ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህ.ወ.ሓ.ት) የአሜሪካ ዓለም አቀፍ ልማት ኤጀንሲ (USAID) የእርዳታ መጋዘኖችን መዝረፉን የኤጀንሲው የኢትዮጵያ የበላይ ኃላፊ ሾን ጆንስ ሰሞኑን ተናግረዋል።
ኃላፊው ከኢትዮጵያ ቴሌቪዥን (ETV) ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ‹‹ … ህወሓት ሁኔታውን ያለአግባብ እየተጠቀመበት እንደሆነ እናምናለን።ከተረጂዎች ላይ በኃይል እርዳታን እየነጠቀ እንደሆነ ይሰማናል።
እርግጠኛ ሆነን መናገር የምንችለው ግን ሰርገው በገቡባቸው አካባቢዎች ሁሉ ያሉትን የእርዳታ መጋዘኖቻችንን ዘርፈዋል፤ ይህ የምናውቀው ሃቅ ነው … ይህንን የምንናገረው የህ.ወ.ሓ.ት ተዋጊዎች መጋዘኖቻችንን እንደዘረፉ በግልጽ ስለምናውቅ ነው …›› ብለዋል።
የህወሓት ተዋጊዎች በገቡባቸው የአማራ ክልል አካባዎች ከፍተኛ ጥፋት በማድረሳቸው የእርዳታ ስራውን በከፍተኛ ሁኔታ እያስተጓጎሉት እንደሆነም ኃላፊው ተናግረዋል።‹‹… የህ.ወ.ሓ.ት ተዋጊዎች ሰርገው በገቡባቸው የአማራ ክልል አካባቢዎች የእርዳታ መጋዘኖችን ዘርፈዋል፤ መኪናዎችን ሰርቀዋል፤ በየመንደሮቹ ብዙ ውድመት አድርሰዋል።ይህ ለተጎጂዎቹም ሆነ ለእኛ ለረጂዎቹ አሳሳቢ የሆነ ነገር ነው …›› በማለት የህ.ወ.ሓ.ትን ወንጀል ዘርዝረዋል።
ከዚህ በተጨማሪም ‹‹ … ‹ዩኤስ ኤይድ ለህወሓት ተዋጊዎች እርዳታ ይሰጣል› ተብሎ መከሰሱ እጅግ አሳዛኝ ውንጀላ ነው፤ ይህ ፍፁም ውሸት ነው›› በማለት ኤጀንሲያቸው ለተዋጊ ኃይሎች እርዳታ እንደማይሰጥ አስረድተዋል።
ይህ የሾን ጆንስ ማብራሪያ በተወሰነ መልኩም ቢሆን የዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃንን ሽፋን አግኝቷል።ጥቂት ምዕራባውያን ባለስልጣናትም ስለጉዳዩ ሃሳባቸውን ሰጥተዋል።ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን ለጉዳዩ ሽፋን የሰጡት የኢትዮጵያ ቴሌቪዥንን ዘገባ ዋቢ በማድረግ ነው።ለአብነት ያህል ይህ ዘገባ በአዣንስ ፍራንስ ፕሬስ (AFP)፣ በዘ ኒው ዮርክ ታይምስ (The New York Times)፣ በሮይተርስ (Reuters)፣ በአል-አረቢያ (Al Arabiya) ዴይሊ ሜይል (Daily Mail) ላይ ሽፋን አግኝቷል።በእርግጥ እነዚህ መገናኛ ብዙኃን ለጉዳዩ ሽፋን የሰጡት የኢትዮጵያ ቴሌቪዥንን ዘገባ በመውሰድ ነው።አንዳንዶቹ መገናኛ ብዙኃን ‹‹ህ.ወ.ሓ.ት እርዳታ አልዘረፈም›› የሚለውን የቡድኑን ቃል አቀባይ ነጭ ውሸት ማስተባበያ በዘገባቸው ውስጥ አካትተውታል።
ሰብዓዊ እርዳታ ለሚፈልጉ ወገኖች የተቀመጡ የእርዳታ ቁሳቁሶችን መዝረፍ ከባድ ወንጀል እንደሆነ ይታወቃል።በወንጀል የተጨማለቀው ህ.ወ.ሓ.ት ደግሞ ይህን ከባድ ወንጀል መፈፀሙን የአሜሪካ ዓለም አቀፍ ልማት ኤጀንሲ (USAID) አስታውቋል።
ህ.ወ.ሓ.ት ከባድ እንደሆነ የሚታወቀውንና በማስረጃ የተረጋገጠበትን ወንጀል ፈፅሞ ሳለ ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን ግን ለዚህ ጉዳይ በቂ ሽፋን መስጠት አልፈለጉም።‹‹የሰብዓዊ መብት ጉዳይ ያሳስበናል›› የሚሉ የመብት ተሟጋቾችና አክቲቪስቶችም የህ.ወ.ሓ.ት ከባድ ወንጀል ቅንጣት ታክል አላስደነገጣቸውም።
በእርግጥ እጅግ አሳዛኝና አሳፋሪ መረጃዎችን የሚያሰራጩት እነዚህ መገናኛ ብዙኃንና ‹‹የሰብዓዊ መብት ተሟጋች›› የሚባሉ ‹‹አክቲቪስቶች›› በአንድም ይሁን በሌላ መንገድ ከህ.ወ.ሓ.ት ጋር ግንኙነት ያላቸው፣ ‹‹ከኤርትራ መንግሥት ጋር ፀብ አለን›› የሚሉ፣ ራሳቸውን አንድ ጊዜ ተንታኝ፣ ዲፕሎማት፤ሌላ ጊዜ ደግሞ ጋዜጠኛ፤ ሲያሻቸውም አማካሪ ወይም ተማራማሪ ብለው የሾሙና በዚሁ ጭምብል የሚንቀሳቀሱ ጥራዝ ነጠቅ የእጅ አዙር ቅኝ ግዛት አምባሳደሮች ስለሆኑ የወዳጃቸውን ወንጀል ለመደበቅ ቢጥሩ ብዙም የሚያስገርም አይሆንም።
በሌላ በኩል ህወሓት የእርዳታ መጋዘኖችን የመዝረፉ ጉዳይ በጥቂት የምዕራብ መንግሥታት ባለስልጣናት ዘንድ አጀንዳ ሆኖ ተመልክተናል።ለአብነት ያህል በአሜሪካ ሴኔት የውጭ ግንኙነት ኮሚቴ ነባር አባል (Ranking Member)ና የአይዳሆ ግዛት ተወካዩ ሴናተር ጂም ሪሽ በህ.ወ.ሓ.ት የዘረፋ ተግባር ማዘናቸውንና ይህን የፈፀሙ አካላትም ተጠያቂ ሊሆኑ እንደሚገባ ገልፀዋል።
የአሜሪካ የተወካዮች ምክር ቤት አባል ካረን ባስ በበኩላቸው ስለጉዳዩ ባወጡት መግለጫ ‹‹ … የሰብዓዊ እርዳታ የያዙ የአሜሪካ ዓለም አቀፍ የልማት ኤጀንሲ (USAID) መጋዘኖች ስለመዘረፋቸው በሰማሁት ዜና በጣም ተረብሻለሁ።ይህ የህ.ወ.ሓ.ት ድርጊት ሰብዓዊ እርዳታ ለሚፈልጉ ወገኖች ላይ ከፍኛ ተጽዕኖ የሚያሳድርና የኤጀንሲውን ስራ የሚያደናቅፍ ተግባር ነው … ህ.ወ.ሓ.ት እርዳታ የሚፈልጉ ወገኖች እርዳታ እንዳያገኙ የሚያደርግ መሰናክል መፍጠር የለበትም …›› ብለዋል።
‹‹ትግራይ እርዳታ እንዳታገኝ ተከልክላለች፣ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ተፈፅመዋል … ብለው ሲጮሁ የከረሙት የአውሮፓና የአሜሪካ ሹማምንት የህ.ወ.ሓ.ትን ከባድ የዝርፊያ ወንጀል ማውገዝ አልፈለጉም።
አንዳንዶቹማ እንኳንስ ዝርፊያውን ሊያወግዙ ይቅርና ዝርፊያውን ሕጋዊ ለማድረግ ሲጋጋጡ ታይተዋል።በስደተኛ መታወቂያ የህ.ወ.ሓ.ት ተዋጊ ሆነው የተገኙ ሰዎችም እንዳሉ የሚሳዩ መረጃዎችንም ተመልክተናል።የመንግሥታቱ ድርጅት የሰብዓዊ እርዳታ ማስተባበያ ቢሮ (OCHA) ‹‹ … በትግራይ ያለው የእርዳታ እህል እያለቀ ነው፤መንግሥት እርዳታ እንዳይገባ መሰናክል እየሆነ ነው …›› ብሎ የተለመደ ውንጀላውን ቢያሰማም ‹‹እርዳታው እንዴት አለቀ?›› ተብሎ ቢጠየቅ ግን እውነተኛውን ምክንያት መናገር የሚፈልግ አይመስልም።
የአሜሪካ ዓለም አቀፍ የልማት ኤጀንሲ (USAID) ዋና አስተዳዳሪ ሳማንታ ፓወር ስለድርጅታቸው መዘረፍ ምንም ማለት አልፈለጉም።የኢትዮጵያን መንግሥት በመክሰስ ግን ሴትዮዋን ማንም አይቀድማቸውም።የሰብዓዊ እርዳታ የያዙ የድርጅታቸው መጋዘኖች በህ.ወ.ሓ.ት ተዘርፈው ሳለ እርሳቸው ግን አሁንም ‹‹የኢትዮጵያ መንግሥት እርዳታ ወደ ትግራይ እንዳይገባ እያደረገ ነው …›› የሚለው የተለመደ ክሳቸው ላይ ተቸክለው ቀርተዋል።
የምዕራባውያን ‹‹የእርዳታና የመብት ተሟጋች ድርጅቶች›› ጉዳቸው ብዙ ነው።በሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦት እና በመብት ተሟጋችነት ሽፋን አስገራሚ የፖለቲካ ሴራዎችን የሚያቀነባብሩ ተዓምረኛ ተቋማት ናቸው።
ይህ ሴረኛነታቸው በቀደሙት የንጉሳዊውና ወታደራዊ ዘመነ መንግሥታት በግልጽ ታይቷል።እርዳታን ከሰብኣዊነት ይልቅ ፖለቲካዊ ገፅታ በማላበስ ተጠምደው እንደነበር ይታወቃል።እርዳታን በቀጥታ ለአማፂያን ከመስጠት ጀምሮ የውሸት መረጃዎችን በመፈብረክ ፖለቲካዊ ዓላማቸውን ሲያስፈፅሙ ነበር።የህ.ወ.ሓ.ትን የዘረፋ ወንጀል መሸፋፈንና ለማውገዝ አለመፈለግም የዚሁ ሴረኛ ግብራቸው ቅጥያ ነው።
የመገናኛ ብዙኃኑ ነገር ሲጨመር ደግሞ ሴራውና ፋታ የማይሰጥ ሆኖ ይገኛል።እንደሚታወቀው ላለፉት ወራት ስለሕግ ማስከበር ዘመቻው እውነቱንም ውሸቱንም (ጥቂት እውነትና ብዙ ውሸት) ሲቀባጥሩ የከረሙት የምዕራብ መገናኛ ብዙኃን፤ ህ.ወ.ሓ.ት ከትግራይ አልፎ ወደ አማራና አፋር ክልሎች ወረራ ሲፈፅም አይተው እንዳላዩ ሰምተው እንዳልሰሙ ፀጥ ብለዋል።
‹‹ሴቶች ተደፈሩ፣ ንብረት ተዘረፈ …›› እያለ ሲጮህ የከረመው ብዕራቸው/አፋቸው የአማራና የአፋር ሕዝቦች ሰቆቃ ግን ደንታ አልሰጠውም።በአፋር ክልል ከ200 በላይ ንጹሃን ሲጨፈጨፉና ከሁለቱ ክልሎች ከግማሽ ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ሲፈናቀል ወገንተኞቹ የምዕራብ ቴሌቪዥኖችና ጋዜጦች ግን አንዲትም ቃል ትንፍሽ አላሉም።ህ.ወ.ሓ.ት ዓለም አቀፍ ሕግጋትን ጥሶ በርካታ ሕፃናትን ለጦርነት ሲያሰልፍ፣ ንፁሃንን ሲገድል፣ ሲዘርፍና ሲያፈናቅል እነዚህ ‹‹ጋዜጠኞች››ና ‹‹አክቲቪስቶች›› ግን የህ.ወ.ሓ.ትን ‹‹ድል›› በኩራት እየዘገቡ ነው።ስለህ.ወ.ሓ.ት የዝርፊያ ተግባርም ‹‹አላየንም፤አልሰማንም›› ብለዋል።
ህ.ወ.ሓ.ት ከፌደራል መንግሥት በተቃራኒ ሕገ-ወጥ ምርጫ ማድረጉን፣ በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች ግድያዎችና መፈናቀሎች እንዲፈፀሙ ማስተባበሩን፣ ሉዓላዊት አገር በሆነችው ኤርትራ ላይ ጭምር ጥቃት መሰንዘሩን፣ በመከላከያ ሰራዊት የሰሜን ዕዝ ላይ ጥቃት ከፍቶ ግድያ፣ የንብረት ውድመትና ዝርፊያ እና እገታ መፈፀሙን እንዲሁም በማይካድራ ከአንድ ሺ በላይ ንፁሃንን መፍጀቱን … ሊነግሩን አይፈልጉም።
መገናኛ ብዙኃኑ መርጦ አልቃሽ/ወገንተኛ ብቻ አይደሉም፤ውሸታሞችም ናቸው።ያልተደረገውን ነገር እንደተደረገ፤ያልተባለውን ነገር እንደተባለ አድርገው ዜና በመስራትም የተካኑ የውሸት ቋቶች ናቸው።‹‹የጋዜጠኝነት መርህ ፈጣሪዎች ነን›› ብለው የሚመፃደቁለት ወሬያቸው ከንቱ ቀረርቶና አስመሳይነት እንጂ እንደሚጮሁለት የእውነት መግለጫ አይደለም።
በእርግጥ ለምዕራባውያን መገናኛ ብዙኃን፣ መንግሥታትና ተቋማት ‹‹እውነት›› ማለት ብሔራዊ ጥቅማቸውና ፍላጎታቸው ነው።የሌሎች አገራት ዜጎች የመብት ጥሰት፣ ረሀብ፣ አፈናና ግድያ ጉዳያቸው እንዳልሆነ ደግመን ደጋግመን አይተናል።ይህን ሴረኛ ስልታቸውን በቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴና በደርግ መንግሥታት ዘመንም ሰርተውበታል።
ከዚህ በተጨማሪም ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃንና ተቋማት እንዲሁም የውጭ መንግሥታት የራሳቸው ዓላማ አላቸው።እነዚህ አካላት በሌሎች አገራት የሚፈጠሩ ክስተቶችን የሚመለከቱትና ብያኔ የሚሰጡት ከራሳቸው ጥቅም አንፃር ነው።ኢትዮጵያ ውስጥ የተፈጠረውን ሁኔታም የሚመዝኑት ዓላማቸውንና ጥቅማቸውን መሰረት አድርገው ነው።ምዕራባውያን አገራትም ሆኑ ለመንግሥታቱ ቅርብ የሆኑት መገናኛ ብዙኃን ሰብዓዊነት፣ እውነት፣ የጋዜጠኝነት መርህ … የሚባሉትን ነገሮች ፈፅሞ አያውቋቸውም።ለእነዚህ አካላት ሰብዓዊነት፣ እውነት፣ የጋዜጠኝነት መርህ … ማለት የተቋማቸውና የመንግሥቶቻቸው ጥቅምና አቋም እንጂ በመርህ የሚነገሩት የጽንሰ ሃሳቦቹ ትክክለኛ ትርጉም አይደለም።
እነዚህ ተቋማት ‹‹ስለህ.ወ.ሓ.ት ወንጀል ለምን አትናገሩም?›› ተብለው ሲጠየቁ ‹‹ … ማስረጃ የለንም፤በአካባቢው ባለው አስቸጋሪ የፀጥታ ሁኔታ ምክንያት ጉዳዩን ለማጣራት አልቻልንም፤ጉዳዩን ለማረጋገጥ የኢትዮጵያ መንግሥት ያቋረጣቸውን የስልክ፣ የመብራትና የባንክ አገልግሎቶች ማስጀመር አለበት …›› በማለት የተለመደውን ጩኸታቸውን ያስተጋባሉ።
‹‹የሰብዓዊ መብት ጥሰት እየተፈፀመ ነው … የሰብዓዊ እርዳታ ተከልክሏል …››ለሚለው ውንጀላቸው ግን ምንም ማጣሪያና ማስረጃ አያስፈልጋቸውም።ጣሊያናዊው ኢኒዮ ባሲ ዓለም አቀፍ ድርጅቶችና መገናኛ ብዙኃን ከህ.ወ.ሓ.ት ጋር ተመሳጥረው በኢትዮጵያ ላይ እየሰሩት ያለውን ወንጀል በዳሳሰበት ጽሑፉ የእርዳታ ድርጅቶቹ በእርዳታ ስም እንዲሁም መገናኛ ብዙኃኑ ደግሞ በጋዜጠኝነት ሽፋን የውሸት ፕሮፓጋንዳዎችን እየሰሩ እንደሆነ አብራርቷል።
ከዚህ ቀደም የነበሩትን ብንረሳቸው እንኳ ያለፉት ጥቂት ወራት የሰብዓዊነት፣ የጋዜጠኝነት መርህና የእውነት ጠበቃ እንደሆኑ የሚያወሩት ምዕራባውያን ጋዜጠኞች፣ አክቲቪስቶችና መንግሥታት ከሰብዓዊነት፣ ከእውነትና ከጋዜጠኝነት መርሆች ጋር ፈፅሞ እንደማይተዋወቁና ዓይናቸውን በጨው ያጠቡ ከሃዲዎች፣ ውሸታሞችና ወገንተኞች እንደሆኑ በግልጽ ያረጋገጥንባቸው ወቅቶች ናቸው።
ዩኤስኤይድ ‹‹በህ.ወ.ሓ.ት ተዘርፌያለሁ›› ብሎ በግልጽ ቢናገርም የምዕራብ መንግሥታት ሹማምንት፣ ዓለም አቀፍ ተቋማት (የእርዳታ ድርጅቶችና የመብት ተሟጋቾች) እና መገናኛ ብዙኃን ግን የህ.ወ.ሓ.ትን ከባድ ወንጀል ማውገዝ አልፈለጉም።
በአጠቃላይ ትልቁ የእርዳታ ድርጅት የሆነው የዩኤስኤይድ የእርዳታ መጋዘኖች በህ.ወ.ሓ.ት መዘረፋቸው በድርጅቱ ኃላፊ ቢነገርም ጉዳዩ ‹‹የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ነን›› ለሚሉ የእርዳታና የመገናኛ ብዙኃን ተቋማት ትርጉም ያለው ዜና/ጉዳይ መሆን አልቻለም፤ ይህ ደግሞ ብዙ ነገር በግልጽ ያሳየናል።ከባድ ወንጀልን ባለማውገዝ ኢትዮጵያን ለማፍረስ እየሰራ ያለ ቡድንን የመደገፍ ከባድ ወንጀለኛነታቸውን ዕያሳዩን ነው!
አንተነህ ቸሬ
አዲስ ዘመን ጳጉሜ 1/2013