ጥበብ መፍለቂያዋና መፍሰሻዋ ብዙ ነው። ጥበብ አብዝታ ሰላምን ትሻለች። በሰላም ውስጥ ስትፈልቅ ታዝናናለች መንፈስን ሀሴት ታላብሳለች። ጥበብ በችግር ውስጥም ትከሰታለች። ያኔ ደግሞ ብሶትን፣ ቁጭትን ክፋትንና ጉዳትን እያስታወሰች የተሰበረን መንፈስ ታክማለች። ትጠግናለች። ጥበብ በጦርነት ውስጥም ትፈጠራለች፤ለተዋጊዎቹ ጉልበትና ወኔን አለብሳ ለትግል ታነሳሳለች።
ጥበብ መንፈስ ስለሆነች ጊዜ፣ ቦታና ሁኔታ አይገድባትም፣ ጋራና ሸንተረር አይጋርዳትም። ውቂያኖስና ጅረቶች አይከፍሏትም። ጥበብ ህዝባዊ ወገንተኝነቷ ወደር አይገኝላትም። ከተበደለው ጋር ስትሆን ጉልበቷ ይበልጥ ያይላል። ለወገነችው ተበዳይ አብራ ነጻ ልታወጣው ብርታት ትሆነዋለች። ለነጻነት መታገል ካስፈለገም ታግላ ታታግላለች።
ኢትዮጵያችን በየዘመኑ ፈታኝ የሆኑ ጦርነቶችን አሳልፋለች። ባሳለፈቻቸው ጦርነቶች ሁሉ የኪነጥበብ ሚና በጉልህ ተጽፎ ለትውልድ ምስክር እንዲሆን በክብር ተቀምጧል። ከሩቁ ብንጠቅስ በአድዋ ጦርነት ወቅት የአዝማሪዎች ሚና ከፍተኛ እንደነበር ታሪክ ከትቦ አስቀምጦልናል። ከቅርቡም ብንጠቅስ በኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት አንጋፋ ሙዚቀኞቻችን ግምባር ድረስ ዘምተው ያቀረቡት የቅስቀሳ ሙዚቃ ምን ያህል የሰራዊቱንና የህዝቡን ሞራል በመገንባት ረገድ ያደረጉት አስተዋጽኦ በቃላት የሚገለጽ አልነበረም።
አሁንም ባጋጠመን ኢትዮጵያን የማዳን ዘመቻ ኪነጥበብ ሚናዋን ለመወጣት የሚያግዳት ነገር አይኖርምና እውቀታቸውን፣ጊዜያቸውንና ሀብታቸውን አስተባብረው ኢትዮጵያን ለማዳን ለመዝመት ዝግጁ ሲሆኑ ተመልክተናል። “ጥበብ ትዘምታለች” ብለውም አዝማቾቿን ለማስተባበር ከፊት ተሰልፈዋል።
ለምሳሌ ያህል እናንሳ ካልን ኢትዮጵያውያን የተጣባቸውን ሽብርተኛ እባጭ ለመንቀል ባደረጉት የህልውና ዘመቻ ላይ መነሻቸውን በራያ ግምባር ከሰራዊቱ ጋር ለመሰለፍ የተገኙ አያሌ የጥበብ ሰዎች ነበሩ። በወቅቱ መሳሪያ ይዞ ከመዋጋት በላይ በስነልቦና ግንባታ ላይ መስራት እንደሚገባ ተመልክተው ያንን ክፍተት ለመሙላትም ከፊት ተሰልፈው ነበር። በአካል ካገኟቸው የጦር መሪዎችና ከመንግስት አካላት የተሰጣቸው ግብረ መልስም ይህንኑ የሚያጠናክር ነበር። እናም ጊዜ ሳናያጠፉ የሙያ አጋሮቻችንን አሰባስበው በስነልቦና ግንባታው ላይ መሳተፉን ቅድሚያ ሰጡ። ሃሳባቸው ሀሳብ ሆኖ እንዳይቀር ደግሞ አጋዥ ያስፈልገናልና የተወሰኑ ሙዚቀኞች ጋር ተወያያይተው ሁሉም ፈቃደኝነታቸውን በፍፁም የአገር ፍቅርና ወኔ ጭምር አሳዩአቸው።
ከነዚህ ጥበበኞች መካከል አንዱም የዜማና ግጥም ደራሲው ተስፋ ብርሃን ነበር። እሱ ካቤናት ኢትዮጵያ እና ውብ ኢትዮጵያ የዘማች ኪነጥበብ አስተባባሪዎች በጋራ በመሆን በቀጥታ ያመሩት ወደ ኢትዮጵያ ሙዚቀኞች ማህበር ፕሬዚዳት ጋሽ ዳዊት ይፍሩ ጋር ነበር። ሃሳባቸውን ከመቀበል አልፈው ጉዳዩ በመንግስት ደረጃ እየተሰራበት መሆኑንና ኮሚቴ መቋቋሙን አብስረዋቸው ነበር።
ሁሉም ነገር በመንግስት ጥሪ ብቻ መከናወን አለበት ብለው ያላመኑት እነዚህ በጎ አሳቢ የአገር ደጀን የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች “የሙዚቃ ባለሙያዎች በራሳቸው ተነሳሽነት ሀገራቸውን የመጠበቅ ግዴታ አለባቸው” በማለት በጭንቅ ሰአት ከወሬና ከሚዲያ ፍጆታ ባለፈ የቁርጥ ቀኑ የሚለይበት ነውና ለዘመቻው ዝግጁነታቸውን አረጋገጡ። ከዚያም ጉዞአቸውን ወደ ግንባር አደረጉ የጠበብ ዘመቻቸውን ትዝታ ለዝግጅት ክፍላችን እንዲህ በጥቂቱ አጫውተውናል።
“የውጫሌ ግምባር ዘመቻ የመጀመሪያው በመሆኑ የቡድኑ አባላት ስሜት ለየት ያለ ነበር” የሚለው ደራሲው ተስፋ ብርሃን (ኢንጂነር ባንጃው) የቡድኑ አባላት ማልደው ለግዳጁ ዝግጁ ሆነው ነበር ይላል። የዘመቻው አካል የሆነው የወሎ ላልይበላ የባህል ቡድንም አብሯቸው ተጉዞ ነበር። ለልምምድ የሚሆን ጊዜ ባለመኖሩ በመንገድ ላይ ከሙዚቃ ባንዱ ጋር ለመግባባት መረጃ እየተለዋወጡ ጉዟቸውን ወደ ሰሜን አቅጣጫ ማድረጋቸውንም ያስታውሳል። በሰላሳ ኪሎ ሜትር እርቀት ላይ ከምትገኘው የሀይቅ ከተማ ጀምሮ ወታደራዊ እንቅስቃሴው ወደ ጦርነቱ ቀጣና እየገቡ እንደሆነ ያሳብቅ በማለት ሁኔታውን አስታውሶናል።
“በተዘረጋው መድረክ የማእከላዊ እዝ የተለያዩ ብርጌዶች ጋር አስደሳች ጊዜ አሳለፍን” የሚለው ደግሞ ሌላኛው አስተባባሪና አርቲስት ዮርዳኖስ አለሜ ነው። እንደ እርሱ ገለፃ በወሎ ላሊበላ የባህል ቡድኗ ድምጻዊት አለም የተጀመረው የሙዚቃ ስራ በፉካራ፣ በቀረርቶበሽለላ ታጅቦ ምድር ቁና አስክትመስል ደረስ በድምጻዊ መብሬ መንግስቴ “መውዜር አማረኝ” ፤በድምጻዊ ዱባለ መላክ”ጉዱገና”፤ በድምጻዊ አስራት ቦሰና ”ጎንደርኛ” በድምጻዊ አማረ መንበሩ “ደሴ ላይ” በድምጻዊ አየለ ጌታቸው የብሄር ብሄረሰቦች ሙዚቃ ወደ ሶስት ሰአት ለሚጠጋ ጊዜ የጎልቮ ምድር አስተናግዳው የማታውቀውን ታላቅ ጥበብ በታሪክ መዝገብ ላይ እንዳሰፈረች ይመሰክራል።
አርቲስት ዮርዳኖስ አለሜ ቀጣዩ ዘመቻቸው በደቡብ ወሎ ዞንና ሰሜን ወሎ ዞንን እንዲሁም ደቡብ ጎንደር ጋር በሚዋስኑት ወረዳዎች ላይ ያነጣጠረ እንደነበር ገልፆ። አሁን ወታደራዊ ግምባሮችን እየለመዷቸው በመምጣቱ የጥበብ ስራዎቻቸውን በማቅረብ ሰራዊቱን ለማነቃቃት እንዳልተቸገሩ ይናገራል። እንደ ወታደር የዘመቻውን ትክክለኛ ቦታ የቡድኑ አባላት ባያውቁትም “ተነሱ!” በተባሉበት ሰአት ለመነሳት የሚያስችለውን “የወትሮ ዝግጁነት” መርህ መቀበላቸውንም ይገልፃል። ወደ ዋድላ ደላንታ የሚወስደውን መንገድ ይዘው በደስታና በወኔ ተጉዘው ከወታደሩ ጋር ተቀላቅለዋል። በዘመቻው ድምጻዊ አሸብር በላይ “እኔነኝ ያለ ይሞክረኛ” በማለት ጀግነትን የሚያላብስ ሙዚቃን አቅርቧል። “እሽክም እሽክም” በሚለው ዜማዋ የምትታወቀው ድምጻዊ ማዲቱ ወዳይም “እኔም ለሀገሬ አለሁ” በማለት ተቀላቅላ ። ሌሎቹ የቡድኑ አባላትም በቂ ዝግጅት አድርገዋል።
“ጉዞውና የተደረገው ኪነ ጥበባዊ ዘመቻ ለቡድኑ እጅግ ፈታኝና መቸም ሊረሳ የማይችል ነበር” የሚለው አርቲስቱ በአንዳንድ ቦታዎች የነበረው የመንገዱ አለመመቸት ከክረምቱ ዝናብ ጋር ተደምሮ እጅግ በጣም አስቸጋሪ የሚባል የነበረ ቢሆንም የጥበብ ዘመቻውን በድል መወጣት እንደቻሉ ገልፆልናል። በቀጣይም ይህን ታሪካዊ የኪነ ጥበብ ዘመቻ እንደሚቀጥሉበት አስረግጠው “በዘመቻ ኪነ ጥበብ ሁለት” የሰሩትን ስራ በቀጣይ ሳምንት ከሌሎች የቡድን አባሎቻቸው ጋር ቀጠሮ አስይዘውልን የነበረንን ቆይታ አብቅተናል። ቸር ይግጠመን!
የዮቶር ክንድ
አዲስ ዘመን መስከረም 9/2014