የኮቪድ 19 ወረርሽኝ መከሰት ፤ በግብይት ሂደቱ ላይ የህገ ወጥ ደላሎች ጣልቃ መግባት፣ በአሁኑ ወቅት መንግስት እያደረገ ያለውን የህልውና ዘመቻ ተገን በማድረግ አንዳንድ ነጋዴዎች የኢኮኖሚ አሻጥር በመፍጠር በሸማቹ ማህበረሰብ ላይ ኢኮኖሚያዊ ጫና በመፍጠር ለኑሮ ውድነቱ መባባስ ምክንያት መሆን ችለዋል፡፡ በነዚህ ምክንያቶች የተነሳ መሰረታዊ ከሚባሉ የምግብ ፍጆታዎች ጀምሮ በተለያዩ ምርቶች ላይ ከፍተኛ የሚባል የዋጋ ጭማሪ መታየት ችሏል።
በህዝቡ ዘንድ በተደጋጋሚ ሲሰማ የነበረውን የዋጋ ንረትን ለመቆጣጠር ብሎም በህገወጦች ላይ እርምጃ ለመውሰድ ከፌዴራል ፖሊስ እና ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየሰራ መሆኑን የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር በያዝነው ሳምንት ማሳወቁም አይዘነጋም።
በቅርብ ጊዜም መንግስት እንደ ስንዴ፣ ዘይት፣ ስኳር እና ሩዝ ያሉ ምግቦች ከቀረጥ ነጻ እንዲሆኑ የመወሰኑ ዜና ሲሰማ በኑሮ ውድነት ጭንቀት በመቀነስ በአንጻሩም ቢሆን ህብረተሰቡን እፎይታ እንዲያገኙ ማድረግ የቻለ ውሳኔ ነው። ከነዚህ በተጨማሪም እንደ ፓስታ፣ መካሮኒ እና እንቁላል ያሉ ምግቦች ላይ ደግሞ ተጨማሪ እሴት ታክስ የተነሳላቸው ምግቦች መሆናቸውም ሚኒስቴሩ መግለጹም የሚታወስ ነው። ውሳኔውን ማድረግ ያስፈለገበት ምክንያትም የዋጋ ንረት በህብረተሰቡ ላይ የሚያሳድረውን ጫና ለመቀነስ ከላይ የጠቀስናቸው ምርቶች ከቀረጥ ነጻ ሆነው እና ከተጨማሪ እሴት ታክስ ነጻ ሆነው እንዲገቡ ተወስኗል።
በዚህ ጠይቁልኝ በሚለው አምድ በተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች የሚነሱ ጥያቄዎችን የምናስተናግድበት ሲሆን በዛሬው አምዳችንም አንድ ጠያቂያችን የጠየቁትን ጥያቄና ለጥያቄያቸውም ምላሽ ይዘን ቀርበናል፡፡ ለመሆኑ ከታክስ ነጻ ሆነው እንዲገቡ የተደረጉ ምርቶች ከመቼ ጀምሮ ነው ተግባራዊ የሚሆነው? በአንዳንድ ምርቶች ላይ የተወሰነ ቅናሽ ይኑር እንጂ ሙሉ በሙሉ ያልቀነሰበት ምክንያቱ ምንድነው? ብላችሁ ጠይቁልን ባሉን መሠረት ጉዳዩ የሚመለከተውን የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴርን ጠይቀን ምላሽ ይዘን ቀርበናል።
በንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር ወይዘሮ አበባ ታመነ እንደሚሉት፤ መንግስት በቅርብ ጊዜ ውስጥ በዘይትና በሌሎች ምርቶች ላይ ከቀረጥ ነጻ ሆነው እንዲገቡ የተደረበት ምክንያት ሲያስረዱ ፤ ዋጋውን ለማረጋጋት የኑሮ ውድነቱ ላይ ለውጥ ለማምጣት እና የኢኮኖሚ አሻጥሩን ለመቀልበስ እንደሆነ ተናግረዋል። ከዚህ በተጨማሪም የኮቪድ 19 ወረርሽኝ የፈጠረውን የንግድ መቀዛቀዝ ለማነቃቃት የታለመ እና አስመጪዎችንም በማበረታታት የአቅርቦት ችግሩን ለመፍታት እንደሆነም አስታውሰዋል።
ውሳኔው ተግራዊ የሚሆነው ከመቼ ጀምሮ ነው? ለሚለው ጥያቄ ምላሽ የሰጡት ወይዘሮ አበባ፤ ይህ ውሳኔ ከተወሰነ ጀምሮ ተግባራዊ ይሆናል በማለት ምላሽ ሰጥተዋል። ምንም እንኳን ውሳኔው ከተሰጠ አጭር ጊዜ በመሆኑ ይህን ያህል ምርት ገባ ብሎ ለመናገር አያስደርፍርም ያሉት ዳይሬክተሯ፤ በውሳኔው ግን ተስፋ ሰጪ ለውጦች መገኘታቸውን አስረድተዋል።
በአሁኑ ወቅት ከታክስ ነጻ ሆነው እንዲገቡ የተወሰነባቸው ምርቶች ላይ የዋጋ ቅናሽ ቢኖርም ሙሉ በሙሉ ለምን አልተቀረፈም ለሚለው ጥያቄም ፤ ውሳኔው የቅርብ ጊዜ ስለሆነ ምርቶቹን ለማስገባት የባንክና መሰል ሂደቶች መሟላት ስላለባቸው ጊዜ ያስፈልጋል ባይ ናቸው። ይህ ከሆነ በኋላ ግን ምርቶቹ ከቀረጥ ነጻ ሆነው ስለሚገቡ በምርቶቹ ላይ የዋጋ ቅናሽ እንደሚኖረው ወይዘሮ አበባ ምላሽ ሰጥተዋል።
ከዚህ በተጓዳኝም በአሁኑ ወቅት የዋጋ ንረቱን ለመቆጣጠር የቁጥጥር ሥራዎች ተጠናክረው በመሠራት ላይ እንደሆነ የገለጹት ወይዘሮ አበባ፤ የተቋቋመው ግብረ ኃይልም ይሁን ሌሎች ባለሙያዎችም የህብረተሰቡን ችግር ለመፍታት እየሰሩ መሆናቸውን አስታውቀዋል። ወይዘሮ አበባ እንደሚሉት በተለይም ደግሞ ፤ ሕገወጥ ነጋዴዎችን እንዲሁም ያለአግባብ የዋጋ ጭማሪ እያደረጉ ባሉ ነጋዴዎች ላይ እርምጃ እየተወሰደባቸው ነው ሲሉም ተናግረዋል።
ግብረ ኃይሉ በአዲስ አበባ ብቻም ሳይሆን በተለያዩ ክልሎች ላይ የዋጋ ጭማሪውን ለመቆጣጠርና ለመከላከል እንቅስቃሴ እያደረገ እንደሚገኝ የገለጹት ዳይሬክተሯ፤ ከዚህ በተጨማሪም ከነጋዴው ማህበረሰብ፣ ከሸማቾች ከአስመጪዎች ጋር ውይይት በማድረግ መግባባቶች መፈጠራቸውንም ያስረዳሉ።
እንደ ዳይሬክተሯ ገለጻ፤ ቅንጅታዊ አሠራሩም በአሁን ሰዓት በተሻለ መልኩ እየተሠራ እንደሆነ በመጠቆም፤ ሸማቹም አምራቹም ይህንን ጊዜ በጋራ ለማለፍ በቅንጅት ለመሥራት ከስምምነት ላይ ተደርሷል ብለዋል።
የዝግጅት ክፍሉም በአሁኑ ወቅት ከታክስ ነጻእንዲገቡ እና የተጨማሪ እሴት ታክስ የተነሳላቸው ምርቶች ወደ አገር ውስጥ እስኪገቡ ድረስ ሸማቾች በዋጋ ንረት እንዳይፈተኑ ብሎም ኢኮኖሚያዊ አሻጥሩ እንዳይስፋፋ ምን እየሰራችሁ ነው ስንል ለዳይሬክተሯ ጥያቄ አነስቷል። ዳይሬክተሯም ህገወጥ ነጋዴዎችን ከማጋለጥ ጎንለጎን እርምጃ መውሰድና እንዲሁም የኑሮ ውድነቱን ሊያረጋጉ የሚችሉን መፍትሔዎች ለማምጣት ስትራቴጂ ነድፎ እንደሚሰራ ተናግረዋል።
ወይዘሮ አበባ አክለው ይህ ችግር የሚፈታው በመንግስት ብቻ ሳይሆን ህብረተሰቡ የነቃ ተሳትፎ ማድረግ ሲቻል እንደሆነ በመግለጽ፤ ህገ ወጥ ነጋዴዎች ምርቶችን ሲደብቁም ሆነ ዋጋ ሲጨምሩ ሸማቹ ህብረተሰብ ይህ እንዴት ጨመረ? ለምን ጨመረ ? ብሎ ቆም ብሎ በመጠየቅ ህገወጥ ተግባራት ሲያጋጥሙት በመጠቆም ማጋለጥ ይኖርበታል ብለዋል።
ከዚህ በተጨማሪም አምራቹ ደግሞ በኃላፊነት ሸማቹ ማህበረሰብ የራሱ ወገን መሆኑን ተገንዝቦ አላግባብ ትርፍ ከማትረፍ ይልቅ ሳይከስር በመጠኑ ቢያተርፍና ቢሸጥ ይመከራል። እንዲሁም ቁጥጥር የሚያደርጉ አካላትም እንደዚሁ የተሰጣቸውን ኃላፊነት ሊወጡ ይገባል በማለት መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
እየሩስ ተስፋዬ
አዲስ ዘመን መስከረም 7/2014