ዛሬ የጀግንነት ቀን ነው። ስለጀግንነት ሲነሳ ደግሞ እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ይነሳል። ኢትዮጵያና ጀግንነት የረጅም ጊዜ ልምምድ እንዳላቸውም ታሪክ ይመሰክራል። አገራችንም በየዘመኑ አዳዲስ ጀግኖችን ስታፈራ ቆይታለች። ሆኖም ጀግና የሚባለው ማነው የሚል ጥያቄ በአእምሮአችን ሲከሰት ብዙውን ጊዜ ከጦር ሜዳ የጀብድ ውሎ ጋር ብቻ እናያይዘዋለን። ነገር ግን ጀግና በየዘርፉ የሚፈጠር የአገር መውደድ ስሜት ውጤት ነው። ጀግና ማለት በተሰማራበት መስክ በታማኝነት አገሩንና ህዝቡን የሚያገለግል ሰው ነው።
አገርን ከወራሪ ከጠላት መከላከል የቻለ ለአገሩ ለህዝቡ አልያም ለብዙሀኑ ህይወቱን የሰጠ ሁሉ ጀግና ነው። በግብርናው ዘርፍ ተሰማርቶ አገርና ህዝብ በምርት እንዲትረፈረፍ ያደረገ። በመንግሥት የሥራ መስክ ህብረተሰቡን በቅንነትና በታማኝነት ያገለገለ እርሱ ጀግና ነው፤ በንግድ ሥራው የተጣለበትን የመንግሥት ግብር በአግባቡ የሚከፍል እርሱም ጀግና ነው፤ በሲቪል ሰርቪስ ውስጥ ተሰማርቶ ህዝብን በቅንነት የሚያገለግል እርሱ ጀግና ነው፤ ብቻ በጠቅላላው ሁሉም በተሰማራበት መስክ አገርና ህዝብን በቅንነት በታማኝነት የሚያገለግል ከሆነ ከእርሱ በላይ ጀግና ከየትም አይመጣም።
በአንድ ወቅት ተጽፎ ያነበብኩትና በጣም ልቤን የነካኝ ብሎም አንዳችን ለአንዳችን መኖርን የሚያሳይ ጽሁፍ ላካፍላችሁ፤ ርዕሱ፤ “ጀግንነት መግደል ማለት ብቻ አይደለም! ስለ ወገን መሞትም ጭምር ነው!!!” ይላል፤ ዲሳ አነቱ ዴማ /Dhiisa anatu demma/ ደግሞ ታሪኩ ነው።ቀጥተኛ ትርጉሙ ተው እኔ እሄዳለሁ ማለት ነው። ጉዳዩ እንዲህ ነው።
ቅልጥ ያለ ጦርነት እየተካሄደ ነው። የሞት ሽረት ፍልሚያ። ከፊት ለፊት ሰማይ ጠቀስ ተራሮች የጥይት እሳት ይንተከተክባቸዋል። ቦንብ ይነድባቸዋል። መድፍና ታንክ እንደ መብረቅ ያጓራባቸዋል። ከወዲያም ከወዲህም የጥይት እሳት ይወረወራል። ተራራዎቹን ለማስለቀቅ ነው መራር ፍልሚያ እየተካሄደ ያለው ። ከዚያም ከዚህም በፅናት መተጋተጉ ቀጥሏል። ከሰዓታት በኋላ ለአንዱ ጓድ መሪ ቀጭን ትዕዛዝ ተሰጠው።
ወለም ዘለም የለም። ወታደር ነህ። ሙት ከተባልክ ትሞታለህ። አልሞትም ብሎ ነገር የለም። አድርግ ማለት አድርግ ነው። ጓድ መሪውም የደረሰውን ትዕዛዝ መፈፀም አለበት። “ጓድ” ማለት ዘጠኝ ወታደሮችን ይይዛል። በስሩ ያሉትን ስምንቱን ወታደሮች ያስተባብራል፤ ይመራል፤ ያዛል። ለጓድ መሪው የተሰጠው ትዕዛዝ (ግዳጅ) እጅግ ፈታኝ ነው። በሰማይ ጠቀሶቹ ተራሮች መሀል አንድ ቀጭን ሸጥ አለች። ያቺ ሸጥ በፈንጂ ታጥራለች። “በፈንጂው ላይ ተራምደህ እለፍ” የሚል ትዕዛዝ ነው የደረሰው። ይህ ትዕዛዝ መፈፀም አለበት። ግድ ነው።
ጓዶቹን አያቸው። እንደ እናት ልጅ የሚተያዩ ናቸው፤ ብዙ ችግር አብረው አሳልፈዋል። ከሰዓታት በፊት አብረው ተመግበው ነበር። አንሶላ ቢጤ ትከሻቸው ላይ ጣል አድርገው ጎን ለጎን ጋደም ብለው አውግተውም ነበር። ከሰዓታት በፊት የአንድ ኮዳ ውሃ አብረው ጠጥተዋል። አሁን ግን … ከእነዚህ እንደወንድም ከሚያያቸው ስምንት ጓዶቹ መሃል አንዱን መርጦ ወደ መስዋዕትነት የመላክ ግዴታ ወደቀበት። በእርግጥ አለቃቸው ነው። አንዱን “ሂድ በፈንጂው ላይ ተራመድ” ማለት ይችላል። ግን ማንን ሂድ ይበል? ጨነቀው። የበላይ ትዕዛዝ ደግሞ መፈፀም አለበት።
ለደቂቃዎች ያህል አሰበ። አሰበና ……እንዲህ አለ፤ Dhiisa anatu demma (ዲሳ አነቱ ዴማ) “ተውት እኔ እሄዳለሁ” ማለት ነው ትርጉሙ። እናም ሄደ። ፈንጂው ላይ ተንከባለለ። ተሰዋ። እሱ በጠረገው መንገድ ላይ ጓዶቹ ሾልከው ወደ ጠላት ወረዳ ገቡ። ተራራውን አልፈው ከጀርባ ተኩስ ከፈቱ። ጠላት ተፍረከረከ። የሚፈለገው ከፍታ ነጥብ (ተራራ) ተያዘ። ድል ተገኘ። ይህ እንግዲህ ለእናት አገር አልፎም ለጓዶች የተሰጠ ትልቅ ፍቅርና ክብር ነው። አዎ ጀግና ማለት ከራሱ በፊት ሌሎችን የሚያስቀድም፤ እኔ እሞታለሁ እንጂ ሙቱልኝ የማይል ለጥቅምና ለግል ፍላጎት እጁን የማይሰጥ ነው።
ጀግንነት መግደል ማለት አይደለም፤ ጀግንነት መሞትም ጭምር ነው። የሌላው ሕይወት ይቀጥል ዘንድ መስዋዕት መሆን ነው። ዛሬም አገራችን ለመግደል ብቻ ሳይሆን ለመሞትም የተዘጋጁ እውነተኛ ጀግኖችን የምትሻበት ወቅት ነው።በእርግጥ ኢትዮጵያ ሲባል ጀግና ፤ ጀግንነት ሲነሳ ኢትዮጵያውያንን የማይጠራ አለ ብዬ አላስብም።
ጀግንነት የእኛነታችን መገለጫ ከመሆኑ ጋርም ተያይዞ ዘንድሮ ጳጉሜን 4 ቀን 2013 ዓም የጀግንነት ቀን ተብሎ እንዲከበር ሁሉም በተሰማራበት መስክ ጀግና ሆኖ እንዲውል ብሎም መጪውን አዲስ ዓመት በጀግንነት ተቀብሎ አገርና ህዝቡን በሁሉም መስክ አርኪ ሥራ ሰርቶ እንዲያሻግር ቃል ኪዳን የሚገባበትም ቀን ነው።
እኛም ጀግንነትና ኢትዮጵያዊ ምንና ምን ናቸው? ስንል በ1972 ዓ.ም በሰራዊቱ ውስጥ የመጨረሻ ከፍተኛ የሆነውን የህብረተሰባዊት ኢትዮጵያ የጀግና ሜዳይ (ወደር የሌለው ጀግንነት ) ተሸላሚ እንዲሁም የጦር ሜዳ የቁስለኛ ሜዳይና የጦር ሜዳ የዘማች አርማ ተሸላሚ ብርጋዴል ጀነራል ተስፋዬ ሀብተማርያም ጋር ቆይታን አድርገናል።
አዲስ ዘመን ፦ ጀግንነት ሲባል በእርስዎ እይታ ምንድን ነው? ኢትዮጵያውንና ጀግን ነትንስ እንዴት ይገልጹታል?
ብ/ጀነራል ተስፋዬ ፦ ጀግንነት ለኢትዮጵያውያን ከአባት ከእናቶቻችን ሲወርድ ሲዋረድ የመጣ የእኛነታችን መግለጫ መሳሪያችን ነው።በመሆኑም ኢትዮጵያውያን በተሰማራንበትና በዋልንበት ሁሉ ብዙ ጀግንነቶችን የምንፈጽም በዚህ ደግሞ ዓለም ሁሉ የሚያውቀንና በአንድ ቃል የሚመሰክርልን ህዝቦች ነን።
ኢትዮጵያ በግንባር ቀደምትነት ከምትታወቅበት የጦር ሜዳ ጀግንነት ባሻገር በተለያዩ ሙያዎች ላይ ተሰማርተው አገርና ህዝብን በማገልገል ብሎም የአገራቸውን ስም ከፍ ብሎ እንዲጠራ በማድረግ ብዙ ጀግንነቶችን የሚፈጽሙ ዜጎችም ያሏት ናት።በዚህም የገበሬ፣ የተማሪ፣ የነጋዴ፣ የቢሮ ሰራተኛው ብቻ ምን አለፋሽ በተሰማራበት መስክ ሁሉ መልካም ሥራን በመስራት ጀግንነትን የሚያሳይ ትውልድ ያለን ሰዎች ነን። በዚህም በጣም ልንኮራ ይገባናል።
በውትድርናው ዓለም ያለውና በሌሎች ዘርፎች ላይ የሚመዘገበው ጀግንነት ትንሽ ለየት ይላል። ምናልባት በውትድርናው ዓለም ላይ ጀግንነትን የሚፈጽሙ ሰዎች ጠንካራ የአገር ፍቅር ስሜት ያላቸው፣ የአገራቸው ሉአላዊነት ሲደፈር የሚቆጡ፣ አራስ ነብር የሚሆኑ፣ ኢትዮጵያዊ ሰላምና ደህንነትን ለማምጣትም የአካል፣ የደም እንዲሁም የህይወት መስዋዕትነትን የሚከፍሉ ናቸው።
ጀግንነትን እፈጽማለሁ ብሎ ሒሳብ ሰርቶ መነሳት አይቻልም ፤ ነገር ግን ሁኔታዎች ሲፈቅዱ እድል ሲገኝ በፍጹም ቆራጥነትና የአገር ፍቅር ስሜት መነሳት ከተቻለ ጀግንነትን መፈጸም ይቻላል ።አንድ ወጣት ለአገሬ ጀግና እሆናለሁ ብሎ ካሰበ በመጀመሪያ የጸና የአገር ፍቅር ስሜት ሊኖረው ይገባል። የግሌ የሚለውን ነገር ሁሉ መተው ለአገሬ አይገቡ እገባለሁ ብሎ በራሱ መወሰን ከዚህ በመቀጠል ደግሞ የሚሰጡ ወታደራዊ ስልጠናዎችን በአግባቡና ስነ ስርዓቱን በተከተለ መንገድ በተገቢው ሁኔታ በወታደራዊ ሳይንስ ጽንሰ ሀሳብ አእምሮውን ማጎልበት ይገባዋል።ቀጥሎም የአካል ብቃት በስነ ስርዓት መታነጽ የአላማ ጽናት የሙያ ፍቅርም በራስ መተማመን ጀግና ለመሆን የሚያስፈልጉ ነገሮች ናቸው።እነዚህን ያሟላ ሰው ግዴታዎች በሚሰጡት ጊዜ በቁርጠኝነትና በፍጹም ተነሳሽነት ኃላፊነቱን መወጣት ግዴታውን መፈጸም ብሎም ጀግና መሆን ይችላል ።
ወታደር ጀግንነት የሚፈጽመው በአላማ ጽናት ለአንድነት ለነጻነት እንዲሁም ለዳር ድንበር መከበር ሰላምን ደህንነትን ለመፍጠር በሚደረጉ ትግሎች ነው። ኢትዮጵያውያን ስንፈጠር በጣም ትዕግስተኞች። ሁሌም ሰላምን የምንሻና ለአንድነት ለአብሮነት ከፍተኛ የሆነ ትኩረትን የምንሰጥ ነን፤ ነገር ግን መብታችንን፣ ነጻነታችንን እናሳጣችሁ
ብለው የሚመጡ የውጭም የውስጥም ኃይሎች ሲኖሩ ደግሞ ወታደር ይሁን ሲቪል ሁሉም እንደ ነብር የምንቆጣ ብሎም ጠላትን ድባቅ ለመምታት ጾታ እድሜ ሃይማኖት ሳንጠይቅ በአገራችን ጉዳይ ላይ አንደራደርም ብለን በደማችን ታሪክ ለመጻፍ የምንተም ድንቅ ህዝቦች ነን።በጠቅላላው ጀግንነት በእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ደም ውስጥ ያለ ነገር ነው።
አዲስ ዘመን ፦ እርስዎ በዘመንዎ በሰሩት ሥራና ባስመዘገቡት ጀግንነት በሰራዊቱ ውስጥ የመጨረሻ ከፍተኛ የሆነውን የህብረተሰባዊት ኢትዮጵያ የጀግና ሜዳይ (ወደር የሌለው ጀግንነት ) ተሸላሚ ኖትና ፤ በዚህ ደረጃ ጀግንነት እውቅና ሲሰጠው ያለው ስሜት ምን ይመስላል ?
ብ/ጀነራል ተስፋዬ ፦ ማንም ለአገሩ ለመዋደቅ ግንባር ሲሄድ መጀመሪያ የሚያስበው ነገር ቢኖር አገሬን እንዴት አድርጌ ነው ከተጋረጠባት ችግር የማወጣት? የሚለውን ነው እንጂ እንዴት አድርጌ ጀግንነት ፈጽሜ እሾማለሁ ወይም እሸለማለሁ ብሎ አይነሳም።ነገር ግን ግዴታዎችን በመወጣት ሂደት ውስጥ ሆኖ ጀግና መሆን ጀግንነት መፈጸም ይቻላል።ይሆናልም ።የሆነውን ይኸው ነው።
ጦር ሜዳ ሄዶ ከጠላት ጋር መፋለም መቁሰል መድማት የሙያ ግዴታ ነው። አንዳንድ ሁኔታዎች ደግሞ በጣም ፈታኝና አስገዳጅ የሚሆኑበት ጊዜ ይፈጠራል። ያን ጊዜ ደግሞ ከቡድን ጓደኞችሽ ጋር በመሆን የምትወስጃቸው እርምጃዎች የምት ሄጅባቸው ሂደቶች ምናልባት ወደ ጀግንነቱ እንዲሁም ጀግና ወደመባል ያደርሳሉ።
በበኩሌ ጀግና እባላለሁ ብዬ የሰራሁት ሥራ አልነበረም ፤ ነገር ግን አገሬን ከጠላት ወረራ ነጻ ለማውጣት ህዝቤ በሰላም ወጥቶ እንዲገባ ሰርቶ እንዲበላ ልጆቹን እንዲያሳድግ እንዲያስተምር ለወግ ማዕረግ እንዲያደርስ አቅሜና ሙያዬ የፈቀደውን ሁሉ አቅሜ በፈቀደው ልክ በጦር ሜዳ ላይ ስወጣ ነበር።የሙያ ግዴታዬን በመወጣት ሂደት ውስጥ ለሰራኋቸው ተጋድሎዎች ግን መንግሥትና በወቅቱ ሰራዊቱን ይመሩ የነበሩ ሰዎች ሙያው ከሚፈልገው በላይ በጣም ከባድና አስቸጋሪ ሁኔታዎችን በማለፍ አገርህን አኩርተሀልና ይህ ሜዳይ ይገባሀል ብለው ሰጡኝ። እኔም በዚህ ከፍተኛ የሆነ ደስታና ኩራት ይሰማኛል።
አዲስ ዘመን፦ ስለ ኢትዮጵያ ሲነሳ ጀግንነት አብሮ ይነሳል፤ በተለይም የውጭ ወራሪ ኃይልን ባለመቀበልና መክቶ በመመለስ በኩል ጠንካራ የጀግንነት ሞራልም ያለን ነንና እንደው ይህንን ሁኔታ እንዴት ያዩታል?
ብ/ጀነራል ተስፋዬ፦ ኢትዮጵያውያን በተለያዩ ጊዜያት ከውስጥም ከውጪም በሚነሱባት ጠላቶች ምክንያት በርካታ ጦርነቶችን አድርጋለች፤ እናም ጦርነቶች በኢትዮጵያ ላይ ሲቃጡ ህዝቡ ተለምኖ ወይንም ተገዶ አይደለም ወደጦር ሜዳ የሚሄደው፤ ይልቁንም አገሬ ስትወረር ቁጭ ብዬ አላይም በማለት በራሱ ፍላጎትና ተነሳሽነት ነው ብዙ ጦርነቶች ላይ በነቂስ በመውጣት ተካፍሎ ብዙ አኩሪ ታሪኮችን የፈጸመው፤ እየፈጸመም ያለው።ለምሳሌ ሶማሌ ድሬዳዋና ሀረርን በወረረች ጊዜ ወጣቱም አዛውንቱም ሴቱም ወንዱም ሆ ብሎ ነው የወጣው። መኪና የማይደርስበት ቦታ ላይ እንኳን እናቶች ውሃ በጀሪካን እየተሸከሙ ያጠጡ ። ቁስለኛውን ነጠላቸውን ቀደው እያሰሩ ህክምና ያደርጉ ነበር፤ ጥይትና የእጅ ቦምብ በነጠላቸው ተሸክመው እያመጡ ለሰራዊቱ አድለዋል ፤ይህንን ሲያደርጉ የነበሩት ግን በማንም ቀስቃሽነትና ገፋፊነት ሳይሆን በራሳቸው ፍላጎትና ተነሳሽነት እንዲሁም በአገራቸው ፍቅር በደማቸው ውስጥ ባለው አትንኩኝ ባይነትና የጀግንነት ስሜት ነው።ከላይ እንደገለጽኩት ጀግንነት በኢትዮጵያውያን ደም ውስጥ ያለ ነገር ነው።
አዲስ ዘመን ፦ በጀግንነት መካከል ደግሞ አልፎ አልፎ ባንዳዎች አይጠፉም፤ በተለይም አሁን አገራችንን በዚህ መልኩ ለማፍረስ የሚ ጥሩ አሉ ፤ ለእነዚህ አካላት ምን መልዕክት ያስተ ላልፋሉ? የህዝቡ ምላሽስ ምን ሊሆን ይገባል?
ብ/ጀነራል ተስፋዬ፦ አሁን አገራችንን የገጠማት ችግርና ከኋላችን ያረዱን አይነት ባንዳዎች እኔንጃ በዓለም ላይም ያሉ አይመስለኝም፤ አብሮ የበላውን የጠጣውን በሥራ ሲደክም ውሎ ከአጠገቡ ጎኑን ያሳረፈ ወንድሙን በዚህ መልኩ በጭካኔ ያረደ የገደለ እንዲገደል ሁኔታዎችን ያመቻቸ ባንዳ በዓለም ታሪክ ታይቶ አይታወቅም።ወታደር ግብሩ ሞት ነው ፤ አምኖበት ለእናት አገሩ ሊሰዋ የተዘጋጀ አካል ከመሆኑ አንጻር መሞታቸው ምንም ላይሆን ይችላል፤ ነገር ግን አብሮት በኖረ ወንድሜ በሚለው አካል ላይ በዚህ መልኩ ክህደት ሲደርስበት ማየት እጅግ ያማል፤ እነዚህ ከሃዲዎችም ምን ዓይነት ቋንቋ ሊገልጻቸው እንደሚችል በእውነቱ አላውቅም።
ኢትዮጵያዊ ሁሉ እኮ በጣም ሲበዛ ሰብዓዊነት ያለው ሃይማኖተኛ ጨዋ እንኳን በዚህ መልኩ ሰው ሊያርድ ይቅርና ለወሬ ለሰማው የሚዘገነን ነው፤ ግን እንደዚህ ዓይነት አረመኔዎች ከየት እንደመጡ በእውነት አይታወቅም ።የጭካኔያቸውንም ልክ ቋንቋ እንኳን ሊገልጸው ይከብዳል።
በመሆኑም ህዝቡ አሁንም እንደምናየው ከምን ጊዜውም በላይ አንድ ሆኖ ለአገር ለድንበሩ እየተመመ የወገኑን ደም ለመወጣት በቁጭት እየተሰለፈ ነው። በእውነት ይህ ጀግንነትና አልበገር ባይነት ተጠናክሮ መቀጠል ያለበት ነው።
አዲስ ዘመን፦ አሁን አገራችን በአሸባሪው ህወሓት የተሰነዘረባትን ጥቃት ለመመከት ወጣቱ እንዲሁም መላው ህዝብ ያሳየው ተነሳሽነት በእርስዎ ላይ ምን ፈጠረብዎት?
ብ/ጀነራል ተስፋዬ፦ በኢትዮጵያዊነቴ ትልቅ ኩራት እንዲሰማኝ አድርጎኛል ።እኔ ወጣቱን እገም ተው የነበረው ምንም የአገር ፍቅር እንደሌለው ። አገር ቢወረር ስሜት እንደማይሰጠው ነበር፤ ነገር ግን ይህ ግምቴ ፍጹም የተሳሳተ መሆኑን አሁን አይቻለሁ።
አሁን ላይ ወጣቱ እውነተኛ ኢትዮጵያዊ ጀግንነትም በደሙ ውስጥ ያለ መሆኑን አስመስክሯል።ኢትዮጵያን በዚህ መልኩ የሚገዳደራት ኃይል ሲመጣ ያለማንም ቀስቃሽነት ማንም ሳይለምነው ሆ ብሎ በመውጣት የአገር ፍቅሩን በሚገባ አሳይቷል፤ ለዚህም ምስጋና ይገባዋል።በዚህም እኔ ብቻ ሳልሆን መላው የአገራችን ህዝብ ትልቅ ኩራት ሊሰማውና ተስፋ ሊሰንቅ ይገባል።
አዲስ ዘመን፦ ወጣቱ እያሳየ ያለውን የአገር ፍቅር ስሜት እንዲሁም በዋለበት አውድ ሁሉ እያስመዘገበ ያለውን የጀግንነት ተግባር በልማቱም እንዲደግመው ከማን ምን ይጠበቃል ይላሉ?
ብ/ጀነራል ተስፋዬ፦ አሁን ላይ ትልቅ የአገራችን እድገት ጎታች ሆኖ ፈተና ውስጥ የጨመረን ነገር በባንዳዎች የእናት ጡት ነካሽ በሆኑ ከሀዲዎች የተከፈተብን ጦርነት ነው።ከዚህ ጦርነት በመቀጠል ድህነት የአገራችን መገለጫ ሆኖ አብሮን እየኖረ ነውና ይህንን የህልውናችንን ጠላት ለመዋጋት ወጣቱ ከጦር ሜዳው ተሳትፎ ባልተናነሰ መልኩ መነሳትና አንድነት መፍጠር ይኖርበታል።
ድህነትን ቁጭ ብለን የምንላቀቀው ነገር አይደለም። በመሆኑም ከድህነት ለማምለጥ ከፈለግን ሁሉም ህዝብ ወንድ፣ ሴት፣ ህጻን፣ አዋቂ፣ ሳይል በህብረት በአንድነት ድህነትን በማጥፋት ሥራው ላይ መሳተፍ አለበት፤ ያን ጊዜ ደግሞ ከችግር እንወጣለን።እኛ ያልናችሁን ካላደረጋችሁ እንዲህ ትሆናላችሁ እንዲያ ይፈጠራል እያሉ የሚያስፈራሩንን አሜሪካና ምዕራባውያኑንም ማሳፈር የምንችለው ከድህነት ስንወጣ በመሆኑ ሰርተን አገራት የደረሱበት ደረጃ ለመድረስ ሁሉም ሰው በአቅሙ በችሎታው መስራት አለበት።ይህንን ካደረግን ከድህነት እንወጣለን።
አሁን ያለንበት መጥፎ ነገር በቅርብ ጊዜ ውስጥ ይጠናቀቃል። ከዚያ በኋላ ግን ወጣቱ በጦርነቱ ላይ ለመሳተፍ ሆ ብሎ እንደወጣ ሁሉ በድህነቱም ላይ የነቃ ተሳትፎን ማድረግ አለበት፤ ደግሞም ያደርገዋል።
አዲስ ዘመን ፦ ዘንድሮ ጳጉሜን 4 ቀን የጀግንነት ቀን ተብሎ ተሰይሟል፤ ይህ የህዝብን ሞራላዊ እሴቶች ከመገንባትም ሆነ ጀግኖችን ከማበረታታት አንጻር ምን ፋይዳ ይኖረዋል ይላሉ?
ብ/ጀነራል ተስፋዬ ፦ አንድ ጥሩ ሥራ የሰራ ሰው በተለይም ደግሞ አገሩ በምትፈልገው ሰዓት ተሰልፎ ደምቶ ቆስሎ ህይወቱን ገብሮ የጀግንነት ሥራን ሲያከናውን በዚህ መልኩ እንዲታሰብ ማድረግ በጣም ትልቅ ሀሳብ ነው። ሌሎች ላይም የሚፈጥረው መነሳሳት በቀላሉ የሚታይ አይሆንም።
አሁን የተጀመረው ጀግኖችን የማበረታታት እንዲሁም በሌሎች ዘርፎች ላይ የተሰማሩ የህብረተሰብ ክፍሎችን የማበረታታትና እውቅና የመስጠት አካሄድ የሚያስመሰግን ነው።አሁን እንኳን ይህ ወራሪ ኃይል በፈጠረው ችግር ጦር ሜዳ ተሰልፈው በጣም ብዙ ጀግንነትን የፈጸሙ ሰዎች አሉና እነሱም በዚህ ቀን እውቅና እንዲያገኙ ቢሆን መልካም ነው።
እስከ ዛሬ ጀግኖች ሲሞቱ ብቻ በመቃብራቸው ላይ የህይወት ታሪካቸውን ከማንበብ ወጥተን በዚህ መልኩ ቀን ተሰይሞላቸው እንዲታሰቡ መደረጉ ትልቅ ሥራ ከመሆኑም በላይ ሌሎችንም በሚገባ የሚያነሳሳ ነው።
አዲስ ዘመን፦ በመጨረሻ እርስዎ ማስተላለፍ የሚፈልጉት መልዕክት ካለ ?
ብ/ጀነራል ተስፋዬ፦ አገራችን እየደማች ነው፤ በመሆኑም እድሜው አቅሙ የጤና ሁኔታ የሚፈቅድለት ሁሉ ለዚህ ትግል በሚችለው ሁሉ መሰለፍ አለበት ።አቅሙ የማይፈቅድለትና እድሜው የደረሰ ደግሞ ባለበት ሆኖ የወገንን ጦር በማበረታታት በውስጥ ያሉ ኃይሎችን በመመከት አገራችንን በሁለት እግሯ እንድትቆም ማድረግ ያስፈልጋል።
አዲስ ዘመን ፦ ለነበረን ቆይታ በጣም አመሰግ ናለሁ።
ብ/ጀነራል ተስፋዬ፦ እኔም አመሰግናለሁ
እፀገነት አክሊሉ
አዲስ ዘመን ጳጉሜን 4/2013