ብቁና የሰለጠነ የመከላከያ ሰራዊት ለማፍራት በሚደረግ ጥረት የማሰልጠና ተቋማት አይተኬ ሚናን ይጫወታሉ። በአንድ ጊዜ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ወጣቶችን አሰልጥኖ ለማውጣት በአግባቡ የተደራጁ ማዕከላት አስፈላጊ መሆናቸው አያጠያይቅም። በአፍሪካ ውስጥ በአቅማቸውና ባላቸው የሰልጣኝ ብዛት ከሚጠቀሱ ውትድርና ማሰልጠኛዎች መካከል የኤርትራው ሳዋ እና በሶማሊያና በቱርክ መንግስትት በሞቃዲሹ የተገነባው ቱርክሶም የተሰኘው የውትድርና ማሰልጠኛዎች በግዙፍነታቸው ተጠቃሽ ናቸው። በኢትዮጵያም እንደብላቴ፣ ሁርሶ፣ ብርሸለቆ፣ አዋሽ40 እና ሌሎችም ረጅም እድሜ ያስቆጠሩ የሀገር መከላከያ ሰራዊት ውትድርና ማሰልጠኛዎች በተለያዩ የሀገሪቷ ክፍሎች ይገኛሉ።
እስከዛሬም በማሰልጠኛዎቹም በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ሰልጥነውባቸዋል። አሁንም የእናት ሀገርን የህልውና ጥሪ የተቀበሉና ጨርቄን ማቄን ያላሉ በርካታ ወጣቶች በውትድርና ማሰልጠኛዎቹ ገብተው እየሰለጠኑ ይገኛል። እኛም የብርሸለቆ መሰረታዊ ውትድርና ማሰልጠኛ ትምህርት ቤት ስራዎች፣ የአሰልጣኞች አቅም፣ የሰልጣኞች የስነምግባርና የክህሎት ስልጠና እንዲሁም የህብረተሰቡን ድጋፍ በተለመለከቱ እና ተጨማሪ ጉዳዮችን በተመለከተ ከማሰልጠኛው ዋና አዛዥ ኮሎኔል ጌታቸው አሊ ጋር ቆይታ አድርገናል።
አዲስ ዘመን፡- የብር ሸለቆ መሰረታዊ ውትድርና ማሰልጠኛ የሀገር መከላከያ ሰራዊትን አቅም ለማዳበር በሚደረገው ጥረት ያክል አስተዋጽኦ እያበረከተ ነው?
ኮሎኔል ጌታቸው፡- የብር ሸለቆ መሰረታዊ ውትድርና ማሰልጠኛ ትምህርት ቤት በደርግ ስርዓተ መንግስት ዘመን በ1978 ዓ.ም የተቋቋመ ማሰልጠኛ ነው። ከፍኖተሰላም ከተማ በማንኩሳ ምዕራብ አቅጣጫ በኩል በ 37 ኪሎሜትር አቅጣጫ ላይ ይገኛል።
ማሰልጠኛው ቀደም ብሎ የሀገር ሉአላዊነትን ለማስከበር የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ምልምል ወጣቶችን ለመቀበል ታስቦ የተዘጋጀ ነው። ላለፉት በርካታ ዓመታት ለ33 ዙር መሰረታዊ ወታደሮችን አስመርቋል፤ በቅርቡ ደግሞ 34ኛ ዙር ሰልጣኞችን ያስመረቀ ሀገራዊ ተቋም ነው።
ማሰልጠኛ ትምህርት ቤቱ የሚገኝበት መልከአምድራዊ አቀማመጥም ሆነ የአየር ንብረቱ ለሰራዊት ስልጠና እና ግንባታ አመቺ ቦታ ነው። በውስጡም በተገነቡለት ሰው ሰራሽ የተኩስ፣ የአካል ብቃት ማዘውተሪያ እና በርካታ ማደሪያ ክፍሎች ወጣቶች አስፈላጊውን የውትድርና ሙያ እና ክህሎት ይዘው እንዲወጡ በእጅጉ አግዘዋል።
ማሰልጠኛው በአንድ ጊዜ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ በርካታ ሰልጣኞችን በአንድ ጊዜ ተቀብሎ ማስተናገድ የሚችልና ሰፊ አቅም ያለው ትምህርት ቤት ነው። ከአራቱም የኢትዮጵያ አቅጣጫዎች የሚመጡ ሀገር ወዳድ ወጣቶች በቂ ስልጠና እና ትምህርት አግኝተው መከላከያ ሰራዊትን እንዲቀላቀሉ እየተደረገ ይገኛል።
ማሰልጠኛው ከሚሰጠው ስልጠና አኳያ እንደማንኛውም ኮሌጅ እና ዩኒቨርሲቲ ሊታይ ይችላል፤ ነገር ግን ወደ ጊቢው የሚገቡ ወጣቶች ተምረው ዲግሪ ለመያዝ አሊያም ሰርተፍኬት ለማግኘት ሳይሆን ለእናት ሀገራቸው ህይወታቸውን ለመገበር የሚያስችል ወኔ እና ዓላማ የሚሰንቁበት ቦታ በመሆኑ ለየት ያደርገዋል። ሀገሬ ብለው የሚመጡ የቁርጥ ቀን ልጆች መፍለቂያ ነው።
ብርሸለቆ ማሰልጠኛ በትክክል ይገለጽ ቢባል እስካሁን ብዙ ያልተነገረለት ቦታ ነው። ለመከላከያ የሰው ኃይል ግንባታ ከፍተኛ አገልግሎት ከሚሰጡ የሰራዊቱ ክፍሎች አንዱ ነው። በማሰልጠኛው ውስጥ እልፍ አዕላፍ የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጆች ወታደራዊ ሙያን እንዲቀስሙ ተደርጓል። በቀጣይም በሰፊው እየሰራንበት ለሰራዊት ግንባታ አስፈላጊውን ሚና የምንጫወትበት ማሰልጠኛ ነው።
አዲስ ዘመን፡- ማሰልጠኛው ከቆይታው አኳያ ያሉት የውትድርና አሰልጣኞች አቅም ምን ያክል ነው?
ኮሎኔል ጌታቸው፡– እጅግ ከፍተኛ ቁርጠኝነትን የሚጠይቀውን የውትድርና ሙያ መርጠው የሚመጡ ወጣቶች ብቁ በሆኑና እና ልምድ ባላቸው አሰልጣኞች ታንጸው እንዲወጡ ማድረግ ትልቅ ትኩረት የሚሰጠው ጉዳይ ነው። ማሰልጠኛው በመሰረተ ልማት አኳያ የእራሱ ውስንነት ቢኖረውም እንኳን ያሉት አሰልጣኞች ብቃትና አቅም ደግሞ የሚያስገርም ነው።
እዚህ ማሰልጠኛ የሚገኝ አሰልጣኝ ለረጅም ጊዜ በጊቢው የቆየ እና በርካቶችን ሲያበቃ የቆየ በመሆኑ የካበተ አቅም አለው። ከአንድ ስልጠና ወደሌላኛው ሲሸጋገር እራሱን እያጠናከረ የመጣ በመሆኑ ልምድና ተሞክሮው ትልቅ ለሀገር ሀብት ነው። በተለይ አሁን ጁንታው ቡድን በሀገር ላይ በፈጸመው ክህደት ምክንያት አሰልጣኞች በእልህና በወኔ ነው የሚሰሩት።
ይህንን ጁንታ ቡድን ለማጥፋት የሚያስችል መሰረታዊ ወታደር ለማፍራት እያንዳንዷን ስልጠና በጥንቃቄና በሳይንዊ መንገድ የሚመራ አሰልጣኝ በርካታ ነው። ለሀገር ህልውና ጥሪ በተደረገበት ወቅት በርካቶች ወደማሰልጠኛው በሚቀላቀሉበት ወቅት ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ በጥንቃቄ የሚሰሩ አሰልጣኞችን ማግኘት ከምንም በላይ ውጤታማ ያደርጋል።
እንደጓደኛም እንደአለቃም ሆነው ወጣቶችን ብቁ ለማድረግ የሚታትሩ በርካታ አሰልጣኞች አሉን። ኮማንዶዎች፣ የመስመር መኮንኖች፣ እና በአጠቃላይም የአስተዳደር ሰራተኞችም በአጭር ጊዜ ውስጥ ሰፊ አቅም ያለው ሰራዊት ለመገንባት የሚያስችል ስልጠና በመስጠት ረገድ ሌት ተቀን የመስራትን ልምድ አካብተዋል።
ማንኛውንም ተመልምሎ የመጣ ወጣት ከሰልፍ አያያዝ፣ ተኩስ ልምምድ፣ የከተማ ውጊያ እና የአካል ብቃት ስልጠና አንስቶ እስከ ልዩ ኦፕሬሽን የሚደርሱ ስልጠናዎችን በብቃት የሚሰጡ ባለሙያዎች አሉ። በዚህም በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ወጣቶችን በማሰልጠን ውጤት ማየት ችለናል።
በዚህ ረገድ በብርሸለቆ ማሰልጠኛ የሚገኙ የመከላከያ ሰራዊት አባላትና አመራሮች ጀግኖችን በማፍራቱ ሂደት ልክ እንደሌሎች ማሰልጠኛዎች ሁሉ የሚጠበቅባቸውን ሚና እየተወጡ ነው ብሎ በእርግጠኝነት መናገር ይቻላል።
አዲስ ዘመን፡- ሰልጣኞች በወታደራዊ ሙያ ስነ-ምግባር ረገድ ብቁ እንዲሆኑ ለማስቻል ምን አይነት ጥረት እየተደረገ ይገኛል?
ኮሎኔል ጌታቸው፡– የአዕምሮ ብቃታቸውን የሚያሳድጉ ትምህርቶችና ፈተናዎችን አልፈው እንዲወጡ እና የስነልቦና ዝግጁነታቸው የሚፈለገው ደረጃ እንዲደርስ ማድረግ የማሰልጠኛው ሃላፊነት ነው። አንድ ወታደር ሊኖረው ከሚገባቸው የስነ-ምግባር አይነቶች የሙያና መለዮ ፍቅርና በእርስ በእርስ ግንኙነት የመከባበር እንዲሁም ታማኝነትን እና ሌሎችንም ዋነኞቹ ናቸው።
በዚህ ረገድ የመከላከያ ሰራዊት ምልምል ሰልጣኞች ወቅቱ የሚጠይቀውን ብቃትና የስነልቦና ዝግጅት እንዲኖራቸው በጥንቃቄ እየተሰራ ይገኛል። በወታደራዊ ማሰልጠኛው ቋንቋ የግንባታ ትምህርት ተብሎ የሚሰጥ ጥብቅ ትምህርት የስነምግባር ይዘት ያለው ነው። ሰልጣኞች ስለሀገራቸው ያላቸውን ፍቅር የሚያጎለብቱበት እና የአካባቢያዊ እሴቶችን የሚላበሱበት ትምህርት በብቁ ባለሙያዎች እየተሰጣቸው ነው የሚሰለጥኑት።
የተለያዩ የመከላከያ ሰራዊቱን ደንቦችን እና መመሪያዎችን ከማሳወቅ ባለፈ የመከላከያ ተቋማዊ እሴቶችን እንዲሁም የሰራዊቱን አደረጃጀት በአግባቡ እንዲረዱ የሚያስችል ስልጠና በሰፊው እንሰጣለን። በስራ ላይ ያለውን ህገመንግስት ከማወቅ ጀምሮ በግዳጅ ቀጠና ስለሚኖሩ የስነምግባርና የወታደራዊ ሙያ ግዴታዎች በአግባቡ የሚሰጡ የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርቶች አሉን።
በተግባርም እንደሚታየው በማሰልጠኛው ቆይታ ያደረጉ መሰረታዊ ወታደሮች በስነምግባር ረገድ አመርቂጥሩ ውጤት የሚያሳዩ ናቸው። በሀገር ፍቅር ስሜት እና ወኔ በፍላጎታቸው የሚመጡ ሰልጣኞች በመሆናቸውም በሚፈለገው መንገድ በስነምግባር ለማረቅ አመቺ ሁኔታ ተፈጥሯል። ሰልጣኞች የተሟል ስብእና፣ ስነምግባርና የእናት ሀገር ፍቅርን ይዘው ጀግናውን የመከላከያ ሰራዊት እንዲቀላቀሉ እየተደረገ ይገኛል።
የጁንታው ቡድን ሀገር ለማፍረስ ቢነሳም ውድ የኢትዮጵያ ልጆች ደግሞ እኛ እያለን ሀገር አትፈርስም በሚል በፍቃደኝነት በማሰልጠኛዎች መግባታቸውን ቀጥለዋል። በማሰልጠኛዎች ውስጥም የገቡ ወጣቶች አካላዊም ሆነ አዕምሯዊ አቅማቸው ይበልጥ የዳበረ እንዲሆን የሚያስችል ሳይንሳዊ ስልጠና እየተሰጣቸውይገኛል።
አዲስ ዘመን፡- ሰልጣኞች ወቅቱ የሚጠይቀውን የአካልና ብቃትና የመሳሪያ አጠቃቀም ችሎታ እንዲኖራቸው በብርሸለቆ ማሰልጠኛ እየተከናወነ የሚገኘው ስራ ምን ያክል ውጤታማ ነው?
ኮሎኔል ጌታቸው፡– በግዳጅ ቀጠናዎች ላይ ትጥቅ እና ስንቅ ይዞ ዳገት ቁልቁለቱን በብቃት ለመሻገር ጠንካራ የአካል ብቃትና ወኔ አስፈላጊ ነው። በማሰልጠኛው የተለያዩ የአካል ብቃት ማሰልጠኛ መሳሪያዎችና ፈተናዎች አሉ።
ስርዓት ባለው መልኩ በቡድን ተከፋፍለው የተለያዩ የሰውነት ማጎልመሻዎችን ይከውናሉ። አንድ መሰረታዊወታደር ከአንድ ማማ ላይ በገመድ መውጣትና መውረድ፣ የእጅና የእግር እንዲሁም የመላ ሰውነት ጡንቻዎችን ማዳበር የሚያስችል የአካል ብቃት ስራ በሰዓቱ እንዲያከናውን ይደረጋል።
መሳሪያ ይዞ ፈታኝ ቦታዎችን የማለፍ፣ በፍንዳታዎች መካከል እራስን ጠብቆ መሰናክሎችን ማለፍ እና የመሳሰሉትን ወታደራዊ ስልጠናዎች በብቃት ካላለፈ በመሰረታዊ ወታደርነት መመረቅ አይችልም። ለዚህም ልምድ ባላቸው አሰልጣኞች ጊዜውን የጠበቀ የአካልና የአዕምሮ ስልጠና ቀንም ሆነ ማታ ይሰጣል።
የተስተካከለ ወታደራዊ ቁመና ያለው ሰራዊት ሆነው እንዲወጡ በእሳት ጭምር ይፈተናሉ። ይህም ከባድ ጓዞችን ይዘው በውጊያ ቀጠና ላይ ያለችግር እንዲንቀሳቀሱ ያግዛል። ጠላትን መደምሰስ የሚያስችል ሁለገብ አቅም መፍጠር ላይ አተኩረን ሰፊ ስራ እያከናወንን ነው። በአጭር ጊዜ ተጨባጭ ለውጥ በሰልጣኞች ላይ አይተናል።
የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ለቀናት በመጓዝ እየተዋጋ ድል ማድረግ የሚችል ሰራዊት መሆኑ በዓለም ደረጃ የተመሰከረለት ነው። ይህን አይነት አቅም የሚፈጠረው ደግሞ በስልጠና ማዕከላት ጭምር ነውና በብርሸለቆ ማሰልጠኛ የሚገቡ ምልምል ወታደሮች ጽናትን እና ጥንካሬንም መሰረት ያደረገ ስልጠና እንዲያገኙ ይደረጋል።
በ34 ኛ ዙር የተመረቁ መሰረታዊ ወታደሮችን ማየት ቢቻል እንኳን በአጭር ጊዜ ውስጥ ወታደራዊ ቁመናቸው እንዲስተካከል የተደረገበትን ሂደት መመልከት ቢቻል ጠንካራ አሰልጣኝ እና ጥብቅ ቁጥጥር ምን ያክል ለውጤታማነት ቁልፍ ሚና እንዳለው መገንዘብ ይቻላል። በዚያው ልክ በመሳሪያ አጠቃቀምና ብቃት ረገድ ሁሉም ተፈትኖ ነው የሚወጣው።
እንደየሁኔታቸው የግልና የቡድን መሳሪያዎችን አጠቃቀም በተመለከተ የእራሱ የሆነ የጊዜ ገደብ ተወስኖለት በቂ ስልጠና ይሰጣል። ሰልጣኞች በሽምቅ ውጊያ፣ የግብግብ እና ሌሎች ግዳጆች ላይ የሚሰጠውን ተልዕኮ በድል ለመወጣት የሚያስችል አካላዊና አዕምሯዊ ስልጠና በበቂ ሁኔታ እንዲያገኙ ተደርጓል። በቀጣይም ወደማሰልጠኛው የሚገቡ ወጣቶች ጊዜው የሚጠይቀው ክህሎትና አቅም እንዲኖራቸው ለማስቻል የማያቋርጥ ጥረት ይደረጋል።
አዲስ ዘመን፡- በስልጠና ሂደት እንደሀገር ያለውን ውስን አቅም ከመጠቀም አንጻር የሚያጋጥሙ ፈተናዎችን ለመሻገር ምን አይነት ጥረት እያደረጋችሁ ነው?
ኮሎኔል ጌታቸው፡– ማንኛውም ስልጠናም ላይ ሆነ ውጊያ ላይ ማንኛውንም ወታደራዊ ግዳጅ ያለመሳሪያዎች እና የተለያዩ አቅርቦቶች ያስፈልጉታል። ነገር ግን እንደማሰልጠኛ በጥቂት አቅርቦትና በጥቂት ግብአት /Resource/ መስራት እንችላለን የሚል አቋም ነው ያለን።
እኛ አሁን ባደረግነውም ስልጠና ሆነ ወደፊት በምናደርገው ስልጠና የሆነ ቦታ ላይ ጉድለት አለ ብለን ወደኋላ አንልም። መንግስት ያለውን አቅም እዚህ ያሉ አሰልጣኞችም በአግባቡ ይረዳሉ። በግራም በቀኝም ያሉትን ኢኮኖሚያዊ ሁኔታዎችን አገናዝበው የእራሳቸውንም መፍትሄ አክለው ብቁ ስልጠና የሚሰጡ በርካታ ባለሙያዎች ስላሉን በዚህ ረገድ የከፋ ችግር አልገጠመንም።
ችግሮች ቢኖሩ እንኳን እንደየሁኔታቸው ጊዜያዊም ሆነ ዘላቂ መፍትሄ በማበጀት በጋራ እየሰራን ይገኛል። የስፖርት እቃዎችንም ሆነ አንዳንድ የማሰልጠኛ ቁሳቁሶችን ከጊቢው በማሰባሰብ የተሻለ ስልጠና እንዲሰጥ ጥረት የሚደረግበት ወቅት አለ። ከዚህ ባለፈ በክረምትም ሆነ በበጋ ወራት የመሰረተ ልማት ችግሮችን ተቋቁሞ ለመስራት የሚደረገው ጥረት አበረታች ነው።
የብርሸለቆ ማሰልጠኛ ጊቢ በስፋት ረገድ ትልቅ ነው፤ የአመሰራረት ሁኔታው ሲታይ ረጅም እድሜ ያስቆጠረ ቢሆንም እንደዕድሜው ያክል ደግሞ በበቂ ሁኔታ የመሰረተ ልማቱ አልተሟላለትም። የመብራት፣ የቴሌኮሙዩኒኬሽን እና የውሃ አቅርቦት ችግሮች አሉበት። ይሁንና ችግሩን እንደሳንካ መመልከት ሳይሆን አሁን ባለን አቅም ብቁ ሰራዊት መገንባት የምንችለው ምን አይነት ስራዎች ስናከናውን ነው የሚል እቅድ በማውጣት ሰርተናል።
በዚህም መሰረት በ10ሺዎች የሚቆጠሩ ሰልጣኞች ሲመጡ እንኳን በአግባቡ አሰልጥነን አስመርቀናል። በጊቢው ያለው ሰራተኛ በአጠቃላይ የተሻለች ኢትዮጵያን የማየት እና ተቋሙንም የማጠናከር ፍላጎት ስላለው የመሰረተ ልማት ችግሮችን ተቋቁሞ እየሰራ ይገኛል። በአጠቃላይ በስልጠና ሂደት እንደሀገር ያለውን ውስን አቅም ከመጠቀም አንጻር ፈተናዎችን ሳያደናቅፉን በትብብር መንፈስ እየሰራን ይገኛል።
ይህ ማሰልጠኛ በቀጣይም በውስን የፋይናንስ እና የሎጂስቲክስ አቅርቦትም ቢሆን የኢትዮጵያን የቁርጥ ቀን ልጆች የሆኑ የመከላከያ ሰልጣኞችን ተቀብሎ ማስተናገድ የሚችል አቅም ያለው ተቋም ነው። በዚህ ረገድ ከስራችን የሚያስተጓጉሉን ፈተናዎች ቢያጋጥሙ እንኳን ሁኔታዎችን በብቃት አልፈን መስራት እንችላለን የሚል አቋም አለን።
አዲስ ዘመን፡- የአሸባሪውን ህወሓት ቡድን ለመደምሰስ በሚደረገው ጥረት አዳዲሶቹ የማሰልጠኛ ወታደራዊ ምሩቃን ከነባሩ ሰራዊት ጋር በመቀናጀት በሚኖራቸው ስምሪት ምን አይነት ግዳጅ ይፈጽማሉ ተብሎ ይጠበቃል?
ኮሎኔል ጌታቸው፡– ለሀገር ህልውና ዘብ እንቆማለን ብለው በፍላጎታቸው ወደማሰልጠኛ የገቡ ወጣቶች በቂ ስልጠና አግኝተው ወደግዳጅ ቀጠና መሰማራታቸው አይቀሬ ነው። ሰልጣኞቹ የመከላከያ ኃይላችንን በማጠናከር ረገድ ትልቅ ሚና አላቸው። በስልጠና የወሰዱትን ክህሎትና እውቀት የጁንታውን ቡድን ለማስወገድ በሚደረገው ጥረት ቁልፍ ሚና ይጫወታሉ።
መሰረታዊ ወታደሮቹ ከሌሎች ነባር አባላት ጋር በመቀናጀት ለሀገር ብቻ ሳይሆን ለምስራቅ አፍሪካም ሰላም የሚበጅ አኩሪ ተግባር እንደሚፈጽሙ ጥርጥር የለውም። ምክንያቱም በስልጠናቸው ወቅት የተሻለ አፈጻጸም ካሳዩ በግዳጅ ቦታ ደግሞ የማይደግሙበት ምክንያት አይኖርም።
በሚሰማሩባቸው ግዳጅ ቦታዎች ላይ የሚያገኟቸው አመራሮችና የተለያዩ የሰራዊቱ አባላት ደግሞ ልምዳቸውን በማካፈል እና አቅማቸውን ይበልጥ በማጎልበት ለተሻለ አፈጻጸም እንደሚያበቋቸው ይታወቃል። ስለዚህ ከየአካባቢው ተሰብስቦ የሚመጣውን የጁንታ ቡድን ብቻ አይደለም ሌላም በአግባቡ የሰለጠነ አካል ቢመጣ መመከት የሚያስችል አቅም እንዲያደራጁ በመደረጉ በርካታ ጀግኖችን ማየታችን አይቀሬ ነው።
መሰረታዊ ወታደሮቹ ለሀገራቸው ያላቸውን ፍቅር እና ጁንታውን ለማስወገድ ያላቸውን ቁርጠኝነት መመልከት ሲቻል ደግሞ ታሪክ እየሰሩ መከላከያን ይበልጥ እንደሚያጠናክሩ ከወዲሁ መናገር ይቻላል። ቀደም ብለው የተመረቁ እና ወደግዳጅ ያመሩ ወታደሮችም በየተመደቡበት ግንባር አኩሪ ተግባር እየፈጸሙ ይገኛል።
ከታላላቆቻቸው ልምድ በመቅሰም እና በግንባር የሚያጋጥማቸውን ፈተና በማለፍ ለሀገር ህልውና ትልቅ ታሪክ እየጻፉ ያሉ በርካታ መሰረታዊ ወታደሮች አሉ። ስለዚህ የአሸባሪውን ህወሓት ቡድን ለመደምሰስ በሚደረገው ጥረት አዳዲሶቹ የማሰልጠኛ ወታደራዊ ምሩቃን ከነባሩ ሰራዊት ጋር በመቀናጀት በሚኖራቸው ስምሪት የሚፈለገውን ዓላማ ለማሳካት ይችላሉ።
ሀገር በልጆቿ ደም እና አጥንት ነው እዚህ የደረሰችው፤ የአሁኖቹ ጀግኖችም እናት ሀገራቸውን በጀግንነት አስከብረው ለቀጣዩ ትውልድ እንደሚያስተላልፉ ጥርጥር አይኖረኝም። በዚህ አኩሪ ተግባራቸው የትግራይን ህዝብም ከጁንታው ቡድን ነጻ አውጥተው መላው ኢትዮጵያዊ በሰላም እንዲኖር የማድረግ ወታደራዊ አቅም አላቸው።
አዲስ ዘመን፡- በአሸባሪነት የተፈረጀውን የህወሓት ቡድን በአፋርና በአማራ ክልል በንጹሃን ላይ የፈጸመው ጭፍጨፋ በተመለከተ ምን ይላሉ?
ኮሎኔል ጌታቸው፡– የአሸባሪው የጁንታ ቡድን በአፋር፣ በአማራ እና በተለያዩ ቦታዎች እያደረሰ ያለው ጭፍጨፋ ከጁንታው መሰረታዊ ባህሪው የሚመነጭ ነው። ህዝባዊ መሰረት ስለሌላቸው ለህዝብ ደንታ የላቸውም። ዓላማውና ፍላጎቱ ሲኦል ብቻ ስለሆነ በህዝብ ላይ ግፍ መፈጸምን እንደዋነኛ ተግባሩ ተያይዞታል።
የጥፋት ቡድኑ በመሰረታዊነት የንጹሃንን ደም ማፍሰስ ተግባሩ ያደረገው በበረሃ ከነበረበት ጊዜ ጀምሮ መሆኑ መታወቅ አለበት። ለገንዘብ እና ለጥቅም እንጂ ለንጹሃን ደም የማይጨነቅ ቡድን ደግሞ መወገድ አለበት።
ሀገር ለማፍረስ የተነሳው የጁንታ ቡድን የአርሶአደሮችን ቤት እያፈረሰ ከብቶቻቸውን እየገደለ ትክክለኛ ባህሪዩን አሳይቷል። ይህ የጥፋት ቡድን ለአንዲት ሰኮንድ እንኳን ስለሰብአዊነት ማሰብ የማይችል ከሃዲ ቡድን ነው። በጦር ግንባር የሚደርስበትን ሽንፈት ላለመቀበል በየደረሰበት ንጹሃን ላይ እጁን እያሳረፈ ይገኛል።
በሰሜን ጎንደር፣ በሰሜን ወሎ በአፋርና በተለያዩ አካባቢዎች አይቀጡ ቅጣት እየደረሰበት ይገኛል። ይህን የተባበረ የኢትዮጵያውያንን ክንድ መቋቋም ባለመቻሉ ቀድሞ በወረራ በያዛቸው አካባቢዎች ላይ ህጻናትን ሳይቀር እየገደለ እግሬ አውጪኝ ብሏል ግማሹም ተደምስሷል።
ይህን የጥፋት ቡድን አሁን ላይ ሁሉም እየታገለው ነው። ጀግናው መከላከያ ሰራዊትም ከሌሎች የጸጥታ ኃይሎች ጋር በመሆን የከሃዲውን ቡድን በሚገባው ቋንቋ እየቀጡት ይገኛል። ለዚህም ዓላማ ከአራቱም አቅጣጫ የተሰባሰቡ የኢትዮጵያ ቁርጥ ቀን ልጆች እኛ እያለን ሀገር አትፈርስም ብለው ተነስተዋል።
የጁንታው ጥፋትና ንጹሃን ላይ የሚያደርሰው በደል የሚቆመው ቡድን ሙሉ ለሙሉ ሲደመሰስ ነው። አሁን ላይ ያለው እውነታም እንደሚያሳየው ሰላም ጠል የሆነውን ጁንታ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለመንቀል የሚያስችል ኦፕሬሽን በተሳካ ሁኔታ እየተከናወነ ይገኛል።
ጁንታው ሲወገድ ሀገር በተሻለ ሁኔታ ህልውናዋ ተከብሮ ንጹሃን ዜጎች በሰላም የሚኖሩበት እድል ይበልጥ ይመቻቻል። ለዚህ ዓላማ እንደእስከዚህ ቀደሙ ሁሉ በአንድነት መንፈስ መንቀሳቀስ ይገባል።
አዲስ ዘመን፡- አሸባሪውን ህወሓት በማጥፋት በሚደረገው ጥረት ህብረተሰቡ እያደረገ ያለው ድጋፍ በተመለከተ ምን ይላሉ?
ኮሎኔል ጌታቸው፡– የአጥፊው ጁንታ ቡድን ዓላማዬ ሀገር መበተን ነው ብሎ ከተናገረ በኋላ ኢትዮጵያውያን በሙሉ በአንድነት ስሜት ተነስተዋል። ይህን ከሃዲ ቡድን ለማንበርከክ ደግሞ በግንባር ከመገኘት ባለፈ የተለያዩ የአይነትና የገንዘብ ድጋፎችን ብቻ ሳይህን የሞራል ድጋፍም የሚያቀርበው ህዝብ ቁጥሩ ከፍተኛ ነው።
የተለያዩ ሀገራት ኢትዮጵያ ላይ ጫና ሲያደርጉ በየሙያ ዘርፋቸው ይህን ጫና ለመቋቋም የሚታትሩ ኢትዮጵያውያን በሚሊዮኖች ይቆጠራሉ። ከነዚህ ሁሉ ድጋፎች በበለጠ ደግሞ ህብረተሰቡ ለመከላከያ ሰራዊት እያደረገ ያለው አጋርነት ታሪክ በደማቁ የሚጽፈው ነው።
ባገኘው አጋጣሚ ሁሉ ለሰራዊቱ ያለውን ክብርና ፍቅር የሚሰጥ ህዝብ ነው ያለው። አንድ በሬ ያለው ሰው ለእራሱ ሳይሳሳ ያለውን ለመከላከያ ሰራዊት ያቀርባል። ልክ በህዳሴው ግድብ ላይ የሚደረገውን ርብርብ አይነት ሁሉም ሀገሩን ወዳድ ኢትዮጵያዊ ለሰራዊቱ ድጋፍ በማቅረብ ላይ መሆኑ የሚያስመሰግን ነው።
በገንዘብ እና በአይነት ባለሀብቱም ሆነ ሰራተኛው የሚያደርገው ድጋፍ እንዳለ ሆኖ ለህይወቱም ሳይሳሳ ወደ ውትድርና ማሰልጠኛ የሚተመው ወጣት ትልቅ አስተዋጽኦ እያደረገ ነው። እናትና አባት ልጆቻቸውን መርቀው ለውትድርና ስልጠና ሲልኩ ማየት ያስደስታል። ይህ የህዝብ ድጋፍ ደግሞ ዓላማው ኢትዮጵያ የተረጋጋ ሰላም እንዲኖራት ለማስቻል ነው። ዓላማው የጁንታው ቡድን ተወግዶ የሀገር ህልውና የበለጠ ማረጋገጥ ነው።
በሌላ በኩል በእርሻ ስራ ላይ የተሰማራ ሚኒሻ እርሻውን ትቶ ነው ወደ ግንባር እየሄደ ያለው። ይህ ህዝብ ለሀገሩ ምን ያክል ፍቅር እንዳለው በግልጽ የሚያሳይ ነው። በየአካባቢው ያለው ኗሪም የዘማቾችን ሰብል በማረምና በመንከባከብ አንድነቱን ያሳየበት ጊዜ ሆኗል።
በእኛ ማሰልጠኛ አካባቢ ያለውም ህብረተሰብ በየጊዜው ምንድን ነው የቸገራችሁ፤ ምን እናግዝ፤ እያለ ድጋፍ ለማቅረብ ቦዝኖ አያውቅም። በጊቢው ቴክኒካዊ ስራዎች ላይ በቀጥታ ገብቶ አይሳተፍ እንጂ ህብረተሰቡም የስራዎቻችን ዋነኛ አጋር ነው። ህብረተሰቡ በችግሮቻችንን ብቻ ሳይሆን በደስታችንም ወቅት አብሮን ነው ያለው።
በአጠቃላይ እያንዳንዱ ሀገር ወዳድ ዜጋ በየተሰለፈበት ሙያ መስክ ለሀገሩ የሚያበረክተው ድጋፍና አስተዋጽኦ መጪው ጊዜ የተሻለ እንደሚሆን አመላካች ነው። ሀገርን የመጠበቅና መከላከያን የመደገፍ ተግባር የአንድ ወቅት ብቻ ሳይሆን ዘላቂ ተግባር የሚጠይቅ ነው። ይህ የህዝብ ትብብርና ድጋፍ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት የሚል መልዕክት ማስተላለፍ እፈልጋለሁ።
አዲስ ዘመን፡- የኪነጥበብ ባለሙያዎች በየወታደራዊ ማሰልጠኛዎች እና በግንባር ለሚገኘው ሰራዊት ስራዎቻቸውን ማቅረባቸው ምን አይነት አስተዋጽኦ አድርጓል?
ኮሎኔል ጌታቸው፡- የኪነጥበብ ስራዎች ባንዳዎችን በማሳፈር እና የወገን ጦር አትንኩኝ ባይነት እንዲሁም ወኔ ከፍ በማድረግ የሚኖረው ሚና ከፍተኛ ነው። በአድዋ ድል እና በኢትዮ ኢጣልያ ወረራም ሆነ በሌሎች አውደውጊያዎች ላይ የኪነጥበብ ባለሙያዎች ስሜት ቀስቃሽ ፉከራዎችንና ቀረርቶዎችን በማቅረብ በርካቶች ለሀገራቸው ህልውና እንዲቆሙ ቀስቅሰዋል፤ አዋግተዋል።
በየዘመኑ ያለውን ታሪክ መቃኘት ቢቻል የኪነጥበብ ስራዎች በሀገር ግንባታ እና የህልውና ዘመቻዎች ላይ የአንድነት ስሜት በመፍጠር የማይተካ ሚና መጫወታቸውን መገንዘብ ይቻላል። ኪነጥበብ ለአሸናፊነት ክብር በማብቃት የስነልቦና ስንቅ የሚሆን አኩሪ ዘርፍ ነው። አሁንም የጁንታው ቡድን ሀገርን በመክዳት እበትናለሁ ብሎ ሲነሳ በርካታ የኪነጥበብ ባለሙያዎች በስራዎቻቸው አይሳካልህም ብለውታል።
ግንባር ድረስ በመዝመት እና በየማሰልጠኛው በመቅረብ የሞራል ድጋፍና ስሜት ቀስቃሽ ሙዚቃዎቻቸውን የሚያቀርቡ የኪነጥበብ ባለሙያዎችም ተገኝተዋል። ይህ የኪነጥበብ ባለሙያዎች የመድረክ ዝግጅት ሰራዊቱ ይበልጥ እንዲበረታታ እና እንዲነቃቃ በማድረግ ለተጨማሪ ድል ያነሳሳ ሆኗል። በተቃራኒው ደግሞ የጁንታውን ቡድን ሞራል በመደምሰስ እና ከሃዲዎችን በማዋረድ ረገድ የተጫወተው ሚና ቀላል የሚባል አይደለም።
ሀገር አፈርሳለሁ ብሎ ምሎና ተገዝቶ የተነሳውን የአሸባሪ ቡድንና አጋሮቹን ለመደምሰስ በሚደረገው ጥረት የኪነጥበብ ባለሙያዎች የሚያቀርቡት የመድረክ ስራ የወገንን ስነልቦና በማሳደግ ረገድ በገንዘብ የማይተመን አስተዋጽኦ እያበረከተ ነው። ሰልጣኝ ወታደሮችም በኪነጥበብ ስራዎች እየተዝናኑ ሀገራዊ ስሜታቸውን እንዲያሳድጉ ኪነጥበቡ ጉልህ ሚና ተጫውቷል።
በማሰልጠኛዎች ውስጥ ሲዜሙ የነበሩ ዜማዎች በአብዛኛው የእነጥላሁን ገሰሰ፣ የእነመሃሙድ አህመድ እና የሌሎችም አንጋፋ ድምጻውያን ስራዎች ስለኢትዮጵያ የሚያቀነቅኑ፤ ተከብረሽ የኖርሽው በአባቶቻችን ደም እያሉ ጀግንነትን የሚያላብሱ ናቸው። እንዲህ አይነት ዜማዎች በብርሸለቆ ማሰልጠኛም ሲቀርቡ ነበር። በኪነጥበብ ስራዎቹም በርካታ የቁርጥ ቀን ልጆች የሚወዱትን የኢትዮጵያን ሰንደቅ በፍቅር ይዘው ሲወዛወዙ ተስተውሏል።
እንደዚህ አይነት ስሜት ቀስቃሽ የኪነጥበብ ስራዎችን ያቀረቡ የኪነት ባለሙያዎች ምስጋና ይገባቸዋል። ለሀገር ህልውና የቀረበውን ጥሩ በሙያቸው በማገዛቸው ሀገር ወዳድ መሆናቸውን በተግባር አሳይተዋል። ተመሳሳይ ዝግጅቶችም እንደሚቀጥሉ ተስፋ አለኝ። እኛም በርቱ ያማረ የኪነጥበብ ዝግጅቶቻችሁ ለስራችን አግዘውናል ማለት እፈልጋለሁ።
አዲስ ዘመን፡- ለነበረን ቆይታ ከልብ አመሰግናለሁ።
ኮሎኔል ጌታቸው፡- እኔም ማሰልጠኛ ድረስ ተገኝታችሁ ስለጠየቃችሁኝ አመሰግናለሁ።
ጌትነት ተስፋማርያም
አዲስ ዘመን መስከረም 3/2014