‹‹ዘራፊ›› የሚለው ቃል ትርጉሙ ከአንድ በላይ ነው።በጥበብ በዕውቀታቸው ቅኔውን በሚስጥር የሚዘርፉ፣ በአመራማሪው ስልታቸው አጀብ የሚያሰኙ እልፍ ሊቆች አሉ።እነሱ የቅኔ ዘራፊ ጠቢባን ይባላሉ።እነዚህ ጥበበኞች ዕውቀታቸው፣ በእጅጉ ያስደንቃል።የጥበባቸው ምጥቀትም የአድማጭ ተመልካች አፍን በእጅ ያስጭናል፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ በራስ ወዳድነት ዛር የተጠለፉ፣ ወደር የለሽ ሆዳሞች አገርን በገሀድ የሚዘርፉት ቀማኞች ናቸው።እንዲህ አይነቶቹ የቀን ጅቦች ለልጆቻቸው ጭምር ምህረት አያደርጉም።ዝርፊያና ንጥቂያው ለእነሱ እስከበጀ በሰው ልጆች ክቡር ህይወት እስከመደራደር ይጓዛሉ።
ለዛሬ ስለጠቢባኑ ቅኔ ዘራፊዎች ጉዳይ ማውጋቱ ይቆየን። እነሱ ምንጊዜም የአገርና ወገን ደማቅ ቀለሞች ናቸው።ሁሌም ቢሆን በማንነታቸው ማንነታችንን ያጎላሉ።በታላቁ ሚስጥራቸው የአገርን ጥበብ ይገልጣሉ። እነሆ! በያሉበት ምስጋናችን ይድረሳቸው።
ወደ አገር ዘራፊዎቹ ቀማኞች እንመለስ።እነዚህ የዘመን ጥላዎች ኢትዮጵያ በዘመኗ ካሳለፈችው በተለየ የራሳቸውን ጥቁር አሻራ ለማተም የሚሮጡ ናቸው።እነ አያ ጅቦ በያዙት አገር የማፍረስ ሴራም የመጀመሪያዋ ትልማቸው ታላቂቱ ኢትዮጵያ ናት፡፡
ንገሩን ካሉን ደግሞ አሳምረን እንነግራቸዋለን። እንዴት ካሉም ከእነሱ ማንነትና ጀርባ ስንቆም ታሪካቸው ሁሉ ዝርፊያ መሆኑን እንደርስበታለንና። በ1977 ዓ.ም በሰሜኑ የአገራችን ክፍል በተነሳው ረሃብ በርካቶች እንደቅጠል ረግፈዋል።ጥቂት የማይባሉትም ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለው ለስደት ተዳርገዋል።
ይህ ዘመን ለኢትዮጵያ እጅግ አስከፊውና አይረሴ ነበር።ልጅ የሙት እናቱን ጡት ሲምግ፣ የታየበት፣ ዕልፎች በረሀብ አለንጋ የተገረፉበት ክፉ ዘመን።በወቅቱ የችግሩን መክፋት ያስተዋሉ ለጋሽ አገራት ታዲያ ለመፍትሄው የእርዳታ እጃቸውን ዘረጉ ።እህልና የምግብ አቅርቦት እንዲደርስም ፈጠኑ።አንዳንድ ልበ ቀና ወገኖች ደግሞ ከያሉበት ሆነው ህይወት ለማትረፍ ተረባረቡ።
ወገኖቼ! የነግፍ አይፈሬ ድርጊት ግን ከነዚህ ሁሉ ተለየ። የድርጊታቸው ገጽታም ማንነትን መሰከረ። ጨካኙ የትህነግ ሰራዊት ረሀብና ችግሩ አላሰጋውም።‹‹እሞትልሃለሁ ›› ሲል የሸነገለው የትግራይ ህዝብ ሰቆቃ አላሳዘነውም። አጋጣሚውን እንደ ድልድይ ተጠቅሞ በእርዳታ የሚገባውን የዕለት ጉርስ ለመንጠቅ ፈጠነ።
አስገራሚው እውነት እንዲህ መሆኑ አልነበረም።ሽፍታ ቡድኑ ከረሀብተኛ ወገኑ ጉሮሮ የፈለቀቀውን እህል እያጋዘ በገንዘብ ቸበቸበው።ያገኘውን ገቢም ለጦር መሳሪያ ግዢ አዋለው።ቢገባውማ ‹‹እሞትልሃለሁ›› ያለውን ወገኑንን በቁም መቅበር የጀመረው የዛኔ ነበር፡፡
አሸባሪው ህወሓት ሆይ! ከፈለግህ አሁንም ልክህን እንንገርህ።ዘንድሮ ራስህ ጭረህ ባስነሳኸው የጦርነት እሳት እኮ የትግራይን ህዝብ ዳግም እየፈጀህ፣ እያስፈጀኸው ነው። ሲሻህ በጦርነት፣ ሲልህ ደግሞ በረሀብ የምታሳቀየው ህዝብ፣ ዛሬም ምክንያትና ሰበብህ ሆኗል።ለፍቅሩ፣ ለክብሩ ሞትንለት የምትለው ህዝብ እኮ ልጆቹን በእናንተው እየተዘረፈ ነው።ማንነቱን፣ ህልውናውን እየተነጠቀም፣ በችግር መቆራመዱን ቀጥሏል። መቼም ውሸትና ዝርፊያ መለያችሁ ሆኗል።አሁንም እየገደላችሁት ያለውን ህዝብ ‹‹እንሞትልሃለን›› በሉት አሉ።
አንዳንዴ ‹‹ግርግር ለሌባ ያመቻል›› እንዲሉ አሸባሪው ቡድን ስልጣኑን ለዝርፊያ ሲጠቀምበት ኖሯል።ሃያ ሰባት ዓመታት በተንፈላሰሰበት መንበሩም ኢትዮጵያን ታክል ታላቅ አገር በቁሟ ሲዘርፍ፣ ሲሞሸልቅ ቆይቷል።ሰፊውን የኢትዮጵያ ህዝብ በድህነት አዘቅት በመጣልም ጥቅሙን ሲያሳድድ ነበር።
እናንተዬ! ጉዳዩ ሁሉ የእነ አልጠግብ ባይ ነገር ሆኖ ጉዳቸውን አፈላው እንጂ ጥቂት ቢቆዩ እኮ ዓይናችን ተዓምር ባየ ነበር።ደግነቱ ‹‹ማር ሲበዛ እሬት›› የሆነባቸው የቁርጥ ቀን ልጆች ከተተከሉበት ስር ነቃቅለው፤ ከተስፋፉበት ወንበር ፈንግለው ለታላቁ አገራዊ ለውጥ አበቁን።ከቀን ጅቦቹ ንክሻ፣ ከአገር ዘረፋው ወጥመድም አተረፉን፡፡
እንዲህ መሆኑ ወተቷ እንደተደፋባት ድመት ያደርጋቸው እነ አጅሬም ዛሬ ጥፍራቸውን አሹለው መቧጠጡን ተያይዘውታል።ከዓመታት በፊት በታንኩም፣ በባንኩም ሲያዙበት ነበር። የዛሬን አያድርገውና የአሸባሪው የስልጣን ጥመኞች በኢትዮጵያ ሀብትና ንብረት እንዳሻቸው ፈንጭተዋል።በዶላሩ፣ በገንዘቡ፣ በወርቅና አልማዙም ተንበሽብሸዋል፡፡
ከራሳቸው አልፎ ለልጅ ልጆቻቸው በተረፈው የህዝብ ንብረት እስከዛሬ ያለ አንዳች ይሉኝታ ቀልደ ዋል። ይህን ሲፈጽሙ ብዙኃኑ የኢትዮጵያ ህዝብ የበይ ተመልካች ሆኖ ነበር።ጠግበው ከተረፋቸው፣ በልተው ከሚደፉት፣ ትራፊ እንኳን ‹‹እነሆ!›› ሊሉት፣ ሊያቃመሱት አልፈቀዱም። የዚህችን ድንቅ አገር አካል እንደ ወለላ ማር ሲልሱ፣ እንደጥንቅሽ አገዳ ሲመጡ ‹‹በቃን፣ ጠገብን›› አላውቁትም።
ይገርማል እኮ እናንተዬ! የቀን ጅቦቹ ዛሬም በአገር ዝርፊያ ልክፍት እንደተጠመዱ ናቸው። ቁንጣን እስኪይዛቸው የጋጧትን አገር ፣ አሁንም ከነአጥንት ጉልጥምቷ ሊምሯት አይሹም።ልክ እንደቀድሞው ከጉያዋ ገብተው ሊቦጠቡጧት፣ ሊቦጫጭቋት ሲሹና ሲጎመጁ ከርመዋል።‹‹ሲያምርህ ይቅር›› አለ ሰውዬው ።አዎ! ሲያምራችሁ ይቅር፡፡
እውነት ነው። አገርን መብላት ለለመደው አምሮታቸው ያልተመቻቸውን የኢትዮጵያ ህዝብ ከስልጣን ፊጥ ብለው ለመዝርፍ፣ ሀገርን ለማፍረስ የጀመሩት የህልም ሩጫ አልተሳካም።ዛሬ የመሮጫው ትራክ እንደትናንቱ አይደለም።የአልጋ በአልጋው መንገድ ደልዳላ ምቹ አልሆነም።
አሁን ላይ የዚህ መንገድ ጉዞ ‹‹በደል በቃን፣ አንገሸገሸን ›› ባሉ ዜጎች ህብር ታሪኩን ቀይሯል።ቅያሱ በእሾህ ታጥሯል።መግቢያ መውጫው ጠፍቶ ዝርፊያ፣ አገር ማፍረስ፣ ይሉት ቋንቋ ከመነሻው ተቀጭቷል።እንግዲህ ምን ትሆኑ? የሀብት ምንጫችሁ ደረቀ፣ የክፋት እጃችሁ ተቆረጠ። ምን ይበጃችሁ? ምንም፡፡
ትናንት ከጥቅማችሁን የተጋሩ የእናንተ ጀሌዎች ዛሬ በየአደባባዩ ይንከባለሉ ይዘዋል።እነሱ አመድ እንዳየ አህያ የሚያንደባልላቸውን እውነት አሳምረው ያውቁታል።ዛሬ ለሚገኙበት አውሮፓና አሜሪካ ያበቃችኋቸው እናንተው ነበራችሁ።እናም ውሻ በበላበት ቢጮህና ቢያላዝን ዓለምን፣ ሊደንቀው አይገባም።አዎ ! እነ እንበር ተንከባላዮች እስቲ በአመድ በአፈሩ ከብለል፣ ደብለል በሉበት።ካሻችሁም ለጨዋታችሁ ማድመቂያ፣ ለድራማችሁ ማሞቂያ ከክበሯችሁ ጀርባ በሊጥና ዱቄት ብቅ በሉ፡፡
እስቲ መላው ዓለም ስለናንተ ጉድ ይወቅ፣ ስትንከባለሉ ከሊጡ እየቀባችሁ፣ ከዱቄቱ እየበተናችሁ፣ ከአሻቦ ፣ ከሽሮ እየቃማችሁ፤ ይሁን።ከጠላው ድፍድፍና እንኩሮ ፣ ከምጣዱ ቂጣና ድርቆሽ ጎረስ ፣ ዋጥ፣ ሰልቀጥ ማድረጉንም አትርሱ፡፡
የእኛ ሰብአዊ መብት ጠያቂዎች ከሌላውም ማጀት ማንጎዳጎዱን እንዳትረሱ።ከመሶቡ እንጀራ፣ ከጓዳው ጠላና አረቄ አለላችሁ።ከጉያችሁ ሸሸግ፣ ደበቅ አድርጉና ጥቂት ተጎንጩለት።የሰው የተባለ እኮ ይጣፍጣል አይዟችሁ! በደንብ ሳቡት፣ ጠጡለት።ፉት…ሳብ.. ፉት.. የዛኔ መገበሪያ እንደበላ ጠንቀኛ በየአደባባዩ እያስለፈለፈ ያንደባልላችኋል።የሰው ሀቅን የበላው ጉሮሮአችሁ እየቀባጠረ፣ ቀኝ ግራ ያስረግጣችኋል፡፡
ይህን ብታደርጉ ጫካ ያሉ አባቶቻችሁን አደራ ትወጣላችሁ። መላው ዓለም የዝርፊያ ታሪካችሁን፣ ያውቃል።ከዘመዶቻችሁ የወረሳችሁትን የአገር ማፍረስ ሴራ ተመልካቹም ይረዳል።አይዟችሁ፣ በርቱ ማንነታችሁን አስመስከሩ።ኡ.ኡ.ኡ.ኡ. እያላችሁ እሪታውን አቅልጡት፤ ጨኸቱን አጡፉት፣ እሪ፣ በሉ ።እሪ .. ኡ .ኡ. ኡ .በሉ ። ተንከባለሉ ፤ ከብለለለለል…
አትሰሙንም እንጂ ለእናንተ የሚበጅ ጥሩ ምክር ነበረን።ባትፈቅዱም ግን እንምከራችሁ፣ ‹‹ከልብ ካዘኑ ዕንባ አይገድም›› እንዲሉ ከእናንተ የሚጠበቀው ችሮታ ይህ ብቻ አልነበረም።ትናንት ከሀገር ከወገን ዘርፈው በሰው አገር ምድር ላንደላቀቋችሁ ባለውለታዎች መንከባለል ብቻውን በቂ አይሆንም፡፡
ከጫካው ዘልቃችሁ፣ ከጉድጓዱ ገብታችሁ፣ ከጎናቸው ልትቆሙ፣ ይገባ ነበር።ጀግንነት እኮ መንደባለል ብቻ አይደለም።ቁርጠኝነትና ውለታ መመለስ በመሳደብና፣ በመፎከር አይገለጽም።ጀግኖች ነን ካላችሁ ማንነታችሁን አስመስክሩ፣ ክንዳችሁን፣ አንድነታችሁን አሳዩ።አዎ! በጦር ሜዳው መሰለፍ፣ መውደቅ መነሳት ይገባችኋል።ምነዋ ሰርቆ ያበላ እጅ፣ አኝኮ ያጎረሰ ባለውለታ ይዘነጋል እንዴ? የአሸባሪው ህወሓት ጀንበር ሳታዘቀዝቅ፣ የኑዛዜው መዝገብ ሳይዘጋ ፍጠኑ እንጂ።ፈጠን!
ለመሆኑ ትናንት በህዳሴው ግድብ ሰበብ የድሀዋ መቀነት ሲፈታ፣ የምስኪኑ ጓዳ ሲበረበር የት ነበራችሁ? ከሁሉም ዜጋ ላብና ወዝ ጠፍ ያለው አንጡራ ሀብት በጠራራ ፀሀይ ሲዘረፍስ አልሰማችሁም እንዴ? ለነገሩ ምን ታደርጉ ዛሬ በአደባባይ የምትጮሁላቸው ሌቦች ትናንት ከዘረፉት ሁሉ ያቃምሷችሁ ነበር ፡፡
የእናንተው ጉዶች እኮ ስልጣን በያዙ ማግስት ድንጋይና አሸዋ የጫኑ ህሊና ቢሶች ናቸው ። ለመላው ህዝብ የሚጠቀምነውን እየለዩም ወደራሳቸው ጓዳ ሲያስገቡ ኖረዋል።አንዱ በደከመበት ሌላው እንዲኖርበት የሚያስችል መርህንም ሲተግብሩት ነበር።‹‹ድመት መንኩሳ ዓመሏን አትረሳ›› ይሉት ማንነታቸው አሁን በገሀድ ወጥቶ እየመሰከረባቸው ነው።
እነሆ! ዛሬ አሸባሪው ቡድን የቀድመውን የዘራፊነት መልኩን ማደስ መጠገኑን ይዟል።አገር በማፍረሰ፣ ህዝብ በማናቆር ታሪኩ የሰነደውን የዶሴ አቧራ እፍ ብሎም ሌላውን ምዕራፍ ጀምሯል።የታሪኩ ጫፍና መድረሻ ሲመረመርም እንደተለመደው የሌብነት ህይወቱን ይመዛል፡፡
አሸባሪው የህወሓት ቡድን ዘንድሮ በሀገር ህልውና ላይ በከፈተው ጦርነት ትልም አድርጎት የተነሳው ጅምሩን የዝርፊያ ታሪክ ማስቀጠል ሆኗል። ቡድኑ ለስልጣኑ ህልውና የሚጠቀምበትን የትግራይ ህዝብ ሲያታልለው ኖሯል።ሁሌም በሚነዛው የሀሰት ትርክትም ታሪክን በማንጋደድ የሚያህለው አልተገኘም፡፡
አሸባሪው ቡድን በየደረሰበት ዝርፊያ መፈጸም መለያው ነው።አንዳንዴ በዚህ ቡድን ቁንጮዎች አገር ስትመራ መቆየቷን ማሰብ በእጅጉ ያስገርማል።እነዚህ ጉግ ማንጉጎች ከራሳቸው በላይ የሚያፈቅሩት ፍጥረት እንዳልነበረ ማሰቡም በእጅጉ ያሳፍራል።ይህ ዘራፊ ቡድን ስልጣን በተቀማ ማግስት መሸረብ የጀመረው አገር ስለማፍረስና ህዝብ ስለመበተን ውጥን ነበር።የዚህ ሴራ መሰረት የተዋቀረውም በዝርፊያው ስልትና ዘዴ ላይ ነው፡፡
እንደው መቼም ወዳጆቼ የዚህ ሽፍታ የዝርፊያ ታሪክ ‹‹ ሌባ ለዓመሉ›› ከሚባልለት በላይ ነው።ይህኛው ሌባ እኮ! ለአምሮት ለፍላጎቱ በእጁ የገባውን የሚሸሽግ የሚደብቅ ብቻ ነው።ወራሪው ህውሀት ግን በየደረሰበት የሚፈጽማቸው ድርጊቶች የተስፋ መቁረጡን ጥግ ከማሳየት የዘለለ ሆኗል፡፡
ሌባው ቡድን ከመኖሪያ ቤት ዘልቆ ሊጥና ዱቄት ከመስረቅ ባሻገር። ሆስፒታል ከተኙ ህሙማን ሰው ሰራሽ እግርና ግሉኮስን ይነጥቃል።በዚህ አጀብ ሲባልለት ከትምህርት ቤት ደርሶ ደብተርና እርሳስ ይሰርቃል።ጀሌዎቹ ስርዓት ይሉትን አያውቁትም።እንደ ተማረ ሰው ከቢሮ ዘልቀው ቁስ ያማርጣሉ። ኮምፒውተሩን፣ ስልኩን፣ ወንበር፣ ጠረጴዛውን፣ ይጭናሉ። በርና መስኮቱን ገንጥለው ቤት ንብረቱን ያቀጥላሉ።
የአሸባሪው ቡድን የሆዳምነት ጥግ ወደር ኖሮት አያውቅም።የትግራይ ህዝብን ለጦርነት እየማገደ፣ ልጆቹን በጭካኔ እያዘመተ ለባዶው ከተማ ያሰበለት ይመስላል። የአርሶ አደሩን ከብቶች የቻለውን ያህል አርዶ ይበላል።‹‹በቃኝ›› ብሎ ሲያስብ ለእንስሳቱ የጥይት ናዳ ያዛል። በሬዎች፣ ላሞችና በጎች፣ ጥጃዎች፤ ኮርማና እምቦሳዎች በከባድ መሳሪያ ሀሩር ይቀጣሉ።ይነዳሉ።
አንዳንዴ ደግሞ ዘራፊው ቡድን ለቤት ለትዳሩ ያስብ ይመስል ከብቶች እየነዳ ይወስዳል፣ የቤት ዕቃ ያግዛል፣ ከሽሮ በርበሬው እየዛቀ፣ ከሊጥ ከዱቄቱ ይቋጥራል።ለሰበበኛው የትግራይ ህዝብ ምን እንደሚል ባይታወቅም እንደ ጎበዝ አዳኝ ግዳዩን ይዞ ሲገባ ‹‹ጉሮ ወሸባዬ›› እንዲባልለት ‹‹እንደው ዘራፌዋ›› እንዲቀኝለት ይሻል።ወይ አለመታደል ‹‹ወግ ነው አሉ›› ሲዳሩ ማልቀስ ።እውነትም ወግ ወጉን ይዞታልና !
እንደው ወዳጆቼ ታላቂቱን አገርን አፍርሶ የራስን ቤት መስራት፣ መገንባት ይቻላል እንዴ? አገርን ወገንን ዘርፎ መንደርና ቀዬን ማሳመርስ ? ህዝብን አፈናቅሎ፣ አገር ሸጦ ሸቅጦ የራሱን ቤተሰብ ማቆም የሚሻው ህወሓት ግን ይህን አሳፋሪ ተግባር እየፈጸመው ይገኛል።የትግል ታሪክ ጀመርኩ ከሚልበት ዓመታቶች ጀምሮ እስከዛሬዋ ዕለት በዝርፊያ የኖረው ይህ ቡድን ዛሬም አልጠግብ ባይነቱን ማረጋገጥ ይዟል፡፡
ዘንድሮ ባደሰው የማንነት ምግባሩ በየደረሰበት የእጅ ዓመሉን እያሳየን ነው።በየገባበት የዘረፈውን መጫን የማያቅተው ጫንቃውም ሁሌም ለሸክም ዝግጁ መሆኑን አስመስክሯል። ዛሬ ህወሓት ይሉት ዘራፊ የሚምረው አንዳች ነገር እንደማ ይኖር ያሳ የን ይዟል፡፡
የዛሬን አያድርገውና እንደአሁኑ አከርካሪው ሳይመታ ህልምና ትልሙ ሰፊ ነበር።አዲስ አበባ መግባት፣ ቤተመንግስቱን መያዘ፣ ሰማይ ጠቀስ ህንጻዎቹን ማስመለስ፣ ባንኩን ታንኩን መውረስ የቅርብ ጊዜያት ዕቅዶቹ በማድረግ ቃዥቷል።
ሽብርተኛው ቡድን ዛሬም ከህልም ቅዠቱ በወጉ አልነቃም።አሁንም የሚያባንነው አገርን የመዝረፍ፣ ዕቅዱ አብሮት እንዳለ ነግቶበታል።አሁን ለነጋበት ጅብ የሚራራ፣ የሚያዝን ዜጋ የለም።ጅቡ ዓይኑን ሲገልጥ ትውልድ እንደሚያጠፋ፣ አገር እንደሚያፈርስ ሁሉም ያውቃል።አያ ጅቦ ገዳዮችህ ሊቀብሩህ በዙሪያህ ቆመዋል።የጅብ ወዳጅ የለምና እጅህን ስጥ ።ጉድጓድህን አሰናዳ፡፡
ከአትጠገብ
አዲስ ዘመን ጳጉሜን 4/2013