ቀኑ ቅዳሜ ነው፤ የእለቱን ስራዬን ጨርሼ ከቢሮ እየውጣሁ ነው። የሳምንቱ እረፍት በሚጀመርበት ሰዓት ላይ እገኛለሁ። እኔ እረፍቱን ግን ለስራ አውዬዋለሁ፤ ስልኬ ጠራ፤ ጓደኛዬ ነው። ከሰዓት በኋላ ለመገናኘት ተቀጣጥረናል። ስልኩን ተጣድፌ አነሳሁት። የመኖሪያ ቤት ጉዳይ በእጅጉ እያሳሰበኝ መሆኑን አጥብቄ ከነገርኩት ጓደኛዬ ጋር ቀጠሮ የያዝነው የሚሸጥ ቤትና ቦታ ለማየት ነው።
በተቃጠርንበት ሰፈር መኖሪያ ቤት በተመጣጣኝ ዋጋ እንደሚሸጥ ጓደኛዬ መረጃው አለው። በዚሁ አካባቢ በቅርቡ መኖሪያ ቤት ገዝቷል። ጓደኛዬ ቤት ገዛሁበት ያለኝ ዋጋ ለማመን ይከብዳል፤ ተመጣጣኝ የሚባል ነው፤ ከእሱ ጋር ቤት ለማየት እሱ ሰፈር ለመሄድ የወሰንኩትም ለዚህ ነው።
አካባቢው ከከተማ ዳር ነው፤ ሆኖም ግን የተባለው ቦታ አዲስ አበባ ላይ መሆኑ ሲታሰብ ዋጋው ያስገርማል። ያልሄድኩበት ቤት ይሸጥበታል የተባለ ቦታ የለም፤ እስኪ ምን አልባት አይታወቅም እድሌን ልሞክር ብዬም ነው ከጓደኛዬ ጋር የተቀጣጠርኩት።
ለሜክሲኮ ታክሲ ለመያዝ አራት ኪሎ ዳግማዊ ምኒሊክ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ፊት ለፊት ታክሲ ተራ ጋር ደረስኩ። በስፍራው ያለ ወትሮው ታክሲ የለም ፤ በርካታ ሰዎች በረጅሙ ተሰልፈዋል። ፈጥኖ መድረስ ስላለብኝ ተቻኩያለሁ፤ ለ5 ደቂቃ ያህል እዚያው ቆምኩ። ረጅም ሰዓት የቆምኩ ያህል ተሰማኝ።
ወዲያው ቤት ለመግዛት ያሰበ ሰው በታክሲ ወረፋ መታገት የለበትም ስል አሰብኩ። እንዴ የባሰ ችግር ሲገጥም መኩረፊያዎች ተፈጥረው አይደል እንዴ አልኩ፤ ኪሴን ማሰብ ጀመርኩ። ስልኬን አውጥቼ ደወልኩና ያለሁበትንና መድረስ የምፈልግበትን ቦታ ነገርኩ፤ ወዲያውኑ አንድ አዲስ ቁጥር ወደ ስልኬ ደወለ። አንስቼም ያለሁበትን ነገርኩት፤ ወዲያው መጣልኝና ጉዞ ወዳሰብኩበት ተጀመረ።
ልክ ብሄራዊ ቤተ መንግስት ስንደርስ ሹፌሩ ያናግረኝ ጀመር። “ይቅርታ ገንዘብ አልቆብኛልና ስልኬ ሲስተሙን አቋረጠው፤ በኪሎ ሜትር እናድርገው?” ሲል ጠየቀኝ። አውቄ ዝም አልኩት፤ እሱ የተስማማሁ ያህል ቆጥሮ ጉዞውን ቀጠለ። የታክሲውን መቁጠሪያ 0 አድርጎ ሲያስጀምር አየሁት።
ስለ ሹፌሩ ማሰብ ጀመርኩ፤ ታዘብኩትም። በእርግጠኝነት ሲስተሙ አላስቸገረውም። ሰዎችን ከአሽከራሪዎቹ ጋር የሚያገናኛኘው ድርጅት በዘረጋላቸው የስራ ዕድልና ባመቻቸላቸው ሲስተም መሰረት ነው እነዚህ አሽከርካሪዎች የሚሰሩት። እነሱ ግን ለድርጅቱ ታማኝ አይደሉም።
ድርጅቱ አሽከርካሪዎቹን ከተገልጋይ ከሚያገኙት ላይ በመቶኛ መጠነኛ ገንዘብ ያስከፍላቸዋል። የአገልግሎት ማለት ነው። እሱን ላለመክፈል ነው እንግዲህ አሽከርካሪዎቹ ሰበብ እየፈጠሩ ደንበኛ ካገኙ በኋላ በኪሎ ሜትር እናድርገው ሲሉ የሚጠይቁት። ስቸኩል መሰል የትራንስፖርት አገልግሎት እጠቀማለሁ፤ ሁሌም ግን የአሽከርካሪዎቹን ባህሪና የሚያደርጉትን ሁሉ እታዘባለሁ። በተደጋጋሚ መሰል ምክንያትም ያቀርቡልኛል። አብዛኞቹ በዚህ በኩል አንድ ናቸው።
የተፈጠረውን ምቹና ተገቢነት ያለው አሰራር መከተል የማይወዱት እነዚህ አሽከርካሪዎች ለድርጅቱ በትክክል ገቢ ቢያደርጉ ገቢያቸው ይታወቅና ግብርም በአግባቡ ይከፍላሉ። በዚህም አገራዊ ገቢ ያድጋል። እነሱ ይህን አየሸሹ ወንጀል ይፈጽማሉ። ለብቻዬ ገቢ ላግኝ ነው ሀሳባቸው። ለዚያውም ተገቢውን የአገልግሎት ክፍያና ግብር ሳልከፍል ማለታቸው ትክክል አይደለም።
ጓደኛዬ የቀጠረኝ ሰፈር ሩቅ ነበርና ግማሽ ያህሉን መንገድ በዚህ መንገድ ከተጓዝኩ በኋላ ወደ ቀጠሮዬ ቦታ የሚያደርሰኝን ባጃጅ ያዝኩ። የአዲስ አበባ ዳር ሁሉ መሀል ሆኗል። ለቡ፣ ሀይሌ ጋርመንት፣ የሚባሉት ሰፈሮች ራሳቸውን የቻሉ መዲናዎች ሆነዋል። የሚገራርሙ መኖሪያ ቤቶች፣ ለሪል ስቴትና ለሌሎች አገልግሎት የተገነቡ ህንጻዎች በስፋት ይታያሉ። ከለቡ ወደ ቱሉ ዲምቱ የሚወሰደውን መንገድ ጭምሮ ከሀይሌ ጋርመንት ወደ ጀሞ እንዲሁም ቃሊቲ የሚወስዱት መንገዶች አካባቢውን ሌላ ከተማ አስመስለውታል። ይህን ሁሉ እየቃኘሁ ሰፈራ ተብሎ ከሚጠራው አካባቢ ደረስኩ።
ከጓደኛዬ ጋር ሰላምታ ተለዋወጥን ቤት ይሸጣል ወደተባለበት ሰፈር ባጃጅ ይዘን ቀጠልን። አንድ ኪሎ ሜትር ያህል ወደ ምስራቅ አቅጣጫ ከተጓዝን በኋላ በተለምዶ ዱላ ማርያም ወደተባለውና ይሸጣል ወደ ተባለው ቤት አካባቢ የሚወስደውን የጠጠር መንገድ ተያይዝን። መንገድ ያንገጫግጫል።
አይኔና ጆሮዬ አሁንም አላረፉም። በአካባቢው አዲስ የሆነብኝ ሁሉ መጠየቄን ቀጥያለሁ። እናም አይኔ ከፊት ለፊቴ ካሉት የጋራ መኖሪያ ህንጻዎች ላይ አረፈ። ከጠጠር መንገዱ በስተግራ ከዋናው አስፋልት መንገድ ደግሞ በቀኝ በኩል እጅግ ባማረ ሁኔታ የተገነቡ የጋራ መኖሪያ ቤቶችን ተመለከትኩ። መኖሪያ ቤቶቹ ተገንብተው ያለቁ ቢሆንም የመሰረተ ልማት ያልተሟላላቸውና ለነዋሪዎች ያልተላለፉ መሆናቸውን ጠይቄ ተረዳሁ።
አሁንም መንገዳችንን ቀጥለናል። በጋራ መኖሪያ ህንፃዎቹ ላይ ሰዎች ውር ውር ሲሉ አየሁ፤ ልብሶችም ተሰጥተዋል፤ ከቤቶቹ መስኮት ሆነው ቁልቁል የሚመለከቱም ነበሩ። በአብዛኛው የጎዳና ተዳዳሪዎች መሆናቸውና አልፎ አልፎም ልጆች ያላቸው የተቸገሩ ሰዎች ህንፃዎቹን ጊዜያዊ መጠለያ እንዳደርጉዋቸው ተነገረኝ።
የጋራ መኖሪያ ህንፃዎቹን አልፈን አንድ ድልድይ ተሻገርንና ቦታው ላይ ደርስን፤ አካባቢው ላይ ቤት ሻጭና ገዢን የሚያገኛኝ እሳት የላሰ የሚሉት አይነት ደላላ አገኘን። ደላላው ገና ብዙም ሳንጠይቀው ከሁኔታችን ተረድቶ ነው መሰለኝ ስለአካባቢው ብዙ ነገረን፤ ይፈጥናል። እዚያ ሰፈር ላይ ከ13 ዓመት በፊት በ15 ሺ ብር በገዛው 300ካሬ ሜትር መሬት ላይ ቪላ ቤት ሰርቶ እንደሚኖር ገለጸልን።
ደላላውን ይዘን ይሸጣሉ የተባሉ ቤቶችን እየዞርን ማጠያየቅና ማየት ጀመርን። ዋጋቸው ቀድሞ ከተነገረኝ ብዙም ልዩነት የለውም። ወደ መንደሩ ሲገባ ካለው የተበላሸ መንገድ በስተቀር አካባቢው ከመሀል ከተማ ብዙም የሚርቅ አይደለም።
ጓደኛዬ የገዛውን ቤት አየሁት። ለመኖር እንዲያስችል ሆኖ በደንብ ተገብቷል። የራሱ ግቢና ውስን ክፍሎች አሉት። ቤቱን የገዛው በዚህ ደላላ አገናኝነት መሆኑን ጓደኛዬ ነገረኝ።
አሁን ደግሞ ቆም ብዬ ስለቤቶቹ ህጋዊነት መጠየቅ ጀመርኩ። ደላላው “ስለ ካርታና ፕሮሰሱ አታስብ›› አለኝ። እነ እከሌና እነክሊት ካሉ ሁሉንም መጨረስ ይቻላል ሲል ነገረኝ። እነሱ እነማን እንደሆኑ ጠየቅሁት። ሌላ ማብራሪያ ከመስጠት ተቆጥቦ መሬቱን ህጋዊ ለማድረግ እንዲሁም ካርታ ለማውጣት የሚያስፈልጉ ሰዎች መሆናቸውን ብቻ ነገረኝ።
ሁኔታ አላማረውም፤ ህጋዊ የማድረጉን ነገር ለእኛ ተወው ሲል ማረጋገጫም ይሰጠኝ ጀመር ። ስልክ እየደዋወልኩ በህጋዊነት ላይ ማረጋገጫ ለማግኘት መጠየቄን ቀጠልኩ። ደላላው የሚለው ህጋዊነት እዚያ ቦታ ላይ ፈፅሞ እንደሌለ ተነገረኝ።
ይሸጣሉ የተባሉትን ቤቶች ባለቤቶች ቀረብ ብዬ ስለካርታ ጉዳይ ስጠይቅም ‹‹ገና ወደፊት ይሰጣል ነው የተባልነው›› ሲሉ መለሱልኝ። ቤቶቹን ህጋዊ ለማድረግ ገና ምንም አይነት እንቅስቃሴ እንዳልተጀመረም ሰማሁ። ምንም አይነት ህጋዊ ሰነድ የሌላቸው ከ250 ሺ እስከ 2 ሚሊዮን ብር የሚጠየቅባቸው ቤቶች አካባቢው ላይ እንዳሉ ተረዳሁ።
አንድ ጓደኛዬ አሁን ከቱሉ ዲምቱ ፍጥነት መንገድ ጋር በሚያገናኛው የለቡ ቱሉ ዲምቱ መንገድ በተገነባበት ቦታ የሆነው ታወሰኝ። የመኖሪያ ቤት ነገር በእጅጉ አሳስቦት ባወጣ ያውጣው ብሎ የጨረቃ ቤት ሰርቶ የደረሰበት። እድሜውን ሙሉ ባጠራቀመው ገንዘብ ቦታ ገዝቶ ቤት ሰርቶ ሲጨርስ ቤቱ የተሰራበት ቦታ መንገድ እንደሚወጣበት ተገልጾ እንዲፈርስ መደረጉ፣ አሁን ቤት ያየንበት አካባቢም ከህገወጥ ግንባታ ጋር በተያያዘ በአንድ ወቅት ትልቅ ውዝግብ የተፈጠረበትና የወረዳ ስራ አስፈጻሚ ህይወት የጠፋበት ሁኔታ ታወሰኝ።
አንዳንዴ ቸኩለውና በደላሎች ተታለው በስንት መከራ ያሰባሰቡትን ቅሪት በትነው ሜዳ ላይ የቀሩትን ሳስብ ቤት የመግዛቱን ሀሳብ በይደር አቆየሁት። አበቃሁ፤ ቸር ይግጠመን።
ተገኝ ብሩ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 22/2013