በርካታ የማእድን ሀብት ከሚገኙባቸው የኢትዮጵያ ክልሎች መካከል አንዱ አሮሚያ ነው።
በክልሉ ከሚገኙ ዞኖች ውስጥ ደግሞ የምስራቅ ሀረርጌ ዞን አንዱ ሲሆን በአብዛኛው በኮንስትራክሽንና ኢንዱስትሪ ማእድን ሀብቱ ይታወቃል፡፡ በከፊል በከበሩ የማእድን ሀብቱም ብዙ አይታማም፡፡ ይሁን እንጂ እጅግ የከበሩ ከሚባሉ የማእድን አይነቶች ውስጥ የሚመደበው ወርቅ በዞኑ እንዳለ አንድም ጥናት አላረጋገጠም፡፡
ዞኑ በውስጡ አቅፎ የያዛቸውን በተለይ ደግሞ የኮንስትራክሽን ግብአት ማዕድናት ወጣቶችን በአነስተኛና ጥቃቅን ማህበራት በማደራጀት በሚገባ እየተጠቀመበት የሚገኝ ቢሆንም ለኢንዱስትሪ ግብአትነት የሚውሉ ማእድናትን ግን በሚፈለገው ልክ እየተጠቀመባቸው አይደለም፡፡ ተጨማሪ የኢንዱስትሪ ማእድናት በዞኑ እንደሚገኙ የሚታመን ቢሆንም በተለያዩ ምክንያቶች ማእድናቱ ተመርተው ጥቅም እያስገኙ አይደለም፡፡
የምስራቅ ሀረርጌ ዞን የማእድን አስተዳደር የስራ ሂደት ባለቤት አቶ ቦንሳ ተመስገን እንደሚሉት፤ ምስራቅ ሀረርጌ ከኦሮሚያ ዞኖች ውስጥ አንዱ ሲሆን በዚሁ ዞን በርካታ የኮንስትራክሽን፣ የኢንዱስትሪና የከበሩ ማእድናት በስፋት ይገኛሉ፡፡ ከኮንስትራክሽን ማእድናት ውስጥም ግራናይት፣ ላይምስቶንና ሳንድ ስቶን በዋናነት ይጠቀሳሉ፡፡ ከኢንዱስትሪ ማእድናት መካከል ደግሞ በብዛት ዶሎማይት፣ ካልሳይት፣ የከሰል ድንጋይና ሌሎች ይገኛሉ፡፡
አብዛኛዎቹ የማእድን ክምችቶች የሚገኙትም በባቢሌ ወረዳ ሲሆን ጋራሙለታ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ለኢንዱስትሪ ግብአትነት የሚውሉ እንደ ከሰል ድንጋይ አይነት ማእድናት በብዛት አሉ፡፡ በከፊል ከከበሩማእድናት ውስጥም እንደነ አጌትና ሩቢ ማእድናት መልካ በሎ በሚባል ወረዳ ላይ በብዛት ይገኛሉ፡፡
ከነዚህ ማእድናት መካከል በአብዛኛው ጥቅም ላይ እየዋሉ ያሉት ለኮንስትራሽክን ግብአትነት የሚውሉት ሲሆኑ በባቢሌ ወረዳ ላይ የሚገኘው ግራናይት አንዱ ነው፡፡ ለኢንዱስትሪ ግብአትነት የሚውለው ዶሎማይት የተሰኘ ማእድንም በተመሳሳይ በባቢሌ ወረዳ ተመርቶ ጥቅም ላይ እየዋለ ይገኛል። ኢንዱስትሪዎችም በአካባቢው ገብተው ማእድኑን በስፋት እያመረቱ ናቸው፡፡
እነዚህ ማዕድናትም በአንድ በኩል በአነስተኛና ጥቃቅን በተደራጁ ወጣቶችና አስራ አንድ በሚጠጉ አልሚዎች እየተመረቱ ይገኛሉ፡፡ ለብርጭቆና ለቀለም ግብአትነት የሚውለው ዶሎማይት የተሰኘውን ማእድን በአብዛኛው ኢንዱስትሪዎች ገብተውበት እያመረቱ ናቸው፡፡ በተጨማሪም ግራናይት የሚባለውንና ለኮንስትራክሽን ግብአትነት የሚያገለግለውን ማእድን በአልሚዎች ደረጃ እየተመረተ ይገኛል፡፡
በ2013 በጀት ዓመትም ከ1 ሺ 400 በላይ የሚሆኑ ወጣቶች በነዚሁ የማእድን ማምረት ስራ ውስጥ ገብተው እያመረቱ ይገኛሉ፡፡ በኮንስትራክን ማእድናት በተለይ ደግሞ እንደ አሸዋ፣ ጠጠርና ላይም ስቶን እያመረቱም ይገኛሉ፡፡
እንደ አቶ ቦንሳ ገለፃ ፤ ከእነዚህ ማእድናት ውጪ ጥቅም ላይ ያልዋሉ ሌሎች በርካታ ማእድናት በዞኑ አሉ፡፡ ለአብነትም ሬድ ጋርኔት ስቶን የተሰኘ የከበረ ማእድን አንዱ ሲሆን በ2009 ዓ.ም ከሃምሳ በላይ የሚሆኑ ወጣቶች ተደራጅተው እየሰሩበት የሚገኝ ቢሆንም እስካሁን ድረስ ገበያ አላገኘም፡፡
የኦሮሚያ ማእድን ልማት ባለስልጣንም ድጋፍ እንዲያደርግ ጥያቄ ቀርቦለት የነበረ ቢሆንም ጉዳዩን ወደ ማእድንና ነዳጅ ሚኒስቴር አስተላልፎታል፡፡ የማእድንና ነዳጅ ሚኒስቴርም ከጥራት ጋር ችግር ስላለ ምርቱን ለመቀበል ፍቃደኛ አልሆነም፡፡ በተመሳሳይ በዞኑ የሚገኙ ሌሎች የከበሩ ማእድናትም ጥቅም ላይ የማይውሉት የገበያ ችግር ስለሚያጋጥም ነው፡፡
በታላላቅ ባለሀብቶች መልማት የሚገባቸው ሌሎች ጥቅም ላይ ያልዋሉ ማእድናትም በዞኑ የሚገኙ ሲሆን ማእድናቱን አምርቶ ስራ ላይ ማዋል ከዞኑ አቅም በላይ ነው፡፡ ለምሳሌ በዞኑ የብረት ማእድን በብዛት እንደሚገኝ ይታወቃል፡፡ ነገር ግን ስራ ላይ ለማዋል ትልቅ አቅም ይፈልጋል፡፡
የምስራቅ ሀረርጌ ዞን ከተለያዩ ዞኖች ጋር የሚዋሰን እንደመሆኑ መጠን በተለይ ደግሞ በሶማሌ ክልል በኩል ከሶማሌና ከሶማሊላንድ ጋር ተዋሳኝ በመሆኑ አብዛኛውን ጊዜ ማእድናት በኮንትሮባንድ መልኩ ይንቀሳቀሳል፡፡ ይህም ከማዕድኑ መገኘት ያለበትን ገቢ እያሳጣና ትልቅ ችግር እየፈጠረ ይገኛል፡፡ ከዚህ አኳያም ዞኑ ከክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ጋር በመተባበር እየሰራቸው ያሉ ስራዎች አሉ፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ በማእድን ዘርፉ በተለይ በህብረተሰቡ ዘንድ የተሳሳቱ የአመለካከት ችግሮችም የሚታዩ ሲሆን በተለይ ደግሞ ከማእድኖቹ ጋር በተያያዘ ህብረተሰቡን ለማሳሳት የሚደረጉ ጥረቶችን ለማስተካከል በዞኑ በኩል ተመሳሳይ ስራዎች እየተሰሩ ይገኛሉ፡፡
በዞኑ በርካታ ማእድናት እንደሚገኙ ቢገመትም በቂ ጥናቶች ባለመደረጋቸው አብዛኛዎቹ መአድናት ጥቅም ላይ እየዋሉ አይደሉም፡፡ በተመሳሳይ ከፌዴራል እስከ ወረዳ ድረስ ጥናቶች እየተካሄዱ ቢሆንም በጥናት የተለየው የምስራቅ ሀረርጌ ዞን የማእድን ሀብት ከ30 በመቶ አይበልጥም፡፡
ለዚህም የማአድን ጥናት ለማከናወን በቂ ቴክኖሎጂ አለመኖር፣ በዘርፉ የሰለጠነ የሰው ሃይል እጥረትና የፋይናስ ችግር በምክንያትነት ይጠቀሳል፡፡ ይህንኑ አሟላቶ ማእድናቱን ጥቅም ላይ ለማዋልም ዞኑ አቅም ያንሰዋል፡፡
በቀጣይም የዞኑ ማእድን አስተዳደር በርካታ እቅዶችን አውጥቶ እየሰራ ይገኛል፡፡ በዋናነት አልሚዎች ወደ ዞኑ ገብተው ማእድናቱን የሚያለሙበትን ሁኔታ በማመቻቸት ከጥናቱ ጀምሮ ያሉ ስራዎች ተከናውነው፤ ሌሎች ፖለቲካዊ ችግሮችም እንዲፈቱ ተደርገው ለወጣቱ የስራ እድል እንዲፈጠርና ህብረተሰቡም ከዘርፉ ተጠቃሚ እንዲሆን አለፍ ሲልም ሀገርም እንድትጠቀም ትልቅ ዝግጅት እየተከናወነ ይገኛል፡፡
አስናቀ ፀጋዬ
አዲስ ዘመን መስከረም 3/2014