የጽድ ሰፈሩ ጠላ ቤት ሁሌም በደንበኞች ይደምቃል። ስፍራውን ሽተው የሚመጡ ሁሉ ጠላ በጣሳ አስቀርበው ይጎነጫሉ። በአቅማቸው ወዳጅ ዘመድ ለመጋበዝ የሚፈልጉ የእማማ ሽታዬን ጠላ ይመርጡታል። ሽታዬ በየቀኑ የሚመጡ ደንበኞችን ተቀብለው በወጉ ያስተናግዳሉ።
አንዳንዴ ጠላ ቤቱ በእንግዶች ተሞልቶ ይውላል። ሰዓት ሳይመርጡ ብቅ የሚሉ ደንበኞች በውሏቸው ጠላውን ቁርስ ምሳ ያደርጉታል። አንዳንዶች ከጠላው ሲደጋግሙ በሞቅታ ይጫወታሉ። ሌሎች ከመናገር ማድመጥ መርጠው በዝምታ ይዋጣሉ።
መደዳውን ተቀምጠው ከሚጠጡት መሀል ጠብና ነገር የሚጭሩ አይጠፉም። እንዲህ አይነቶቹ ከብዙዎቹ ሲጣሉ ሲናቆሩ ማየት የተለመደ ነው። እማማ ሽታዬ ሁሉን እንደባህሪው እያስማሙ፣ የሚሄድ የሚመጣውን ሲያስተናግዱ ይውላሉ።
አንዳንዴ ደንበኞች ሲበረክቱ ቤት ደጁ በሰው ይሞላል። እንዲህ በሆነ ጊዜ የእማማ ሽታዬ ጠላ ለሁሉም አይደርስም። ጥቂቶች ተስተናግደው ብዙዎች ይቀራሉ። ይህን አውቀው ኮማሪቷ ‹‹አልቋል፣ጨርሻለሁ›› ሲሉ የቤቱ ቋሚ ደንበኞች ይበሳጫሉ። ከውጭ የሚገቡትም ከደጅ ይመለሳሉ።
አንዳንዴ ደግሞ በሽታዬ ቤት የጣሳ ምልክት አይተው የገቡ ሁሉ በበቂ ይስተናገዳሉ። ወይዘሮዋም እስከ ምሸት አስተናግደው ለነገው ያስባሉ። በጆግ እየተሞላ በየጠረጴዛው የሚቀርበውን ጠላ ፉት እያሉ ቀናቸውን የሚገፉ ደንበኞች በርካቶች ናቸው። እንዲህ አይነቶቹ ለዕለት መጎንጫቸው አጥተው፣ ተቸግረው አያውቁም።
ከሽታዬ ቤት ደንበኞች አብዛኞቹ በአነስተኛ ኑሮና ህይወታቸው ይታወቃሉ። ከነዚህ መሀል በርከት ያሉት የቀን ገቢ ያላቸው ለፍቶ አዳሪዎች ናቸው። የቀን ሰራተኞቹ ከፍ ካሉ መዝናኛዎች አዘወትረው አያውቁም። ውሃ በጠማቸው ጊዜ ለጉሮራቸው ማርጠቢያ የሽታዬን ጠላ መጎንጨትን ይመርጣሉ።
ከበደ ማሩ
ከበደ ማሩ ተወልዶ ያደገው በአዲስ አበባ ነው። በልጅነቱ የትምህርት ዕድል አግኝቷል። በዕድሜው ከፍ እንዳለ ወላጆቹ እንደ እኩዮቹ ትምህርት ቤት እንዲገባ አድርገዋል። ከበደ የአንደኛ ደረጃ ትምህርቱን በወጉ ተምሯል። የዛኔ ቤተሰቦቹ እንደ ልጅነቱ የሚሻውን ሁሉ እያሟሉ፣ያማረውን እያለበሱ የፍላጎቱን አሟልተዋል። ሁለተኛ ደረጃ ሲደርስ ለራሱ አላነሰም። በትምህርቱ በርትቶ ነገን የተሻለ ለመሆን ሲጥር ሲጎብዝ ቆይቷል።
ከበደ አስረኛ ክፍል ሲደርስ ለማትሪክ ፈተና ተቀመጠ። ፈተናውን አጠናቆም የጓጓለትን ውጤት ጠበቀ። አይምሮው ከውጤቱ ጀርባ የሚሆነውን እያሰበ መልካሙን ሁሉ ይመኛል። እንዳሰበው የማትሪክ ውጤቱ ካማረለት የነገውን ብሩህ ህይወት ከብርታት ጋር ይቀበላል። በርካቶች በትምህርት ድህነትን እንዳመለጡ የሚያውቀው ከበደ ከእነሱ ጥግ ለመድረስ ራሱን አስቀድሞ አዘጋጀ።
ከበደ ውጤቱ እስኪደርሰው መልካሙን ሁሉ ሲያስብ፣ ሲያቅድ ከረመ። በትምህርቱ የሚያገኘውን አሸናፊነት በምናብ ጨብጦም ከከፍታው ተገኘ። የማትሪክ ውጤትን የመስሚያው ጊዜ ሲቃረብ ተፈታኞች የአይምሯቸውን ስራ ለማየት ከትምህርት ቤቱ ተገኙ። ከተገኙት ገሚሶቹ እንዳሰቡት ሆነላቸው። ውጤታቸው ነጋቸውን የሚሰራ፣ መንገዳቸውን የሚያቀና መሆኑን ሲረዱ ለቀጣዩ በሰፊው አቀዱ። ከተማሪዎቹ አንዳንዶቹ በመካከለኛ ውጤት ከመውደቅ ተረፉ። እነሱ አማራጮች አስልተው፣ ከቤተሰብ ተማክረው የተሻለውን ነደፉ።
ከበደና መሰሎቹ ውጤታቸው አልሰመረም፤ በማትሪክ ውጤታቸው ካለፉት ዘንድ አልደረሱም። በአሸናፊነት ያሰቡት ባይሳካ ብዙዎች በራሳቸው መንገድ ቀጠሉ። ኑሮን ለመምራት፣ ህይወትን ለማሸነፍ በተገኘው የእንጀራ ገመድ ታሰሩ።
ከበደ የማትሪክ ውጤቱ እንዳልተሳካ ሲያውቀው መተዳደሪያውን ፈላለገ። ስለትምህርት ማሰቡን ረስቶም ገንዘብ ለማግኘት ሮጠ። ቆይቶ ሙከራው መልካም ሆነለት። ጉልበቱን ሲገብር፣ ላቡን ሲያንጠፈጥፍ የልፋቱን፣ የድካሙን ማግኘት ያዘ።
የትናንቱ ተማሪ የዛሬ ለፍቶ አዳሪ ሊሆን ግድ አለ። የስራ ውሎው ቀለም ከቆጠሩት፣ በትምህርት ከላቁት ተረታ አላቆመውም። የእንጀራ ምንጩ፣ የጉልበት ዋጋ ከሚከፈልበት፣ የላብ ጠብታ ከሚታይበት፣ ስፍራ ሊሆን ግድ አለው።
ከበደ በስራ ሲደክምና ውሎ መዝናናት ሲያምረው ከእማማ ሽታዬ ጠላ ቤት ጎራ ይላል። በዚህ ስፍራ አብረውት የሚታደሙ ባልንጀሮች አያጣም። እነሱን ባገኘ ጊዜ ጆግ ሙሉ ጠላ አዞ አብሯቸው ይጋራል። ጓደኛሞቹ ከጠላው እየቀዱ፣ እየደገሙ ከሞቅታና ስካር ይደርሳሉ። ይሄኔ የሚጠጡት ጠላ ብዙ እያስወራ ያስቀባጥራቸዋል።
አንዳንዶች መጠጡ ከእነሱ ሲዋሃድ ብሶተኛ ይሆናሉ። መተከዝና ማልቀስ ያምራቸዋል። ሌሎች ደግሞ ስካሩ ሲያሸንፋቸው በአፋቸው ነገር ይሞላል። አይምሯቸው ቂም እያመላለሰ ጠብና ድብድብ ይሻሉ። እንዲህ አይነቱ ዝብርቅርቅ ባህሪይ በደንበኞቹ ዘንድ የተለመደ ነው።
ባለ ጠላ ቤቷ በቤታቸው የሚመላለሱ እንግዶችን እንደ ባህሪ አመላቸው ይዘው፣ እንደአመጣጡ ይመልሳሉ። በዚህ ስፍራ በሀሳብ የማይስማሙ፣ ያለምክንያት የሚጋጩ ይበረክታሉ። ብዙ ጊዜ ስለኑሮና ህይወት፣ ስለ አገርና ፖለቲካ፣ እየተመዘዘ ውይይት ክርክሩ ይጦፋል። አብዛኞቹ በጭቅጭቅ ብዛት ስካራቸው ያይላል፣ እየቆየ በሚያጃጅላቸው ትኩስ ጠላ ደንብዘውም አፍ አንደበታቸው ይታሰራል።
ይህ አይነቱ ትዕይንት በጽድ ሰፈሩ እማማ ሽታዬ ጠላ ቤት አዲስ ሆኖ አያውቅም። ዓመታትን በቆጠሩ ደንበኞች ማንነት ውስጥ መገለጫ ባህሪ እንደሆነ ዘልቋል።
ከበደ ከስራ መልስ ብቅ በሚልበት ጠላ ቤት ብዙዎች ያውቁታል። እሱም ቢሆን የአብዛኞቹ ማንነት አይጠፋውም። ሁሉም የወግና ደንቡን ለማድረሰ በሚታደምበት ስፍራ ፍቅር ከደስታ፣ ጠብ ከግልግል፣ ቂምን ከጥላቻ ሲጋሩ ቆይተዋል። ያም ሆኖ እንደየስሜትና ልምዳቸው በአንድ ቦታ የመገኘታቸውን ልማድ ትተውት አያውቁም።
የካቲት 6 ቀን 2011
ከበደ በዚህ ቀን ስራ ውሎ ወደቤት እየተመለሰ ነበር። ወደሰፈሩ መቃረቢያ ሲዳረስ ከደስታ ጋር ፊት ለፊት ተገናኙ። ደስታ ሀይልና ጉልበቱ ከሰው የሚያጋጨው ጎረምሳ ነው። በእጁ የቢራ ጠርሙስ ይዟል። አስቀድሞ ሲጠጣ ስለነበር ስካሩ በፊቱ ይነበባል። ደስታ ሀይለኛና ተደባዳቢ መሆኑን ያውቃል። ብዙ ጊዜ ከሰዎች እየተጣላና እየጎዳ በእስር መቆየቱን ሰምቷል።
ከበደ በመንገዱ ሰው አለመኖሩን አይቶ ደነገጠ። ደስታ በግልጽ ካገኘው ያለምክንያት እንደሚጣላው ገመተ። እየሰጋ፣ እየፈራ አጠገቡ ደረሰ። ደስታ ከበደን እንዳየው ውስጡ በሸቀ። ዓይኑን አፍጥጦ ቀረበው። ሁኔታውን ያየው ከበደ መንገድ ሊለቀለት ሞከረ። ይህን ሲያይ ቀደመውና አጠገቡ ደረሰ።
ደስታ የያዘው የቢራ ጠርሙስ ፊቱ ላይ ሲያርፍ ከበደ ሰማይ ምድሩ ዞረበት። እንደደነገጠ ከስፍራው ሊያመልጥ ሞከረ። ፊቱ ደም በመልበሱ አልሆነለትም። ይህን ሲያይ ደስታ ያንገላታው ጀመር። ከበደ እንደምንም ከእጁ አምልጦ ከቤቱ ደረሰ። የተፈነከተው ፊቱ ህመም በስቃይ አውሎ አሳደረው። ይህን ያዩ ጉዳዩን ለህግ እንዲያቀርብ፣ ለፖሊስ እንዲያመለክት መከሩት። ከበደ ድርጊቱ ሲፈጸም ሰው ባለመኖሩ የታሰበውን አላደረገም። በቁጭት እንዳዘነ በንዴት እንደበገነ፣ ቀናትን ቆጠረ።
ቤት ያከረመው የከበደ ቁስል ከስራው አደናቅፎ ካሰበው ሁሉ አስቀረው። ከስራ መስተጓጉሉን እያሰበ በትካዜ ከረመ። ደስታ ያደረገውን በቀላሉ መርሳትና መተው አልሆነለትም። ጠርሙሱ ያረፈበትን ምልክት እያሻሸ ህመሙን አጣጣመው። በሆነው ሁሉ እሱን ከሶ ለፍርድ ያለማቆሙ ያናደድ፣ ያንገበግበው ያዘ።
ከበደ አንዳንዴ ደስታን በሩቁ ሲያይ ውስጡ ይቀየራል። እንደዋዛ ፈሶ የቀረው ደሙ ፣ በፊቱ የታተመው ምልክትና የተፈጸመበት ድርጊት ሁሉ እንደ አዲስ ይታየዋል። አንዳንዴ ድንገት ደርሶ ‹‹እንቀው›› ከሚል ስሜቱ ጋር ግብግብ ይገጥማል። ከራሱ እየታገለ ውስጡን ሲያሸንፍ ደ ግሞ መረጋጋት ይጀምራል።
ደስታ ከበደን በጠርሙሱ ሲመታው ለአንዴ ብቻ አልነበረም። እየደጋገመ በፊቱ ላይ አሳርፏል። በድርጊቱ ለራሱ እማኝ የሆነው ከበደ ይህን ሲያስታውሰ ይበልጥ ይበሽቃል። እየበሸቀ አርቆ ያስባል። እያሰበ ብዙ ያቅዳል።
የጠላ ቤቱ ውሎ እንደተለመደው ቀጥሏል። ከስራ መልስ በስፍራው ብቅ የሚሉ ደንበኞች የልምዳቸውን እያደረሱ ይወጣሉ። ደስታ ከህመሙ አገግሞ ስራ ከጀመረ ወዲህ የጠላ ቤት ደንበኝነቱ ቀጥሏል። ኮማሪቷ ሽታዬ እንደወትሯቸው የመጣውን እንግዳ ይቀበላሉ። ጠላው ተሸጦ ካለቀባቸው ለስፍራው እንግዶች በወጉ አስረድተው በሰላም ይሸኛሉ።
ከበደ በሚያዘወትርበት ጠላ ቤት አልፎ አልፎ ደስታን ያያዋል። ባገኘው ቁጥር የሚታወሰውን እውነት በቀላሉ አይዘነጋም። የተጎዳ ፊቱን እያበሰ የፈሰሰ ደሙን ያስታውሳል፣ የድርጊቱን ክፋት እየሳለ የሆነውን ሁሉ ይከልሳል። ደስታ በከበደ የፈጸመውን የሚያስታውሰ አይመስልም። የመጣበትን ጠጥቶ ከሌሎች ጨዋታ ተጋርቶ ወደመጣበት ይመለሳል።
የካቲት 21 ቀን 2012 ዓም
ከበደ ቀናትን መቁጠር ይዟል። ደስታ ያደረሰበት ጥቃት ድፍን አንድ ዓመት ሆኖታል። የፊቱ ምልክት የጥቃቱ አሻራ እየደበዘዘ ነው። የውስጡ ቂምና በቀል ግን እንደፋመ፣ እንደጋለ ቀጥሏል። ሁሌም ደስታን ባየው ጊዜ እንደ አዲስ የሚግመው ውሰጠቱ እየፈተነው፣ እየታገለው ነው።
ከበደ በዚህ ቀን ከስራ መልስ ከእማ ሽታዬ ጠላ ቤት ተገኝቷል። ከመምጣቱ በፊት በሹራቡ እጅጌ የሻጠው የዳቦ ቢላዋ በስፍራው መኖሩን እየነካ አረጋግጧል። መንገድ ላይ ደስታን ካገኘው ራሱን መከላከል ይኖርበታል። ከተተናኮለውም እንደቀድሞው ዝም እንዳይል ከራሱ ጋር መክሯል።
ጠላ ቤቱ በደንበኞች ተሞልቷል። ኮማሪቷ ባዶ የሆኑ የጠላ ጆጎችን ከየቦታው እያነሱ ነው። ከበደ ቦታው ሲደርስ ጓደኞቹን አገኛቸው። አጠገባቸው ደርሶ ጠላ እንዲቀርብላቸው ጠየቀ። ሁለት ሙሉ ጆግ ጠላ ከጠረጴዛቸው ቀረበ። ከእሱ እየደጋጋሙ ተገባበዙ።
ጥቂት እንደቆየ ከበደ ሞቅታ ተሰማወ። አሁንም ደጋግሞ እየተጎነጨ ወደውጭ አሻግሮ ቃኘ። ድንገት ዓይኖቹ ከአንድ ሰው ላይ አረፉ። ደስታ ከውጭ ወደ ውስጥ ብቻውን ሲገባ ተመለከተው።
ከበደ ደስታን ሲያየው ተቁነጠነጠ። ከዓመት በፊት በእሱ ላይ የፈጸመውን ድርጊት ተመላለሰበት። ደስታ ከበረንዳው ቁጭ እንዳለ ጠላ እንዲቀርብለት አዘዘ። ባለጠላዋ ሽታዬ ቀረብ ብለው ጠላ ማለቁን ነገሩት። ደስታ ከጠላ ቤቱ በረንዳ ላይ እግሩን አጣምሮ ተቀመጠ። ከጎኑ ማንም ስለሌለ በግላጭ ይታያል። በእጁ ያለውን ስልክ እየነካካ በዝም ታ ተውጧል።
ከበደ ይህን እንዳየ አይምሮ ብዙ አሰበ። ከአንድ ዓመት በፊት የፈጸመበት በደል፣ ትውስ አለው። ባጋጠመው ችግር ከስራ የቀረባቸውን ቀናት እያስታወሰ ተብሰለሰለ። የቆየ ንዴቱ እያገረሸ ነው። ውስጡ በንዴት መቀጣጠል ሲጀምር ከነበረበት ተነስቶ ደስታ ወዳለበት በረንዳ ተንደረደረ። ካለበት ደርሶ የሹራቡን ቢላዋ መዞ ሲያወጣ ልብ ያለው የለም ።
ጊዜ አላጣፋም ። በመጣበት ፍጥነት የደስታን ጉሮሮ አንቆ ከመሬት ጣለው። ደስታ በድንገቴው ጥቃት ተደናግጦ ለመሮጥ ሞከረ። ፈጥርቀው የያዙት የከበደ እጆች አላላወሱትም።
ሁለቱም ተያይዘው መታገል ጀመሩ። የከበደ ሀይል መበርታት ሲጀምር ቢላዋውን ከሹራቡ አውጥቶ በደስታ የግራ ትከሻ ላይ አሳረፈው። ቢላዋው ከአካሉ እንደተሰካ ደስታ ከመሬት ወድቆ ተዘረረ። ከበደ ይህን ሲያረጋግጥ ቢላዋውን ከትከሻው ነቅሎ ወደ በሩ አቅጣጫ ተፈተለከ። እማማ ሽታዬ ከመሬት ወድቆ በደም የተለወሰውን ደስታ እያዩ የድረሱልኝ ጩኸት አሰሙ። ጨኸቱን የሰሙ ሁሉ ወደ ጠላ ቤቱ ጎረፉ።
ከበደ ከስፍራው እንደወጣ ደም የነካውን ቢላዋ ይዞ ተፈተለከ። ደስታ ከዓመት በፊት በእሱ ለፈጸመው ድርጊት የእጁን እንደሰጠው እየተሰማው ነው። በአካባቢው ካለ አንድ ቤተክርሲቲያን አጸድ ሲጠጋ ጨለማው ከዓይን መያዝ አልፎ ነበር። እየሮጠ ወደ መቃብር ስፍራው አመራ ። በእጁ የያዘውን ቢላዋ በርቀት አሽቀንጥሮ ከግቢው ተረጋግቶ ወጣ።
የፖሊስ ምርመራ
የአካባቢው ፖሊስ አባላት ወንጀሉ ወደተፈጸመበት ስፍራ ሲደርሱ የሰፈሩ ነዋሪዎች ደስታን ወደ ሆስፒታል ወስደውት ነበር። ፖሊስ ሙሉ መረጃ ለማግኘት እማኞችን ጠየቀ። ካገኘው እውነት ተነስቶም ተፈላጊውን ማሰስ ጀመረ። እንዲህ በሆነ በማግስቱ ተጎጂው በህክምና ላይ እያለ ህይወቱ ማለፉ ተሰማ። ዜናው ከተሰማ ጥቂት ቆየት ብሎም ተጠርጣሪው ከበደ ማሩ ከፖሊስ ጣቢያ ደርሶ እጁን ለህግ ሰጠ።
መርማሪዋ ኢንስፔክተር ዓለም ጸሀይ መካሻ የግለሰቡን የዕምነት ክህደት ቃል ተቀብለው የምስክሮችን እማኝነት አሰፈሩ። የምርመራው ሙሉ ቃል በፖሊስ የወንጀል መዝገብ ቁጥር 1139/12 ላይ በወጉ ተመዝግቦ ዶሴው ለዓቃቤ ህግ የክስ ሂደት ተላለፈ።
ውሳኔ
ሀምሌ 16 ቀን 2011 ዓ.ም በችሎቱ የተሰየመው የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በተከሳሽ ከበደ ማሩ ላይ የመጨረሻውን የፍርድ ውሳኔ ለመስጠት በችሎቱ ተሰይሟል። ፍርድ ቤቱ ተከሳሹ የቀረበበትን ቴክኒክና የሰዎች እማኝነት ከግምት አስገብቶም ጥፋተኛ መሆኑን አረጋግጧል። በዕለቱ በሰጠው ውሳኔም እጁ ከተያዘበት ጊዜ አንስቶ በሚታሰብ የአስራ ሁለት ዓመት ጽኑ እስራት እንዲቀጣ ብይኑን አሳልፏል።
መልካምስራ አፈወርቅ
አዲስ ዘመን መስከረም 1 ቀን 2013 ዓ.ም