በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ወጣቱ ማህበረሰባዊ ተሳትፎ እያደረገ ሲሆን አቅመ ደካማዎችን በማገዝ ረገድ ከፍተኛ ሚና እየተጫወተ ነው።የመረዳዳትና የመደጋገፍ ባህል በሁሉም ቦታዎች እየተቀጣጠለ ሲሆን በተለይ በተለያዩ ምክንያቶች የተፈናቀሉ ወገኖችን በመርዳት ወጣቱ ግንባር ቀደም ነው።
መንግሥትም ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የተቸገሩን በማብላትና ቤታቸውን በመጠገን ውጤታማ ሥራ እያከናወነ ነው።ይህም እንቅስቃሴ በዓላት ወቅት ብቻ ሳይሆን በሌሎችም ወቅቶች ሊሰራ የሚገባው ጉዳይ ነው።የሲቪክ ማህበራት አዋጅ ከተሻሻለ በኋላ በሁሉም ቦታዎች በጎ አድራጎት ማህበራት እየተበራከቱ ይገኛል።በተለይ የህብረተሰቡን ችግር ከሥሩ ለመፍታት ውጤታማ ሥራ እያከናወኑ ይገኛሉ፡፡
በብዛት ወጣት ከሚገኝባቸው አገራት መካከል አንዷ ኢትዮጵያ ናት።በኢትዮጵያ ታድያ ወጣቱ ክፍል ከመስራትና አገርን ከማሳደግ ይልቅ ባልባሌ ትርክቶች ተጠምዶ እርስበርስ ሲጋጭ ማስተዋል ከተጀመረ ዋል አደር ብሏል።በአገሪቱ የሚሰራ ሥራ ጠፍቶ ሳይሆን አለመስማማቶች በመበራከታቸው የሚሰሩ እጆች ለጥፋት እየዋሉ ይገኛሉ።በመንግሥትም ደረጃ ጠንከር ያሉ ሥራዎች ባለመከናወናቸው ዝርፊያና ቅሚያ በከተሞች አካባቢ እየተስፋፋ ይገኛል።
ይህን ጉዳይ ያለ ምክንያት አይደለም ያነሳሁት።ለጥፋት የሚውሉ እጆች እንዳሉ ሁሉ ለበጎ ተግባራት የሚሰነዘሩ እንዳሉ ለማሳየት ፈልጌ ነው።የተቸገሩ አረጋውያንንና የጎዳና ተዳዳሪዎችን የሚደግፉና አለንላችሁ የሚሉ በርካታ በወጣቶች የተመሰረቱ ማህበራት እንዳሉ በዚሁ አምዳችን አስቃኝተናችሁ ነበር።አብዛኛዎቹ ማህበራት እውቅናና ፈቃድ አግኝተው እርዳታ በማሰባሰብ ድጋፍ የሚያደርጉ ናቸው፡፡
አረጋውያን አገራቸውን ለማቅናት ደፋ ቀና ብለው የደከሙ በመሆናቸው ተከታታይ የሆነ ድጋፍ ያስፈልጋቸዋል።በተለያዩ አካባቢዎች አረጋውያንን የሚደግፉ ማህበራት እየተበራከቱ ናቸው።እነዚህ ማህበራት አረጋውያኑን ከመደገፍ ባሻገር የህክምናና ሌሎች ነገሮችን እያሟሉላቸው ነው።እንደነዚህ አይነት ሥራዎች በመንግሥት ደረጃ የሚደገፍ ካልሆነ የታሰበለትን ግብ መምታት አይችልም።ለዛሬ በወላይታ ሶዶ የሚገኘውን የጤናዳም የአራዳ ልጆች በጎ አድራጎት ማህበር እንመለከታለን፡፡
ማህበሩ የተመሰረተው በቅርብ ቢሆንም በርካታ ሥራዎችን አከናውኗል።ማህበሩ ከአረጋውያን በተጨማሪ በወላጅ አልባና በጎዳና ልጆች ላይ ሥራዎችን ያከናውናል።የወላይታ ሶዶ ከተማ አስተዳደር ለማህበሩ አስፈላጊ ድጋፍ በማድረግ ላይ መሆኑ ይነገራል።ከማህበሩ መስራችና አባል ወጣት ጥላሁን አቡሼ ጋር ስለ አጠቃላይ የማዕከሉ እንቅስቃሴ ቆይታ አድርገናል።መልካም ንባብ፡፡
የማህበሩ አመሰራረት
ማህበሩ የተመሰረተው መጋቢት ወር 2011 ዓ.ም ላይ ነው።ማህበሩን ለመመስረት ምክንያት የነበረው በወላይታ ሶዶ ከተማ አራዳ የሚባል አካባቢ ያለው የአኗኗር እቅስቃሴ ነው።የአካባቢው ነዋሪ ለየት አድርጎ እንዲታይ ያደረገው ሁሉም የእምነት ተከታዮች ተባብረው የሚኖሩበት በመሆኑ ነው።በባህልም በእምነትም መቻቻል በሰፈነበት ሁኔታ የሚኖሩ ማህበረሰቦች ናቸው።በአካባቢው የታመሙትን በመጠየቅ፣ የታሰሩትን በመጠየቅ፣ እንዲሁም ሌሎች የማህበራዊ ህይወታቸው የተለየ ነው።ቀደም ብለው በአካባቢው የሚኖሩ ሰዎች ይዘውት የነበረው የበጎነትና የመረዳዳት ባህል እየጠፋና እየተረሳ ሲሄድ በአካባቢው የሚገኙ ወጣቶች ይህን ለመታደግ ተሰባሰቡ፡፡
ቀደም ብሎ የነበረውን ማህበራዊ መስተጋብር እየተቀዛቀዘ በመምጣቱ በአካባቢው የሚገኙ ወጣቶች ተሰባስበው የበጎ ሥራዎችን በምን አይነት መንገድ ማስቀጠል ይቻላል የሚለው ላይ ውይይት ተደረገ።የተወሰኑ ወጣቶችን በመምረጥ ወደ ሌሎች የከተማው አካባቢዎች በመሄድ ወጣቶችን ማሰባሰብ ጀመሩ።ከወጣቶቹ ጋር መስማማት በመደረሱ የበጎ አድራጎት ማህበር እንዲመሰረት መሰረት ተጣለ።የበጎ አድራጎት ማህበሩ አመሰራረትና አጠቃላይ ሥራው ምን እንደሚሆን ለወጣቶቹ ግንዛቤ ተሰጠ።ሁሉም ወጣት ሥራውን ለማከናወን ፈቃደኛ በመሆኑ ወደ ሥራው ተገባ።ማህበሩ የተለያዩ የበጎ አድራጎት ሥራዎችን ለማከናወን እቅድ ይዞ ሥራውን የጀመረ ሲሆን ከወላይታ ዞን ህጋዊ ፈቃድ አግኝቶ ከህዳር ወር 2012 ዓ.ም በሶዶ ከተማ በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛል።
ማህበሩ ያከናወናቸው ተግባራት
ማህበሩ ህጋዊ እውቅና አግኝቶ ከተመሰረተ በኋላ አቅም የሌላቸውን አረጋውያንንና የኢኮኖሚ አቅማቸው ዝቅተኛ የሆኑ ማህበረሰቦችን በመደገፍ ነው።በአራዳ አካባቢ ቤት ለቤት በመዞር አቅም የሌላቸውን በመለየት የእለት ጉርስ እንዲሆናቸው ለአረጋውያን፣ አቅም ለሌላቸውና በህመም ቤታቸው ለዋሉ ሰዎች የምግብ ቁሳቁስ ድጋፍ ተደርጓል።ድጋፍ የሚደረግላቸው ሰዎች ተመርጠው የተዘጋጁ በመሆናቸው ከባለሀብትና ከአካባቢው ነዋሪ የተሰበሰበውን ድጋፍ እንዲደርሳቸው ይደረጋል።
በተመሳሳይ በበዓላት ወቅት ለ107 አረጋውያን የበዓል መዋያ የሚሆን ዱቄት፣ ዘይት እንዲሁም የንፅህና መጠበቂያ ቁሳቁሶች ተሰጥቷቸዋል።የድጋፍ ሥራው በተጠናከረ መንገድ መከናወን የጀመረው ጥቅምት ወር 2012 ዓ.ም ላይ ነበር።በወቅቱ በህመም ምክንያት ለረጅም ዓመታት በአልጋ ላይ የነበረችን ሴት መደገፍና ቤት የማደስ ሥራ የማከናወን ሥራ ተጀመረ።ህመምተኛዋ የተለያዩ ረጂ ድርጅቶች መጥተው ያዩዋት ቢሆንም ምንም ድጋፍ ሳያደርጉላት ቀርተዋል።ማህበሩ ግን የዘመመ ቤቷን ለማደስና አስፈላጊ ድጋፍ ለማድረግ ብዙ ሥራዎችን አከናውኗል።ነገር ግን ቤቷ ታድሶ እንደተጠናቀቀ ሴትየዋ በነበረባት ህመም ህይወቷ ሊያልፍ ችሏል።ማህበሩ እውቅናውን ካገኘ በኋላ ዘጠኝ የአቅመ ደካማ ቤቶችን አድሶ ለባለቤቶቹ አስረክቧል።ቤቶቹ የአቅመ ደካማና የአረጋውያን ሲሆኑ ቤቱን ሙሉ ለሙሉ በማፍረስ እንደ አዲስ እንዲገነባ የተደረገ ነው።
የኮሮና ወረርሽኝ ከተከሰተ በኋላ ማህበሩ ቀደም ብሎ በሶዶ ከተማ ለሚገኝ ማረሚያ ቤት ለሚገኙ ታራሚዎች የንፅህና መጠበቂያ ቁሰቁስ እንዲሰጣቸው ተደርጓል።508 ሊትር ላርጎ፣ 31 ካርቶን የእጅና የገላ ሳሙና፣ 1500 ማስክ እንዲሁም አልኮሎች በድጋፍ መልክ ለማረሚያ ቤቱ ተሰጥቷል።ይህ ድጋፍ ለአንድ ሺህ አምስት መቶ ታራሚዎች እንዲሰራጭ ተደርጓል።ለጥምቀት በዓልም በተመሳሳይ ለአቅመ ደካማዎችና ለአረጋውያን እንዲሁም በልመና የሚተዳደሩ ሰዎችን የመመገብ ሥራ ተከናውኗል።በሌላም በኩል ወድቀው የተሰበሩ አንድን አረጋዊ በግል ሆስፒታል የሚታከሙበት ሁኔታ እንዲመቻች ተደርጓል።
ማህበሩ አቅም በሌላቸው ተማሪዎች ላይ ትኩረት ሰጠቶ እየሰራ ሲሆን ማህበሩ የተመሰረተበት ወቅት ላይ ሁለት መቶ የድሀ ድሀ ለሆኑና ለወላጅ አልባ ህፃናት የመማሪያ ቁሰቁስ በማሰባሰብ ተሰጧቸዋል።በተመሳሳይ ቀን ለመቶ አረጋውያን አልባሳትን በማሰፋት እንዲሰጣቸው ተደርጓል።በ2012 ዓ.ም በተመሳሳይ የመማሪያ ቁሳቁስ ድጋፍ የተደረገ ሲሆን በዚህ ድጋፍ ለመቶ አርሷአደር ልጆች የመማሪያ ቁሳቁስ ተለግሷል።ወላጅ ለሌላቸው ልጆችና በጎዳና ላይ የሚገኙ ልጆች ድጋፍ እየተደረገ ነው።የወላይታ ሶዶ የኢትዮ ቴሌኮም ቅርንጫፍ ለሁለት ልጆች የሥራ እድል እንዲፈጠርላቸው ተደርጓል።በኮቪድ ወረርሽኝ ወቅት በትምህርት ቤት ግቢ ውስጥ ሶስት መቶ በጎዳና የሚገኙ ልጆች እንዲጠለሉ ተደርጎ ነበር።ልጆቹን ከከተማ አስተዳደሩ ጋር በመሆን ለሶስት ወራት ክትትል ተደርጎ ውጤታማ ሥራ ተሰርቷል።የምገባ፣ ልብስ ማጠብና እንዲሁም ነብሰጡር የነበረችን ልጅ ስትወልድ ጥሩ እንክብካቤ ተደርጎላታል።
የህብረተሰቡ አቀባበል
ማህበሩ ሥራዎችን በሚያከናውንበት ወቅት የህብረተሰቡ አቀባበል ጥሩ ነበር።ባለሀብቱና የአካባቢው ማህበረሰቦች እገዛ ባያደርጉ ኖሮ ማህበሩ እንቅስቃሴ ማድረግ አይችልም ነበር።በሚያስገርም ሁኔታ የከተማ አስተዳደሩ ድጋፍ የሚያደርግ ቢሆንም አብዛኛው ድጋፍ ከህብረተሰቡ የሚመጣ ነው።ባለሀብቱም በቻለው አቅም ከፍተኛ ድጋፍ እያደረገ ነው።በተለይ አቶ ጳውሎስ የተባሉ ባለሀብት ማህበሩ በሚፈልጋቸው ወቅት ሁሌም ይገኛሉ።የቤት እድሳት በሚደረግበት ወቅት አስፈላጊ ግብዓት በመግዛት እያቀረቡ ይገኛሉ።በቀጣይም ለሚደረጉ እድሳቶችም ድጋፍ ለማድረግ ቃል ገብተዋል።
ሌሎችም ባለሀብቶች በቻሉት አቅም ማህበሩን እየደገፉ የሚገኙ ሲሆን ቲሸርቶችና ባነሮችን በማሳተም ድጋፍ የሚያደርጉ ሰዎች አሉ።የከተማ አስተዳደሩ 2012 ዓ.ም ለገና በዓል ለአረጋውያን የገንዘብ ድጋፍ አድርጓል።የከተማ አስተዳደሩን በከንቲባነት የሚያገለግሉ አመራሮች ለማህበሩ ቅን አሳቢ ናቸው።በ2013 ዓ.ም ደግሞ በልመና ለሚተዳደሩ ሰዎች አስተዳደሩ ከማህበሩ ጋር በመተባበር የማብላት ሥራ አከናውኗል።ከማህበረሰቡ ከሚገኙ ገንቢ አስተያየቶች በተጨማሪ የገንዘብና በጉልበት ከፍተኛ አስተዋፅኦ እያደረገ ይገኛል።
ማህበሩን ያጋጠሙ ችግሮች
ማህበሩ ከተመሰረተ በኋላ ብዙ እንቅፋቶችና ችግሮች አላጋጠሙም።ከሁሉም አካላት ሞራል ከማግኘት ውጪ እንቅፋት የሚባል ነገር አላጋጠመም። ማህበሩ በተንቀሳቀሰባቸው ቦታዎች ከፍተኛ የሆነ የህብረተሰብ ተቀባይነት እያገኘ ይገኛል።ማህበረሰቡም አባል ለመሆን ከፍተኛ ጥያቄ እያቀረበ ይገኛል።ከበጀትና ከፋይናንስ አካባቢ ችግሮች አሉ።ሥራዎችን ለማከናወን አባላትና ባለሀብቱ ሥራዎችን ለማከናወን የገንዘብ ድጋፍ ያደርጋል።የማህበሩ አመራሮች በየወሩ ስብሰባ በማካሄድ እቅድ በማዘጋጀት ወደ ሥራ ይገባል።ከዛም እቅዱን የገንዘብ ድጋፍ ለሚያደርጉ ባለሀብቶች በማስረዳት ወደ ተግባር ይገባል።ማህበሩ በራሱ የሚያመነጨው የፋይናንስ ገቢ የለውም።
የማህበሩ ቀጣይ እቅድ
ማህበሩ የ2013 ዓ.ም እቅድ ክንውኑን በማስገምገም የቀጣይ ዓመት እቅዱን አውጥቶ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል።ማህበሩ የሚንቀሳቀስበት ቦታ በድህነት ስር የሚኖሩ ሰዎች ባሉበት አካባቢ ነው።አብዛኛዎቹ ቋሚ የሆነ መኖሪያ ቤት የሌላቸው ማህበረሰቦች ናቸው።ይህን ችግር ለመፍታት ማህበሩ ትኩረት ሰጥቶ ለመስራት እቅድ አስቀምጧል።ወደፊት ማህበሩ በአንድ ጉዳይ ላይ ብቻ አተኩሮ የሚሰራበት ሁኔታ ለመፍጠር ሀሳብ አለው።ለሰባት ሰዎች መኖሪያ ቤት ለመገንባት ማህበሩ አቅዶ እየተንቀሳቀሰ ሲሆን አባላቱንና ባለሀብቶችን በማሰባሰብ ሥራውን ለማከናወን ታስቧል።
ሌላው እቅድ ደግሞ በየጊዜው የደም ልገሳ የማድረግ ሥራ ማስቀጠል ነው።ማህበሩ አባላትንና በጎ ፈቃደኞችን በማስተባበር የደም ልገሳ እያከናወነ ይገኛል።በቀጣይም ይህን ሥራ ለማከናወን እቅድ ተይዟል።በሌላ በኩል ለ120 አቅመ ደካማዎች የበዓል መዋያ ለመደገፍ እህል የማሰባሰብ ሥራ ተከናውኖ ስርጭት ለማድረግ ዝግጅት ተደርጓል።እንዲሁም 207 ደርዘን ደብተር ለችግረኛ ተማሪዎች ከበዓል በኋላ ለማከፋፈል ዝግጅት ተደርጓል።የኢትዮ ቴሌኮም ወላይታ ቅርንጫፍ ለመቶ ወላጅ አልባ ልጆች መቶ ደርዘን ደብተር ድጋፍ አድርጓል።
በአካባቢው ያለ አስታማሚ አልጋ ላይ የሚገኙ ሰዎችን የማስታመምና የማሳከም እቅድ አለ።የቤት ጥገና ለማከናወንም ማህበሩ ሃሳብ አለው።በጎዳና የሚገኙ ልጆችን በመሰብሰብ ከሰራተኛና ማህበራዊ ቢሮ እንዲሁም ከወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር ልጆቹን ካሉበት ችግር ለማውጣት እቅድ ተቀምጧል።በተጨማሪም በድንገተኛ ሁኔታ ለሚመጡ ድጋፍ ለሚፈልጉ ሰዎች አስፈላጊውን ድጋፍና እገዛ ለማድረግ እቅድ ተቀምጧል።
መርድ ክፍሉ
አዲስ ዘመን ጳጉሜን 5/2013