ውድ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን፣
አስቀድሜ፣ ይህን የአዲስ አመት የእንኳን አደረሳችሁ ሠላምታና የመልካም ምኞት መግለጫ መልዕክቴን በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ስም ሳስተላለፍ ከፍ ያለ ክብርና ታላቅ ደስታ እየተሰማኝ ነው። የአዲስ አመት ዘመን መባቻ በኢትዮጵያውያን መንፈስ ውስጥ የለውጥ መገለጫ ከመሆን ባለፈ አዲስ አመት የጸሐይን ብርሃንን እና በቀለማት ያሸበረቁ መልከአምድሮችንም ያሳየናል። ይህ አዲስ ዓመት በአዲስ መንፈስ ከፍ የምትሉበት፣ እንዲሁም በወንድማማችነትና በአንድነት የምትደምቁበት እንዲሆንላችሁ ልባዊ ምኞቴን ልገልጽላችሁ እወዳለሁ።
ባለፈው ዓመት ከታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ፣ አሰራርና ሙሌት ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን የሀገራችንን ሉአላዊነት ለማስጠበቅ ያለንን አንድነትና ቁርጠኝነት በሚያንጸባርቅ መልኩ አከናውነናል። ግድቡን በምንገነባበት ወቅትም የገንዘብም ይሁን የቴክኒክ ድጋፍ ሁላችንም የበኩላችንን በተሻለ ደረጃ ከማበርከት ወደኋላ አላልንም። በዚህ ረገድ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵውያን ባደረጉት ርብርብ እጅግ ተደስታቸለሁ። ይሁንና! ከዚህ የበለጠ አስደናቂ ውጤችን እንድናስመዘግብ ይህንን ታላቅ ሃገራዊ ፕሮጀክት መደገፋችሁን አጠናክራችሁ እንድትቀጥሉ አሳስባለሁ።
ከዚሁ ጋር ተያይዞ የህዳሴው ግድብ ቁልፍ ጉዳዮች ላይ የአሸናፊነት ነጥቦችን እንድናስመዘግብ የጎላ ሚና የተጫወቱትን ዲፕሎማቶቻችንና ከተለያዬ ዘርፍ የተውጣጡትን ባለሙያዎቻችንን ልናደንቃቸውና ልናመሰግናቸው ይገባል። እንዲሁም የአፍሪካ ህብረት የወቅቱ ሊቀ መንበር ከሆኑት ፊሊክስ ትሼኬዲ ጋር ያደረግናቸው ተከታታይ ውይይቶችን ተከትሎ “ለአፍሪካ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሄዎች” የሚለውን እሳቤ ይዘው፤ በአፍሪካ ህብረት ጥላ ስር የሚመራውን የድርድር ሂደት እውን ለማድረግ እና የህዳሴ ግድቡ የሶስትዮሽ ድርድር በመርሆዎች ስምምነት መሰረት እንዲሆን ያደረጉትን ያላሰለሰ ጥረት እናደንቃለን።
ሁለተኛው የህዳሴ ግድብ ሙሌት ኢኮኖሚዊ ዕድገታችንን ለማነቃቃትና በርካታ ኢትዮጵያውያንን ከድህነት አዘቅት ውስጥ ለማውጣት ያነገብነውን የብልጽግና ተልእኮ ከግብ ለማድረስ አንድ ትልቅ ምዕራፍን የተሻገርንበት ነበር። ይሁን እንጂ አሁን ያስመዘገብነውን ስኬት እያዬን ዋናውና የመጨረሻ ግባችንን መርሳት አይኖርብንም። ገና ብዙ ስራ እንደሚጠብቀን አስተውለን በተባበረ ክንድ የብልጽግና ህልማችንን እውን እናደርገዋለን።
ውድ ኢትዮጵያውያን፣
ያለፈው ዓመት ኢትዮጵያውያን የውስጥና የውጪ ተግዳሮችን በመቋቋም ጽናታቸውንና መንፈሰ-ጠንካራነታቸውን ከፍ አድርገው ያሳዩበት ዓመት ነበር። ከዚህም በላይ ህዝባችንን ከዳር እስከ ዳር ያስደነገጠው የጥቅምት 24ቱ የኢትዮጵያ ጠሉ ከሃዲ ቡድን የምሽት ጥቃት በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ጥቁር ምልክትን ጥሎ ያለፈ ክስተት መሆኑን ኢትዮጵያውያን መቼም ቢሆን አይዘነጉትም። በዚህ ደርዝ ባጣ ድፍረቱና ጨካኝ ድርጊቱ በሰሜን እዝ የነበሩ በርካታ ጀግና ወታደሮቻችንን አጥተናቸዋል። ይሁንና የሀገራችን ቀንደኛ ጠላት ከሆነው ህወሓት የተቃጡብንን ተግዳሮቶች በሚገባ በመመከትና ከጠላቶቻቸን በተቃርኖ የቆመ የተባበረ ህዝባዊ ግንባርን በመፍጠር ጀግኖቻችን ለከፈሉት መሰዋትነት አክብሮትን አሳይተናቸዋል።
አሁንም ቢሆን በወያኔ የተደቀኑብን ፈተናዎች ገና አላለቁም። በአማራ፣በአፋርና በትግራይ ክልሎች ያሉ ወገኖቻችንን ከአሸባሪው ቡድን ቀንበር ነጻ መውጣታቸውንና ተፈናቃዮች ወደ የቀድሞ የመኖሪያ ስፍራቸው እንዲሁም የተጎዱ ሰዎችም ወደ መደበኛ ህይወታቸው መመለሳቸውን ማረጋገጥ ይኖርብናል። ይህን ስናደርግ በእርግጠኝነት ቁስሎቻችን ይፈወሳሉ።
ጠላቶቻችን እኛን ለውጭ ጥቃት ተጋላጭ ከመዳረጋቸው ባሻገር በኢኮኖሚያችንን ላይም መጠነ ሰፊ ጥቃቶችን ከፍተውብናል። ሆኖም ከድህነት ለመውጣት የምናደርገውን ጥረት እንዲያደናቅፉት በፍጹም መፍቀድ የለብንም። እነርሱ መሠረታዊ የፍጆታና ልዩ ልዩ የመገበያያ እቃዎችን በማከማቸት እንዲሁም የውጭ ምንዛሬን ህጋዊ ባልሆኑ መንገዶች በማስተላለፍ የልፋታችንን ፍሬ ሊያሳጡን የሚችሉትን ሁሉ እያደረጉ ይገኛሉ። ይህንን ደባ ይበቃል የምንልበት ጊዜው አሁን መሆኑን ተገንዝባችሁ፣ ኢትዮጵያውያንንና ትውልደ ኢትዮጵያውን በኢትዮጵያ ለወዳጅ ዘመድ ገንዘብ በምትልኩበት ጊዜ በሕጋዊ የገንዘብ ማስተላለፊያ ተቋማት በመጠቀም ኢትዮጵያን እንድትደግፉ እሳስባለሁ።
ውድ የኢትዮጵያ ልጆች፣
በመካከለኛው ምስራቅ በርካታ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች እየደረሰባቸው ያለውን ችግር ብንረዳም፤ ነገር ግን አስፈላጊውን እገዛ ከማድረግ ባለፈ፣ በሺዎች የሚቆጡትንም ወደ ሀገራቸው መመለሳችንን አጠናክረን ቀጥለናል። የኮቪድ ወረርሽ ከስደተኞቹ ብዛት ጋር ተዳምሮ ቢፈትነንም እርዳታ ለሚፈለጉ ዜጎቻችን ሁሉ ለመድረስ አቅማችን በፈቀደው ልክ እየተንቀሳቀስን ነዉ። በቀጣይም ሚኒስቴር መስሪያ ቤታችን ከሀገር ውስጥና ከአለም አቀፍ ባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት ችግሮችን ለመቅረፍና ዘላቂ መፍትሔ ለማበጀት እንደሚሰራ ቃል እገባለሁ።
ውድ ኢትዮጵያውያን፣
በርካቶች ተዓማኒና ሰላማዊ ምርጫ ለማካሄድ የሚያስችል አቅማችንን ተጠራጥረውት ነበር። ይሁን እንጂ ለሰላም ጥልቅ ፍቅር ላለው ኢትዮጵያዊ ምስጋና ይግባውና፣ 6ኛው ሀገራዊ ምርጫ ኢትዮጵያውያን ያለማንም ከልካይነት፣ በነጻነት ድምጻቸውን የሰጡበትና አሻራ ያስቀመጡበት መሆኑን አስመስክሯል። የምርጫዎቹ ውጤቶችም በአዲሱ አመት ወርሃ መስከረም መጨረሻ ልናቋቁመው ላለው አዲስ መንግስት የኢትዮጵያውያን የማስተማመኛና የማስረገጫ ማህተሞች ናቸው። ይህንንም እውነት ለማድረግ ኢትዮጵያውያን ሰላምን፣ብልጽግናንና ህብረትን መርጠዋል። ስለሆነም ሁሉን አቀፍ የፖለቲካ ውይይት በማድረግ እና ባለፉት ሶስት ዓመታት የጀመርናቸውን ዘርፈ ብዙ ተሃድሶዎችን በማፋጠን የብልጽግና ህልማችንን እውን እናደርገዋለን።
በዘህ ወቅት ለሁሉም ኢትዮጵያዉያን የማስተላልፈዉ ዋንኛ መልዕክት ራሷን የቻለችና የበለጸገች ኢትዮጵያን ለመፍጠር ልዩነቶቻችንን ሁሉ ወደ ጎን በማድረግ እጅ ለእጅ እንድንያያዝና በአንድነት ጸንተን እንድንቆም ነዉ።
የውጪ ጉዳይ ሚኒሰቴር መስሪያ ቤታችን የአዲሱ መንግስታችንን ጥንካሬ ነጸብራቅ ከሆኑ መልህቅ ተቋማት መካከል አንዱ እንደመሆኑ ፣ከመጪዎቹ የተሃድሶ ፍሬዎች ተቋዳሽ ይሆናል። የእኛ ተቋማዊ ተሃድሶም የሀገራችንን የዳበረ የዲፕሎማሲ ታሪክ የሚመጥን ጠንካራና ብቁ የዲፕሎማሲ ሰራዊት ይፈጥራል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ። እንዲሁም ይህ ተሃድሶ የሀገራችንን ጥቅም በሁለትዮሽና በባለዙ ወገን መድረኮች ለማስጠበቅ እንደሚረዳ ተስፋ አድርጋለሁ።
በመጨረሻም አዲሱ አመት ለሁላችሁም የሠላም ጤና፣ የደስታና የብልጽግና ይሆንላችሁ ዘንድ ከልብ እመኛለሁ።
አመሰግናለሁ!
አዲስ ዘመን መስከረም 1 ቀን 2013 ዓ.ም