዱ ደግሞ ለአራትና አምስት ልጆች ምግብ ለማቅረብ በመስማማታቸው የምግቡንም ጉዳይ በዚህ አይነት መልኩ ለመፍታት ይበቃል። በጥቂት ጊዜ ወስጥም ለአርባዎቹም ልጆች ምሳና እራታቸውን ማሟላት ተቻለ።
ይህ የሆነው አዲሱ ቤት በገቡ በሰባተኛው ወር ሲሆን እስከዛ ድረስ ተስፋ ልጆቹን ይቀልብ የነበረው እቤት እየኖሩ ከየሆቴሉ የተራረፈ ምግብ በባሊ እየሰበሰበ በማቅረብ ነበር። ህብረተሰቡ በስፋት መደገፍ እስኪጀምር ድረስም ለአንድ ዓመት ከስድስት ወር በሙሉ አራትና አምስት ብር እየለቀመ ነበር ልጆቹን ሲንከባከብና ሲያስተምር የነበረው።
በዚህ ሁኔታ እያለ የሚሰራው ስራ በብዙ ሰዎች ዘንድ በመዳረሱ የድጋፍ አድራጊውም ቁጥር እየጨመረ ይመጣል። ዝናውን ከሰሙት መካከል ከአሜሪካ የቪ.ኦ.ኤ ጋዜጠኛ የሆነችው ጽዮን አስተባብራለትም ከውጭ የሚደረግለት ድጋፍ እንዲጨምር ታስደርግለታለች። በዚህ አይነት ሁኔታዎች እየተሻሻሉ ሲመጡ የተስፋም ፍላጎት እየጨመረ በመምጣቱ ሌሎች ልጆችንም መሰብሰቡን ቀጠለበት። እናም በአሁኑ ወቅት ያሉትን ዘጠና ልጆች ለመያዝ በቃ። እነዚህ ልጆች በሙሉ ተማሪዎች ሲሆኑ ግማሾቹ በቤተሰብ ማጣት ትምህርታቸውን አቁመውየጎዳና ህይወትን የተቀላቀሉ ስለነበሩ ትምህርታቸውን ካቆሙበት እንዲቀጥሉ ያደርጋቸዋል።
በአሁኑ ወቅት ካሉት ልጆች መካከል በትምህርት ትንሽ የሚባሉት ዘንድሮ “ኬጂ አንድ” ለመግባት የተዘጋጁት ሲሆኑ ትልቋ ደግሞ የኤሌክትሪካል ኢንጂነሪንግ አራተኛ ዓመት ተማሪ የሆነችው ናት። ከእሷ በተጨማሪ ሶስት ልጆች በሀሮማያ ዩኒቨርሲቲ የሁለተኛ ዓመት የአካውንቲንግ ተማሪዎች ለመሆን በቅተዋል። ሌሎቹ አስራ ሁለተኛ ክፍል ተፈታኝ አስራ አንደኛ ክፍልና በሌሎች የክፍል ደረጃዎችም እየተማሩ ያሉ ናቸው።
ይህም ሆኑ ህብረተሰቡ ግን ድጋፉንም እያደረገ ቢሆን በአንድ ወገን ስራው የሚዘልቅ ስለማይመስላቸው በሌላ በኩል ልጆቹ ሱሰኛ ስለሆኑ አይለወጡም በሚል እሳቤ ስጋታቸውን ይገልጹ ነበር። በሌላ በኩል ደግሞ ራሳቸው ልጆቹ ደግሞ የሚፈልጉት ነገርም ነበር። ከጎዳና ሲነሱ ወደ ቤት እናስገባቸው ከቤተሰብ ይቀላቀሉ አልያም በአንድ ቤት ይሰባሰቡ ሲባል የለመዱት ነጻነት ስለሚነካባቸው አይመቻቸውም ነበር። ስለዚህም ተስፋ በቅድሚያ የእያንዳንዱን ልጅ ወደ ጎዳና የወጣበትን ምክንያት በማጥናትና ምን እንደሚያስፈልገው በመለየት የእነሱን ትእዛዝ በመቀበልና መሰረት በማድረግ እንክብካቤውን ይቀጥላል። ህብረተሰቡንም ያለውን ሁኔታ በበጎ ጎኑ እንዲረዱት እያደረገ ይቀጥላል።
ለዚህም በልጆቹ በኩል እንደ አማራጭ መንገድ የተጠቀመው ስፖርት ማሰራትን ነበር። ዛሬ ከሱስ ለማስወጣት በሚል አንዳንዶቹን ያስጀመራቸው ስፖርት ከሱስ ለመላቀቅ ብቻ ሳይሆን እንጀራም ሊሆናቸው በቅቷል። አንደኛው ልጁ በእግር ኳስ የሀረር ከተማ ስፖርት ክለብ ተጫዋች ሆኖ ላለፉት ሶስት ዓመታት እየሰራ ይገኛል። ሌላው በኢትዮጵያ ወጣቶች አካዳሚ ለእግር ኳስ ተመርጦ በመጫወት ላይ ይገኛል። ሌላው ደግሞ ዘንድሮ ከአስራ ሰባት ዓመት በታች ለኢትዮጵያ ታዳጊ ወጣቶች ብሄራዊ ቡድን ለመመረጥ በቅቷል።
ልጆቹ በትምህርታቸውም ጎበዞች ሲሆኑ በዘንድሮው ዓመት ዝቅተኛ ውጤት አመጣ የተባለው ልጅ ከክፍል ሰባተኛ የወጣ ነው። ከዚህ ውጪ አርባ ዘጠኙ ልጆች በደረጃ ከአንድ አስከ ሶስት የወጡ ናቸው። ሁሉም የሚማሩት በመንግስት ትምህርት ቤት ነው። ይህም ሆኖ በየወሩ ባይከፈልም የምዝገባ ክፍያ አለ። ለዚህም በራስ መኮንን አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እንዲሁም በኦሮምኛ አፍ መፍቻ የሚያስተምር አንደኛ ሞዴል የሚባል ትምህርት ቤት ለሚማሩት ትምህርት ቤቶቹ ሙሉ ድጋፍ እያደረጉለት ይገኛል። በእነዚህ ትምህርት ቤቶች ምዝገባው በነጻ ነው። ለተማሪዎች የትምህርት መሳሪያዎች ድጋፍ ይደረጋል ልጆቹንም በልዩ ትኩረትና ክትትል ይንከባከቧቸዋል። ወደ ሁለተኛ ደረጃ ሲገቡ ግን እንደማንኛውም ተማሪ ተስፋ የሚሸፍንላቸው ይሆናል።
በአሁኑ ወቅት ተስፋ ለተከራየው ቤት በወር አስራ አምስት ሺህ ብር ኪራይ እየከፈለ ይገኛል። በዚህ ዓመት የክልሉ ፕሬዚዳንት መጥተው ልጆቹን ጎብኝተው ስለነበር የአንድ ዓመት የቤት ኪራይ ክፍያ እንደሚችሉት ቃል ገብተውለታል። የሀረር ራስ ሆቴል ባለቤት የሆኑት አቶ ደበበ ደግሞ ከመጋቢት 2013 ዓ.ም. ጀምሮ ለልጆቹ ቁርሳቸውን ድርጅቱ እስካለ ለማብላት ቃል ገብተውለት እየደገፉት ይገኛል። አቶ ደበበ ከዚህም ባለፈ ለዘመን መለወጫ በዓል ድግስ በማዘጋጀት በትምህርታቸው በሃይማኖትና በስነ ምግባር የተሻለ ለሆኑት ልጆችም ሽልማት ይሰጣሉ። ለእስልምና በዓላትም በረመዳን ተመሳሳይ ነገሮችን ያደርጋሉ።
ይህም ሆኖ ተስፋ የራሱን መኖሪያ ለልጆቹ እስኪቀልስ ድረስ እረፍት የለውም። ሁሌም ቢሆን ምላሽ ባያገኝበትም ከመንግስት የሚጠይቀው የመኖሪያ ቤት ጉዳይ ነው። ተስፋ አሁንም ቢሆን ከሀረር ጎዳናዎች አንስቶ ልጆች ለመጨመር ሃሳብ አለው። በከተማው ካሉ ክሊኒኮች ስምንቱ አባልና የነጻ ህክምና አገልግሎት ይሰጣሉ። የቆዳ የጥርስ የውስጥ ደዌ የህጻን ስፔሻሊስቶች አሉ። የመንግስት ሆስፒታሎችም ተባባሪ ናቸው። ጸጉር ቤቶች በነጻ የልጆቹን ጸጉር ያስተካክሉለታል።
ተስፋ ሌላው እድለኛ ነኝ የሚያሰኘው የሚያሳድጋቸው ልጆች ትብብርና መፋቀር ነው። በጊቢው ውስጥ የሚቀጠር ሰራተኛ የለም ታላላቅ ልጆች አንዳንድ ልጅ በሃላፊነት በመውሰድ በየደረጃው ይንከባከባሉ። ልብስ ያጥባሉ፣ ያስጠናሉ ወዘተ። በጊቢው ሶስት ሃይማኖቶች አሉ የተለያዩ ብሄር ብሄረሰቦችም ይገኙበታል። ልጆች ተጥለው ሲገኙ የእናቱን ሃይማኖት በመጠየቅና መረጃ በማሰባሰብ የቤተሰባቸውን ሃይማኖት እንዲከተሉ ይደረጋል። በጊቢው ሃይማኖት አልባ መሆን ብቻ ነው የማይፈቀደው።
የአካባቢው ሰውም በመጀመሪያ ሰሞን ስጋት የነበረበት ቢሆንም አሁን ግን ልጆቹን እንደራሱ ልጆች ማየት ማቅረብ በመጀመሩ ልጆቹም ለህብረተሰቡ ያላቸው ፍቅር እየጨመረ መጥቷል። ልጆቹ ተስፋን “አባ” የሚሉት ሲሆን ባለቤቱን ዶክተር ቃልኪዳን እያሱን ደግሞ “እማ” ይሏታል። በጊቢው ያለው ሰው በሙሉ እንደ አንድ ቤተሰብ የሚተያይ ነው። ተስፋ ልጆቹን በጥሩ ኢትዮጵያዊነት እንዲያድጉ የሚያደርግ ሲሆን ባለቤቱ የሃሳቡ ደጋፊ በመሆኗ በየቀኑ ስራ ከመሄዷ በፊት ልጆቹን ትጎበኛለች።
በአንድ ወቅት ከተማ ውስጥ ረብሻ ሲፈጠር መንገድ በመዘጋቱ ሆቴሎች ስራ ሲያቆሙ ትልቅ ችግር ገጥሞት ነበር። በዛ ወቅት የሀረማያ ዩኒቨርሲቲ ህክምና ሳይንስ ኮሌጅ ፕሬዚዳንት ዶክተር ያደታ በተደጋጋሚ እንጀራና ወጥ በማቅረብ ያንን ክፉ ቀን እንዲያውል አድርገውታል። ያን እድል ባያገኝ ኖሮ በርካታ ከአምስት ዓመት በታች የሆኑ ህጻናት ለከፋ ችግር የመጋለጣቸው ጉዳይ ሳይታለም የተፈታ ነው።
ተስፋ ለቀጣይም በገቢ ማስገኛ ስራዎች ላይ ለመሳተፍ እቅድ አለው። ለዚህ ደግሞ የቦታ አቅርቦት ያስፈልጋል። በመሆኑም የክልሉ መስተዳድር የመኖሪያ ቤት ባይገኝ እንኳን ለስራ የሚሆን ኮንቴኔር ቢሰጠኝ አትክልት የማቅረብ ስራ የመስራት እቅድ አለኝ ይላል። ባጠቃለይም ሌላም ሃሳብ ያለው ሰው የደረሱትን ልጆች ስራ በመፍጠር ቢተባበርለትና ማህበሩን ራሱን እንዲችል እንዲደግፉት እንደሚሻም ይናገራል።
ራስወርቅ ሙሉጌታ
አዲስ ዘመን መስከረም 21/2014