‹‹ ጠላት በአውሮፕላን በአየር ሲንደረደር ፣
የአርበኞቹ መሪ ደባለቀው ከአፈር ፣
አንተ አበበ አረጋይ ፈረስህ ገስጥ ፣
የፋሺስትን አንጎል የሚበጠብጥ::››
ይህ ግጥም የተገጠመው በፋሺስት ኢጣሊያ ወረራ ወቅት ከጠላት ጋር እልህ አስጨራሽ ፍልሚያዎችን ለተፋለሙት፣ ከፋሺስት ጋር ካደረጓቸው ውጊያዎች መካከል በአንዱ የጠላትን አውሮፕላን በእሩምታ ተኩስ እንዲወድቅ ላደረጉት … ታላቅ የጀግንነት ታሪክ ለጻፉት ለስመጥሩ አርበኛ ለሌተናንት ጀኔራል ራስ አበበ አረጋይ (አባ ገስጥ) ነው::
አበበ አረጋይ የተወለዱት ነሐሴ 14 ቀን 1896 ዓ.ም በተጉለትና ቡልጋ አውራጃ፣ ጅሩ ውስጥ ተወለዱ:: አባታቸው አረጋይ ቢቸሬ በሙግት ስርዓት ልምድ ያላቸው ሰው ስለነበሩ በተለያዩ የዳኝነት ደረጃዎች ሰርተዋል፤ አፈንጉሥም ለመሆን በቅተዋል:: በመጨረሻም የአክሱም ጽዮን ንቡረ እድ ተብለው ተሹመውም ነበር:: እናታቸው ወይዘሮ አስካለማርያም ጎበና ደግሞ የዳግማዊ አፄ ምኒልክ የጦር አበጋዝ የነበሩት የራስ ጎበና ዳጬ ልጅ ናቸው:: ራስ ጎበና ዳጬ እና አፈ ንጉሥ አረጋይ ቢቸሬ ከዝቅተኛ ደረጃ ተነስተው በጠንካራ ስራቸውና በታማኝነታቸው ለከፍተኛ ደረጃ የበቁና ከነገሥታቱም ጋር የቅርብ ግንኙነት የነበራቸው መኳንንት ነበሩ::
አበበ በልጅነታቸው መምህር ተቀጥሮላቸው በቤታቸው ውስጥ የግዕዝና የአማርኛ ጽሕፈት፣ መንፈሳዊ ትምህርትና ስነ ምግባር እንዲሁም የአገር ወግና ስርዓት እየተማሩ አደጉ:: በአዲስ አበባ ከተማ በተቋቋመው ተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት ገብተው በፈረንሳይኛ ቋንቋ ዘመናዊ ትምህርት ተከታትለዋል:: በወጣትነታቸውም ዘመን ከአባታቸው ችሎት በመዋል ልማዳዊውን ሕግ ከነስርዓቱ አጥንተዋል:: በክብር ዘበኛ ደንብ በውትድርና ሙያ ሰልጥነው በመጀመሪያ የመቶ አለቅነትን፤ ቀጥሎም የሻምበልነትን ማዕረግ አግኝተዋል::
በፋሺስት ኢጣሊያ ወረራ ወቅት የአዲስ አበባን ሰላምና ጸጥታ የማስከበሩና ከወራሪው ኃይል የመከላከሉ ግዳጅ የተሰጠው ለአራዳ ዘበኞች ነበር:: በፈረስ ስማቸው ‹‹አባ ገስጥ›› በመባል የሚታወቁት አበበ አረጋይ፣ በክብር ዘበኛ ሰራዊት በመኮንንነት ካገለገሉ በኋላ በ1926 ዓ.ም በባላምባራስ ማዕረግ ለግማሹ የአዲስ አበባ ከተማ ጥበቃ በአራዳ ዘበኛ አለቃነት ወደ አዲስ አበባ ከተማ ማዘጋጃ ቤት ተዛውረው ነበር:: በ1928 ዓ.ም ንጉሰ ነገሥት ቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ ወደ ሰሜን የጦር ግንባር ሲዘምቱ ባላምባራስ አበበ አረጋይ የአራዳ ዘበኛ ጠቅላይ አዛዥ ሆነው ተሾሙ::
የፋሺስት ኢጣሊያ ጦር መጠነ ሰፊ ወረራውን ቀጥሎ ወደ አዲስ አበባ ከተማ ሲያመራ የአራዳ ዘበኛ ፈታኝ ሁኔታ ገጠመው:: ንጉሰ ነገሥቱ ወደ ዓለም መንግሥታት ማኅበር ሄደው እንዲያመለክቱ በመወሰኑ ንጉሰ ነገሥቱ ቤተሰቦቻቸውን፣ ጥቂት ታላላቅ መኳንንትንና የቅርብ ረዳቶቻቸውን ይዘው ወደ ውጭ አገር ሄዱ:: የንጉሰ ነገሥቱን ከአገር መውጣት ተከትሎ መጠነ ሰፊ ዝርፊያ ተጀመረ::
የአራዳ ዘበኞች ዝርፊያውን ለማስቆም የተቻላቸውን ያህል ቢጥሩም ዝርፊያው ከቀን ወደ ቀን እየጨመረ በመሄዱ ከአቅማቸው በላይ ሆነ:: ይህም በአራዳ ዘበኛው አለቃ በባላምባራስ አበበ አረጋይ ላይ ብርቱ ስጋት አሳደረባቸው:: የወቅቱ የአዲስ አበባ ተጠባባቂ ከንቲባ ብላታ ታከለ ወልደሐዋርያት የከተማውን ሹማምንት ሰብስበው ተወያዩ:: በውይይቱም ወራሪውን ኃይል ከተማ ውስጥ ለመከላከል መሞከር ሕዝቡን ማስጨረስ እንሚሆን ተነገረ:: በሌላ በኩል ደግሞ ድል መሆንን በመቀበል ከተማውን ለጠላት አሳልፎ መስጠት ሕሊናን የሚያቆስል ዘለዓለማዊ ውርደት ሆኖ ታየ:: ስለሆነም አዲስ አበባን ለቆ በመውጣት በዱር በገደል የፋኖ ውጊያ ለመቀጠል ተወሰነ:: ባላምባራስ አበበም ውሳኔውን ለሰራዊቱ ሹማምንት አሳወቁ::
በወቅቱ የጠላት ጦር ጣርማ በርን አልፎ ወደ አዲስ አበባ እየተጠጋ ስለነበር የፋሺስት ጦር በእግሩ ሊረግጠው ይቅርና በአውሮፕላኑ እንኳ ኢላማውን ለይቶ ለመምታት በማይችልበት ‹‹በሰሜን ሸዋ ገደላገደልና ሸንተረር ውስጥ በመመሸግ አዲስ አበባ ውስጥ የሚከማቸውን የጠላት ጦር ሰላም በመንሳት ሌት ከቀን እንዲባንን ማድረግ
ይኖርብኛል›› በማለት ውለው ሳያድሩ ቤተሰቦቻቸውንና ሌሎች ጥቂት ሰዎችን አስከትለው ለአርበኝነት ተጋድሎ ወደ ሰሜን ሸዋ አመሩ:: የፋሺስት ጦር አዲስ አበባ የደረሰው አባ ገስጥ ከተማዋን በለቀቁ ማግሥት ነበር::
የሰሜን ሸዋ አካባቢ ለሽምቅ ውጊያ አመቺ በመሆኑና ከአዲስ አበባ ከተማ ጋር በብዙ አቅጣጫዎች ስለሚዋሰን በቅርብ ርቀት ላይ ሆኖ በየጊዜው በወራሪው ጦር ላይ አደጋ ለመጣል የሚመች ስፍራ ነበር:: አባ ገስጥ ወደ ስፍራው ያቀኑትም አካባቢው ላሰቡት ዓላማ ምቹ ሆኖ በማግኘታቸው ነው:: ግንቦት 6 ቀን 1928 ዓ.ም ጅሩ ገቡ:: ጅሩ እንደደረሱም ፋሺስት ኢጣሊያ በኢትዮያ ላይ እያደረገ ስላለው ነገር ሁሉ ለአካባቢው ሕዝብ ገለፁ:: ሕዝቡም እየተገናኘ ተወያየ፤ ስንቅና መሳሪያውን አዘጋጀ፤ ለአገር ነፃነት ለመዋጋት የወሰነው ሁሉ ከአባ ገስጥ ጋር ተቀላቀለ:: አባ ገስጥም አብሯቸው ለመታገል ከወሰነው አርበኛ መካከል በወታደርነትና በማስተባበር ልምድ ያላቸውን እየመረጡ አርበኛውን በአለቆች አደራጁት::
ባላምባራስ አበበ የፀረ-ፋሺስት ትግል ለመጀመር ዝግጅት እያደረጉ መሆናቸውን የሰማው የጠላት ጦር በበኩሉ በባላምባራስ አበበና ተዋጊዎቻቸው ላይ አደጋ ለመጣል ዝግጅት አደረገ:: ባላምባራስ አበበም ስለጉዳዩ ሰምተው አርበኞቻቸው ሁሉ በአንድ ቦታ እንዲሰባሰቡ አደረጉ:: የፋሺስት ጦር በቀኛዝማች ቁምቢ ከምሲ እየተመራ ለፍልሚያ ገሰገሰ:: ግንቦት 24 ቀን 1928 ዓ.ም ደነባ ላይ ከጠዋት እስከ ማታ ድረስ የዘለቀ ውጊያ ተካሄደ:: አባ ገስጥም ከወዲያ ወዲህ እየተሯሯጡ ሲተኩሱና ሲያስተኩሱ ዋሉ፤ አርበኛውም በኃይለኛ ወኔ ተዋጋ:: በመሳሪያው ጥራት ተማምኖ የነበረው የፋሺስት ጦርም ‹‹አሸንፋለሁ›› የሚለው ጉጉቱና እርግጠኛነቱ እንደጉም ተነነበት:: ከአባገስጥ አርበኞች የተረፈው የጠላት ጦር ከነአዛዡ ሸሽቶ ደብረ ብርሃን ገባ::
በጦርነቱ ማግሥት አባ ገስጥ ከአርበኞቻቸው መሪዎች ጋር በሌሎች የሰሜን ሸዋ አካባቢዎች የፀረ-ፋሺስት ትግል ከጀመሩ አርበኞች ጋር መተባበር እንደሚገባ ተወያዩ:: በሃሳቡ ላይ በመስማማታቸው አባ ገስጥ ከደጃዝማች አበራ ካሳ ጋር ለመነጋገር ወደ ፍቼ ተጓዙ:: እግረ መንገዳቸውንም ከፊታውራሪ ዘውዱ አባ ኮራን ጋር ተገናኝተው ተወያዩ:: ሰኔ 25 ቀን 1928 ዓ.ም ደጃዝማች አበራ ካሳ፣ ወንድማቸው ደጃዝማች አስፋወሰን ካሳ፣ ፊታውራሪ ዘውዱ አባ ኮራን የሐይማኖት አባቶችን፣ መኳንንትንና ወታደሮችን ይዘው ከአባ ገስጥና የጦር አበጋዞቻቸው ጋር ተገናኙ:: ጠላትን በትብብር ለመከላከልም ተስማሙ::
ደነባ ላይ ሽንፈት የገጠመው የፋሺስት ጦር የበቀል እርምጃ መውሰዱ እንደማይቀር አባ ገስጥ ገምተው ነበርና በፍጥነት ወደ ጦር ሰፈራቸው ተመለሱ:: የገመቱት አልቀረም … የጠላት ጦር ከ50ሺ የማያንስ ጦር አሰልፎ ወደ አባገስጥ ሰፈር ተመመ:: በወቅቱ የነበረው የኃይል አለመመጣጠን ባላምባራስ አበበ ሳላይሽ የተባለውን አካባቢ ለቀው ወደ ሌላ ስፍራ ሄዱ:: ኅዳር 25 ቀን 1929 ዓ.ም ቀንና ሌሊት ከባድ ጦርነት ተደርጎ የአባ ገስጥ አርበኞች በጠላት ጦር ላይ ከፍተኛ ጉዳት አደረሱ::
በፋሺስት ወረራ ወቅት የጠላት ኃይል ሲበረታ ከጠላት መሰወርና ቦታ እየቀያየሩ ጠላትን መፋለም የአርበኛው ሁሉ ተግባር ስለነበር ባላምባራስ አበበም አዳኝም ታዳኝም ስለነበሩ በአንድ ስፍራ ላይ ለረጅም ጊዜ አይቆዩም ነበር:: በዚህም ምክንያት በሰኔ 1929 ዓ.ም ከመርሃቤቴ ወደ ግንደበረት እየተጓዙ ሳለ መንከራተት የበዛባቸው ባለቤታቸው ወይዘሮ ቆንጂት አብነት በድንገት ምጥ ያዛቸው:: ሰኔ 17 ቀን 1929 ዓ.ም ግንደ በረት በረሃ ላይ ወንድ ልጅ ተገላገሉ:: ቀደም ሲል ገና በአስረኛ ወሩ በአንቀልባ ታዝሎ በጅሩ በረሃ ውስጥ የሞተው ልጃቸው ምትክ ሌላ ወንድ ልጅ አገኙ::
ባላምባራስ አበበ ባለቤታቸውን ከሌሎች ሴቶችና ከጠባቂዎቻቸው ጋር ትተው ጉዟቸውን ቀጠሉ:: ይሁን እንጂ የፋሺስት ጦር በባንዳዎች ጥቆማ እነወይዘሮ ቆንጂት ያሉበትን ቦታ በማወቁ ወይዘሮ ቆንጂትንና ልጃቸውን ማርኮ ወሰደ:: የፋሺስት ጦር አዛዥ ለቀናት ያህል በረሃብ ለተጎዱት ወይዘሮ ቆንጂት ዳቦ ሲሰጣቸው ‹‹ያንተን ምግብ አልበላም›› ብለው መልሰው ወረወሩለት:: አባገስጥም የባለቤታቸውንና ልጃቸውን መማረክ ባወቁ ጊዜ ክፉኛ አዘኑ:: ወይዘሮ ቆንጂት መጀመሪያ ወደ አዲስ አበባ ከዚያም ወደ ደብረ ብርሃን ተወስደው ታሰሩ:: ደብረ ብርሃን ለጥቂት ጊዜያት ያህል ከቆዩ በኋላ እንደገና ወደ አዲስ አበባ ተመልሰው ለአምስት ወራት ያህል ታሰሩ፤ በመጨረሻም ወደ ሸኖ ተልከው በእስር እንዲቆዩ ተደረገ:: በዚያ ሳሉም ልጃቸውን ይዘው ለማምለጥ ሲሞክሩ ተይዘዋል::
ገና በ15 ዓመቱ ውጊያ ላይ የተሰለፈው የባላምባራስ አበበ የበኩር ልጅ ዳንኤል አበበ ቆስሎ ተማርኮ ነበር:: ታዳጊው ዳንኤል ሕክምና እንዳያገኝ ተከልክሎ በቀጥታ ወደ እስር ቤት ተወስዶ ተቆለፈበት:: የባላምባራስ አበበ ፈተና በዚህ ብቻ ሳያበቃ በውጊያ ላይ ሳሉ ቆስለው የነበሩት እናታቸው ወይዘሮ አስካለማርያም ጎበናም ተማረኩ:: ባላምባራስ አበበ ግን ይህ ሁሉ መከራ ቢደርስባቸውም ጠላትን ከመፋለም አልታቀቡም:: ፋሺስቶች የግንደበረት አገረ ገዢ አድርገው የሾሙትንና ሕዝብን ሲያሰቃይ የነበረውን ሰው ሰኔ 21 ቀን 1929 ዓ.ም ውጊያ ገጥመው ድል በማድረግ መቀጣጫ አደረጉት::
የቡልጋ አርበኞች በየአካባቢው ያለውን የአርበኞች እንቅስቃሴ በአገር ደረጃ ለማስተባበር ንጉሥ ማንገስ አስፈላጊ መሆኑን በማመን ከሌሎች የአካባቢው አርበኞች ጋር ደብዳቤ ተፃፅፈው እንግዳእሸት የተባለውንና በአብዩ ገዳም የነበረውን የልጅ ኢያሱ ሚካኤልን ልጅ ‹‹መልዐከፀሐይ›› በሚል ስም አነገሱ::
አዲሱ ንጉስ እድሜው ገና ልጅ ስለነበርና በቤተ መንግሥት አስተዳደግ ያላለፈ በመሆኑ እንደራሴ ያስፈልገው ስለነበር ልጅ ኃይለማርያም ማሞ እንደራሴ እንዲሆኑ ሃሳብ ቀረበ:: ልጅ ኃይለማርያም ግን ‹‹በጦር መሪነት ላይ የአስተዳደር ስራ ደርበው መስራት የሚችሉት ባላምባራስ አበበ አረጋይ ስለሆኑ እርሳቸው እንደራሴ ቢሆኑ ይሻላል›› በማለት ተናገሩ:: ሃሳቡን የደገፉ አርበኞች ቢኖሩም በወቅቱ ከባላምባራስ አበበ የበለጠ ማዕረግ ያላቸው አርበኞች ስለነበሩ የባላምባራስ አበበ ለእንደራሴነት መታጨት ተቃውሞ ገጠመው:: በመጨረሻ ግን አባ ገስጥ እንደራሴ ሆነው ተመርጠው የራስነት ማዕረግ ተሰጣቸው:: ራስ አበበም በአርበኞች ቁጥጥር ስር ያለውን አገር ሲያስተዳድሩና ንግሥናውም በመላ ኢትዮጵያ ተቀባይነት እንዲያገኝ ጥረት በማድረግ ላይ ሳሉ ወጣቱ ንጉሥ መልዐከፀሐይ በድንገት አረፈ:: መልዐከፀሐይ ቢያርፍም ራስ አበበ ግን ሕዝቡን የማስተዳደሩን ስራ ያከናውኑና ሚዛናዊ ፍርድ ይሰጡ ነበር::
የአርበኞችና የጠላት ፍልሚያ ቀጥሎ የራስ አበበና የፋሺስት ጦር ደንገዜ ተራራ አካባቢ ተፋጠጠ:: የፋሺስት ጦር አዛዥ ኮሎኔል ማሌቲ አካባቢውን በመድፍና በአውሮፕላን ቢደበድበውም የራስ አበበ ጦር ከጠላት መሐል ገብቶ የፋሺስትን ጦር በስፍራው በታተነው:: ያ የጦር ሜዳ ውሎ የጀግንነት ወኔ፣ የዓላማ ቆራጥነትና የውጊያ ስልት ከመሳሪያ ጥራትና ብዛት የበለጠ ፋይዳ እንዳላቸው የታየበት ሆነ:: የፋሺስት ወታደሮች አስክሬንም የሚያነሳው ጠፍቶ አውሬ በየሜዳው ጎተተው::
ከዕለታት አንድ ቀን አባ ገስጥ ሰራዊታቸውን አስከትለው ወደ ጦር ግንባር እያመሩ ከፊታቸው ያጋጠማቸውን የባንዳና የፋሺስት መሰናክልም እየረመረሙት አለፉና ለመከላከል ስፍራ ይዞ የነበረውን
የጠላት ጦርም በመትረየሥ አስፈነጠሩት:: የኢትዮጵያ አርበኞችም
‹‹አቶ ሙሶሊኒ ምን አቅበጠበጠው ፣ አልነገረውም ወይ ከዓድዋ ያመለጠው›› ብለው በፋሺስቱ ሙሶሊኒ እብሪት ላይ ተሳለቁበት::
ከዚያም በመቀጠል አባ ገስጥ በሰልሜ በኩል አቋርጠው እንሳሮ ገቡ:: የፋሺስትን ጦር ለመውጋት ጦራቸውን አሰልፈው ወደ ካቢ ሄደው ፍልሚያ ጀመሩ:: በውጊያ ላይ ሳሉ የጣሊያን ወታደሮች ወደ እርሳቸው ሲመጡ በእጅ ቦንብ ደመሰሷቸው:: ሌላ ባለመትረየስ የፋሺስት ወታደርም አቁስለው ስለነበር ከራስ አበበ አርበኞች መካከል አንዱ ቁስለኛውን ገድሎ መትረየሱን ማረከ:: ውጊያው በረድ ሲል ራስ አበበ ተራራ ላይ ወጥተው በመነፅር ሲመለከቱ የጠላት ጦር አዛዥ ዕይታቸው ውስጥ ገባ:: ራስ አበበም ወዲያውኑ አነጣጥረው በመተኮስ አዛዡን ገደሉት፤ አብረውት የነበሩት ወታደሮችም እግሬ አውጭኝ ብለው ሸሹ:: ከዚያም በፅኑ ቆስለው ለነበሩት ለባሻ ሚኮ ረዳት መድበው የጠላት ጦር ወደሚሸሽበት አቅጣጫ ተከትለው ሄዱ:: ከባንዳዎቹ መካከል አንዱ ራስ አበበን ያውቃቸው ስለነበር ‹‹አበበ መጣላችሁ!›› ብሎ ሲናገር የባንዳ ወታደሮች ለመሸሽ ሲሮጡ አባ ገስጥ በእጅ ቦንብ አጋያቸው፤ አንድ የፋሺስት ጦር መኮንንም የአባ ገስጥ ሽጉጥ ሲሳይ ሆነ::
አባ ገስጥ ጠላትን የሚቀጡት በውጊያ ሜዳ ብቻ ሳይሆን በመኖሪያ ቤቱም ጭምር ነበር:: ቁምቢ ከምሲ የተባለ የባንዳ አለቃ በተሾመበት አካባቢ የሚኖረውን ሕዝብ ያሰቃይ ስለነበር ወደ ሰፈሩ ሄደው ድል በማድረግ ጀግንነታቸውን አስመስክረዋል::
ፋሺስት ኢጣሊያ ከራስ አበበ ጋር ተደጋጋሚ ውጊያዎችን ቢያደርግም ራስ አበበን መማረክ/ማስገበር አልቻለም:: ስለሆነም ከራስ አበበ ጋር መታረቅ ብቸኛ አማራጭ መሆኑን በማመን የእርቅ ጥያቄ አቀረቡ:: ይሁን እንጂ ከራስ አበበ ጋር የቀረቡት ተደጋጋሚ የእርቅ ጥያቄዎች በአባ ገስጥ ዘንድ ተቀባይነት ሳያገኙ ቀርተዋል:: በአንድ ወቅት ኮሎኔል ማሌቲ የተባለው የደብረ ብርሃንና አካባቢው አገረ ገዢ ራስ አበበ አረጋይ ለኢጣሊያ እንዲገብሩ የሚያሳስብ ደብዳቤ ሲልክባቸው አባ ገስጥ ‹‹ … እኔና ሌሎች አርበኞች የምንታገለው ለውዷ አገራችን ነፃነትና ክብር እንዲሁም ለሕዝቧ ደህንነት መሆኑን እወቀው:: ማንኛውም ኢትዮጵያዊ በፋሺስት ኢጣሊያ ኮቴ ሲረገጥ እንደማይኖር አረጋግጥልሃለሁ … ›› የሚል ምላሽ ልከውለታል::
በ1931 ዓ.ም ‹‹የጥንታዊት ኢትዮጵያ የጀግኖች ማኅበር›› ሲቋቋም ራስ አበበ አረጋይም የማኅበሩ የክብር ፕሬዝደንት ሆነው ተመረጡ:: በ1933 ዓ.ም ማኅበሩን የሚመሩ አመራሮች በድጋሚ ሲመረጡ ራስ አበበ አረጋይ የማኅበሩ ፕሬዝደንት ሆነው ተመርጠው ነበር::
ንጉሰ ነገሥት ቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ ከእንግሊዝ ወታደሮች ጋር በመሆን በሱዳን በኩል አድርገው ወደ ኢትዮጰያ ሲገቡ ሚያዝያ 27 ቀን 1933 ዓ.ም ራስ አበበ 10 ሺህ ጦራቸውን ይዘው እንጦጦ አካባቢ ለንጉሰ ነገሥቱ አቀባበል አደረጉ:: ወዲያውኑም ራስ አበበ አረጋይ የሜጀር ጀኔራልነት ማዕረግና የአዲስ አበባ ገዢነት ተሰጣቸው:: ተማርከው ከነበሩት ቤተሰቦቻቸው ጋርም ተገናኙ::
ራስ አበበ በአዲሱ ሹመታቸው ቀዳሚ ተግባራቸው ያደረጉት በከተማዋ ሕግና ስርዓት እንዲከበር ማድረግ ነበር:: የራስ አበበ አገር የማረጋጋት ተግባር በሌሎች አካባቢዎችም በማስፈለጉ በነሐሴ 1933 ዓ.ም የሲዳሞ፣ የቦረናና የወላይታ አገረ ገዢ ሆነው ተሾሙ:: የካቲት 16 ቀን 1934 ዓ.ም የጦር ሚኒስትር ሆነው ተሾሙ:: በዚህ ኃላፊነታቸውም በተለያዩ አካባቢዎች እየተዘዋወሩ ሰላምና ጸጥታን አስከብረዋል:: በ1941 ዓ.ም ደግሞ የአገር ግዛት ሚኒስትርነትን ተሹመው ውስብስብ የነበረውን የአገር አስተዳደር መልክ ለማስያዝ ደፋ ቀና ሲሉ፤ በ1947 ዓ.ም በሌተናንት ጀኔራል ማዕረግ የመከላከያ ሚኒስትር ሆነው ተሾሙ:: ጠቅላይ ሚኒስትር ተደርገው ተሹመውም ነበር::
በወንድማማቾቹ ብርጋዴር ጀኔራል መንግሥቱ ንዋይ እና ገርማሜ ነዋይ በታኅሣሥ 1953 ዓ.ም በንጉሰ ነገሥት ቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ መንግሥት ላይ የተሞከረው የመፈንቅለ መንግሥት እንቅስቃሴ ለራስ አበበ አረጋይ ሕይወት ማለፍ ምክንያት ሆነ:: የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራው ጠንሳሾች ታኅሳሥ 7 ቀን 1953 ዓ.ም በግፍ ከረሸኗቸው የንጉሰ ነገሥቱ መንግሥት ሹማምንት መካከል አንዱ ራስ አበበ አረጋይ ነበሩ::
አንተነህ ቸሬ
አዲስ ዘመን መስከረም 12/2014