ዛሬ የአገልጋይነት ክብር ቀን ነው። ማገልገል ደግሞ ክብር ነው። በየትኛውም የስራ ዘርፍ ላይ ሆነው ሃገራቸውን በተለያዩ የሙያ ዘርፎች ያገለገሉ ዜጎች ይህ እለት ይመለከታቸዋል፤ ክብርም ይሰጣቸዋል።
የኢትዮጵያ የበጎ ሰው ሽልማት ድርጅትም ዘጠነኛውን ሽልማት ባለፈው እሁድ በአስር ዘርፎች አበርክቷል። ከነዚህ ዘርፎች መካከል ደግሞ በመምህርነት ዘርፍ እና መንግስታዊ የሥራ ኃላፊነትን በብቃት መወጣት ዘርፍ ይጠቀሳሉ። እናም የአገልጋይነት ክብር ቀንን መነሻ በማድረግ በነዚህ ዘርፎች የተሸለሙ የሁለት ኢትዮጵያውንን ግለታሪክና ስራ ልናስቃኛችሁ ወደድን፤ መልካም ንባብ።
በመምህርነት ዘርፍ
በዚህ ዘርፍ የቀረቡት ሶስት ምሁራን ናቸው። እነሱም ፕሮፌሰር ጥሩሰው ተፈራ፤ ዶክተር ልዑልሰገድ ዓለማየሁ እና ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ ናቸው። እነዚህ ምሁራን ረጅም የስራ ዘመን አገልግሎት ያላቸው ሲሆን በሙያቸውም ሃገራቸውን በማገልገል ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረከቱ ናቸው። ከነዚህ ውስጥ ደግሞ የዓመቱን የበጎ ሰው ሽልማት ያሸነፉት ዶክተር ልዑልሰገድ ዓለማየሁ ናቸው።
የዶክተር ልዑልሰገድ አለማየሁ የኋላ ታሪክ በአጭሩ
በደፋሪዋ ጣሊያን ወረራ ምክንያት ተቋርጦ የነበረውን የሀገራችንን ዕድገት ከ1933ቱ ነፃነት በኋላ ታይቶ በማይታወቅ፣ ለማስረዳትም በሚያቅት መንፈስና መነሣሣት፣ እንዴት በሚያሰኝ አርበኛዊ ስሜት ሀገራችንና ሕዝቦችዋን መልሶ ማንሳትና መገንባት በሁሉም፣ በልጆችም ሆነ በአዋቂዎች፣ በወንዶችም ሆነ በሴቶች ኢትዮጵያውያን ሁሉ ሁለንተናዊ ልብና ሰውነት ውስጥ ነበር። ለዚህም ክንፍ አውጥቶ ለመብረር የሚረዳው አስፈላጊ ነገር ዘመናዊ ትምህርት መሆኑን በመገንዘብና፤ ይህንኑ በሠፊው፣ ለሁሉም የሀገራቸው ሰዎች ለማዳረስ፣ በአውሮፓ ያዩትን፣ የሰሙትንና ያጠኑትን ዘመናዊ ሥልጣኔ በሀገራችን እንዲያብብ ለማድረግ ግርማዊ ንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ፣ ከፊት ለፊት ሆነውና፣ ራሳቸው የትምህርት ሚኒስትርነቱን ኃላፊነት አንግበው በእምርታ የወገኖቻቸውን መማር ማደግና መበልጸግ በአስፈላጊው የሥልጣኔ ምጥቀት በመምራት አሳድገውናል።
በዚያን ጊዜ የመማሪያና የማስተማሪያ መጻሕፍቱ በቤተ ክርስቲያን ታዛ ሥር በየኔታ መሪነት ማስተማሪያ ከነበረው ተስፋ ገብረሥላሴ በቁጭት ተሞልተው በመነሳሳት፣ የሌለን ትምህርት ሁላችንም እንዲኖረን በማሰብ፣ በገፍ ማዘጋጀት ከጀመሩት ፊደል፣ አቡጊዳ፣ ወንጌልና ሌሎችም የፀሎት መጻሕፍት ውጭ በተለያዩ የዕድሜ ክልል ውስጥ ለነበሩት ሕፃናት በዕድሜና ደረጃ የተመዘነና የተመጣጠነ ዝግጅት አልነበረም።
ታዋቂው ደራሲ ክቡር ዶክተር ከበደ ሚካኤልም ያዘጋጇቸው መጻሕፍትም ቢሆኑ፤ በማንኛውም ዕድሜ ለሚገኝ ተማሪ በይድረስ ይድረስነት ያቀረቧቸው፣ ደረጃ ያልነበራቸው፣ ታሪክና ምሳሌዎቻቸውና ሌሎችም በዚሁ ዓይነት የተዘጋጁ ነበሩ። በደረጃቸው የተመጠኑ ባይሆኑም የክቡር ዶክተር ከበደ ሚካኤል መጻሕፍት ለወቅቱ ችግር መፍቻ ሆነው በሠፊው ሊታሰብ በማይቻል ሁኔታ ተፈቅረውና ተናፍቀው አገልግለውናል።
ጊዜው የመልሶ ማቋቋምና ሀገርን በሥር ነቀልነት ከመሬት አንስቶ የመገንባት፣ መምህራንን ለአንደኛም ሆነ ለሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ከውጭው ዓለማት የመቅጠርና ትምህርትን ለዜጎች በማዳረስ ኢትዮጵያችንን መልሶ የመገንባቱ አጣዳፊ ጊዜ ነበር። በጊዜው ያገኘናቸው መጻሕፍት ሁሉም ከጊዜውና ከተማሪዎች ዕድሜና ሕይወት ጋር ያልተሳሰሩ፣ ለየዕድሜው ክልል ሕፃናት ዕውቀትን ለመስጠትና ክሕሎትን ለማዳበር የቀረቡ ባይሆኑም፤ በጊዜው በኔ ዕድሜ ለነበርነው ሁሉ በፍቅር ተምረንባቸው በማደግ በኋላም አስፈላጊውን ለውጥና ዝግጅት ለተከታይ ትውልድ ለማስተላለፍ ላደረግነው ከፍተኛ ጥረትና ርብርብ ጠቅመውናል።
ሆኖም ማንኛውም ዕርዳታ ከየትኛውም አቅጣጫ አሜን ተብሎ በሚተገበርበት በዚያን ጊዜ ለሀገራችን ኢትዮጵያ መሠረታዊ የሥልጣኔ ድጋፍና ዕርዳታን ለመስጠት፤ በ1940ዎቹ ውስጥ የአሜሪካን መንግሥት አሉ የተባሉ ምርጥ የየሥልጣኔው ዘርፍ አዋቂዎቻቸውን ሐዋርያዊ መሪዎች እንዲሆኑን በገፍ ወደ ሀገራችን የላኩበት ዘመን ነበር፤ ውለታቸውም መዘንጋት የሚቻል አይደለም።
እነዚህም የየሙያው ሊቆች በየተቋቋመውና መቋቋም በሚኖርበት መንግስታዊ የዕድገትና አገልግሎቶችና ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች ጎን በመሰለፍና በብዛት በመሳተፍ የሥልጣኔ ግንባታ መረቦችን ዘረጉ። የሚታወቁትም ‹‹ፖይንት ፎር›› በመባል ሲሆን፤ በእያንዳንዱ መንግሥታዊ ተቋምን ተግባር ይለዩ ነበር።
በትምህርት ሚኒስቴር ጎን የተዋቀሩት ‹‹ፖይንት ፎር ኤጁኬሺን›› ተብለው ሙያዊ የሆነውን የትምህርት አገልግሎት፣ እንደ ምርምርና ጥናት ሂደትን፣ በዚያም ላይ በመመርኮዝ የመማሪያ መጻሕፍት ዝግጅት ሕትመትና ሥርጭትን፣ ለአንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ተማሪዎች ወርሃዊ የማንበብ ጊዜ በሚል ርዕስ በአማርኛ፣ ለሁለተኛ ደረጃ ደግሞ ‹‹ታይም ቱ ሪድ›› በሚል ርዕስ በእንግሊዝኛ መጽሔቶችን ማዘጋጀት፣ ማሳተምና በመላ ሀገሪቱ ትምህርት ቤቶች ማሠራጨትን ተግባራዊ አደረጉ።
እነዚህም ለትምህርቱ ዕድገት ሥራ የተላኩት የአሜሪካ ሐዋርያት የኢትዮጵያ ትምህርት እንዲስፋፋ፣ ለሚቀጥሉት ዓመታት ሂደትም የሀገሪቱን ዕቅድ ከመተንበይ ጋር ተያይዞ በዕድሜና በደረጃ እየተዘጋጁ የሚዳረሱ መጻሕፍትን በጥናትና ምርምር ላይ አስመርኩዞ ማዘጋጀት፤ ማሳተምና ማሠራጨትን ተያያዙት። በየተሰማሩበትም መስክ ሁሉ አገልግሎቱ ቀጣይነት እንዲኖረው ያጎዳኟቸውን ኢትዮጵያውያን ባልደረቦቻቸውን ወደ አሜሪካና ቤሩት ወደሚገኘው የአሜሪካን ዩኒቨርሲቲ እየላኩ መጀመሪያ በሁለት ዓመት ቀጥሎ በሌላ ሁለት ዓመት በዲግሪ ማሠልጠን ነበር። በዚህ መልክ ነው ይህ ‹‹ፖይንት ፎር›› የተባለ የዕድገት ወሳኝ ፕሮግራም፤ ሀገራችን የነበራትን በስምና በመልክ ይታወቁ የነበሩትን በጣት ከመቆጠር የማያልፉ ውጭ ሀገር ተምረው በዲግሪ የተመረቁትን የሀገር ልጆች በሺዎች ያበዛው።
እኔም በዚህ ጊዜ ነው ዕድል በሯን ከፍታልኝ ከነዚህ የአራት ሐዋርያዊ አሜሪካን ቡድን ጋር በመደመር፤ የመማሪያ መጻሕፍት አዘጋጅ ባለሙያዎች ከሆኑት ከአቶ ገብሬ ወዳጆ እና ከአቶ ተፈራ ወንድማገኘሁ ጋር በመመካከር ኦወን አር ላቭሌስ ከተባለው አሥራ አንድ የሩቅ ምስራቅ ቋንቋዎች ከሚናገረው ሐዋርያ ጋር በመቀናጀትና በመረዳት፤ በጥናት ላይ የተመሠረቱና በዕድሜና በደረጃ የተመጠኑ የትምህርት መጻሕፍትን ማዘጋጀት ጀመርሁ ሲሉ የህይወታቸውን ጅማሮና ውጣ ውረዱን ያስታውሳሉ።
ለሽልማት መብቃት
ሰሞኑን በኢንተር ኮንትኔታል ሆቴል በተካሄደው ዘጠነኛው የበጎ ሰው ሽልማት በአገልግሎት በጎ ሥራ ሰርተዋል ሲል ሽልማቱ ካባ ደርቦላቸዋል፤ አክብሯቸዋል። እርሳቸውም ብዙ አገልግሎ ብዙ ሰርቶ እንደመከበር መልካም ነገር ምን አለ ሲሉ ነበር ሽልማቱን የተቀበሉት። እርሳቸው ትምህርት ላይ የሚውለው ኢንቨስትመንት ከምንም በላይ እጅግ ደስተኛ እንደሚደርጋቸውና ትምህርት ላይ አቅምና እውቀትን ማውጣት ትውልድን መታደግ ሀገርን መገንባት እንደሆነ በፅናት ያምናሉ። በዚህም ከልጅነታቻው እስከ እርጅና ዘመናቸው ህይወታቸውን በትምህርትና በትምህርት ቤት አሳልፈዋል።
ዶክተር ልዑልሰገድ ለመሸለም ያበቃቸው ምንድን ነው?
በዘጠነኛው የበጎ ሰው ሽልማትም ዶክተር ልዑልሰገድ ዓለማየሁ አሜሪካ ትምህርት ላይ እያሉ ኮሎራዶ ቤተመጻሕፍት መግቢያ ላይ Enter here the timeless fellowship of the human mind የሚለው ፅሁፍ ትኩረታቸውን ይወስደዋል። “ከባዕድ ጎርሰህ ወደ ዘመድ ዋጥ” እንደሚለው ብሂል ሀሳቡን ወደአማርኛ “ከዚህ ከማይሞተው የሰው ልጅ ማደጊያ ስፍራ ግቡ” በማለት ይመልሱታል፤ ይህ ፅሁፍ መድኃኔዓለም ትምህርት ቤት መግቢያ ላይ ጎልቶ ይነበባል። የመድኃኔዓለም ትምህርት ቤት መለያም ሆኖ ለዓመታት ዘልቋል።
ዶክተር ልዑልሰገድ የተወለዱት ጅማ ከተማ ነው። የአባጅፋር ጸሐፊ የነበሩት አባታቸው ለትምህርት ቦታ የሚሰጡ ነበርና ከትምህርት ዓለም ጋር እድሜ ልካቸውን ተሳስረው እንዲቆዩ መሰረት የጣሉላቸው አባታቸው ናቸው። በጅማ ሚያዝያ 27 ትምህርት ቤት ሲማሩ ቆይተው በኋላ ብዙም ሳይቆይ ወደ ሀረር በተዘዋወረው ጅማ መምህራን ማሰልጠኛ ትምህርታቸውን አጠናቀቁ። በመምህርነት ለማገልገልም አለታወንዶ ተመድበው ለሶስት ወራት ከሰሩ በኋላ ወደ ይርጋለም ተዛወሩ።
ለመምህርነት እንደተፈጠሩ ማሳያ ከሚሆኑት ታሪካቸው መካከል በይርጋለም ቆይታቸው በስራቸው ከአስተዳደሩ ጋር ተጋጭተው እንደቅጣት ከሀዋሳ ከተማ ወጣ ባለችው ለኩ ሸበዲኖ በተመደቡ ጊዜ የሆነው ይጠቀሳል። ቦታው ለኑሮ አስቸጋሪ፣ ተሽከርካሪ የማይገባበት፣ በሽታ በተለይም የቆላ ቁስል ልጆችን የሚያስቸግርበት ነበር። የሚማረው ሰው ደግሞ ከተማው ላይ ያለው ብቻ ነው ይህንን ለመቀየር በተለይም የአካባቢው ነዋሪዎችን እንዲማሩ ለማድረግ ከባልደረባቸው ጋር ወደይርጋለም በእግራቸው ሄደው መርጃ መሳሪያና የትምህርት መፅሐፍ ይዘው በመመለስ ተማሪዎችን እንዲማሩ ቅስቀሳ ይጀምራሉ። በየአምስት ቀን የገበያ ቀን ጠብቀው መጻሕፍቱንና የትምህርት መሳሪያውን በተማሪዎች አስይዘው ገበያ ውስጥ በመዘዋወር ቅስቀሳ ያደርጉ ነበር። ገበያተኛው ከገበያ መልስ ወደ ት/ቤቱ ሲመጣ ት/ቤቱ የተከፈተው እዚያ ከተማ ላለው ብቻ እንዳልሆነ፣ እነሱም ሊማሩበት እንደሚገባ፣ ካልተማሩ ብዙ ነገርን ባለመረዳት እንደሚጎዱ በመስበክና በማሳመን ክፍል የመጣለትን ተማሪ ብቻ ከማስተማር የተሻገረ የመምህርነት ስራን አሳይተዋል በዚያ ዓመት እሳቸው መጋቢት ወር ሲደርሱ 225 የነበረው የተማሪ ቁጥር ሰኔ መጨረሻ 520 ደርሶ ነበር።
ወደ አዲስ አበባ ከተዘዋወሩ በኋላ የመማሪያ መፃህፍት አገልግሎት ይቀጠራሉ። ያን ጊዜ ነው “አረንጓዴው ጓደኛዬ”፣ “ሁለተኛው የንባብ መፅሐፌ” ፣ “ሶስተኛው የንባብ መፅሐፌ” እና “የፅህፈት ፋና” የተሰኙትን የመማሪያ መፃሕፍት ያዘጋጁት። ከፋሽስት ጣልያን ወረራ በኋላ በሀገራችን ለመጀመሪያ ጊዜ የአንደኛ ደረጃ ማስተማሪያ የሆኑት እነዚህ መጻሕፍት ከ23 ዓመታት በላይ ተደጋግመው በመታተም በሰፊው ያገለገሉ፣ ዕድሜን እንዲመጥን ሆነው በደረጃና በቅቡልነት ተጠንተውና ተለክተው የተዘጋጁ ነበሩ።
ዶክተር ልዑልሰገድ ወታደራዊው መንግስት ወደስልጣን ሲመጣ በሌሎች መፃሕፍት እንደሚደረገው ሁሉ በነዚህ የመማሪያ መጻሕፍትም ላይ የአፄ ኃይለስላሴ ፎቶ በመኖሩ ምክንያት ብቻ እንዲቃጠሉና እንዲወገዱ መደረጋቸው ለሀገሩ ጉዳት መሆኑን ይናገራሉ። ፎቶውን ብቻ አስቀርቶ መፃህፍቱን መጠቀም ይቻል ነበር እያሉ ይቆጫሉ። የትምህርት ዕድል አግኝተው ወደ አሜሪካ በመሄድ በመጀመሪያ ባችለር ኦፍ ሳይንስ ከዩኒቨርሲቲ ኦፍ ኮሎራዶ፣ ከዩኒርቨሲቲ ኦፍ ካሊፎርኒያ ደግሞ ማስተር ኦፍ ኤጁኬሽን እና ዶክተር ኦፍ ኤጁኬሽን አግኝተዋል። ወደ መድኃኔዓለም ትምህርት ቤት ከተዛወሩ በኋላ፤ ሁለተኛ ደረጃ ተማሪ 12ኛ ክፍልን ፈጽሞ የመልቀቂያ ፈተናውን አለፈም አላለፈም፣ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርትን ማጠናቀቁን የሚያረጋግጥ የምስክር ወረቀት በመድኃኔዓለም ትምህርት ቤት በማስጀመር ለሌሎችም ፋና ወጊ ሆነዋል። እንዲሁም የትምህርት ቤቱንና የተማሪዎቹን እንቅስቃሴ የሚያሳይ “የመድኃኔዓለሞቹ/ Medhane Alemian” ብለው የሰየሙትን ዓመታዊ መጽሔት በማስጀመር ቀዳሚ ተጠቃሽ ናቸው።
በመድኃኔዓለም ትምህርት ቤት ያሳዩት ከፍተኛ ትጋት በትምህርትና ሥነ ጥበብ ሚኒስትር ዴኤታ ጥያቄ የሕዝብ ግንኙነት ዲሬክሲዮን በአስተባባሪነት አቋቁመው በ1955 ዓ.ም. የመጀመሪያውን የትምህርት ዜና መጽሔት አሳትመዋል። በአሜሪካ ከፍተኛ ትምህርታቸውን በሚማሩበት ጊዜ በአሜሪካ ሬዲዮ ቪኦኤ፣ የመጀመሪያዎቹ ከአሜሪካ የተላለፉት ፕሮግራሞች የመርሊን ዘ ስቶሪ ቴለር ተረቶች፣ ጃዝ ሙዚቃዎች ለአድማጮች ማቅረባቸው ይታወሳል። በኢትዮጵያ ሬዲዮ የልጆች ጊዜ ፕሮግራም፣ ቀጥሎም የነገው ሰው የተባለ በየሳምንቱ ቅዳሜ በዘጠኝ ሰዓት አዘጋጅተው ያቀርቡ ነበር።
የኮተቤ የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ መምህራን ማሠልጠኛ ኢንስቲትዩት (ቲቲአይ) ፕሪንሲፓል በአማርኛ ራሳቸው “ርእሰ መምህር” ብለው እንዲጠራ ያደረጉ፣ የግቢው ሕንፃዎችና ሜዳዎች በታሪካዊ ነገሥታት፣ በልዩ ልዩ ከተሞች፣ በዕውቀት አባቶችና በታዋቂዎች እንዲሰየሙ አድርገዋል። ለምሳሌ በሳባ፣ ቴዎድሮስ፣ ዮሐንስ፣ ፋሲል፣ ተፈሪ፣ ያሬድ፣ መምህር አካለ ወልድ፣ አዶሊስ፣ ሐረር፣ ዓባይ፣ ጊቤ፣ አይጠየፍ አዳራሽ፣ ምኒልክ ሜዳ፣ ቲቲአይ ከመሆኑ በፊት በኮተቤ ቀ.ኃ.ሥ. ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ዝነኛ የመረብ ኳስ ተጫዋች በነበሩት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ከተማ ይፍሩ ስም “ከተማ ሜዳ” ተብለው እንዲሰየሙ አድርገዋል። ይህም “ኮተቤዎቹ” እና “KOTEBEAN” ብለው ማሳተም በጀመሩት ዓመታዊ መጽሔት ላይ ከነፎቷቸው ይታያሉ። በ1960ዎቹ መጀመሪያ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በተጋባዥ መምህርነት የትምህርት ፍልስፍና አስተምረዋል፣ በ1967 ዓ.ም. ብሔራዊ የከፍተኛ ትምህርት ኮሚሽን ሲቋቋም የመጀመሪያው ዋና ጸሐፊ ሆነው ሠርተዋል። በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሥር በዩኔስኮ በከፍተኛ ባለሙያነት ተቀጥረው በተለያዩ አገሮች አገልግለዋል። ከ1983 የመንግሥት ለውጥ በኋላ በአዲስ አበባ የነገው ሰው ትምህርት ቤትን በመመሥረት፣ በ1990ዎቹ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በድኅረ ምረቃ ማስተማርና መመረቂያ ጽሑፎችን በመሪ ገምጋሚነት ሠርተዋል።
የኢትዮጵያ የትምህርት ጥራትን መውደቅ የሚያሳየውን የ2001 (እ.ኤ.አ.) ጥናት በማሳየት፣ የሲዋዚላንድን ትምህርት ባዳኑበት መንገድ ሀገሬን ልርዳ ብለው ከ1990ዎቹ ጀምሮ የትምህርት ሚኒስቴርን ለሚመሩ ሚኒስትሮች በተደጋጋሚ ደብዳቤ ቢፅፉም ቀና ምላሽ አላገኙም።
የዶክተሩ ህልም
እኚህ ሰው በዚህ ሽልማት ብቻ የሚያቆሙ አይደሉም። ገና ብዙ እሰራለሁ ሲሉ ያስባሉ። በተለይም ደግሞ እስከ ህይወት ፍፃሜያቸው ኢትዮጵያን ህዝብ ማገልግል ትልቁ ህልማቸው ነው።
“ልጆቼን በሙሉ አስተምሬ ለቁምነር ማብቃቴ ብቻ ሳይሆን ዓለም አቀፍ እውቀት ቀስመው እጅግ ወሳኝ በሆኑ ተቋማት ውስጥ እየሰሩ ነው። በጥረቴ ውስጥ የልጆቼ ስኬት ይታየኛል። ስኬት በልጆች ብሳ የተገደበ መሆን የለበትም ብዬ አስባለሁ። በመሆኑም ለዓመታት በቀሰምኩት ልምድ ለሀገሬ በምችለው ሁሉ ለማገልገል ጥረት ሳደርግ ኖሬያለሁ። እውቀቴንና ገንዘቤን ሳልሰስት የምችለውን ሁሉ ለሀገሬ ስሰራ ነው የኖርኩት፤ አሁንም አቅሜ የፈቀደውን ሁሉ በመስራት ላይ ነኝ” ይላሉ ዶክተር ልዑልሰገድ።
“በመጨረሻም ስለአከበራችሁኝ አመሰግናለሁ፤ ጥሩ አገልጋይ መሆን ክብር እንደሚያጎናፅፍ ተረድቻለሁ። ትንሽ ሰርቼ እውቅና ከተሰጠኝ ከዚህ በበለጠ ብሰራስ ብዬ ተመኘሁ፣ ለዚህ ያበቃችኝን ውድ ባለቤቴንም አመሰግናለሁ” ሲሉም በማለት በሽልማት ስነስርዓቱ ላይ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
መንግስታዊ የሥራ ሐላፊነትን በብቃት የመወጣት ዘርፍ
በዚህ ዘርፍም በእጩነት የቀረቡት ሶስት የመንግስት የስራ ሃላፊዎች ናቸው። እነሱም አቶ ይኩኖአምላክ መዝገበ፤ ዶ/ር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ እና ኢንጂነር ሃብታሙ ተገኝ ናቸው። እነዚህ ሃላፊዎች ረጅም የስራ ዘመን አገልግሎት ያላቸው ሲሆን በሙያቸውም ሃገራቸውን ያለገሉና ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረከቱ ናቸው። ከነዚህ ውስጥ ደግሞ የዓመቱን የበጎ ሰው ሽልማት ያሸነፉት ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ ናቸው። ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ የውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር ሲሆኑ በተለይ ከታላቁ ህዳሴ ግድብ ጋር ተያይዞ “ግድቡ የኔ ነው” በሚል ያነሱት ሃሳብ በመላ ኢትዮጵያውያን ዘንድ የሰረጸ ጥልቅ ሃሳብ ሆኖ እንዲቀር ያደረጉ ናቸው። እኛም በዛሬው የአገልጋይነት ክብር ቀን ስለእሳቸው ጥቂት መረጃዎችን ልናካፍላችሁ ወደድን። መነሻችን ለዚሁ የተዘጋጀው መጽሄት ነው።
ስለዶ/ር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ ታሪክ በአጭሩ
ዶክተር ኢንጅነር ስለሺ በቀለ ተወልደው ያደጉት በምዕራብ ሸዋ ዞን ጀልዱ ወረዳ ልዩ ስሙ ፎጮቢ በሚባል ቦታ ነው። የካቲት 1 ቀን 1957 ዓ.ም ለቤተሰቡ ልዩ ቀን ነበረችም። ከዚያ እድሜያቸው ለትምህርት ሲደርስ ቤተሰብ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ በዚያው በትውልድ ቀያቸው በጀልዱ 1ኛና መለስተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት አስገባቸው። ቀጣዩን ትምህርት ለመማር ደግሞ በአካባቢያቸው በቅርብ ርቀት ላይ ትምህርት ቤት ባለመኖሩ ወደ አምቦ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መዛወር ነበረባቸውና በዚያ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ ሆነዋል።
በጥሩ ውጤት የ12ኛ ክፍል ትምህርታቸውን ከአጠናቀቁ በኋላ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲን መቀላቀል ችለዋል። በ1979 ዓ.ም በሲቪል ምሕንድስና የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ያገኙ ሲሆን፤ በመቀጠልም ከእንግሊዙ ኒውካስትል አፕኦንታየን ዩኒቨርሲቲ በ1983 ዓ.ም በሃድሮሊክ ኢንጂነሪንግ እና ሃይድሮሎጂ የሁለተኛ ዲግሪያቸውን በከፍተኛ ማዕረግ መመረቅ ችለዋል። ከ1990 እስከ 1993 ዓ.ም በሀገረ ጀርመን ድሪዝደን ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ የሦስተኛ ዲግሪ ትምህርታቸውን ተከታትለው በውሃ ሀብት እና ሃይድሮሊክ ኢንጂነሪንግ በ“እጅግ ከፍተኛ ማዕረግ” የተመረቁ ሲሆን ፤ በዚሁ ዩኒቨርሲቲም በመምህርነት አገልግለዋል።
ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ ሀገራቸውን ማገልገል የጀመሩት በቀድሞው የአርባ ምንጭ ውሃ ቴክኖሎጂ በአሁኑ አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በመምህርነት ነው። በዚሁ ተቋም እስከ 1996 ዓ.ም ድረስ ለድኅረ ምረቃ ትምህርት ወደ ውጭ ሀገራት የተጓዙባቸው ጊዜያት እንደተጠበቁ ሆነው በመምህርነት፣ በዲንነትና በዋና ኃላፊነት አገልግለዋል። በተቋሙ በቆዩባቸው ዘመናት በግድብና ሃይድሮ ፓወር፣ በመስኖና ድሬኔጅ፣ በውሃ ሀብትና ሃይድሮሎጂ እንዲሁም በሌሎችም ዘርፎች የሁለተኛ ዲግሪ ፕሮግራም እንዲጀመር በማድረግ ጉልህ አስተዋጽኦ በማበርከት ተቋሙ ወደ አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲነት እንዲያድግ የመሪነት ሚና ተጫውተዋል።
ዶክተር ኢንጅነር ስለሺ ከ1997 እስከ 2003 ዓ.ም በኢንተርናሽናል ወተር ማኔጅመንት ኢንስቲትዩት ናይል ቤዝንና የምስራቅ አፍሪካ ከፍተኛ ተመራማሪ እና የተቋሙ ዋና ዳይሬክተር በመሆን ለሰባት ዓመታት የሰሩም ናቸው። በዚህ ተቋም ውስጥም በስራ ላይ የዋሉ ከ30 በላይ መጽሐፍትና ጆርናሎች በማሳተም፣ ከ60 በላይ በሥራ ላይ የዋሉ ሰነዶችንና የሥራ መመሪያዎችን በማዘጋጀት ታላቅ አስተዋጽኦ አበርክተዋል።
ከ2003 ዓ.ም ጀምሮ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን (UNECA) ውስጥ የውሃና አየር ንብረት ለውጥ ከፍተኛ ባለሙያ በመሆን ያገለገሉት ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ፤ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ውስጥም ሰርተዋል። ይህ ደግሞ በሁሉም የአፍሪካ ክፍሎች የውሃና አየር ንብረት መሳሪያዎችን በማስተከል፣ የአየር ንብረት ለውጥ፣ ውሃ፣ ግብርና እና ኢነርጂ ዙሪያ የፖሊሲ ምርምር ውጤቶችንና ምክረ ሃሳቦችን እንዲያደርጉ አግዟቸዋል። አበርክቷቸውም በዚህ ልክ የሚገለጽ ነው።
በኢሲኤ/የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን/ እየሠሩም የብሔራዊ ባለሙያዎች መማክርት (ፓናል) በማቋቋምና በመምራት ህዳሴ ግድብን እና በዙሪያው የሚነሱ ጉዳዮችን ለመመከት የሚያስችሉ ሥራዎችን አስተባብረዋልም። በመቀጠልም ኒውዮርክ በሚገኘው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና መስሪያ ቤት በዘላቂ ልማት ግቦች ዘርፍ በኢኮኖሚና ማህበራዊ ጉዳዮች መምሪያ ውስጥ በአህጉራት ከፍተኛ አማካሪነት እስከ 2008 ዓ.ም ድረስ መስራት የቻሉም ናቸው።
ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በዚህ ኃላፊነታቸው በዋናነትም በአፍሪካ፣ እስያ፣ ላቲን አሜሪካ፣ እና በካረቢያን የአህጉራቱን የዘላቂ ልማት ግቦችን በማሰናሰል ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረከቱ ናቸው። በተለይም ለኢትዮጵያ ለዚሁ ዓላማ የሚያገለግሉ ስትራቴጂያዊ ዕቅዶችን በማዘጋጀት ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርገዋል።
የኢትዮጵያ መንግስት ባቀረበላቸው ጥሪ መሠረት የነበሩበትን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዓለም አቀፍ ኃላፊነት፣ በዓመት ከ200 ሺህ የአሜሪካ ዶላር በላይ ደመወዝ ከሚያገኙበትና የተመቻቸ የሥራ ዕድል ካለበት ቦታ ትተው አገራቸውን መርጠው የመጡት ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ፤ ከ2009 ዓ.ም ጀምሮ በኢ.ፌ.ዲ.ሪ የውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር ሚኒስትር በመሆን የሚወዷትን ሀገራቸውን ኢትዮጵያንና ህዝባቸውን እያገለገሉ የሚገኙ የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጅ ናቸው። ይህ ውሳኔያቸው እሳቸውን ተከትለው ለመጡ ሌሎች የዲያስፖራ አባላት ልዩ አርአያነትም የሰጠ ነው።
ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ አገራቸው ላይ በመምጣት ብቻ ሳይወሰኑ በርካታ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ምሁራን ባሉበት ክፍላተ ዓለማት ሆነው ሀገራቸውንና ህዝባቸውን እንዲያገለግሉ አንቂ ስልጠናዎችንና ትምህርቶችን በመስጠት እንዲሁም ንግግሮችን በማድረግ ብሔራዊ አንድነትን በመገንባት ረገድ እጅግ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረከቱ እንደሆኑ ብዙዎች ምስክርነታቸውን ይሰጡላቸዋል።
አሁን በተመደቡበት ሚኒስቴር መስሪያ ቤት የውኃ ሀብት አስተዳደር ፖሊሲ ከሁለት አስርት ዓመታት አገልግሎት በኋላ ዘመኑን የዋጀና የኢትዮጵያን አሁናዊ የልማት ፍላጎት ሊመልስ በሚችል መልኩ እንዲከለስ በማድረግና የ10 ዓመት መሪ ዕቅዱ እንዲዘጋጅ በማድረግ ኃላፊነታቸውን የተወጡት ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ፤ በሚኒስትርነት በሚመሩት የመንግስት ተቋም ውስጥ ክትትል የሚደረግለትን ብሔራዊ ፕሮጀክታችን የሆነውን የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት በሚመለከት ከነበረበት ችግር ተላቅቆ ግንባታው በሚፈለገው ፍጥነትና ጥራት እንዲከናወን፣ የመጀመሪያውና የሁለተኛው ዙር የውሃ ሙሌት በስኬት እንዲጠናቀቅ እንዲሁም ከታችኛው የተፋሰሱ ሀገራት በዋናነትም ከግብጽና ሱዳን ጋር በሚካሄደው ድርድር ላይ የዘርፉን ከፍተኛ ባለሙያዎች በማዋቀርና በማስተባበር፣ በተከታታይነት ግድቡ ድረስ በመገኘት የሥራ መመሪያና አቅጣጫ በመስጠት፤ ከምንም በላይ የመሪነቱን ሚናም በመጫወት ዛሬ ለደረስንበት ከፍተኛ ስኬት ድርሻቸውን በሚገባ የተወጡ ናቸው።
ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ፕሮጀክትን አስመልክቶ ከአንድ ዓለም አቀፍ የመገናኛ ብዙኃን ድርጅት “ግድቡን ማን ያስተዳድረዋል (Who will operate the dam?)” ተብሎ ለተሰነዘረላቸው ጥያቄ ቆፍጠን ብለው “ግድቡ የእኔ ነው! ስለዚህ እኔው አስተዳድረዋለሁ (What do you mean? It is My Dam, I will Operate It)” በማለት የሰጡት ምላሽ እንደ ኃይሌ ገብረሥላሴው ‹ይቻላል› ብሔራዊ መግባቢያ ተደርጎ ተወስዶላቸዋል።ይህ ደግሞ አርዓያነታቸው በኢትዮጵያዊያን ጭምር ምንኛ የናኘ እንደሆነ የሚያሳይ ነው።
በአጠቃላይ ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ እንደ መሪ ወሳኙን ሚኒስቴር መስሪያ ቤት በዓለም ላይ ያሉ ባለሙያዎችን በማስተባበር የሚመሩላት፣ እንደ መሐንዲስ በየፕሮጀክቱ እየተገኙ የሚተጉላት፣ እንደ ዲፕሎማት በዓለም አቀፍ መድረኮች የሚሟገቱላት የኢትዮጵያ ውድ ልጇ ናቸው። በትክክለኛው ጊዜ ትክክለኛ ቦታ ላይ የሚገኙ፤ ተገቢና ወሳኝ ሀሳብ ለሚፈለገው አካል የሚያስረዱ የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጅም መሆናቸውን ማንም አይክድም። ስለሆነም እንዲህ አይነት በጎ አሳቢና አገር ወዳድ አገልጋይን ለአገራችን ያብዛልን እያልን ሀሳባችንን ቋጨን። ሰላም!
ክፍለዮሐንስ አንበርብር እና ጽጌረዳ ጫንያለው
አዲስ ዘመን ጳጉሜ 2/2013