ኢትዮጵያ ከሌላው ዓለም በተለየ የራሷ የዘመን ስሌትና ቀመር ያላት ጥንታዊት አገር ናት። ክረምት አልፎ መስከረም ሲጠባ፣ አሮጌ አመት ሄዶ አዲሱ ይገባል :: ለኢትዮጵያውያን መስከረም የአመት መጀመሪያ ወር ናት:: ከአንዱ ዘመን ወደ ሌላው የመሸጋገሪያ ምልክት ናት፡፡
በወርሃ መስከረም የሀምሌ ጨለማ፣ የነሃሴ ዝናብ ይሻራል:: የክረምት ጨለማ አልፎ ብርሃን ይመጣል:: የደፈረሰ ጅረት ይጠራል ፤ ሰማዩ ይጠራል:: ወንዞች ኮለል ይላሉ:: አበቦች ይፈካሉ:: ወፎችም በደስታ ይዘምራሉ። በአዲሱ ዓመት መባቻ በወርሃ መስከረም ሜዳው፣ ጋራው፣ ሸንተረሩ በአደይ አበባ ይለመልማል። በአረንጓዴ ነገሮች ከመከበቡም ሌላ ነፍስን የማለምለም ሀሴትን የመፍጠር ጉልበት አለው፡፡
ዶክተር ሀብተማርያም አሰፋ‹‹የኢትዮጵያ ታሪክ ጥያቄዎችና ባሕሎች›› በሚሉት መጽሐፋቸው መስከረምን እንዲህ ገልጸውታል:: መስከረም ‹‹ምስ-ከረም›› ከከረመ በኋላ ወይም ክረምት ካለፈ በኋላ ማለት ነው:: የመስከረም ወር ዝናብ የሚቆምበት ፀሐይ የምትወጣበት ወንዞች ንጹሕ ውሃ ጽሩይ ማይ የሚጎርፍበት፣ አፍላጋት የሚመነጩበት፣ አዝርዕት ማለት የተዘሩት አድገው ማሸት የሚጀምሩበት፣ ሜዳዎችና ተራራዎች ሸለቆዎችም በአበባ የሚያሸበርቁበትና የሚያቆጠቁጡበት ነው፡፡
ኢትዮጵያ የክረምት ወቅቷ የሚያስከትለው ዝናባማ፣ ቀዝቃዛ የአየር ሁኔታ ተገልጦ ተስፋ ከብርሃናማ የሰማይ ድምቀት፣ ከምድሯ ልምላሜና የአደይ አበባ ፍካት ጋር ተደማምሮ በህዝቧ የአኗኗር ባህል ውስጥ የኖረ፣ ያለና የዳበረ ልዩ የአዲስ አመት ክብረ በዓልም አላት ። ይሕም የዘመን መለወጫ በዓል እንቁጣጣሽ በመባል ይጠራል።
ለቃሉ የተለያዩ ትርጓሜ ሲሰጠው ይስተዋላል። በተለይም በመንፈሳዊ ፣ በዓለማዊውና ከታሪክ አንፃር የሚሰጠው ትርጉም የተለያየ ቢሆንም ሁሉም ከዘመን መለወጫ በዓል ጋር የሚያያዙ መሆናቸው አንድ ያደርጋቸዋል። መስከረም አንድ የዘመን መቀየር አብሳሪው የቀኖች ሁሉ ደማቁ፣ የደስታ ቀኖች ሁሉ ታላቁ ሆኖ፤ የዘመን ሽግግር ‹አንደኛ ቀን››ሆነ ይከበራል::
አዲስ ዘመን ለኢትዮጵያውያን ታላቅ አውደ አመት፣ ልዩ ቀን ነው:: በዚህ ቀን መስከረም በውበት ትሽሞነሞናለች:: መስኩ ፣ደን እና ሸንተረሩ በአበቦች ፍካትና ሙላት ይታጀባል:: የአእዋፋት ድምፅ እና ዝማሬ በየቦታው ውበት ይሆናል:: ክረምቱ ማብቃቱን የምታበስረው የመስቀል ወፍ ከተደበቀችበት ብቅ ስትል አደይ አበባ ፍካቱን እንካችሁ ትላለች፡፡
በዘመን መለወጫ በዓል አሮጌው አልፎ አዲስ ይተካል:: ኢትዮጵያውያን የመስከረም ወር መጀመሪያ የጨለማ የችግርና የጊዜ የሚያበቃበት የብርሃን፣ የደስታ፣ የእሸት፣ የፍሬና የጥጋብ ጊዜ የሚጀምርበትና የሚተካበት ነው ብሎ ይምናሉ:: የዕንቁጣጣሽ በዓልን ከሁሉ አብልጦ ግምት ስለሚሰጠው በእሳት ብርሃንና በእሳት ቡራኬ በየቤቱ እንደ ሁኔታው እንስሳ አርዶ ፤ ደም አፍስሶ ይቀበለዋል:: ያከብረዋል፡፡
መስከረምና እንቁጣጣሽ፣ ከተፈጥሮ ጋር ተጋግዘው በሚስብ ውበት፣ በሚጥም ቃና፣ በአበቦች ታጅበው፣ በችቦ ተከብበው ስለሚመጡ፣ ብርሃን ብርሃን
ይሸታሉ:: የመስከረምን ድባብ ለየት ያለ ገፅታ አለው:: በተለይ የበአሉ ሽርጉድ ዕለቱን ያስናፍቃል፡፡
አዲስ አመት ሁሉም ኢትዮጵያዊ እንደ አቅሙ ደግሶ አዘጋጅቶ በደስታ በሰላም፣ በፍቅር ይቀበለዋል:: እንደ ስሙም አዲስ አመትም፣ አዲስ ዘመንም አይደል? አመቱን አዲስ ለማድረግ ሁሉም በየፊናው ይዘገጃጃል:: መኖሪያ ቤታቸውን አሳምረውና አድሰው፤ አልባሳትን አጥበዉ፣ ቄጤማ ጉዝጓዙ፣ ጠላዉ፣ ዶሮዉ፣ በግና በሬው፣ ቅርጫ ስጋው ፣ ዳቦዉ፣ ከየቤቱ የሚወጣው የሚያውድ መዓዛ፣ ለበዓል ዝግጅት የሚትጎለጎለው ጭስ አንዳች ስሜትን ይፈጥራል:: የዘመድ አዝማዱ መሰባሰብ የጎረቤቱ ድግስና አብሮ መብላት መጠጣት እንደ አቅም መጠጥ በወረቀት ጠቅልሎ ወይም ድፎ ዳቦ ይዞ ዘመድ አዝማድ ለ መጠየቅ የሚደረገው ሂደት በአሉን ተናፋቂ ያደርጉታል፡፡
በክረምት ወቅት በተለይ በገጠራማው ክፍል ወንዝ እስከሚጎድል ዘመድ ከዘመድ አይገናኝም:: ‹‹መስከረም ሲጠባ አደይ ሲፈነዳ እንኳን ሰው ዘመዱን ይጠይቃል ባዳ››የሚለው ግጥም እንደሚያመልክተው፣ አዲስ ዘመን፣ ወንዞች ይጎድላሉ፤ ዘመድ ከዘመድ ይጠያየቃል፡፡
ወዳጅ ዘመዱ ጋር መልካም ምኞቱንም ባገኘው አጋጣሚ ሁሉ ይለዋወጣል። እንዴት ከረማችሁ ይባባላል። «እንኳን አደረሰህ ! አደረሰሽ፣ መልካም አዲስ አመት፣ የሰላምና የጤና ዓመት ይሁንልን» እየተባባሉ ያልኖሩትን ነገን በጎ ሆኖ እንዲጠብቃቸው እርስ በእርስ መልካም ምኞታቸውን ይገላለፁበታል። በበአሉ ቤተሰብ ጎረቤት በያለበት በጋራ ያለውን ደግሶ አብሮ በልቶና ጠጥቶ ለእለቱ ያደረሰውን አምላክ አመስግኖ ‹‹የከርሞ ሰው››ይበለን ብሎ ይመራረቃል:: ደግ ደጉን ይመኛል:: በጎ ነገር እንደሚገጥመው ተስፋ አድርጎ በተስፋ ይደሰታል። መልካም መልካሙን ለሀገሩ ይመኛል። ምክንያቱም ሀገር ከሌላ በዓል አውዳመት ፤ ሀገረ ከሌላ አብሮ መብላት መጠጣትና መደሰት፤ ሀገር ከሌለ ሁሉም ነገር የለምና ለሀገሩ ሰላም፣ ልማትና ብልጽግና ይመኛል።
እናቶች እና አባቶች የአገር ባሕል ልብስ ለብሰው፣ ልጆች ደግሞ ስጦታቸውን ተሸክመው ቤተሰብ ጋር ይሄዳሉ:: በአካባቢ በእድሜ ፀና ያሉ አዛውንቶች ነጭ የአገር ልብሳቸውን ለብሰው፣ አዲሱ አመት፣ የእርቅ ና የምህረት እንዲሆን ይመርቃሉ:: ሰዉም ምርቃቱን ከልብ በመነጨ ስሜት አሜን ‹‹ይሁንልን›› ሲል ይቀበላል:: ዝናቡ የምህረት፣ እህሉ የበረከት እንዲሆን፣ ሰላም እንዲወርድ ይፀለያል:: ‹‹እህል ይታፈስ ገበሬ ይረስ፤ አራሽ ገበሬውን ሳቢ በሬውን ይባርክ››እየተባለ የሽማግሌዎች ምርቃት ይጎርፋል :: ‹‹ክፉውን ያርቀው መልካሙን ያቅርበው ›› ሲል አዛውንቱ ሁሉ ይመርቃል።
ጭፈራዎቹም የባህሉ አንድ አካል ናቸው:: በሽታውን፣ ችግሩንን ሁሉ በችቦ የተስፋ ብርሃን እንጎሮ ጎባሽ እያለ በመተርኮስ ያባርራል:: ችቦም ድቅድቁን ጨለማ የሚሰነጥቅ ብርሃን ስላለው፣ ከጨለማ ወደ ብርሃን የመሄዳችን ትዕምርት ተደርጎ ሊቆጠር ይችላል:: ‹‹የጎመን ምንቸት ውጣ፤ የገንፎ ምንቸት ግባ›› በሚልም የእህል መድረስን በችቦ ማብራት በብርሀን እየታየው መሆኑን ያመለክታል።
ሰኔ ግም ብሎ፣ የሃምሌን ጨለማ አልፎ፣ የነሐሴን ጎርፍ ሙላትን በእኝኝ ተሻግሮና ተንተርሶ በጠንካራው ዝናብ ምክንያት ብቅ የምትለዋ አደይ አበባ ናትና፤‹‹ኢዮሃ አበባዬ መስከረም ጠባዬ››ይባላል:: በተለይ ህጻናትና ልጃገረዶች አደይ አበባ እንግጫ እየለቀሙ እና እየጎነጎኑ ይቦርቃሉ፡፡
አዲስ አመት የደስታ ቀን ነው ፤ የእረፍት ቀን
ነው:: ሁሉም እንደየአቅሙ ደስ ብሎትና ለብሶ የሚዘፍንበት፣ የሚዘምርበት፣ ዕልል የሚልበትና እስክስታ የሚወርድበት ቀን ነው:: እንደ ጥጃ የሚፈነጩበት ቀን ነው:: የዚህን ዕለት ብስራት ለመንገር ከልጃገረዶቹ ፈጥኖ ማልዶ የሚነሳ ማንም የለም፡፡
በበአሉ እለት ሴቶች ይበልጥ ይደምቃሉ:: እንደ የአካባቢያቸው አለባበሳቸውን ያሳምራሉ:: ልጃገረዶች ሳዱላቸውን ያሳምራሉ:: አደስ ይቀባሉ:: እንሶስላ ይሞቃሩ:: ወንዝ ይወርዳሉ:: እንግጫ ይለቅማሉ:: ፀአዳ ልብሳቸውን ይለብሳሉ:: አሽንክታባቸውን ያጠልቃሉ:: ‹አበባ አየህ ሆይ ለምለም› በማለት ተሰብስበው ብቅ ይላሉ:: የወርሀ መስከረም ብሩህ ተስፋና ስሜት ያስተጋባሉ፡፡
አደይ አበባ ቀጥፈው እንግጫ ነቅለው፣ በተለያዩ ጌጣጌጦች ተሸልመው ይቀርባሉ:: ከግጫው፣ ከአደዩ በእቅፋቸው ይዘው ፤ አይናችሁን ግለጡ ዘመን ተለውጧል የሚል ብስራት ያሰማሉ:: በውብ ዜማ ይናገራሉ:: ያንጎራጉራሉ:: ከየሰው ደጃፍ እየቆሙ ዕንቁጣጣሽ እያሉ እርጥብ ቄጠማ ይሠጣሉ:: ወላጆችም ልጆቻቸውን በየሰዉ ደጃፍ እየቆሙ እንዲያንጎራጉሩ ፈቃድ አይከለክሉም፡፡
በየአደባባዩና በየመስኩ ለበዓላቱ የሆኑት ዘፈኖች የግጥም ምስጢር ጊዜውን የሚከተል ነው:: መስከረም’ ምድር በልምላሜ የምትታይበትና በአበባ የምትሸፈንበት ወቅት በመሆኑ ለዕንቁጣጣሽ የሚመረጠው ዘፈን፤ ልምላሜን በሚያደንቁ ቃላት እንደሆነም ይነገራል፡፡
በኢትዮጵያ የክዋኔ ጥበባት ውስጥ እንደ አዲስዘመን የተዘፈነለት፣ የተገጠመለትና የተወራለት ጉዳይ ቢኖር ፍቅር ብቻ መሆኑም የሚካድ አይደለም:: ከመስከረም ወር የሚጀምረው የምድር ፍካት በአደይ አበባ የታጀበ ልምላሜ የሚፈጥረው የተፈጥሮ ዕይታ በግጥምና ከዜማ አዋደው የተለያዩ ስራቸውን እንካችሁ ያሉን አርቲስቶችም ቁጥር በርካታ ነው:: አንድ ሁለቱን ስናስታውስ ለእኔ የመረጥኳቸውን ልጥቀስ፡፡
የሙዚቃው ንጉስ ጥላሁን ገሠሠ‹‹በየአመቱ ለእኛ እንቁጣጣሽ ደስ ይበለን እንኳን ደህና መጣሽ ›› ሲል መጫወቱ የሚታወስ ነው:: ሀመልማል አባተም፣
‹‹የክረምቱ ወር አልፎ ለበጋው ለቋል››
ሜዳው ሸንተረር ጋራው – በአበቦች ደምቋል፤
ሸሞንሟናዬ ውብ ሽቅርቅሩ፤ ድረስ ባውዳመት ናልኝ የኔ ኩሩ።
በወራት መጀመሪያ – ባዲሳመቱ መግቢያ፤
በል ፈጥነህ ድረስልኝ – በዘመድ መሰብሰቢያ፤
አበባየሆሽ ሲባል – ሆያሆዬው ሲጨፈር፤
ዓውድ ዓመት እንዲህ ያምራል
ካንተ ጋር ሁሉ ይሰምራል›› ስትል ፍቅሯን በእንቁጣጣሽ ድባብ እና መልክ የገለፀችበት ዘመን አይሽሬ ስራ መስራቷ ይታወሳል፡፡
መሰል የሙዚቃ ስራዎች በዓላትን ጠብቀን የምንሰማቸው ቢሆኑም የአውዳመት ድባብና የመስከረም እና የተፈጥሮን ትስስር እያስቃኙ በአል በመጣ ቁጥር ሁሌም የሚታወሱ ዘመን ተሻጋሪ ስራዎች መካከል ከፊተኞቹ ተርታ የሚሰለፉ ናቸው፡፡
የዘመን በዘመን ፤ የጊዜ በጊዜ መተካት የማያቋርጥ ሂደት ቢሆንም ለአዲስ ዓመት በአዲስ መንፈስ መነሳት የግድ ይላል:: አዲስ አመት የስሜት መነቃቃት እንደሚፈጥር በርካቶችን ይስማሙበታል:: በአዲስ አመት አዲስ ተስፋን ሰንቆ በአዲስ መንፈስ አመቱን መጀመር በአብዛኛው የአለማችን ክፍል የተለመደ ነው፡፡
በአዲስ አመት በመላው አለም የሚኖሩ ህዝቦች የነገን አዲስ ህይወታቸውን በአዲስ ተስፋ ሰንቀው ለአዲስ ጉዞ አንድ ብለው የሚጀምሩበት ቀን ነው:: ዘመን አልፎ ዘመን ሲተካ ሀገርና ህዝብ በአዲስ መንፈስ በአዲስ ዕቅድ አዲሱን ዓመት በመቀበል አሮጌውን ትተው በአዲሱ ዘመን መልካም ነገሮችን ይዘው ይነሳሉ፡፡
እውነተኛ የአዲስ ዓመት ትርጉሙ ግን አዲስ ሰውነት፣ አዲስ አስተሳሰብ፣ አዲስ ለውጥ፣ አዲስ የሕይወት መንገድ የምናበጅበት፣ ለራሳችን ቀና አስተሳሰብ የምንቀይስበት ነው:: አዲስ ዓመትን ስንቀበል የተበላሸውን አስተካክለን መልካሙን ለማስቀጠል ቆራጥ መሆን የግድ ይለናል:: በተለይ የኢትዮጵያዊነታችን መገለጫ ለሆነው፡ ሰላም ፍቅር እና አንድነትን ቅድሚያ መስጠት ይኖርብናል፡፡
ከአዲስ ዓመት አከባባር ላይ የሚንፀባረቁ የበጎ አድራጎት ስራዎችን ማስቀጠል ይገባል። ለአብነት ያህል የአቅመ ደካሞችን ቤት መጠገን፣ አቅም ለሌላቸው ወላጆች ለልጆቻቸው በአዲሱ ዓመት ትምህርት እንዲቀጥሉ በቁሳቁስ መደገፍ፣ በበጎ ፍቃድ ደም መለገስ እና የመሳሰሉት መልካም ተግባራት በአዲስ ዓመት 2014 አ.ም ማስቀጠል ይኖርብናል። ይሄ መልካም ተግባር በተወሰኑ አካባቢዎች ብቻ የሚቀር መሆን የለበትም፤ በሁሉም የኢትዮጵያ አካባቢዎች ሁሉንም ህብረተሰብ ባሳተፈ መልኩ ዘወትር ሊከናወን የሚገባው ቅዱስ ተግባር ነው።
እነዚህ ተግባራት በዓላትን ወይም የሆነ ወቅትን ጠብቀን የምናከናውናቸው ሊሆኑ አይገባም። ሁሌም ሊከናወኑና ባህላችን የሆነውን መረዳዳትን ማጠናከር አለብን:: ለወገን ደራሽ ወገን ነው እንደሚባለው እርስ በእርሳችን መደጋገፍና መቆም ካልቻልን የተሻለችና የተለወጠች ኢትዮጵያን ማየት እንደማንችል መረዳት ይኖርብናል፡፡
መልካም አዲስ አመት፡፡
2014 ዓ.ም የደስታ ፣ የሰላም፣ የብልፅግና፣የፍቅር ፣ የአንድነት ዘመን ይሁንልን!
ታምራት ተስፋዬ
አዲስ ዘመን መስከረም 2 ቀን 2013 ዓ.ም