
እነሆ 2014!
አንድ ብለን መቁጠር ጀመርን። ያለፈው ዓመት ወራቱና ቀናቱ ትዝታ ሆነው ከኋላችን ናቸው። የዘመናችንን ታሪክ ለመስራት የተገለጡ አዳዲስ ቀናት። በውስጣዊ ሰውነት በአዲስነት ለሚቀበለው ትርጉም የሚሰጥ። የለውጥ መንገድን የራሱ ላደረገ።
በዘመን መለወጫ ወቅቶች በዓመቱ ውስጥ ሽልማት የተገባቸውን ለይቶ እውቅና የመስጠት ባህል እየተለመደ ያለ ባህል ሆኗል። በዘርፉ ላይ ጎላ ብለው የወጡና አስተዋጾ ያደረጉትን መርጦ የመሸለም ተግባር። ሰዎች በአደባባይ የሚሸልሟቸው ወደ ደረጃው ከመውጣታቸው በፊት ራሳቸውን የሸለሙ መሆናቸውን አስበን እናውቅ ይሆን? እውነታው ግን እርሱ ነው። ለራሳችን ከራሳችን በላይ የሚቀርብ ስለሌለ ራሳችንን ለመሸለም ማንም ሊቀድመን አይገባንም ብሎ የሚያምን ሰው የሚያደርገው። ለራስ ትርጉም በመስጠት የህይወት ቅኝት ውስጥ የሚመዘዝ አንድ ሰበዝ።
አዲስ ዓመትን ለማብሰር የሰፈሩ ልጃገረዶች አበባይሆሽ እያሉ ነው። በየቤቱ ደጃፍ ሄደው እየቆሙ ዜማቸውን አሰምተው የሚሰጣቸውን እየተቀበሉ ከአንድ ቤት ወደ ሌላ ቤት የሚደረግ። ዜማቸውን ለመስማት ተራ በደረሰው በአንድ ቤት በርላይ ቆመው ግን ግርምት ላይ ወደቁ። የደረሱበት ቤት ውስጥ ደስ የሚል የቤተሰብ አባላት ሳቅን ያደምጣሉ። አባት እናት ልጆች ምን እንዳሳቃቸው አያውቁም ከት ብለው እየሳቁ ነው። አበባየሁሽ የሚሉት ታዳጊዎች ቀስ ብለው ድምጻቸውን ዝቅ አድርገው የሚሰሙትን የሳቅ ድምጽ መስማት ቀጠሉ። አባትም ይስቃል፣ እናትም እንዲሁም ልጆችም። ታዳጊዎቹ የቤተሰቡ የደስታ ምክንያት የተከፈተ የቴሊቪዥን ድምጽ ይሆን ብለው አስበው ጆሯቸውን ቢጥሉም የቴሊቪዥን ድምጽ ሊሰማቸው አልቻለም። ግርም አላቸው። የሞቀው ቤተሰብ የሞቀ ጨዋታና ደስታ ትኩረትን በጉልህ የሚስብ ነበር።
ቤተሰቡ በአካባቢው በመልካም ስም የሚጠራ ቤተሰብ ነው። የቤተሰቡ የደስታ መገለጫ የሆነው ሳቅ በረድ ሲል ከልጆቹ መካከል አንዱ ልጅ “እንዴ ስራችንን እኮ ረሳነው” ብላ ጓደኞቿን አስታወሰች። ጓደኞቿም ምላሽ ሰጥተው አበባየሁሽ እያሉ ዜማቸውን ማቅረብ ጀመሩ። ያም ቤተሰብ በሩን ከፍቶ በደስታ አስገባቸው፤ ዳቦ ቆርሶ ፈንዲሻ አዘግኖ ለእያንዱ ልጅ ቤተሰቡ ያዘጋጀውን ጥቅልል ወረቀት በክብር እንደሽልማት ስጦታ ከእያንዳንዱ ቤት የሚጠብቁትን ገንዘብም ሰጥተው ሸኟቸው።
ልጃገረዶቹ ከሌላ ቤት ከተቀበሉት ስጦታ የተለየውን የወረቀት ጥቅልል ፈትተው ለማየት እጅግ ስለ ጓጉ ከፍተው ሳያዩ ማምሸት አልሆንላቸው አለ። በቤተሰቡ የሞላው ሳቅ ግን ከወረቀቱ በፊት ሁሉም ልጆች አንዳች ደስታን ቀድመው ወስደዋል። በራሳቸው ቤት ባለው የሳቅ ልክ የቤተሰቡን ሳቅ መዝነውም በውስጣቸው የተፈጠረባቸውም ስሜት አለ። አባትና እናት በተጣሉ ቁጥር ስቃዩን የምታየው የአበባይሆሽ ቡድን አንዷ አባል ይበልጥ ልቧ ላይ የጎደላት ነገር ሲሰማት ታወቃት። በእርሷ ቤት እናትና አባቷ ሲጣሉ፣ ሲገለማመጡ፣ ሲሰዳደቡ እንጂ እንዲህ ሲሳሳቁ አታውቅምና የእዚህ ቤት ልጆች ምንኛ የታደሉ ናቸው አለች። አንዷ ልጅ ደግሞ እናትና አባቷ በፍቺ ስለተለያዩ ከእናቷ ጋር ስለምትኖር ከምትወደው አባቷ ጋር አብራ ሆና ቤተሰቡ እንዲህ ሲሳሳቅና በደስታ ሲኖር ባለማየቷ ትካዜ ውስጥ ገባች።
የአበባየሆሽ ቡድኑ ህግ የሚቀበሉትን ስጦታ ሁሉ ማታ ለመከፋፈል ቢሆንም የተሰጣቸው የወረቀት ጥቅልል ግን ትኩረታቸውን ስለሳበው “አሁን እንክፍተው ወይንስ ማታ?”ብለው ተነጋገሩ። አብዛኛዎቹ “አሁን አሁን” አሉ። መታገስ አልቻሉምና። በአካባቢያቸው ወዳለው ዛፍ ስር ሄደው ጥቅልሉን ሲፈቱት በሚያምር ጽሁፍ “ቤታችን ድረስ መጥታችሁ መልካም ምኞታችሁን ስለገለጻችሁልን እናመሰግናለን፤ ልጆች ደስታችሁን ራሳችሁ ፍጠሩ ደግሞም ትችላላችሁ!” ይላል። ጽሁፉን ደጋግመው አነበቡት። ፊታቸው ላይ ፍካት ታየ። ከመልካም ቃላቱ ውስጥ የወጣው ፍካት። እናመሰግናለን ተብለው የማያውቁት ታዳጊዎች ይህ ቃል ቦታ ያላቸው መሆናቸውን እንዲረዱ አደረጋቸው።
እኛም ዛሬ የልጆቹን እለት ልዩ ያደረገውን ጽሁፍ መነሻ አድርገን መዳረሻችንን የመሻገር ብስራት አድርገን አዲሱን ዓመት በፍካት እንቀበል።
እናመሰግናለን
የምስጋና ባህል አዎንታዊ መንፈስን በመፍጠር ያለው ሚና ከፍተኛ ነው። በእኛ በኢትዮጵውያን ዘንድ የምሥጋና ባህላችን ጠንካራ የሚባል አይደለም። በአጠገባችን ምሥጋና የሚገባቸው የበረከቱ ሰዎች ኖረው እንኳን አጠገባችን ሳሉ መመልከት ሳንችል ቀርተን እለተ ሞታቸውን እንጠብቃለን። አንዳችን በአንዳችን ህይወት ውስጥ ያለን ቦታ ትርጉሙ ትልቅ ነው። ዛሬ ላይ የሆንበትን ቦታ ተመልክተን ወደ ኋላ ስንመለከት በህይወታችን ውስጥ ትርጉም ያለው ተጽዕኖዎችን ያሳደሩ መልካም ሰዎችን እናገኛለን።
መልካም ሰዎችን ለማመስገን የሚደፍር ባህል መልካም ሰዎች እንዲበዙ የሚያደርግ ነው። የተዘራው ዘር ለሌላ ለሚዘራ ዘር እንዲሁ የሚቀርብ መሆኑን መረዳትም ይገባናል። አስተውለን ማየት ከቻልን መልካም ሰዎች በዙሪያችን አሉ። መልካም ሰዎች ግን መልካምነታቸውን ማየት የሚቻለው የተከፈተ አይን ስናይ ብቻ ነው።
የለቅሶ ስርዓታችን የሚወስደው ቀንና በለቅሶ ጊዜ የምናወጣው ጥልቅ ኀዘን ምንጩ የሟች መልካምነት ትውስታ ሆኖ ይታያል። አንዳችን በአንዳችን ውስጥ ያለን ቦታ የጨመረ በሆነ ቁጥር የለቅሶ ቀን ትርጉሙ ሌላ ነው። ለአንዳንዱ ለቅሶ መድረስ የሆነውን ግቡን ለመምታት ወደ ለቅሶ ቤት ይሄዳል። ሌላው ከልቡ አዝኖ ሊያጽናናም ይገኛል። ለሃዘንተኛው ግን ጉዳዩ ሌላ ነው። በህይወቱ መልካም ነገር የሆነለትን ሰው ማጣት። በመልካምነት ትዝታው ውስጥ ሆኖ ኀዘኑን ማስተናገድ። ከመልካም ሰው ትዝታ ውስጥ የሚወጣ፤ ጥልቅ ኀዘን።
የማመስገን ህይወትን አቅጣጫ ስለማስተካከል ስናነሳ ቅደምተከተሉን ከምንወደው ሰው ማድረጉ ምቾት የማይሰጣችሁ አንባብያን መፈጠራችሁ አይቀርም። ምክንያቱም “እንዴት ከፈጣሪ ቀድሜ ሰውን ስለማመስገን ላስብ” ልትሉ ስለምትችሉ። በእርግጥ አሳማኝ ምክንያት ነው። ነገርግን በአጠገባችን ያለውን በአካል የምናውቀውን ሰው ሊመሰገን ሲገባው ያላመሰገንን እንዴት በአካል የማናውቀውን እግዚአብሔርን እናመሠግናለን? ይህን አመክንዮ በልባችን ይዘን ንባባችንን አስተካክለን መቀጠል እንችላለን። ምሥጋናን ለፈጣሪያችን።
በዙሪያችን ወላጆቻችን፣ አሳዳጊዎቻችን፣ እህት ወንድሞቻችንን፣ ጓደኞቻችንን፣ የሥራ ባልደረቦች፣ ጎረቤቶች፣ የእቁብ የእድር አባላት ወዘተ መልካም ሰዎች በዙሪያችን አሉ። እኒህ መልካም ሰዎች የእኛን ፍላጎት ሁሉ የሚሞሉ ሆነው አይገኙ ይሆናል። እኒህ መልካም ሰዎች ፍጹማን ሆነውም አይገኙ ይሆናል፤ እኛ እንዳይደለነው እነርሱም ላይሆኑ ይችላሉ።
በዙሪያው ያሉትን መልካም ሰዎች ተመልክቶ የምሥጋናን ቃል ማውጣት የቻለ ሰው በጉዞው አስቸጋሪ የሆኑ ሰዎችን ሲያይ እንዲሁ ከቃሉ ሊነፍጋቸው አይገባም። ሰነፍን ስለ ስንፍናው አመስግነው አይደለም፤ ከቁምነገሩ ይልቅ ወሬው ያመዘነበትን ሰው ስለተዛባው ጉዳይ አበጀህ በለውም አይደለም፤ መልካም እሴትን እየናደ ለመኖር የሚታትረውን ሰው ግፋበት ማለትም አይደለም፤ ነገር ግን በየትኛውም ሰው ውስጥ ሊገኝ ስለተቻለው ጥቂት የሚባልም መልካምነት ምሥጋና ይገባል ከሚል ልብ ነው። አስቸጋሪ ሰዎች ከቤታችን እስከ አደባባይ የበረከቱ ናቸው። ነገር ግን እኒህ አስቸጋሪ ሰዎች ጋር የሚኖረን የትኛውም መስተጋብር ወደ ውጤት የሚያደርስ ላይሆን ቀርቶ ልንለያቸውም እንገደድ ይሆናል።
አንተ ወደ ግራ እኔ ወደ ቀኝ ብለን የተለያየንና በሰላም አቅጣጫ የለየን ከሆነ ተገናኝቶ ክፉ ደጉን የማውራት እድሉም የጠበበ ነው። ነገር ግን አብረን እየኖርን ከሆነ አንዳች መንገድ ያስፈልገናል። ምናልባት አስቸጋሪው ሰው የትዳር አጋራችን ሊሆን ይችላል፣ ወይንም ልጃችን፣ ወይንም አለቃችን ወይንም ጓደኛችን ወይንም ሌላ ሰው። ከእዚህ ሰው ጋር አብረን እየኖርን ነው? ምላሻችን “አዎ”ከሆነ ከአስቸጋሪው ሰው ብዙ አሉታዊ ጎኖች ይልቅ መልካም ጎኖቹን ፈልገን ባገኘነው መልካም ጎን ላይ ቃላችንን እናውጣበት። የምስጋናን ቃል። ይህ ሰው ከስህተቱ እንዲመለስ የምናደርጋቸውን ምክሮች ሆነ ተግሳጾች የማይተካ ራሱን ችሎ የሚገለጥ የምስጋና ቃል። ጠንካራ በሆነበት ነገር ላይ የሚነገር የምሥጋና ቃል።
አስቸጋሪው ሰውን በጠንካራ ጎኑ እንዲበረታ ባደረግነው ቁጥር ደካማ ጎኑን እየቀነሰ የመሄድ እድልን ይፈጥራል። አበባየሁሽ ብለው የሄዱ ልጆች በየቤታቸው ያሉትን አስቸጋሪ ሰዎችን አስበው ይህን ቢተገብሩ በቤታቸው ለውጥን ማየት መቻላቸው እሙን ነው። ሂደቱ አስቸጋሪው ሰውን መርዳት ብቻም ሳይሆን የራስን ደስታ የመፍጠር ሂደትም አካል ነው።
ደስታችሁን ራሳችሁ ፍጠሩ
ልጆቹ ወደ ቤታቸው ይዘውት ከሄዱት መልእክት ውስጥ “ደስታችሁን ራሳችሁ ፍጠሩ” የሚለው መልእክት ደምቆ የተጻፈ ነው። ሰው ብዙ ጊዜ ደስታውን የሚያጣው
የመሻገር ብስራት
በራሱ ሳይሆን በሌሎች ነው። በሌባ የተሰረቀ ሰው በሌባው ምክንያት ደስታውን የተነጠቀ መሆኑን ያነሳል። በህይወቱ ውስጥ መከዳት የገጠመው ሰው እንዲሁ የደስታው መነጠቅ ምክንያት ከዳተኛው ግለሰብ መሆኑን ጠቅሶ ይነሳል። ይህ እይታ እንዴት ስህተት ሊሆን ይችላል? ተብሎ ቢጠየቅ ምላሹ “እንደየትም ሊሆን አይችልም” የሚል ይሆናል።
በተቃራኒው ግን አደገኛው ልማድ መኖሩን መካድ አይቻልም። ሌሎች የደስታችን መደፍረስ ምክንያት ናቸው ብሎ መቀበል ህይወታችን የተረጋጋና ወጥ የሆነ ድባብ ሳይኖረው ሁልጊዜ በውጫዊ ነገር እንቅስቃሴ ላይ የተመሰረተ እንዲሆን ሊያደርገው ይችላል። ውጫዊው ነገር ሁልጊዜ ተቀያያሪ ነው። በተቀያያሪው ነገር ላይ የህይወትን መስመር ለመበየን መነሳት አሳሳች የህይወት አቅጣጫን ያስይዛል። በተቃራኒው ያለው አደገኛው ልማድም ይህ ነው።
ህይወትን በውስጣዊ እንጂ በውጫዊው ሁኔታ እንድትመራ መፍቀድ አይገባም የሚለው አተያይ ደጋግሞ ማሰላሰል የሚገባ ነው። አንባቢው በህይወቴ ተጎዳሁ የሚልባቸውን ክስተቶች ለማሰብ ይሞክር። ምን ያህሉ ከውጫዊ አካል በኩል በመጣ ተጽእኖ የተፈጠረ እንደሆነ ያስባል? ሁሉም የመሆን እድሉ ከፍተኛ ነው። ከጉዳቱ ለመውጣት የተሄደበት ነገር “ውጩውን በመቀየር” ወይንስ “ውስጥን በመቀየር” የሚለውን አስከትሎ እንዲሁ ይጠይቅ።
ደስታችሁን ራሳችሁ ፍጠሩ ትኩረት የሚያደርገው በውስጣዊ ጥንካሬያችሁ ውጭውን ተቆጣጠሩት የሚል ነው። ውጫዊው ነገር በየወቅቱ የሚቀያየር ነው። በመሆኑም የተረጋጋ ህይወትን ከመምራት የሚከለክለው እርሱ ነው። መፍትሄው ውስጥን መገንባት። መፍትሄው በተለዋወጭ ውጫዊ ተጽእኖ ውስጥ እየቀዘፈ ወደ መዳረሻው መሄድን ግቡ ያደረገ ጉዞ ነው።
የመሰጠት ቁርጠኝነት፣ ትእግስት፣ ፍቅር፣ ተስፋ፣ ራእይ፣ ማካፈል፣ ወዘተ በውስጥህ ልትሰራባቸው የሚገቡ የውስጥ ማነጺያ ግብዓቶች ናቸው። በመሰጠት የታነጸ ሰው በዝናብ በቸነፈሩ ውስጥ አልፎ ማሳካት የሚፈልገውን ለማሳካት ስለሚሄድ የውጫዊው አየር መቀያየር ከጉዞው አይመልሰውም። አትሌቶቻችን ለእዚህ ጥሩ ምሳሌ ሊሆኑ ይችላሉ።
ደስታችሁን ራሳችሁ ፍጠሩ ውስጥ አስቸጋሪ ሰዎችን ምስጋና በተገባቸው መልካም ጎናቸው በማመስገን መልካምነትን ማስፈት እንዲገባ አንስተናል። ሌላው ደስታን በራሳችን መፍጠር መልካም ከምንላቸው ሰዎች ጋር አብዝቶ በመዋል የጋራ የምንለውን ነገር ማስፋትንም ይጠይቃል። ህልሙ እግርኳስ ተጫዋች የሆነ ሰውና ለእዚያ እየኖረ ያለሰው ውሎውን ተመሳሳይ ራእይ ከሚጋራው ጋር ቢያደርግ ጥቅሙ ለእርሱ መሆኑ እሙን ነው። በተመሳሳይ ሁኔታ ከፈጣሪያችን ጋር ጊዜን ማሳለፍ። ከፈጣሪ ጋር እና አብረውን ካሉ መልካም ሰዎች ጋር ጊዜን በማሳለፍ ረገድ ውስጣችን ውጫዊውን ተጽእኖ ተቋቁሙ ማደግ የሚችልበትን አቅም ያገኛል። ማድረግ እችላለሁ መንፈስ ደግሞ ተሰርቶ ያለቀው ቤት ቆርቆሮ እንደሆም፤ ሊሰራ የታሰበው ቤት መሰረት ነው። እችላለሁ ብሎ አንድ ማለት።
ደግሞም ትችላላችሁ
አዲስ ዓመት ስለሆነ በዓመቱ ውስጥ ምን ማሳካት እንዳሰብን የመዘርዘር ልማድ ይኖረን ይሆናል። ማሳካት የፈለግነውን ማሳካትን ስናስብ አስቸጋሪ የሚሆኑብንን ነጥቦችም እንዲሁ ልንለያቸው እንሞክራለን። ለለውጥ መነሳትን ስንመርጥ አትችልም የሚለን በአካባቢያችን የሚሰማ ድምጽ እግራችን ላይ የታሰረ ገመድ ሆኖ ልናገኘው እንችላለን።
አትችልም፤ አትችይም የሚለው ድምጽ በበረከተበት ከባቢ ውስጥ እየኖረን በእችላለሁ መንፈስ ለለውጥ የሚነሱት ማግኘት አንችልም። ልጆች ሲያድጉ የሚነገራቸው፤ ታዳጊዎ ብላቴና ከውስጧ የመዘገበችው፤ ወጣቱ ለለውጥ ጊዜውን እንዲጠበቅ የሚጠበቅበት ወዘተ በአልችልም መንፈስ ውስጥ ሆኖ ለመስራት የሚነሳው ሁሉ እየጨነገፈበት ቢቸገር እንዴት ሊገርመን ይችላል።
አለመቻልህን በውስጥህ ከምታመላለስ መቻልህን ለራስህ ንገር። በዙሪያህ ያለው ሳርቅጠሉ ስለመቻል የሚናገረው ድምጽ ጎርናነቱ በዝቶ ጆሮህን እስክትይዝ የሚያደርስ ቢሆንም አሁንም መቻልን አስብ። ቀላል አይደለም ከባድ ነው። የምንኖርበት የድህነት ጥግ ይታወቃል። አልጠራ ያለው የፖለቲካ መንገዳችን የፈጠረው ውጥንቅጡ እንዳለ ነው። የትምህርት ጥራቱ አሽቆልቁሎ ባለዲግሪውና ዲግሪው የሌለው መካከል በእውቀት ላይ ልዩነት የሌለው ሆኖም ይታያል። ሁሉም ነገር አለመቻላችንን እየነገረን ባለንበት ዘመን ውስጥ ስለ መቻል ማንሳት እብደትም ሊመስል ይችላል። የለውጥ መንገዱ ውስጥ ግን የመቻል መንፈስ ግን የሚይዘው ቦታ በቀላሉ የሚታይ አይደለም። የመቻል መንፈስ ለሁላችን እንዲሆንልን በአዲሱ አመት ያስፈልጋል።
ግለሰቡ እንደ ግለሰብነቱ የሚታጠቀው የመቻል መንፈስ፤ ወደ ቤተሰብ ሲጋባ፤ ከቤተሰብ ወደ አካባቢና ማህበረሰብ አድጎ የጋራ ጉዟችን በመቻል ሲገለጽ መዳረሻችን ስኬት በሚለው ቃል ሊገለጽ የሚችል ነው።
ብላቴኖቹ እቤታቸው ይዘውት የሄዱት መልእክት “ደግሞም ትችላላችሁ” በቤታቸው ውስጥ ሊፈጥሩት ለሚያስቡት ተጽእኖው አስተዋጽኦ ምን ያህል ይሆን? በቁጭትና በመነሳሳት ልብ ውስጥ የሆኑትን ምን ያህል ያስደፍራቸውስ ይሆን?
ከዘመን ዘመን የምናደርገው ሽግግር በህይወታችን ውስጥ አዎንታዊ ተጽእኖን መፍጠርን እየጨመረ እንድሄድ በብርቱ ልንሻ ይገባናል። 2014 በቀደሙቱ ዓመታት ውስጥ ያጣነውን ምርኮ የምንመልስበት፣ ለማሳካት ያሰብነውን በእችላለሁ መንፈስ የመንዘረጋበት፣ ምስጋናችን ለተገባቸው የምስጋናን ቃል በማውጣት መልካምነትን የምናበዛበት በድምር ውጤቱ በውስጣችን ውስጥ በሚሆን መታደስና ጥንካሬ ደስታችንን ከውጫዊው ነገር ሳይሆን ከውስጥ በሚሆን ምሪት የምንቆጣጠርበት እንዲሆን ያሻናል። የመሻገር ብስራት ውስጥ ያለው መልእክትም ይህ ነው። ከትናንት ወደ ነገ ልናሸገር መሆኑን፤ ብሩህ የሆኑት ቀናት ኮቴ እየተሰማ መሆኑን ይህንን ብስራት ጨለማ በመሰለ ጊዜ ውስጥ ማሰማት መቻል፤ ከውስጥ ወደ ውጪ።
የመሻገር ብስራት
ብላቴኖቹ በእለቱ እንዲያገኙ ካሰቡት የአበባየሁሽ ገንዘብ በላይ ዓመቱን በአዲስ እይታ አይተው የሚራመዱበትን መንገድ ተመለከቱ። የመሻገር ብስራትን ከደስተኛው ቤተሰብ ተቀብለው ይዘው ሄዱ። የተጻፉት ቃላት በላይ በተግባር ያዩት ቤተሰብ ደስታን ከቤታቸው እንዲሆን መሻትን ጨመረላቸው። ከመሻታቸው አልፎ እውን እንዲሆን የሚፈልጉት ደስታ ግን ከራሳቸው ሃላፊነትም እንደሚነሳ ተረዱ። ሌላውን እንዴት መያዝ እንዳለባቸውና በውስጣዊ አቅማቸው እድገት ውስጥ።
ለአንባቢው ሁሉ ባለበት ስፍራ የመሻገር ብስራቱ እንዲደርሰው እሻለሁ። ያለንበትን እውነታ መካድ መፍትሄ እንደሆነ ስለማላስብ ያለንበትን የትኛውም አይነት ዝቅታን እረዳለሁ። ከዝቅታው የመውጫው መንገድ ግን ከእጃችን መኖሩን ፈጽሞውኑ አንዘነጋ። ወደራሳችን፤ ወደውስጣችን መመልከት በቻልን ቁጥር ወደ መሻገሪያው ድልድይ እንቀርባለን። የሆነውን ሆነን ባለን ነገር ተደስተን ለትልቁ ደግሞ ትጋትን መሻት ባደረግን ቁጥር አሁንም ወደ መሻገሪያው ድልድይ እንጠጋለን። ለሌሎች እውነተኛ ለመሆን ስለምንገባው መሃላ ሳይሆን ቀዳሚው ለራሳችን የምንሆነው እውነተኝነት ነው።
የመሻገር ብስራት ለኢትዮጵያ እንዲሆን የሚሻ ሁሉ እጅ ለእጅ ብቻ ሳይሆን ልብ ለልብም ለመገናኘት ውድ የሆኑ ቀናት ከፊትለፊታችን አሉ። እውቀት ሊቀይረው የሚችለው ነገር የሌሎችንም ሃሳብ ለማድመጥ ጆሯችንን የሚያስከፍተን እስከሆነ ድረስ ነውና የመሻገር ብስራቱ በመደማመጥ ውስጥ የጎላ ትርጉም እንዳለው ይሰመርበት።
በድህነት፤ በጦርነት፤ በመገፋፋት፤ በመናናቅ ያለፍንባቸው ወራት የሰጡንን ለመመልከት ዛሬ በህይወት ያለን ሰዎች በቂዎች ነን። ወደ መሻገሪያው ድልድይ ሁላችንም እንጠጋ። ድልድዩም ወደ ውስጣችንን በመመልከት ውስጥ ጸንቶ ይዘረጋል። ሊሆን የምሻው ይህ እንዲሆን እምነት በማድረግ እነሆ የመሻገር ብስራት ለሁላችን፤ ለኢትዮጵያ! መልካም 2014!
እነሆ 2014!
አዲስ ዘመን መስከረም 1 ቀን 2013 ዓ.ም