እንደምናውቀው የዛሬው እኛ መሰረቱ የጥንት እናት አባቶቻችን ናቸው። ከዛ ከእሩቁ ጊዜ ጀምሮ ደግሞ ትውልዶች ተፈራርቀዋል። ሁሉም የየድርሻውን እየተወጣ (ቅብብሎሽ) እዚህ የዛሬዎቹ እኛ ላይ ደርሷል። “እኛስ ምን እያደረግን ይሆን?” የሚለውን ሌላ ጸሐፊ ሊቀጥልበት የሚችል ሲሆን የዚህ ጽሑፍና እንግዳው ትኩረት ግን፣ ከርዕሱ አኳያ የቅርብ ሃላፊው ላይ ይሆናል።
ሁልጊዜ ትውልድ በዥረት ይመሰላል። በተለይ ሳያቋርጥ የመሄዱ ጉዳይ ነው ለዚህ ያበቃው። በመሆኑም እየፈሰሰ እየፈሰሰ እየፈሰሰ እዚህ ደርሷል። ሲፈስ ግን ሁሉም አንድ አይነት አይደለም። አንዳንዱ ፀጥ ብሎ ሲፈስ፣ አንዳንዱ ደግሞ እንደ ጋጋኖ እየጮኸ ነው። ሌላው ጥርት ያለ ሲሆን አንዳንዱ ግን ደም ያደፈረሰው ይመስል የቀላ ይሆናል። ባጠቃላይ ዥረትም እንበለው ወንዝ በይዘት፣ መጠን፣ ርዝመት፣ ጥልቀትና ስፋት ይለያያል እንጂ ከመፍሰስ የሚያግደው ኃይል የለም። በዚህ ዥረትና ፍሰቱ ሂደት ግን አንድን ተዘውታሪ ጥቅስ ጠቅሶ ማለፍ ተገቢ ነው፤ “አገሬ ለኔ ምን አደረገችልኝ ሳይሆን እኔ ላ’ገሬ ምን አደረኩላት”።
እርግጥ ነው በአንዳንድ ክፉ ጊዜያት “አገሬ ለኔ ምን አደረገችልኝ ሳይሆን እኔ ላ’ገሬ ምን አደረኩላት” ያሉ ሰዎች እንኳን ሊጠቀሙ ሲጎዱ እንጂ ማንነታቸው እንኳን ሲታወቅላቸው አይታይም። የኢትዮጵያ ሰራዊት ስሙ “የደርግ ሰራዊት” ነበር። ከዛ በፊትም እንዲህ አይነት ሁኔታ ስለመኖሩ መጠራጠር የማይቻል ሲሆን “እምዬ ኢትዮጵያ ሞኝ ነሽ ተላላ / የሞተልሽ ቀርቶ የገደለሽ በላ” የሚለው ማስረጃችን ነው። (በተለይ የንጉሥ ኃይለሥላሴ አስተዳደር በዚህ በኩል ከተሸወዱት የኢትዮጵያ መንግስታት ቀዳሚው ሲሆን፤ በአመራሩ ውስጥ የተሰገሰጉት በአብዛኛው ባንዶችና አጃቢዎቻቸው ነበሩ ይባላል። በተለይ ጣሊያን በተደቆሰ ማግስት።)
ምናልባት ስለ ትውልድ ሲነሳ ሳይጠቀስ ሊታለፍ የማይገባው አቢይ ጉዳይ ቢኖር አባላቱ ናቸው። የእያንዳንዱ ትውልድ አባላት የየዘመናቸው አንቀሳቃሽ ሞተሮች፤ የየዘመኖቻቸው ታሪክ ሰሪና ፀሀፊዎች ናቸው። ያለ አባላቱ ተግባርም የለም፤ ታሪክም የለም፤ ምንም የለም። በየዘመኑ ጥፋትም ኖረ ጥሩነት ሀላፊነቱ የዛ ትውልድና አባላቱ ነው። የዛሬው እንግዳችን የየትኛው ትውልድ አባል ናቸው፣ ምን ምን ሀላፊነትንስ ተወጡ፣ ምን ምን ተግባራትን ፈፀሙ፣ ምንስ አተረፉ? እንደሚከተለው ቀርቧል።
ወ/ር አሰፋ አለሙ ይባላሉ። (ማእረጋቸው “አልመጣም” (ለውጡ አደናቀፈው) እንጂ መቶ አለቅነት እንዳገኙ ነግረውናል።) ገና በ1967 ዓ.ም ውትድርናውን ዓለም ተቀላቀሉ፤ ስልጠናቸውንም በሁርሶ ማሰልጠኛ ጣቢያ ተከታተሉ። ተወልደው ያደጉት እዚሁ አራት ኪሎ ባሻ ወልዴ ችሎት አደባባይ ሲሆን አራት ልጆችን አፍርተው ለወግ ማእረግ ያበቁ ሲሆን አንዱም ታዋቂው የብሔራዊ እግር ኳስ ተጫዋቹ ሙሉአለም እጅጉ (“እጅጉ” በወዳጅ አድናቂዎቹ የሚጠራበት የኳስ ሜዳ የፍቅር ስሙ ሲሆን፤ ትክክለኛ ስሙ ሙሉአለም አሰፋ ነው)፤ አሁን እንግሊዝ ሀገር ነው ያለው።
ልጆቻቸውን በተመለከተም “እኔ የቀረብኝ አንሶ የእነሱ መስተጓጎል የለበትም” በሚል በደንብ ማስተማሩን ተያያዙት፤ ተሳካላቸውም። ሁሉም ልጆቻቸው ለአገር የተረፉ ባለውለታ ሆነዋል፤ እየሆኑም ያሉ አሉ። የመጨረሻዋ ልጃቸው ዶ/ር ሰላማዊትም አሁን አብራቸው ነው የምትኖረው።
“እኔ ቤተሰቦቼ እንዲጎሳቆሉ አልፈልግም። በመሆኑም እላይ እታች ብዬ፤ ደክሜ አስተምራለሁ። እግዚአብሔር ይመስገን ሁሉም ጥሩ ደረጃ ላይ ናቸው” ሲሉም አባታዊ ሀላፊነታቸውን በሚገባ መወጣታቸውን ይናገራሉ። “አሁንም እኔ የትም ሮጬ ተባራሪ ስራ እሰራለሁ። ለምሳሌ አሁን በአንድ የመንግስት ተቋም (ቴሌ) በየሶስት ወሩ በሚታደስ የኮንትራት ውል ስራ እየሰራሁ ነው።” ሲሉም ያሉበትን የጥንካሬ ሁኔታ ይገልፃሉ።
“ከስልጠና በኋላ በቀጥታ ያመራነው ወደ ጅጅጋ ሲሆን የመጀመሪያ ግዳጄንም የተወጣሁት በዚሁ ጦር ግንባር የዚአድባሪን ጦር አይቀጡ ቅጣት በመቅጣት ነው” የሚሉት ወታደር አሰፋ ከጦርነቱ ከባድነት የተነሳ በሳንጃ እጅ ለእጅ መሞሻለቅ ሁሉ እንደነበርና በመሞሻለቁ ወቅትም በሳንጃ የተጎዳውን (በረጅሙ የተቀደደውን) እጃቸውን እያሳዩ ከባድ የመቁሰል አደጋ ሁሉ ይደርስ እንደነበር አጫውተውናል።
“በመጨረሻም ካራማራ ላይ ታሪክ ተሰራ፤ ሁሉም ነገር ያለቀው ካራማራ ተራራ ላይ ነው። ሁሉም ነገር እዛ ላይ ተሰራ፤ እዛ ላይ አለቀ። ድል ሆነ፤ ድል ተመዘገበ።” ያሉን ባለታሪኩ ከዛ በኋላ አለቆቻችን በህይወት የተረፍነውን ሰበሰቡንና በሉ እንግዲህ ደመወዝ የለም፤ ክፍያ የለም፤ በመንግስት መስሪያ ቤቶች ውስጥ 10፣ 10 ሰዎች ትመደባላችሁ። ደሞዝተኛም ሆናችሁ ትኖራላችሁ ተብሎ እንደተነገራቸውም ይናገራሉ።
“ለምንድን ነው ደመወዝ የሌላችሁ?” ብለናቸውም “ከዚህ እንደተወሰድን ሚሊሻ ነው የተደረግነው፤ ሚሊሻውን ነው እንድንቀላቀል የተደረገው። በነፃ ነው ላገራችን የዘመትነው። ሱማሌን ለመግረፍ ነው የሄድነው፤ ገርፈናታል። ሚሊሻ እንጂ መደበኛ ወታደር አልነበርንም። ለዛ ነው ደመወዝ የሌለን።” ሲሉ መልሰውልናል።
ወታደር አሰፋ እንደነገሩን ከሆነ በዚህ የመንግስት ውሳኔ መሰረት በ1969 ዓ.ም ወ/ር አሰፋ አንበሳ ጫማ ፋብሪካ ይመደባሉ። በቅርፃቅርፅ /ዲዛይን/ ክፍል ውስጥ እየሰሩ እያሉ ሌላ ዙር ጦርነት በአገሪቱ ይከሰታል። በወቅቱ በሰሜኑ በኩል ጦርነት ተፋፍሞ ስለነበር፤ የዳግም ዘመቻ ጉዳይ መጣ። እሳቸውም ጥሪውን በመቀበልና ዳግም ዘማች በመሆን እንደ ገና ወደ ሰሜን ጦር ግንባር፤ ወደ ሱዳን (በራስታ መልክ የሚታየው ፎቷቸውን ሱዳን፣ አባይ ወንዝ ጋ ነው የተነሱት) ተንቀሳቀሱ።
በወቅቱ ከአባይ ጋር በተያያዘ (ፕሬዝዳንት መንግሥቱ አባይን ለመገደብና ሙሉ ለሙሉ መሰረቱን ለማስጠናትና ፕላን ለማስነሳት ከእስራኤል፣ ጃፓን፣ ሶቪየት ህብረት፣ ጀርመን ሰዎች መጥተው አካባቢው ላይ ውጥረት የነገሰበት ጊዜ ነበር) በአካባቢው የታላላቅ አገሮች እንቅስቃሴ ሁሉ ነበር። ያኔ ሁሉ እዛ ናቸው። ይህንንም “መንግሥቱ የአባይን ወንዝ ፕላን ሁሉ ሲያስነሳ እዛ ነን፤ እዛ ብዙ ስራ ሰርተናል።” በማለት ነው የሚገልፁት።
አስመራ፣ ናቅፋ፣ ቃሩራ፣ አልጌና፣ አቆርዳት …. ያልተዋጉበት የሰሜን ጦር ግንባር እንደሌለ፤ ምን ግዜም በአገር ጉዳይ ላይ ወደኋላ የሚባል ነገር እንደሌለ ያጫወቱን ወ/ር አሰፋ “ወንበዴውን በራያና ቆቦ ሁሉ ደምስሰነዋል። መሳሪያውን ሁሉ ማርከን ደብረ ዘይት (መሳሪያ ግምጃ ቤት) አምጥተን አስረክበናል። ይህች አገር ስንትና ስንት ሰው የሞተላት አገር ነች። አሁን እንደዚህ የማንም መጫወቻ ….. እ ….. ማላገጫ …” (ፊታቸውን በሀዘንና ንዴት ውስጥ ባለ ድብልቅ ስሜት አጅበው ነበር የሚናገሩት) ስንት የሆንለት፤ ስንት የሆንበት አገር ነች።” ካሉ በኋላ “እኔ አገሬን እወዳለሁ። አገሬን በጣም እወዳለሁ። እስካሁንም ድረስ መዋጮ እንኳን ሲባል እንዲያመልጠኝ አልፈልግም። ከየትም ከየትም ብዬ እሰጣለሁ። እኔ እምፈልገውም የአገሬን አንድነት ነው።” ሲሉም የአገር ፍቅር ስሜታቸው እስካሁንም እንደተንቀለቀለ መኖሩን ይናገራሉ።
“ስለጦር ሜዳ ትውስታዎ እስኪ ትንሽ …” ብለናቸውም ነበር። “የአስመራው ነው። በመርከብ አድርገን ከአሰብ ተነስተን በቀይ ባህር በኩል ኤርትራ ገባን። መሳሊትና ጉዝጉዛይ ላይ፣ ሰማይ ጥግ ነው፣ ስምንት ሰዓት የፈጀ አደገኛ ውጊያ ሲካሄድ ነበር። ጀነራል ሁሴን አህመድ የሚባል አዛዥ “በቃ ተመለሱ” ብሎ ልንጨርሳቸው አንድ ሺህ የማይሞሉ የቀሩንን “በቃ አዛዥች አይገደሉም። ይህንን ማእረግ እኮ ያገኘሁት በእነሱ ነው” ብሎ አስቆመን። በውስጣችን የተሰገሰጉት የእሱ አጫፋሪዎችም ደገፉት። ይሄ አይረሳኝም። በዛ ውጊያ ላይ ቆሰልኩ፤ ከረን ሆስፒታል መጥቼ ታከምኩ። ከዛም ወደ ዘነበወርቅ ተላኩ። ይሄ ግራ አይኔ (መነፅራቸውን አውልቀው እያሳዩን) የእኔ አይደለም፤ አሁን አይሰራም። ይህም የሆነው በዚሁ በውጊያው ምክንያት በደረሰብኝ አደጋ ነው። ለአገሬ ስል ነው። እኔ አገሬን ማንም እንዲነካብኝ አልፈልግም።
“ወደ አሁኑ ሁኔታና ኑሮዎ እንመለስና በምን ሁኔታ ላይ ነው ያሉት?” ብለናቸውም ነበር። “አሁን የምኖረው በተባራሪ ስራ ነው። ከአንበሳ ጫማ አንድ ሺህ ብር ጡረታ አገኛለሁ። ከዛ ውጪ ምንም የተደረገልኝ ነገር የለም። ከመንግስት ምንም አላገኘሁም። ወታደር ስለመሆናችን እንኳን አሁን ነው እውቅና የተሰጠን። አሁን ማዕረጋችን እየተሞላ የአገር መከላከያ ሰራዊት አባል (ወታደር) ስለመሆናችን መታወቂያ ተሰጥቶናል። ማህበርም አለን። እንግዲህ ሌላ ሌላውንም ጥቅማ ጥቅም ይሰጡናል ብለን ተስፋ እናደርጋለን።
ለአገራችን ያን ሁሉ ለፍተን ደክመን ምንም የተደረገልን ነገር የለም። ቤት የለንም፤ ቦታ የለንም። እንደ ሌሎቹ፣ ማለትም ከእኛ ጋር ዘምተው እንደነበሩት አንድ ነገር ሊደረግልን ይገባል። ከገጠር ለመጡት ወደ አካባቢያቸው እንዲመለሱ ተደርጎ መሬት ተሰጥቷቸዋል። ቤት ወይም የቤት ቦታ ይሰጣል። እኛ ከከተማ የሄድነው ግን ምንም የለንም።
መንግስት ሰጥቶኝ የነበረውን ቤት (አራት ኪሎ ባሻ ወልዴ ችሎት አደባባይ) ያለአግባብ ፈረሰ። እንደ ሻይ ቤት ነገር ሁሉ አድርገን ቤተሰቡን የምናኖርበት ነበር፤ ፈረሰ። አሁን ያለሁባትን ነው ምትክ ብለው የሰጡኝ። ቤት፣ መስሪያ ቦታ ሊሰጠን ይገባል። ሜዳ ላይ ወድቀን ልንቀር አይገባም። አስር ሳንቲም ደመወዝ ሳይኖረኝ ካንዴም ሁለቴ ዘምቻለሁ። ታዲያ እንዴት ሜዳ ላይ ወድቄ ልቅር? ስለዚህ መንግስት አንድ ነገር ሊለን ይገባል።
የአሁኑን፣ የወቅቱን፣ የጁንታውን አገር የማፍረስ ተግባር በተመለከተም የሚከተለውን ብለውናል።
በጣም ነው ያበሳጨን። ያልተናደደ የለም። ያልተበሳጨ የለም። ጁንታው በሰራው ስራ ስሜቱ ያልተነካ የለም። ልክ ጁንታው ይሄንን አገር የማፍረስ ተግባሩን እንደፈፀመ በተደረገው ጥሪ መሰረት ወደ ግንባር መዝመት እንፈልጋለን ብለን ሄደን ነበር። ሌሎቹ ሄዱ። 27 የምንሆነውን ግን በጤና እክል ምክንያት አትችሉም ብለው በምስጋና መለሱን።
እኔ እራስ ምታት የሆነብኝ ሰው እንዴት አገሩን፣ ተወልዶ ያደገበትን፣ ልጅ ወልዶ ያሳደገበትንና ያስተማረበትን አገሩን ያፈርሳል፣ ሰው እንዴት ባንዳ ሆኖ አገሩን ይክዳል፣ ሰው እንዴት የወንድሙን ደም ያፈሳል? አሁን የሚያስፈልገን ፍቅር፣ ሰላም፣ አንድነት ነው። ይሄ ነው የሚያስፈልገን። ለዚህ ደግሞ እስከመጨረሻው አለሁ። በመዋጮም ሆነ በማንኛውም አቅሜ በፈቀደ ሁሉ አለሁ።
ግርማ መንግሥቴ
አዲስ ዘመን መስከረም 1 ቀን 2013 ዓ.ም