እቁብተኞቹ ተረኛውን እድለኛ ለማወቅ ከሳምንታዊ መሰባሰቢያቸው ቦታ ላይ ተሰባስበዋል። የእቁብ ማህበራቸው ዓመታትን ያስቆጠረ ማህበር ነው። እለተ እሁድ በእቁብ ድባብ ልዩ ሆኖ የሚያልፍ ቀን ነው። ድምቀቱም የሚመነጨው “ተረኛው እቁብተኛ ማን ይሆን?” ከሚለው መጠበቅና ተረኛው ሲታወቅ በሚሆነው የደስታ ስሜት ነው። እቁቡን ለማግኘት ሲጠብቅ የነበረ ሰው የጠበቀውን በሚያጣበት ጊዜ የሚሰማው ሃዘንም የድባቡ አካል ነው።
እጣ በሚወጣባት ሰዓት ሁሉም ትኩረቱ ወደ እጣው ነው፤ ገንዘብ የወጣለትን ሰው ማንነት ለመመልከትና ደስታውን ለመጋራት። በትኩረት መከታተል።
በእለቱ የሚጣለው የእቁቡ ገንዘብ ይዞ መገኘት ያልቻለ ሰው ግን በቦታው አይገኝም። የሚጠበቅበትን ማድረግ ስላልቻለ የሚያደርገው መደበቅ። ይህ የገጠር ሳምንታዊ እቁብ ገጽታ ነው። በአብዛኛው ቅዳሜ ገበያን ተከትሎ በሚመጣው እሁድ ያለ ድባብ።
እጣ የማውጣት ሂደቱ ከተጠናቀቀ በኋላ ለመቀማመስና የውይይት አጀንዳ ከፍቶ አንድ ሁለት ለማለት የእቁብ መድረክ ይጠበቃል። አንድ ቀን እጣ ማውጣት ሂደቱ ተጠናቆ አጀንዳው ሲከፈት “ስለ እቁባችን እናውራ” ተባለና ውይይት ተጀመረ። በእቁብ ሂደቱ ላይ በሚያስደስትና በሚያሳዝን ክስተት ላይ የተደረገ ውይይት። አንዳንዱ ሃሳቡን በገጠመኝ እያዋዛ አቀረበ። ከቀረቡት ሃሳቦች መካከል በጊዜ እቁቡን በመክፈል የተመሰከረለት ባለ ምግብ ቤት እቁብተኛ ይገኛል።
ይህ ሰው እንዲህ አለ “እኔ እቁባችንን በጣም ነው የምወደው። የእቁብ ቀን ደርሶ የእቁብ ገንዘብ ይዤ ስመጣ የሚሰማኝ ደስታ ልነግራችሁ አልችልም። ደስታው ለሌላ ደስታ የሚያነሳሳኝ ነው። በትኩረትና በመሰጠት ሰርቼ ያገኘሁትን ይዤ መጥቼ ስሰራ ለሚቀጥለው ሳምንት እቁብ እንዲሁ በትኩረትና በመሰጠት እንድሰራ እራሴን አዘጋጅበታለሁ። ሁላችሁም እንደምታውቁት እኔ ምግብ ቤት ውስጥ ‘ሁለት ክንፍ’ ብዬ የለጠፍኩት አለ። እቁብ በመጣ ጊዜ ሁለቱ ክንፎች ትዝ ይሉኛል። ከሁለቱ ክንፍ አንዱ ክንፍ ከጎደለ ለሳምንታዊ እቁብ የሚሆን ገንዘብ ማግኘት አልችልም።”
የእቁቡ ዳኛ “ሁለቱ ክንፍ ምን ይሆን?” ሲል ጠየቀው፤ ባለ ምግብ ቤቱ ሲቀጠል “እነርሱማ ትኩረት እና መሰጠት ናቸው። ምግብ ቤቴ በትኩረት እያንዳንዱን ደንበኛ እየተከታተለ አገልግሎት መስጠት እንዳለበት ስለማምን ትኩረት አንዱ ክንፍ ነው። አይናችንን ከደንበኛችን ላይ ሳንነቅል በትኩረት እናገለግላቸዋለንና። በትኩረት ለማያቸው ደንበኞች የምሰጠው አገልግሎት ከመሰጠት ውስጥ የሚፈልቅ ነውና መሰጠት ሁለተኛው ክንፍ ነው። ለቁርስ ዝግጅት ሌሊት ጀምረን ካልሰራን ደንበኛችንን በአግባቡ ማገልገል አንችልም። ስለሆነም መሰጠት ግድ ይለናል። በአጭሩ ደንበኛው ቤቴን እረግጦ እስኪወጣ ድረስ አገለግለዋለሁ። በትኩረትና በመሰጠት፤ በውጤቱም እቁቤን በሚገባ እከፍላለሁ። ሁለቱ ክንፍ በአግባቡ እየሰራ መሆኑን በየሳምንቱ ወደ እቁብ ቤታችን ስንመጣም አስታውሳለሁ።” በማለት ንግግሩን አደረገ።
ሁሉም እቁብተኛ እንዲሁ ሀሳባቸውን ሲሰነዝሩ ቆይተው፤ ጨዋታው እየደራ፤ አንድ ሁለት ማለቱን ቀጠሉ። የዘውትር እሁዱ የገጠር እቁብ ገጽታ። በማህበራዊ ህይወት አብሮ መቆሚያ፤ ደግሞም ትምህርት መለዋወጫ መድረክ።
የመጀመሪያው ክንፍ – ትኩረት
የትላንት ውሏችንን መለስ ብለን እንመልከትና ትኩረታችን ምን ላይ እንደነበር እናስታውስ። ያለፈው አንድ ሳምንት እንቅስቃሴ ውስጥ ትኩረት ሰጥቼ የሰራሁት የምንላቸውን ተግባራት ለይተን ምን ላይ እንደሚያተኩሩ እንመርምራቸው። ከቻልን አንድ ወር እንዲሁም ዓመት ብለን ምርመራችንን እናድርግ። አዲስን ዓመት ስንቀበልና ስንሸኝ በትኩረት ልናከናወነው የምንፈልገውን ነገር መዘርዘራችን አይቀሬ ነውና።
ማሳካት የምንፈልገውን በትኩረት ለማሳካት የምናደርገው እንቅስቃሴ ወደ ውጤት የሚያደርሰን ነው ወይ ብለን መጠየቃችን አይቀሬ ነው። መቼስ ያለ ትኩረት ከተሰራው በትኩረት የተሰራው የተሻለ ውጤት እንደሚያመጣ ጥርጥር የለውምና።
ትኩረት የሚደረግበት ሥራ ወደ ውጤት ሊቀየር ካልቻለ ለምን ብለን እንጠይቅ። በትኩረት እንዲህ ማድረግ ፈልጌ ነበር ነገር ግን በተጨባጭ የሆነልኝ እንዳሰብኩት አይደለም ብለን እናስብም ይሆናል። በትኩረት መስራት የሚገባንን ለመለየት እንዲሁም እንዳቀድን ለመስራት ራሳችንን መመልከት ሁልጊዜ ተገቢነቱ ወደ ጎን የሚባል አይደለም። ግለሰባዊ ጥንካሬያችንን ማወቅና እዚያ ላይ ትኩረት ማድረግ የመፍትሄው መንገድ ነው።
ጆን ማእክስዌል የተባለ ጸሃፊ ትኩረት ልናደርግ የሚገባባቸውን አቅጣጫዎች “70%፡25%፡5%” በማለት ይገልጻቸዋል።
ጥንካሬ
ውጤታማ መሪዎች ወደ ውጤታማ ከፍታ መውጣታቸው ሲመረመር የተገኘው ውጤት ብዙዎች የበዛውን ጊዚያቸውን በጥንካሬያቸው ላይ የሚያተኩሩ ሆነው መገኘታቸው ነው።
የሥነ-አመራር መምህር የሆኑት ፒተር ድራከር እንዲህ ይላሉ “ታላቁ ተቃርኖ ሰዎች ነገሮችን በመጥፎ መንገድ መስራታቸው ሳይሆን አልፎ አልፎም ቢሆን በጥሩ ሁኔታ የሚሰሩበት አግባብ መኖሩ ነው። ብቃት ማነስ በሁሉም ቦታዎች ላይ የሚገኝ ነው። ጥንካሬ በግልጽነት መለየትና መታወቅ የሚችል ነው። በአንድ ነገር ጠንካራ አቅም ያለው ሰው በሌላ ነገር የግድ አቅም አለው ማለት የሚቻል አይደለምና” በማለት ተናግሯል።
የአንድ ሰው ጥንካሬና ድክመት በቀላሉ ሊለይ የሚችል ነው። ጥንካሬያችን ሌሎች ሰዎች በቀላሉ ሊያዩት የሚችሉት ነገር ነው። ጥንካሬያችንን ለይተን ማወቅ እና በጥንካሬያችን ላይ የተመሰረተን ስራ ብንሰራ መልካም ነው።
ውጤታማ ለመሆን ከፈለግህ በጥንካሬህ ላይ አተኩር እርሱንም አሳድግ። 70% የሚሆነውን ጊዜህን፣ ሃይልህን፣ እና ሃብትን ጥንካሬ ላይ ማዋል።
አዲስ
ሁሉም ነገር ባለበት ሆኖ ሺ ዓመታትን ሊቆይ አይችልም። ሺ ቀርቶ መቶ ዓመታትም ሊቆይ አይችልም። አስርም ሆነ አምስት እንዲሁም አንድ ዓመት ውስጥ የሚሆነው ለውጥ ብዙ ነው።
ለውጥ ተፈጥሯዊ ወይንስ ሰው ሰራሽ የሚለውን ክርክር ወደ ጎን አድርገን የለውጥ መኖርን ግን ልንክድ አንችልም። እድገት ከለውጥ ጋር እኩያ ነው።
በለውጥ ጉዞ እየተሻሸሉ መሄድን እናስባለን። እየተሻሻልን መሄድን የምናስብ ከሆነ መለወጥን እና ነገሮችን እያሻሻሉ መሄድ ይገባል። አዳዲስ ነገሮች ከጥንካሬ ጋር የተገናኙ ሊሆኑ ይገባል። በጥንካሬያችን ላይ አዳዲስ ነገሮች መጨመር። ጥንካሬያችን ይበልጥ ጠንካራ እንዲሆን ማድረግ። ልዩነት መፍጠር የሚያስችል ጥንካሬ ላይ መድረስ።
25% የሚሆነውን ጊዜህን፣ ሃይልህን፣ እና ሃብትን በጥንካሬህ ላይ አዳዲስ ነገሮችን በማድረግ ማዋል። ይህ ሲሆን የሚመጣው ለውጥ በእድገት ውስጥ ትርጉም ያለው ይሆናል።
ትኩረት የማድረግ ችግር ያለባቸው ሰዎች ሁሉም ነገር ላይ ሲባትሉ ይገኛሉ። በባተሉበት ሁሉ ፍሬ ሊያገኙ አይችሉም። በጥንካሬያቸው ላይ የተመሰረተ መባተል ቢሆን በቀላሉ ሊያሳኩት እንዲሁም በጥንካሬያቸው ላይ አዲስ ነገር በመጨመር እጅግ የበለጠ ሊያከናውኑት ከሚችሉት ይጎድላሉ። ባለ ምግብ ቤቱ ጥንካሬው ደንበኛ አያያዙ፤ ደንበኛ ተኮር ሆኖ አገልግሎቱን መስጠቱ ነው። አዲስ ነገር እዚያ ላይ እየጨመረ በሄደ ቁጥር እጅግ ጠንካራ መሆን ቻለ ማለት ነው። ምናልባትም በሳምንት ውስጥ አንድ እቁብ ሳይሆን ሁለት እቁብ መግባት የሚችልም ሊሆን ይችላል።
ድክመት
ድክመት የሌለበት ፍጡር ምን አለ? በፍጽምና ውስጥ ልንገልጸው የምንችለውን ሰው ከቤታችን ተነስተን በቢሊዮኖች በሚቆጠረው ሰው መካከል ብንፈልግ አናገኘም። ሁሌም ድካም አለበት፤ ሁሉም ደግሞ የራሱ ጥንካሬ አለው።
የትኩረት ህይወትን ስናስብ ድክመታችን ማሰብ አለብን። ማንኛውም ሰው ድከመቱ ላይ ፈጽሞውኑ ከመስራት ሊቀርለት አይችልም፤ ድክመት ሁሉም ሰው ውስጥ የሚገኝ ስለሆነ። በዙሪያችን ያሉ ሰዎችን በስራዎች ላይ መወከል በመቻል የእኛ ድክመት የምንመራውን ስራ እንዳይጎዳ ልናደርግ ይገባል።
አንድ የመድረክ ላይ ተጽእኖ ፈጣሪ ተናጋሪ የእርሱ ጥንካሬ መድረክ ላይ ተገኝቶ አስተማሪና አነቃቂ ንግግርን ማድረግ ነው። ይህ ከሆነ ትኩረቱን በሚያደርገው ንግግር ላይ ከማድረግ ባሻገር በሌሎች ስራዎች ማለትም የአውሮፕላን ትኬት መቁረጥ፣ የመድረክ ዝግጅት፣ የሰዎች ጥሪ ወዘተ ስራዎች ውስጥ እራሱን ሙሉ ለሙሉ ጨምሮ መገኘት ውጤታማ አያደርገውም። በመሆኑም እኒህ አቅጣጫዎች የእርሱ የድክመት አቅጣጫዎች ተደርጎ የእርሱን ጊዜም ሆነ አቅም መውሰድ ያለባቸው 5% ትኩረት መሆን አለበት ማለት ነው። ሌሎች ሰዎችን ለእኒህ ስራዎች በመወከል ስራው እንዲሰራ ማድረግ ግን አስፈላጊ ነው።
ሁለተኛው ክንፍ – መሰጠት
ምግብ ቤቶች ዘወትር ድግስ እንዳለበት ቤት በብዙ ሲደክሙ ይታያሉ። በዓመታት ውስጥ በተቀባይነት ከዘለቀ ምግብ ቤት ጀርባ ወጥነት ባለው ሁኔታ በመሰጠት የሚሰሩ ሰራተኞች አሉ። መሰጠት አስፈላጊ እንደሆነ በተለያዩ መንገዶች ሲነገር እንሰማለን። በመሰጠት ዙሪያም ብዙ ምክርች ይቀርባሉ። መሰጠት ከባድ የሚሆነው በዝናቡም በሙቀቱም ውስጥ በወጥነት መራመድን የሚጠይቅ መሆኑ ነው።
ኤድ ማክኤልሮይ የተባሉ ሰው ስለ መሰጠት ጠቀሜታ ሲናገሩ መሰጠት ልዩ ሃይል ይሰጠናል። በሽታ፣ ድህነት ወይንም ማእበል ቢመጣም ከግባችን ላይ አይናችንን ሳናነሳ ጉዞችንን እንድንቀጥል የሚያደርገን መሰጠት ነው ብለዋል።
መሰጠት ምን ማለት ነው ለእያንዳንዱ ሰው የራሱ የሆነ ትርጉም አለው። ለምሣሌ መሰጠት ለቦክሰኛው ተዘርሮ ከወደቀበት የቦክስ ውድድር ሜዳ ዳግም ለሌላ ዙር ውድድር የሚነሳበት አቅም ነው፤ ለማራቶን እሯጩ አቅሙን አጥቶ ባለበት ጊዜ ሌላ አስር ማይል ለመሮጥ እንዲተጋ የሚያደርገው ነው፤ ለወታደሩ በሌላው አቅጣጫ ምን እንደሚጠብቀው ሳያውቅ ቋጡኝን እየዘለለ በፍልሚያ ሜዳው ላይ መገኘቱን በጽናት መቀጠል ነው፤ ለሚስዮናዊው ለሌሎች ሰዎች መልካም ህይወት ሲል የራሱን ምቾት ተሰናብቶ በመውጣት እስከ እድሜው መጨረሻ የወንጌል ሰባኪ ሆኖ መገኘት ማለት ነው፤ ለመሪ ደግሞ ሁሉም ነገር ማለት ነው።
ውጤታማ መሪ ለመሆን የምትፈልግ ከሆነ የተሰጠህን መሆን አለብህ። እውነተኛ መሰጠት ሰዎችን ያነሳሳል እንዲሁም ወዳንተ እንዲሳቡ ያደርጋል። በምትሰራው ነገር ላይ እምነት እንዳለህም የሚያሳይ ነው። በምትሰራው ነገር ላይ እምነት ያለህ ሲሆን ነው ሰዎችም በአንተ ላይ እምነት የሚኖራቸው።
እውነተኛ መሰጠት ሦስት ባህሪያት አሉት። የመሰጠት ህይወትን መለማመድ የሚፈልግ ሰው በእኒህ ሦስት ባህሪያት ውስጥ እራሱን ሊፈልግ ይችላል።
1. ከልብ የሚጀምር፣
ተቀምጠው ለውጥን የሚናፍቁ ሰዎች አሉ። አዎን ተቀምጠው። በመሰጠት ውስጥ ከእነርሱ የሚጠበቀውን አድርገው ሳይሆን እንዲሁ ተቀምጠው። ለምንም ነገር ራሳቸውን መስጠትና መሰጠት ሳይፈልጉ ሁሉም ነገሮች ግን ፍጹም እንዲሆኑ የሚፈልጉ ሰዎች። እኒህ ሰዎች እንዲህ የሆኑት በተግባራቸው አይደለም፤ በቅድሚያ በልባቸው ነው።
መሰጠት ከክንውን በፊት የሚቀድም መሆኑን መረዳት ያስፈልጋል። ልባችን መልካም ነገርን ከታላቅ ነገር የምንለይበት ታላቅ ስፍራ ነው። አንተ በሌሎች ሰዎች ህይወት ውስጥ እንደ መሪ ለውጥን ማምጣት የምታስብ ከሆነ ልብህ ውስጥ መሰጠት መኖሩን ተመልከት። ልብህ ውስጥ መሰጠት በቅድሚያ መኖር አለበት፤ መሰጠትህን ልታምንበት ይገባልና።
ከልባቸው ትልቅ መሰጠት ያላቸው፤ ነገር ግን በተጨባጭ ደግሞ የማይገኙም አሉ። በልባቸው ትልቅ የሚያልሙ፤ ህልማቸውንም የሚናገሩ፤ ነገር ግን ተግባራዊ እርምጃ የማይራመዱ። ሁለተኛው የመሰጠት ባህሪ እዚህ ጋር የሚመጣ ነው።
2. በተግባር የሚፈተን፣
መሰጠት በተግባር የሚፈተን ነው። ስለ መሰጠት ማውራት አንድ ነገር ሆኖ፤ በመሰጠት ውስጥ መስራት ግን ሌላ የሆነው መሰጠት መሰጠት በተግባር ውስጥ ትርጉሙን የሚያገኝ በመሆኑ ነው። ብቸኛው የመሰጠት መለኪያ ተግባር ነው። አርቱር ጎርደን የተባለ ሰው እንዲህ አለ “ቃላትን እንደመናገር ቀላል ነገር የለም። የተናገሩትን ቀን በቀን እንደመኖር ደግሞ ከባድ ነገር የለም።”
ባለንበት በሚዲያ ዘመን ብዙ ድምጾችን ከየአቅጣጫው እንሰማለት። ብዙ ሃሳብ፣ ብዙ ምክር፣ ብዙ አስተማሪነት፣ ብዙ አድርጉ ባይነት፣ ሌላም ብዙ። ከበዙት ድምጾች ውስጥ በተግባር ያልታገዘ ድምጽ የመሰጠት ድምጽ አይደለም።
3. በመከናወንን በር ውስጥ የሚታይ፣
መሰጠት መዳረሻ ቦታ አለው፤ መከናወን። ባለ ምግብ ቤቱ በትኩረትና በመሰጠት ያሳለፋቸው ስድስት የስራ ቀናቶቹ በሰባተኛው ቀን በፈገግታ ከእቁቡ ቤት በር ላይ ያደርሱታል። በብዙ ትኩረትና ትጋት ነገር ግን በአሻጥርና በሌላም ነገር ተጠልፈው የሚወድቁ መኖራቸውን አብዝተን እንረዳለን። እነርሱም ሳይቀር በትኩረትና በመሰጠት ተነስተው የሚቆሙ ናቸውና የመሰጠት መዳረሻ የመከናወን በር ነው።
እንደ መሪ እስከአሁን የገጠመህ መሰናክልና ተቃውሞ ከሌለ ወደፊት እንደሚገጥምህ ጠብቅ። መሰጠት ብቻውን ወደፊት የሚያሻግርህ ወቅትም ይመጣል። ነገ መድረስ የምትፈልግበት የትኛውም ቦታ ላይ ለመድረስ መሰጠትህ የግድ ይላልና።
ሁለቱ ክንፎች በአንድነት
ትኩረት እና መሰጠት ሁለት ክንፍ ሆነው አብረው ለመብረር አስፈላጊ ናቸው። የሁለቱ ክንፎች በተናጠል ያላቸው ጥቅም እንዳለ ሆኖ በጋራ ያላቸው ውህድ አቅም ደግሞ አስገራሚ ነው። የተሰጠ ደግሞም በትኩረት የሚኖርን ሰው ፈልገህ አግኝ፤ ይህ ሰው ተጽእኖ ፈጣሪ ነው። ይህ ሰው ማስተከል የቻለ ነው። ይህ ሰው አምራች ነው። ይህ ሰው አንዳች መፍትሄ የሚገኝበት ነው። ከችግሮች በላይ መብረር የሚችል ነው።
እውነተኛ ውጤታማነት ላይ ለመድረስ ቁልፉ ምን ማድረግ ነው? የሚሉ ጥያቄዎች ለሚጠይቁ ቅድሚያ ለሚሰጠው ቅድሚያ መስጠት (Priorities) እና ቀልብን በመሰብሰብ መቻል (concentration) ውስጥ በሚገለጸው ትኩረት አድራጊነት እና መሰጠት ነው።
ቅድሚያ መስጠት የሚገባውን የሚያውቅ ነገር ግን ቀልቡን ሰብስቦ ከእዚያ አንጻር በመሰጠት መስራት ያልቻለ መሪ ምን መስራት እንዳለበት ያወቀ ግን ደግሞ መስራት ያልቻለ ማለት ነው። በተቃራኒው ደግሞ ትኩረቱን መሰብሰብ የሚችል ነገር ግን ቅድሚያ የሚሰጠውን መለየት ያልቻለ ከሆነ ልቀት ያለው መሪ ነገር ግን እድገት የሌለው ነው የሚሆነው። ነገር ግን ሁለቱን አጣምሮ መሄድ የሚችል ከሆነ ትልልቅ ነገሮችን ማሳካት የሚችል ይሆናል።
በአመራር ቦታ ላይ ያሉ ነገር ግን ጥቃቅን የሚባሉ ጉዳዮችን ዋና ጉዳይ አድርገው በጥቃቅን ጉዳዮች ተጠ ምደው የሚውሉ ሰዎች ብዙ ጊዜ ይታያሉ፤ ትኩረታቸውም ሆነ መሰጠታቸው ወደሚፈለገው ውጤት የማያደርሳቸው። ዋናው ጥያቄ እንዴት ጊዜህን እና ሃይልህን በትኩረትና በመሰጠት ስራ ላይ ታውላለህ ነህ?
ትኩረት በማድረግ ረገድ እራስህን እንዴት ትገመግማለህ? በጥቃቅን ነገሮች ላይ ብዙ ጊዜህን ታውላለህ? ጥንካሬህ ላይ ከማተኮር ይልቅ ድክመት በሆኑብህ ነገሮች ላይ ብዙ ጊዜህን ታጠፋለህ? ለስራህ ጥቅም የሌላቸው ሰዎች ብዙ ጊዜህን ይወስዱታል? ይህ ከሆነ ትኩረት ያጣህ ሰው የመሆን እድልህ ሰፊ ነው። ትኩረት ላደረክበት ነገር ያለው መሰጠትህስ?
በመሰጠት ውስጥ ወደ ሆነ ትኩረት ወደማድረግ አቅምህ ለመምጣት በራስህ ላይ ስራ፡- አንተ የእራስህ ትልቅ ሃብት ነህና በራስህ ላይ ስራ።
ትኩረት ማድረግ ባለብህ ነገር ላይ ትኩረት አድርግ፡- ጦርነትህና ትግልህ ትኩረት ማድረግ ባለብህ ነገር ላይ መሆን አለበት። ትኩረት መንታፊ ሰበር ዜናዎችን ወደ ጎን አድርገህ ትኩረት ማድረግ ያለብህ ነገር ውስጥ ተገኘ። ራስን እየጠበቁ ለቤተሰብ አባላት ጊዜ በመስጠት፤ ከማህበራዊ ህይወትም መፋታት ሳይሆን ሚዛኑን የጠበቀ ትኩረት ማድረግ። እቁብተኛው ባለ ምግብ ቤት ለማህበራዊ ህይወቱ የሚሆነውን ጊዜ ያላጣ ሰው ነው። ሥራውና ማህበራዊ ህይወት ተቆራኝቶ እንደውም ድጋፍ የሆነው።
በጥንካሬህ ላይ ስራ፡- በፍጹም ምንም የሌለህ ሰው አድርገህ ራስህን አትቁጠር። አንተ ልዩ ፍጡር ነህ። አንች ልዩ ፍጡር ነሽ። ሁላችንም ልዩ አቅም አለን። ወደ እምቅ-አቅምህ መድረስ እንድትችል የራስህን ጥንካሬ ለይተህ በማወቅ ጥንካሬህ ላይ በትጋትና በመሰጠት ስራበት።
አብረውህ ካሉት ጋር ስራ፡- ብቻህን ውጤታማ መሆን ስለማትችል አብረውህ ካሉት ጋር፣ ከአንተ ጋር ከሚሄዱት ጋር፤ ግብህን ለማሳካት ከሚረዱህ ጋር አብረህ ስራ። ባለ ምግብ ቤቱ ብቻውን ሁሉን ሥራ ልስራ ቢል ምን ይገጥመው እንደነበር አስበው። አንዳችን ለአንዳችን የምናስፈልግ ወደ ውጤት ለመድረስ በጋራ መገመድ ያለብን ነን።
ሁለቱ ክንፎች አብረው ሲሆኑ የሚፈጥሩት አቅም ከፍ እያልን እንዲበር የሚያደርግ ነው። ከፍ ብሎ መብረር፤ ያቀዱትን እየሳኩ አሁንም ከፍ ብሎ መብረር።
በአገልጋይ ዮናታን አክሊሉ
አዲስ ዘመን መስከረም 15/2014