ወይዘሮ ሜላት ጌታቸው ይባላሉ ትውልዳቸውም እድገታቸውም እዚሁ መዲናችን አዲስ አበባ ነው። ከተትረፈረፋቸው ቤተሰብ የተወለዱ ባይሆኑም እናታቸው የሚያስፈልጋቸውን ቁሳዊ ነገር ብቻ ሳይሆን የጥሩ ስነ ምግባር ባለቤትም እንዲሆኑ አድርገው አሳድገዋቸዋል።
በትምህርት ዝግጅታቸውም በአካውንቲንግ ዲፕሎማ እንዲሁም በማኔጀመንት የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ይዘዋል። ወይዘሮ ሜላት ገና በወጣትነት እድሚያቸው ነበር የብዙ ልጆች እናት የመሆን ትልቅ ህልም የነበራቸው። አባታቸውን ያጡት ገና በልጅነታቸው ቢሆንም እናታቸው በችግር ወስጥ ሆነው ካላቸው ላይ ለሌሎች ሲያካፍሉ፤ የታመመ ሲጠይቁ እያዩ አድገዋል።
እናታቸው ብዙ ልጆች ቢኖረኝ ብለው ይመኙም ስለነበር ወይዘሮ ሜላት ይህንንም ለማሳካት ያስቡ ነበር። የእነ ሜላት ቤት እንግዳ የማያጣው በመሆኑም በቀላሉ ከሌሎች ጋር የመግባባት ክህሎትንና ከሰው ጋር ተካፍሎ የመኖር ጥበብን ገና በልጅነታቸው አዳብረውበታል። በልጅነት ግዜያቸው ሌላው ቀርቶ ቋንቋቸውን የማይናገሩ ዘመዶቻቸው ሲመጡ እንኳን ቁጭ ብለው በልጅነት አንደበታቸው ሲያስቋቸው ሲያጫውቷቸው ያመሹ እንደነበር ያስታውሳሉ።
በተመሳሳይ ባለቤታቸው አቶ ሀይሉ ገመቹ አዲስ አበባ ተወልደው ያደጉ ሲሆን በኢንጅነሪንግ የመጀመሪያና ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ይዘው በአሁኑ ወቅት ደግሞ ሦስተኛ ዲግሪያቸውን በማጠናቀቅ ላይ ይገኛሉ። በመከላከያ ዩኒቨርሲቲ በመምህርነት እያገለገሉም ይገኛል። አቶ ሀይሉም በድሃ ቤተሰብ ውስጥ ያደጉ ቢሆንም እንግዳ ከቤታቸው ጠፍቶ እንደማያውቅ ይናገራሉ።
በዚህም እሳቸውን ጨምሮ በቤት ወስጥ ያሉት አምስቱም የቤተሰብ አባል እግር ከማጠብ ጀምሮ የመጣን እንግዳ መቀበል የዘወትር ስራቸው እንደነበር ያስታውሳሉ። የቤተሰባቸው ትልቁ ልጅም የስጋ ተወላጅ ሳይሆን የዘመድ ልጅ ነበር። እኒህ ሁለት ጥንዶች ያጠመራቸው ፍቅር የመሰረተው የትዳር ግንኙነት ቢሆንም በሁለቱም ልብ ውስጥ ትልቅ ተቋም መስርቶ ወላጅ አልባ ህጻናትን የመታደግ የረጅም ጊዜ ህልምም ነበራቸው።
እያደጉና ነገሩን በቅርበት እየተመለከቱት ሲመጡ በአንዳንድ ግብረ ሰናይ ድርጅቶች ላይ የሚወራው ወሬ ስላላስደሰታቸው ድርጅት የማቋቋሙን ሃሳብ እርግፍ አድርገው ይተውታል። ይህም ሆኖ ወላጅ አልባ ህጻናትን የማሳደጉ ነገር በወስጣቸው ነበር። በጉዳዩ ላይም የመከሩበት ገና የሶስት ጉልቻን ጉዞ ከመጀመራቸው በፊት ነበር። እናም በወይዘሮ ሜላት አነሳሽነት የቀረበውን ሃሳብ ባለቤታቸውም አቶ ሀይሉ ውስጣቸው ስለነበር የአብራካቸው ክፋይ ያልሆኑ አስራ ሁለት ህጻናትን ለማሳደግ ተስማምተው ህይወታቸውን ይጀምራሉ። ጋብቻ ከፈጸሙና አንድ ልጅ ከወለዱ በኋላ ግን ነገሮች እንዳሰቡት ቀላል ሳይሆኑ ይቀሩና ህልማቸውን በልባቸው እንደያዙ ኑሯቸውን ይቀጥላሉ።
አንድ ቀን ግን ወይዘሮ ሜላት በማርሲል መንፈሳዊ ቴሌቪዠን ቅኝት የሚል ፕሮግራም እየተከታተሉ ሳለ ለዓመታት ውስጣቸው የነበረውን ነገር የሚቀሰቅስባቸው አጋጣሚ ይፈጠራል። በፕሮግራሙ የቀረቡት ሁለት ቤተሰቦች በጉዲፈቻ ልጆች ወልደው የሚያሳድጉ ነበሩ። በፕሮግራሙ ሌላ ቤታኒያ ከሚባል ድርጅት የመጣ አንድ ባለሙያ ደግሞ በኢትዮጵያ ያሉ ህጻናት ያለባቸውን ችግር በዝርዝር ሲያስረዳ ያዳምጣሉ። ባለሙያው የችግሩን አሳሳቢነት ከመግለጽ ባለፈም ቀና ልብ ያላቸው ዜጎች ህጻናቱን በመታደጉ ስራ እንዲሳተፉ ጥሪ አቅርቦ ነበር። ወይዘሮ ሜላት ከባለሙያው የሰሙትን ነገር ለማመን ይከብዳቸዋል።
በየጎዳናው ዳርቻ ህጻናት ልጆችን ማየት ለአዲስ አበባ ነዋሪ አዲስ ባይሆንም እውን ኢትዮጵያ ውስጥ በዚህ ደረጃ ህጻናት ለስቃይ እየተዳረጉ ይሆን? ወይንስ ተጋኖ ይሆን» የሚል ነገርም ይፈጠርባቸዋል። በተለይም በየምናምኑ ስር ተጥለው ከሚገኙት ልጆች በህይወት የሚተርፉት ጥቂቶች መሆናቸውን ሲሰሙ ልባቸው እጅግ ይነካል። ወይዘሮ ሜላት ባለቤታቸውን እስኪመጡ ጠብቀው ያለውን ነገር ያዋዯቸዋል። በአንድ ሃሳብም ከስምምነት ይደርሳሉ።
ወዲያውኑ ስልካቸውን አንስተው ወደያዙት ቁጥር ሲደውሉ ያገኛቸው የቢታንያ የአዋሳው ቅርንጫፍ ተወካይ ነበርና ወደ አዲስ አበባው ያስተላልፋቸዋል። ወይዘሮ ሜላትም የተቀበሉትን ስልክ ደውለው የቤታንያን አድራሻ በመቀበል በበነጋው ወደዚያው ያቀናሉ።
ወደ ቤታንያ ካቀኑ በኋላ ግን ከሰሙትም ከገመቱትም በላይ ሌላ አዲስ ነገር ይገጥማቸዋል። የቢታንያ ኃላፊ ልጅ ለመውሰድ መምጣታቸውን ከሰሙ በኋላ ምን አይነት ልጅ ነው የምትፈልጊው ይሏቸዋል። ነገሩ ያልገባቸው ወይዘሮ ሜላት ምን አይነት ልጅ ማለት ምንድን ነው፤ የመጣሁት ያው የምትሰጡኝን ልጅ ወስጄ ለማሳደግ ነው ይላሉ። ኃላፊዋም ያልተረዱት ነገር እንዳለ ሲገባቸው ብዙ ሰዎች ሲመጡ አንዳንዱ የጾታ፤ አንዳንዱ የመልክ፤ አንዳንዱ የጤና፤ ብቻ የራሳቸውን ምርጫ ይዘው ይመጣሉ። እኛ ደግሞ መከልከል ባንችልም ስለሚያስቸግረን ለመለየት ብለን ነው የምንጠይቀው ይሏቸዋል። ወይዘሮ ሜላትም በቃ ሰው የማይፈልገውን፤ ሰው ያልመረጠውን ስጪኝ ብለው ይመልሳሉ።
የቢታንያ ኃላፊዎችም ይህን ስምምነታቸውን ይዘው ደጋግመው ከተሰበሰቡ በኋላ ሁለት ልጆች ማንም ያለመረጣቸው ስለነበሩ ከእነሱ መለየት እየሞከሩ እያለ ወይዘሮ ሜላት ጉዳዬ ለምን ቆየ ብለው ተመልሰው ጎራ ይላሉ። ኃላፊዎቹም ሁለት ልጆች እንዳሉና ከእነሱ አንዱን ለመምረጥ እየመከሩ መሆናቸውን ይነግሯቸዋል። ወይዘሮ ሜላትና ባለቤታቸው የፕሮቴስታንት እምነት ተከታይ ሲሆኑ «ከአምልኮ ሁሉ ትልቁና እውነተኛው ወላጅ አልባ ህጻናትንና አረጋውያንን መንከባከብ ነው» የሚለውን አስተምህሮ ቅድሚያ ይሰጡት ነበር። እንዲሁም ከልጅነታቸው ጀምሮ ልጆችን በአደራ መቀበል እንጂ የሚያኖራቸው ፈጣሪ ነው የሚል ጽኑ እምነት ስለ ነበራቸው በፎቶ ያዩዋቸውን ሁለቱንም ልጆች ለመቀበል ወስነው ይመለሳሉ። ‘
በኋላ ግን ክበበ ጸሀይ ሄደው ልጆቹን ሊቀበሉ ሲሉ ከፎቶው የተለየ አዲስ ነገር ይገጥማቸዋል። ከሁለቱ ልጆች አንዱ መናገርም መራመድም አይችልም በተጨማሪ ተደራራቢ የጤና ችግሮችም የነበሩበት ስለነበር በህይወት የመቆየቱም ነገር የሚያጠራጥር ነበር። ሁለተኛውም እግሩ ላይ ትልቅ ችግር የገጠመው በመሆኑ ራሱን ችሎ መራመድ አይችልም ነበር። ለካስ ሌሎቹ ሰዎች እነዚህን ህጻናት ያልመረጧቸው በዚህ ምከንያት ነበር። ይህም ሆኖ በውሳኔያቸው የጸኑት ጥንዶች ከቢታንያ የተሰጣቸውን ስልጠና ወስደው ልጆቻቸውን ይዘው ወደቤታቸው ያቀናሉ።
በዚህ ጊዜ ወይዘሮ ሜላት ቀድሞ ሲሰሩት የነበረውን የባንክና የሂሳብ ስራ አቁመው የቤት እመቤት ሆነው ነበር። እናም የቅርብ ሰዎቻቸው ዘመዶቻቸውን ጨምሮ ይህን ስራቸውን ሲያዩ በክፋት ሳይሆን ለእነሱ በማሰብ ይሄ ነገር ያስቸግራችኋል። አንድም የልጆቹን ቁጥር ብትቀንሱ አልያም አንቺ ስራ እስክትጀምሪና እስክትጠናከሩ ብትቆዩ ይሻላል የሚል ምክረ ሀሳብ ያቀርቡላቸዋል።አንዳንዶቹ አለፍም ብለው ተያይዛችሁ ልትቀውሱ ነው እንዴ? እንዴት እንዲህ ታደርጋላችሁ? ይሏቸው ነበር። ሌላው ቀርቶ በልግስናቸው የማይታሙት የሜላት እናት ነገሩ ግራ አጋብቷቸው ኧረ ይሄ ነገር እንዴት ነው ብለው ነበር።
ይህም ሆኖ ጥንዶቹ የመጣውን ለመጋፈጥ በመወሰናቸው ሁለቱንም ልጆቻቸውን ይዘው ወደ ቤታቸው ያቀናሉ። የውጪውን ማህበረሰብ ጫና በእነሱ ጠንካራ ውሳኔ ሊቋቋሙት ቢችሉም ልጆቹን የመንከባከቡ ነገር ግን እንዲህ በቀላሉ አልጋ በአልጋ ሳይሆን ይቀራል። ልጆቹን ያመጡት እቤት ወስጥ ጥሩ ሞግዚት ቀጥረውና አቅማቸው በፈቀደ ዝግጅት አድርገው የነበረ ቢሆንም ልጆቹ የጤና መጓደል ስለነበረባቸው የሚያስፈልገው ዝግጅት ከዛም በላይ ሆኖ ያገኙታል።
በተለይ የነርቭ ችግር ያለበትን ህጻን ልብስ ለማልበስና ዳይፐር ለመቀየር የግድ ሦስት ሰው ያስፈልግ ስለነበር ሁኔታው ለነወይዘሮ ሜላት ፈታኝ ይሆናል። ከወይዘሮ ሜላትም ከሞግዚቷም ባለፈ ባለቤታቸው አቶ ሀይሉ የግድ ተሳታፊ መሆን ነበረባቸው። ሳይደግስ አይጣላም እንዲሉ ጥንዶች ለተወሰነ ግዜ በዚህ አይነት ህጻናቱን እየተንከባከቡ ከቆዩ በኋላ ቀስ በቀስ አንዱ ህጻን የመሻል ለውጥ ማምጣት ይጀምራል። እነ ወይዘሮ ሜላትም ከትጋታቸውም ከፀሎታቸውም ሳያቋርጡ ቀን ከሌሊት እንክብካቢያቸውን ይቀጥላሉ።
ይህም ሆኖ አንዱ ህጻን ሙሉ ለሙሉ ራሱን ችሎ መንቀሳቀስና መራመድ አይችልም፤ አንደኛውም በተመሳሰይ እግሩ ላይ እክል ያለበት ነበር። በተጨማሪ ልጆቹ በአመጋገብ ስርዓታቸው የተለዩ በርካታ ምግብ የሚፈልጉና የሚነጫነጩም ነበሩ። በሚፈልጉበት ሰዓት ምግብ ካልቀረበላቸው ይነጫነጫሉ። በመሆኑም በቀን እስከ አምስት ግዜ መመገብ ያስፈልግ ነበር። ህጻናቱ በብዙ ነገር ደስተኛም አልነበሩም።
በዚህ ሁኔታ ውስጥ እያሉ ደግሞ ዓለምን ለከፋ ችግር የዳረገው ኮሮና በኢትዮጵያም ሲከሰት ወይዘሮ ሜላትና አቶ ሀይሉ ሌላ ተጨማሪ በጎ ነገር በአእምሯቸው ይከሰታል። በወቅቱ በመንግሥት ውሳኔ ታራሚዎች ተለቀው ወደቤታቸው ሲገቡ በተሌቪዠን ሲመለከቱ እዛ የተቀመጡት ልጆች በአእምሯቸው ይመጣሉ። ምን ሆነው ይሆን አንድ ሰው ቫይረሱን ይዞት ቢገባ ሁሉም ሊያልቁ ይችላሉ።
ስለዚህ እኛ ቢያንስ አንድ ልጅ እንጨምርና የአንድ ህጻን ነፍስ እንታደግ ሲሉ ይወስናሉ። ነገር ግን ሁለቱን ልጆች የወሰዱ ጊዜ ለማሳደግ በቂ ሁኔታ አለ ወይ የሚለው ሲጣራ ትንሽ አነጋግሮ ስለነበር አሁን እንደማይሰጧቸው የገመቱ ቢሆንም። እነዚህ ልጆች እዛ ከቆዩ መጨረሻቸው ሞት ሊሆን ይችላል። ከመቃብር ደግሞ የእኛ ቤት ይሻላል አብረን የሆነውን እንሆናለን ብለው ሶስት ልጅ ይሰጠኝ ሲሉ በድጋሚ ጥያቄያቸውን ለቢታንያ ያቀርባሉ።
የቢታንያ ኃላፊዎችም አሁን ባላችሁበት ነባራዊ ሁኔታ ሦሰት ለመጨመር አትችሉም ነገር ግን ከኮሮና ባሻገር በማቆያው ተፈጥሮ የነበረ ወረርሽኝ ስለነበረም አንድ ልጅ መውሰድ ትችላላችሁ ይሏቸዋል። በዚሀም አንዲት የአእምሮ ችግር የነበረባት ልጅ ስለነበረች እሷን ለመውሰድ ይስማማሉ።
እናም ሁለቱ ልጆች ከመጡ ከአንድ ዓመት በኋላ ሰኔ አንድ ቀን 2012 ዓ.ም ሦስተኛ ልጃቸውን ተረክበው ወደቤታቸው ያቀናሉ። ዛሬ ወይዘሮ ሉሊትና አቶ ሀይሉ የሁለት ሴትና የሁለት ወንድ ልጆች እናትና አባት በመሆን በጎፋ የመከላከያ ካምፕ ውስጥ በሚኖሩበት ቤት ራሳቸውን ጨምሮ ዘጠኝ ቤተሰቦችን እያስተዳደሩ ይገኛሉ። ይህም ሆኖ ግን አሁንም በቃኝ አላሉም «እስቲ ፈጣሪ ያሳካልን እንጂ በልባችን ብዙ አለ ይላሉ»።
«አብዛኛውን ማህበራዊ ችግሮቻችንን ለመቅረፍ አውሮፓ ወይንም አሜሪካ ማማተር አይጠበቅብንም» የሚሉት ወይዘሮ ሜላትና አቶ ሀይሉ የሚከተለውን መልእክትም ለሚመለከተው ሁሉ አስተላልፈዋል። በህጻናት ለይ የሚደርሱ ችግሮችን በተለይ ከመፈጠራቸው በፊት ለመቅረፍ መንግሥትና የሀይማኖት ተቋማት ትልቅ ኃላፊነት አለባቸው። አብዛኛው ችግር እየተፈጠረና ህጻናት ለአስከፊ ችግር እየተዳረጉ ያሉት ከስነምግባር ጋር በታያያዘ ነው። በመሆኑም መንግሥት ስነ ምግባርን በተመለከተ በትምህርት ካሪኩለም ውስጥ ሊያካትት ይገባል።
ብዙዎቹ የመረዳዳት ባህላችንን የሚሸረሽሩ አካሄዶች የሚመጡት ከትምህርት ተቋማትና ከማህበራዊ ሚዲያው ነው። በመሆኑም ይህንን የሚሻገር በነበረው ኢትዮጵያዊ የመረዳዳት የመተሳሰብ የመከባበር ባህልና ስነምግባር የተገራ ትውልድ መፍጠር ይጠበቃል። ይህን ማድረግ ከተቻለ በአንድ ወገን እንደዚህ አይነት ችግሮች የሚፈጠሩበት እድል ይጠባል በሌላ በኩል የመረዳዳቱም ባህል የተጠናከረ ስለሚሆን አንዳንድ ነገሮች ቢከሰቱም የጎላ ችግር በህጻናቱ ላይ እንዳይደርስ ያደርጋል።
የሀይማኖት መምህራንና መሪዎችም ለተከታዮቻቸው ከስብከት ባለፈ የተግባር መምህር ምሳሌ መሆን አለባቸው። ማህበረሰቡም ቢሆን እየተስፋፋ ከመጣው ግለኝነት በመውጣት ከተረፈው ሳይሆን ካለው ላይ ማካፈልን መልመድ እንዲሁም ለበጎ ምግባር ከይሉኝታ መውጣት አለበት።
መረዳዳትም ሆነ ጉዲፈቻ ለኢትዮጵያውያን የኖርንበት ባህላችን ነው። ስለዚህ ችግራችንን በራሳችን አቅም ለመቅረፍ የሚጠበቅብን ከተጣበቅንበት የሚያራርቅ የውጭ አስተምህሮ ወደራሳችን መመለስ ብቻ ነው። በዚህ አይነት ሁሉም ሳይሆን ጥቂት ኢትዮጵያውያን ብቻ ልባችን ቢመለስ ሁሉንም ችግረኛ መታደግ እንችላለን። እናም የአቅማችንን ከማድረግ አንቦዝን ሲሉ መልእክታቸውን አስተላለፈዋል።
ራስወርቅ ሙሉጌታ
አዲስ ዘመን ጳጉሜን 3/2013