አገር ሊመሰረት የሚችለው ሰዎች ተስማምተው በአንድ ህግ ስር ለመተዳደር ሲወስኑ ነው። በአለም ላይ የሚገኙ ሁሉም አገራት በሰዎች ስምምነት የተመሰረተ ቢሆንም የሀሳብ ብልጫ ለማግኘት ግን ጦርነትም አድርገዋል። ለዚህ ጥሩ ምሳሌ ልትሆን የምትችለው ኢትዮጵያ ናት። ኢትዮጵያ በተለያዩ ጊዜያት ያስተዳደሯት መንግስታት ሀሳባቸውን ለማስፋት ጦርነት አድርገዋል። ስለዚህ ኢትዮጵያን ለመመስረት ከሀሳብ ስምምነት ውጪ ጦርነት መካሄዱ መዘንጋት የለበትም።
በሌላ በኩል አገርን ለመመስረት ለመኖሪያነት ምቹ የሆነ በመልከዓ ምድር መምረጥና በዛም መስፈር የግድ ብሏል። ሁሉም አገራት አንድ ወጥ የሆነ አሰፋፈር ቢኖራቸውም ለኑሮ ምቹ የሆነ መልከዓ ምድር ለማግኘት ከጎረቤት አገራት ጋር ረጅም ጊዜ የፈጀ ጦርነት ያደርጋሉ። በዚህም ግዛታቸውን ማስፋፋት ችለዋል። በተጨማሪም ጉልበታቸውን አጠናክረው ቅኝ የሚገዙትን አገር ፍለጋ የተለያዩ አህጉራትንም ይዞራሉ።
ሰው ከፍ ያለ አስተሳሰብ የሚያራምድ አእምሮ ባለቤት በመሆኑ ምክንያት በርካታ አስገራሚ የሆኑ ስራዎችን እንዲያከናውን አድርጎታል። ይህ ከፍ ያለ አስተሳሰብ ከሚገለፅባቸው መንገዶች አንዱ ደግሞ ለሰዎች በምናደርገው ድጋፍ ነው። በአገራችን ሰዎችን መርዳት እንደ ጠንካራ ባህል የሚወሰድ በጎ ተግባር ነው። በበዓላት ወቅት ከመንግስት ጀምሮ አቅም ለሌላቸው ሰዎች ድጋፍ ሲደረግ ይስዋላል። ለዚህ ደግሞ ያለፈውን የትንሳኤ በዓል ማንሳት በቂ ነው። የመንግስት ተቋማት ይሁን ሌሎች ግለሰቦች በዓላትን ብቻ በመጠበቅ ስጦታ መስጠትን እንደ ባህል ይዘውታል። ድጋፍ ማድረጉ ጥሩ ተግባር ቢሆንም ሁልጊዜ አለመቀጠሉ ተረጂውን የከፋ ችግር ውስጥ ይከተዋል። ይሁን እንጂ እንዲህ አይነት በጎ ተግባራት አሁን አሁን ከተወሰኑ ምክንያቶች ጋር ብቻ እየተያያዙ በሌላ ጊዜ የሚጠፉበት ሁኔታ ይስተዋላል።
ከመረጃዎች መገንዘብ እንደሚቻለው ዓለማችን በየቀኑ ለመኖር የማትመች እያደረጓት ያሉ ፈተናዎቿ በቁጥር እየጨመሩ ናቸው። እነዚህም ችግሮች መፍትሔ እንዲያገኙ ደግሞ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ከሚያደርጓቸው ድጋፎች በተጨማሪ የእያንዳንዱን የምድር ነዋሪ የበጎ ፈቃደኝነት አገልግሎት የሚሹ ሆነዋል። ኢትዮጵያ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የመስጠት ባህል የነበራትና በፍጹም ወንድማማችነት ዜጎች የሚኖሩባት ችግራቸውን በጋራ በመተባበር የሚያሳልፉባት ሀገር ነች። ይህ በመስጠት የሚገለጸው በጎ ፈቃደኝነት የሀገሩ ባህል ነው። ልዩ ልዩ ዓይነት ልማድና ወግም ነበር። ሲወልድ የግምዶ፣ ሲያዝን የዝን ብሎ ከመስጠት ጀምሮ ሲዘምት የስንቅ፣ ሲመለስ የደስታ፣ ሲሻር የሹመት አይደንግጥና ሲሾም የምስራች ብሎ እስከመስጠትም የረቀቀ ነው። ከነዚህ ሁኔታዎች አንፃር በመመልከት በአሁኑ ወቅት በተለያዩ ቦታዎች የበጎ አድራጎት ማህበራት እየተቋቋሙ ይገኛሉ።
የሚቋቋሙ በጎ አድራጎት ማህበራት የሚኖሩበት ከተማ አስተዳደር አስፈላጊ ድጋፍ ሊያደርግላቸው ያስፈልጋል። ነገር ግን በአንዳንድ አካባቢዎች የሚገኙ ማህበራት በድጋፍ እጦት ምክንያት ያሰቡትን ያክል እየሰሩ አይደለም። ለዛሬ የምንመለከተው በስልጤ ዞን በወራቤ ከተማ ስለሚገኘው የበረካ የልማና የበጎ አድራጎት ማህበር ነው። ማህበሩ የተመሰረተው በቅርብ ጊዜ ውስጥ ቢሆንም ድጋፍ በማድረግና የስራ እድሎች በመፍጠር ጥሩ የሚባል እንቅስቃሴ እያደረገ ይገኛል። ስለአጠቃላይ የስራ እንቅስቃሴው ከማህበሩ ሰብሳቢ አቶ ጅብሪል ኢብራሂም ጋር ቆይታ አድርገናል። መልካም ንባብ።
የማህበሩ አመሰራረት
ማህበሩ 2011 ዓ.ም ጥር ወር ላይ የተመሰረተ ሲሆን በስልጤ ዞን እውቅና አግኝቶ መንቀሳቀስ ጀመረ። በዋናነት ማህበሩ እንዲመሰረት ያደረገው በስልጤ ዞን አካባቢ የሚታዩ ችግሮችን ለመፍታት ነው። ሁሉም ችግር በመንግስት የሚፈታ ስለማይሆን ማህበሩ በልማትና ለበጎ አድራጎት ስራ እንዲደራጅ ተደርጓል። ማህበሩ በወራቤ ከተማ ውስጥ አባላትን በማፍረት ከአካባቢው ገንዘብ በመሰብሰብ የመረዳዳት ባህል ለማሳደግ አላማ አድርጎ የተመሰረተ ማህበር ነው። በማህበሩ ውስጥ መንግስት ሰራተኛው፣ ነጋዴውና ሌሎች የማህበረሰቡ ክፍሎቸ በአባልነት እንዲካተቱ ተደርጓል።
ማህበሩ ያከናወናቸው ተግባራት
ማህበሩ ሲመሰረት የልማትና የበጎ አድራጎት ስራ ለማከናወን ነው። ልማት ሲባል በትምህርት ላይና በጤና ጉዳዮች ላይ ትኩረት አድርጎ ይሰራል። በተጨማሪም ህብረተሰቡን ሊጠቅሙ የሚችሉ የልማት ስራዎች ላይ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል። በአረጋውያንና በአካል ጉዳተኞች ላይ ማህበሩ ድጋፍ የሚያደርግ ሲሆን ወላጅ የሌላቸው ህፃናትን መደገፍ ማህበሩ ከሚያከናውናቸው ስራዎች ውስጥ ይካተታል። ማህበሩ ህጋዊ እውቅና አግኝቶ ከተመሰረተ በኋላ ወላጅ የሌላቸውንና አቅም የሌላቸውን ልጆች የመማሪያ ቁሳቁስ የመደገፍ ስራ የተከናወነ ሲሆን አስር ሺህ ደብተርና የመማሪያ ቁሳቁስ ከማህበረሰቡ፣ ከልማት ድርጅቶችና ማህበሩ ከራሱ ጨምሮ ድጋፍ አድርጓል። በጤናው ዘርፍ ከፍለው መታከም ለማይችሉ አቅመ ደካማዎች የጤና መድህን ክፍያ እየተከፈለላቸው ይገኛል። በሌላም በኩል ከፍተኛ ህክምና ለሚያስፈልጋቸው ማህበሩ አቅሙ በቻለው ልክ እያሳከመ ይገኛል።
አረጋውያንን ከመንከባከብና ከመደገፍ አንፃር
ደግሞ ምንም ገቢ የሌላቸውን የመደገፍ ሁኔታዎች አሉ። ማህበሩ ሁሌም ምግብ መመገብ ብቻ ሳይሆን በቋሚነት ችግረኛ ሰዎች ካሉበት ሁኔታ እንዲወጡ ማህበሩ ስራዎችን አከናውኗል። ሰውን በየጊዜው ከመርዳት ይልቅ ቋሚ የሆነ የስራ እድል ፈጥሮ ሰውን ማደራጀት ላይ እየተሰራ ይገኛል። በዚህ መሰረት በሁለት አመታት 82 ሺህ ብር በመመደብ በስራ እድል ፈጠራ ላይ ስራዎች ተከናውነዋል። እንጀራ ጋግሮ የመሸጥ፣ ዳቦ የማከፋፈል፤ ሳንቡሳ ጠብሶ መሸጥ፣ እንቁላል ማከፋፈልና ሌሎች ስራዎች ስራ ፈላጊዎች እንዲሰሩ እየተደረገ ነው። ልጆቻቸውን ለመመገብ አቅም የሌላቸውን ወላጆች ዘላቂ የሆነ ስራ በማስያዝ እራሳቸውን እንዲችሉ ተደርጓል።
በኮቪድ ወረርሽኝ ወቅት በሽታውን ለመከላከል የሳኒታይዘርና የእጅ መታጠቢያ ሳሙና የተሰጠ ሲሆን ሰው የሚበዛባቸው ቦታዎች ላይ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎች ተከናውነዋል። በሃይማኖት ተቋማትና በሌሎች ቦታዎች ለህብረተሰቡ ግንዛቤ የመስጠት ስራ ተከናውኗል። በግንዛቤ ስራውም ብዛት ያለው ሰው ተደራሽ እንዲሆን ተደርጓል። አቅም ለሌላቸው ሰዎች የአስቤዛ ድጋፍ ተደርጎላቸዋል። ማህበሩ በዋነኝነት የገንዘብ ምንጩ የአባላት መዋጮ ነው። በተጨማሪም ማህበሩን ከሚደግፉ ድርጅቶች ከሚገኝ ድጋፍ አስፈላጊ ስራዎችን እያከናወነ ይገኛል። ለአቅመ ደካማዎች ቤት እድሳት ተከናውኗል። በሌላ በኩልም የቆርቆሮና ሌሎች ለቤት ግንባታ የሚውሉ ቁሳቁሶችን ማህበሩ ድጋፍ እያደረገ ይገኛል።
በከተማው በድንገት በተከሰተው የእሳት አደጋ ምክንያት ለተጎዱ ወገኖች የአልባሳትና የዱቄት እንዲሁም ሌሎች ቁሳቁሶች ተሰጥተዋል። ቤታቸው ለፈረሰባቸው ሰዎች የቤት ጥገና እንዲከናወን ተደርጓል። በስራ እድል ፈጠራው ደግሞ የፍየል እርባታ ለአስር ሰው፣ ለአንድ
ወጣት በእጅ የሚገፋ ጋሪ፣ እንጀራ በመሸጥ ስራ አንድ እናት እንድትሰራ ተደርጓል፣ ዳቦና ሳንቡሳ ጋግሮ የመሸጥ ስራ ለአንድ እናት እንድትሰራ ተደርጓል። እንዲሁም የእንቁላል ማከፋፈል ስራዎች እንዲመቻቹ ተደርጓል። ባለፈው አመት በተከሰተ የጎርፍ አደጋ ምክንያት ለተጎዱ ዜጎች ድጋፍ ተደርጓል።
የህብረተሰቡ አቀባበል
የአካባቢው ህብረተሰብና የከተማ አስተዳደሩ አስፈላጊ ድጋፍ ለማህበሩ እያደረጉ ይገኛሉ። ከከተማና ከዞን አስተዳደሩ ጋር ጥሩ በሆነ ስሜት ስራዎች እየተሰሩ ሲሆን አስተዳደሩ አስፈላጊ የሚባሉ ድጋፎችን አድርጓል። ስራውም መሬት ላይ የሚታይ ተጨባጭ የሆነ ስራ ነው። የከተማ አስተዳደሩ ለአረጋውያን፣ ለህፃናትና ለአካል ጉዳተኞች አስፈላጊውን ድጋፍ ከተማ አስተዳደሩ እያደረገ ይገኛል። ህብረተሰቡ የማህበሩን ስራ ከመደገፍ አልፎ አስፈላጊ በሚሆኑ ቦታዎች ላይ ተሳትፎ ያደርጋል። በተወሰነ መልኩ የገንዘብ ምንጭ ከህብረተሰቡ የሚገኝ በመሆኑ ማህበሩ ከህብረተሰቡ ጋር ተቀናጅቶ እየተንቀሳቀሰ ነው።
ማህበሩን ያጋጠሙ ችግሮች
ማህበሩ እውቅና አግኝቶ መንቀሳቀስ ከጀመረ በኋላ በርካታ ችግሮች አጋጥመውታል። ማህበሩ ስራዎችን ለማከናወን እቅድ አስቀምጦ በበጀት እጥረት ምክንያት የታሰበውን ያክል መንቀሳቀስ አልቻለም። በቂ የሆነ የገንዘብ ፍሰት ባለመኖሩ ሰፋፊ እቅዶችን ይዞ መስራት አልተቻለም። ሌላው ደግሞ ድጋፍ የሚደረግላቸው ሰዎች ሁሌም እየተረዱ መኖር መፈለጋቸው ችግር እየፈጠረ ይገኛል። ሰዎቹ ላይ የጥገኛነት መንፈስ እየፈጠረ ነው። መቶ ሰው ለመርዳት ሲፈለግ ከአምስት መቶ በላይ ሰዎች የመምጣት ሁኔታዎች አሉ። ይህን ለማስተናገድ ማህበሩ አቅም የለውም። ይህን ለመፍታት ሰዎች በቋሚነት የሚቋቋሙበትን ሁኔታ መፍጠር አስፈላጊ ነው። ቢያንስ በአመት አምስት ሰው ከድህነት ማውጣት ከተቻለ ችግሩ ሊቃለል ይችላል።
ማህበሩ ቋሚ የገቢ ምንጭ ለመፍጠር ስራዎች ያስፈልጋሉ። ይህን አስተባብሮ መስራት ላይ ክፍተቶች ይስተዋላሉ። ድጋፍ ከሚያደርጉ ድርጅቶች እርዳታ ለማግኘት ከፍተኛ የሆነ ልምድ የሚያስፈልግ ሲሆን ማህበሩ ለዛ የሚሆን አቅም አላዳበረም። ድጋፎችን ለማግኘት የሰራ እንቅስቃሴ ከፍተኛ መሆን አለበት። ሌላው ደግሞ ከረጂ ድርጅት ድጋፍ ለማግኘት ፈቃድ ከሲቪል ማህበረሰብ ኤጀንሲ ማግኘት የግድ ይላል። ማህበሩ ፈቃዱን ያገኘው በዞን ደረጃ በመሆኑ ስራውን እንዲወሰን አድርጎታል።
የማህበሩ ቀጣይ እቅድ
ማህበሩ በቀጣይ በርካታ ስራዎችን ለማከናወን እቅድ ይዞ እየተንቀሳቀሰ ሲሆን የአረንጓዴ ልማት ስዎችን ለማሳደግና ህብረተሰቡን ለማሳተፍ እቅድ ተቀምጧል። በዚህ ስራ አረንጓዴ ቦታዎችን የማልማት ስራዎች ተሰርተዋል። በስራ እድል ፈጠራ ዙሪያ ደግሞ ከማይክሮ ፋይናንስ ጋር በመቀናጀት ቋሚ የሆነ የስራ እድል ለመፍጠር እንዲሁም ወላጅ አልባ ልጆችን በመጪው የትምህርት ዘመን የሚሆኑ የመማሪያ ቁሳቁሶች እየተሰባሰቡ ይገኛሉ። አቅም ለሌላቸው ልጆችና ለወላጅ አልባ ልጆች አስፈላውን ለማሟላት ስራዎች ተጀምረዋል። በጤናው ዘርፍ ደግሞ የጤና መድህን የመክፈል አቅም የሌላቸውን ሰዎች ለመደገፍ እቅድ ተቀምጧል። በገንዘብ እጦት ምክንያት መታከም ሳይችሉ የሚሞቱ ሰዎችን ለመታደግ ታስቧል። ለአቅመ ደካማዎችና ለወላጅ አልባ ልጆች በየጊዜው የአስቤዛ ድጋፍ ይደረጋል። ለአካል ጉዳተኞችም በተመሳሳይ ድጋፍ የሚደረግ ይሆናል። በቀጣይ ፕሮጀክት ተቀርፀው ፋይናንስ የማፈላለግ ስራ ለማከናወን ታስቧል። የፋይናንስ አቅምን ለማሳደግ የተለያዩ ስራዎችን ለማከናወን ታቅዷል።
መርድ ክፍሉ
አዲስ ዘመን መስከረም 7/2014