በአገሪቱ በክረምት ወራት አብዛኛው ወጣት ክፍል ከትምህርት እረፍት የሚወስድበት ወቅት በመሆኑ በተለያዩ በጎ ፈቃድ አገልግሎቶች ላይ ሲሳተፍ ማየት የተለመደ ተግባር ነው።መንግሥትም ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የመንግሥት ተቋማት በበጎ ሥራዎች ላይ እንዲሳተፉ እያደረገ ይገኛል።በተለይ የአቅመ ደካማዎችን ቤት ማደስና ለበዓል መዋያ መደገፍ ባህል እየሆነ መጥቷል።ይህን ተግባር ወጣቱ እየወረሰው እንዲሄድ ለማድረግ የአዲስ አበባ ወጣቶች ማህበር የበኩሉን እየተወጣ ይገኛል።የማህበሩን የክረምት በጎ ፈቃድ እንቅስቃሴ ምን እንደሚመስል ከማህበሩ ዋና ፀሐፊ ወጣት ይሁነኝ መሀመድ ጋር ቆይታ አድርገናል።መልካም ንባብ።
አዲስ ዘመን፡- በክረምት ወራት ማህበሩ ለማከናወን ያቀዳቸው የበጎ ፈቃደኝነት ሥራዎች ምን ምን ነበሩ?
ወጣት ይሁነኝ፡– ማህበሩ በክረምት ወራት በበጎ ፈቃደኝነት ሊሰራቸው ያሰባቸው ሥራዎች በከተማ፣ በክፍለ ከተማና በወረዳ ደረጃ በግለሰብ፤ በተቋማትና በሌሎች ላይ ለመስራት አቅዶ ነበር።ሥራዎቹን በሃይማኖት ተቋማት ውስጥ፣ በሆስፒታልና በተለያዩ ጉዳዮች የበጎ ፈቃድ ሥራ ይከናወናል ተብሎ እቅድ ተይዞ ነበር።የመጀመሪያው ቀደም ብሎ የተጀመረውን የኮቪድ ወረርሽኝን የመከላከል ሥራ ዋነኛ ጉዳይ ነበር።ይህን ለመከላከል ከመጀመሪያ ጀምሮ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች እንዲሳተፉ ተደርጓል።እነዚህን አሁን ያለው መዘናጋትና ትኩረት ማነስ እንዲሁም ያለውን የሀሳብ መበተን አቅፈው ወደ ተግባር እንዲገቡ የማድረግ ሥራው ተጀምሯል።በኮሮና ወረርሽኝ ርቀት የማስጠበቅ፣ ሳሙናና ሳኒታይዘር የመጠቀም እንዲሁም ሌሎች መሰል ተግባራቶችን እንዲከናወን እናደርጋለን።
ሌላው ማህበሩ ባለው አቅም ወጣቶችን በማስተባበር ሃምሳ ያረጁ ቤቶችን ማደስና ለተጎዱ ሰዎች ምቹ ማድረግ ሥራ በእቅድ ተይዞ ነበር።‹‹ካለኝ አካፍላለው›› በሚል መሪ ሀሳብ በየክፍለ ከተማው ድጋፍ የሚፈልጉ ሰዎችን በመለየት የክረምት ምገባ እንዲከናወን ተደርጓል።ወጣቱ የተለያየ አግባብ የሚያገኛቸውን ድጋፎች ለህብረተሰቡ እያደረገ የምገባ ጉዳዮች ላይ ትኩረት ተሰጥቶ ተሰርቷል።የችግኝ ቦታዎችን በመለየት መንግሥት በህብረተሰቡ ትኩረት ቢሰጣቸው ብሎ ያስቀመጣቸውን በመከተል በልዩነት የተለዩ ሃያ የችግኝ መትከያ ቦታዎች ተዘጋጅተው ወደ ተግባር ተገብቷል።
አብዛኛው መስሪያ ቤትም ሆነ ተቋም ወደ ችግኝ ተከላ ትኩረት የሚያደርግ በመሆኑ ቀደም ሲል የነበሩትንና ህብረተሰቡንና በተለያዩ የንቅናቄ አግባቦች የተተከሉ ችግኞችን ደግሞ እየተከታተሉ ችግኞቹን የመንከባከብ ሥራ ተሰርቷል።ግማሽ ሚሊዮን ችግኞችን ለመትከል እቅዶ ተይዞ የነበረ ሲሆን ይህን ሥራ በጥሩ እየሄደ ይገኛል።በዚህ ተግባር ላይ 27 ሺህ ወጣቶች ተሳታፊ ሆነዋል።የችግኝ ተከላው ሥራ በተለያየ ጊዜ መሰራት የሚችል በመሆኑ ሥራው ቀጣይነት ይኖረዋል።የአካባቢ ፅዳትና ውበት መጠበቅ ላይ ማህበሩ በበጎ ፈቃደኞች በክረምት ለማከናወን ካቀዳቸው ተግባራት አንዱ ነበር።በክረምት ወቅት የፍሳሽ ማስወገጃ ትቦዎች የተደፈኑ በመሆናቸው ጎርፍ እየተከሰተ ነው።ለዚህ ደግሞ ከሚመለከታቸው ጋር በመሆን የጎርፍ መከላከያ ሥራዎች እንዲሰሩ፣ ለጎርፍ ተጋላጭ የሆኑ ትቦዎች ጠረጋ ዝግጅት የማድረግ ሥራ፣ በጎርፍ አደጋ የሚመጡ አላስፈላጊ አካባቢንና ህብረተሰቡን ሊጎዱ የሚችሉ ነገሮችን የማፅዳት ሥራ ተከናውኗል።
ማህበሩ በሚያደርጋቸው የበጎ ተግባራት የኮሮና ወረርሽኝ እንዳይስፋፋ የኬሚካል ርጭት ያከናውናል።የኤች አይ ቪ ቫይረስ በአሁኑ ወቅት ትኩረት እየተሰጠው አይደለም።ኤች አይ ቪን የመከላከል፣ የምርመራና የስነ ተዋልዶ ግንዛቤ የመስጠት ሥራው ትኩረት ለሰጠው ይገባል በሚል በእቅድ ተይዞ ወደ ተግባር ተገብቷል።ለዚህ ተግባር በይበልጥ ተጋላጭ የሚሆነው ወጣቱ ነው።ለዚህ ደግሞ በተለያዩ መንገዶች ለወጣቱ ትምህርትና ግንዛቤ የመስጠት ሥራዎች እየተከናወኑ ናቸው።በተጨማሪም በሚደረጉ የወጣቶች መድረክ ላይ የኤች አይ ቪ ምርመራ ጎን ለጎን ደግሞ የስነ ተዋልዶ ትምህርት እየተሰጠ የኮሮና ወረርሽኝ ግንዛቤን በማያያዝ ትምህርት እየተሰጠ ይገኛል።
የደም ልገሳ አገልግሎት ተጠናክሮ መቀጠል አለበት በሚል በእቅድ ተይዞ ሥራው የተከናወነ ነው።ማህበሩ በእቅድ ሶስት ሺህ ወጣቶችን በማሳተፍ ደም ልገሳ እንዲከናወን አስቦ ከወቅታዊ ሁኔታው አንፃር በብዛት ህብረተሰቡ ደም እየለገሰ በመሆኑ ከተቀመጠው እቅድ በላይ ማሳካት ተችሏል።የደም ልገሳ ሥራው በዋነኛ ሥራነት ተይዞ እንቅስቃሴ የተደረገበት ሲሆን ከፍተኛ ንቅናቄ መፍጠር ተችሎበታል።በኪነጥበብ ሥራዎች ላይ ማህበሩ በክረምት ወጣቶች ከትምህርታቸውና ከሌሎች ጉዳዮች አረፍ የሚሉበት ወቅት በመሆኑ ጊዜያቸውን በአግባቡ እንዲያሳልፉ ትልልቅ የሚባሉ በቲያትር፣ በስነፅሁፍ፣ በስነ ጥበብና በሌሎች ዘርፎች የራሳቸው አበክርቶ ያደረጉ አካላትን በመለየት ለወጣቶች የልምድ ልውውጥና ስልጠና እንዲሰጡ ተደርጓል።
ስልጠና የወሰዱ ወጣቶች ወደ ታች ላሉት እንዲሰለጥኑና ሥራዎቻቸውን በኢግዚቢሽን መልክ እንዲያቀርቡ ተደርጓል። ወቅታዊ በሆኑ ጉዳዮች ላይም መልዕክት የሚተላለፍበትና አጫጭር ሥራዎች እንዲቀርቡ እየተደረገ ነው።በቅርፃ ቅርፅ፣ በትወናና በስነፅሁፍ ስልጠና እየተሰጠ ነው።በጎነት በሆስፒታል የሚል ዘመቻ ማህበሩ ወጣቶችን በማሰማራት በክረምት ወራት ለማከናወን እቅድ ይዞ ነበር።ይህ ሥራ ባለፈው 2012 ዓ.ም ላይም በተመሳሳይ ሁኔታ ተከናውኖ ነበር።በሆስፒታል እጅግ ትኩረት መሰጠት ያለበት ነገር ያለ ሲሆን በኮሮና ወረርሽኝ ወቅት ወረርሽኙን ለመከላከል አስታማሚዎችና የታማሚዎች ርቀት ጠብቀው እንዲንቀሳቀሱ የማድረግ ሥራ ተከናውኗል።በተጨማሪም የሆስፒታል ውስጥ የአይቲ ትምህርት የተማሩና እውቀት ያላቸውን በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች ለሆስፒታሉ የሰነድ ማደራጀት ሥራ እንዲሰሩ ተደርጓል።
በአሁኑ ወቅት ተጨማሪ ነገር ለማከናወን የግንዛቤ ሥራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ።በአዲስ አበባ ሆስፒታሎች ውስጥ ከተለያዩ ቦታዎች ከህክምና የሚመጡ ታካሚዎች ይስተናገዳሉ።እነዚህ ታካሚዎች ከተማውን ስለማያውቁትና ቋንቋ መናገር ስለማይችሉ እነሱን የሚንከባከብና አስፈላጊ አገልግሎት የሚሰጣቸው የበጎ ፈቃድ ወጣት እንዲመደብላቸው ተደርጓል።በተጨማሪም የላቦራቶሪና የመድኃኒት ትዕዛዝ ለታካሚው በሚሰጥበት ወቅት በጎ ፈቃደኞቹ ከታካሚው ጋር በመሆን አስፈላጊውን ትብብር እያደረጉ ይገኛሉ።ሌላው ስፖርታዊ ውድድርና እንቅስቃሴ በክረምት በጎ ፈቃድ ውስጥ የተካተተ አንዱ ሥራ ነው።ወጣቱ ብቁና ንቁ የሆነ ዜጋ እንዲሆን ከህክምናና ከአመጋገብ በዘለለ ስፖርታዊ እንቅስቃሴ ወሳኝ ነገር ነው።ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎች በተለያዩ ዘርፎች ላይ ማህበሩ ተሳትፎ አድርጓል።ለምሳሌ የእግር ኳስ ውድድር በአንድ ክፍለ ከተማ ውስጥ ወረዳ ከወረዳ እንዲወዳደሩ ተደርጓል።ስፖርታዊ የሆኑ ስልጠናዎችን በመስጠት ወጣቱ በክረምት ወራት በእነዚህ ስፖርታዊ እንቅስቃሴ ላይ እንዲያተኩር ተደርጓል።ስፖርታዊ ስልጠናዎች በባለሙዎች እንዲሰጡ ተደርጓል።
ሌላው ማህበሩ በክረምት ወራት ያቀደው የትምህርት ቤትና የሃይማኖት ተቋማትን ማፅዳት ሥራ ነው። ትምህርት ቤቶች ምዝገባቸውን አከናውነው ሲጨርሱ ተማሪዎችን ወደ መቀበል ይገባሉ።ተማሪዎችን ሲቀበሉ ትምህርት ቤቶች በክረምት ዝግ ስለነበሩ ዝግጁ መሆን አለባቸው።ማህበሩ የራሱን አስተዋጽኦ ለማበርከት በትምህርት ቤቶች የኮሮና ወረርሽኝ እንዳይስፋፋ ከትምህርት ተቋማት ጋር በመሆን ሥራ ማከናወን፣ የፅዳት ሥራ ለመስራት ወጣቶችን ማሰማራት እንዲሁም ሌሎች ሥራዎች እየተከናወኑ ነው።ድንበር ዘለል በጎ ፈቃድ አገልግሎት ለማከናወን ማህበሩ ሥራዎችን የጀመረ ሲሆን በቅርቡ ከድሬዳዋ ከመጡ ወጣት ማህበራት ጋር የልምድ ልውውጥ አድርጎ በሚሊኒየም ፓርክ የችግኝ ተከላ ተከናውኗል።ከሌሎች ጋርም ለመስራት ዝግጅት እየተደረገ ነው።
የታላቁ የህዳሴ ግድብ ቦንድ በመግዛት ወጣቱ ተሳታፊ እንዲሆን ማህበሩ ሥራዎችን እየሰራ ነው።በክረምት ወራት የቦንድ ግዢ እንዲከናወን ተደርጓል።ለዚህም ህዝብ በሚበዛባቸው ቦታዎች ጫማ በመጥረግና ሌሎች ሥራዎችን በመስራት የቦንድ ግዢ ተፈፅሟል።የህብረተሰብ ንቅናቄ በመፍጠር የቦንድ ግዢ እንዲፈፀም የማነሳሳት ሥራ እየተከናወነ ነው።የአካባቢን ፀጥታና ሰላም ለማስጠበቅ፣ የከተማ ግብርና እንዲሁም ሌሎች ሥራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ። አንድ ወጣት አካባቢውን እንዲጠብቅ ማህበሩ በጎ ፈቃደኞችን አሰማርቶ ከፖሊስ ጋር እየሰራ ነው።
አዲስ ዘመን፡- በደም ልገሳ፣ በችግኝ ተከላ እንዲሁም በቤት እድሳት በክረምቱ ምን ውጤታማ ሥራ ተከናወነ?
ወጣት ይሁነኝ፡- ማህበሩ በክረምት ወራት ለመስራት ከያዛቸው እቅዶች ውስጥ በውጤታማነት እየሄደ ነው የሚባለው የችግኝ ተከላ፣ የደም ልገሳና የአቅመ ደካማዎችን ቤት ማደስ ሥራ ነው።ማህበሩ ሥራዎቹን ቀደም ብሎ ሲያከናውነው ነበር።መንግሥት ደግሞ አሁን ለሥራዎቹ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራባቸው ይገኛል።አሁን ላይ ወጣቶችና ህብረተሰቡ የተጎዱ ወገኖችን ቤት በማደስ ላይ ልዩ ትኩረት በመሰጠቱ ከተያዘው እቅድ በላይ ማከናወን ተችሏል።ከዚህም በላይ እየተሰራ ይገኛል።የህብረተሰቡ አንድነትና መተባበር ለውጥ የሚያመጣ በመሆኑ የአንዱ ችግር የኛም ነው በሚል በመነሳቱ ቤት ማደስ ሥራው ወደ ቀላል ተግባርነት መለወጥ ተችሏል።
ሁሉም ወጣት በሚኖርበት አካባቢው በሙያው እየተሳተፈ የአቅመ ደካማዎችን ቤት የማደሱ ሥራ እየተፋጠነ ነው።ቤት ለመገንቢያ የሚውሉ ግብዓቶች በበጎ ፈቃደኛ ባለሀብቶች እየተሸፈነ ይገኛል።መንግሥትም ለጉዳዩ የሰጠው ትኩረት ጉልበትና ሃይል ለማህበሩ ጨምሮለታል።የታሰበው ሥራ ወደ ውጤት እንዲደርስ አድርጓል።የችግኝ ተከላና እንክብካቤ ሥራው በእቅድ በተመራ መልክ የተሰራ ሲሆን መንግሥት ‹‹ኢትዮጵያን እናልብስ›› በሚል መሪ ሀሳብ ከፍተኛ እንቅስቃሴ አድርጎበት ነበር።በክረምቱ ወራት በችግኝ ተከላ መርሐ ግብሩ በማህበሩ በኩል ከግማሽ ሚሊዮን በላይ ችግኞችን መትከል ተችሏል።የችግኝ መንከባከቡ ሥራ ከታቀደው በላይ ወጣቶችን ባሳተፈ መልኩ ተከናውኗል።
ይህ ሊሆን የቻለው የመንግሥት ተቋማትና የግል መስሪያ ቤቶች እንዲሁም ህብረተሰቡ ችግኝ መትከልን እንደ ባህል ይዞ እየተንቀሳቀሰ በመሆኑ ነው።እዚህ ላይ የሚያስፈልገው የባለሙያ ድጋፍ ሲሆን እንዴት መተከልና በምን አይነት መልኩ እንክብካቤ መደረግ እንዳለበት ግንዛቤ ያስፈልጋል።ማህበሩም ይህን እየሰራ ይገኛል።የችግኝ ተከላው ሥራ ቀጣይነት እንዲኖረው እየተሰራ ነው።
የደም ልገሳ ሥራው በወቅታዊ የአገሪቱ ሁኔታ በደንብ ትኩረት ተደርጎ እየተሰራ ያለ ጉዳይ ነው።አሁን ባለው የህግ ማስከበር ዘመቻ በሚደርሱ ጉዳቶች ደም አስፈላጊ በመሆኑ ብዙ ደም እየተሰበሰበ ይገኛል።ነገር ግን በተለያዩ ቦታዎች ማለትም በወሊድና በድንተኛ አደጋዎች ምክንያቶች ደም አስፈላጊ በመሆኑ ማህበሩ ወጣቱን በማስተባበር ደም እንዲለገስ እያደረገ ይገኛል።በተለይ በመልካም ጤንነት ላይ የሚገኙ ወጣቶች ባላቸው ጊዜ ደም ቢለግሱ የደም እጥረትን መቅረፍ ይቻላል።ወጣቱ በየሶስት ወሩ ደም እንዲለግስ ንቅናቄ እየተሰራ ነው።
አዲስ ዘመን፡- ማህበሩ እየሰራቸው የሚገኙትን የበጎ ፈቃድ ሥራዎች በበጋ ወራት ለመቀጠል እቅድ ይዟል?
ወጣት ይሁነኝ፡– ማህበሩ የወጣቶችን ተጠቃሚነት ለማሳደግ እየተንቀሳቀሰ የሚገኝ ነው።ወጣቱ ያለውን ጉልበት ተጠቅሞ የተለያዩ ሥራዎች ላይ እንዲሰማራ የበጎ ፈቃድ ሥራዎች ላይ እንዲሳተፍ ለማድረግ ሀሳብ ተቀምጧል። የበጎ ፈቃድ ሥራ በክረምት ወራት ብቻ ተሰርቶ የሚተው ጉዳይ አይደለም።በጎ ፈቃድ ሥራ በወቅቶች የሚገደብ ሳይሆን በማንኛውም ጊዜና ሰዓት የሚከናወን ነው።በተለይ የችግኝ መንከባከብ ሥራ በበጋ ወቅት በትኩረት መሰራት ያበት ነገር ነው።በበጋ የሰው ቁጥር ቢያንስም የበጎ ፈቃድ ሥራ ለማከናወን እቅድ ተይዞ እየተሰራ ነው።በተጨማሪም አቅም የሌላቸውን ሰዎች ቤት ማደስና ለበዓል ድጋፍ ማድረግ መለመድ ያለበት ጉዳይ ነው።በጎ ፈቃድ በሆስፒታል የሚለው መርሐ ግብርም በበጋ ወቅት ቀጥሎ የሚከናወን ሥራ ነው።
አዲስ ዘመን፡- ለሰጠኸን ማብራሪያ እናመሰግናለን።
ወጣት ይሁነኝ፡– እኔም አመሰግናለው።
መርድ ክፍሉ
አዲስ ዘመን ጳጉሜን 5/2013