ኢትዮጵያ የምትባል ሀገር ነበረች፤ አሁንም አለች፤ ወደፊትም የምትቀጥል ይሆናል። ይህ እውነታ ያልተዋጠላቸው ጥቂት ግለሰቦች ቡድን በማቋቋም ላለፉት አርባ ዓመታት ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊነትን ለማጥፋት ሲንቀሳቀሱ ቆይተዋል።
መጨረሻቸው ባይምርላቸውም በተለይ ባለፉት ሃያ ሰባት ዓመታት በግልጽ «ኢትዮጵያዊ የሚባል ማንነት» የለም በማለት ህዝቡን ለተለያዩ በሀሰት ለተፈጠሩ ግጭቶች ሲዳርጉት ቆይተዋል። ዛሬ ግን በዓይናችን እንደምናየው ጊዜው ቢረዝምም የተከፈለው መስዋእትነት ተከፍሎ በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያዊነት እያሸነፈ መጥቷል። ይህ ተቀብሮ አልቀር ያለው በኢትዮጵያዊ ማንነት ስር የሚገኝ የአሸናፊነት ስነልቦና እንዴት ተፈጠረ ስንል በደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ የሳይኮሎጂ ትምህርት ክፍል መምህር የሆኑትን አቶ ስንታየሁ አምባቸውን አነጋግረን የሚከተለውን ይዘን ቀርበናል።
አቶ ስንታየሁ እንደሚያብራሩት ኢትዮጵያ ከሰለጠኑት ሀያላን ሀገራት መካከል ጠንካራ የሆኑትን ማሸነፍ የቻለችው ኢትዮጵያዊ የሚባል ማንነት ስለነበረ ብቻ ሳይሆን ህዝቡ ከጫፍ እስከ ጫፍ ያምንበትም ስለነበረ ነው። ይህ የኢትዮጵያዊነት የአሸናፊነት ስነ ልቦና ደግሞ በኢትዮጵያ ስር ላሉ ህዝቦች ቀዳሚው የመሰባሰቢያ ጥላቸው ነበር። በየወቅቱ እንደ ሀገር የተገኙት ድሎችም የሁሉም ኢትዮጵያዊ ተሳትፎ የነበረባቸው ናቸው። ዛሬ ያለው እያንዳንዱ ዜጋም አሁን ያለችውን ኢትዮጵያ የተቀበላት ቅድም አያቶች ነፍስና ስጋ ከፍለው ባቆዩለት መስዋእትነት ነው።
ለዚሀ እንደማሳያ ከሚጠቀሱት መካከልም የዓድዋ ጦርነት ቀዳሚውና ፈር ቀዳጁ ነው። የዓድዋ ጦርነት በአመራርም ኢትዮጵያውያን መሪዎች በአሸናፊነት ስነ ልቦና የተቃኙ መሆናቸውን ያሳየናል። ለዓድዋ ዘመቻ ንጉሱ አጼ ምኒልክ ጥሪ ሲያደርጉ የተናገሩት አዋጅ ለዚህ አንዱ ማሳያ ነው «የሀገሬ ህዝብ ሆይ ተሰባስበህ በጥቅምት ወር ወረኤሉ ከተህ እንገናኝ» ሲሉ የለዩት ብሄር ጎሳ አልነበረም።
ኢትዮጵያውያንም ጥሪውን ተቀብለው ከሁሉም አቅጣጫ ዘምተው በህብረት ጠላትን ድል ማድረግ ችለዋል። በመሰረቱ ጠላት በኢትዮጵያውያን ሲሸነፍ የኖረው ኢትዮጵያውያን የተባባረ ክንድ ስለነበራቸው እንጂ ከኢትዮጵያ ውስጥ በአንድ የተወሰነ ማህበረሰብ ተሳትፎ ብቻ አልነበረም። እነዚህን ኢትዮጵያውያንን ያሰባሰባቸው ደግሞ በኢትዮጵያ ጥላ ስር ያለው ኢትዮጵያዊ ማንነት ነው።
ግብጾች፤ ድርቡሾችና እንግሊዞች ጋር የነበረን ግንኙነት ሁሉ ይህንን የአሸናፊነት ታሪካችንን የሚያዘክር ነው። የማይጨው ጦርነትም በሀይል መበለጥ ኢትዮጵያ ባታሸንፍም የተከፈለው መስዋእትነትና የነበረው ሂደት ግን ከጅምሩ የኢትዮጵያዊያንን አሸናፊነትና ህብረት ያንጸበረቀ ነበር። ለዚህ የሩቁ ብቻ ሳይሆን የቅርቡ የካራ ማራ ድልም አንዱ ማሳያ ነው። በዚህም እስከ ቅርብ ጊዜ እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ በአስተሳሰቡ በሞራሉና በምግባሩ ኢትየጵያዊነትንን የሚረዳው በአሸናፊነት ስነልቦና ውስጥ ነበር። ይህም በጦርነት ሜዳ ብቻ ሳይሆን በስፖርቱም ዓለም ገኖ የወጣ ነበር። አንድ አትሌት በዓለም አቀፍ መድረኮች ውድድር አሸንፎ ባንዲራ ሲያነሳ በመላው ኢትዮጵያ ውስጥ አሸናፊነትን ይዘራል። ሁሉም በአንድ ልብ ሲደግፈውም ይታያል።
እነዚህ ሁሉ የሚያሳዩን አሸናፊነት በኢትዮጵያውያን ታሪካዊ ስነ ልቦና « ሳይኮ-ሂስትሪ» ውስጥ አብሮ የኖረና አሁንም ያለ ወደፊትም የሚቀጥልም መሆኑን ነው። ይህንን ደግሞ ኢትዮጵያዊ የሚባል ህዝብ ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያዊ የሚባል ማንነት መኖሩን ኢትዮጵያን የሚደግፉት ብቻ ሳይሆኑ የማይወዷትም በታሪካቸው ሰንደውታል።
ይህ እውነታ እንደተጠበቀ ሆኖ በታሪክ አጋጣሚ የተከሰቱና እውነታን መሸከም የሚፈሩ የራሳቸውም ማንነት የተዛባባቸውና የተጋጨባቸው ኢትዮጵያዊ ማንነት የለም ብለው አውጀው ነበር። እነዚህ ባገኙት አጋጣሚ የራሳቸውንና የጥቂቶችን ፍላጎት ለማሳካት ኢትዮጵያዊ የሚባል ማንነት የለም ሲሉ የነበሩ አካላት ችግር ሲገጥማቸው መደበቂያ ያደረጉት ግን ኢትዮጵያዊነትን ነበር። ለዚህ ዋነኛው ማሳያ የኢትዮ ኤርትራ ግጭት ነው። ህወሓቶች ከኤርትራ ጋር የነበራቸውን ቅራኔ የተሻገሩት በኢትዮጵያ ጥላ ስር ነበር። በቅርቡ ችግሩን ለውጡ እስኪፈታውም መደበቂያቸው የነበረው ኢትዮጵያዊነት ነበር።
በወቅቱ የነበሩት የወያኔ መሪዎችም ከኤርትራ ጋር የነበራቸውን ችግር ለመፍታት ኢትዮጵያዊ የሚባል ማንነት መኖሩን በስፋት ሲሰብኩ ነበር። እዚህ ላይ ልብ ሊባል የሚገባው እነዚህ አካላት በአስራ ዘጠኝ ስልሳዎቹ ሲያቀነቅኑት የነበረውና በአስራ ዘጠኝ ስልሳ ስምንት የጻፉት ማኒፌስቶ ተቀባይነት ይኑረው ሲሉ ለሺ ዘመናት የኖረውን ኢትዮጵያዊነት ሊሽረው እንደማይችል እነሱም ራሳቸው ይገነዘቡት እንደ ነበር ነው።
እነዚህ አካላት ላለፉት ሃያ ሰባት ዓመታት በከፍተኛ ደረጃ ህዝብን በመከፋፋል ኢትዮጵያዊነትን ለማጥፋት ሲሰሩ ነበር። ይህንንም አድርገው በተወሰነ ደረጃ ተቀባይነት ሊያገኙ የቻሉት ጊዚያዊ ልዩነቶችንና ጊዜያዊ ጥቅሞችን በማጉላት ነበር። ነገር ግን በእለታዊ መኳረፍ፤ በአካባቢያዊ ግጭትና በጊዜያዊ ልዩነት ውስጥ የተወሰነ ክፍተት ቢኖርም ኢትዮጵያዊ ማንነትን ሊነካ የሚችል አይደለም። ለዚህም ነው በአሁኑ ወቅት ከሁለት አስርት ዓመታት በኋላ በተግባር ኢትዮጵያዊነት እያሸነፈ ለመምጣት የበቃው።
በሌላ በኩል ዓለም ኢትዮጵያዊ ብሎ በአንድ ማንነት መድቦ የሚያውቀን ህዝቦችም ነን። በተጨማሪ የፖለቲካ የኢኮኖሚያዊና የመልክዓ ምድር ብቻ ሳይሆን አንድ ሀገራዊ ስነ ልቦናዊ ማንነት ያለን ህዝቦች ነን። በተግባር እንደምናየው የማህበረሰቡም ስነ ልቦና ስሪትና እሴቱም እስካሁን እንዳለ ነው። ወደፊትም እያሸነፈ የሚቀጥል ይሆናል። ይህ የሚሆነው ደግሞ ኢትዮጵያ ስታሸንፍ የሚያሸንፈው፤ ስትሸነፍ የሚሸነፈው አንድ ቡድን ብቻ ሳይሆን መላው ኢትዮጵያዊ በመሆኑ ነው ።
ራስወርቅ ሙሉጌታ
አዲስ ዘመን ጳጉሜ 2/2013