ኢትዮጵያዊነት ከመልካምነት ጋር መያያዙ እንዲሁ የሚነገር አይደለም። በሚሊዮን እውነታዎች የታጀቡ ደግነቶች ስለሚስተዋሉ፤ ምድሪቱን የሞሉ ሰናይ ምግባሮች ምስክር ስለሚሆኑ እንጂ። ያገር ሰው ካስተዋልክ! እዚህች ምድር ላይ “መልካምነት” ከማስመሰል የራቀ እውናዊ ትዕይንት ነው። ኢትዮጵያዊ መልካምነት በበጎ ግብረ ገብ የተኳለ፣ በአብሮነት ፍቅር የፀና በማህበራዊና ስነልቦናዊ ውቅር የተበጀ ማንነት ነው።
መንገድ ስትሄድ አንዳች ነገር ካደናቀፈህ “እኔን” የሚል የሚያውቅህ ብቻ አይደለም። አካባቢው ላይ ያለ ሁሉ አንድም ቀን እንኳን አይቶህ የማያውቅ ሰው ነው። መደናቀፍህ አስደንግጦት መውደቅህ የራሱ ህመም አድርጎ “እኔን” ብሎ ያንተ መውደቅ ለሱ ያደርግልሃል። ይህ ነው ኢትዮጵያዊ ደግነት፤ ይህ ነው ኢትዮጵያዊ መልካምነት ስነ ልቦና።
እስኪ ንገረኝማ የትኛው ዓለም ላይ ነው ይህ በጎነት፤ ይሄን የሚስተካከል ከራስ ጋር የተሰራ መልካምነት የምታገኘው። እስኪ የትኛው ማህበረሰብ ነው ከሌለው ላይ ቀንሶ ለወገኑ የሚያካፍል? ተቸግረህ እጅህን ብትዘረጋ ከጎደለው ላይ ቆርሶ የሚያካፍልህ፣ ሊሰጥህ አስቦ ኪሱ ዳብሶ ሳንቲም ቢያጣ የእጅህ መዘርጋት አይቶ ከአንጀቱ የሚንሰፈሰፍልህ ከንፈሩን በሀዘን የሚመጥልህ? ይህ የምታየው በዚህች የእምነት አገር፤ በዚህች የደጋጎች የልበ ቀናዎች ምድር ላይ ነው።
አብሮ መብላት ባህሉ ያደረገ፣ ግለኝነትን አጥብቆ የሚኮንን፣ መልካም መስራት እጅጉን የሚያስከብር፣ ክፉን ማሰብ የሚያስኮንን እዚህ መልካምነት ባህሉ ባደረገ ማህበረሰብ ነው። ቡና አፍልተው ብቻዬን አልጠጣም የሚሉ ደጋግ እናቶች፣ ወንድሜ ሳይጠግብ እኔ አልቀምስም የሚሉ ሩህሩህ አባቶች፣ አንተ ትብስ አንቺ የሚባባሉ አብረው መሶብ እንጀራ የሚቆርሱ ጎረቤታሞች እዚህ አገር ላይ የበቀሉ ደጎች መለያ ባህሪና ተግባር ነው። በኢትዮጵያዊ መልካም ግብረገብ የታነፁ በአበሻነት በጎ ስነ ልቦና የታነፁ ምግባረ ሰናዮች እርግጥም እዚህች ምድር ላይ በዝተው አሉ።
የማያውቀው ሞተ ሲሉት ደረቱን እየደቃ በሀዘን የሚደብን፣ ወገንህ ታመመ አልያም ተቸገረ ሲሉት “ያንተን ለኔ” ያድርገው እያለ ለወገኑ አንጀቱ የሚላወስ ኢትዮጵያዊ ለብዙዎች ሳቅ እራሱን አሳልፎ የሚሰጥ ሀበሻ የመሰለ፤ እንካ ሲል አምጡ የማይል ማህበረሰብ ካለ ንገረኝማ ጎበዝ። አዎ አታገኙም። ከተገኘም መፈለጉ ቀላል አይሆንም።
እዚያ ማዶ የበረከተ ደግነት አለ፤ ባህር ተሻግሮ እጅ ባፍ የሚያስጭን መልካምነት አለ ብትሉኝ፤ ኣኣ ያገሬ ሰው እዚያ ያለው መልካምነት መልካም ያልሆነ ነው እላችኋለሁ። መልካምነቱ ከዚያ መልካም ነገር ከፍ ያለ መልካም ነገር ለመንጠቅ ነው ብዬ እሞግትሃለሁ። በሰጥቶ መቀበል መርህ ላይ የተመሰረተ መልካምነት ነው። እራሳቸው ይሉሃል እኮ አልሰማህም ?
እንዲሁ እንካ እንደማይሉህ ሲነግሩህ “There is no free lunch” ይሉሃል ደጋግመው። ነፃ ግብዣ የሚባል ነገር የለም እንደማለት። የሚሰጡህ ሊቀበሉህ ካሰቡት ትንሹን ነው። የሚቸሩህ ላንተ ሊቸረችሩት ያሰቡት ነገር ሲኖር ነው። እንባ የሚያሳዩህ ብዙ ሊያስነቡህ ሲያስቡ መሆኑን ጠርጥር። መርሀቸው ትንሽ ሰጥቶ ብዙ መቀበል ነውና። ትንሽ እንካ ብለው ብዙ አምጣ ሊሉህ አስበው ነው። መልካምነታቸው መልኩ ሌላ ነው።
የአገሬ ሰው የእነሱን ልግስና ከታሪክ ማህደር ገልፀህ አንብብ። የሚበዛው መልካምነታቸው የሚያሳዩት መልካም የሚሉት ነገርህን ለመንጠቅ ሲያስቡ ነው። የሰው ልጅ ምድር ላይ በረሀብና እርዛት እየተጠበሰ ለውሻና ድመታቸው በሚሊዮን ዶላር ተናዘው የሚሞቱ ናቸው። ስለ እነሱ ምቾት አለመጉደል ሲባል ሌላው እንዲኖር እንኳን አይፈቅዱም፤ አልያም መኖሩን ቢፈልጉት ለእነሱ መጠቀሚያ እንዲሆን ነው። በእርግጥ እነሱ መሀል እውነተኛ ደግ መልካምነት ተፈጥሮ የሆነ የለም ማለት አይደለም።
እዚህም ከእኛ ጋር ያልታረቀ ከኢትዮጵያዊ መልካምነት ጋር ያልተወዳጀ እንዳለ ሁሉ እነሱም ጋር መልካምነት የተላበሰ አይጠፋም። ነገር ግን እዚያ ያለው ደግነት እራሱ ደግ ያልሆነ ደግነት፤ መልካም ያልሆነ መልካምነት ነው።
እርግጥ ነው እዚህም የእነዚያ ስነ ልቦና ባርነት የተፀናወተው ኢትዮጵያዊ አታጣም። አልፎ አልፎ ኢትዮጵያዊ ሆኖ ከዚህ ማህበረሰብ ተፈጥሮ ኖሮና አድጎም ከኢትዮጵያዊነት ፍፁም የራቀ ማንነት ከዚህች አገርና ህዝብ ግብረ ገብ የራቀ ምግባር ሲፈፅም ትመለከት ይሆናል።
እግዞ ! የሚያስብል ከኢትዮጵያዊ ባህልና ምግባር የማይጠበቅ ተግባር ልታይ ትችል ይሆናል። ግን ደግሞ እወቅ ይህ ግለሰብ አልያም ቡድን አካላዊ ባርነቱን በሌሎች እንዳይደፈር አባቶቹ ዘብ ሆነው ቢጠብቁለትም፤ መንፈሳዊ ባርነት ማምለጥ ያልቻለ ከኢትዮጵያዊ ስነ ምግባርና ግብረ ገብነት ያፈነገጠ መሆኑ እርግጠኛ ሁን።
ኢትዮጵያዊ መልካምነት በበዛ በጎ ተግባር ይገለፃል። በመልካም ገፅታችን ይንፃባረቃል። ኢትዮጵያዊ ደግነት ግለኝነት በማህበራዊ ትስስር የገረሰሰ፣ ስግብግብነት የራስን አሳልፎ በመስጠት የተካ፣ ጭካኔን በመራራት የለወጠ ማህበረሰባዊ ማንነት ነው። ኢትዮጵያዊ መልካምነት መልካም ሆኖ ብቻ የሚታይ በጎ ተግባር ነው። ሌላኛው ማንነት ግን ንፅህና የጎደለው ከእኛና ከእኛነታችን እሴቶች ፍፁም የተራራቀ ማንነት ነው።
ከእኔ ይልቅ ህዝቤ ከሁሉ በፊት አገሬ ብሎ ሳይሰስት እራሱን አሳልፎ እስከመስጠት የሚደርስ ማንነት ነው ኢትዮጵያዊነት። ማህበራዊ አብሮነትን የሚያፀና በጎነትን የሚያላብስ መልካምነት ነው ኢትዮጵያዊነት።
ግለኝነት ኢትዮጵያዊ ልማድ አይደለም። ስግብግብነት እራስ ወዳድነት የዚህ ህዝብ መለያ ባህሪ ሊሆን ፈፅሞ አይችልም። የዚህ ህዝብና አገር ስነ ልቦና መልካም ነገር ላይ ማዘውተር ነው። ለአገርና ለወገን መቆርቆር ከራስ ይልቅ አብዝቶ ለሌሎች ማሰብና መኖር ነው ልማዱ። ቅድሚያ ለአገርና ለህዝብ የሚለው የመልካምነት መገለጫ ባህሪ ከስግብግብነትና ግለኝነት የራቀው ሀበሻዊ ስነ ልቦናው በራስ ወዳድነት የተካ መንፈሳዊ ኮብላይ እንጂ ሌላ ሊሆን አይችልም።
እዚህ አገርህ ላይ ያለው ደግነት መልኩ ሌላ ነው። ኢትዮጵያዊ የሆነው መልካምነት ባህሪይ የሚገለፅበት በሰጥቶ መቀበል መርህ ሳይሆን የራስን ለሌሎች በመስጠት የሚገለፅ ነው። ከራስ ወዳድነት ፍፁም የራቀ ከግለኝነት ራስ ወዳድነት የተላቀቀ እውነተኛ ወዳጅነት የሚንፀባረቅበት አብሮነት የሚጎልበት ማህበራዊ ትስስር እጅጉ የሚታይበት እውነተኛ መልካምነት ነው። መልካም የሆነ መልካምነት።
አገርህ ላይ ያለው መልካምነት ግን ከዚያ እጅጉን ልዩ ነው። አዎን አበሻ ደም ላይ ያለ መልካምነት ከራስ ጋር የተሰራ ስብዕና ከማንነትና ከስነ ልቦና ጋር የተጋመደ ሰዋዊነት ነው። ካንተ ለማግኘት ብሎ አያዝንልህም፤ ጥቅም ስለሚያገኝብህ ብቻ አይረዳህም። ሳያውቅህ ያንተ እንደራሱ ስቃይህ ያመዋል። ክፉ ነገር ሲገጥምህ አለውልህ ይልሃል። ኢትዮጵያዊ ደግነት በጥቅም ላይ ያልተመሰረተ በሰጥቶ መቀበል መርህ ላይ ያልተንጠለጠለ ነው የምልህ በምክንያት ነው።
በደስታህ ጊዜ ቀርቦ ድግስህን ያደምቃል፤ በሀዘንህ ተሰባስቦ ሀዘንህ እስኪያልፍ ያበረተሀል መከፋትህ እንዳይፀና አብሮ አልቅሶ እንባህን ያብሳል። ልጅ መውለድ የአንተ ሀላፊነት ሊሆን ይችላል ማሳደጉ ግን የአካባቢህ ሰው ሁሉ ሀላፊነት ይሆናል። ልጅ ስጠፋም ምንአገባኝ ብሎ አይተውም። እንደ ልጁ ገስፆና እንደ ታናሹ መክሮ ይገራልሀል። መልካም ነገሩን አይቶ ያሳድግህ ብሎ ይመርቅልሀል። ስኬቱን ተመልክቶ እሰይ..እሰይ ብሎ ያበረታሃል።
ኢትዮጵያዊ በክፉ ቀን ተደጋግፎ በደጉ ቀን ተመራርቆ አብሮነቱን የሚያፀና መነጣጠልን የሚያወግዝ መተባበርና መረዳዳት ባህሉ ያደረገ ማንነት ነው። በመልካምነት የሚደገፍ ፍቅር፤ በመተሳሰብ የደረጀ አብሮነት የሚንፀባረቅበት ማህበራዊነት ነው። በአብሮነት እልልታ የሚያደምቅ በመተሳሰብ ኡኡታን የሚገታ። መልካምነት የኢትዮጵያዊ እውነተኛ መገለጫ ነው። ማህበራዊ ስሪቱና ስነ ልቦናዊ መርሁ ነው የምለው ለዚያ ነው።
ይህ መልካምነት እንዲሁ አልተገኘም። መልካም የሆኑ አባቶች የዘሩት መልካም ፍሬ እንጂ። መልካምነት ካልጠበቁት የሚረግፍ ጣፋጭ ፍሬ ካልተላመዱት የሚቀየር ባህሪ ነው። ኢትዮጵያዊ መልካምነታችን ሀበሻዊ ጨዋነታችን መጠበቅ ብሎም ማዝለቅ ደግሞ የእኛ ሀላፊነት ነው። ኢትዮጵያዊ መልካምነት የመደጋገፍና የአብሮነት ትስስሩ ማጥበቅ ንፁህ የሆነውንና ምላሽ የማይጠብቀው መልካምነት መላበስ ይገባናል።
ሰው ውጫዊ የሆነ ተፅዕኖ ከመልካምነት መንበሩ ካላወረደው በቀር በተፈጥሮው አዛኝ ሩህሩህና መልካም ነው። መልካም በመሆን የሚገኘው መንፈሳዊ እርካታ በየትኛው ተግባርና እሳቤ ውስጥ ሊላበሱት አይችሉም። የሰው ልጅ ከሌላው እንስሳ የሚለየው በውስጡ ያለ የርህራሄ ወይም ሰዋዊ ባህሪና በጎ ስሜቱ ነው። በየትኛውም ፍጥረት ውስጥ ከሚታየው መልካምነት ከፍ ያለ በጎ ተግባር የሰው ልጆች ሲከውኑት ታያለህ።
የክረምቱ ጭጋግ በብርሃን ሊለወጥ ያረጀው ዘመን ወደ አዲስነት ሊሸጋገር፤ ይሄው ቀጠሮው ደርሶ መስከረም ሊጠባ ሶስት ቀን ብቻ ቀረው። መልካም አዲስ ዓመት ልንባባል እንኳን አደረሳችሁ አደረሰን የሚሉ መልዕክቶችን ልንለዋወጥ በዝግጅት ላይ ነን። የዘመን ሽግግሩ ኢትዮጵያዊ መልካምነታችን የሚንፀባረቅበት አብሮነታችን የሚጠብቅበት ይሆን ዘንድ መልካሙን እናልም። አዲሱ ዘመን መልካም እንዲሆንልን የተለመደው ኢትዮጵያዊ መልካምነታችን ላይ እንፅና። ኢትዮጵያ መልካም እንድትሆን ህዝቦችዋም መልካምነት ማደሪያቸው እንዲሆን መልካም ነገርን እንመኝ። መልካም ሀሳብ ብሩህ ዘመንን ይወልዳል። አበቃሁ፤ መልካሙን ያሰማን።
ተገኝ ብሩ
አዲስ ዘመን ጳጉሜን 3/2013