በአዕምሮ ጤና አገራችን ካፈራቻቸው በጣት የሚቆጠሩ ሰዎች መካከል አንዷ ናቸው:: ለአገራቸው ሲሉ የሚሳሱት ነገር የሌላቸውና ብዙ መደላደል ቢኖርም ለአገር ሲባል ይተዋልን በተግባር ያሳዩም ናቸው:: ምክንያቱም በአሜሪካን አገር የሁለተኛ ድግሪ ተማሪዎችን በማስተማር ከፍተኛ ደሞዝ እየተከፈላቸው መኖር ሲችሉ ከአገሬ የሚበልጥ የለም በማለት አገራቸው ያደረገችላቸውን ለመክፈል ተመልሰዋል::
በዚያ ሳሉም ቢሆን ለአገራቸው ያላደረጉት ነገር አልነበረም:: በተለይም አገር ፈታኝ ችግር ውስጥ ስትሆን በፍጥነት ከሚሳተፉ የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጆች አንዷ ናቸው:: ለዚህም በአብነት የሚጠቀሰው ኮሮና በተስፋፋባቸው እና መፈናቀል ባለባቸው አካባቢዎች ላይ ለመድረስ የሠሯቸው ሥራዎች ናቸው:: በእርግጥ ብቻቸውን ሳይሆን አንድም ኮሚቴ፣ አንድም አባል በመሆን ከአገራቸው ልጆች ጋር ያደረጉት ነው:: በሌላ በኩል በትምህርት ብቃታቸው አገራቸውን ጭምር የሚያስጠራ ፤ ለሴቶች አርኣያ የሚሆን ተግባር የፈጸሙ ናቸው:: ለዚህም ለመማር ያላቸው ፍላጎትና ውጤታማነት ማሳያ ነው:: ምክንያቱም እንግዳችን በአገራቸው አንድ ሁለተኛ ድግሪ ያላቸው ሲሆን፤ በውጭ ደግሞ ሁለት የሁለተኛ ድግሪ በአጠቃላይ ሦስት የሁለተኛ ዲግሪ ትምህርት ተምረው በብቃት አጠናቀዋል::
ሦስተኛ ድግሪያቸውንም እንዲሁ በአዕምሮ ጤና የትምህርት መስክ በአሜሪካን ሃገር ተምረው የተመረቁ ሲሆን፤ በዘርፉም በአገሪቱ አሉ ከሚባሉት መካከል አንዷ መሆን ችለዋል:: ከዚህ በተጓዳኝ ከቲቲአይ/የአንደኛ ደረጃ መምህርነት/ መነሳታቸውም ብዙዎችን የሚያስተምርና በትምህርት ተስፋ ካልተቆረጠ የት ላይ እንደሚያደርስ የሚያሳዩና የሚያስተምሩ ያደርጋቸዋል:: ስለሆነም እኛም ይህንን እናም ተሞክሯቸውን ማህበረሰቡ በተለይም ሴቶች እንዲጠቀሙበት በማሰብ ዶክተር ማስተዋል መኮንንን ለዛሬ ‹‹ የህይወት ገጽታ›› አምድ እንግዳችን አድርገናቸዋል:: ትማሩባቸው ዘንድም ጋብዘናችኋል::
ልጅነት በነፃነት
በቀድሞ ጎጃም ክፍለአገር ፣ በደብረማርቆስ አውራጃ ከደብረማርቆስ 28 ኪሎሜትር ወደምሥራቅ ራቅ ብላ በምናገኛት የቦቅላ ቂርቆስ ውስጥ መርካቶ በምትባል ቀበሌ ገበሬ ማህበር ተወለዱ:: ልዩ ስፍራዋ አዲስ አንባ ትባላለች:: እናም በዚህች መንደር ውስጥ አብዛኛውን የልጅነት ጊዜያቸውን አሳልፈውባታል:: ቦርቀውና በራሳቸው እየተመሩም ነው ያደጉት:: እናት አባታቸው ስለሚያሞላቅቋቸው የፈለጋቸውን እያደረጉ እንዲያድጉ ሆነዋል::
የገጠር ልጅ ቢሆኑም የከተማውን የአኗኗር ዘዬ ነው የሚከተሉት:: ለዚህ ደግሞ ነፃነት የሰጣቸው አባታቸው ከማህበረሰቡ ቀድመው የነቁና ልጆቻቸውን በነፃነት የሚያሳድጉ መሆናቸው ነው:: ስለዚህም በባህሪ ከወንዶቹ ጋር ባይመሳሰሉም ውሏቸው ግን ከእነርሱ አይለይም ነበር:: ጨዋታም ሆነ ሥራ ከእነርሱ ጋር ማከናወን ይመቻቸዋል:: እንደውም ልዩ ተሰጥኦአቸውን ሳይፈሩና ሳይሸማቀቁ ማውጣት የቻሉት ከእነርሱ ጋር ጊዜን በማሳለፋቸው እንደሆነ ይናገራሉ::
በወቅቱ ዘመናዊና ባህላዊ ሙዚቃዎችን ያንጎራጉሩ ነበር:: ጭፈራ ላይም ቢሆን ማንም አያክላቸውም:: በተለይ ግን አገራዊ ዘፈኖች ላይ ብቃታቸው ልዩ እንደነበር ያስታውሳሉ:: የሠርግ ዘፈንም እንዲሁ ይወዳሉ:: የአካባቢው አድማቂም ነበሩ:: በእርግጥ እዚህ ላይ የቤተሰብ ክልከላ አንዳንዴ ይኖርባቸዋል:: ምክንያቱም ነገሮች ከበዙ ትምህርቷ ላይ ጫና ይፈጥርባታል ብለው ይሰጋሉ:: ከዚህ አንጻር በቃሽ ሊባሉ ይችላሉ:: ከአደረጉት በኋላ ለምን አደረግሽው ተብለው ግን አያውቁም::
አባት ለልጆቻቸው ራሳቸውን ችለውና ራሳቸውን ሆነው እንዲያድጉ ዕድል በመስጠት ይታወቃሉ:: የጎረቤት ልጆች ጭምር ሲጫኗቸው እረፉ ባይ ናቸው:: ስለዚህም እንግዳችን ነፃ የሆነ የአስተዳደግ ዕድልን አጣጥመውት እንዲያድጉ ሆነዋል:: በዚያ ላይ በቤት ውስጥም ቢሆን ብዙ ሥራ እንዲሠሩ አይደረጉም:: እርሻና ከብት ጥበቃ እንኳን ሰው ቀጥረው ያሠራሉ እንጂ እነርሱን በጫና ውስጥ እንዲያልፉ አንድም ቀን አላደረጓቸውም:: ሆኖም ወደው እንዲሠሩ ይበረታታሉ:: ስለዚህም ፈልገው ካልሆነ በስተቀር የአንቺ የሥራ ድርሻ ነው ተብለው የሠሩት ሥራ የለም:: ፈልገው ግን እንጀራ ከመጋገር ውጪ ያሉትን ማንኛውንም ተግባራት ይከውናሉ:: በተለይ ችግኝ መትከልና መንከባከብ የእርሳቸው የልዩ ፍላጎት ሥራ እንደነበር ያስታውሳሉ::
ባህሪያቸው እንደ ዕድሜ ደረጃቸው የሚለያዩ ሲሆን፤ እስከ ስምንተኛ ክፍል በሚማሩበት ጊዜ ተደባዳቢ፣ ተቀናቃኝ፣ እኔ ያልኩት ብቻ ይሁን ባይ ነገር ግን ሳይታዘዙ የሚሠሩ ነበሩ:: ከዚያ በኋላ ያላቸው ባህሪ ደግሞ በእናታቸው አማካኝነት ተለውጦ የእርሳቸውን ባህሪ ተላበሱ:: በዚህም አርቆ አስተዋይ፣ ታዛዥ፣ ቸርና ሰው አክባሪ መሆን ቻሉ:: በተለይ ቅድሚያ ለሌላ የሚሉት ነገር ዛሬ ድረስ እንዳልጠፋ ይናገራሉ:: እንደውም መምህር የመሆን ፍላጎት ያደረባቸውም ከዚህ ባህሪያቸው የተነሳ እንደሆነ አጫውተውናል::
መምህርነት በወቅቱ ተወዳጅ ሙያ ከመሆኑም በላይ የሚያሳዩት ባህሪ ይገዛ ነበር:: በአካባቢው ሰው መወደዳቸው፣ የእውቀት ልካቸውና ምክራቸው ከእነርሱ ውጪ መሆንን አያስመኝም ነበር:: ስለዚህ መልካም መሆንን ስለሚወዱ መምህር መሆንን አስበዋል፤ ሆነውታልም:: ዛሬ ድረስ የሚደሰቱበት ሙያም ነው::
ብዙ ነፃነት ባለበት ቤት ያደጉት ባለታሪካችን በአካባቢው ባህል ዘንድ በስድስት ዓመታቸው ተድረው እንደነበር አይረሱትም:: ለዚህ ያበቃቸው ደግሞ ቆሞ ቀር የሚለው እሳቤ ነው:: ቤት ያሉት ሴት ልጆች ሁሉም ሲዳሩ እርሳቸውም ደርሳ ትምጣ ተብለው ተልከው ነበር:: ሆኖም ነቃ ያሉና በፍጥነት ነገሮች የሚገባቸው ዓይነት ልጅ ስለነበሩ ሳምንት ሳይቆዩ ነው ከባል ቤት ወደቤተሰቦቻቸው ጋር የተመለሱት:: ከዚያ በኋላም ቢሆን ቤተሰብ አስገድዶ ተመለሽ አላላቸውም:: ስለዚህም የልጅነት ፍላጎታቸውን ወደሚያሳኩበት መስመር ጉዟቸውን ቀጠሉ::
የትምህርቱ ሂደት
የትምህርትን ሀሁ የጀመሩት ባደጉባት ቀበሌ የቦቅላ ነው:: ከአንደኛ እስከ ስምንተኛ ክፍል ከቤተሰብ ሳይነጠሉ የቦቅላ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ትምህርታቸውን መከታተል ችለዋል:: ከዚያ በአካባቢው ትምህርት ቤት ስለሌለ ወደ ደብረማርቆስ እንዲያቀኑ ሆኑ:: ከሴት ጓደኛቸው ጋር ቤት ተከራይተውም ከዘጠነኛ እስከ 12ኛ ክፍል ያለውን ትምህርታቸውን ተከታተሉ:: ይህ ጊዜ እጅግ ፈታኝ እንደነበር ያስታውሳሉ:: ምክንያቱም ሴት በመሆናቸውና ወደቤተሰብ በሚሄዱበት ጊዜ ችግሮች ያጋጥማቸዋል:: በስንቅ ጉዳይ አንድም ቀን ተቸግረው አያውቁምና በእርግጥ አርፈው ተቀምጠው መማር ይችሉ ነበር:: ምክንያቱም አባት እዚያው ገዝተው የሚበሉበትን በቂ ገንዘብ ሰጥተው ይልኳቸዋል:: ሆኖም እንግዳችን የእናታቸው ነገር ስለማይሆንላቸው በ15 ቀን አንዴ አራት ሰዓት በእግራቸው ተጉዘው ይሄዳሉ:: ይህ ደግሞ የህይወት ፈተናዎችን ያዩበት ጊዜ እንዲሆን አድርጓቸዋል::
ወደ ቤተሰብ ለመጓዝ ሲያስቡ ሴት በመሆናቸው የሚደርስባቸው ፈተና ብዙ እንደነበርም ያስታውሳሉ:: እንደውም ይህንን ሲያስቡ አንድ ቀን ያደረጉትን መቼም አይረሱትም:: ነገሩ እንዲህ ነው:: ወንዶች ኮረዳ ሴት ሲያዩ የሚያደርጋቸው ይጠፋል:: እናም እነርሱ በጉዞ ላይ እያሉ ለመደፈር የሚያስችል አደጋ ከፊታቸው ይጋረጣል:: እና ይህንን ጊዜ ለማለፍ አንድ ዘዴ መዘየድ እንዳለባቸው በዚያችው ቅፅበት ያስባሉ:: እናም አንድ ሃሳብ ይመጣላቸዋል:: ይህም በእጃቸው የያዙትን የቅባት ዕቃ ቦንብ አስመስለው ‹‹አበላሸሁህ›› በማለት ለመወርወር ይዘጋጃሉ:: በዚህ ጊዜ ያልታሰበ ነገር የገጠማቸው ጎረምሶች ፈርጥጠው በመሮጣቸው ከአደጋው ያመልጣሉ፡፡
ከቤተሰብ መነጠሉም እንዲሁ የህይወት ውጣ ውረዱ አንዱ እንደነበር የሚያነሱት ዶክተር ማስተዋል፤ አንዳንዴ የከሰዓት ተማሪ ከሆኑ ሰኞ ጠዋት ስለሚነሱ እናት ችግር እንዳይገጥማት በማለት ከሰው ጋር እስኪቀላቀሉ ድረስ ይሸኟቸው እንደነበርም አይረሱትም:: በትምህርታቸው ከክፍል ብቻ ሳይሆን ከወረዳውም ሆነ ከዞኑ አንደኛ በመውጣት ሁልጊዜ ሽልማት የሚያገኙ ሲሆኑ፤ የ12ኛ ክፍል ውጤታቸው ግን ዩኒቨርሲቲ ሊያስገባቸው አልቻለም:: ለዚህ ደግሞ ሁለት ምክንያቶችን ይጠቅሳሉ:: የመጀመሪያው የእናታቸው በጠና መታመም ሲሆን፤ እርሳቸውን ለማስታመም ሁለት ወር ሳይማሩ ማቋረጣቸው ነው:: በዚህም ለፈተናው ዝግጅት ማድረግ አልቻሉም::
ሁለተኛው ማትሪክ ላይ የመጀመሪያዎቹን ሁለቱን ፈተናዎች ብቻ እንደወሰዱ የወንድማቸውን ሞት መስማታቸው እንዲረበሹና ቀጣዩን ትምህርት በተረጋጋ መንፈስ እንዳይሠሩት አድርጓቸዋል:: ይህ ደግሞ የ12ኛ ክፍል ውጤታቸው ላይ ተጽዕኖ አሳረፈ:: ስለዚህም ውጤቱም ያልተጠበቀ ሆነ:: ይህም ቢሆን ተስፋ አልቆረጡም:: ይልቁኑም ዳግም ለመፈተንና ከጓደኞቻቸው እኩል ለመሆን ራሳቸውን ወደማዘጋጀቱ ገቡ:: ዓመትም ጠብቀው ተፈተኑ:: ነገር ግን አሁንም ቢሆን የፈለጉት ላይ ለመግባት አላስቻላቸውም:: ስለዚህም መጀመሪያ ትተውት የነበረውን የቲቲአይ ትምህርት ለመቀጠል ወሰኑ::
ወደ ደብረብርሃን መምህራን ማሰልጠኛ ተቋምም ተመድበው ትምህርታቸውን በዚያ ተከታተሉ:: ቀደም ሲል የነበራቸው አቅምም በዚህ ላይ ታይቶ ነበር:: ከማሰልጠኛው ከፍተኛ ውጤት በማምጣት ብዙ ሽልማቶችን መውሰድ አስችሏቸዋል:: እንደውም አንዱ ሽልማት የፈለጉት ቦታ ላይ እንዲመደቡ ዕድል መሰጠቱ እንደነበር ያስታውሳሉ::
አንድ ዓመት እንዳስተማሩም ሰበታ የመምህራን ማሰልጠኛ ኮሌጅ የልዩ ፍላጎት ትምህርት ማለትም የብሬልና የምልክት ቋንቋን ጨምሮ ብዙ ትምህርቶችን ተማሩ:: ከዚያ ከዘጠኝ ዓመት ከመንፈቅ ሥራ በኋላ ነው ደብረማርቆስ እያስተማሩ በክረምቱ ክፍለጊዜ ጎንደር ዩኒቨርሲቲ ዲፕሎማቸውን መማር የቻሉት:: በቋንቋ ትምህርትም በከፍተኛ ውጤት ትምህርቱን አጠናቀዋል::
ብዙም ሳይቆዩ በአድቫንስ ድግሪያቸውን ለመማር ወደ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ያቀኑት ዶክተር ማስተዋል፤ ትምህርት ለመጀመር አስበው የመጡት በአማርኛ ቋንቋ ትምህርት ነበር:: ሆኖም ሰበታ ሲሠለጥኑ የሚያውቋቸው የስነልቦና መምህራቸውን ማግኘታቸው ነገሮች እንዲቀየሩ አደረጋቸው:: ይህም ልዩ ፍላጎት ትምህርት የሚቀጥለው ዓመት በድግሪ ስለሚከፈት የቀጣዩዋ መምህራችን እንድትሆኝ እንፈልጋለንና በዚህ መስክ መቀጠል የለብሽም ብለው የትምህርት መስኩን ማስቀየራቸው ነው:: በእርግጥ በእርሳቸው ቢሆን ኖሮ በወቅቱ የሚቻል አይሆንም ነበር:: ነገር ግን መምህሩ ወደዚያ ቀይረው የገቡ በመሆናቸው ሁሉንም ነገር አመቻችተውላቸው ከአማርኛ ቋንቋ ትምህርት ለልዩ ፍላጎት ወደሚቀርበው ሳይኮሎጂ ትምህርት እንዲቀይሩ ሆኑ:: በሳይኮሎጂ ትምህርትም መማራቸውን ቀጠሉ::
ዶክተር ማስተዋል ዕድሉን አላገኙም እንጂ ብቃታቸው ያው ነበረ:: በጣም ጎበዝና ውጤታማ ተማሪ ናቸው:: ለዚህም ማሳያው ሳይኮሎጂ ትምህርት ክፍልን ተቀላቅለውም በከፍተኛ ውጤት ነው የተመረቁት:: እንደውም ከዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች የማዕረግ ተመራቂ ናቸው:: በወቅቱ ዋንጫዎቹን ጠራርገው የወሰዱትም እርሳቸው ነበሩ:: የመጀመሪያዋ ሴት የወርቅ ተሸላሚ መሆን የቻሉም ለመሆን በቅተዋል:: ይህ ውጤታቸው በአገር አቀፍ ደረጃ ጭምር ሳይቀር ወርቅ ያሸለማቸው እንደነበርም አጫውተውናል::
ከሁሉም በላይ ትምህርታቸውን የሚቀጥሉበት አጋጣሚም መሆኑ ያስደስታቸዋልም:: ምክንያቱም
በዩኒቨርሲቲው ቀርተው እንዲያስተምሩም እንዲማሩም ሆነዋል:: ስለዚህ ሁለተኛ ድግሪያቸውን ከማስተማሩ ጎን ለጎን በማህበራዊ ሳይኮሎጂ ትምህርት መስክ ማጠናቀቅም ችለዋል::
አባታቸው ከቄስ ትምህርት ባያልፉም ልጆቻቸው እንዲማሩ የሚያደርጉት ትግል ዛሬ የሦስት ማስተር ባለቤት እንዳደረጋቸው የሚናገሩት ዶክተር ማስተዋል፤ ሁለተኛ ድግሪያቸውን ተመርቀው መቆም አልቻሉም:: ሁልጊዜ ለመማር በመሞከር ላይ ነው ጊዜያቸውን የሚያሳልፉት:: በዚህም ሙከራቸው አንድ ቀን ዕድልን ሰጣቸው:: ያውም በሁለት መልኩ የሚጠሩበትን:: ይህም የኔዘርላንድና የአሜሪካ መንግሥት ጥሪ ነው:: ሆኖም የአንዱ ማለትም የአሜሪካው ትምህርት ሙሉ ወጪን የሚሸፍን አልነበረም:: የመጀመሪያ ዓመቱን ዩኒቨርሲቲው እንዲችላቸው የሚጠይቅ ነው:: ስለዚህም ዩኒቨርሲቲው ቀድሞ ያስተማራቸው ስለሆነ ዳግም መጠየቁን አልፈለጉትምና እርሱን በመተው የኔዘርላንዱን መርጠው ተጓዙ::
በኔዘርላንድ መንግሥት አማካኝነት ያገኙት ይህ ዕድል ሙሉ ወጪን የሚሸፍን ሲሆን፤ በማህበራዊ ጤና ሳይንስ ትምህርት የተማሩበት ነው:: ዩኒቨርሲቲው ውሃግንገር ዩኒቨርሲቲና ሪሰርች ሴንተር የሚባል ነው:: ስለዚህም እንደተለመደው ሁለተኛ ድግሪያቸውን በዩኒቨርሲቲው በከፍተኛ ውጤት ማጠናቀቅ ችለዋል:: በእርግጥ ይህ ጊዜ እንደሌላው የትምህርት ጊዜ በቀላሉ ያለፈ አልነበረም:: ብዙ ትግል የተደረገበት ነው:: ምክንያቱም ሌላኛውን ሁለተኛ ድግሪ በአሜሪካ ጀምረው ሁለቱ ጋር እየተመላለሱ ያገኙት ነው:: የሁለቱ አገራት የትምህርት አሰጣጥ ሥርዓት መለያየቱና የዕረፍት ጊዜያቸውን መጠቀም መቻላቸው እንዲሁም የኔዘርላንዱ ትምህርት የመመረቂያ ጽሑፍ ፕሮፖዛል ያለቀለትና ሦስት ኮርሶች ብቻ የቀረው መሆኑ አግዟቸዋል::
የመጨረሻው ጽሑፋቸውን ደግሞ አገራቸው ላይ ለመሥራት ስለወሰኑ ብዙም የተቸገሩበት አልነበረም:: ይሁንና መረጃ በማሰባሰብ እንደ ዶክተር የሺመቤት ደምሴ ዓይነት ሰዎች ባያግዟቸው ኖሩ ይህ ሊሳካ አይችልም ነበር ይላሉ:: ለዚህም እርሳቸውን የሁልጊዜ ባለውለታቸው አድርገው እንደሚወስዷቸውና እንደሚያመሰግኗቸው ይናገራሉ:: በአሜሪካ ትምህርታቸውን የተከታተሉት በሞንታና ዩኒቨርሲቲ ሲሆን፤ የወጣቶችና የልጆች ዓለምአቀፋዊ አስተዳደግ በሚባል የትምህርት መስክም ነው ሁለተኛ ድግሪያቸውን መሥራት የቻሉት::
ከዚህ በኋላ ልሰብስበው ወደሚል ሃሳብ ውስጥ ገቡ:: ምክንያቱም ሁለተኛ ድግሪዎች ስምን አይቀይሩም:: በዚያ ላይ ምንም እንኳን የእውቀት አቅም በየጊዜው እንደየትምህርት ክፍሉ የሚጨምር ቢሆንም ወደ አገር ቤት መጥቶ ለመሥራት ግን ብዙ ፈተናዎች ይገጥማሉ:: ስለሆነም የቤተሰቦቻቸውን ህልም እውን ለማድረግና ዶክትሬታቸውን ለመያዝ መማር እንዳለባቸው አመኑ:: የሦስተኛ ድግሪያቸውን ለመማር አሁንም በአሜሪካ አመለከቱ:: ዕድሉን በማግኘታቸውም ኖርዘርን ኢሊኔዊስት ዩኒቨርሲቲ በሜንታል ሄልዝ ካውንስል ኦፍ ኢዲኩዌሽን ወይም በአዕምሮ ጤና የትምህርት መስክ ተመረቁ:: በመማር ደረጃ እነዚህን ትምህርቶች የተማሩ ሲሆን፤ የተለያዩ ሥልጠናዎችንም ወስደው አቅማቸውን ገንብተዋል:: ማስተማርም መማር ነው ብለው ስለሚያምኑ ከትምህርት እንዳልተለዩ ይሰማቸዋል::
ከሐበሻ እስከ ኦክላማ
ሐበሻ አንደኛ ደረጃ ትምህርትቤት የልጅነት ህልማቸው መተግበሪያ ነበረ:: መምህርት ሆነው ለዓመት ከመንፈቅ ያህል የአካባቢያቸውን ልጆች አስተምረውበታል:: አሁንም የቀደመ ውጤታቸው ጠቅሟቸው ደብረማርቆስ ከተማ ውስጥ የንጉሥ ተክለሃይማት ትምህርት ቤት በመግባትም ብዙዎችን ሲቀርጹ ቆይተዋል:: እነዚህ ተማሪዎች ልዩ ፍላጎት ያላቸው በመሆናቸውም የተለየ የማስተማር ጥበብን ተጠቅመው ነበር የሚያስተምሯቸው:: በእርግጥ ወደዚህ ትምህርትቤትም የመጡት በምክንያት ነው:: መምህራን ሲመለመሉ መስፈርት ነበረው:: ይህም ወጣት፣ በትምህርታቸው የላቀ ውጤት ያላቸውና በስነምግባር ምስጉን የሆኑ መምህራን የሚል ነው:: ስለዚህም እርሳቸው አንዷ ሆነው በመገኘታቸው ወደዚህ እንዲመጡ ተደርገዋል:: የታሰበውን ያህል መሥራት እንደቻሉም ይናገራሉ::
ከስምንት ዓመት የአገልግሎት ጊዜ በኋላ ወደ ትምህርት ያቀኑ ሲሆን፤ ከትምህርት በኋላ ደግሞ መሥራት የጀመሩት አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ነው:: ይህም እንደላይኛው የተለየ ገጠመኝ የነበረበት እንደሆነ ያስታውሳሉ:: መጀመሪያ በትምህርት ሚኒስቴር አማካኝነት ምድባቸው ደብረብረሃን ዩኒቨርሲቲ ሆኖ ነበር:: ነገር ግን ውጤታቸው ከፍተኛ በመሆኑ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሊለቃቸው አልቻለም:: ስለዚህም ቀጣዩ የሥራ ቆይታቸው አዲስ አበባ ሆኗል:: በሳይኮሎጂ ትምህርት ክፍልም ገብተው ማስተማራቸውን ቀጥለዋል::
ከሦስት ዓመታት የአገልግሎት ጊዜ በኋላ ደግሞ ወደ ውጭ ለመማር ስለሄዱ በዚያው ሥራ እንዲጀምሩ ሆነዋል:: ለዚህ ያበቃቸው ደግሞ ለአገሬ በትምህርት ብቻ ሳይሆን በልምድም ብዙ የማመጣቸው ነገሮች አሉ ብለው ማመናቸው ነው:: ስለዚህም ትምህርት እንዳጠናቀቅሁ ወደአገራቸው ሳይመለሱ በሳውዝ ኢስተርን ኦክላማ ስቴት ዩኒቨርሲቲ በአዕምሮ ጤና የትምህርት መስክ የሁለተኛ ድግሪ ተማሪዎችን ማስተማር ጀመሩ:: ለሦስት ዓመታትም በዚያ ቆዩ:: ከዚያም በላይ የሚቆዩበትና የሚያስተምሩበት ብዙ ዕድል ነበራቸው:: ሆኖም ብዙ ላደረገችልኝ አገሬ መቼ ልሠራ ነው በሚል ድሎታቸውን ትተው አገራቸውን ለማገልገል መጡ::
ከሁሉም በላይ እየተመላለሱ የሚሠሯቸው ሥራዎች ጠቅልለው መጥተው ቢሠሩት የበለጠ ውጤታማ እንደሚያደርጋቸው ስላመኑ እንደመጡም አጫውተውናል:: የመምጣታቸው ምስጢር በተለይም ወጣቱ ላይ ለመሥራት እንደሆነም ነግረውናል::
የአገር አበርክቶ
ለአገራቸው ሁልጊዜ የሚቆሙና የሚያገለግሉ እንዲሆኑ አባታቸው ሁልጊዜ ይመክሯቸው ነበር:: በተለይም ተምረው ከአገራቸው ውጪ እንዲኖሩ አይፈልጉም:: ስለዚህም እርሳቸውም የአባታቸውን ቃል ለማክበር ሲሉ የነበራቸውን ምቹ ሁኔታ ወደጎን በመተው ወደ አገራቸው ተመልሰዋል:: በእርግጥ እዚያም ሆነው ለአንድም ቀን አገራቸውን ረስተው አያውቁም:: ለአገር የተባለ ነገር ላይ ሁሉ ይሳተፋሉ:: ከዚያም አልፈው ኮሚቴና ሰብሳቢ ጭምር በመሆን በትውልድ ቀያቸውና በክልላቸው ላይ እንዲሁም በአጠቃላይ አገር ላይ በሚደረጉ እገዛዎች ወደኋላ ሳይሉ ይሰራሉ፤ ብዙ ነገርም አድርገዋል:: ለአብነትም የአመራር ስልጠና ከደብረማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር በተደጋጋሚ ሰጥተዋል::
በክቡር አዲስ አለማየሁ ስም ለተከፈተው አዳሪ ትምህርትቤት የሚሆኑ ቁሳቁሶችንም ጎፈንድሚ በመክፈት ከ38 በላይ ኮሚፒውተርና ላፕቶፕ በመግዛት ከላኩት መካከል አንዷ ናቸው:: መንግሥት በኮቪድ ጊዜ ለአማራ ክልል ባለሀብቶች ጥሪ በሚያደርግበት ወቅት ኮሚቴ ውስጥ ጭምር በመግባት የኢትዮጵያ ተወላጆችን በማነቃቃት የህክምና ቁሳቁስ ተገዝቶ እንዲላክም ያደረጉ ናቸው::
በስደት ያሉ ወጣቶችና መሰደድን የሚመኙ ወጣቶች ላይ የሚደርሰውን የስነ ልቦና ጫና ለመቅረፍም ከአንድ አሜሪካ ካለ ኢትዮጵያዊ መምህር ጋር በመሆን በርቀት የማማከር ሥራ ይሠሩም ነበር:: ወቅታዊ ሁኔታ ላይ በተለይም ልጆች አስተዳደግ ላይ ያተኮረ ሥራ የሚሠራ ደውል ቲዩብ የሚባል በመክፈት የምክር አገልግሎትና የነበራቸውን ክህሎት ያጋሩም ለእውቀት የማይሰስቱ ባለሙያ ናቸው:: ይህ ደግሞ በተለይም በውጭው ዓለም ለሚያድጉ ኢትዮጵያዊያን ፍቱን መድሀኒት የሰጠ እንደነበር ይናገራሉ::
ቤተሰብ በኢትዮጵያ ባህል ልጁ እንዲያድግ ሲፈልግ ልጁ አሻፈረኝ ይላል:: በተቃራኒው ልጁ ሲፈልግ ቤተሰብ ያንን አይፈልግም:: እናም ሁለቱን ለማስማማት ይህ ቲዩብ እጅግ እንደጠቀመ ያነሳሉ:: በተመሳሳይ በሥራ ማጣትና ባሉበት ሁኔታ ችግር ራሳቸውን ለማጥፋት ድረስ የሚመኙ ወጣቶችን ለመታደግም እንደጠቀማቸው ያስረዳሉ::
በአገሪቱ ነባራዊ ሁኔታ የአመራሮች በጥሩ ሁኔታ አለመያዝ፣ የሚደርስባቸው ግፍና በደል በጣም ስለሚያሳዝናቸው የፖለቲካ ሰው ባይሆኑም ህመማቸው ግን ያማቸዋል:: በዚህም ነፃ የውይይት መድረኮች እንዲከፈቱ በማድረግ የተለያዩ ስልጠናዎችንም በአካል ጭምር እየመጡ ይሰጣሉም፤ ሲሰጡም ቆይተዋል:: ከዚህ ጎን ለጎን የኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲዎች ከውፅዎች ጋር /የውል ስምምነት/ኤምኦዩ እንዲፈራረሙና የውጭ አገር መምህራን እዚህ እየመጡ የእኛ አገር መምህራንም እዚያ እየሄዱ የሚያስተምሩበትን መንገድም ከፍተዋል::
በአካባቢያቸው ትምህርትቤትና ክሊኒክ ባለመኖሩ፣ ልጆቻቸው ርቀው ሄደው መማራቸው በጣም የሚያንገበግባቸው አባታቸው የራሳቸውን መሬት ሰጥተው ትምህርትቤትም ክሊኒክም እንዳሸሩ የሚያስታውሱት ዶክተር ማስተዋል፤ አባቴ በዚያ ዘመን ከዚህም አልፎ ችግኝ በማፍላት በቅናሽ ዋጋ ለአካባቢው ሰው በማቅረብ ልማት እንዲስፋፋ ማድረጉ፤ አዳዲስ ሥራዎችና ዘመናዊነት ወደ አካባቢው ማምጣቱ ሁልጊዜ ራሴን እንድጠይቅ ያደርገኛል ይላሉ:: ከ30 ዓመት በፊትም ለትምህትና ለጤና መስፋፋት በዚህ ደረጃ እርሱ ይህንን ካደረገ እኔስ እንዲሉ ያስቻላቸው እንደነበርም ያነሳሉ:: እንግዳችን በወቅታዊ ሁኔታዎች ላይ ማለትም በስነልቦና ጉዳይ ላይ በተለያዩ ሚዲያዎች ላይ የተለያዩ አስተያየቶችንም ይሰጣሉ:: በተለይም በኮሮና እና አሁናዊ አገራዊ ጉዳዮች ላይ ጥልቅ ትንታኔ በፈለጉዋቸው ጊዜ የሚሰጡና ወደኋላ የማይሉም ናቸው::
‹‹አገሬን በመሀል እየመጣሁ ማገልገሌ ወቅታዊ ፈተናዎቹን ጭምር እንድረዳቸውና እንዳውቃቸው ሆኛለሁ:: ሲቀጥልም ሁሉ የተደላደለ ከሆነ ለምን መጥቼ እሠራለሁ›› ሲሉ የሚጠይቁት ዶክተር ማስተዋል፤ ችግሮችን ለመለወጥ እስከመጣሁ ድረስ ችግሮችን መቋቋም እንዳለብኝ አምኜ ገብቼበታለሁ:: ስለዚህም ነገሮች ቢከብዱም በትዕግስት ለማለፍ እሞክራለሁ:: ሙሉ ለሙሉ ለመለወጥ ሳይሆንም የራሴን ድርሻ ለመወጣት በማሰብ ስለሆነ የመጣሁት የቻልኩትን ያህልም አደርጋለሁ ይላሉ::
የአዕምሮ ጤና ሲባል የሚዳሰስና የሚታይ ስላልሆነ ፈተናዎች ብዙ ሊሆኑ ይችላሉ:: ነገር ግን መሥራት የምፈልገው በዚህ ላይ በመሆኑ እታገለዋለሁም ብለውናል:: በዚያ ላይ የአዲሱ ፓርላማ አባልና የጎዛመን ወረዳ የህዝብ እንደራሴ በመሆናቸው ይህንን በቀላሉ ለመሥራት እንደሚያግዛቸው በጭውውታችን መካከል አንስተውልናል:: ከዚህ በተጓዳኝ የጀመሩትን የማስተማር ሥራ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ለመቀጠልም ማሰባቸውን አጫውተውናል:: አሁን የቅጥር ሁኔታቸው በሂደት ላይ እንደሚገኝም ነግረውናል::
ከዚህ ቀደም ሁለት ሆነው ከደብረማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመፈራረም ተመርቀው ሥራ ያጡ ወጣቶች ላይ የሚሠራ ፕሮጀክት ነድፈው ሲሠሩ እንደቆዩ ያጫወቱን ዶክተር ማስተዋል፤ ከ15 ቀን በፊት በደብረማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ፓናል ውይይት እንዳደረጉና ስድስት መሰረታዊ ኮርሶችን በማሰልጠን የሥራ ዕድል የሚፈጥሩበትን ሁኔታ እንደዚህ ቀደሙ እንደሚያመቻቹ አስረድተዋል:: ልምዱና ስልጠናው በደብረማርቆስ ብቻ እንዲወሰንም መሥራት ይፈልጋሉም:: ምክንያቱም አሁን ካለበንበት ችግር የምንወጣው ወጣቱ ሥራ ሲያገኝ ነው የሚል እምነት አላቸው::
መልዕክት
በግለሰብ ደረጃ ለውጦች እንዲመጡ ከፈለግን መጀመሪያ የአስተሳሰብ ለውጥ ላይ መሥራት ያስፈልጋል:: ለአብነት አንድ ሰው ጊዜያዊ ደስታ ለማግኘት ብሎ በእርሱ ውስጥ ያሉትን ሰዎች ደስታ ከፈተነና በድርጊቱ ዝም ከተባለ ድርጊቱን መቀጠል ሳይሆን ለምን ተሸነፈልኝ ብሎ ማመንና ቆም ብሎ ራሱን ማየት ይኖርበታል:: ምክንያቱም ይህ የሆነለት የእርሱን የሰዓታት ደስታ ላለመንጠቅ ይሆናል:: እናም እንዲህ ዓይነት አስተሳሰቦች ልምድ መሆን አለባቸው የመጀመሪያው መልዕክታቸው ነው::
ከሰውነት እጥበት የህሊና ንፅህና ምን ያህል ዋጋ እንዳለው ማንም ይረዳል:: ስለሆነም ከበጎ ሽታ በጎ ህሊና ማትረፊያ ነውና ምናልባት አሁን ያለው ሁኔታ ትንሿ ጀንበር እንደጠለቀችብን እንድናስብ ቢያደርገንም ነገ የሚቀጥል ህይወት እንዳለ በማመን በትዕግስት አሳልፈን ትልቋን ፀሐይ እንድናያትና እንድትወጣልን ማድረግ ላይ መሥራት ይኖርብናል:: ለዚህ ደግሞ ሥነ ምግባራዊ መልካምነትን ፍጹም በሆነ ዕውቀት ውስጥ እንዲያልፍ መሥራት ያስፈልጋል::
በየትኛውም የህይወት ሁኔታ ውስጥ ብንሆን በዚህ ምክንያት በአካባቢያችን ባሉት ሰዎች ይህ ደረሰብን አንበል:: ከዚያ ይልቅ ለምን እንደ ሆነብን ወደመገንዘቡ እንግባ:: ምክንያቱም ይህ የሆነው በምክንያት፣ በእኛ ስህተት ሊሆን ይችላል:: እናም ለምን በዚህ ልዩ ሁኔታ ውስጥ ገባሁ ሲሉ በእርግጠኝነት በጥሩ ሁኔታ የተገለገሉበትን ነገር ያገኙታል:: መልካም አሳቢ የሚሆኑበትን ዕድልም ይፈጥርልዎታልም ምክራቸው ነው::
በሕይወት የምንጓዝበት መንገድ በእኛ የአመለካከት ነጥብ ላይ የተመሠረተ ነው:: የአመለካከት ነጥባችን ወደ አዘነበለበት እንዘማለን:: ስለዚህ መልካሙ እንዲደፋ መሥራት ከሁሉም ይጠበቃል:: ለዚህ ደግሞ ጊዜ መስጠትና ደጋግሞ መሥራት ግድ ነው:: መልካምና አገር ወዳድ ሰዎችን አርአያ አድርጎ መውሰድም እንዲሁ:: ከዚያ የእነሱ ብሩህ አመለካከት የተሻሉ ሰዎች ለመሆን ያግዘናል:: ነገሮችን ከብርሃን ጎኑ አንጻርም የምናይበትን መንገድ ይጠርጉልናል:: እኛም ጨለማው እስኪበራ ድረስ እንድንጠብቅ እንሆናለን:: በዚህ ደግሞ እኛን ብቻ ሳይሆን አገራችንንም ከገጠማት አደጋ እንታደጋለን የመጨረሻው መልዕክታቸው ነው
ጽጌረዳ ጫንያለው
አዲስ ዘመን መስከረም 2/2014