የተወለደው በሐረር ከተማ ነው። አባቱ የህክምና ባለሙያ በመሆናቸው ቤተሰቡ በስራ ምክንያት ወደ ተለያዮ አካባቢዎች ይዘዋወሩ ስለነበር የልጅነት እድሜውን ከቤተሰቦቹ ጋር በተለያዩ አካባቢዎች በመዘዋወር አሳልፏል። በተለይ ምስራቅና ደቡብ ምስራቅ የኢትዮጵያ አካባቢዎችን የመመልከት ዕድል አግኝቷል።
ከተወሰነ ዕድሜው በኋላ ደግሞ ቤተሰቦቹ ኑሯቸውን በአዲስ አበባ በመመስረታቸው ረዥሙን የዕድሜ ዘመኑን ያሳለፈው በአዲስ አበባ ከተማ ነው። ቤተሰቦቹ ሁለት ልጆችን ብቻ የወለዱ ሲሆን ለቤተሰቡ ሁለተኛ ልጅ ሆኖ ነው ይህችን አለም የተቀላቀለው።
የልጅነት ፍላጎትና ህልሙ አርቲስት መሆን ነበር። በተለይም ለስነጽሁፍ ከፍተኛ ፍላጎትና ዝንባሌ ነበረው። የልጅነት ህልሙን ለማሳካት በአዲስ አበባ ቴአትርና ባህል አዳራሽና በተለያዩ የኪነጥበብና የስነ ጽሁፍ ክበባት በመሳተፍ ፍላጎቱን ለማሳካት ጥረት አድርጓል።
ውስጡ ያለው ፍላጎት ከስነ ልቦና ጋር የተያያዘ ነው።በዩኒቨርሲቲ ሲማር የወሰደው የሳይኮሎጂ ትምህርትም የረጅሙን ህይወት መስመር አማላከች የሆነለት ይመስላል። ከሰመራ ዩኒቨርሲቲ ከወጣ በኋላ ቀን እያስተማረ ማታ በአዲስ አበባ ዮኒቨርሲቲ የማህበረሰብ ስነ ልቦና ትምህርት ክፍልን በመቀላቀል ሁለተኛ ዲግሪውን ሰርቷል። ይህ ለዛሬው እንግዳችን ትልቅ ምዕራፍ ከፋች እንደሆነለትም ይመሰክራል።
በማህበረሰቡ ያለውን ችግር ለመፍታት ኢትዮጵያዊ መፍትሄ ማምጣት ያስፈልጋል የሚል እምነቱ ነበር ለመማር ምክንያት የሆነው።እየገጠመን ያለው ችግር ኢትዮጵያዊ ነው፣ መፍትሄው መሆን ያለበትም ኢትዮጵያዊ ነው፣ ህብረተሰቡን ማንቃትና ለዚህ ማዘጋጀት ያስፈልጋል ከሚል እሳቤው ነው። በማህበረሰብ ስነ ልቦና ህብረተሰቡን በመገንባት በርካታ ተግባራትን መስራት ችሏል።ኑሮውን በአገረ አሜሪካ በማድረግ በኢሳት ቴሌቪዠን የፖለቲካ ተንታኝ ከሆነው ጋዜጠኛ ጴጥሮስ መስፍን ጋር ያደረግነው ቆይታ እንደሚከተለው ይቀርባል።
አዲስ ዘመን:- ኢትዮጵያዊነትን እንዴት ትገልጸዋለህ?
ጋዜጠኛ ጴጥሮስ:- ለእኔ ኢትዮጵያዊነት ብዙ ቀለም አለው። ኢትዮጵያዊነት ቀስተ ደመና ነው። የበርካታ ቀለም ውህድ ውጤት ነው። አንዱን ከአንዱ ነጥለህ የማታወጣው ማለት ነው። ስለዚህ ኢትዮጵያዊነት በብዙ ህብረ ብሄራዊነት የተገነባ የጋራ አንድ ማንነት ነው። ከእዛ ውስጥ አንዱን ሰበዝ ነጥለህ ማውጣት አትችልም።
ቀስተ ደመና ስትል ካሉት ቀለማት አንዱን ነጥለህ አይደለም። ሁሉም በእዛው ውስጥ በአንድ ለይ የተዋሃደ ነው። ስለዚህ ለእኔ ኢትዮጵያዊነት የብዙ ውህድ ውጤት ነው። በብዝሃነት ውስጥ የሚገኝ አንድነት ነው። ከተለያየ ማንነት፣ አስተሳሰብና ባህል መጥቶ ግን በአንድነት ተላምዶ የሚኖር ማህበረሰብ ነው ለእኔ ኢትዮጵያዊነት።
አዲስ ዘመን:- የኢትዮጵያን የዲፕሎማሲ ስራ እንዴት ትገመግመዋለህ?
ጋዜጠኛ ጴጥሮስ:- አገራችን ያለችበትን የዲፕሎማሲ ቀውስ ስናስብ ዛሬ ላይ ብቻ ያለውን ካወራን ንፋስ እንደመከተል ይሆናል። ዘለቅ ብለን ከየት ተነስቶ ነው እዚህ የደረሰው የሚለውን ማየት ያስፈልጋል። አገራት በዲፕሎማሲ ብዙ የሚሰሯቸው ስራዎች አሉ። አንደኛው የዲፕሎማሲ አካል ገጽታ ግንባታ ነው። ሌላኛው ደግሞ የአገርን እቅድና ሃሳብ መሸጥ ነው። ምክንያቱም ያለው ነባራዊ ሁኔታ እድገታችንን ለማፋጠን አጋሮች ያስፈልጉናል። አለማችን ደግሞ በግሎባላይዜሽን ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ እየተቀራረበ መጥቷል።
የአንዱ አገር ጉዳይ የሌሎች በርካታ አገሮችን የውስጥም የውጭም ጉዳዮችን የሚነካበት ሁኔታ አለ። አሁን ያለንበትን ሁኔታ ማየት ትችላለህ። የኢትዮጵያ ጉዳይ የመላው ምስራቅ አፍሪካ፣ ከአፍሪካ ሲያልፍም የአውሮፓና የአሜሪካ አጀንዳ የሆነበት ነገር አለ። የቀይ ባህርና የባህረ ሰላጤው ጉዳይ የሆነበትን ነገር ታያለህ። ስለዚህ ዲፕሎማሲ ከገጽታ ግንባታ ባሻገር ከአንድ አገር ህልውና ጋር የሚያያዝበት ሁኔታ ላይ ነን። ከእዚህ አንጻር ኢትዮጵያ የገባችበት የዲፕሎማሲ ቅርቃር ዛሬ ወይንም ትናንት የመጣ ሳይሆን ሲወርድ፣ ሲዋረድና ሲንከባለል የመጣ ነው።በዋነኛነት ሁሉም ኢትዮጵያዊ ሃላፊነት ተሰምቶት የአገሩ ዲፕሎማት ነው ብንልም ግን እንደ ተቋም የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ይህንን ሃላፊነት ወስዶ ይሰራል። የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ደግሞ ላለፉት በርካታ ዓመታት የነበረበት ትልቁ ችግር ከጎጠኝነት የወጣ አልነበረም።
የአንድ ጎሳ ወይም ቡድን ፍላጎት የሚያስከብር ተቋም ነበር። ይሄ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ብቻ ሳይሆን በኢትዮጵያ ያሉ የበርካታ ተቋማት ችግር ሆኖ ቆይቷል። በሃላፊነት ደረጃ የአንድ ብሄር ተወላጅ ካለ የእርሱን ሰዎች የመሰብሰብ በጣም የተለመደ ነው። ለሃገሬ የቱ ይጠቅማል ሳይሆን ለእኔ ወገን የቱ ይጠቅማል የሚል የራስን ቡድን የማከማቸት ችግር ነበር።
ይህንን ተከትሎ ደግሞ መንግስት ለረጅም ጊዜ ግልጽ ባያደርገውም ግን በተከተለው እስትራቴጂ አምባሳደርነት ከፖለቲካው ገለል የሚደረጉ ወይም መገፋት ያለባቸው ሰዎች የጡረታ ስፍራ ነበር። በሚሄዱበት አገር ውስጥ ብቃት ኖሯቸው የአገርን ጥቅም የሚያስከብሩ ሰዎች ሳይሆኑ በፖለቲካው ውስጥ በነበራቸው ተሳትፎ ለጊዜው ገለል እንዲሉ ወይም እንደካሳ የሚቆጠርላቸው ቦታ ነበር።በዲፖሎማሲው፣ በቋንቋ ክህሎት፣ በትምህርት ዝግጅት ብቃት የሌላቸው ሰዎች የሚቀመጡበት ነው። ይህንን በውጭ አገር የሚኖሩ ሰዎች በደንብ ይረዱታል። በየኤምባሲዎቹ የራሳቸውን ዘመዶች፣ የራሳቸውን ሰዎች፣ በጥቅም የሚፈልጓቸውን ሰዎች የሚሰበስቡበት ስፍራ ነው። የእኛ የዲፕሎማሲው ዋና አውታር የአገርን ጥቅም ከማስከበር ወጥቶ የግለሰቦችንና የቡድንን ጥቅም ማስከበር ላይ ያተኮረ ነበር።
ለውጥ መጥቶ ግለሰቦች ወደ አገርነት መቀየር ሲጀምሩ፣ የግለሰቦች ሚና ወደ አገር ሚና መምጣት ሲጀምር፣ ከግለሰብ ይልቅ አገር መቅደም ሲጀምር እነዛ ሰዎች የቡድንና የግለሰብን ጥቅም እንጂ የአገርን ጥቅም ማስጠበቅ አልቻሉም። ከ60 በላይ ኤምባሲዎችና ቆንስላዎች ኖረውን ግን የኢትዮጵያን ጉዳይ በአግባቡ ማስረዳት የማንችልበት፣ በቋንቋ ክህሎት መሞገት የማንችልበት፣ ማስረጃ አቅርበን የማንሟገትበት ችግር ገጥሞናል።
የኢትዮጵያን ኤምባሲ በአሜሪካ በአብነት እናንሳ፤ ከለውጥ በፊት ጥቂት ሰዎች የሚምነሸነሹበት፣ ልደት የሚያከብሩበትና የሚጨፍሩበት ስፍራ ነበር። ከለውጡ በኃላ ብዙ ነገሮች እየተለወጡ ቢሆንም፤ ካለው ወሳኝ የፖለቲካ ስፍራ አንጻር በብቃት የኢትዮጵያን ሃሳብና አጀንዳ በአለም አቀፍ መድረክ መሸጥና ማሳየት የቻሉ አይደሉም።
አዲስ ዘመን:- ከዲፕሎማሲ ተግባር አንጻር ተቆርቋሪ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በቋሚነት ዋነኛው የሥራው ባለቤት ለማድረግ ምን መተግበር አለበት?
ጋዜጠኛ ጴጥሮስ:– ይህ ወሳኝ ተግባር ነው።ለረጅም ጊዜ ሲሰራ የነበረው ኢትዮጵያውያንን ከኢትዮጵያዊነት የማውረድ ስራ ነበር። ኢትዮጵያውያንን ከኢትዮጵያ ከፍታና ስሜት ወርደው መንደር፣ ጎጥና ቀበሌ እንዲሰበሰቡ ሲሰራ ነበር። በጎጥና በመንደር ተሰብስቦ ያለን ኢትዮጵያዊያንን ከእዛ ዝቅታ አውጥተህ ወደ ኢትዮጵያ ከፍታ መመለስ ያስፈልጋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ (ዶ/ር) ወደ ስልጣን ሲመጡ ከዳር እስከ ዳር ሕዝቡ ልቡን ከፍቶ የተቀበላቸው ኢትዮጵያዊነትን ይዘውት የመጡበትና የገለጹበት መንገድ ነበር። ከስራ በፊት በመጀመሪያው የምክር ቤት ንግግራቸው ነው ሰው የተቀበላቸው። እንድትገፋውና ወደ መንደር እንድትወርድ የገፋህን አስተሳሰብ ሰብሮ ወደ ኢትዮጵያ ከፍታ እንዲመለስ የሚያደርግ ነው።
በአገር ውስጥ ብቻ ሳይሆን በመላው አለም የተሰራጩ ኢትዮጵያውያን ላይ በየኤምባሲው ሲሰራ የነበረው ይሄ ነበር። የኢትዮጵያውያን ማህበር ብሎ ከመመስረት ይልቅ የትግራይ ማህበር፣ የአማራ ማህበር፣ የኦሮሞ ማህበር፣ የጉራጌ ማህበር በሚል ሰውን ወደ ተለያየ መንደር ውስጥ እንዲገባ ነው ያደረገው። ሰዎች ተወልደው ያደጉበትን አካባቢ ተመልሰው ማገዝና መርዳት ቢችሉ ጥሩ ነው።ግን ሃሳቡ እርሱ አልነበረም። ሰዎችን በትንንሽ ጎጥ ውስጥ ከፋፍሎ በጋራ በአንድነት የሚቆሙለትን አገርና አላማ ማሳጣት ነበር ስራው።
ስለዚህ የመጀመሪያው የኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት ስራ ላይ ትልቁ የመንግስት ስራ መሆን ያለበት በየጎጡ እንዲከፋፈሉ የተደረጉ ኢትዮጵያውያንን ወደነበሩበት ከፍታቸው እንዲመለሱና የባለቤትነት ስሜት እንዲሰማቸው የጉዳዩ ባለቤት ማድረግ ይገባል።
የግብጽ ዲፕሎማሲ ሲታይ፤ ግብጾች ገንዘብ አላቸው፣ ጂኦ ፖለቲክሱ በጣም የሚረዳቸው ቦታ ላይ ነው ያሉት፣ የአረብ ሊግ ደግሞ የግብጽ የልብ ትርታ ነው። ስለዚህ ግብጾች በየሄዱበት ቦታ ሁሉ የአገራቸው አምባሳደሮች ናቸው። ካላቸው ጠቀሜታዎች ባሻገርም እያንዳንዱ ግብጻዊ ምሁር ባለበት ዩኒቨርሲቲ፣ ባለበት ተቋም ውስጥ የአገሩ አምባሳደር ነው። በአገሩ ጉዳይ ላይ መንግስታቸው እስኪጠራቸው አይጠብቁም። እንዳውም መንግስትን እጁን ጠምዝዘው ሕዝብ የሚፈልገውን ጉዳይ እንዲፈጽም ያስገድዱታል።
ወደ እኛ አገር ስትመጣ መንግስታዊ በሆነ አሻጥር ኢትዮጵያውያን ከኢትዮጵያ ከፍታ እንዲወርዱ ተደርገው ኖረዋል። አሁን መንግስት ኢትዮጵያውያን ወደ ነበሩበት ከፍታ እንዲመለሱና የባለቤትነት ስሜት ላይ መሰራት አለበት።
እያንዳንዱ ሰው ሲሰራ እኔ የምሰራው ለአገሬ ነው የሚል አስተሳሰብ ማስረጽ ይገባዋል።አገርና ፓርቲ አንድ ላይ የተጣበቁ ናቸው፤ እነዚህን ነጥሎ መመልከት ይገባል። በፊት በነበረው ስርዓት ውስጥ መንግስትን ከረዳህ ኢህአዴግ የሚባለውን ቡድን ነው የምትረዳው። ስለዚህ ኢህአዴግን ላለመርዳት መንግስትን ትቃወማለህ፤ የአገርህ ጠላት እስክትመስል ድረስ በአገር ልማት ውስጥ ራሱ ተቃዋሚ ሆነህ የምትቀርብበት ጉዳይ አለ። ምክንያቱም አገር፣ መንግስትና የፖለቲካ ፓርቲ የተጣበቁ ተደርገው ስለተያያዙ ማለት ነው።
አሁን ያንን እሳቤ መነጠል አለብን። አገር ከሁሉም ቀድማ መምጣት አለባት፣ አገር ስትኖር ነው መንግስት ያለው፣ መንግስት ደግሞ የአገርን ህልውናና ሉዐላዊነት ላይ የማይደራደር ሊሆን ይገባል። መንግስትን የሚመራው ማንም ይሁን ማን አገር በሚቀጥልበት ሁኔታ ላይ የጋራ መግባባት መያዝ ያስፈልጋል። በኢትዮጵያ ትልልቅ ስፍራ ላይ ያሉ በርካታ ምሁራን አሉ። በስልጣን ደረጃም ትልልቅ ደረጃ ላይ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን አሉ። መንግስት እነዚህን ሰዎች ማንቀሳቀስና ወደ ስራ ማስገባት ይጠበቅበታል።
አሜሪካ በተለይ ዴሞክራቶች ተመሳሳይ ስህተቶችንና በደሎችን በኢትዮጵያ ላይ ፈጽመዋል። ይሄ ማለት አሜሪካ የእኛ ጠላት ነች ማለት አይደለም። አሜሪካ ወዳጅም ሆና በርካታ ነገሮች አድርጋለች። ተላላኪና ጉዳያቸውን የሚያስፈጽም መንግስት ካገኙ ምርጫቸው ነው።ጠንካራ መንግስት ካገኙም ከጠነከረውና ብርቱ ከሆነው መንግስት ጋር አብረው ይሰራሉ። የኢትዮጵያ መንግስት እዛ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን አብረን በመስራት ጠንካራ መሆናችንን ማስመስከር አለብን።
አዲስ ዘመን:- የተለያዩ የውጭ ሃይሎች በኢትዮጵያ ላይ ጫና ለማሳደር የሚያደርጉት ጥረት ከምን ይመነጫል?
ጋዜጠኛ ጴጥሮስ:- ብዙ ምክንያት አለ። አሁን ያለውን ስንመለከት የየአገራቱ የራሳቸው አገራዊና ቀጠናዊ ፍላጎቶች ትልቁን ሚና ይይዛል። ከራሳቸው ጥቅም አንጻር እንጂ ከሌላኛው ጥቅም አንጻር አያዩም። እንኳን እንደዚህ ባለ ጦርነት፣ የፖለቲካ ምህዳር አይደለም በጤናማው ጊዜ ለሰላማዊ አገልግሎት እንኳን እርዳታን ሲያቀርቡ ከሚረዳው አገር ጥቅም ሳይሆን ከራሳቸው ጥቅም አንጻር ነው የሚሰሩት።
ምሳሌ ብንወስድ የዩኤስ ኤይድ ዋና ዳይሬክተሯን ሳማንታ ፓወር ቃል ከገቡባቻቸው ጉዳዮች አንዱ ዩኤስ ኤይድን በመጠቀም የቻይናን ተጽእኖ በአፍሪካ ውስጥ ለማስቀረት ወይም ለመቀልበስ ነው። የሚለገሰው እርዳታ ላይ የተቀመጠው መልእክት የአሜሪካ ሕዝብ የሚሰጠው ርዳታ ነው። ርዳታው ዝም ብሎ የሚሰጥ ሳይሆን የአሜሪካንን ፖሊሲ ለማስፈጸም የሚሰጥ ነው እንጂ በጣም የዋህና ደግ ስለሆኑ ለሰው የሚራሩ ስለሆኑ ብቻ አይደለም። ምናልባት እርዳታው ሲሰበሰብ የዋህነት የተሞሉ ምስኪን አሜሪካውያን ይኖራሉ። ርዳታው ሲሰጥ ግን የአሜሪካን መንግስት ከራሱ ጥቅም ነው የሚሰጠው። የሌሎች አገሮችም ሲታይ ማስፈጸም የሚፈልጉት ፖሊሲና አጀንዳ አላቸው።
የራሽያና የቻይና ተጽእኖ እንዳይመጣ የመግባት እንቅስቃሴም አለ። አሜሪካኖች ከሱዳን ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት መስርተዋል። ሱዳን በኢትዮጵያና በህወሓት መካከል የተፈጠረውን ነገር እንድታደራድርም ጥሪ አቅርበዋል። የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ሱዳንን በዲሞክራሲ መንገድ ላይ ያለች አገር ናት ብሏል። የኢትዮጵያን መሬት ወርራ የያዘች አገር የወታደራዊው ክፍል ሲቪሉን አስተዳደር ሊውጠው ባለበት ስርዓት ውስጥ፣ ዜጎቹ አሁን ድረስ አመጽና ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ችግር ውስጥ ጥያቄ እያነሱባት ባለችባት ሁኔታ ውስጥ አሜሪካኖቹ ጥያቄያቸውን እያስፈጸሙ ስለሆነ እነርሱ ዴሞክራት አገር ናት ብለው በይፋ ተናግረውላታል። የሰው አገር ወርራ እያለች ለእነርሱ በአሸማጋይነት የምትመረጥ አገር ሆናለች።ይህንን ስታይ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚደረገው ጣልቃ ገብነት ከምን አንጻር እንደሆነ ትገነዘባለህ።
እያንዳንዱ አገር ላይ በግላቸውም በቀጠናውም ያላቸው ፍላጎት ነው። ኢትዮጵያ ያለችበት ጂኦ ፖለቲክስ በጣም ወሳኝ ነው።ኢትዮጵያ አቅሟን ገንብታ በጉልበቷ ጠንክራ መውጣት ካልቻለች በስተቀር መቼም ቢሆን ማንም አግዟት ጠንክራ አትወጣም። የቀይባህር ፖለቲካ፣ የህንድ ውቅያኖስ ጉዳይ አለ፣ ከጂቡቲና ከሶማሊያ ጋር ያለን ግንኙነት አለ።በሌላ በኩልም አባይን በመገንባት የምናዳብረው የኢኮኖሚ አቅምም አለ።
ግብጾች በዋነኝነት በኢትዮጵያ የውስጥ ጣልቃ እንዲገቡ የሚያደርጋቸው ግድቡ የሚይዘው የውሃ መጠን ብቻ አይደለም። ውሃው ለሃይል ማመንጫነት መሆኑን ያውቃሉ። ሃይል አመንጭቶ ተመልሶ ፍሰቱን አንደሚቀጥል ማንም ይገነዘበዋል። ግን እነርሱ የሚፈሩት ኢትዮጵያ በእዛ ግድብ የምትፈጥረው የኢኮኖሚ፣ የፖለቲካ፣ የመደራደር አቅም ይዞላት ይመጣል የሚል ነው።
ግብጽ በቀጠናው ላይ ብቻዋን አደራዳሪ፣ ተወካይም የሁሉም ነገር የበላይ ሆና ያለችበትን ነገር ኢትዮጵያ መንጠቅ ትጀምራለች። ምክንያቱም ግብጽ አብሯት ያለው አረብ ሊግ ሲሆን፤ ኢትዮጵያ ግን የአፍሪካ ሕብረት የሚባል ሰፊ የሆነ አቅም ያለው ህብረት ማዕከል ናት።
ኢትዮጵያ በእዚህ አቅሟ የምታድግና የምትጎለብት ከሆነ ጉዳዩ አልፎ የግብጽን ሚና ወደ መንጠቅም ይደርሳል። የአፍሪካ ሕብረት ከኢትዮጵያ ጎን ነው የሚቆመው። ውሃው የሚፈጥረው ኢኮኖሚያዊ አቅም፣ በኢኮኖሚ የሚመጣ የኢኮኖሚና የሲፕሎማሲ አቅምም ያስፈራቸዋል። ያንን አቅምና ሃይሏን ካጣች ደግሞ አጋሮች ከግብጽ፣ ከሱዳን ጋር እንደነበሩት ሁል ጊዜም ከአሸናፊ ጋር ስለሚቆሙ ከኢትዮጵያ ጋር ይሆናሉ።ይሄ ለእነርሱ ሁል ጊዜ ስጋታቸው ነው። ይዞ የሚመጣው በርካታ ተያያዥ ጉዳዮችም አሉ። የቀይ ባህር ጉዳይ፣ ኢትዮጵያ፣ ሱማሊያና ኤርትራ እየመሰረቱት ያለው ጥንካሬ አለ። ስለዚህ በኢትዮጵያ ጉዳይ ጣልቃ እንዲገቡ የሚያደርጋቸው አንዱ ጉዳይ ይሄ ነው።
የህወሓት ፖለቲከኞች የውጭ ጣልቃ ገብነት እንዲኖር ይጋብዛሉ። ኢኮኖሚያችን አሁን እንደሚታየው ውጥረት ሊፈጥሩብን፣ ማዕቀብ ሊጥሉበን፣ የዶላር እጥረት እንዲመጣ ሊያደርጉ ይችላሉ። በተለይ መሰረታዊ የሆኑ ከውጭ የሚገቡ እንደመድሃኒት፣ ዘይት፣ ነዳጅ፣ ስንዴና የመሳሰሉትን ነገሮች ላይ ተጽእኖ ሊፈጥሩብን ይችላሉ።ኢኮኖሚያችን አሁን የሚታየው አይነት ግሽበት ሊያስተናግድ ይችላል፣ የኑሮ ውድነት ሊጨምር ይችላል። ግን የውጭ ሃይል በአንድ አገር ጣልቃ ስለገባ ያሸንፋል ማለት አይደለም።
ሊቢያን አሜሪካኖች አደቀቋት፤ ግን አምባገነንም ቢሆን ሊቢያ ለአሸባሪ የማይመች መንግስት ነበራት። አሁን እንደ እዛ አይነት መንግስት የላትም። አይ ኤስ አይ ኤስ የሰራውንና እንቅስቃሴው የሚታወቅ ነው።ሁል ጊዜም በሊቢያ ጉዳይ ስጋት ላይ ናት። በሊቢያ መንግስት ላይ ጠንካራውን መንግስት ካፈረሱ በኋላ ሌላ ጠንካራ መንግስት መመስረት ባለመቻሉ የትሪፖሊ መንግስት፣ የቤንጋዚ መንግስት እየተባለ በየቦታው አማጺ አለ። አሸባሪው እንደልቡ የሚፈነጭበትና ከሊቢያ አጎራባች ሁሉ ስጋት የሆነ ነገር እየተፈጠረ ይገኛል። ሶሪያን ስንመለከትም ሕዝቡን ስደተኛ አደረገው እንጂ የሚፈለገው ውጤት ሊመጣ አልቻለም።የመን ሌላ ምሳሌ ናት።አፍጋኒስታንን ስንመለከት ወደ 20 ዓመታት ጦርነት ተካሂዶባታል። በዚህ ጦርነት ውስጥ ወደ 65 ሺህ የሚጠጉ የአፍጋን ወታደሮች አልቀዋል።ከሁለት ሺህ በላይ የአሜሪካ ወታደሮች፣ ከአንድ ሺህ በላይ የኔቶ ወታደሮች ህይወታቸውን ሰውተዋል። በ10 ሺዎች የሚቆጠሩ ሲቪሎች በእዚህ ጦርነት ተገድለዋል። ከጦርነቱ የተመለሱ የአሜሪካ ወታደሮች በስነ ልቦና ቀውስ የሚጎዱ አሉ።ኢኮኖሚውም በእዚህ ምክንያት ተጎድቷል።
ከ20 ዓመታት በኋላ በአሜሪካ የታገዘው የአፍጋኒስታን መንግስት ካቡል ስትወረር ሙሉ ለሙሉ ሚኒስትሮቹን ይዞ ደም ላለማፋሰስ በሚል ወደ ካዛኪስታን ሸሽቷል። አሜሪካ ከቪየትናም በኋላ ትልቁን ውርደት አስተናግዳለች። ኤምባሲዋን ዘግታ ሰራተኞቿንና አጋዥ አፍጋኒስታውያንን ይዛ ወደ መሸሽ ነው የገባችው። ቻይና ከመጣው መንግስት ጋር በሰላም የመቀጠል ፍላጎት አላት። ቻይና (ይህ ቃለ ምልልስ እስከተደረገበት ጊዜ ድረስ) ኤምባሲዋን እስካሁን አልዘጋችም። የአሜሪካ ወታደር ከወጣ ከወር በልበለጠ ጊዜ ውስጥ መላ አገሪቱን ዋና ከተማዋን ካቡልንም ጭምር ተቆጣጠሩ፤ ታላቁን ቤተ መንግስትንም ያዙ። ታሊባኖች 20 ዓመታት በአሜሪካ አቅም ቢቀጠቀጡም ጣልቃ ገብነቱ ከኢኮኖሚ ባለፈ የጦርነት ጣልቃ ገብነት ቢሆንም ግን የህዝቡን ትግል ሊያሸንፉት አለመቻላቸውን ነው።
በኢትዮጵያ ጉዳይም በሕዝብ ብዛት፣ ባለን የስነ ልቦና ውቅርና በአስተሳሰባችንም ከአፍጋኒስታን ሕዝቦች የምንለይ ነን። እንኳን አሁን በሰለጠነው ዘመን ይቅርና በዛን ዘመንም ልዩነታችንን ጥለን ተዋግተን ያሸነፍን ሕዝቦች ነን። እኔ የሚያሳዝነኝ ህወሓትን የሚደግፉ፣ ሸኔን የሚደግፉ ሰዎች ወይም ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ተቃዋሚ ሃይሎችን መሳሪያ ያነገቡና ንጹሃንን ለሞት የሚዳርጉ ሃይሎችን የሚደግፉ በውጭም በውስጥም የሚገኙ ሃይሎች አሉ። የውጭ ድጋፍ የት ድረስ እንደሆነ ከታሊባን፣ ከአፍጋኒስታን መማር ያስፈልጋል።
አዲስ ዘመን:- ህጻናትን ለጦር ዓላማ ከማዋል አንጻር የሚስተዋለው የአሸባሪው ህወሓት ሁኔታ እንዴት ታየዋለህ? የአለም አቀፍ ሰብአዊ መብት ተቋማትና ሚዲያዎችም ድርጊቱን በችግሩ ልክ አለማውገዛቸው ለምንድን ነው?
ጋዜጠኛ ጴጥሮስ:– ከህጻናት ወታደርነት ባሻገር ወደ ኋላ ተመልሰን የማይካድራ እልቂትንም ማየት እንችላለን። በማይካድራ ያ ሁሉ ችግርና ሰቆቃ ተፈጸመ። የማይካድራ ሰቆቃ የሚዳሰስ፣ የሚታይና የሚጨበጥ እልቂት ነው። የእልቂቱ ተጎጂዎች በአካል በተንቀሳቃሽ ምስል እየተቀረጹ ምስክርነት ሰጥተዋል።የሞቱ ሰዎች መቃብራቸው አለ። ሊዳሰስ፣ ሊታይና ሊጨበጥ የሚቻል ነገር ነው። ግን ከእዚህ ይልቅ የአክሱም ጭፍጨፋ ተብሎ የሚወራው የበለጠ ሚዛን ደፍቶ ይታያል።
ማክሲን ፕላውት ወደ 700 ሰዎች ተጨፈጨፉ ብሎ ዜናውን አሰራጨ። ይህንን ተከትሎ በርካታ ድርጅቶች ጉዳዩን ለማጥናት ሞከሩ፣ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን ጥናት ሰርቷል። የሂዩማን ራይት ዋች በእዚህ ላይ ሰርቷል፣ ሲኤን ኤንም ዘገባ ሰርቷል። ሲኤን ኤን በሰራው ዘገባ የወዳደቁ ጫማዎችን እንጂ በትክክል የተቀበሩ ሰዎችን እንደማይካድራው የተጨበጠ ነገር ሊያሳየን አልቻለም። ሰው አልተገደለም ወይም ሲቪሊያንሶች አልተገደሉም እያልኩ አይደለም። ነገር ግን ተፈጸመ የተባለውን ተግባር በትክክለኛ ማስረጃ ሊያረጋግጡት አልቻሉም።ተፈጸመ ባሉት ደረጃ እንዳልሆነም በሚወጣው መረጃ የሚጋጭ መሆኑን ተመልክተናል።
የማይካድራው ግልጽ ሆኖ ሳለ የተሰጠው ሽፋን ግን በጣም አነስተኛ ነው። የዚህ ዋነኛ ምክንያቱ አንድም ትኩረት ሊሰጡት ስላልፈለጉ፣ ሌላው ደግሞ የእኛ የዲፕሎማሲ ድክመት ነው። በተገበቢው መንገድ መረጃዎችን እየሰነዱ በተለያዩ ቋንቋዎች ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ማቅረብና ማሰራጨት ላይ ክፍተት አለ።
ህጻናትን ለውትድርና ማሰለፍ በአለም አቀፍ ደረጃ ትልቅ ወንጀል ነው። እነሱ ሆን ብለው የሚያነሷቸው ወንጀሎች አሉ። ሴቶች ተደፍረዋል፣ ንጹሃን ተገድለዋል፣ ረሃብ ገብቷል ይላሉ። እነዚህ ሶስቱ ነገሮች አለም አቀፉን ማህበረሰብ የሚያነቃንቁ እውነቶች እንደሆኑ ስለሚያውቁ ነው። አንዳንዱ የምር የተፈጸመና በጦርነት የሚመጣ ጉዳት ነው። የጉዳት መጠኑን ትቀንሰዋለህ እንጂ ፈጽሞ ልታጠፋው አትችልም።
ይሄ ጉዳይ ለፕሮፖጋንዳ ሲባል የጮኸበት መጠን ነው ይሄንን ነገር ይዞ የመጣው። አጠቃላይ በኢትዮጵያ በኩል ህጻናት ወታደር ተደርገው መሳሪያ ይዘው ሲቆሙ መንግስት ለረጅም ጊዜ ተኝቶ ነበር። ህጻናት ወታደሮች ከስምንት ወራት በፊትም ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም መከላከያ ላይ ጥቃት ከተፈጸመ በኋላ በነበረው ጥቃት ለምሳሌ በዳንሻና አካባቢው በነበረው ጦርነት ላይ ህጻናት ተማርከው ነበር። እጅግ በጣም የሚያሳዝኑ ህጻናት ጦርነት ውስጥ ተሳትፈው የእዛን ጊዜ አጀንዳ አድርጎ ማቅረብ አልተቻለም። አሁን ከስምንት ወራት በኋላ ነው አጃንዳ ሆኖ የመጣው።በመንግስት በኩል ከዛን ጊዜ ጀምሮ አጀንዳ አድርጎ የማቅረብ የዲፕሎማሲና የፖለቲካው ስራ በጣም ደካማ ነው። ይሄ ወንጀል አፍሪካ ላይ ኡጋንዳ ላይ አምጾ ከነበረው ቡድን ጋር ይገናኛል። የቡድኑ ትልቁ ኪሳራ የሚባለው በእዚሁ ህጻናትን ለጦርነት በመጠቀም ምክንያት ነው። ትልቅ ውግዘት ደርሶበትም የአለም አቀፉ ማህበረሰብ የተረባረበበት። እነ ላይቤሪያና ሴራሊዩንን ብታነሳም ተመሳሳይ ነገር ታገኛለህ። አለም አቀፉ ማህበረሰብ ኢትዮጵያ ውስጥ እየተፈጸመ ያለውን ህጻናትን ለጦርነት ማሰለፍ ያላወገዙት ህወሓት እየገፋ እንዳለ ስላሰቡ ነው።
በየትኛውም መንገድ አሸንፎ የእነርሱ ሃሳብና አጀንዳ እንዲፈጸምላቸው ስለሚፈልጉ ነው። እንዴትም ብትጮህ አጀንዳቸው ስላልሆነ ሊሰሙ አይፈልጉም። በእኛም በኩል የተሰራው ስራ እጅግ በጣም አነስተኛና ደካማ ነው።እነዚህን ህጻናት ባለሙያ ቀርቦ ቃለ መጠይቅ እየተደረገላቸው፣ የህክምና ክትትል እየተደረገላቸው በትክክል በማስረጃ መያዝና ይህንንም ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ማቅረብ ተገቢ ነው።
አሁን አፋር ውስጥ ጋሊኮማ የተፈጠረ ችግር አለ።ወደ 300 የሚጠጉ ሰዎች ህይወታቸውን አጥተዋል።107 የሚሆኑት ህጻናት ናቸው። ይህንን ጉዳይ አጀንዳ ለማድረግ ምን ያህል ተሰርቷል? ብዙሃን መገናኛዎች በቦታው በመገኘት ተጎጂዎችን በማነጋገር፣ የደረሰውን ጥቃት በማሳየት፣ ከተረፉ ሰዎች መረጃ በመሰብሰብ ምን ያህል ተሰርቷል? ይሄ ብሄራዊ ሃዘን መሆን አለበት።ለጉዳዩ ትኩረት መሰጠት አለበት።በአፋር ክልል ጋሊኮማ የተፈጠረውን ክስተት መንግስት በሚገባው ደረጃ አልሰራበትም።
ይሄ በወገኖቻችን ሞት መነገድ ሳይሆን፤ ቢያንስ ሞታቸው ከንቱ እንዳይሆን ገዳያቸው ምን አይነት እንደሆነ ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ማሳየት ነው።ለቀረው ኢትዮጵያዊ ክፍል ነገሩን የወንድማማች ጦርነት እያለ ለሚያድበሰብስ ክፍል ማሳያ የሚሆን ነው። አለም አቀፉ ማህበረሰብ ትኩረት የነፈገን አንድም ከግላቸው ጥቅም አንጻር ትኩረት ለመስጠት ስላልፈለጉ፣ የዲፕሎማሲ፣ የፖለቲካ ስራውና የመገናኛ ብዙሃን ስራው በጣም የተዳከመ ስለሆነ ነው ብዬ አስባለሁ።
አዲስ ዘመን:- እንደ አንድ የሚዲያ ባለሙያ ህዝብን የማሸበር የትህነግን የሃሰት ፕሮፖጋንዳ እንዴት ትገልጸዋለህ? የኢትዮጵያ የመገናኛ ብዙሃን አጠቃቀምንስ እንዴት ትመለከተዋለህ?
ጋዜጠኛ ጴጥሮስ:- ህወሓት ይህንን ቀድሞ የተዘጋጀበት መሆኑን የምትገነዘበው በይፋ ጦርነት ከመጀመሩ አስቀድሞ የነበሩ እንቅስቃሴዎችን በመመልከት ነው።የእነ ዶክተር ደብረጺዩን ቡድን በህገ መንግስቱ የተደነገገውን ጥሰው ደብዳቤዎችን ይጽፍ ነበር።ለአፍሪካ ሕብረት ደብዳቤ ጽፏል፣ ለአውሮፓ ሕብረት፣ ለተባበሩት መንግስታት ድርጅትና ለተለያዩ አለም አቀፍ ድርጅቶች ደብዳቤ ሲጽፍ ነበር።የኢትዮጵያ መንግስት እያለ በግል ደብዳቤ የሚጽፉበት ምክንያት ግልጽ አልነበረም።ሕወሓት በዲፕሎማሲውም፣ በፕሮፖጋንዳው በተግባርም ጦርነት በማድረግ አስቀድሞ እነዚህን ስራዎች ሲሰራ ነበር።የኢትዮጵያ መንግስት በአንጻሩ በሚገባ ደረጃ ምላሽ እየሰጠ አልነበረም።
ወደ ሃሰት ፕሮፖጋንዳ ስንመለስም መንግስት ምንም ቢሰራም እነርሱ የሀሰት ፕሮፖጋንዳ ከመስራት አይመለሱም ነበር። ምክንያቱ በጦርነቱም መሸነፋቸውን ሲያዩ የመጀመሪያው ፉከራ ወደ ለቅሶ ሲቀየር እጃቸው ላይ የነበረው የዲፕሎማሲና የፕሮፖጋንዳ ጦርነት ነው። የኢትዮጵያን የውጭ ግንኙነት ለ30 ዓመታት ተቆጣጥረውት ነው የቆዩት፣ ዲፕሎማሲውን በደንብ ያውቁታል፣ በስልጣን በነበሩበት ጊዜ የፈጠሩት የጥቅም ግንኑነት አለ። ስለዚህ ከአለም አቀፍ ተቋማትና አገራት ጋር የመገናኘት ዕድሉ በእጃቸው ነበር።
ለሐሰት ፕሮፖጋንዳው ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ በጎ አድራጎት ተቋማትም አግዘዋቸዋል። በተለይ በትግራይ አካባቢ በሚንቀሳቀሱ በጎ አድራጎት ተቋማት ውስጥ ከቋንቋ ተመራጭነት አኳያም ቢሆን በክልሉ ተመራጭ ስለነበሩ ይንቀሳቀሱ የነበሩት የራሳቸው የህወሓት ሰዎች ነበሩ።ድርጅቶቹ ሲገቡ የራሳቸውን ሰዎች እንዲጠቀሙ በማድረግ እንደ ቅድመ ሁኔታ በማስቀመጥ የራሳቸውን ሰዎች አስገብተዋቸዋል። ጦርነቱ ከተጀመረ በኋላ በሶስት ሳምንታት ውስጥ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ሪፖርት ያወጣው በጥቅምትና በህዳር ወር ሪፖርት የወጣው ከ150 ሺህ እስከ 200 ሺህ ሰዎች ወደ ሱዳን ተሰደዋል የሚል ነበር። ጦርነቱ ካለቀ ከስምንት ወራት በኋላ የተሰደደው ሰው የተባለው ከ45 ሺህ እስከ 60 ሺ ሰዎች ነው።ይህንን ሪፖርት የሰሩት መረጃም ያቀበሉት እዛው ከስር ያሉ የህወሓት ሰዎች መሆናቸውን ትገነዘባለህ። ነጮቹ ከበላይ ሆነው ነው የሚሰሩት።
ይህን ያህል ሰው ተርቧል፣ ተደፍረዋል፣ተጠምቷል የሚል ሪፖርት ከጤና ጣቢያ ነው የሚሰበሰበው። ጤና ጣቢያ የሚሰሩት ሰዎች እነማን እንደሆኑ መመልከት ነው። ግን ወገኖቻችን በጦርነት ውስጥ ሰለባ አልሆኑም ማለት አይደለም። በጦርነቱ ውስጥ ሰለባ የሆኑ ሰዎች ቢኖሩንም ግን ደግሞ ይህንን ጉዳት ለፖለቲካ ትርፍ እየተጠቀሙበት ይገኛሉ። ሪፖርቱ ለውሸት ፕሮፖጋንዳው ነው የጠቀማቸው፣ ከእዛም የውሸት ዜና ይሰራሉ። የውሸት ዜናና ፕሮፖጋንዳው ከስር በሪፖርት ይደገፋል።
ስለዚህ ወደ ተባበሩት መንግስታት ድርጅት ስትሄድ በማስረጃ የተደገፈ የበርካታ ሰዎች ሰነድ እጃችን ለይ እየደረሰን ነው ይላሉ። የደረሳቸው ከታችኛው መዋቅር ነው፣ እዛ ደግሞ የሚሰሩት የህወሓት ሰዎች ናቸው። ስለዚህ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አጣራሁ ይበል እንጂ መረጃው የሚመጣው የእዛው ቋንቋ ተናጋሪ የሆኑ በህወሓት ውስጥ ስራ የነበራቸው ሰዎች ናቸው። ይህንን መለስ ብሎ ተሰደዱ የተባሉት ሰዎች ጉዳይ በማስረጃ መመልከት ይቻላል።
ተሰደዱ የተባሉት አብዛኞቹ ሰዎችም ነፍሰ ገዳይ ሆነው ሳምሪ በተባለው ቡድን ውስጥ ተደራጅተው ማይካድራ ውስጥ ንጹሃን ሰዎችን የጨፈጨፉ ናቸው። ንጹሃን ሰዎች በጦርነት ውስጥ መሰደዳቸው ግን የሚገጥም ነው።ህወሓትን ለማገዝ የሙዚቃ ኮንሰርት እየተደረገ ያለው ሱዳን ውስጥ ነው። በሱዳን ሚሊተሪ አጋዥነት ኮንሰርት እየተደረገ ነው። በሱዳን ስደተኞች ናቸው፣ የጦርነት ገፈት ቀማሽ ናቸው የተባሉት ለጦርነት እየሰለጠኑ እየተደራጁ መልሰው ኢትዮጵያን ሊወጉ ወደ አገር እየገቡ ትመለከታለህ።ስለዚህ ፕሮፖጋንዳውና ውሸቱ ከላይ ይፈበረካል፤ ከስር ደግሞ በሃሰት ሪፖርት ይደገፋል።
ነጮቹና ምዕራባውያን ከራሳቸው ጥቅም አንጻር ከህወሓት ጋር መወገናቸው እንዳለ ሆኖ፤ በኢትዮጵያ በኩል ደግሞ የደከምንባቸው በርካታ ነገሮች አሉ። መረጃ ባግባቡና በጊዜ መስጠት ላይ መንግስት ደካማ ነው። ጦርነቱ እንደተጀመረ መረጃ ቶሎ ቶሎ ይሰጥ ነበር። ግን ሊቀጥል አልቻለም።
አለም አቀፉ ማህበረሰብ ይቅርና ኢትዮጵያውያንን ለማሳመን የሚችሉ አልነበሩም። እነርሱ ቤተክርስቲያን ውስጥ ይህንን ያህል ጥቃት ተፈጸመብን፣ ይህንን ያህል ሰው ተገደለብን፣ በማለት ኢትዮጵያውያንን ሁሉ ልብ የሚከፍል መረጃ ነበር የሚያቀርቡት። በመንግስት የተደረገውን ተደርጓል፣ ያልተደረገውን አልተደረገም ብሎ መረጃን በማስረጃ አስደግፎ ማቅረብ ላይ እጅግ በጣም ደካማ ነበር። ብዙሃን መገናኛም የሚጠበቅበትን ስራ አልሰራም።
እነ ቢቢሲ አማርኛው፣ ዶቸ ቬሌና የአሜሪካ ድምጽ በዘገባቸው መንግስትን ቅርቃር ውስጥ የሚከት ስራ እንደሚሰሩ መታዘብ ይቻላል። በእነርሱ ደረጃ እንኳን ብዙሃን መገናኛ ሊሰራ አልቻለም። ብዙ ባለሙያዎች እያሉ አቅም እያለ በቦታው ጋዜጠኞችን ወስዶ መዘገብ ሲቻል የሚገባውን ያህል አልተሰራም።ስለዚህ የሃሰት ፕሮፖጋንዳ እንዲቆጣጠረው እድል አግኝቷል።በማህበራዊ ሚዲያ እንቅስቃሴ የመንግስት ባለስልጣናት እንቅስቀሴ በጣም ደካማ ነው።ትዊተር የሚጠቀሙ አነስተኛ ናቸው። የመንግስት ደጋፊዎች በፓርቲ በኩል በዚህ ዘርፍ እንቅስቃሴ የላቸውም።የመረጃ አሰጣጡ በቂ አይደለም።ኤምባሲዎች በሙሉ በዚህ ጉዳይ ላይ መስራት አለባቸው።ዲፕሎማቶች አምባሳደሮች ይህንን መስራትይጠበቅባቸዋል።
በዚህ ወቅት ማህበራዊ ሚዲያን መጠቀም ወሳኝ ጉዳይ እንጂ ሲደላ የሚደረግ አይደለም። ጦርነት እየተደረገ ያለው በተግባር መሬት ላይና በፕሮፖጋንዳ ነው።የተግባር ጦርነቱን አሸንፈን የፕሮፖጋንዳው ላይ እጅ ሰጥተናል።እርሱ ደግሞ ተጽኖ ይዞብን መጥቷል።የእነርሱ ውሸት በሪፖርት መደገፍ የእኛ ደግሞ እውነትን በማስረጃ አስደግፎ አለማቅረብ ትልቁ ድክመት ሆኖ ለእነርሱ መሳሪያ ሆኖ ጠቅሟቸዋል።
አዲስ ዘመን:- በአሸባሪነት የተፈረጁት ህወሓትና ሸኔ በቅርቡ ወታደራዊ ስምምነት የመፍጠራቸው ሁኔታ ምን አንድምታ አለው? እስከምንስ ያዘልቃቸዋል?
ጋዜጠኛ ጴጥሮስ:- ሲጀመር የተለያዩ ነበሩ ወይ ? የሚል ጥያቄ ነው የማነሳው። የዳውድ ኢብሳ ቡድንና አሁን ሸኔ የተባለው ቡድን ከህወሓት ጋር ጠላት ነበሩ ወይ? ብሎ መጠየቅ ጥሩ ነው። ኦነግ ለረጅም ዘመን ጫካ የታገለ፣ ታግሎ ያታገለ ድርጅት ነው። በረጅም ዘመኑ አንድ ቀበሌ ይዞ የኦሮሞን ገበሬ እረፍት አልሰጠውም። በእዛ ሁሉ የትግል ዓመታት ለኦሮሞ ማህበረሰብ የተረፈው ኦነግ ናችሁ በሚል እስር ቤት መታጎርና መገረፍ ነበር።
አቶ ጌታቸው ረዳ ከለውጡ በፊት ኦነግን ይሄንን ሁሉ ዓመታት ጫካ ተቀምጦ ታግሎ ማታገል ያልቻለ ይለዋል። ህዝቡን አስተባብሮ ነጻ ማውጣት ያልቻለ ድርጅት ነው እያለ ሲኮንነው ነበር። ያ ድርጅት ጭራሽ ተበታትኖና ተከፋፍሎ ዋናውን መዋቅሩን ካጣ በኃላ እንዴት አጋር ሊሆነው ቻለ? ባለፈው ቃለ ምልልሱ ድሪባ ኩምሳ ( ጃል መሮ) ‹‹በጦርነት ውስጥ ቋሚ ጠላት ቋሚ ወዳጅ የለም፤ ለእኛ እስከጠቀመን ድረስ አብረን እንሰራለን የት ድረስ ይዘልቃል የሚለው ጊዜ የሚፈታው ይሆናል›› ብሏል።
በርግጥ ቋሚ ወዳጅ ላይኖር ይችላል፤ ግን እነርሱ ቋሚ ጠላት ነበሩ ወይ? ኦነግ ከኤርትራ በረሃ ሲገባ በትግራይ በኩል ምሳ ሲጋበዝ የመጀመሪያ ጥያቄዬ ነበረ።ምክንያቱም ገና ቁስሉ አልደረቀም። ህወሓት እስር ቤት ያሰቃያቸው ሰዎች፣ የበደላቸው፣ እግራቸው የተቆረጠ ሰዎች ባግባቡ ህክምና አላገኙም፣ ሙሉ ለሙሉም ከእስር አልተፈቱም ነበር።
እንጀራ የመቁረስ ልብ ከየት አገኙ፣ እንዴት ባንድ ጊዜ ሊያምናቸው ቻለ። ቂም ይያዝ ጥላቻን ያዳብር እያልኩ ግን አይደለም። ከተማ ከገባ በኋላም የሚያደርጋቸው እንቅስቃሴዎች ሲታዩ የሸኔ ሰራዊት ከህወሓት ሰራዊት ጋር የተለየ ስሜትና ፍላጎት አልነበራቸውም። ከሚለያዩበት ይልቅ የሚመሳሰሉባቸው ነገሮች ይበልጣሉ።
አሸባሪዎቹ ህወሓትና ሸኔ ለህዝባቸው ቀንበርና መከራ ነው ይዘው የመጡት። ህወሓት ባለበት ወጣቶች ታዳጊዎች በሰላም መማር አልቻሉም። ሸኔም ባለበት ወጣቱ መስራት ወደ ልማት መምጣት አልቻሉም። ህወሓት ባለበት ሰው ሰላማዊ ኑሮ መኖር አልቻለም።ሸኔም ባለበት የሰላም ኑሮ መኖር አልቻሉም። ሁሌም የሚታያቸው የትጥቅ ትግል ነው። ፍሬ የማያፈራ ትግል ነው።ቢያንስ ህወሓት መንግስት ሆኖ ቆይቷል። ሸኔ ግን ተሳዳቢ ሆኖ ጫካ የኖረ ነው። ባሳለፍናቸው 40 ዓመታት ውስጥ አንድ ቀበሌ ይዞ የኦሮሞ አርሶ አደርና አባቶችና እናቶችን እፎይ ማስባል ያልቻለ ቡድን አሁን ባለቀ ጊዜ ከህወሓት ጋር ህብረት መፍጠሩ ታሪካዊ ስህተት ነው።የግንኙነቱ አንዱ ፍላጎታቸው ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ በሁሉም አካባቢ ውጥረት ውስጥ ነች የሚል መልእክት ማስተላለፍ ነው። በሰሜኑ ከትግራይ ጋር ብቻ የተደረገ የህግ ማስከበር ዘመቻ አይደለም።ጉዳዩ አገር አቀፍ ችግር ነው ለማለት ነው። ሸኔ ሰፊ በሆነው የኦሮሚያ ክፍል ላይ እንቀሳቀሳለሁ ብሎ ስለሚያነሳ አገሪቱ በሁሉም አቅጣጫ ውጥረት ላይ ናት ለማለት ነው። በአፋር በኩል ታጣቂ አለ፣ በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል የጉምዝ ታጣቂ አለ፣ ኦሮሚያ ላይ ሸኔ አለ፣ በአማራ ክልል የቅማንት ታጣቂን ፈጥረው ራሳቸው አደራጅተዋቸው የሚዋጉ አሉ።በትክክል ንጹህ የሆነ የፖለቲካ ጥያቄ የሚያነሱት አይደለም እያልኩ ያለሁት።
ህገ ወጥ በሆነ መንገድ ተደራጅተው የገዛ ወገናቸውን የሚወጉ አሉ። ስለዚህ አገሪቱ ለመበታተን በቋፍ ላይ ናት የሚል መልእክት ነው። በመንግስት ላይ ያለው ተቃውሞና አመጹ በህወሓት በኩል ብቻ ሳይሆን በመላው አገር የትጥቅ ትግል አለ የሚለው ትልቁ ትርፋቸው ነው።
ኢትዮጵያ ውስጥ አጋጣሚ የሚያዮ ፖለቲከኞች አሉ። የሃይል ሚዛኑ ወዳጋደለበት ሃይል ጠብቀው የሚሰለፉ አጋጣሚ የሚመለከቱ ፖለቲከኞች አሉ።ሸኔ፣ ህወሓት ብሄርተኛ ድርጅቶች ሲሆኑ አገር ወደ አንድነት ስትመጣ አይጠቀሙም። የሚጠቀሙት አገር ስትበታተን ኮንፌዴሬሽን የሚለውን ጽንሰ ሃሳብ ተግባር ላይ እናውለዋለን የሚል ቅዠት አላቸው። ለቅዠታቸው የሚጠቅማቸው ደግሞ የህወሓት መጠንከር ነው። ህወሓት አለቃ ስትሆን እኛ የሰፈር አለቃ ለመሆን ዕድል እናገኛለን ብለው ነው የሚያስቡት። አንድ ትልቅ አገር ከሚኖራቸው ይልቅ አንድ ሰፈር ተፈጥሮ የእዛ ሰፈር አለቃ ተብለው መጠራት የሚፈልጉ ፖለቲከኞች አሉ።የትጥቅና የሃሳብ ትግል በማከናወን መንግስትን ለመገፍተር ነው ቅዠታቸው።ከውጭውም እነ አሜሪካ ያግዙናል ብለው ይጠብቃሉ።ምርጫው አሳታፊና ሚዛናዊ አይደለም የሚል መግለጫ ቢያወጡላቸው እነዚህን ሃይሎች ይዘው ሃይል መካፈልና ስልጣን መካፈል የሚል ቅዠት ነው። ለእዚህም ነው ይህንን ህብረታውን የሚጠቀሙት።እንጂ ህብረታቸው የሚያዛልቅና የሚጠቅማቸው አይደለም።
አዲስ ዘመን:- አሸባሪው ህወሓት ነጥያቸዋለሁ ከእዚህም በኋላ አይተባበሩም ያላቸው ሃይሎች ኢትዮጵያን ለማጽናት ያቋቋማቸውን ሃይል ለማጥፋት በአንድነት የመንቀሳቀሳቸውን ሁኔታ እንዴት ትመለከተዋለህ ?
ጋዜጠኛ ጴጥሮስ:- እርሱ የኢትዮጵያውያን ድል ነው። ኢትዮጵያውያን ድል ያደረግነው ህወሓት የፈጠረልንን አጥር አፍርሰን ስንወጣ ነው። ህወሓት ተልቁ ስኬቴ ብሎ የሚያስበው ኢትዮጵያውያንን ከኢትዮጵያ ከፍታ አውርዶ መንደርና ጎጥ ውስጥ ሲከትታቸው ነበር።የምናከብራቸውን ትላልቅ ሰዎች ጭምር መንደርና ጎጥ ውስጥ ከትቷቸው ከመንደራቸው በላይ እንዳያስቡ አድርጓቸው ቆይቷል።
አሸባሪ ቡድኑ ኢትዮጵያውያንን ከኢትዮጵያ ከፍታ አውርዶ፣ መንደርና ጎጥ ውስጥ ከትቷቸው፣ ከመንደራቸው በላይ እንዳያስቡ አድርጓቸው ቆይቷል፣ በስልጣን ዘመኑ ከፋፍያቸዋለሁ፣ አንድ እንዳይሆኑ ነጥያቸዋለሁ በሚል ያቋቋማቸው ሃይሎች መልሰው በአንድነት አገር ለማጽናት መንቀሳቀሳቸው ታሪክ ይመዘግበዋል።
ኢትዮጵያውያን ድል ያደረግነው አሸባሪው ሕወሓት የፈጠረውን አጥር አፍርሰን መውጣታችን ነው።ኢትዮጵያውያንን ከኢትዮጵያ ከፍታ አውርዷል፣ የምናከብራቸውን ትላልቅ ሰዎች ጭምር መንደርና ጎጥ ውስጥ ከትቷቸው ከመንደራቸው በላይ እንዳያስቡ አድርጓቸው ነበር።
አሁን የኢትዮጵያውያን ትልቁ ስኬትና ድል ደግሞ ያንን የመንደርና የጎጥ አጥር አፍርሰው በጋራ መቆም መቻላቸው ነው። በመተባበርና በአንድነት ትህነግ የገነባውን የመነጣጠል ግንብ ማፍረስ መቻላቸው ትልቅ ድል ነው። አማራን ነጥለነዋል፣ ሌሎቹ ስለማያግዙት እናጠቃዋለን ብለው ሰርተዋል፤ ነገር ግን የአሸባሪው ህወሓት ሴራ ፈርሶ ኢትዮጵያውን በተባበረ ክንድ አብረው መቆም ችለዋል፣ ጦርነቱ የተጀመረውም በድል ነው።
ጦርነቱ የእኔ አይደለም ከማለት ይልቅ አጥሩን በማፍረስ አማራም አፋርም ሲነካ ቤቴ ነው የተነካው፣ አገሬ ናት የተደፈረችው በማለት በጋራ መተባበር መቻላችን የኢትዮጵያውያን ትልቁ ስኬታችን ነው። አሸባሪ ቡድኑ በመጀመሪያ የሰራው አማራን እንደ ገዢ መደብ ተቆጥሮ በጠላትነት የመፈረጅ ስራ፣ በመቀጠል ደግሞ የሁሉም የጋራ ጠላት የማድረግ ስራ ነበር።
አማራ እንደ ቅኝ ገዢ፣ በዝባዥ መደብ ተደርጎ እንዲቆጠር ነው የተደረገው፣ ነገር ግን በሁሉም ማህበረሰብ ገዢ መደብ፣ ጭሰኛ ባላባት አለ።በእራሱ ውስጥ የነበረውን ገዢ መደብ ጨቋኝ እንደነበረ ይረሳውና የአማራው ጠላት ብቻ ይሆናል። አሸባሪው ህወሓት ይህንን ስልት መጀመሪያ የፈጠረው የትግሉን አቅጣጫ ወደ ሌላ በማዞር ሕዝብ እርስ በእርስ እንዳይስማማ ለማድረግ የተከተለውና ስልጣኑን ለማጽናት የተጠቀመበት ስሌት ነው። ስለዚህ ሁሉም ብሄር ብሄረሰቦች ጠላታችን ብለው የሚሉት ነፍጠኛ ብለው አማራን ነው።
ትክክለኛው የአገር ጠላት የሆነው አሸባሪው ህወሓት በተጠቀመው ስሌት አገሪቱን በፈለገው መንገድ ሲዘውራት ቆይቷል። በስልጣን ዘመኑ ሰው እየገደለ፣ እያሰረ፣ በኢኮኖሚ ህብረተሰቡን እያደቀቀ፣ በተለያዩ ፖሊሲዎች ከጥቅም እያገለለ የነበረ ቡድን ነው።እርሱን እንዲታገለው የምናብ ጦርነት በመፍጠር ከ100 ዓመታት በፊት ከሞተ ምኒሊክ ጋር እንዲታገሉ፣ ትግላቸውን በተለያየ ቦታ የእለት ጉርሱን ለመሙላት ከሚንከራተት የአማራ አርሶ አደር ጋር እንዲጋጩ በማድረግ ስልጣን የማራዘም ስልት ተግባራዊ አድርጎ ቆይቷል።
ሌላው የህወሓት ትልቁ ስኬቴ የሚለው ኢትዮጵ ያውያንን መበታተን ነው። ከተሳካልኝ ኢትዮጵያን እመራለሁ፤ ካልተሳካልኝ ትግራይን ይዤ እቀጥላለሁ ነው። ትግራይን ይዞ ሲቀጥል አዋሳኝ ክልሎች አሉ። አማራ፣ ደቡብ ምዕራብ፣ አፋርና ኤርትራ አሉ።
ኤርትራ ላይ ፕሬዚደንት ኢሳያስ አፈወርቂን ካስወገድን ከእኛ ጋር የሚተባበር ቡድን አናጣም የሚል ተስፋ አላቸው። አልተሳካላቸውም እንጂ ፕሬዚደንት ኢሳያስን ለማስገደል በተደጋጋሚ ሙከራ አድርገዋል። ከአማራ ጋር የወልቃይት ጉዳይ አለ። መቼም የማይቀር ነው። ከአፋርም የወሰዱት መሬት አለ፤ የአፋር ሕዝብ የህልውና ጥያቄ አለ። ተበታትኖ ተንከራትቶ እንዲኖርም ምክንያት ናቸው።በአፋር ስም ኢኮኖሚውንና ፖለቲካውን ተቆጣጥረው የኖሩ ራሳቸው ናቸው።
አማራን ስታጠቃው ኦሮሞ እንዳያግዘው ቀድመህ አጣልተከዋል፣ አፋርን ስታጠቃው ሱማሌ ክልል እንዳያግዘው አጣልተዋል፣ አለያይተዋል። አማራው ጦርነት ውስጥ ቢገባ ይሄ የነፍጠኛ ጦርነት ነው ብሎ ኦሮሞ፣ ሲዳማው፣ ወላይታው ይቀመጣል የሚል ስሜት ነበር የነበራቸው። ሁሉንም ብቻቸውን እናጠቃለን ካልተባበረብን የሚል ትእቢት አለባቸው።
አማራ ሲነካ ሱማሌው፣ ኦሮሞው፣ ሲዳማው ሌሎቹም ወታደር ላኩ። ነጥለን እናጠቃለን የተባሉት ኢትዮጵያውያኖች አብረው ቆሙ። ጦርነቱ የስነ ልቦና፣ የመዋቅርና የሲስተም ጦርነት ስለሆነ መዋቅርና ሲስተም ውስጥ ያለውን በመተባበር አፈረስነው። የመጀመሪያው የኢትዮጵያውያን ስኬት በጎጥ መቀመጥ ትተው አጥሩን በማፍረስ አማራው ሲነኩ፣ አፋሩ ሲነካ የእኔም ነገር ነው የተነካው፣ ቤቴ ነው የፈረሰው፣ አገሬ ናት የተደፈረችው በማለት መተባበር መቻሉ የኢትዮጵያውያን ስኬት ነው።
አዲስ ዘመን:- የህወሓት አሁናዊ እንቅስቃሴው በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ከግድቡ ጋር የሚያገናኘው ነገር ይኖር ይሆን ?
ጋዜጠኛ ጴጥሮስ:- እዚህ ሃሳብ ውስጥ ብዙ አሻሚ ነጥቦች ይነሳሉ። ግድቡ ከተሰራበት ስፍራ ጀምሮ መመልከት ይገባል። ለሱዳን ድንበር ቅርብ ቦታ ላይ ነው። ግድቡን በጣም አሻሚ ቦታ ላይ ነው ያስቀመጡት። በቅርቡ ከኢትዮጵያ ውስጥ ጥያቄ እንዲነሳ ተደርጎ ነበር። ከትህነግና ከእርሱ የፖለቲካ አዲማቂዎች የተነሳ ጥያቄ አለ። ቦታው የሱዳን ነው የሚል። ሱዳኖችም አልገፉበትም እንጂ በማህበረሰብ አንቂዎቻቸው አማካኝነት ያንን ተከትለው የቦታ ይገባኛል አይነት ነገር ሲያስነግሩ ነበር። የድንበር ይገባኛል ጥያቄ ቢነሳ የጦርነት ቀጠና ሊሆን የሚችል ቦታ ነው።
በቤኒሻንጉል ክልል በተደጋጋሚ ለሰዎች እልቂት ምክንያት የሚሆነው ሌላ ምክንያት አይደለም።አንድም ከእዚህ የተፈጥሮ ሃብት ጋር የተያያዘ ነው። ከእዚህ በፊት በብዙሃን መገናኛ ተለቅቆ በይፋ ይቅርታ ያሉበት የወጣ ካርታ አለ። አማራ ክልል ከሱዳን እንዳይዋሰን አድርጎ ትግራይ፣ ወልቃይትን፣ ሑመራን ይዞ ከቤንሻንጉል ጉሙዝ ጋር የሚዋሰን እስከ ጋምቤላ ክልል የሚወርድ ካርታ ሰርተው ነበር። ያ ካርታ በስህተት ነው ብለው በሚዲያ ይቅርታ ጠይቀው ነበር። ግን በትክክል ስህተት ነው ወይ? አንድ ህጻን ልጅ ሲጫወት የሳለው ስእል አይደለም። ባለሙያ ቁጭ ብሎ አጥንቶ የሰራው ነው። ይሄ ስህተት ነበር ወይስ በሃሳብ ደረጃ እነርሱ ልብ ውስጥ ነበር?
በዋናነት የጉምዝ ታጣቂ የሚባል አለ።ቤኒሻንጉል ጉሙዝ የሚያምጽና ከኢትዮጵያ የመገንጠል ጥያቄ የሚያነሳ ከሆነ ሱዳን ልትረዳው ትችላች። እነርሱ አጋር ይሆናሉ፣ በጋራ ህብረት ፈጥረው የግድቡ ተጠቃሚ ይሆናሉ ወይም በግድቡ ላይ ተደራዳሪ እና ተፈላጊ ይሆናሉ የሚል ተጨባጭ ለማድረግ የሚከብድ የሩቅ ስሌት አለ።
አማራን ፈጽሞ ካላጠፋህ ይሄ ስሌት እውን ሊሆን አይችልም። ስለዚህ ይህ ስሌት እንደማያስኬድ ሲያውቁ ሌላኛው ስሌት የጉምዝ ታጣቂን በማደራጀት ሱዳን እንድትደግፈው ማድረግ ነው። የጉምዘ ታጣቂ ደግሞ መጨረሻ ላይ ነጻ አውጪ ወደ መሆን ይመጣና የመገንጠል ጥያቄ ያነሳል። ምክንያቱም ህገ መንግስት ውስጥ የተቀመጠ የህግ አግባብ ስላለ ቤኒሻንጉል አገር እሆናለሁ ብሎ የሚያስብ ከሆነ አገር የሚሆነው የህዳሴውን ግድብ ይዞ ነው።ያ ማለት አሁን ባለበት መዋቅር ውስጥ ራሱን ችሎ ለመቆም ስለማይችል ቤኒሻንጉል አገር በሆነ ማግስት የሱዳንና የህወሓት ሰለባ ይሆናል። ስለሆነም የሱዳንና የግብጽ ፍላጎት በእዚህ ውስጥ ይሳካል ተብሎ ይጠበቃል።
ህወሓት ራሱን እንደ ኢትዮጵያዊ አይቆጥርም። የሚጠላውን አገር ኢያስተዳደረ ነው።ኢትዮጵያ ላይ ካለው ጥላቻ የተነሳ ‹‹እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል›› የሚል እንቅስቃሴ ስላላቸው የሱዳንንና የግብጽን ድጋፍ ለማግኘት በህዳሴ ግድብ ላይ ጣልቃ እንገባለን የሚል ቃል ሊገባላቸው ይችላል። ተከዜ ግድብን አትንካባቸው እንጂ ለእነርሱ በህዳሴ ግድብ ላይ በመቆመሪያነት ወይም ሂሳብ ማወራረጃነት ቢያቀርቡት የማይጠሉት ነው።
በፊት ግድቡ በተያዘለት አሰራር የግድቡ የበላይ ሃላፊ የነበሩት ዶክተር ደብረጺዮን ናቸው። በእዚ ሂደት ውስጥ ግንባታው መቼም እንደማያልቅና ምን አይነት ሳንካ እንደነበረው የሚታወቅ ነው። የሲቪል ስራው ምን ያህል ተንቀራፍፎ እንደነበርና ሜካኒካል ስራው የነበረበት ድክመት በግልጽ ይታወቃል።
በእንሰራዋለን ሰበብ በማጓተት የእነርሱን ሃሳብና ፍላጎት ማስፈጸሚያ ያደርጉታል።በሌላ መንገድ ደግሞ ግድቡ ላይ ችግር አለ ተጭበርብሯል፣ ተሸጧል የሚል ፕሮፖጋንዳ ነበር። ማን እንደሸጠው ህዝቡ በትክክል አረጋግጧል። ስለዚህ ህወሓት የህዳሴ ግድብን በመጠቀም የግብጽና የሱዳንን ድጋፍ ለማግኘት እንደመያዣነት ሊጠቀምበት ይችላል።
አዲስ ዘመን:- አሸባሪው ህወሓት ከግልጽ ጦርነት ባለፈ ኢትዮ ጵያን ለማፍረስ ከሚጠቀማቸው ድርጊቶች መካከል ሰው ሰራሽ የኑሮ ውድነት፣ ግሽበት መፍጠርና የመሳሳሉት ይጠቀሳሉ፤ እነዚህን ሁኔታዎች እንዴት ትመለከተዋለህ?
ጋዜጠኛ ጴጥሮስ:- ህወሓት በአካል ጦርነት፣ የፕሮፖጋንዳና የዲፕሎማሲ ጦርነት ከፍቷል፣ ሶስተኛው የከፈተብን ደግሞ የስነ ልቦና ጦርነት ነው። ከሁሉም ከባዱ የስነ ልቦና ጦርነት ሲሆን፤ ድል አገኘ ባንልም ግን በጣም እየሰራበት ይገኛል። የስነ ልቦናው ጦርነት የህወሓት ምሁራን የፈጠሩት ወይም የገነቡት አስተሳሰብ አለ።ያም እኛ ጦረኞች ነን፣ እናሸንፋለን ምንም አይበግረንም፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የድልና የጀብደኝነት ታሪክ በሙሉ የእኛ ታሪክ ነው የሚል ፕሮፖጋንዳ ቀርጸዋል።
ሌላው ደግሞ ኢትዮጵያዊ በስነ ልቦናው ደካማ፣ እርስ በእርሱ የተበታተነና የተከፋፈለ፣ አንድነት የሌለው ነው የሚል እሳቤ ፈጥረዋል። በቀላሉ እንማርካለን፣ እንይዛለን፣ ከባዱን ጦር አሸንፈናል የሚሉ ሃሳቦችን ያነሳሉ።
በተግባር ስትመጣ ከባዱን የደርግ ጦር እነእርሱ አላሸነፉም። በደርግ የተማረረ ሕዝብ ነው እጃቸውን ይዞ መርቶ ከኤርትራ ወታደር ጋር ተባብሮ አራት ኪሎ ቤተ መንግስት ያስገባቸው። የህወሓት ትልቁ ድክመቱ የሚፈጥረውን ውሸት እራሱ ያምናል፣ እውነት መስሎትም ይቀጥለዋል። ወልዲያ ላይ፣ ቆቦና ሌሎች አካባቢዎች ላይ ያደረጉትን እንቅስቃሴ ተመልከት፤ ለምሳሌ ወልዲያ ላይ በአካል መጥተው ሲቪል የለበሱ ሰዎች በአካባቢው ሰው ተከብበናል መከላከያ ደግሞ ትዕዛዝ አልተሰጠኝም ብሎ እየተዋጋ አይደለም የሚል የስነልቦና ጦርነት ይጀምራሉ።
በዚህ የስነ ልቦና ጦርነት ሰው እንዲሸነፍና እጅ እንዲሰጥ ያደርጋሉ። በዚህ የሥነ ልቦና ጦርነት መጀመሪያ ራሳቸውን ጦረኛ አድርገው ይቀርጻሉ ቀጥለው ደግሞ ቀሪውን የኢትዮጵያ ሕዝብ ቀሽም አድርገው ይቀርጹታል። ከእዛ በኃላ ደግሞ በመንግስት ላይም ያለህን እምነት እንድታጣ ያደርጉሃል። ቀጥለውም በተመሳሳይ መንገድ ጸባችን ከደርግ ጋር እንጂ ከህዝብ ጋር አይደለም ይሉ እንደነበረው፤ ጸባችን ከአብይና ከብልጽግና ጋር ነው ይላሉ።
መንግስት አሁን በአለም አቀፍ ድርጅቶት ይሰጠው ከነበረው ገንዘብ ተይዞበታል። በርካታ ፕሮጀክቶች አሉ። የህዝብ ቁጥር እድገት የሚያመጣውን ጫና ከግምት እያስገባነው አይደለም። የኢኮኖሚ አሻጥር ለበርካታ አመታት ኢኮኖሚው በጥቂት ግለሰቦችና ኩባንያዎች የተያዘ ነበር። ጥቂት ግለሰቦች ዘይት፣ መድሃኒቱን፣ ዱቄቱን፣ ልብሱንም፣ ቆርቆሮውንም ብረቱንም አስመጪዎች ናቸው። አንድ ቡድን አንድ ኩባንያ ወደ 15 የሚጠጉ ኩባንያዎችን በስሙ ይዞ ሞኖፖላይዝድ አድርጎታል።
ነጻ ኢኮኖሚ ወይም ኢኮኖሚ መር ገበያ ይባላል፤ በውስጡ ሞኖፖላይዝድ የተደረገ ነው። በውስጡ የአንድ ቡድን፣ የአካባቢ፣ የአንድ ሰፈር ሰዎች የሚሰሩበት ሂደት ነው የነበረው። ይሄ ለኢኮኖሚ አሻጥር ክፍትና የተመቻቸ አድርጓል። አሁን ስርዓቱ ላይ ቁጥጥር ማድረግ ሲጀመር በንግድ ሰንሰለቱ ከነርሱ ውጭ የሚታዩት በጣም ጥቂቶች ናቸው።
በርግጥ ጥቂት ሚዛናዊ የሆኑ አገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን ነጋዴዎች ይኖራሉ። ግን መዋቅሩ የተዘረጋበት መንገድ የሚታወቅ ነው። ኢኮኖሚው የተዘረጋበት መንገድ አሻጥሩም አብሮ ተዘርግቷል። ኢኮኖሚው በተዘረጋበት መንገድ ነው ተንኮሉም የተዘረጋው። ስለዚህ የመጀመሪያው ስራ የአቅርቦት እጥረት እንዲፈጠር ማድረግ፣ ሁለተኛው ስራ የዋጋ ግሽበት እንዲመጣ ማድረግ ነው። የብሩ ዋጋና መጠን በጣም እየቀነሰ ነው።
ኢኮኖሚያችን ጦርነትን ለመሸከም አይችልም።ከውጭ በሚገቡት ላይ፣ ኮቪድን ተከትሎ የመጡ ተጽእዎች አሉ እዚህ ላይ ደግሞ የኢኮኖሚ አሻጥር አለ። አቅርቦት ላይ ለምሳሌ በቅርቡ የተገኘው የብረት ክምችት አንድ ማሳያ ነው። ኮንስትራክሽን ላይ እክል እንዲፈጠር በማድረግ በዘርፉ ትልቅ የኢኮኖሚ ተጽእኖ መፍጠር ነው። የምግብ ሸቀጦች ህገ ወጥ በሆነ መንገድ በማከማቸትም ሕዝቡ በኑሮ ውድነት እንዲማረር ማድረግ አለ።
ተደራዳሪ ቡድኖችን በማዳከምና መውጫ እንዲያጡ በማድረግ የሚከናወን የግጭት አወጋገድ ስርዓት አለ። ግጭት ውስጥ ሲገቡ ተደራዳሪዎች ተመጣጣኝ አቅም ላይ ካልደረሱ ሁለቱም ካልደከማቸው እኩል ለማደራደር አስቸጋሪ ይሆናል። ሃይል አለኝ ብሎ የሚያስበው ለመደራደር ፍቃደኛ አይሆንም። ስለዚህ የኢትዮጵያ መንግስት መንግስት ነኝ ስላለ ለመደራደር ፍቃደኛ አልሆነም። ህወሓት ደግሞ ተምቤን ጫካ ነው የነበረው።ለመደራደር ብቁ አልነበረም። የኢትዮጵያ መንግስት ከወጣ በኋላ ወዲያውኑ እንዲገፋ ፈቀዱለት።
የሕጻናትን ወታደር የሕዝብንም ማዕበል ተጠቅሞ ሲገፋ የውጭ ሃይሎች ዝም ያሉት ገዢ መሬት ይዞ ለመደራደር አቅም እስኪያገኝ ድረስ እየጠበቁት ነው። ልብ ብለህ ከሆነ ህወሓት መሬት ከያዘ በኋላ በጻድቃን በኩል ቃል የተገባላቸው ነገር ነበር። ከጥቂት ቀናት በኋላ የሚሌን መንገድ እንይዛለን፣ ጅቡቲ የሚገባውን ርዳታ በቀጥታ እኛ እንቀበላለን፣ ወደ አዲስ አበባ የሚዘረጋውን መንገድ እንዘጋዋለን ብሏል።
በመቀጠል አዲስ አበባ የሸቀጥና የምርት አቅርቦት ይፈጠራል፣ ሕዝቡ ችግር ላይ ሲወድቅ በመንግስት ላይ ያምጻል። መንግስት ተገድዶ ለመደራደር ይገደዳል የሚል ስሌት ነበራቸው። ግን አልተሳካም ሚሌ ላይ ከሸፈ፤ አፋር ላይ ያለው ጦርነት በድል ሲጠናቀቅና ባሰቡት ፍጥነት መሄድ ሲያቅታቸው በሶማሌና በአፋር መካከል የኖረ ግጭትን በመቀስቀስ በተላላኪ አማካኝነት የአዲስ አበባ ጂቡቲ መስመር በአመጽ እንዲዘጋ አደረጉ። ግን እሱ ምናልባትም ከአንድ ቀን የዘለቀ ጊዜ እድል አላገኘም። ይሄም ከኢኮኖሚ አሻጥሩ ጋር ይገናኛል።
መንግስት የኢኮኖሚ ችግር እየገጠመው ነው፣ መንገድ ሲዘጋበት ደግሞ ህብረተሰቡ የበለጠ ለችግር ይዳረጋል ይህንን ተከትሎም ህብረተሰቡ ለተቃውሞ ይነሳል። ችግሩን ለመቅረፍም መንግስት ለውይይት ይቀመጣል የሚል ሰሌት ነበር። ይህ ነገር እንደተፈጠረ አሜሪካ የድርድር ሃሳብ ይዛ መጣች። ለአንድ ወር ሙሉ ግን ህወሓት እየገፋ፣ ህጻናትንና ህዝቡን ለጦርነት እያሰለፈ ጥያቄ አላነሳችም ነበር። ገዢ መደብ ይዟል ብላ ስታስብ ተነሳች።ህወሓት ከወሎ አካባቢ የያዘውን መሬት ቆቦንና ሌሎች አካባቢዎችን ይልቀቅ። እናንተ ደግሞ አማራ ክልልን ራያ፣ ሁመራን ልቀቁ የሚል ጥያቄ ነው። አየህ ጠብቀው በጠረጴዛ ዙሪያ ለመደራደር እንዲችል እኩል አደረጉት።
ይህ ስሌት ግን በብዙ ምክንያት ከሸፈ። አንደኛው ህወሓት እንዳለው መስመሩን ሙሉ ለሙሉ መዝጋት አልቻለም። ርዳታውንም በራሱ መቀበል አልቻለም። አፋር ላይም ከባድ የሆነ ሽንፈት ገጠመው። ህጻናትንና ሰዎችን ጎድቶ በአፋር በኩል ያለው በእንደዚህ አይነት ሁኔታ ተጠናቀቀ።በአማራ በኩል ያለው ዋና ሃሳቡ ወደታች በቀረበ ቁጥር ወልቃይትና አካባቢው ያለው ሃይል እንዲለቅ በማድረግ በሱዳን ያለውን ኮሪደር ማስከፈት ቢሆንም እርሱም አልሆነም።የኢትዮጵያ መንግስትም ድርድሩን አልተቀበለም።
አሁን እየሰሩ ያሉት ትልቁ መሳሪያቸው በተራዘመ ጦርነት አገርንና መንግስትና ማዳከም ነው። ጦርነት ገንዘብ ያስፈልገዋል፣ በጀት ይጠይቃል፣ ሃብትና ከፍተኛ ሎጅስቲክ ይፈልጋል። በእዛ ላይ የኑሮ ውድነቱ ዋጋ እንዲጋሽብ ከባድ የሆነ የኢኮኖሚ አሻጥር ተሰራ። የውጭ ምንዛሬውን አንቆ በመያዝ፣ አማላይ የሆነ የጥቁር ገበያ በማቅረብ ሰውን ከባንክ ወደ ጥቁር ገበያ የመጎተት ስራ ተሰራ። የአቅርቦት እጥረት እንዲፈጠርም ሸቀጥ የማከማቸት ስራ እየሰሩ ናቸው። ይህንን በማድረግ መንግስት ወደ ውይይት እንዲመጣ የሚደረግበት አንዱ መንገድ ነው። ይሄ ማህበራዊ ቀውስ ይፈጥራል።
አሁን ሕዝቡ የሚፈተንበት ወሳኝ ሰዓት ነው። ሀገር ጦርነት ላይ እያለ፣ መንግስት ለመከላከያ ገንዘብ እየለመነ ባለበት ወቅት፣ ከባድ የኢኮኖሚ አሻጥርን ለመቋቋም ደፋ ቀና እያለ ባለበት ሁኔታ የመንግስት የሥራ ሃላፊዎች ባጀት ለመንግስት እንዳይመለስ በሚል በሚሊዩን የሚቆጠር ገንዘብ አዳማ፣ ቢሾፍቱና ሐዋሳ እየተጓዙ በስልጠና ሰበብ እያባከኑ ናቸው። ጦርነት ላይ ላለች አገር ይሄ የማይመጥን አሰራር በመሆኑ ሊፈተሸ ይገባዋል።
አዲስ ዘመን:- ለነበረን ቆይታ በዝግጅት ክፍሉ ስም ከልብ አመሰግናለሁ!
ጋዜጠኛ ጴጥሮስ:- እኔም ለተሰጠኝ እድል አመሰግናለሁ።
ዘላለም ግዛው
አዲስ ዘመን ነሐሴ 29/2013