አሸባሪው የህወሓት ቡድን በአገሪቱ በከፈተው መጠነ ሰፊ የሽብር ተግባር ለበርካታ ሰዎች መፈናቀል፣ ሞትና ንብረት መውደም ምክንያት እየሆነ ይገኛል። እጅግ በሚያሳዝን ሁኔታ ከትግራይ እናት ጉያ ስር በግድ የተነጠቁ ወጣቶችን ወደ እሳት እየማገደ ዳግም የስልጣን ወንበር ላይ ፊጥ ለማለት ዛሬም ድረስ የሞት ሽረት ትግል እያደረገ ነው። በየቦታው ያሰማራቸው ዲያስፖራ ተላላኪዎቹም ቡድኑን ለማዳን የማይፈነቅሉት ጉድጓድ የለም።
በተለይም እውነትን በማጣመም ነገር ሲከፋ በተበዳይነት ስሜት፣ ድል ያገኙ ሲመስላቸው ደግሞ በወራሪነት ድንፋታ ዓለምአቀፉ ማህበረሰብን እያሳቱ ነው። ይህንን እውነታም ለዓለም ለማሳወቅ ኢትዮጵያውያን ጥረት ጀምረዋል። ከዚህም ንቅናቄ አንዱ ‹‹ነጩ ደብዳቤ ለነጩ ቤተመንግስት›› የሚለው ነው። ይህ ንቅናቄ የኢትዮጵያን ሀቅ እና እውነት የአሸባሪ ቡድኑን ግፍ በግልጽ ለዓለም ለማሳወቅ ያለመ ነው። የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅትም ‹‹ዘማች ወጣት›› በሚል ርዕስ በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳይ ላይ ለወጣቶች የምክክር መድረክ አሰናድቶ ነበር።
በመድረኩ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ጌትነት ታደሰ እንደተናገሩት፤ አሁን እየተደረገ ያለው ጦርነት አገር ለማፍረስ እየሠራ ያለ ሃይልና አገርን ለማስቀጠል በሚሰራ ሃይል መካከል ነው። ይሄ ጦርነት መጀመሪያውኑ አገር ሲያፈርስ የኖረና መጀመሪያም የጥፋት ሃይል የነበረውን በአንድነት መንፈስ ድባቅ እንደሚመታ ምንም ጥርጥር የለውም። ጦርነት አራት ገፅ አለው። አንደኛው መሬት ላይ የሚካሄደው ውጊያ ነው። በዚህ ግንባር ህይወታቸውን ለመስጠት ለጥይት ፊት የቆሙ ስለ አገር፣ ስለ ፍትህ፣ ስለ ኢትዮጵያውያን የቆሙ በርካታ ወጣቶች አሉ። አሁን ባለንበት ሁኔታ ስለወጣቶቹ ማሰብ ያስፈልጋል።
ሁለተኛው የኢኮኖሚ ግንባር ነው። እንደሚታወቀው ከአርሶአደር እስከ ኢንቨስተር የአገሪቱ ልማት እንዳይቋረጥ ሌሊት ተቀን የሚሰሩ አርሶአደሮች እንዲሁም እጅግ የሚያኮሩ ባለጠጎች ያሉበት ሁኔታ አለ። ሶስተኛው ግንባር የዲፕሎማሲው ግንባር ነው። በዚህ ግንባር ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት እየተንቀሳቀሱ ሰፊ የዲሎማሲ ስራዎች እየሰሩ ይገኛሉ። አራተኛው ግንባር የሚዲያና የኮሙኒኬሽን ግንባር የሚባለው ነው። በዚህ ዘርፍ በርካታ አገር ወዳድ ህዝብ በቲውተር፣ በፌስቡክ፣ በጋዜጣና በሌሎች መንገዶች የራሳቸውን አስተዋፅኦ እያደረጉ ናቸው። በተዘጋጀው መድረክ ላይ ከነዚህ አራት ግንባሮች ወጣቱ በየትኛው ግንባር መሰለፍ እንዳለበትና የራሱን አስተዋፅኦ ማበርከት እንዳለበት አቶ ጌትነት ያመለክታሉ።
የአገር መከላከያ ሚኒስቴር ህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ኮሎኔል ጌትነት አዳነ፤ መከላከያ ወጣትን ሲያስብ ሶስት ነገሮችን አማክሎ ነው። ወጣት ሲመለምልም ስሜትን መሰረት አድርጎ ሲሆን እዘምታለሁ፣ እችላለሁ፣ የአገሪቱን ጠላት አሳፍሬ እመልሳለሁ የሚል የውስጥ ተነሳሽነት ይመለከታል። ሁለተኛው እውቀት ይታያል። እውቀት በትምህርት የሚገኝ ሲሆን ተጨማሪ እውቀት ለመሸመት ዝግጁ የሚሆን ወጣትና የዕውቀት ባለቤት ነው። ሶስተኛው ጉልበት ሲሆን ጉልበት ያለው ወጣት አባሮ የሚይዝ፣ የቆሰለ ወገንን የሚሸከም ሰው መሆን አለበት። መከላከያ ወጣቱ የአገር ዋልታና ማገር ነው ብሎ እንደሚያምን ይናገራሉ።
በወጣት እድሜ ብዙ መስራት የሚቻልበት እድሜ እንደመሆኑ ለአገሩ በወጣትነቱ ምንም ያላደረገ ሰው እድሜው እየገፋ ሲሄድ ምንም መስራት እንደማይችል ኮሎኔል ጌትነት ይጠቅሳሉ። ወጣትነት በምግባር መታረቅና በስነምግባር የታነፀ መሆን አለበት። ይህ መሆን ካልቻለ በጣም አስቸጋሪ እንደሚሆን ይገልፃሉ። ከስነ ምግባሮች ሁሉ ትልቁ የሆነው ደግሞ ሌብነትን እጅግ መፀየፍ ነው። በአሁኑ ጊዜ የሽብርተኛው ህወሓት ቡድን አመራሮች በስተርጅናቸው ሌቦች ሆነው ይገኛሉ። ጉልበተኛ ሰው ጉልበቱ ሲደክም ስራውን ሊያቆም ይችላል። ሌብነት ግን በጣም ክፉ በመሆኑ ከሚሳይል ስርቆት ወደ ሊጥ ሰርቆት የሚያሸጋግር ስለሆነ ሊታረምና ሊቆም የሚገባ ተግባር መሆኑን ያስረዳሉ።
ወጣቱ ለአገሩ ሲሰራ ሌብነትን በማውገዝ መሆን አለበት። ሁሉም በሙሉ ልብ ለአገሩ ለመስራት መንቀሳቀስ አለበት። በወጣትነት እድሜ የሚገኝ ንቃት ያስፈልገዋል። ለሁሉም ጉዳይ ንቁ ሆኖ መንቀሳቀስ ያስፈልጋል። ወጣቱ በተደራጀ መልኩ መንቀሳቀስ ያስፈልጋል። ከመደራጀት በፊት ግን ቅድሚያ የሚሰጠው ለምን ዓላማ መደራጀት ያስፈልጋል የሚለው ጉዳይ ነው። አገርን ለመጠበቅ ነቅቶ መደራጀት የግድ ነው። ለዚህ ደግሞ አስፈላጊ ስልጠና መውሰድ አስፈላጊ ነው። ከነዚህ በኋላ ወደ ስምሪት ይደረጋል ማለት ነው። ስራው የሚመገምበት ሁኔታም መፈጠር እንዳለበት ኮሎኔል ጌትነት ያመለክታሉ።
ኮሎኔል ጌትነት ‹‹ለሚፈጠሩ እንቅፋቶች መፍቻ ቁልፍ ነገሮች አሉ። ይህ ከተገኙ ነገሮች ማወቅ ይቻላል። ስራዎች በሚሰሩበት ወቅት ስህተቶች ይኖራሉ። ከስህተት እራስን የማረም ጥበብ አለው። ማንም ስህተትን ሳይናገር እራስን የማረም ጥበብ አለው። ማንም መካሪ ሳያስፈልግ እራስን ማረም የሚቻልባቸው ብዙ መንዶች አሉ። ሌላው ደግሞ ይቅርታ የመጠየቅ ልምድ ማዳበር ያስፈልጋል። ጉልበትና እውቀት የሚባክነው ለአገሪቱ ጠላት ብቻ ነው። አገሪቱን ለማፍረስ የሚነሳ ካለ ይሄ ታጋሽነት ቁጣ ሆኖ ይነሳል። ስለዚህ እርበርስ ከሆነ ግን የመተራረም ባህል ሊፈታ ይገባል። ›› ይላሉ።
አሁን እየተደረገ ያለው ዘመቻ በሁሉም መስክ ቢሆንም አሁን ፈተና እየሆነ ያለው ወሬ ነው። ሰዎች የሚኖሩበትን ከተማ ለቀው እየሄዱ ያሉት በወሬ ነው። በሁሉም ቦታዎች ‹‹መጡ›› የሚል ወሬ በማስወራት ህብረተሰቡ እንዲሸበር ይደረጋል። የቤቶቹ ባለቤቶች በወሬ ፈርተው ሲወጡ ሌባና ዘራፊው ሃይል ገብቶ ይዘርፋል። ይህን ወሬ በበጎ ነገር መቀየር የሚችል ሃይል ተሰባስቦ ይገኛል። ይህ ታላቅ ድል ነው። ወጣቱ አገሩን የሚያገለግልበት አጋጣሚ በማግኘቱ ሊጠቀምበት እንደሚገባ ያሳስባሉ።
የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት የሥራ አመራር ቦርድ አባል ሙዓዘ ጥበባት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት እንደሚናገሩት፤ ሁሉም ሰው በቀጣይ ስራዎችን በሚሰራበት ወቅት ብዙ ነገሮችን ማስታወስ መቻል አለበት። የመጀመሪያው ይህ ወቅት ያልፋል። አሁን አገሪቱ ያለችበት ሁኔታ እንደሚያልፍ መታወቅ አለበት። ኢትዮጵያ ባለችበት ምንም ሳትሆን ትቀጥላለች። አሁን ያለው ሁኔታ በአግባቡ መፃፍ አለበት። ሁሉም ነገር አልፎ ታሪክ ተከትቦ ከተቀመጠ አጠቃላይ የሆነውን መረዳት ያስችላል። ሁሉም ወጣት ታሪክ ለመስራት መዘጋጀት አለበት። ማንኛውም ሰው በአካል እያለ የሰራው ስራ ነው ታሪክ ሆኖ የሚቀመጥለት።
በጣሊያን ወረራ ጊዜ ሰዎች የማያልፍ መስሏቸው ባንዳ ሆነዋል፤ በአምስት ዓመት ውስጥ ውጊያው ሲያልፍ ግን ትዝብት ነው ያተረፉት፤ የባንዳነት ታሪኩም ተጽፎ ተቀምጧል፤ ይሄ አሁን ያለንበት ክስተትም ይጻፋል በጣሊያን ወረራ ጊዜ አባቶቻቸው የዘመቱ በኩራትይናገራሉ፤ አባታቸው ባንዳ የነበሩ ግን አንገታቸውን ደፍተው ኖረዋል። የአባቶቻቸውን የባንዳነት ታሪክ የያዘ መጽሐፍ ሲያገኙ ይሸማቀቃሉ። የአባቶቻቸውና አያቶቻቸው ፎቶ እንዳይታይ ያጠፉታል። የእገሌ ልጅ ነኝ ላለማለት፤ ታሪኩን ደብቀው በአጎታቸው ወይም በአክስታቸው ሌላ ዘር ይቆጥራሉ። አባት አያቶቻቸው የዘመቱ፣ ለአገራቸው የሰሩ ግን ደረታቸውን ነፍተው እንደሚሄዱ ሙዓዘ ጥበባት ዲያቆን ዳንኤል ይጠቁማሉ።
‹‹ድሮ ታሪክ የሚጻፈው ብራና ተፍቆ፣ ቀለም ተበጥብጦ ነበር፤ አሁን ግን በየሰከንዱ ያለ ክስተት በፍጥነት ይጻፋል። የመገኘት ዕድሉም ቀላል ነው። ነገ በዚህ ታሪክ የሚኮሩ ልጆችን ለመፍጠር የሚያኮራ ታሪክ ማስቀመጥ ይገባል›› ሲሉ የሚናሩት ሙዓዘ ጥበባት ዲያቆን ዳንኤል፤ ይህ አስከፊ ወቅት ያልፋል፤ በዚህ በሚያልፍ ወቅት የማያልፍ የባንዳነት ጥቁር ታሪክ መፃፍ የለበትም። ኢትዮጵያ ከዚህም የከፉ ችግሮችን አሳልፋለች በወቅቱ የከዱ ግን አሳፋሪ ታሪክ ሰርተው ዛሬ እያፈሩ ነው፤ በመሆኑም ወጣቱ ነገ በኩራት የሚናገረው ታሪክ መስራት እንዳለበት ያመለክታሉ።
አሁን ያለው ችግር እንኳን ተፈጠረ የሚያስብል አንድነት ታይቷል። በተፈጠረው ክስተት ህዝባዊ አንድነት፣ የአገር ፍቅር ስሜት፣ መከላከያን የመቀላቀልና የመውደድ ወኔዎች ታይተዋል፤ ይህም ለጥፋት ቡድኑ ዓላማ መክሸፍ ምክንያት ሆኗል። በኢትዮጵያ ህዝብ እየተከፈለ ያለው መስዋዕትነት በአገሪቱ ሰንደቅ ዓላማ ይመሰላል። ቀዩ መስዋዕትነት ግንባር ድረስ ሄደው ሊዋጉ መከላከያን የተቀላቀሉ አሉ፤ አረንጓዴው መስዋዕትነት አነስተኛ ገቢ ካላቸው ሰዎች ጀምሮ ለመከላከያ የኢኮኖሚ ድጋፍ ተደርጓል፤ የንግዱም የአርሶ አደሩም ማህበረሰብ ለአገሩ ኢኮኖሚ እየሰራ ነው። ቢጫው መስዋዕትነት ደግሞ በሁለቱም በኩል ያለ ነው። ከጦርነቱ በኋላ የአገሪቱ ኢኮኖሚ እንዳይጎዳ አረንጓዴው መስዋዕትነት ተጠናክሮ መቀጠል እንደሚኖርበትም ሙዓዘ ጥበባት ዲያቆን ዳንኤል አሳስበዋል።
በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማዕከል አስተባባሪ ሚኒስትር ዶክተር ቢቂላ ሁሬሳ በመድረኩ ላይ እንደተናሩት፤ ኢትዮጵያውያን ያጋጠማቸውን ፈተናዎች እንደ መልካም አጋጣሚ ተጠቅመውበታል። የህወሓት የሽብር ቡድን አገር ሊበታትን የነበረውን የጥፋት ዕቅድ አምክነውታል። አሸባሪው የህወሓት የጥፋ ቡድን ከምስረታው ጀምሮ ኢትዮጵያን ለማፍረስ የተለያዩ አፍራሽ ዘዴዎችን ሲጠቀም የኖረ ነው። በህዝቦች መካከል አለመተማመንን በመፍጠር በምስራቅ አፍሪካ ጠንካራ ኢትዮጵያ እንዳትኖር ሲሰራ ቆይቷል። ዳሩ ግን የጋለ ወኔ እና የአገር ፍቅር ስሜት ያላቸው ወጣት ኢትዮጵያውያን ይህን እኩይ ዓላማውን ሁሉ አክሽፈዋል።
የኢትዮጵያውያን የአገር ፍቅር ስሜት፣ የአልደፈርም ባይነት ወኔ በዚህ ፈታኝ ወቅት ታይቷል ያሉት ዶክተር ቢቂላ፤ ወጣቶች ወደ መከላከያ ሰራዊት ለመቀላቀል ያሳዩት ጀግነት የሚደነቅና በቤታቸው ውስጥ ምንም ንብረት የሌላቸው እናቶች ሳይቀር ለአገራቸው አንድነት ካላቸው ጸኑ ፍላጎት አኳያ ለጀግናው መከላከያ ሰራዊት ድጋፍ እያደረጉ መሆናቸውን ዶክተር ቢቂላ ይናገራሉ።
መርድ ክፍሉ
አዲስ ዘመን መስከረም 7/2014