
የተባበሩት አረብ አሚሬቶች በምዕራብ እስያ የምትገኝና በዚሁ ቀጠናም ግዙፍ ኢኮኖሚ ያላት ሀገር ናት። በውጪ ቀጥታ ኢንቨስትመንትም በርካታ አልሚዎችንና ሰራተኞች በመሳብ ትታወቃለች። ለኢንቨስትመንት ምቹ በመሆኗም የበርካታ ሀገራትን ቀለብ በቀላሉ ለመሳብ ችላለች። ይህም ከሀገሬው ሰው ይልቅ የውጭ ሀገር ዜጎች በብዛት የሚኖሩባት ሀገር አሰኝቷታል።
ልክ እንደብዙዎቹ ሀገራት ሁሉ የተባበሩት አረብ ኢምሬትም ኢኮኖሚዋ በኮቪድ-19 ተናግቷል። ወረርሽኙ በሀገሪቱ ከተከሰተ ወዲህ እስካሁን ድረስ ከ724 ሺ በላይ የሚሆኑ ዜጎቿ በቫይረሱ የተያዙ ሲሆን ከ2 ሺ በላይ የሚሆኑት ደግሞ ለህልፈተ ህይወት ተዳርገዋል። ከ713 ሺ በላይ የሚሆኑት ደግሞ ከበሽታው አገግመዋል። በኮቪድ 19 ወረርሽኝ ምክንያት የተናጋውን ኢኮኖሚዋን ወደነበረበት ለመመለስና በተለይ ደግሞ ከኢኮኖሚ የምንግዜም ተፎካካሪዋ ሳኡዲ አረቢያን ልቆ ለመገኘት በቀጣዮቹ ዘጠኝ ዓመታት ውስጥ አሳካዋለሁ ያለችውን ዕቅድ ይዛ መጥታለች።
እንደ አልጀዚራ ዘገባ ከሆነ የተባበሩት አረብ ኢምሬቶች በቀጣዮቹ ዘጠኝ ዓመታት ውስጥ የ150 ቢሊዮን ዶላር የቀጥታ የውጪ ኢንቨስትመንት ለመሳብ ማቀዷን የመንግስት የስራ ሃላፊዎች ተናግረዋል። ይህንኑ እቅድ ለማሳካትም ከአሁኑ እንቅስቃሴዎች ስለመጀመራቸው ተነግሯል።
የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች የአገሪቱን ኢኮኖሚያዊ ተወዳዳሪነት ለማሳደግ እና በሚቀጥሉት ዘጠኝ ዓመታት ውስጥ የ550 ቢሊዮን ድርሃም ወይም የ150 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ 50 አዳዲስ ኢኮኖሚያዊ ፕሮጀክቶችን ለመጀመር ማቀዷ ተገልጿል።
አንዳንዶቹ አዳዲስ ፕሮጀክቶች ባለፈው እሁድ በመንግስት ባለስልጣናት በኩል ይፋ መደረጋቸውንና በቴክኖሎጂ ኢንቨስት ማድረግ እና ነዋሪዎችን እና የሰለጠኑ ሰራተኞችን ወደሀገሪቱ ለመሳብ አዲስ ቪዛ መፍጠርን እንደሚያጠቃልልም ተጠቁሟል።
የባህረ ሰላጤዋ ሀገር የተባበሩት አረብ ኢምሬቶች በኮቪድ- 19 ወረርሽኝ ሳቢያ የተጎዳውን ኢኮኖሚዋን ለመጠገን ከባለፈው ዓመት ወዲህ አልሚዎችንና የውጪ ሀገር ዜጎችን ለመሳብ በርካታ እርምጃዎችን ስለመውሰዷም ተጠቅሷል።
በኮቪድ-19 የተጎዳውን ኢኮኖሚዋን ከመጠገን በዘለለ የተባበሩት አረብ ኢምሬቶች አዳዲስ ፕሮጀክቶችንና ለውጦቹን ይዛ ብቅ ያላቸው ባለችበት የባህረ ሰላጤው ቀጠና ያላትን ኢኮኖሚያዊ የበላይነት ለማስጠበቅና የንግድ ማዕከል ለመሆን አለፍ ሲል ደግሞ ከጎረቤቷ ሳኡዲ ዓረቢያ በኩል እያደገ በመጣው የኢኮኖሚ ፉክክር ውስጥ ልቆ ለመገኘት መሆኑንም ተንታኞች ገልጸዋል።
ከፕሮጀክቶቹ መካከል የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች እና የኤሚሬትስ ልማት ባንክ በኢንዱስትሪ ቴክኖሎጂ እና ከፍተኛ በሆኑ የቴክኖሎጂ ዘርፎች 5 ቢሊዮን ድርሃም ኢንቨስት የሚያደርጉባቸው በዋናነት ይጠቀሳሉ ሲሉ የሀገሪቱ የኢንዱስትሪ እና የላቀ ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ሱልጣን አል ጃብር ለመገናኛ ብዙሃን በሰጡት መግለጫ መናገራቸውም ተጠቁሟል።
የከፍተኛ ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ሣራ አል አሚሪ በበኩላቸው ‹‹የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች እነዚህን አዳዲስ ፕሮጀክቶች በዘጠኝ ዓመታት ውስጥ ተግባራዊ ለማድረግ ያቀደችው ለቀጣዮቹ 50 ዓመታት በተለያዩ የኢንዱስትሪ ዘርፎች ውስጥ ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ ለመሆን ካላት ፍላጎት የመነጨ ነው›› ሲሉ ለሮይተርስ የዜና ወኪል መናገራቸውም ተመላክቷል።
‹‹በቀጠናው ላለፉት አምስትና አስርት ዓመታት ዒላማ አድርገን እየተንቀሳቀስን ያለነው ይህንኑ ተግባራዊ ለማድረግ በመሆኑ አሁንም ብዙ ዘርፎቻችን በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ መሆናቸውን ለማረጋገጥ ትጋታችንን እንቀጥላለን›› ብለዋል ሚኒስትር ዴኤታዋ።
ሁለት አዲስ የቪዛ ምድቦች – አንዱ ለነፃ ሠራተኞች እና ሌላኛው ደግሞ ለሥራ ፈጣሪዎች እና ለሠለጠኑ ሠራተኞች እንደሚዘጋጅና ይህም የውጭ ዜጎችን በተፈላጊ ክህሎታቸው ለመሳብ እና በሀገሪቱ ለማቆየት የሚያስችል ስለመሆኑ በመንግስት ባለሥልጣናት ባለፈው እሁድ መገለፁ ተነግሯል። በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ውስጥ ያሉ የውጭ ሀገር ዜጎችም ከሥራ ስምሪት ጋር ለተያያዙ ጉዳዮች ለጥቂት ዓመታት ብቻ የሚታደስ ቪዛ እንዳላቸውም ተገልጿል።
አዲሱ “አረንጓዴ ቪዛ” የስራ ክህሎት ላላቸው ሠራተኞች የቤተሰብ አባላትን ስፖንሰር ለማድረግ የበለጠ አመቺ እንደሚሆን እና አንድ ሥራ ካለቀ በኋላ አዲስ ሥራ ለማግኘት በሀገሪቱ ብዙ ጊዜ ለመቆየት እንደሚፈቅድም እነዚሁ የሀገሪቱ ባለሥልጣናት መናገራቸውም ታውቋል።
ባለፈው ዓመት የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች የ10 ዓመት ነዋሪነትን የሚሰጥ ተጨማሪ “ወርቃማ” የቪዛ ስርዓት ምድቦችን የዘረጋች መሆኑንና ይህ እርምጃም ዱባይ እስከ አንድ በመቶ ኢኮኖሚዋን ሊያሳድግላት እንደሚችልም ተጠቁሟል።
የተባበሩት አረብ ኢሚሬቶች በመካከለኛው ምስራቅ ከቱርክ፣ ሳኡዲ አረቢያና ኢራን ቀጥሎ አራተኛው እንደሆነ የሚነገር ሲሆን እ.ኤ.አ በ2020 በወጣ መረጃ መሰረት የሀገሪቱ ጠቅላላ ሀገራዊ ምርት 241 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር ወይም 1 ነጥብ 5 ትሪሊዮን የአረብ ኢምሬቶች ድርሃም እንደሆነ መረጃዎች ያሳያሉ።
አስናቀ ፀጋዬ
አዲስ ዘመን ጳጉሜን 3/2013