የኮቪድ 19 ወረርሽኝ በዓለም አቀፍ ደረጃ ሆነ በሀገራችን ከተከሰተበት ጊዜ ጀምሮ እስካሁን መፍትሔ አልተገኘለትም። በጤና ባለሙያዎቹ አንድና አንድ መፍትሔ ተብሎ የተቀመጠው መከላከልና መከላከል ብቻ ነው። በዚህም የወረርሽኙን የስርጭት አድማስ ለመከላከልና ለመቆጣጠር የሚያስችሉ የተለያዩ የመከላከያ ዘዴዎች ተግባራዊ እየተደረጉ ይገኛሉ። ክትባቱም እንዲሁ እየተሰጠ ነው። አሁን ላይ የቫይረሱ አይነት እየተቀያየርና እየተለዋወጠ መምጣቱ ደግሞ ሌላ የራስምታት እየሆነ ነው።
የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ክትባት ተገኝቶ የተስፋ ጭላንጭል እየታየበት ባለበት በዚህ ወቅት ሌላ አደገኛ የሆነ አዲስ የኮቪድ ዝርያ መፈጠሩ ስጋት ሆኗል። ይህ አዲሱ የኮቪድ-19 ዝርያ ማዕበል ከወደ ሀገረ እንግሊዝ መገኘቱ ከተሰማ በኋላ ስርጭቱም የዝርያውን አይነት እየቀያየረ በተለያዩ የዓለማችን ክፍሎች በፍጥነት እየተስፋፋ ይገኛል። ከአፍሪካ ሀገራትም በኬንያ ስርጭቱን አስፋፍቷል። ሀገራችንስ ቢሆን መቼ ቀረላትና ። በአስፈሪ ሁኔታ የቫይረሱ ስርጭት እየተስፋፋ መምጣቱን የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩትና የጤና ሚኒስቴር በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ መግለጻቸው የሚታወስ ነው።
በዚህ ጠይቁልኝ በሚለው አምድ በተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች የሚነሱ ጥያቄዎችን የምናስተናግድበት ነው። በዛሬው አምዳችንም አንድ ጠያቂያችን ያቀረቡትን ጥያቄና ምላሽ ይዘን ቀርበናል። አዲሱ “ዴልታ” የተሰኘው የኮሮና ቫይረስ በሀገራችን እውን ተከስቷል ወይ? ቀድሞ ካለው የኮቪድ 19 ቫይረስስ በምን ይለያል? ለስጋት የሚያደርሰው የተለየ ሁኔታ ምንድነው? ሲሉ በወረርሽኑ ዙሪያ ያለውን አጠቃላይ መረጃ እንድናጋራቸው ጠይቀውናል።
እኛም ይህንን ጥያቄ ያቀረቡልንን ጠያቂያችንን እያመሰገንን ለጥያቄቸው ምላሽ ይሆናል ያልነውን ከጤና ሚኒስቴርና ከህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ያገኘውን መረጃ እንደሚከተለው አጠናክረን ይዘን ቀርበናል።
ባለፈው ሳምንት የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት እንዳስታወቀው በዓለም ላይ ለመስፋፋቱ እንደ ዋና ምክንያት የሚጠቀሰው ኮቪድ-19 ቫይረስ እራሱን ወደ ተለያዩ አዳዲስ የቫይረስ ዓይነቶች መቀየሩ ነው። በተለይም “ዴልታ” የሚባለው የቫይረስ ዓይነት በከፍተኛ ፍጥነት በመሰራጨቱ ይህ የዴልታ ቫይረስ በሀገራችን መኖሩን ለመለየት የተለያዩ ሥራዎች እየተከናወኑ እንደነበር ይታወሳል ። በያዝነው ሳምንት መጀመሪያ ላይ ደግሞ አደገኛው ዴልታ የተሰኘው የኮቪድ ዝርያ በሀገራችን እንደተገኘ ጤና ሚኒስቴርና የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት አስታውቀዋል።
በቅድሚያ ዓለም ላይ ዳግም ስጋትን የደቀነው አደገኛ የሆነ “ዴልታ” የተሰኘው የኮሮና ቫይረስ ዙሪያ ያሉ መረጃዎች ማየት ተገቢ ነው። የአሜሪካ በሽታ መቆጣጠሪያና መከላከያ ማዕከል እንደሚለው ይህ “ዴልታ” የኮቪድ ዝርያ ከሌላው የቫይረስ ዝርያ ሁለት እጥፍ የመስፋፋት አቅም ያለው ሲሆን፤ የሚያስከትለው ህመምም ከፍ ያለ ነው።
አዲሱ የኮቪድ ዝርያ ከተለመደው የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ምልክቶች በተጨማሪ የራስ ምታት፣ አጠቃላይ የሰውነት መድከም፣ ምቾት የማጣት ስሜት ፣ የጡንቻ ህመም፣ የንፍጥ መብዛት፣ የአንጀትና የሆድ እቃ ህመሞች ፣( የማቅለሽለሽ፣ ማስታወክ፣ ተቅማጥ ፣ የሆድ ህመም) የቆዳ ሽፋታ ምልክቶች ሊታዩ ይችላሉ።
አዲሱ የኮቪድ ቫይረስ ዝርያ ቀደም ካለው በገዳይነቱ የከፋ ሲሆን፤ አብዛኛውን ጊዜ የሚተላለፈውም ረዘም ላለ ጊዜ በሚኖር የቅርብ ንክኪ አማካኝነት እንደሆነ መረጃው ያመላክታል ። በቫይረሱ ከተጠቃ ሰው 1 ነጥብ 5 ሜትር ባላነስ ርቀት ከተቀራረቡ፣ በፈሳሽ ጠብታ አማካይነት፣ ቫይረሱ ያለበት ሰው ከተነፈሰ፣ ካወራ ፣ ካስነጠሰ፣ የቫይረሱ ተሸካሚ ጠብታዎች በቅርብ ርቀት ወደ የሚገኘው ሰው በመተንፈሻ አካላት አማካኝነት ሊተላለፉ ይችላሉ። አንድ በሽታው የያዘው ሰው ምልክቶቹ ከመታየታቸው ከሁለት ቀን በፊት እና ከታዩ ከ10 ቀናት በኋላ በሽታውን ሊያስተላልፍ እንደሚችል ተመላክቷል።
በያዘነው ሳምንት መጀመሪያ የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ በኢትዮጵያ “ዴልታ” የተሰኘው የኮሮና ቫይረስ ዝርያ መገኘቱን አረጋግጠዋል። ዶክተር ሊያ እንዳሉት በኢትዮጵያ በወረርሽኑ የሚያዙ ሰዎች ሞትና የፅኑ ህሙማን ቁጥር በጣም እያሻቀበ መሆኑን ገልጸዋል። አዲሱ ዝርያ ሁሉንም የዕድሜ ክልል የሚያጠቃ፣ ለከባድ ህመምና ሞት የሚዳርግ ሲሆን በተለይም ባልተከተቡ ሰዎች ላይ የሚበረታ እንደሆነ ሚኒስትሯ አስረድተዋል።
‹‹ዴልታ›› የተሰኘው ዝርያ በስርጭት ፍጥነት ቀደም ብሎ ከነበረው አልፋ ከተሰኘው ዝርያ በ2 እጥፍ እንደሚበልጥ ነው ።በኢትዮጵያ ባለፈው ሳምንት ብቻ 8 ሺህ 3መቶ ሰዎች በወረርሽኑ ሲያዙ እስካሁን በአገሪቱ 3 መቶ 13 ሺህ ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው እና 1 ሺህ 18 ሰዎች መሞታቸው ተጠቁሟል። ሳምንታዊ በቫይረሱ የመያዝ ምጣኔ ከ1 በመቶ ወደ 20 በመቶ ያሻቀበ ሲሆን፤ የሞት ምጣኔውም አማካይ በቀን 16 ሰዎች መሆኑ ተገልጧል።
የክትባት ተደራሽነት እየሰፋ ነው ያሉት ዶክተር ሊያ፤ በሁሉም የሀገሪቱ ክፍሎች የሚገኙና ዕድሜያቸው ከ18 ዓመት በላይ የሆኑ ዜጎች መከተብ እንደሚችሉ አስታውቀዋል። ህብረተሰቡ ክትባት በየጤና ተቋማቱ በመገኘት እንዲወስዱ፣ የኮቪድ ፕሮቶኮል ማሟላት ከሁሉም ተቋማትና ግለሰቦች የሚጠበቅ መሆኑን አሳስበዋል።
አዲሱ የኮሮናቫይረስ ዝርያ ሙሉውን የበሽታውን መከላከያ ክትባት በወሰዱ ሰዎች ላይ የሚኖረው ጉዳት ዝቅተኛ እንደሆነ ይነገራል። በኢትዮጵያ ውስጥ የወረርሽኙ መከላከያ ክትባት መሰጠት ከጀመረ አንስቶ ከ2ነጥብ5 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ክትባቱን ማግኘታቸው ተጠቁሟል።
የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ምክትል ዳይሬክተር ዶክተር ጌታቸው ቶሌራ በበኩላቸው አዲሱ ዝርያ መኖሩ በቅርብ ቢረጋገጥም ስርጭቱ እንደቆየ የሚያሳዩ ጥናቶች መኖራቸውን ጠቁመዋል። በርካታ አገራት በ3ኛና 4ኛ የኮቪድ ስርጭት ማዕበል እየተመቱ መሆናቸውን ጠቁመው፤ ለዚህም ህብረተሰቡ አስፈላጊውን ጥንቃቄ በማድረግ ወረርሽኙ ከዚህ በላይ እንዳይስፋፋ ማድረግ አለበት ሲሉ አሳስበዋል። ።
የወረርሽኙን ስርጭት ለመግታትና ለመቆጣጠር ከዚህ በፊት ይደረጉ የነበሩ አካላዊ ርቀቶችን መጠበቅ፣ ማስክን ሁልጊዜና በአግባብ ማድረግ፣ የእጅን ንፅህና መጠበቅና ሳንታይዘር መጠቀም ያስፈልጋል። አዲሱ ዴልታ ቫይረስ ከዚህ በላይ እንዳይሰፋፋና የከፋ ጉዳት እንዳያደርስ ሁሉም የራሱን ኃላፊነት መወጣት አለበት።
በአጠቃላይ በአገሪቱ ውስጥ የኮሮና ቫይረስ በሽታ በከፍተኛ ሁኔታ መስፋፋት በመቀጠሉ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ከጥቂት ሳምንታት በፊት በሽታውን ለመከላከል መወሰድ ስላለባቸው የጥንቃቄ እርምጃዎች ያወጣውን መመሪያ በማሻሻል በጥብቅ ተግባራዊ እንዲሆን ማዘዙ ይታወሳል።
ከዚህ በተጨማሪ የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት እንዲያግዝም በሥራ ላይ የነበረው የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የወጣውን መመሪያ ቁጥር 30/2013 ማሻሻያ በማድረግ አዲስ መመሪያ ቁጥር 803/2013 ወጥቷል።ሚኒስትሯም በአዲሱ መመሪያ መሠረት ሁሉም ሚናውን ሊወጣ ይገባዋል ብለዋል።
ወርቅነሽ ደምሰው
አዲስ ዘመን ጳጉሜን 5 ቀን 2013 ዓ. ም