ሻምበል ተክላይ ገ/ሕይወት በ1981 ዓ.ም የአገር መከላከያ ሰራዊትን የተቀላቀሉ ናቸው፤ በደረሰባቸው የአካል ጉዳት ሳቢያ ከመከላከያ ሰራዊት በ2005 ዓ.ም በቦርድ እስከተሰናበቱበት ድረስ ለ24 ዓመታት የአገራቸውን ዳር ድንበር በማስከበር ህዝባቸውን አገልግለዋል። እርሳቸውም ከመከላከያ ሰራዊት በቦርድ ከተሰናበቱ በኋላ በደረሰባቸው የአካል ጉዳት እንዳሻቸው ወጥተው ወረደው፤ ተሯሩጠው ሰርተው የዕለት ጉርሳቸውን ለመሸፈንና የቤት ኪራይ ከፍለው ለማደር ተስኗቸው እንደነበር ይናገራሉ።
ይህንንም ተከትሎ ከፍተኛ የመኖሪያ ቤት ችግር እንዳለባቸውና ከመከላከያ ሰራዊት በአካል ጉዳት በቦርድ መሰናበታቸውን የሚያሳዩ መረጃዎችን አደራጅተው ቤት እንዲሰጣቸው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቤቶችና ኮንስትራክሽን ቢሮን የድጋፍ ደብዳቤ እንዲጽፍላቸው በማመልከቻ በጠየቁት መሰረት፤ ቢሮው ለአራዳ ክፍለ ከተማ የመኖሪያ ቤት በመስጠት ትብብር እንዲያደርግላቸው በጻፈው ደብዳቤ መሰረት በክፍለ ከተማው ወረዳ 10 ቀበሌ 09 የቤት ቁጥር 740 የሆነውን ሶስት ክፍል የቀበሌ ቤት በ2007 ዓ.ም መንግስት እንደሰጣቸው ይናገራሉ።
ነገር ግን አሁን ላይ መንግስት በሰጣቸው ቤት በሰላም እንዳይኖሩ ሁከት እየተፈጠረባቸው ከመሆኑ ባሻገር በመንግስት ቤቶች የኪራይ ውል በፍ/ብ/ህ/ቁ 16781731 በተዋዋሉት መሰረት የአከራይ እና ተከራይ ውል ወረዳው አላድስም በሚል መንግስት የሰጣቸውን ቤት በህገወጥ መንገድ ለማፍረስና ለሌሎች አሳልፎ ለመስጠት እየሰራ ነውና ህዝብና መንግስት ይፍረደኝ ሲሉ ለዝግጅት ክፍላችን አቤቱታ አቅርበዋል።
ሻምበል ተክላይ ያቀረቡትን ዝርዝር አቤቱታ፣ የግራቀኙን ምላሽ እና ዶክመንት አገላብጠን ያገኘነውን መረጃ እንደሚከተለው በዛሬው የፍረዱኝ አምዳችን የበኩላችሁን ፍርድ ትሰጡ ዘንድ ይዘን ቀርበናል።
የቅሬታ አቅራቢው ዝርዝር አቤቱታ
ቅሬታ አቅራቢው እንደሚሉት፤ በመንግስት ቤቶች የኪራይ ውል መሰረት መንግስት የሰጣቸውን ሶስት ክፍል ቤት በወር 24 ብር እየከፈሉ የአከራይና ተከራይ ውል ከ2007 እስከ 2012 ዓ.ም ላለፉት አምስት ዓመታት በየዓመቱ ሲያድሱ ነበር።
ሻምበል ተክላይ ቤቱን ከመረከባቸው በፊት ቤቱን ይዘው ሲያስተዳድሩት የነበሩት ግለሰብ አንደኛው ክፍል ላይ እንጀራ እየጋገሩ ይሸጡበት ስለነበር የቤቱ ጣሪያና ግድግዳ በማርጀቱ ከሶስቱ ክፍሎች አንዱ እድሳት የሚያስፈልገው ስለሆነ ግድግዳው ባለበት ሁኔታ በተመሳሳይ ቁሳቁስ ለማደስ፤ የኮርኒስ ስራ ለማከናወንና ወለሉን ሊሾ ለማድረግ የወረዳውን ግንባታ ፈቃድና ቁጥጥር ጽህፈት ቤት በደብዳቤ በጠየቁት መሰረት በ28/07/2012 ዓ.ም ቤቱን እንዲያድሱ የእድሳት ፈቃድ ተሰጥቷቸዋል።
ነገር ግን ህጋዊ የግንባታ ፈቃድ አውጥተው ቤቱን ለማደስ ወደ ስራ ሲገቡ ውል ላይ ሶስት ክፍል ቤት ተብለው ቢዋዋሉም የሚያድሱት አንድ ክፍል ቤት ክፍት ቦታና መተላለፊያ ኮሊደር ስለሆነና ቤት ስላላይደለ እድሳት ማድረግ አትችሉም ብሎ የወረዳው ቤቶች ልማት ጽህፈት ቤት እንዳገዳቸው ሻምበል ተክላይ ጠቁመው፤ የወረዳው ቤቶች ልማት ጽህፈት ቤት ኃላፊ “አንድ ክፍሉን ቤት አፍርሱ” በሚል ዛቻና ማስፈራሪያ እንዳደረሰባቸው ይናገራሉ።
እርሳቸውም ቤቱን ከመረከባቸው በፊት ቤቱን ይዘው ሲያስተዳድሩት የነበሩት ግለሰብ አፍርሱ የተባሉትን አንድ ክፍል ቤት በ1989 ዓ.ም ሰርተው የጋራ መኖሪያ ቤት እድለኝ ሆነው ቤቱን እስከለቀቁበት እስከ 2007 ዓ.ም ድረስ ሲገለገሉበት ከመኖሩ ባሻገር እርሳቸውም ቤቱን በ2007 ዓ.ም ከተሰጡበት ጊዜ ጀምሮ ላለፉት አምስት ዓመታት እየተገለገሉበት ያለን ህጋዊ ቤት “በምን አግባብ ነው? የማፈርሰው እስካሁን ስገለገልበት አይደል የነበረው። አሁን ምን አዲስ ነገር ተፈጥሮ ነው?” ብለው ይጠይቃሉ ።
ቅሬታ አቅራቢው ይሄንን ምላሽ ሲሰጡ የወረዳው ቤቶች ልማት ጽህፈት ቤት ኃላፊ “አፍርሱ ብያለሁ አፍርሱ” የሚል ዛቻና ማስፈራሪያ ሲያደረስባቸው፤ “አፍርስ ካላችሁኝ የማፈርስበትን ምክንያት በደብዳቤ ጻፉና ስጡኝ” ብለው ሲጠይቁ በቃል ዛቻና ማስፈራሪያ ከመስጠት ባለፈ በደብዳቤ ምክንያቱ ምን እንደሆነ ለመስጠት ፈቃደኛ አለመሆናቸውን ይናገራሉ።
ሻምበሉ የወረዳው ቤቶች ልማት ጽህፈት ቤት ኃላፊ መንግስት በሰጣቸው ቤት በሰላም እንዳይኖሩ አንድ ክፍሉን ቤት አፈርሰዋለሁ እያለ ዛቻና ማስፈራሪያ ከማድረሱ ባለፈ የወረዳውን የደንብ ማስከበር ጽህፈት ቤት ግብረኃይል አዋቅሮ ቤቱን እንዲያፈርሱ ይዞ መምጣቱን ጠቁመው፤ የወረዳው ቤቶች ልማት ጽህፈት ቤት ኃላፊ መንግስት የሰጣቸውን ስልጣን ያለአግባብ በመጠቀም የአረጀውን ቆርቆሮ ነቃቅሎ እና የበሰበሰውን የግድግዳውን እንጨት መነቃቅሮ በመጣል ቤቱን ትርምስምስ ካደረገ በኋላ የቀረውን ቆርቆሮና እንጨት ነቃቅሉና ወረዳ ውሰዱ ብሎ ለደንብ አስከባሪዎች ትዕዛዝ መስጠቱን ተናግረዋል።
ነገር ግን የወረዳው ደንብ ማስከበር ጽህፈት ቤት ኃላፊ በወቅቱ በቦታው ተግኝተው ቤቱን በአካል ስላዩት “ህገወጥ ግንባታና አዲስ ግንባታ ተቆጣጠሩ ነው እንጂ የተባልነው፤ ይሄንን ነባር ቤት አናፈርስም” በሚል ቤቱን ሳያፈርሱት ግብረኃይላቸውን ሰብስበው ትተው መሄዳቸውን ያወሳሉ።
ቅሬታ አቅራቢው የወረዳው ደንብ ማስከበር ጽህፈት ቤት ይሄንን ነባር ቤት አናፈርስም ብሎ ትቶ ከሄደ በኋላ በተሰጣቸው ህጋዊ የግንባታ ፈቃድ መሰረት ቤቱን ለማደስ ወደ ስራ ሲገቡ፤ የወረዳው ቤቶች ልማት ጽህፈት ቤት ኃላፊ መጥተው “ውሉ ላይ በስህተት ነው ሶስት ክፍል ቤት የተባለው። ስለዚህ የሚታደሰው ቤት ክፍት ቦታና መተላለፊያ ኮሊደር እንጂ ቤት ስላላደለ እድሳት ማድረግ አትችሉም” በማለት ከመከልከሉ በላይ አንድ ክፍል ቤቱን በ17/09/2012 ዓ.ም አሽጎ እንዳትነኩ ብሎ መሄዱን ተናግረዋል።
የወረዳው ቤቶች ልማት ጽህፈት ቤት የእርሳቸውን ህጋዊ መብት ከመጣሱ ባሻገር ቤቱ ህጋዊ ነው አድሳቹህ መገልገል ትችላላቹህ ብሎ የወረዳው ግንባታ ፈቃድና ቁጥጥር ጽህፈት ቤት የሰጠውን ህጋዊ ፈቃድ ጭምር በመሻር የጽህፈት ቤቱን ስልጣን ጭምር እንደተጋፋ ቅሬታ አቅራቢው ገልጸው፤ በፍታብሄር ህግ ቁጥር 16781731 የአከራይና ተከራይ ውል ፈጽመው መንግስት ከሰጣቸው ሶስት ክፍል ቤት አንዱን ክፍል ያላአግባብ ፈርሶብኛል፣ ታሽጎብኛል እንዲሁም ህጋዊ የእድሳት ግንባታ ፈቃድ አውጥተው እንዳያድሱ መከልከላቸውን ለወረዳው የህዝብ ቅሬታና አቤቱታ ማስተናገጃ ጽህፈት ቤት እንዲሁም ለወረዳው ዋና ስራ አስፈጻሚ በደብዳቤ ማሳወቃቸውን ይናገራሉ።
ነገር ግን ቅሬታቸውን በዚህ መልኩ ለወረዳው ቢያቀርቡም ቅሬታው ተቀባይነት የለውም ከሚል የቃል ምላሽ ውጭ በጽሁፍ መልስ የሚሰጥ አካል ወረዳው ላይ ባለማግኘታቸው ለክፍለ ከተማው አቤት ማለታቸውን የሚናገሩት ሻምበል ተክላይ፤ የክፍለ ከተማው የህዝብ ቅሬታና አቤቱታ ማስተናገጃ ጽህፈት ቤት በደብዳቤ ቁጥር አ/ክ/ህ/ሰ/አስ/ማ/ይ/ል/0427 በቀን 12/10/12 ዓ.ም በሰጠው የጽሁፍ ምላሽ “ቤቱ ባለሶስት ክፍል ተብሎ በኪራይ ውሉ ላይ ቢጠቀስም ከኃላፊዎች እንደተገለጸውና በተጨባጭ ቦታው ላይ ወርደን እንዳየነው የቤቱ ሶስተኛ ክፍል ተብሎ የተጠቀሰው የቤት ቁጥር 740 እና የቤት ቁጥሮች 741 እና 742 መካከል ያለ አንድ ሜትር ቦታ (ኮሪደር) ነው ፤ በጂ አይ ኤስ ላይም ቦታው የቤት ቁጥር 740 መሆኑን የማያሳይ በመሆኑ ቅሬታው አግባብነት የሌለውና ግንባታውም ህገወጥ ነው” የሚል ምላሽ መስጠቱን ይናገራሉ።
በፍርድ ቤት ያደረጉት ክርክር እና የፍርድ ቤት ውሳኔው
አቤቱታቸውን በመልካም አስተዳደር በኩል ታይቶላቸው እንዲፈታ ያደረጉት ጥረት አልሳካላቸው ሲል ሰኔ 17 ቀን 2012 ዓ.ም በፍ/መ/ቁ 21662 በአዲስ አበባ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ችሎት የወረዳውን ቤቶች ልማት ጽህፈት ቤት መክሰሳቸውን የሚናገሩት ቅሬታ አቅራቢው፤ የአከራይና የተከራይ ውል በህግ አግባብ የፈጸሙ መሆኑን በመጥቀስ፤ “ሶስተኛው ክፍል ቤት በ1989 ዓ.ም ተሰርቶ ላለፉት 23 ዓመታት አገልግሎት ሲሰጥ የቆየ እንደሆነና በመንግስት ቤቶች መመሪያ ቁጥር 5/2011 ዓ.ም አንቀፅ 88/5 መሰረት ህጋዊ ስለሆኑ፤ ተከሳሽ እየፈጠረ ያለውን ሁከት እንዲያስወግድና ለክሱ መነሻ በሆነው ቤት የተደረገው እሽግ እንዲነሳ እንዲሁም በተፈቀደላቸው የግንባታ ፈቃድ መሰረት እድሳቱን እንዲያከናውን” በሚል ክስ መስርተዋል።
ፍርድ ቤቱ “ተከሳሽ በከሳሽ የፈጠረው የሁከት ተግባር አለ? ወይስ የለም? ከሳሽ የተፈቀደላቸው የእድሳት ፈቃድ ተከልክለው ቤቱ ላይ የተደረገው እሸጋ የህግ አግባብነት ያለው ተግባር ነው? ወይስ አይደለም?” የሚሉትን ጭብጥ ይዞ መዝገቡን ከመረመረ በኋላ በ18/01/2013 ዓ.ም በዋለው ችሎት፤ “ከሳሽ ክርክሩ የቀረበበት ቤት በህጋዊ መንገድ ውል በመዋዋል የተሰጣቸው በመሆኑና በህጋዊ መንገድ በተሰጣቸው የግንባታ ፈቃድ መሰረት እንዳይገነቡ ተከሳሽ እየፈጠረ ያለው ሁከት በመሆኑ፤ ሁከቱ በፍ/ህግ/ቁ 1149/3/ መሰረት ይወገድ ብሎ” ወስኗል። እንዲሁም ተከሳሽ ክርክሩ የቀረበበት ቤት ወይም ክፍሉ ላይ ያደረገው እሸጋ ያለአግባብ ስለሆነ ሊነሳ ይገባል። ከሳሽ በተሰጣቸው ግንባታ ፈቃድ ግንባታ ማከናወን ይችላሉ ተብሎ መወሰኑን ገልጸዋል። የፍርድ ቤት ውሳኔውንም ለዝግጅት ክፍላችን አቅርበዋል።
እርሳቸውም ፍርድ ቤቱ በወሰነው ውሳኔ መሰረት በፍታብሄር ሥነ ስርዓት ህግ ቁጥር 378 መሰረት ፍርድ እንዲፈጸምላቸው መስከረም 26 ቀን 2013 ዓ.ም ፍርድ ቤቱን መጠየቃቸውን ጠቁመው፤ በፍታብሄር ሥነ ስርዓት ህግ ቁጥር 371 መሠረት የአፈጻጸም መዝገብ ተከፍቶላቸው የፍርድ ባለዕዳ ተጠርቶ ፍርድ ቤት ቀርቦ “በውሳኔው መሰረት በቤቱ ላይ የፈጠረው የሁከት ተግባር እንዲወገድና በቤቱ ላይ ያደረገውን እሽግ እንዲያነሳ ትዕዛዝ ይሰጥልኝ” ሲሉ ለፍርድ ቤቱ ማመልከታቸውን ተናግረዋል።
“የፍርድ ባለዕዳ የፈጠሩትን የሁከት ተግባር እማያስወግዱና በቤቱ ላይ ያደረጉትን እሽግ የማያነሱ ከሆነ ምክንያቱን በጽሁፍ ይዘው እንዲቀርቡ” በሚል ፍርድ ቤቱ የሰጣቸውን መጥሪያ ለፍርድ ባለዕዳ መስጠታቸውን ቅሬታ አቅራቢው ገልጸው፤ ፍርድ ቤቱ “የፍርድ ባለዕዳን መልሱን በጽሁፍ እንዲያሳውቅ” ቢልም ባለማሳወቁ ለሁለተኛ ጊዜ መልስ ይዘው የማይቀርቡ ከሆነ በፖሊስ ተይዘው እንደሚቀርቡ አውቀው በሁለተኛው ቀጠሮ እንዲቀርቡ በሚል ማስጠንቀቂያ ፍርድ ቤቱ ሰጠ። ነገር ግን የወረዳው ቤቶች ልማት ጽህፈት ቤት ለሁለተኛ ጊዜ በተደረገለት ጥሪም ባለመቅረቡ ሶስተኛ ላይ በፖሊስ ተይዘው እንዲቀርቡ መደረጉን ይናገራሉ።
የወረዳው የቤቶች ልማት ጽህፈት ቤት ኃላፊ በፖሊስ ተገደው ፍርድ ቤት ቀርበው ለምንድን ነው እሽጉን የማታነሱት ሲባሉ፤ “አጎራባቾች ቅር ስለሚሰኙ አናነሳም” የሚል ምላሽ ለፍርድ ቤቱ ሲሰጡ “አንተ እንደአንድ የመንግስት አካል ሁሉንም የማህበረሰብ ክፍል በእኩል አይን ነው እንጂ ማየት ያለብህ ለሌሎች ግለሰቦች ማን ጠበቃ አቆመህ። አጎራባቾች ፍርድ ቤቱ በሰጠው ውሳኔ ቅር ከተሰኙ የራሳቸውን ፋይል ከፍተው መከራከር ይችላሉ። ስለዚህ ፍርድ ቤቱ በወሰነው መሰረት የፍርድ ቤቱን ውሳኔ ትፈጽማለህ? ወይስ አትፈጽምም?” በሚል ሲጠየቅ ይግባኝ እንላለን የሚል መልስ ሰጠ። የፍርድ አፈጻጸም ፍርድ ቤቱም “መጀመሪያ የፍርድ ቤቱን ውሳኔ ፈጽመህ ነው እንጂ ዝም ብለህ ይግባኝ ማለት አትችልም። አሻፈረኝ የምትል ከሆነ በዚሁ ወደ እስር ቤት ትሄዳለህ” ሲባል እሺ የፍርድ ቤቱን ውሳኔ እፈጽማለሁ ማለቱን ተናግረዋል።
ፍርድ ቤቱም በአምስት ቀን ውስጥ እሽጉን አንስተህ ማረጋገጫ ደብዳቤ ለፍርድ ባለመብት ትሰጣለህ የሚል ትዕዛዝ ሰጥቶ ስለነበረ፤ በአምስተኛው ቀን የወረዳው የቤቶች ልማት ጽህፈት ቤት ኃላፊ እሽጉን መጥቶ ማንሳቱን የሚናገሩት ቅሬታ አቅራቢው፤ እሽጉን መጥቶ ሲያነሳ “እሽጉን ስለማንሳትህ የማረጋገጫ ደብዳቤው የት አለ” በሚል ሲጠይቁ ነገ ቢሮ መጥተህ ውሰድ ብሏቸው በነገታው ቢሮ ደብዳቤውን ሊቀበሉ ከሰዎች ጋር በሄዱበት ወቅት “ለአዲስ አበባ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ለአራዳ ምደብ ችሎት” በሚል የፍርድ ቤቱን ውሳኔ ተግባራዊ ስለማድረጋቸው የሚገልጽ ደብዳቤ አዘጋጅቶ ይሄው ደብዳቤው ውሰድ እንዳላቸው ያወሳሉ።
እሽጉ መነሳት አለመነሳቱን “ማረጋገጫ የምትሰጠኝ ለኔ እንጂ ለፍርድ ቤቱ አይደለም መልስ የምትሰጠው። ፍርድ ቤቱማ ውሳኔ ስጥቶ ፋይል ዘግቷል። አርስቱን አስተካክሉት” ብለው ሲጠይቁ ቢሮ ውስጥ እንዳሉ የወረዳው የቤቶች ልማት ጽህፈት ቤት ኃላፊ “ደብዳቤውን አምጣ ብሎ ነጥቆ እርሳቸው ጋር ድብድብ ውስጥ መግባቱንና የወረዳውን ፖሊስ ጠርቶ ህገወጥ ሰው ነው” ብሎ ችግር ሊፈጥርባቸው እንደነበር ተናግረዋል።
በአጠቃላይ ፍርድ ቤቱ በወሰነው ውሳኔ መሰረት የታሸገው ቤት እሽጉ ተነስቶ በተሰጣቸው ህጋዊ የግንባታ ፈቃድ መሰረት ጭቅጭቅ የተነሳበትን አንድ ክፍል ቤት አድሰው እየተገለገሉበት እንደሚገኙ ሻምበሉ ገልጸው፤ የ2013 ዓ.ም የአከራይ ተከራይ ውል ለማሳደስ የወረዳውን ቤቶች ልማት ጽህፈት ቤት ሲጠይቁ “ባለሁለት ክፍል ቤት ብለን ነው እንጂ፤ ባለሶስት ክፍል ቤት ብለን አናዋውልም” ብለዋቸው እስካሁን ድረስ የ2013 ዓ.ም ውላቸውን ሳያድሱ በጀት ዓመቱ መገባደዱን አመልክተዋል።
እርሳቸውም ጽህፈት ቤቱ ይህንን ምላሽ ሲሰጣቸው “ፍርድ ቤት የተዋዋሉት ሶስት ክፍል ቤት መሆኑን አረጋግጦ፤ ቤት አይደለም መተላለፊያ ኮሊደር ነው ያላችሁት ቤት ፍርድ ቤቱ ቤቱን አጽድቆት ሁከት ይወገድላቸው፣ እሽጉም ይነሳላቸው እንዲሁም በተሰጣቸው ህጋዊ የግንባታ ፈቃድ መሰረት ግንባታ እንዳከናውን ተወስኖልኛል” የሚል ጥያቄ ለወረዳው ሲያነሱ፤ የወረዳው ቤቶች ልማት ጽህፈት ቤት “ፍርድ ቤት የወሰነውን ውሳኔ አሻፈረኝ” በማለት “በደፈናው ሶስት ክፍል ቤት በሚል አናዋውልም” የሚል መልስ እንደተሰጣቸው ያስረዳሉ።
እርሳቸውም ይህን የመሰለ ድፍን ያለ መልስ ሲሰጣቸው ለወረዳው የህዝብ ቅሬታና አቤቱታ ማስተናገጃ ጽህፈት ቤት በደብዳቤ ቅሬታቸውን ማቅረባቸውን ጠቁመው፤ የወረዳው የህዝብ ቅሬታና አቤቱታ ማስተናገጃ ጽህፈት ቤት የወረዳውን ቤቶች ልማት ጽህፈት ቤትን ስለጉዳዩ ጠይቆ “በደብዳቤ ቁጥር የአ/ወ/10/ቤ/አስ/ጽ/ቤት271/2013 በ26/04/2013 ዓ.ም በደብዳቤ አሳወቀኝ” ባለው መሰረት ቤቶች ልማት ጽህፈት ቤት የእርሳቸውን የቤት ውል አናድስም ሳይሆን ያለው፤ “ከአሁን በፊት በስህተት ሶስት ክፍል ተብሎ ውል ሲታደስላቸው የቆየ ሲሆን፤ በተገባደደው በጀት ዓመት የወረዳውን የቤቶች መረጃ በአዲስ ሲስተም ውስጥ ስናስገባ ቀድሞ ቤቱን ሲረከቡ ሁለት ክፍል መሆኑና አሁንም በሁለት ክፍል መዋዋል ይችላሉ” የሚል ምላሽ እንደሰጣቸው ለቅሬታ አቅራቢው ገልጸዋል።
ስለዚህ ከአሁን በፊት በተዋዋሉት መሰረት ውል እንዲታደስላቸው ጠይቀው አናድስም በመባላቸው ላቀረቡት ቅሬታ የወረዳው የህዝብ ቅሬታና አቤቱታ ማስተናገጃ ጽህፈት ቤት በሰጣቸው ምላሽ፤ “የወረዳው ቤቶች ልማት ጽህፈት ቤት በአዲስ ሲስተም ውስጥ ባስገባውና መጀመሪያ ተከራዩ የተረከቡት ሁለት ክፍል ቤት ለመሆኑ ከአራዳ ክፍለ ከተማ ቤቶች ልማትና አስተዳደር ጽህፈት ቤት በደብዳቤ ቁጥር የአ/ክ/ከ/ቤ/ል/ቤ/ማ/ 5055/2007 በቀን10/07/2007 ዓ.ም ለወረዳው ቤቶች ልማት ጽህፈት ቤት በጻፈው ደብዳቤ ባለ ሁለት ክፍል ቤት የሚል ማስረጃ ያለ በመሆኑ በሁለት ክፍል ቤት በሚል ውሉን እንዲያድሱ የውሳኔ ሃሳብ አቅርበናል” የሚል ምላሽ መስጠቱን ጠቁመዋል።
እርሳቸው በእጃቸው ከያዙት የተከራይና የአከራይ ውል በስተቀር ከዚህ በፊት ቤቱን ይዘው ሲያስተዳድሩት የነበሩት ግለሰብ ውልና የጽህፈት ቤቱ ከእርሳቸው ጋር ያደረገው የውል ስምምነት መረጃ ከጽህፈት ቤቱ ሆን ተብሎ እንዲጠፋ ተደርጓል የሚሉት ቅሬታ አቅራቢው፤ ከወረዳው ቤቶች ልማት ጽህፈት ቤት ጋር ፍርድ ቤት በነበራቸው ክርክር “ጽህፈት ቤቱ ከእርሳቸው ጋር የተዋዋለው ሁለት ክፍል ቤት ነው” ብሎ ሲሞግት ፍርድ ቤቱ “መረጃህን አቅርብ” ሲለው አላቀረበም። ነገር ግን እርሳቸው ሶስት ክፍል ቤት የተዋዋሉበትን ማስረጃ በማቅረባቸው ሶስተኛው ክፍል ቤት ጸድቆ እድሳት እንዲያከናውኑ ፍርድ ቤት እንደወሰነላቸው አስታውቀዋል።
ስለዚህ የወረዳው የህዝብ ቅሬታና አቤቱታ ማስተናገጃ ጽህፈት ቤት ይህንን ምላሽ ሲሰጣቸው መልሱ ተገቢ አይደለም ብለው ለወረዳው ዋና ስራ አስፈጻሚ ቅሬታቸውን ማቅረባቸውን ገልጸው፤ ሶስት ክፍል በሚል ውል ፈጽመው ከአምስት ዓመት በላይ ይዘው ሲያስተዳድሩት የነበረ ቤት “አሁን ላይ ምን አይነት አዲስ ሲስተም መጥቶ ነው? ሁለት ክፍል ቤት ነው ውል የፈጸምከው” ልባል የቻልኩት። “ከዚህ በፊት ሶስት ክፍል ቤት ብዬ ስዋዋል አንደኛውን ክፍል የተዋዋልሁት በአየር ላይ ነው? እንዴ የሚል ጥያቄ ለዋና ሰራ አስፈጻሚው ሲያነሱ የህዝብ ቅሬታና አቤቱታ ማስተናገጃ ጽህፈት ቤት “የሰጠው ምላሽ በቂ ነው” የሚል መልስ ሲሰጧቸው፤ “ጽህፈት ቤቱ የሰጠው መልስ በቂ ነው ከተባለ በደብዳቤ መልስ ይሰጠኝ” ሲሉ መልስ በደብዳቤ ሊሰጣቸው አለመቻሉን ያመለክታሉ።
እርሳቸውም የወረዳው ቤቶች ልማት ጽህፈት ቤት በውል ላይ ያለውን ባለ ሶስት ክፍል ቤታቸውን ባለሁለት ክፍል ቤት ነው በማለት ውል አላዋውላቸው በማለቱና ቤቱን በማሸጉ ምክንያት ፍርድ ቤት ከሰው ፍርድ ቤቱ እንደወሰነላቸውና ወረዳው የፍርድ ቤቱን ውሳኔ አልፈጽምም በማለቱ ቅሬታቸውን ለክፍለ ከተማው ቤቶች ልማትና አስተዳደር ጽህፈት ቤት አቤት ማለታቸውን ገልጸው፤ ጽህፈት ቤቱ ምላሽ አልሰጣቸው ሲል ለክፍለ ከተማው የህዝብ ቅሬታና አቤቱታ ማስተናገጃ ጽህፈት ቤት በቀን 23/10/2013 ዓ.ም በደብዳቤ ቅሬታቸውን ማመልከታቸውን ገልጸዋል።
የክፍለ ከተማው የህዝብ ቅሬታና አቤቱታ ማስተናገጃ ጽህፈት በደብዳቤ ቁጥር አ/ክ/ከ/የህ/ቅ/አ/ማ/ጽ/ቤት/367/13 በቀን 30/10/2013 ዓ.ም በቀረበው የሰነድ ማስረጃ መሰረት ለቅሬታ አቅራቢው በሰጠው ምላሽ፤ ከ2009 እስከ 2011 ዓ.ም ድረስ ቅሬታ አቅራቢው ከቤቶች ጽህፈት ቤት ጋር በገቡት ውል ላይ የክፍል ብዛት ሶስት መሆኑን እንደሚያሳይ ገልጿል።
እንዲሁም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት የአራዳ ምደብ ችሎት በፍ/መ/ቁ 21662 በቀን 18/01/2013 ዓ.ም በዋለው ችሎት ተከሳሽ ወይም የወረዳው ቤቶች ልማት ጽህፈት ቤት ቤቱ ሁለት ክፍል ነው ከማለት ውጭ በማስረጃ ያላስረዳ ስለሆነ የተከሳሽ ድርጊት በፍ/ሕ/ቁ አንቀጽ 1149 /3/ መሰረት ሁከትና ተገቢነት የሌለው መሆኑን፤ ክርክሩ የቀረበበት ቤት ወይም ክፍል ላይ ያደረገው እሸጋ ያላግባብ ስለሆነ ይነሳ መባሉ እና ከሳሽ በተሰጣቸው የግንባታ ፈቃድ መሰረት ግንባታቸውን መገንባት ይችላሉ በማለት የፈረደ መሆኑን ያሳያል።
ስለሆነም የወረዳው ቤቶች ልማት ጽህፈት ቤት ይህንን ውሳኔ በይግባኝ ባላሻረበት ሁኔታ የተሰጠውን የፍርድ ውሳኔ አላስፈጽምም ማለቱ ተገቢነት የሌለው ስለሆነ፤ የክፍለ ከተማው ቤቶች ልማት ጽህፈት ቤት “ውሳኔው እንዲፈጸም በማድረግ አፈጻጸሙንም በአዋጅ 64/2011 መሠረት በአምስት የስራ ቀናት ውስጥ እንዲያሳውቀኝ” ሲል የክፍለ ከተማው የህዝብ ቅሬታና አቤቱታ ማስተናገጃ ጽህፈት ቤት በደብዳቤ ማሳሰቡን አመልክተዋል።
እንዲሁም ክፍለ ከተማ በአሰራሩ መሰረት ጉዳዩ እንዲፈጸም ብሎ ለወረዳው ዋና ስራ አስፈጻሚ ደብዳቤ መጻፉን ሻምበል ተክላይ ገልጸው፤ ነገር ግን ጠዋት ማታ እየተመላለሱ ቢጠይቁም እስካሁን ወረዳው የሰጣቸው ምላሽ እንደሌለ ጠቁመው፤ በፍርድ ቤት ውሳኔው መሰረት እንዲሁም ከበላይ አካል በወረደለት አቅጣጫ ወረዳው ምላሽ ለመስጠት ፈቃደኛ አይደለም ብለዋል።
በአጠቃላይ በ2009 ዓ.ም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ባካሄደው የቤቶች ቆጠራ ሶስት ክፍል ቤት ተብሎ ተመዝግቧል። እንዲሁም ከወረዳው ጋር የተዋዋልሁት ውል በፍታብሄርና በወንጀል ህግ የጸና ይሆናል ነው የሚለው። ስለዚህ ወረዳው በህግ የተዋዋለውን ውል ክዶና ሽሮ በደል እያደረሰባቸው ከመሆኑ ባሻገር ፍርድ ቤት ቀርቦ ጥፋተኛ ተብሎ ተወስኖበት እያለ “የፍርድ ቤቱን ውሳኔ ለመፈጸም አሻፈረኝ” ብሏል። በመሆኑም ወረዳው መንግስት የሰጣቸውን ቤት ከህግ በላይ በመሆን ያላግባብ ለመንጠቅና ለማፍረስ እየሰራ ይገኛልና ህዝብና መንግስት ይፍረደኝ ሲሉ ሻምበል ተክላይ አቤቱታቸውን ከረጅሙ ባጭሩ በዚህ መልክ ለዝግጅት ክፍላችን አቅርበዋል።
የዝግጅት ክፍላችን የወረዳው ዋና ስራ አስፈጻሚና ቤቶች ልማት ጽህፈት ቤት ግለሰቡ ላቀረቡት አቤቱታ ምላሽ እንዲሰጡን በደብዳቤ የጠየቀ ሲሆን፤ የዝግጅት ክፍላችን መርማሪ ጋዜጠኛ መረጃ ለመጠየቅ ወደ ወረዳው በሄደበት ወቅት ሁሉም የወረዳው አመራር ክፍለ ከተማ ለስብሰባ ተጠርተው በመሄዳቸው በወቅቱ ምላሻቸውን ለማግኘት ሳይቻል ቀርቷል። ይሁን እንጂ በጉዳዩ ላይ ምላሽ ለመስጠት የወረዳው አመራር ፈቃደኛ መሆናቸውን በስልክ ስላሳወቁን በቀጣይ ክፍል ወረዳው የሚሰጠንን ምላሽ ይዘን የምንቀርብ ይሆናል።
ሶሎሞን በየነ
አዲስ ዘመን ጳጉሜን 3/2013