ወዳጆቼ! እንደምን ከረማችሁ? እንኳን ለአዲሱ ዓመት በሰላም፤ በጤና አደረሳችሁ። አዲስ ዓመት ሲመጣ ከማይረሱት ነገሮች ውስጥ አንዱ እቅድ ነው። ሰዎች በዓመት ውስጥ ለማከናወን ያሰቡትን ውጥን በእቅድ መዝገብ ላይ ያሰፍሩታል። በአዲሱ ዓመት ይህንን አደርጋለሁ፤ ይህንን ደግሞ አላደርግም በማለት የጊዜ ቅደም ተከተል ይሰጡታል። እቅዳቸውን በመዝገብ ሳያሰፈሩ በአእምሮ መዝገብ አኑረው ለመፈጸም ቃል የሚገቡ እንዳሉ ሁሉ፤ ‹‹በቃል ያለ ይረሳል በጽሑፍ ያለ ይወረሳል›› ያሉት ደግሞ በጽሑፍ ያሰፍሩታል። ያም ሆነ ይህ ዞሮ ዞሮ ዋናው ጉዳይ እቅድ መታቀዱ ነው።
ታዲያ እቅድ አስፈላጊ የሚሆነው ሰዎች በፕሮግራም ተመርተው ካሰቡበት ለመድረስ የሚያደርጉትን ጥረት የሚያግዝ ስለሆነ ነው። እቅድ ለሰዎች ከሚሰጠው ጥቅም ባሻገር ለሀገርና ለዜጎች ጠቃሚ የእድገት መሠረት የሚሆን፣ ለነገ የተስፋ ብርሃን የሚፈንጥቅ መሆን አለበት። ዛሬ በእቅድ ዙሪያ በዚህ መልኩ እንድሽከረከር ሀሳብ ያመነጨልኝ የእነ አያልቅበት እቅድ በእጅጉ ቢያሳስበኝ ነው። የእስከዛሬ እቅዳቸው እንደዘንድሮ የሚያስገርም እንዳልነበር አስባለሁ። እስካሁን ሳያሳወቁን ቢዘገዩም፤ ለማወቅ ያለኝ ጉጉት ጨምሮ እስከ አሁን ያልገለፁልን ምን ነክቷቸው ይሁን? ብዬ ተጨንቄያለሁ። ለዚህ ነው፤ እናንተን ሳይሆን እነርሱን የተስፋ ብርሃን ፈንጣቂ ዕቅዳችሁን አጋሩን ስል ይህን ጽሑፍ ለመፃፍ የተነሳሳሁት።
ወዳጆቼ! እስኪ ፍርዱኝ ሊያውም በመደመደሚያው በመጨረሻው ዓመት እንዲህ መዘግየታቸው አያሳስብም ትላላችሁ። ነገሩ እነ እንቶኔ አገርን የእድገት ማማ ላይ የሚያስፈነጥር ለዜጎቿ ተስፋ የሰነቀ፤ ራዕይ ያለው እቅድ አቅደው አሳይተውን አሁን የደረስንበት ደረጃ ላይ ደርሰናል። አሁን ላይ ደግሞ ኢትዮጵያን በማፍረስ አንጸባራቂ ድል ለማስገኘት፤ ኢትዮጵያን አንድ እርምጃ ወደ ኋላ እንድትጓዝ የሚያግዝ እቅድ አቅደው ነበር፤ አሉ። ካቻምና አልሳካ ቢላቸው አምና ያው በ2013 ዓ.ም አቅደው ዕቅዳቸውን ፈፅመውታል።
ይህንን ስትራቴጂካዊ ያሉት በእውኑ ዓለም ታይቶ የማይታወቅ የገዛ አገርን የማፍረስ አስማት መሳይ አስገራሚ እቅድ አቅደው ብዙ ርቀት ተጉዘዋል። የሀገራችንን መጻኢ ዕጣ ፈንታ የሚወስን ግሩም እቅዳቸውን ለማሳካት መጣራቸው በተግባር ቢያሳዩም፤ ለዘመናት ሲሰሩ መቆየታቸውን እግረ መንገዳቸውን ለሕዝብ አሳይተዋል።
ወዳጆቼ! በእነርሱ ዕምነት ብሩህ ተስፋን የሚያጭር፤ የሀገር እድገት የሚወሰን፣ የዜጎች አለኝታ ነው ብለው የሚያምኑበትን ዕቅድ አቅደው አሳክተናል ብለዋል። በእርግጥ አሳክተው ይሆን? በፍፁም ዕቅዳቸው አልተሳካም። ተሳሳትኩ እንዴት! ኧረ በፍጹም አልተሳሳትኩም። እንዲያውም ምንም ዓይነት ማጋነን የሌለበት ፍንትው ያለ እውነት ነው። አዎ እውነት ነው። አገር መክዳት የት ድረስ መሆኑን አሳይተዋል። እንደምስጥ ውስጥ ለውስጥ መሬት ለመሬት ሲሄዱ ነበር። የቀኑ ቀን ደርሶ እንዲህ ፍንትው ብሎ በአደባባይ ዕቅዳቸው ሲታይ እንዳልተሳካላቸው አረጋግጠናል።
እናንተዬ! ለሁሉም ጊዜ አለው እንዲሉት ሆኖ ነው። እንዳናየው የተጋረደው ጥቁር ሽፋን ሲገለጥ እውነቱ ጋር መፋጠጥ የግድ ሆነ። ከአምና የዘንድሮ ይለያልና የእነእንቶኔ ብልጣ ብልጥነት መቼም የማይረሳ አስገራሚ ዕቅድ መሆኑ ታወቀ። ሲያስተዳድሩን በመንበር ሥልጣናቸው ላይ ሆነው ከፊት የሚያሳዩን ሌላ ከውስጡ ሌላ ሌላውን ሲሰሩ እንደነበር አወቅን። አምና ዓቅደው በፈፀሙት ክህደት በየዓመቱ ምን ሲያቅዱና ሲሰሩ እንደነበር አረጋገጥን። ሾላ በድፍኑ ዓይነት ነገር እየሰጡን ሳናላምጥ እንዲሁ እንድንውጠው ሲያደርጉን ኖረው ዕቅዳቸውን ስንለው ኖርን። አቤት ጉዳቸው አያልቅም እኮ።
ትንቢት ነገር መናገርም ይሞክራሉ። ለምን አይሞክሩም። የዘንድሮውን ብቻ ሳይሆን የመጪውን ጊዜ ጨምረው ሊነገሩን የሚችሉት ጉዳይ ብዙ አላቸው። ምክንያቱም ለዘመናት አቅደው የገዛ እናታቸውን ለማፍረስ ሲሰሩ ቆይተዋል፤ የሚያስደንቀው ዕቅዳቸው የገዛ ሀገራቸውን ለማፍረስ መሆኑን አለመረዳታቸው ነው። ስለዚህ የትኛውም ሕዝብ ሳያውቅ እና ሳይገምት አገር የማፍረስ ዕቅድ እንዳላቸው አሳይተዋል። ስለዚህ ወደ ፊት ኢትዮጵያ ትበተናለች የሚል ትንበያን ለመስጠት እና ለመተንተን ሞክረዋል።
ምነው ተጠራጠራችሁ እንዴ? በፍጹም አትጠራጠሩ! ረሳችሁት እንዴ? እስኪ ላስታውሳችሁ እነእንቶኔ እኮ በገዛ ሕዝብ ላይ በወንድም እና እህት ላይ የማሴር የ27 ዓመታት ብቻ ሳይሆን በአጠቃላይ የ50 ዓመታት በላይ የካበተ ልምድ አላቸው። በሥልጣን ዘመናቸው ገና ከጀምሩ የመዓዛው ጠረን ከሩቅ የሚጣራ ለነገ ብሩህ ተስፋ የሚያሰንቅ የሚመስል ለሀገር የምንጊዜም ስንቅ የሆነ ስትራቴጂካዊ እቅድ አቅደው ነው ወይስ በሚያዛቸው የውጭ ኃይል ታቅዶላቸው፤ በአናት በአናታችን ሲግቱን አልከረሙም እንዴ? ከዓመት ወደ ዓመት አሸጋግረው ያለምንም መከፋፈል አንድነታችንን አስጠብቀን ወደፊት እንድንጓዝ አላደርጉም እንዴ?.. ይሄኔ ነው መሳቅ ።
ኧረ ምኑ ቅጡ ስንቱን ተናግረን፤ ስንቱን እንተዋለን? ይህ ሁሉ የሆነው በእነሱ እኮ ነው። ሀገራችንን ከነበረችበት አዘቀት ወጥታ የከፍታ ማማ ላይ ሆና፤ አድጋ ተመንድጋ ከበልጸጉት ሀገራት ጎራ ተሰልፋ የምናያት ይመስለን የነበረው በየትኛው ዕቅድ ነበር? የቀድሞ የእነእንቶኔ ድካምና ልፋት ያ ትልልቅ እቅድ፤ አሁንም ድካማቸውና ልፋታቸው መና እንዲቀር አልፈለጉም። ለዚህም ነው፤ ዛሬም ከእነ አጋፋሪዎቻቸው በሞት ጥርግርግ እያሉ እንኳን አቅላቸውን ስተው እቅዳቸውን ከግብ ለማድረስ አፈር እየላሱ እየተነሱ ነው።
ለእነርሱ ይህንን ማለት እፈልጋለሁ። ‹‹እናንተ የእናት ወጪት ሳባሪ የሆናችሁ ሀገር ልታፈርሱ ብዙ ዓመታትን ደክማችኋል። ዜጎቿን ከፋፈላችሁ አንድነቷን ለመበታተን ያደረጋችሁት ጥረት አልተሳካም። ኢትዮጵያውያን መቼም ቢሆን በሀገራቸው ጉዳይ ወደ ኋላ ብለው አያውቁም። አሁን አይታችኋል። እናንተ ልታፈርሷት ያለማችሁትን ሀገር ዜጎቿ ሊያድኗት ቀፎው እንደተነካ ንብ ከያሉበት ቦታ ወጥተው ሲተሙ በዓይናችሁ አይታችኋል። የአገር ፍቅር የሚባል ነገር ባይገባችሁም፤ ይህኛው አገር የማፍረስ ዕቅዳችሁ አልተሳካም›› እላለሁ።
ኧረ ክፋት አሉ እማማ! ውጥንቅጧ ወጥቶ እንድትፈርስ የፈለጓት አገር እንደማትፈርስ ቢያረጋግጡም ዜጎቿን ለመጉዳት ሰማይን ተንጠራርቶ የመቧጠጥ ያህል ጥረት በማድረግ ላይ ናቸው። እነዚህ አስማተኛ ዕቅድ ዓቃጆች ጆሯቸው ለማዳመጥ ዝግጁ ባይሆን እንኳ ከእውነተኛ ትምህርት ብሎ ነገር ባይገባቸውም ማዳመጥ ባይችሉም መስማታቸው አይከፋም። በዘመናቸው አይተው በማያውቁት መልኩ ኢትዮጵያውያን አገር ወዳድ መሆናቸውን እያረጋገጡ ነው።
ለእነእንቶኔ ‹‹እናንተ ሳትሰሩ የቆያችሁትን ሌላው መጥቶ እየሰራው ነው። ሕዝቡም በቀናነት እየተባበረ ይገኛል። እናንተ ያልሄዳችሁበት መንገድ ላይ ሌላው እየተጓዘ ነው። መንገዱ ኢትዮጵያን ያሻግራታል። ›› ለማለት እፈልጋለሁ።
የአሁኑ ዕቅድ ድፍድፍ ነው። ውሃ ተሞልቶ ተጨምቆ ምርጥ መጠጥ ይወጣዋል። ኢትዮጵያውያን በሙሉ በደስታ እና በሃሴት የሚሞላ መጠጥ። የእናንተ አተላው ዕቅዳችሁ ይደፋል፤ ይጠፋል።
መጥፎው ጥንስስ ሻግቷል። መልካም ሆኖ ሳይጠጣ አተላ ሆኖ ሽታው ሰንፍጦ ሰዎች ርቀዋል። የከረመው እና የከረፋው ዕቅድ ከዛሬ ነገ መሻሻሎች ይኖሩታል ተብሎ የሚጠበቅ አይደለም። በዚህ ምክንያት የዕቅዱ አስፈፃሚዎች ተራ በተራ ወደ ገደል እየወረዱ ነው።
ወዳጆቼ! የእነ እንቶኔ ሀገር ለማፈራረስ አቅላቸውን አስቶ የቆየ ስትራቴጂካዊ እቅዳቸውን ግን አሁንም ድረስ የሙጥኝ ብለዋል። በአገሪቱ ዙሪያ በተለያየ ቦታ የለኮሱት እሳት እንዳሰቡት ተቀጣጥሎ ሀገር ሊያፈርስላቸው ባይችልም ዕቅዳቸው ብዙዎችን ለሰቆቃና ስቃይ ዳርጓል።
በተለይ በ2013 ዓ.ም የጥቅምት ወር ተራውን ለኅዳር ለመልቀቅ የቀናት እድሜ ሲቀረው የማይደፈረውን ደፍረው፤ በመከላከያ ሠራዊት ላይ የፈጸሙት አስነዋሪ ድርጊት የክፋታቸው ጥግ ድብቁን ዓላማቸውን ፍንትው አድርገው የሀገር ማፍረስ እቅዳቸውን አሳይተውበታል።
‹‹ጉድ ሳይሰማ መስከረም አይጠባም›› እንደሚባለው ሆኖ በአደባባይ ወጥተው ሀገር ለማፍረስ ሲኦል መውረድ ካለብን እንወርዳለን ሲሉ በእድሜ ዘመናቸው ሲመኙት የኖሩት ሀገር የማፍረስ ዘመናት እቅድ በአደባባይ ይፋ አድርገው፤ በመከላከያ ላይ ያረፈው የጭካኔ ዱላ በኢትዮጵያ ምድር ሆኖ የማያውቅ ወደፊትም ይሆናል ተብሎ የማይገመት ዘግናኝ ድርጊታቸውን የዘላለም ዕቅዳቸው ተምሳሌት ሆኖ በታሪክ ማህደር ላይ ሰፍሯል።
ከእናት ማህጸን ወጥቶ የእናት ጡት ነካሽ መሆናቸውን፤ ህልማቸው ሁሉ ከሰው ልጅ የማይጠበቀውን ሰይጣናዊ ድርጊትን መፈፀም መሆኑን አይተናል። በለውጡ ማግስት የታየው የተስፋ ብርሃን ላይ ውሃ ቸልሰው የጨለማ ጽልመት አልብሰው፤ ዕቅዳቸው ዕድገት ሳይሆን ጥፋት መሆኑን አሳይተዋል።
የግፈኞቹ በደል አባይ በጭልፋ እንዲሉት ዓይነት ሆኖ፤ ጥቂቶችን ለማንገስ ዓቅደው ኢትዮጵያን ለማፍረስ አልመው፤ በማይካድራ፣ በጋሊኮማ እና በጭና ምድር በአሰቃቂ እና ዘግናኝ በሆነ መልኩ ንጹሃን ዜጎችን መጨፍጨፋቸው ሲታወስ በእርግጥም የእነዚህ ሰዎች ዕቅድ እስከምን ድረስ የዘለቀ መሆኑን ማሰብ ይከብዳል። የንጹሃን ደም ደመከልብ አድርገው ለሰሚው ግር የሚል አሳዛኝ ድርጊት ሲፈፅሙ ሰዎቹ ይህ ዘግናኝ ድርጊታቸው ጊዜ በማይሻረው የታሪክ መዝገብ ላይ ስማቸውን በመልካም ሳይሆን በመጥፎ በደማቅ ጥቁር ቀለም ለማተም ያቀዱ ይመስላል።
ወዳጆቼ! አሁን አሁን ደግሞ እነ እነቶኔ በአዲሱ ዓመት እቅድ ምን አቅደው ይሆን? ስል አሰብኩ። እንግዲህ ሀገር ለማፍረስ ስትራቴጂያዊ እቅድ አውጥተው ተንቀሳቀሰው፤ ሳይሳካላቸው ባሰቡት ባለሙት ልክ መጓዝ አቅቷቸው፤ አይቀጡ ቅጣት ተቀጥተው፤ ክንዳቸው ተመትቶ ዙሪያው ገደል ሆኖባቸው፤ መላው ጠፍቶቸው፤ አፈግፍገዋል። ቀድሞውኑ አቅላቸው የዞረባቸው ናቸውና በዚህ ላይ ሰማይና ምድር ሲደፋባቸው፤ የትግራይን ሕዝብ አስጨርሰው ብቻቸውን በቆሙበት በዚህ የፈጻሚው ደውል ጆሯቸው ላይ እያቃጨለ ምን ሊያቅዱ ይችላሉ? አርቀው የቆፈሩት ጉድጓድ መልሶ እራሳቸው ሊቀበሩበት መሆኑን ጠንቅቀው ያውቁታል። አሁን ሞታቸው ቢፈጥን ይመኛሉ እንጂ ሌላ ምን ሊያቅዱ?
እናንተዬ! ኧረ ጉድ እኮ ነው። መቼም አሟሟቴን አሳምረው ብለው ያቅዱ ይሆን? አይመስለኝም። ግን ምን ይታወቃል? እነሱ እኮ እየበላን እንሙት የሚሉ ናቸው። ከመሞቴ በፊት ምን ልብላ? ይሉ ይሆናል። ይልቅ የመጨረሻው ጊዜ መቃረቡ ከገባቸው አንዳንዶቹ ግብዓተ መሬታቸው መፈጸሙ እንደማይቀር አውቀው፤ ምናልባት መቃብራቸው ላይ ስለሚፃፈው ጽሑፍ እየተጨነቁ ይሆናል። ምን ተብሎ ይጻፍልን? በየትኛው ቀለም እና እነማን ይጻፉልን? የሚለው እያስጨነቃቸው ይሆናል።
ወዳጆቼ! ወደው አይሰቁ ማለት ይሄኔ ነው። ያልመደባቸውን አስበውና ተጨንቀው በትክክል መታቀድ ያለበትን ያቅዱ ይሆናል። እኔ ግን አንድ ነገር ማለት እፈልጋለሁ። እምብዛም አትጨነቁ፤ ሆዳችሁን ባር ባር አይበለው። አይዞችሁ ጠንከር በሉ። እኛ ኢትዮጵያውያን ከማፈረሳችሁ በፊት እናንተ ስትፈርሱ፤ በእናንተው ጦስ የመጣው ጣጣ ከእናንተ ጋር አብሮ ሲቀበር በሀገርና በወገን ላይ የፈጸማችሁት ግፍና በደል ተዘርዝሮ የአገር ከሃዲዎች ተብሎ በደማቁ ይከተብላችኋል። ምድር ግዴታዋ በመሆኑ ብትቀበላችሁም፤ በምድር በሰዎች ስቃይ የደላት ስጋችሁ ፈርሳ፤ ነፋሳችሁ በሰማይ በደላችሁን ታወራርዳለች።
አሁን ጊዜው የመጨረሻው የእስትንፋሳችሁ መቋጫ የደውል ድምፅ እያስተጋባ ነው። ኖራችሁ ለማንም አልበጃችሁም። ሽርፍራፊ ሴኮንድ ካለችሁ ስታታልሉት የኖረውን የትግራይ ሕዝብ ይቅርታ ጠይቁ።
አሁን የኢትዮጵያ ነቀርሳ ይነቀላል። ምድር ትጸዳለች። ሀገር ለማፍረስ ያለመ ሴራችሁ ከእናንተው ጋር አብሮ በቆፈራችሁት ጉድጓድ አርቀን አብረን እንቀብራችኋለን። እናንተ የተከላችሁት መርዝ ከተነቀለ፤ ነቀርሳ ከነሰንኮፉ ወደ ጉድጓድ ከተወረወረ የሀገራችን የትንሳኤ ዕውን ይሆናል።
ምንም እንኳን የክፉዎች ክንድ ቢበረታም ኢትዮጵያ አትፈርስም። ለጥቁር ሕዝቦች ሳይቀር የነጻነት ቀንዲል የሆነችው አገር፤ አገር መሆኗ ብቻ ሳይሆን ተምሳሌትነቷም ይቀጥላል። በህልውና ዘመቻው ከበቂም በላይ የሆኑ ኢትዮጵያውያን ለመዝመት ተዘጋጅተዋል። ስለዚህ የ2014 ዕቅዳችሁ እውን ይሆናል። ኢትዮጵያን ማፍረስ ሳይሆን በመቃብራችሁ የሚፃፈው ታሪክ እየተዘጋጀ ይገኛል። ኢትዮጵያ ግን ለዘመናት ካቀዳችሁላት የመፍረስ አደጋ ወጥታ በለውጥ ጎዳና ወደ ከፍታ ማማ ትወጣለች። ጉዞዋ ስኬታማ እንዲሆን መንገዱ እንዲቃና በማድረግ ረገድ ትንኮሳችሁ ብቻ ሳይሆን ተንኮላችሁም በእጅጉ ጠቅሞናልና ለአሁኑ አመስግናለሁ።
ትንሳኤ አበራ
አዲስ ዘመን መስከረም 6/2014