የጥላቻ ንግግሮች በአንድ ሰው ወይም በቡድኖች ላይ ጥላቻን፣ ዓመፅን እና መድልዎን የሚደግፉ፣ የሚያነቃቁ፣ የሚያስተዋውቁ ወይም የሚያጸድቁባቸውን በርካታ መግለጫዎችን እንደሚያካትት የአውሮፓ ህብረት ምክር ቤት ያወጣው መረጃ ያሳያል። የጥላቻ ንግግር ለዴሞክራሲያዊ ኅብረተሰብ ውህደት፣ ለሰብዓዊ መብቶች ጥበቃ እና ለሕግ የበላይነት ከባድ አደጋዎችን እያስከተለ ይገኛል።
ካልታሰበበት እና መፍትሄ ካልተፈለገለት በሰፊ ደረጃ ወደ ሁከትና ግጭት ድርጊቶች ሊያመራ ይችላል። በዚህ መሠረት የጥላቻ ንግግር ለጥላቻ ወንጀል አስተዋጽኦ ያለው እንዲሁም በቡድኖች እና በግለሰቦች መካከል አለመቻቻል እንዲሰፍን የሚያደርግ ነው። በጥላቻ ንግግር እና በአመፅ መካከል ያለውን አደገኛ ትስስር በመገንዘብ፣ የጥላቻ ንግግር በግለሰቦች ወይም በተወሰኑ ቡድኖች ላይ ጥቃትን ሳያነሳሳ የመከላከል ስራ ሊሰራበት ይገባል።
ይህንን በመገንዘብ ችግሩን ቀድሞ ለመከላከል ጥረት የሚያደርጉ ቢኖሩም በተለይም የማህበራዊ ሚዲያዎችን መስፋፋት ተከትሎ ችግሩን ለመቅረፍ የሚደረገው ጥረት የሚፈለገውን ውጤት እያስገኘ አይደለም። በተለይም የማህበራዊ ድረ ገጾች ተጽዕኖ እና ተደራሽነት እየሰፋ መምጣትን ተከትሎ የጥላቻ ንግግሮች ስርጭትን በሰው አቅም ለመከላከል የሚደረገውን ጥረት አዳጋች አድርጎታል። እነዚህን ተግዳሮቶች ለመቅረፍ እና ሰዎችን ለብጥብጥ ከሚያነሳሳ እና የኩባንያውን የጥላቻ ንግግር ፖሊሲ የሚጥስ ይዘትን በተሻለ ሁኔታ ለመከላከል ፌስ ቡክ አዲስ ዘዴ ይዞ ብቅ ብሏል።
የጥላቻ ንግግር ስርጭትን ለመግታት ሰው ሰራሽ አስተውሎት ስርዓቶችን በፌስቡክና ኢንስተግራም ላይ ተግባራዊ ማድረጉን የፌስ ቡክ ኩባንያ ይፋ አድርጓል። ከቀደሙት ጊዜያት በተሻለ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸውን የጥላቻ ንግግሮች እና ሌሎች አላስፈላጊ ይዘቶች ስርጭትን ለመቀነስ ሪኢንፎርስሜንት ኢንቴግሪቲ ኦፕቲማይዘር (አር አይ ኦ) የተሰኘ የሰው ሰራሽ አስተውሎት ስርዓት ተግባራዊ መሆኑን ዜድ ዲ ኔት ላይ የወጠው መረጃ አመላክቷል።
ይህ ስርዓት አ.አ.አ በ2020 መገባደጃ ላይ ስራ የዋለ ሲሆን ኩባንያው የጥላቻ ንግግሮችን በንቃት እንዲለይ እያገዙት ይገኛል። የአር አይ ኦ መሰረታዊ ዓላማው እና ዋነኛው ትኩረት አድርጎ የሚሰራው የማህበራዊ ሚዲያዎቹ ተጠቃሚ ሰዎች የጥላቻ ንግግር ይዘት ያላቸውን መረጃዎችን እንዳያዩ መከላከል ሲሆን፤ ይህ ስርዓት ከሌሎች ተመሳሳይነት ካላቸው ስርዓቶች ጋር በመቀናጀት የተሻለ ውጤት ከማስመዝገባቸው ባሻገር ተጨባጭ ለውጦችንም እያመጡ ናቸው ይላል።
የጥላቻ ንግግሮችን ለመከላከል ስራ ላይ የዋለው የሰው ሰራሽ አስተውሎት ሞዴል የተለያዩ ተግባራትን መፈጸም የሚችል ሲሆን ከነዚህ መካከል አንድ ንግግር የጥላቻ ንግግር ወይም የአመፅ ቀስቃሽ መሆኑን ይተነብያል፣ ከዚያም እርምጃ አንድ እርምጃ መወሰድ እንዳለበት ይወስናል።
ለምሳሌ በማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ የተለጠፈውን መሰረዝ ካለበት ይሰርዛል፣ ማውረድ ካለበትም ያወርዳል፤ በባለሙያ መገምገም ያለበት ከሆነም እንዲገመገም ወደ ባለሙያ ይልካል። ይዘት ላይ ትኩረት አድርገው የሚሰሩ ቡድኖች የስርዓቱን አጠቃላይ ውጤታማነት መገምገም እና ትንበያ ማሻሻል ላይ ብቻ ትኩረት አድርገው የሚሰሩ ይሆናል።
ዜድ.ዲ ኔት የተሰኘ ድረ ገጽ ላይ የወጣው መረጃ እንደሚያሳየው፤ በዚህም አመርቂ ውጤት እየተመዘገበ ነው። በአውሮፖያዊያኑ 2021 ሶስተኛ ሩብ ዓመት 31 ነጥብ አራት ሚሊየን ይዘቶች ላይ እርምጃ በመውሰድ እንዲወገድ ተደርጓል። በመጀመሪያው ሩብ ዓመት ከተወገዱት 25 ነጥብ ሁለት ሚሊየን የጥላቻ ይዘቶች አንጻር ሲታይ የስርጭት መጠኑን መቀነስ አስችሏል።
የማህበረሰብ ደረጃዎች ማስፈጸሚያ ዘገባ ፌስቡክ እ.አ.አ በ2021 ሁለተኛው ሩብ ዓመት የጥላቻ ንግግር ስርጭት በተከታታይ ለሶስተኛ ሩብ መቀነሱ የተመላከተ ሲሆን፤ ይህ የሆነው በፌስቡክ ዜና ምገባ ውስጥ የጥላቻ ንግግሮችን በንቃት በመለየት እና የደረጃ ለውጦችን በማሻሻሉ ምክንያት ነው።
በሁለተኛው ሩብ ዓመት ውስጥ ለእያንዳንዱ 10 ሺህ የይዘት እይታዎች የጥላቻ ንግግር አምስት ዕይታዎች እንደነበሩ ሪፖርቱ አመልክቷል። ያ በአንደኛው ሩብ ዓመት ውስጥ በ10 ሺህ እይታዎች ከአምስት እስከ ስድስት እይታዎች መቀነሱን አመላካች መሆኑን ፌስቡክ ዋናው የቴክኖሎጂ ኦፊሰር ማይክ ሽሮፔፈር ተናግረዋል።
የጥላቻ ንግግሮችን የማስወገድ ተግባር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣ ሲሆን መተግበሪያው በስራ ላይ ከዋለ በኋላ የጥላቻ ንግግሮችን የመለየት እና የማስወገድ ስራ በ15 እጥፍ ከፍ ብሏል። በዚህም የጥላቻ ንግግሮች ተጠቃሚዎች ጋር እንዳይደርስ መከላከል እየተቻለ ነው። ይህ ተግባር ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ዋናው የቴክኖሎጂ ኦፊሰር አረጋግጠዋል።
ከጥላቻ ንግግሮ ባሻገር ከኮቪድ 19 ጋር ግንኙነት ያላቸው ይዘቶችንም ለመከላከል እገዛ እያደረገ መሆኑ የተጠቆመ ሲሆን በሶስተኛው ሩብ ዓመት ከCOVID-19 ጋር በተዛመደ የተሳሳተ መረጃ ላይ ፖሊሲዎቹን በመጣሱ በዓለም ዙሪያ ከ20 ሚሊዮን በላይ ይዘቶችን ከፌስቡክ እና ከኢንስታግራም ማስወገዱንም ጠቁሟል። COVID-19ን የክትባት የተሳሳተ መረጃን በተደጋጋሚ ህጎቹን ስለጣሱ ከሶስት ሺህ በላይ መለያዎችን፣ ገጾችን እና ቡድኖችንም ማስወገዱን ነው የጠቆመው።
ቴክኖሎጂው በቢሊዮኖች የሚቆጠሩ የማህበራዊ ሚዲያዎች ተጠቃሚዎች የፌስቡክ ስታንዳርዶችን እንዳይጥሱ ለመከላከል ከማስቻሉም ባሻገር መተግበሪያው በበርካታ ቋንቋዎች አገልግሎት የሚሰጥ በመሆኑ ፌስ ቡክ በበርካታ ቋንቋዎች ፖሊሲውን እንዲያስከብር እየረዳ መሆኑም ነው የተገለጸው።
ከዚህ ቀደም የነበሩት ስርዓቶች ከበይነ መረብ ግንኙነት ውጭ በውስን ዳታ ይሰለጥኑ እንደነበር የጠቀሰው መረጃው፤ አዲሱ ስርዓት በተቃራኒው አሁናዊ በሆኑ በትስስር ድረ- ገጹ ላይ ከሚወጡ ይዘቶች የመማርና ስራውንም ራሱ የመገምገም ሂደት በመከተል አላስፈላጊ ይዘቶች በተጠቃሚዎች ከመጠቆማቸው በፊት እርምጃ ለመውሰድ እያስቻለ መሆኑ ተገልጿል።
ፌስቡክ ዋናው የቴክኖሎጂ ኦፊሰር ማይክ ሽሮፔፈር ለሪፖርተሮች በሰጡት መግለጫ እንዳብራሩት፤ ሰው ሰራሽ አስተውሎት በማይታመን ሁኔታ በፍጥነት እያደገ እና እየተለወጠ ያለ መስክ ነው፣ ዛሬ አብዛኛዎቹ የሰው ሰራሽ አስተውሎት ስርዓቶች በጣም አስፈላጊ ክፍሎች እንደ ራስ ቁጥጥር ባሉ ቴክኒኮች ላይ የተመሰረቱ ናቸው።
የሰው ሰራሽ አስተውሎት (አርቴፊሻል ኢንተሊጀንስ) ሥርዓቶች የሰለጠኑትን መረጃ ያህል ብቻ ጥሩ መሆናቸውን የሚያብራሩት ማይክ ሽሮፔፈር የጥላቻ ንግግሮችን ለመቋቋም የሚያስችሉ መሳሪያዎች በሚገነቡበት ጊዜ ይህ በተለይ እውነት እና አስፈላጊ ነው። የጥላቻ ንግግር ከሀገር ወደ ሀገር አልፎ ተርፎም ከቡድን ወደ ቡድን ይለያያል።
በአንድ ሀገር የጥላቻ ንግግር ተደርጎ የሚወሰድ በሌላ ሀገር የጥላቻ ንግግር ላይሆን ይችላል። በአንድ ቡድን ዘንድ የጥላቻ ንግግር ተደርጎ የሚወደሰው በሌላኛው ቡድን ዘንድ እንደ ጥላቻ ንግግር ላይቆጠር ይችላል። እናም የጥላቻ ንግግሮች ወቅታዊ ክስተቶችን ወይም አዝማሚያዎችን መሠረት በማድረግ በፍጥነት ሊዳብር ይችላል።
ሰዎች እንዲሁ የጥላቻ ንግግሮችን በአሽሙር እና በንግግር፣ ሆን ብለው በተሳሳተ ፊደል እና በተራቀቁ የፎቶ ሾፖች ለማስመሰል ይሞክራሉ። እና የጥላቻ ንግግሮችን ለመከላከል የሚዘጋጁ ውጤታማ መሣሪያዎች ችግሮችን መፈለግ ብቻ ሳይሆን ስህተቶችን ማስወገድ አለባቸው። የሐሰት አዎንታዊ አንድ ሰው ከጓደኞቹ ወይም ከማህበረሰቡ ውስጥ ከሌሎች ጋር እንዳይግባባ እና እንዳይገናኝ ሊያግደው ይችላል።
አር አይ ኦ የጥላቻ ንግግሮችን ለመለየት በየትኛውም ቦታ ስራ ላይ ሊውል የሚችል ማዕቀፍ ነው። በዓለም ላይ በርካታ ተገልጋዮች የሚጠቀሙባቸው ፌስቡክ እና ኢንስታግራም ላይ የሚለጠፉ ይዘቶች በሙሉ በራስ አቅሙ የሚገመግም እና የጥላቻ ንግግር ምደባዎችን ለማመቻቸት የሚያገለግል ነው።
እነዚህ ስርዓቶች እንዲህ በአጭር ጊዜ እውን ይሆናሉ ተብለው የማይታሰቡ ነበሩ ያሉት ማይክ ሽሮፔፈር የፌስቡክ ሰው ሰራሽ አስተውሎት ስርዓቶች የፌስቡክ የማህበረሰብ ደረጃዎችን በማስከበር ረገድ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ግለሰቦች የሚሰሩትን ስራ እየሰሩ ይገኛሉ ብለዋል።
ሪኢንፎርስሜንት ኢንቴግሪቲይ ኦፕቲማይዘር (አር አይ ኦ) በማስፋፋት የጥላቻ ንግግሮችን ብቻ ሳይሆን ሌሎች ጎጂ ይዘቶችን ለመቋቋም እና ይህን ጎጂ ይዘቶችን ለመከላከል ጥረት ለሚያደርጉት የተለያዩ ማበረታቻዎችን በማቅረብ መሰል ችግሮችን ከምንጩ ለማድረቅ የመስራት እቅድ እንዳለው ያብራራው የፌስቡክ መግለጫ፤ ይህም በሰዎች ህይወት ላይ ተጨባጭ ለውጥ ለማስመዝገብ እንደሚያስችል ገልጿል።
ሰው ሰራሽ አስተውሎት ብዙ ዓይነት የጥላቻ ንግግር ጥሰቶችን፣ ፈጣን እና በበለጠ ትክክለኛነት ለመለየት እያስቻለ መሆኑን የጠቆመው ፌስ ቡክ፤ አሁንም ቢሆንም የጥላቻ ንግግሮች የሚያስከትለውን አሉታዊ ጫናዎችን ለመቋቋም እንደኩባንያ ብዙ የሚሰራው ሥራ መኖሩን ጠቁሟል።
የፌስ ቡክ ቴክኖሎጂ በአንጻራዊ ሁኔታ በአጭር ጊዜ ውስጥ ብዙ ተሻሽሏል፤ በቀጣይም የፌስ ቡክ እና የኢንስተግራም ምርቶችን የሚጠቀሙ ሰዎች የጥላቻ ንግግሮችን እንዳያሰራጩ ለመከላከል እና ለመጠበቅ ሰው ሰራሽ አስተውሎትን ለመጠቀም አዳዲስ መንገዶችን መፈለጉን እንደሚቀጥልም ፌስ ቡክ አብራርቷል።
የጥላቻ ንግግርን በመዋጋት እና በሌላ በኩል የመናገር ነፃነትን በመጠበቅ መካከል ሚዛን መጠበቅ ስላለበት በጥላቻ ንግግር ላይ የሚደረጉ ማናቸውም ገደቦች በቁጥር አናሳ ቡድኖችን ዝም ለማሰኘት እና በኦፊሴላዊ ፖሊሲዎች፣ በፖለቲካ ተቃዋሚዎች ወይም በሃይማኖታዊ እምነቶች ላይ ትችቶችን ለማስፈን አላግባብ ጥቅም ላይ እንዳይውልም ከፍተኛ ጥንቃቄ መደረግ እንዳለበት ተጠቁሟል።
መላኩ ኤሮሴ
አዲስ ዘመን ጳጉሜ 2/2013