መስከረም ነጋ፤ 2014 ዓ.ምም ሆነ፡፡ ኢትዮጵያ አዲሱን ዓመቷን ተቀብላለች፡፡ 2014 ዓ.ም ምን ይዞባ(ላ)ት እንደሚመጣ አገሪቱና ዜጎቿ እርግጠኞች አይደሉም። ከአንድም ሁለት ጊዜ አዲስ ዓመት ሲመጣ መልካሙን ተመኝተውና አልመው ነበር፤በተግባር የታየው ግን ይሆናል ብለው ያላሰቡትና ያልጠበቁት ነበር፡፡ ያለፉት ጥቂት ዓመታት ኢትዮጵያ በረጅም ዕድሜዋ ካየቻቸው አስከፊ ጊዜያት መካከል የሚመደቡ ናቸው።
የሰላም እጦት፣ የዜጎች አሰቃቂ ሞትና መፈናቀል፣ የኑሮ ውድነት … ተደጋግመው ታይተዋል፡፡ በእርግጥ ‹‹አገሪቱ በእነዚህ ሁሉ መከራዎች ውስጥ ሆና ስኬቶችንም አስመዝግባለች›› የሚለውን የሌላኛውን ወገን ዕይታንም አልዘነጋሁትም። ነገር ግን ሌላው ሁሉ ይቅርና በማንነት ምክንያት ከመገደልና ከመፈናቀል ስጋት ነፃ ሆኖ በሰላም ወጥቶ መግባትን ያላሰፈነ ስኬት እንደስኬት የመጠቀሱ ምክንያታዊነት ማስተዛዘቡ አይቀርም፡፡ እንግዲህ እንዲህ እንዲህ እያልን 2014 ዓ.ም ላይ ደርሰናል፡፡ በዚሁ ሁሉ ችግር ውስጥ ሆነን ለአዲሱ ዓመት መብቃታችን ‹‹ዕድለኛ›› ሳያደርገን አይቀርም፡፡
ኢትዮጵያ ታላቅ አገር ለመሆን የሚያግዟት እምቅ የተፈጥሮ ሀብት፣ ግዙፍ የሠው ኃይል፣ የተከማቸ የታሪክ እርሾ እንዲሁም ሌሎች ጠቃሚ ግብዓቶች ያሏት አገር ናት፡፡ እነዚህን ግብዓቶች አቀናጅታ ታላቅና ኃያል አገር የመሆን ዕድል ቢኖራትም ይህን ዕድል በተግባር የመተርጎሙ ነገር ግን በተጨባጭ ሊሰምር አልቻለም፡፡ ከሺ ዓመታት በፊት በበሬ የሚያርሰው የኢትዮጵያ ገበሬ ዛሬም ከዚሁ የአስተራረስ ዘዴ መላቀቅና ከእጅ ወደ አፍ የሆነ ኑሮ ከመምራት መሻገር አልቻለም፡፡
ረሀብ ደጋግሞ ጎብኝቶን ‹‹ኢትዮጵያ›› የሚለው ስም የረሀብና የችጋር ምሳሌ ተደርጎ ቆይቷል፡፡ ጦርነት የአገሪቱ ዋነኛ መገለጫ እስኪመስል ድረስ ለቁጥር የሚታክቱ ደም አፋሳሽ ጦርነቶች በኢትዮጵያ ምድር ተካሂደዋል፡፡ የፖለቲካ ርዕዮተ ዓለሞች ከውጭ አገራት እየተቀዱ መጥተው ሕዝብ ያለምንም ማሰላሰል እንዲሸከማቸው ተደርጎ ብዙ ዋጋ አስከፍሏል፡፡ የውሸት ትርክቶች ‹‹ለምን፣ እንዴት …?›› የሚል ጠያቂ አጥተው የአንድ አገር ልጆች ጎራ ለይተው እንዲጫረሱ አድርገዋል፤በጠላትነት መፈራረጅን አስከትለዋል፤የአገሪቱ ቅርጽ (ካርታ) እንዲቀየርም አድርገዋል፡፡ እነዚህ ችግሮች ከመቃለል ይልቅ ይበልጥ እየተወሳሰቡ መጥተው ዛሬም ኢትዮጵያንና ሕዝቧን መራራ ዋጋ እያስከፈሉ ቀጥለዋል፡፡
ቀደም ባሉት ዘመናት ኢትዮጵያ በውጭ ጠላቶች ላይ ድሎችን በመቀዳጀት ረገድ ዓለም የሚደነቅባቸው አንፀባራቂ ታሪኮችን አስመዝግባለች፡፡ ጉራዕ፣ ጉንደት፣ ሰሃጢ፣ ዶጋሊ፣ ዓድዋ እና ካራማራ የእነዚህ ታሪኮች ጥቂት ማሳያዎች ናቸው፡፡ እነዚህ ድሎች ኢትዮጵያውያን ለጋራ ዓላማ በጋራ ተሰልፈው ዓለምን ያስደነቀ ገድል መፈፀማቸውን ለመላው ዓለም ያሳዩባቸው አኩሪ ገድሎች ናቸው፡፡ ይሁን እንጂ እነዚህ ድሎች ያስገኙት በረከትና የፈጠሩት ዕድል በሚገባ ተመንዝሮ ጥቅም ላይ አልዋለም።
የእነዚህን ድሎች ትርጉሞችና በረከቶችን እያሰብን የኢትዮጵያን ያለፉትን ዓመታት (በተለይ 50 ዓመታት) ጉዞ ስንቃኝ ‹‹ለመሆኑ ኢትዮጵያ/ኢትዮጵያውያንና የጉንደት/ጉራዕ/ዓድዋ/ካራማራ ድሎች ይተዋወቃሉ?›› ብለን ለመጠየቅ እንገደዳለን፡፡ አገሪቱ በረሃብ፣ በግጭት፣ በዘረኝነትና በጦርነት ጎዳናዎች ላይ ደጋግማ መመላለሷና ከድህነት ጋር ተቆራኝታ መዝለቋ እነዚህ ታላላቅ ድሎች ያስገኙላትን በረከቶች መዘንጋቷንና አለመጠቀሟን ቁልጭ አድርጎ ያሳያል፡፡
እስኪ ጉዳዩን ግልጽ ለማድረግ የዓድዋን ድል እንደማሳያ በመውሰድ ላብራራው፡፡ ብዙ ሰዎች ‹‹ … የካቲት 23 ቀን 1888 ዓ.ም ጥቁሩ የኢትዮጵያ ሠራዊት ነጩን የኢጣሊያ ሠራዊት ድል አድርጎ ኢትዮጵያን በቅኝ ግዛት ከመገዛት ነፃ አወጣት … ኢትዮጵያ በቅኝ ግዛት ያልተገዛች ብቸኛ አገር ሆነች … አባቶቻችን በከፈሉት ታላቅ መስዋዕትነት ተከብረን ኖርን …›› በማለት የዓድዋ ድል አልፋና ኦሜጋ ትርጉም አገርን ከወራሪ ኃይል መጠበቅ ብቻ እንደሆነ አድርገው ይናገራሉ/ይፅፋሉ፡፡ እውነታው ግን ያ ብቻ አይደለም፡፡
የዓድዋ ድል ኢትዮጵያን ከወራሪ ኃይል ጠብቆ የማቆየት አኩሪ ታሪክ እንደሆነ አይካድም፡፡ የዓድዋ ድል በማኅበራዊ፣ በኢኮኖሚያዊና በፖለቲካዊ መስኮች ጠንካራና ኃያል የሆነች አገር ለመገንባት የሚያስችል እምቅ አቅም ያለው ድል ነበር፡፡ ኢትዮጵያን ከወራሪ ኃይል ጠብቆ ማቆየትና በቅኝ ግዛት አለመገዛት ግን የድሉ አልፋና ኦሜጋ (መነሻም መድረሻም) አይደሉም፤ሊሆኑም አይገባም፡፡
ቀደምት ኢትዮጵያውያን ከወራሪው የኢጣሊያ ጦር ጋር የተፋለሙት ኢትዮጵያን ከወቅቱ ወራሪ ኃይል ለመጠበቅ (ዳር ድንበሯን ለማስከበር) ብቻ ሳይሆን ወራሪው ኃይል ውሎ አድሮ በኢትዮጵያና በኢትዮጵያውያን ላይ የሚያደርሰውን ጥፋት በመገንዘብ ያን ጥፋት በእንጭጩ ለመቅጨትም ጭምር ነው፡፡
ስለዚህ የዓድዋ ድል የመጀመሪያው ውጤት (አበርክቶ) ኢትዮጵያን ከወራሪ ኃይል ጠብቆ ማቆየት ሲሆን፤ ዘላቂው ውጤት ደግሞ ድሉ ያስገኘውን መልካም ፍሬ መንዝሮ ማኅበረሰባዊ ንቃት ያዳበረች፣ በኢኮኖሚ የበለጸገች፣ ልዩነቶችን አስማምታ አንድነቷን የጠበቀች ኃያል የሆነች ኢትዮጵያን መፍጠርና መገንባት ነበር፡፡ ይህን ዘላቂ ውጤት ማሳካት የነበረባቸው ደግሞ ድሉንካስገኘው ትውልድ ቀጥሎ የመጡት ትውልዶች ነበሩ፡፡ በሚያሳዝንና በሚያሳፍር ሁኔታ እነዚህ ትውልዶች ግን ያን ማድረግ አልቻሉም/አልቻልንም፡፡
የዓድዋን ድል ትርጉም በቀላል ምሳሌ በማስደገፍ እንመልከት፡፡ ዚብባብዌና ደቡብ አፍሪካ፣ በተለይ ከመሬትና ሌሎች ሀብቶች ባለቤትነት ጋር በተያያዘ፣ የቅኝ ግዛት ካመጣባቸው ጣጣ ዛሬም ድረስ ሊላቀቁ አልቻሉም፡፡ የዚምባብዌው ሮበርት ሙጋቤ መሬትን ከቅኝ ገዢዎቹ ነጮች ነጥቀው ለጥቁሮች መስጠታቸው አገሪቱ ዛሬም ድረስ ልትወጣው ያልቻለችው ከባድ አዘቅት ውስጥ ከቷታል፡፡ ደቡብ አፍሪካ ጊዜ እየጠበቀ በሚነሳ የመጤ ጠል (Xenophobia) እሳቤ እየተፈተነች ነው፡፡
የኢትዮጵያው ሌተናል ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማርያም ግን የመሬት አዋጅን ለማወጅ ሲነሱ የገጠማቸው ያደረ የቅኝ ግዛት ጥያቄ/ጫና አልነበረም (ጥቂት ከታሪክ ጋር ሆድና ጀርባ የሆኑ ጥራዝ ነጠቆች ኢትዮጵያውያን ባላባቶችንና የመሬት ከበርቴዎችን እንደቅኝ ገዢ መቁጠራቸው ከተረትነትና ከቀልድ ያለፈ ትጉም ስለሌለው)፡፡ ይህም አዋጁን ለማወጅና ለመተግበር ምቹ ሁኔታ ፈጥሮላቸዋል፡፡ ዓድዋ ማለት እንዲህ ነው/ነበር!
ቀደምት ኢትዮጵያውያን ለኢትዮጵያና ለኢትዮጵያውያን ነፃነት፣ ክብርና አንድነት ሲሉ በዓድዋና በሌሎች ስፍራዎች ለማመን የሚከብዱ ከባድ ተጋድሎዎችን አድርገው ነፃ አገር ለ‹‹ተተኪው ትውልድ›› ቢያስረክቡም ‹‹ተተኪው ትውልድ›› (በተለይ ልኂቃኑ) ግን ያን ታሪክ ማወቅ አልፈለገም፤ይባስ ብሎ በብሔርና በሃይማኖት ተከፋፍሎ አገር ለማፍረስ ታጥቆ ሲሠራ ኖረ፤አሁንም እየሠራ ነው … የሰማዕታቱ መስዋትነት ባከነ፤ተረሳ፤ውለታቸውም ቅርጥፍ ተደርጎ ተበላ። የጉንደት፣ የዶጋሊ፣ የዓድዋና የካራማራ ድሎች የዚህ አሳፋሪ ዕጣ ፋንታ ሰለባ ለመሆን ተገደዋል፡፡
የዓድዋ ድል ያስገኘልንን በረከቶች መንዝረን ተጠቅመንባቸው ቢሆን ኖሮ … ዛሬ በዓባይ ወንዛችን ላይ በምንገነባው ግድባችን ምክንያት ማንም እየተነሳ አያስፈራራንም፤ታሪካዊና ሕጋዊ መብታችንን በአደባባይ ሊነጥቀን አይሞክርም ነበር፡፡ [በነገራችን ላይ የዓድዋ ድል በዓባይ ወንዛችን ላይ እየገነባነው እንዳለው ዓይነት ግዙፍ የልማት ሥራዎችን እንድንሠራ ስንቅ የሚሆን ድል ነው] … የዓድዋን በረከቶች ብናውቃቸውና ብንጠቀምባቸው ኖሮ በብሄር ፖለቲካ የምታመስ፣ ሚሊዮኖች በችጋር የሚሰቃዩባትና የሚፈናቀሉባት …. አገር አትኖረንም ነበር!
ኢትዮጵያ በዘር፣ በሃይማኖትና በአመለካከት ሳይከፋሉ ዓድዋ ላይ ጠላትን ድል ያደረጉ ልጆች እናት መሆኗን ማሰብና ከዓድዋ ድል በኋላ ባፈራቻቸው ‹‹ልጆቿ›› ምክንያት በአስከፊ የዘር ፖለቲካ ስትታመስ መመልከት እጅግ አሳዛኝና አስገራሚ ተቃርኖ ነው፡፡
ኢትዮጵያ ብዙ ሺ ዓመታትን ባስቆጠረው ዕድሜዋ ‹‹ረሀብንና ጦርነትን ደጋግማ የማስተናገዷ ምክንያት ምንድን ነው? ደጋግመው ካጋጠሟት ችግሮቿ መላቀቅ ያልቻለችው ለምን ይሆን?›› የሚለው ጥያቄ መሰረታዊው ነጥብ ነው፡፡ ኢትዮጵያውያንም ሆኑ ሌሎች አካላት ለዚህ መሰረታዊ ጥያቄ ብዙ ምላሾችን ሰጥተዋል፡፡ ከእነዚህም መካከል የውጭ ኃይሎች ሴራ፣ መደማመጥ አለመቻል፣ የልኂቃን በጎ ያልሆኑ እሳቤዎች፣ የሕዝቦቿ ማኅበራዊ ስሪት … የሚሉት ምክንያቶች ተጠቃሽ ናቸው። አገሪቱ በችግሮች ውስጥ ደጋግማ የመገኘቷ ምክንያት ‹‹የመለኮታዊ ኃይል ቁጣ›› እንደሆነ የሚያምኑም አሉ፡፡
ምክንያቶቹ የተለያዩ ቢሆኑም ለችግሩ ዘላቂ መፍትሔ ለመስጠት ግን አልተሞከረም፡፡ የአንዱን ንጉሥ ንግሥና ያልተቀበለ የግዛት አለቃ በንጉሡ ላይ ሲሸፍት፤ልኂቃን ከውጭ አገራት የሰሟቸውንና ያነበቧቸውን የፖለቲካና ምጣኔ ሀብት ርዕዮተ-ዓለሞች ያለምንም ማሰላሰል ወደ ኢትዮጵያ አምጥተው አገሪቱና ሕዝቧ ላይ ሲጭኑ ሕዝቡ ‹‹የባሰ አታምጣ›› በሚል ግራ የመጋባት ስሜት ሲቀበል፤እሳቤዎቹን የተቃወሙ አካላት ደግሞ አለመስማማታቸውን ለመግለጽ ብረት አንስተው ‹‹ጥራኝ ጫካው›› ሲሉ … ኢትዮጵያም ባለፈችበት መንገድ ደጋግማ እየተመላለሰች ኖረች፡፡ ረሀብ፣ ጦርነትና ድህነት ደግሞ ያለማንም ከልካይ ደግመው ደጋግመው አገሪቱን እንዲያሰቃዩ ዕድል አገኙ፡፡
ኢትዮጵያ ‹‹ለምን?›› እና ‹‹እንዴት?›› ብሎ ለመጠያየቅ፣ ለመከራከርና ለመወያየት የሚያስችል የሰለጠነ ባህል አላዳበረችም፡፡ ማሰብን፣ ማሰላሰልን፣ ሚዛናዊ ዕይታንና መመርመርን የሚጠይቀው እንዲሁም ‹‹ምን?››፣ ‹‹እንዴት?››፣ ‹‹ለምን?››፣ ‹‹መቼ?››፣ ‹‹የት?›› የሚሉትንና ሌሎች ተያያዥ መሠረታዊና አመክንዮን የተከተሉ ወሳኝ ጥያቄዎችን በማንሳት እውነትን ከሐሰት አብጠርጥሮ የማጥራት እሳቤን የያዘው ምክንያታዊነት የተባለው ጽንሰ ሃሳብ ቦታ አላገኘም፡፡
ሳያሰላስሉ በጅምላ የመደገፍና የመቃወም ድርጊት መለያችን የሆነ እስኪመስል ድረስ ደጋግመን ተመላልሰንበታል፡፡ እንደ?›› ብለው የጠየቁ ወገኖች ጥቂት አይደሉም፡፡ ይህ የኢ-ምክንያታዊነት አስተሳሰብ ከረጅም ዓመታት በፊት ጀምሮ ዋጋ እያስከፈለን ዛሬ ላይ ደርሷል፡፡ ‹‹ማን አለ?›› እንጂ ‹‹ምን አለ?›› ለሚለው ጉዳይ ትኩረት መስጠትን ትኩረት ነፍገነዋል፡፡ በቂ ባልሆነ ምክንያትና ማገናዘብ የታጀበው የድጋፍና የተቃውሞ ባህላችን እንደአገር ያገኘናቸው በርካታ የለውጥ ዕድሎች እንዲከሽፉ አድርጓል፡፡ ይህም አገራችን መድረስ የሚገባት ደረጃ ላይ እንዳትደርስ ትልቅ እንቅፋት ሆኗል፡፡ ይበልጥ የሚያስገርመውና ግራ የሚያጋባው ነገር ደግሞ ብዙ ዋጋ ካስከፈለን አደገኛ ተግባራችን ዛሬም ትምህርት ለመውሰድና ለመሻሻል አለመሞከራችን ነው፡፡
ምንም እንኳ ኢትዮጵያውያን ለዘመናት የቆየ አብሮ ተሳስቦና ተከባብሮ በጋራ የመኖር አኩሪ ቢኖራቸውም ይህ ድንቅ መስተጋብር ግን በተለይ በፖለቲካው ዘርፍ ምክንያታዊ እሳቤን መፍጠር አልቻለም፡፡ የኢትዮጵያ ፖለቲካ፣ ለጭፍን ድጋፍና ለጭፍን ተቃውሞ የሚመች ነው። በቅንነት የሚመክርና የሚተች እንዲሁም ከስህተት የሚገስጽ ሰው/ቡድን እንደጠላት ይቆጠራል። ለእውነት መታመን፣ ጥፋቶች እንዲታረሙ በቅንነትና በምክንያታዊነት ተቀናቃኝን ያለ ጥላቻ መተቸት ‹‹የድክመትና የፍርሐት ምልክት›› ተደርጎ ይታያል።
ለአገርና ለወገን የሚበጅ ግሩም ሃሳብ ያላቸው ወገኖች በጭፍን ጥላቻና ተቃውሞ ምክንያት ድምፃቸው እንዲታፈን ተደርጓል፡፡ በጭፍን ጥላቻና ድጋፍ ምክንያት አገሪቱ ብዙ እድሎችን አባክናለች፡፡ በአጠቃላይ ኋላቀሩ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ቅኝት ለምክንያታዊነት አይመችም። ይህ የምክንያታዊነት መንጠፍ ደግሞ ኢትዮጵያን በተለያዩ ዘመናት ብዙ ዋጋዎችን እንድትከፍል አድርጓታል፡፡ ጭፍን ተቃውሞና ጭፍን ድጋፍ አገሪቱ ያገኘቻቸውን የለውጥ እድሎች በሚገባ እንዳትጠቀምባቸው መሰናክል ሆነውባታል፡፡
በእርግጥ ዛሬ የዓለምን ምጣኔ ሀብትና ፖለቲካ በበላይነት የሚመሩት አገራትም በብዙ ችግሮች ውስጥ አልፈዋል፡፡ እነዚህ አገራት የችግሮቻቸውን ምንጮች በመገንዘብና ለችግሮቹ ዘላቂ መፍትሔ በመስጠት ኃያላን ለመሆን በቅተዋል፡፡ ጊዜያቸውን ለአሉባልታ መስጠትንና ትናንትናቸው ላይ ተቸክለው መቅረትን አልመረጡም፤መራራ የሆኑ እውነታዎቻቸውን ያለምንም ማድበስበስ በግልጽ ተነጋግረዋል፤ በችግሮቻቸው ላይ በግልጽና በድፍረት ተነጋግረው መፍትሔዎችን ማስቀመጥ በመቻላቸው አሁን ለደረሱበት ታላቅነት በቅተዋል፡፡
ታላቅ አገር ለመገንባትና የኃያል አገር ባለቤት ለመሆን የታላቅና በጎ አስተሳሰብ ባለቤት መሆን ያስፈልጋል። ከዚህ አንፃር ኢትዮጵያ ያለፈችባቸውን መንገዶቿን በጥልቀት ተፈትሸው፤ችግሮቿና ስብራቶቿ በግልጽ ውይይት ተደርጎባቸው የእስካሁኑን የኋልዮሽ ጉዞዋን በማስቆም ወደፊት እንድትራመድ ማድረግ ይገባል። ለተደጋጋሚ ረሀብና ጦርነት የዳረጓትና ከተለመደና ከተሰለቸ የ‹‹ታላቅነት›› ወሬ ተሻግራ እውነተኛ ኃያልነትን እንዳትላበስ ያደረጓት የዘመናት ሰንኮፎቿ በግልጽ ሊነገሩና ምላሽ ሊሰጣቸው ያስፈልጋል! ኢትዮጵያ ችግሮቿን በግልጽ የሚናገርላትና መፍትሔ የሚፈልግላት ልጅ ትሻለች! ‹‹ኢትዮጵያ ታላቅ ናት … እያደገች ነው … አትፈርስም …›› የሚሉ የቃላት ድርደራዎች ምንም አልፈየዱላትም፤አይፈይዱላትምም፡፡ አዲሱ 2014 ዓ.ም ደግሞ ስለኢትዮጵያ ችግሮች በግልጽ ተነጋግሮና ተማምኖ እውነተኛና ዘላቂ መፍትሔ ለማበጀት ተግባራዊ እንቅስቃሴዎች የሚደረጉበት ሊሆን ይገባል! ኢትዮጵያም ከዚህ በላይ ለመጠበቅና ጊዜ ለማባከን ዝግጁ አይደለችም!
አንተነህ ቸሬ
አዲስ ዘመን መስከረም 3/2014