ከኖረበት አካባቢ አዲስ አበባ ለመምጣቱ ምክንያት የተሻለ ህይወትን ፍለጋ ነበር። ተወልዶ ባደገበት የጎጃም ገጠር እድሜውን የገፋው በእርሻ ስራ ላይ ነው። ለዓመታት በግብርናው ሲዘልቅ ኑሮና እቅዱ ከገጠር ህይወት አልራቀም። በአካባቢው መልካም ገበሬ መሆን፣ ስሙን በጥንካሬ ማስጠራት ምኞት አድርጎት ዘልቋል ።
ደርቤ እንደ እድሜ እኩዮቹ የትምህርት እድልን አላገኘም። ወላጆቹ ቀድመው ያስተማሩት ግብርናን ነበር። እሱም ቢሆን በወቅቱ ለምን ብሎ አልጠየቀም። ከቤተሰብ ፣ ከአካባቢ የተረከበውን የእርሻ ስራ እየከወነ የምርቱን ፍሬ ከመረ።
ዓመት አልፎ ዓመት ሲተካ የደርቤ ህልም እርሻና ከብቶቹ ናቸው። ሁሌም ለከርሞ የሚዘራውን፣ የሚያፍሰውን፣ የሚከምረውን ምርት እያሰበ ያቅዳል። በጉልበቱ ድካም በላቡ ወዝ ያሰበው እውን ሲሆን የልቡ ይሞላል። መልካም ገበሬነቱ ያኮራዋል። ጥንካሬ ብርታቱ ያስደስተዋል።
አዲስ ህልም
ደርቤ በእርሻው መሀል በትካዜ የሚዋጥበትን ሃሳብ በቀላሉ መተው አልፈለገም። በጉዳዩ አንድ ሰሞን ጊዜ ሰጥቶ ሲብሰለሰልበት ነበር። መብሰልሰሉ ትርጉም ሰጥቶም በየአጋጣሚው ውል እያለው ተቸግሯል። ይህ ስሜት አብሮት ቢሰነብት መቁረጥ፣ መጨከን እንዳለበት አምኗል።
በሬዎቹን በጠመደ ቁጥር የሚሸፍተው ልቡን ‹‹ተው›› ማለት አልቻለም። አሁን መንገድ ያሰቡ እግሮቹ ተጣድፈዋል። መሄድ፣ መራቅ፣ እንደሌሎች መለወጥ አምሮታል። ውሳኔው በሬዎቹን አስፈትቶ፣ ካደገበት ቀዬ አርቆ የሚወስደው ሆኗል። እንዲህ በመሆኑ የሚቆጭ፣ የሚናደድ አይመስልም።
ስለ አዲስአበባ ደግ ደጉን ሲሰማ የቆየው ደርቤ ኑሮውን በስፍራው ለማድረግ ከወሰነ ቆይቷል። አስቀድሞ አዲስአበባ የዘለቁ የአገሩ ልጆች ዛሬ ያሉበትን ያውቃል። አብዛኞቹ በኑሮ ተለውጠዋል። ጥቂት የማይባሉት ለበርካቶች ተርፈዋል።
አዲስአበባ
ደርቤ እንዳሰበው ሆኖ የአዲስአበባን ህይወት ተቀላቀለ። በከተማው የአገሩን ልጆች ሲያገኝ ኑሮን እንደአመጣጡ ለመቀበል ራሱን አዘጋጀ። ስፍራውን እስኪለምድ፣ ዘመድ ወዳጅ እስኪያውቅ ጉልበቱ የፈቀደውን ከወነ ።
ውሎ ሲያድር ለወደፊት ማንነቱ የሚበጀውን የስራ አይነት መዘነ። አዲስ አበባ የመረጠውን አቀረበችለት፣ ያሻውን እየሰራ በጉልበቱ፣ በላቡ፣ በድካሙ ቀናትን ተሻገረ። በሰራው ልክ ለኪሱ አላጣም። ያገኘውን እየቋጠረ ስለነገ መትጋቱን ቀጠለ።
ደርቤ አዲስ አበባ በመጣ በዓመቱ ብቸኝነቱን የምትጋራ፣ ሃሳብ ጭንቀቱን የምትካፈል የትዳር አጋር አገኘ። ባለትዳር ከሆነ በኋላ ሃላፊነቱ ጨመረ። ቤት ተከራይቶ መኖር ሲጀምር ወጪዎቹ ጨመሩ። በኑሮው ደስተኛ መሆኑ ነገውን በተሻለ እንዲያስብ እድል ሰጠው።
ጥንዶቹ አዲስ ህይወት እንደጀመሩ ኑሯቸው ሰመረ። በመተሳሰብ ማደራቸው ጎጇቸውን አቅንቶ ህይወታቸውን አደመቀ። አጋርነታቸውን በመተሳሰብ አጥንተው በፍቅር ዘለቁ። የአዲስአበባ ህይወት እንደገጠር አይደለም። እህሉ እንዳሻው ከአውድማ፣ አይታፈስም። ወተትና እርጎው ከጓዳው አይቀዳም። ይህን እውነት የሚያውቀው ደርቤ አቅሙን እንደቤቱ መጥኖ መኖሩን ቀጠለ።
ደርቤና ባለቤቱ የትዳር ህይወታቸውን የሚያደምቁ፣ ሁለት ልጆች ካገኙ በኋላ የቤታቸው ሃላፊነት ይበልጥ ጨመረ። ትናንት ለራሳችን ይሉት የነበረው ወጪ ዛሬ ልጆቻውን አክሎ ፍላጎትን አበዛ። እንዲህ በሆነ ጊዜ የደርቤ የስራ ውሎ ከነበረበት ሊቀየር ግድ አለው።
በቀን ስራ ውሎ የተጀመረው መተዳደሪያ ቀስ በቀስ እድገት አሳየ። ደርቤ ኑሮውን የመለወጥ ጥረቱ ሰመረለት። እንጨትና ከሰል እያስመጣ መሸጥ ጀመረ። ስራው በርከት ያሉ ደንበኞችን አፈራለት። ከሰልና እንጨቱ እየተገላበጠ የሚያመጣው ገቢ ትርፍ ቢያስገኝለት ስራውን ከፍ ማድረግ አሰበ።
ካዛንቺስ አካባቢ የእንጨትና የከሰል መደብር ከፍቶ ስራውን በሰፊው ተያያዘው። ባለቤቱን ጨምሮ ሁለት ልጆቹ መተዳደሪያ የሆናቸውን የሽያጭ ቦታ በትኩረተ ተሳተፉበት። ደርቤ በከሰልና በእንጨት ንግድ ታዋቂ ነጋዴ ሆነ።
አንዳንዴ በስራው አካባቢ ተጨማሪ አማራጮች ይገኛሉ። የሚሸጡ፣ የሚገዙ እቃዎችን ደላሎች ያገበያያሉ። እንዲህ አይነቱ አጋጣሚ በተገኘ ጊዜ ሁሉም ደላላ ይሆናል። የሚገዛውን እያተረፈ ፣ የሚያተርፈውን ያስማማል።
በአካባቢው የብሎኬት ማምረቻዎች ተስፋፍተዋል። በነዚህ ቦታዎች በርካቶች ጉልበታቸውን ከፍለው ላባቸውን ጠብ አድርገው ያድራሉ። ከመሃላቸው የበረቱ የራሳቸውን ከፍተው ሌሎችን ይቀጥራሉ። ስራን ከእነሱ የሚማሩ አስተዋዮችም የነገውን መለወጥ እያሰቡ የተሻለ ያቅዳሉ።
ደርቤ በስራው መጠንከር፣ በኑሮው መለወጥ ከጀመረ ወዲህ ብዙዎችን ተዋውቋል። የትምህርትን ጫፍ አለማየቱ ዛሬ አንብቦ ላለመጻፉ ምክንያት ሆኗል። ይህ አጋጣሚ አሁንም ድረሰ በጣት አሻራው ያስፈርመዋል። አሁን የደርቤና የቤተሰቦቹ ህይወት እየተለወጠ ነው። ይህን አሳምሮ የሚያውቀው አባወራ ለራሱና ለቤተሰቦቹ መጠበቂያ የሚሆን መሳሪያ እንደሚያስፈልገው ሲያስብበት ቆይቷል። ይህ ሃሳብ ውስጡ እንዳለ አንድ ቀን ከአንድ ሰው ጋር ተገናኘ።
ሰውዬው ደርቤ የሚያስበውን ጉዳይ ካወቀ ቆይቷል። በእጁ የሚገኘውን ሽጉጥ ሊሸጥለት እያስማማው ነው። ለዚህ ፍላጎት ያደረበት ነጋዴ የመሳሪያውን አቅምና ጉልበት ፈተሸ። እያገላበጠ፣ እያነጣጠረ ሲነካካው በእጁ ያለውን ስታርተር ሽጉጥ ወደደው። ሽጉጡ ህገወጥ ቢሆንም ዋጋ ተነጋግሮ አስቀረው።
ደርቤ ሽጉጡን ከገዛ በኋላ የስራ ቦታውና የቤተሰቡ ደህንነት ከስጋት የራቀ መሰለው። ኮሽ ባለ ቁጥር በእጁ ያለውን መሳሪያ ያስባል፣ እያሰበ ማድረግ የሚገባውን ያቅዳል። ሽጉጡ ከብዙ ጉዳዮች እንደሚጠብቀው እየተማመነ ነው። አንዳንዴ በድብቅ ይዞት መውጣት ልምዱ ነው። ከጎኑ ወሽቆት ይውላል ።
ደርቤ ዓመታትን በሰራበት የካዛንቺስ አካባቢ ከሚያውቀው በቀለ ደስታ ጋር የዓመታት ባልንጀሮች ናቸው። በቀለ ልክ እንደሱ የእንጨትና ከሰል ነጋዴ ነው። ሁለቱም ለተጨማሪ ገቢ ተገዝቶ የሚሸጥ እቃ ካገኙ ዓይናቸውን አያሹም። እቃውን በአነስተኛ ዋጋ እየገዙ አትርፈው ይሸጣሉ።
አሁን አራት ኪሎና አካባቢው በልማት ምክንያት እየፈረሰ ነው። በዚህ ስፍራ ከቆዩ ነባር ቤቶች የሚወገደው በርና መስኮት ለሽያጭ መዋል ጀምሯል። ቦታውን አስረክበው ከሚሄዱ ነዋሪዎች ቤት የሚገኘውን ጥቅም ያወቁ አንዳንዶች ዕቃዎችን እየገዙ በተሻለ ዋጋ መሸጥና መለወጥ ልምዳቸው ሆኗል።
ከቀድሞ መኖሪያ ቤቶቹ የሚገኙ ቁሶቹን ብዙዎች ይፈልጓቸዋል። በተለይ ብረት የሆኑ በርና መስኮቶች፣ የበረንዳ መከለያዎችና መሰል ንብረቶች በገበያው ተፈላጊነታቸው የላቀ ነው። እነዚህን ጨምሮ ያገለገሉ የመጸዳጃ ዕቃዎች ፣ የመብራት አምፖሎችና የቤት ቁሳቁሶቸ የገዢዎችን ዓይን ይስባሉ። እነዚህን ቁሶች ለመሸጥ፣ ለመለወጥ በየቦታው የሚደልሉና የገዙትን አትርፈው የሚሸጡ፣ በርካቶች ናቸው።
ደርቤና በቀለ እንዲህ ዓይነት ንብረቶች ባገኙ ጊዜ ፈጥነው ይገዛሉ። የገዙትን አክርመውም ለፈላጊዎች በጥሩ ዋጋ ይሸጣሉ። እንዲህ አይነቱ አጋጣሚ ለበርካቶች ሲሳይ ሆኖ ጎዶሎን ሲሞላ ቆይቷል። ሽያጩ ያዋጣቸው ገቢው ያተረፋቸው አንዳንዶች ንግዱን እንደስራ ቆጥረው ይጠቀሙበታል።
አንድ ቀን ደርቤና በቀለ ከልማት ተነሺዎች የተገኘ የቤት ፍራሽ ቆርቆሮ ገዝተው ከእጃቸው አስገቡ። ቆርቆሮው እንደሚያተርፋቸው አውቀዋል። ለገዙት ዕቃ ዋጋ ተምነው፣ ትርፋቸውን አሰቡት። እንዳሉት ሆኖ ሽያጩ የተሻለ ፍሬ አለው። ይህን አውቀው ቀንና ጊዜን ጠበቁ ።
ንብረቱ እጃቸው በገባ ጥቂት ቀናት ከእነ ደርቤ የእንጨትና ከሰል መሸጫ ገዢዎች ተመላለሱ። ባልንጀሮቹ የመሸጫ ዋጋውን ቆርጠው እንቅጩን ተናገሩ። አንዳንዶች እየተከራከሩ፣ ዋጋ ለማስቀነስ ሞከሩ። ሌሎች በሽያጩ ሳይስማሙ ያለ ይሁንታ ተለያዩ። በሌላ ቀን በአካባቢው ብቅ ያሉ ገዢዎች ስለቆርቆሮው ጠየቁ። ሻጮቹ አጠቃላይ ዋጋው አስራ አምስት ሺህ ብር ስለመሆኑ ነገሯቸው። ገዢዎቹ ከቆርቆሮው ገሚሱን ብቻ እንደሚወስዱ ተናገሩ።
ሻጮቹ ከቆርቆሮው ቆጥረው፣ የሚገባውን ዋጋ ቆርጠው ገንዘቡን ተናገሩ። ገዢዎች ባሉት ተስማምተው አምስት ሺህ ብር ቆጥረው ለሻጮች አስረከቡ። ውስን ቆርቆሮው ከእጃቸው እንደወጣ ደርቤና በቀለ ስለቀሪው ተወያዩ። የመጀመሪያውን የሽያጭ ብር ደርቤ ወሰደ።
አሁን ቀሪውን የአስር ሺህ ብር ቆርቆሮ በቀለ ሸጦ ብሩን እንዲካፈሉ ተስማምተዋል። በቀለም ሽያጩን ከውኖ ገንዘቡን ለማምጣት ቃል ገብቷል። ደርቤ የቀደመውን ብር ከወሰደ በኋላ ቀሪውን ብር ለማግኘት የቆርቆሮውን መሸጥ ጠበቀ። ይህን አስቦም በቀለን ደጋግሞ ጠየቀ። በቀለ ባልንጀራው ያለውን አድምጦ ጥቂት እንዲጠብቅ ነገረው። በስምምነት ተለያዩ።
ቀናት መቁጠር ጀምረዋል። ደርቤ በቀለ እጅ ያለውን ቀሪ ገንዘብ አልዘነጋም። ባገኘው ቁጥር ስለገንዘቡ እያነሳ ይጠይቃል። እስካሁን የሰጠው ምላሽ በቂ አለመሆኑ እያናደደው ነው። እቃውን በአስር ሺህ ብር እንደሸጠው ደርሶበታል። ደርቤ ይህን ከሰማ ጀምሮ ገንዘቡን እንዲሰጠው ሲለምነው፣ ሲያስጠይቀው ቆይቷል።
በቀለ የደርቤን ጥያቄ ከራሱም ከሌሎችም ሰምቷል። በተገናኙ ቁጥር ገንዘቡን እንደሚመልስ ቃል ይገባል። ምክንያትና ሰበብ እየፈጠረም ቀናት ያራዝማል። ደርቤ በበቀለ ደርጊት ብሸቀት ጀምሮታል። ቃሉን ያለማክበሩ ያናድደዋል። እንዲህ በተሰማው ጊዜ ሰዎች ልኮ ያስጠይቀዋል። መልዕክተኞቹ በየጊዜው ለውጥ የለሽ ምላሽ ያመጡለታል። ውስጡ ይተክናል። ደጋግሞ ያማርራል።
ደርቤና በቀለ ዓይጥና ድመት መሆን ከጀመሩ አንድ ዓመት ተቆጠረ። ጊዜውን የሚያሰላው ደርቤ ገንዘቡ ያደርግለት የነበረውን ጥቅም ደጋግሞ ያስባል። እያሰበም ይበሳጫል። ብስጭቱን ያስተዋሉ አንዳንዶች ሊመክሩት፣ ሊያጽናኑት ይሞክራሉ። ደርቤ በቀለ ያደረገውን እያሰበ ጥርሱን ይነክሳል።
መስከረም 2 ቀን 2006 ዓ.ም
አዲስ ዓመት በተለመደው ድምቀት በየቤቱ ተከብሯል። ዕለቱን በተለየ ስሜት የተቀበሉ በርካቶች በአዲሱ ዘመን መልካም ምኞታቸውን፣ አዲስ እቅዳቸውን፣ እያሰቡ ነው። ከአንድ ቀን በፊት የተከበረው እንቁጣጣሽ በብዙዎች ዘንድ መልካም እንደሆነ አልፏል።
ማግስቱን በትናንትናው ስሜት የተቀበሉት አንዳንዶች ቀናቸውን ብሩህ ሊያደርጉ ከመዝናኛው፣ ከሲኒማው ፣ ከዘመድ ቤት ውለዋል። ዕለቱ የበዓል ማግስት ነው። ልክ እንደትናንቱ በድምቀት ታጅቧል። በአገር ልብስ የደመቁ በጎዳናው ይታያሉ። የበዓሉ ድባብ አልደበዘዘም። በየሆቴሉ ሙዚቃ ይሰማል። በየቤቱ የወጥ ሽታ ያውዳል።
ደርቤ አዲስ ዓመትን ከቤተሰቦቹ ጋር አሳልፏል። ባለቤቱና ሁለቱ ልጆቹ አብረውት ውለዋል። ከበዓል ማግስት ወደስራው ዘልቆ ደንበኞችን ሲያስተናግድ አርፍዷል። ከጀርባው የወሸቀው ሽጉጥ ዓይን እንዳይስብ ሸሸግ እያደረገው ነው።
ከሰአታት በፊት ደርቤ ከበቀለ ጋር ክፉ ደግ ተነጋግሯል። ንግግሩ ከውስጡ አልጠፋም። ቂም ይዟል፤ አምርሯል። ምሽት አራት ሲሆን ደርቤ ከርቀት ሰዎችን ተመለከተ። ከመሃላቸው ነጥሎ ካለው አንደኛውን አስተዋለው በቀለ ነበር።
ሰዎቹ አጠገቡ እስኪደርሱ ጠበቀ። ከበቀለ ጋር ፊት ለፊት ተያዩ። ደርቤ የተለመደውን ጥያቄ አቀረበ። ‹‹እባክህን ገንዘቤን ስጠኝ፣ ሀቄን መልስልኝ›› አለው። ይህን የሰማው በቀለ ፊቱ በንዴት ጋየ። እንደቀድሞው አልተጨነቀም፣ አልተለማመጠም። ከወትሮ የፈጠነ ምላሽ ሰጠው። ‹‹የምን ገንዘብ ነው ፤አትላክብኝ፣ አትጠይቀኝ፣ ስሜን አታጥፋው አለው››
ደርቤ ንዴቱ ጨመረ ፤ ትዕግስቱ አለቀ። የበቀለን ተጨማሪ ስድቦች ለመስማት አልጠበቀም። ከጀርባው ያለውን ሽጉጥ እየነካካ አጠገቡ ደረሰ። ፈጥኖ የተቀባበለ ሽጉጡን ሲያወጣ ቀጣዩን የገመተ አልነበረም። ቃታውን ስቦ ወደ በቀለ አነጣጣረ። ከሽጉጡ አፍ ፈጥና የተወረወረች አንዲት ጥይት ከበቀለ ግራ ጎን ዘልቃ ተመሰገዘገች።
በብሎኬት መሸጫው መንደር ጨኸት በረከተ። ግርግር ተፈጠረ። ገሚሱ የተመታውን ለማንሳት፣ ቀሪው የመታውን ለመያዝ ተዋከበ። ደርቤ በቀለን በሽጉጥ እንደመታ ወደቤቱ ገሰገሰ። ቤቱ ሲደርሰ ባለቤቱን አገኛት። የመደናገጥ ፣ መዋከቡን ስታይ ምክንያቱን ጠየቀች። ደርቤ ትንፋሹ እያጠረው የሆነውን ነገራት። ባለቤቱ ክው እንዳለች ልታረጋጋው ሞከረች ። መረጋጋት አልቻለም። ራሱን ሊያጠፋ እንደሆነ አሳወቃት። አልተቀበለችውም።
ባለቤቱ እጁን ይዛ እጁን ለፖሊስ መስጠት እንዳለበት ነገረችው። ጥቂት ተረጋጋ። ሽጉጡ የት እንዳለ ጠየቀችው። ያለበትን ነገራት። ተረጋግቶ ቤት እንዲያድር አሳመነችው። በሃሳቧ ተስማማ። ንግግራቸውን የምትስማው ልጃቸው ሽጉጡ የት እንዳለ አውቃ ወደስፍራው አመራች። ከቆሻሻ መጣያው አገኘችው።
በነጋ አልነጋ ጭንቀት ያደረችው የደርቤ ልጅ ጨለማው ሳይገልጥ ሽጉጡን በልብሷ ሸሽጋ ከቤት ወጣች። እናቷ አብራት አለች። ልጅ ድንጋጤ ይዟታል፤ እየተንቀጠቀጠች ትገላመጣለች። ከአንድ ዘመዳቸው ጊቢ ደርሰው በሩን ሲያንኳኩ ሰአቱ ከለሊቱ 11፡ ከ 30 ይል ነበር። ገነት እየተዋከበች አባቷ ከሰው ስለተጣላ ሽጉጡን እንዲደብቅላት ነገረችው። ዘመድዬው ያለችውን አምኖ ተቀበለ።
የፖሊስ ምርመራ
ወፍ እንደተንጫጫ ከደርቤ መኖሪያ ቤት የደረሱት ፖሊሶች ግለሰቡን በቁጥጥር ስር አዋሉ። የወንጀሉ ፍሬ የሆነውን ሽጉጥም ከሚገኝበት ደርሰው ተረከቡ ። ደርቤና ሚስቱን ጨምሮ አራት ተጠርጣሪዎች ለጥያቄ ቀረቡ። ደርቤ ድርጊቱን ስለመፈጸሙ አልካደም። መርማሪ ፖሊስ ረዳት ኢንስፔክተር ታምሩ ቀነኒ ተገቢውን ምርመራ አጠናቆ መዝገቡን ለዓቃቤህግ ክስ አሳለፈ።
ውሳኔ
ህዳር 3 ቀን 2008 ዓ.ም በችሎቱ የተሰየመው የልደታው ከፍተኛ ፍርድ ቤት በተከሳሹ ላይ የመጨረሻ ውሳኔ ለማሳለፍ በቀጠሮ ተገኝቷል። ተከሳሹ ጥፋተኛ ስለመሆኑም አረጋግጧል። ፍርድቤቱ ለወንጀሉ ተባባሪ ናቸው የተባሉ እናት ልጅ እንዲሁም ዘመዳቸውን ጉዳይ ሲመረምር ቆይቷል። በዕለቱ በሰጠው ውሳኔም ተከሳሹ እጁ ከተያዘበት ጊዜ አንስቶ በሚታሰብ የ14 ዓመት ጽኑ እስራት እንዲቀጣ በይኗል። ሌሎቹ ተከሳሾች እያንዳንዳቸው የ500 ብር የገንዘብ ቅጣት እንዲጣልባቸው ሲል ወስኗል።
መልካም ስራ አፈወርቅ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 29/2013