ወጣትነት ለውጥ ናፋቂነት ነው፡፡ የአንድ አገር ቀጣይነት ያለው እድገት የሚለካው ባላት ሃብትና ንብረት ብቻ ሳይሆን ያንን ተረክቦ በአደራ ለትውልድ ማስተላለፍ የሚችል ትውልዳዊ ትስስር ሲኖር ነው። ይህንንም እንደ ድልድይ ሆኖ ከአንዱ ትውልድ ወደ ቀጣዩ ትውልድ የሚያስተላልፈው ወጣቱ የህብረተሰብ ክፍል ነው። በማንኛውም አገር፣ ጊዜና ዘመን እያንዳንዱ ተተኪ ትውልድ የአገሩ ወራሽ፣ ተተኪና ተረካቢ፣ ጠባቂና ለሚቀጥለውም ትውልድ የማውረስ፣ የማስተላልፍና የማስረከብ ኃላፊነትና ግደታ አለበት። አገርን ከእነ ሙሉ ክብሯ ለሚቀጥለው ትውልድ ማስተላለፍ ከወጣቱ የዜግነት ግደታዎች ውስጥ አንዱ ነው። አገር በአንድና በሁለት ትውልድ ብቻ የሚቆምና የሚያልፍ ሳይሆን የማያቋርጥ ቀጣይነት ያለው ትውልድ ሁሉ የሚቀባበለው፣ የሚጠብቀው ያለፈውንና የሚመጣውን ትውልድ ሁሉ የያዘና ያቀፈ የአገርና የሕዝብ የታሪክ ሂደት ነው። ወጣት ለአንድ አገር በሦስቱም ዘርፍ ማለትም በማህበራዊ፣ በሥነ ምጣኔ ሃብታዊና በፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ያደርጋል። ለዚህም ነው ወጣት ለአንድ አገር የጀርባ አጥንት ነው የሚባለው።
በአገሪቱ በአሁኑ ወቅት ወጣቱ ትውልድ በአንድ ሆኖ ሰላሟን የሚያስጠብቅላት ጊዜ ላይ ትገኛለች። የሽብርተኛው የህወሓት ቡድን በከፈተው አገርን የማፍረስ ዘመቻ ለመመከት በሁሉም ክልሎች የሚገኙ ወጣቶች ወደ ግንባር እያቀኑ ይገኛሉ፡፡ የሽብርተኛ ቡድኑን ስራ ለማቆምና አገርን ወደ ነበረችበት ሰላም ለመመለስ ቆርጠው የተነሱ ወጣቶቸ በወታደራዊ ማሰልጠኛዎች ውስጥ በንቃት እየሰለጠኑ ናቸው። መንግስትም የዘማች ቤተሰቦችን ለመንከባከብና ለመጠበቅ የበኩሉን ድርሻ እየተወጣ ይገኛል፡፡
የአዲስ አበባ ወጣቶች ማህበርም ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመቀናጀት ወጣቱ ለአገር ህልውና ዘመቻ እንዲሳተፍ ከመቀስቀስ ጀምሮ ለዘማች ቤተሰቦች የሚገባቸውን እንክብካቤ እያደረገ ይገኛል፡፡ ማህበሩ ለዘማች ቤተሰቦች ቤታቸውን ከማደስ ጀምሮ ልጆቻቸውን ለማስተማር ቅድመ ዝግጅት እያደረገ ይገኛል፡፡ የአዲስ አበባ ወጣቶች ማህበር ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዚዳንት ወጣት ተከስተ አያሌው ጋር ለዘማቸ ቤተሰቦቸ እየተደረገ ስላለው ድጋፍና ስለህልውናው ዘመቻ አጠቃላይ ሁኔታ ከዝግጅት ክፍሉ ጋር ቆይታ አድርጓል፡፡ መልካም ንባብ፡፡
አዲስ ዘመን፡- በህልውና ዘመቻው የአዲስ አበባ ወጣቶች ማህበር በምን ስራዎች ላይ ተሳትፎ እያደረገ ይገኛል?
ወጣት ተከስተ፡- በህልውናው ዘመቻ ላይ የአዲስ አበባ ወጣቶች ማህበር እያከናወነው ያለው ተግባር ብዙ ነው፡፡ የመንግስትን ጥሪ በመቀበል ወጣቱ ተሳትፎ ማድረግ እንዳለበት ከተጠየቀበት ወቅት አንስቶ ወጣቱ ለህልውናው ዘመቻ ወደ ተለያዩ ቦታዎች እየተንቀሳቀሰ ነው፡፡ ወጣቱ በራሱ ተነሻሸነት ለአገሩ ዘብ ለመቆም እንዲዘምቱ የመለየት ስራ ተከናውኗል፡፡ በተጨማሪም መሰረታዊ የሆኑ ስልጠናዎችን እንዲያገኙ ለማድረግ ከመንግስት ስራዎች እየተከናወኑ ነው፡፡
ሌላው ማህበሩ ያከናወነው ለመከላከያ ሰራዊቱ የሚደረጉ ድጋፎች ላይ ተሳትፎ እያደረገ ይገኛል። ለመከላከያ ሰራዊቱ በገንዘብ፣ በአይነትና በሌሎች ነገሮች ቦታው ድረስ በመሄድ ድጋፍ ተደርጓል። ድጋፉ ከወጣቶችና ከባለሀብቱ የተሰበሰበ ሲሆን ሰራዊቱን ለማበረታታት ግንባር ድረስ ጉዞ ተደርጓል። በመቀጠልም ለመከላከያ የደም ልገሳ ተከናውኗል። በዚህም በየወረዳው በርካታ ወጣቶች በየቦታው የደም መለገስ ፕሮግራም አድርገዋል። ህብረተሰቡንም በማስተባበር እየተሰራ ይገኛል፡፡ በኪነጥበብም ደግሞ ጀማሪ የኪነጥበብ ባለሙያዎች በማስተባበር ከአዲስ አበባ ባህልና ቱሪዝም ጋር በመተባበር ሰራዊቱን የመደገፍ ስራዎች አጠቃላይ ነገር ላይ ማህበሩ ትልቁን የሆነ አስተዋፅኦ እየተወጣ ይገኛል፡፡
አሁን እየተደረገ ባለው ዘመቻ ከሁለቱም ወገን እያለቀ ያለው አምራቹ ወጣቱ ክፍል ነው፡፡ በእንደዚህ አይነት ሁኔታ እንዲቀጥል አንፈልግም። የአገሪቱ የጀርባ አጥንት የሚባለው ወጣቱ አምራች ትውልድ ነው፡፡ በተመሳሳይ ዘር ተክቶ የሚያልፈውም ወጣቱ ነው፡፡ ከጦርነት የሚገኝ ምንም ነገር የሌለውና የሰውን ሂወት የሚቀጥፍ እንደመሆኑ ሁኔታውን በአፋጣኝ ለመፍታትና ሰላም ለማውረድ ያስፈልጋል። በጦርነት ውስጥ የአገር ኢኮኖሚ ማሳደግ ስለማይቻል ሰላም መምጣት አለበት፡፡ የውጭ ኢንቨስትመንት ለማግኘት የግድ አገሪቱ መረጋጋት አለባት፡፡ አገሪቱ መረጋጋት ካልቻለች የስራ አጥ ቁጥር እየተበራከተ ስለሚመጣ አደገኛ ነገር ሊፈጠር ይችላል፡፡
ጦርነት ውስጥ ተሁኖ አገርን ማሳደግ አስቸጋሪ ስለሚሆን ጉዳዩ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ተቋጭቶ የሰላም አየር መተንፈስ ይገባል፡፡ በተለይ የተጀመሩ ትላልቅ ፕሮጀክቶች የህዳሴ ግድቡን ጨምሮ እንዲጠናቀቅ ጦርነት መቆም አለበት፡፡ በአገሪቱ ሌሎች የልማት ስራዎች እንዲሰሩ ወጣቱ ፍላጎት ስላለው ከጦርነትና መሰል አገር አፍራሽ ተግባራት ወጣቱ እንዲጠበቅ መደረግ አለበት፡፡ በአዲስ አበባ ወጣቶች ማህበር መንግስት የጀመረውን የህግ ማስከበር ዘመቻ ከመጀመሪያው ጀምሮ በመደገፍ ወጣቱ ተሳታፊ እንዲሆን እያደረገ ይገኛል፡፡ ጦርነቱ በፍጥነት መቋጫ አግኝቶ ሁሉም ወደ ስራው መመለስ አለበት፡፡
አዲስ ዘመን፡- በህልውናው ዘመቻ ላይ የተሳተፉ ወጣት ዘማች ቤተሰቦች ምን አይነት ድጋፍ እየተደረገላቸው ይገኛል?
ወጣት ተከስተ፡- አሁን በመጀመሪያው ዙር ላይ አራት ሺህ 200 የሚሆኑ ወጣቶች ወደ ግንባር ዘምተዋል፡፡ ወጣቶቹ የአገርን ህልውና ለማስከበር ሲሄዱ የራሳቸውን ሂወትና የቤተሰባቸውንም ሁኔታ ወደ ጎን ትተው ስለሄዱ ማህበሩ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርና ከአአዲስ አበባ ወጣቶችና በጎ ፈቃድ አገልግሎት ቢሮ ጋር በመሆን አቅም የሌላቸውን የዘማች ቤተሰቦች ለመደገፍ እንቅስቃሴ ተጀምሯል። በዚህ መሰረት በአራት አይነት መንገድ ድጋፍ ለማድረግ ሀሳብ እንዲቀመጥ ተደረገ፡፡
የመጀመሪያው የዘማች ቤተሰቦች አቅመ ደካማዎች ከሆኑ የሚኖሩበትን ቤት የማደስና የቤት እቃዎችን እንዲሟሉላቸው ማድረግ ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ በአግባቡ ወጣቶችንና ባለሀብቱን የማስተባበር ስራ እየተሰራ ነው፡፡ ሁለተኛው ደግሞ የገንዘብ እጥረት ያለባቸውን የዘማች ቤተሰቦችን በመለየት የገንዘብ ድጋፍ ማድረግ ነው፡፡ ምክንያቱም ወጣቶቹ ቤተሰባቸውን በተለያዩ መንገዶች ሲረዱ የቆዩ በመሆናቸው ወደ ዘመቻ ሲሄዱ ቤተሰባቸው ለችግር እንዳይጋለጥ ድጋፍ ይደረጋል፡፡ ሶስተኛው ደግሞ ግብዓት የማሟላት ማለትም ለምግብነት የሚያስፈልጉ ነገሮችን ገዝቶ በመስጠት ነው፡፡ ለዘማች ቤተሰቦች ፓስታ፣ መኮረኒ፣ ዱቄትና የተለያዩ የምግብ ፍጆታዎች ድጋፍ እየተደረጉ ናቸው፡፡ አራተኛው ደግሞ እንክብካቤና ድጋፍ የሚፈልጉትን የዘማች ቤተሰቦች ያካተተ ነው፡፡ በልጆቻው ድጋፍ ውስጥ የነበሩ አረጋውያንን የመደገፍና የመንከባከቡ ስራ ማህበሩ እያከናወነ ነው፡፡
ይህ ስራ ማህበሩ በየዓመቱ በበጎ ፈቃደኛ ወጣቶች አማካኝነት ሲያከናውነው የነበረ ሲሆን በክረምት ወራት በተጠናከረ መልኩ ሲሰራ የቆየ ነው፡፡ ቤት የማደስና ማዕድ የማጋራት ስራው ቀደም ብሎም ተግባር ላይ ውሎ ነበር፡፡ ለዘማች ቤተሰቦች የአዲስ አበባ ወጣቶች ማህበር ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጋር በመሆን የዘማች ልጆችን ወደ ትምህርት ገበታ የሚሄዱበትን ሁኔታ ለመፍጠር ታስቧል፡፡ ቅድሚያ ዘማቾቹ ምን ያክል ልጆች አሏቸው የሚለውን በመለየት ወደ ትምህርት ገበታ እንዲገቡ ይደረጋል፡፡
በአሁኑ ወቅት ከአራት ሺህ 200 ዘማች ቤተሰቦች ውስጥ በዋነኝነት ድጋፍ የሚፈልጉት የትኞቹ ናቸው የሚለው ተለይቷል፡፡ ከዚህም ወስጥ ሁለት ሺህ 350 ዘማች ቤተሰቦችን ማህበሩ ድጋፍ እንዲያገኙ አድርጓል፡፡ ይህ ድጋፍ የሚቆም አይደለም፡፡ በቀጣይ እስከመጨረሻው ድረስ የሚቀጥልበት ሁኔታ አለ፡፡ የማህበሩ አመራሮችም ወደ ግንባር የዘመቱ በመሆናቸው ደመወዛቸውንና ጥቅማጥቅማቸውን ሳይቆራረጥ ለቤተሰቦቻቸው እንዲደርስ እየተደረገ ነው፡፡ ከተለያዩ የስራ ገበታ ላይ ተነስተው ወደ ህልውናው ዘመቻ የሄዱ የመንግስትና የግል ሰራተኛ ቤተሰቦችን ከህብረተሰቡ ጋር በመተባበር ድጋፍ የሚያገኙበት ሁኔታ እየተፈጠረ ነው፡፡ በቀጣይ እየታየ ድጋፍ የሚያስፈልጋቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ምንድነው የሚፈልጉት የሚለውን ከተለየ በኋላ ድጋፎቹ ይቀጥላሉ፡፡
አዲስ ዘመን፡- ወጣቱ አካባቢውንና ከተማውን ነቅቶ እንዲጠብቅ በማህበሩ በኩል ምን ምን ስራዎች እየተከናወኑ ናቸው?
ወጣት ተከስተ፡- እንደሚታወቀው በአዲስ አበባ ከተማ የሚኖሩ ወጣቶች በፈቃዳቸው ወደ ግንባር የዘመቱ እንዳሉ ሁሉ አካባቢያቸውንና ከተማቸውን በመጠበቅ ላይ የተሰማሩ ወጣቶች አሉ። በሁሉም ወረዳዎች ላይ ከሁሉም ወጣቶች ጋር ሰፊ ውይይት ተደርጓል፡፡ ከአዲስ አበባ ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ጋር በመተባበር እንዲሁም ከአዲስ አበባ ፖሊሲ ኮሚሸን ጋር ለወጣቶች ስልጠና ተሰጠቷል፡፡ የትኛውም የህብረተሰብ ክፍል አካባቢውን በንቃት የመጠበቅ ኃላፊነት አለበት፡፡ የትኛውም አካባቢ የፀጥታ መደፍረሶች እንዳይኖሩና ለሰላም ስጋት የሆኑ እንዲሁም አጠራጣሪ የሆኑ ነገሮቸ ሲታዩ መጠቆም ያስፈልጋል፡፡ በተለይ ከትራንስፖርት ጋር የተያያዙ እንዲሁም ከሆቴሎች ጋር በተገናኘ ጥንቃቄ ዙሪያ ውይይት ተደርጓል፡፡
አሁን ያለውን ወቅት በጋራ ለማለፍ የግል ጥቅም ለማግኘት የሚደረጉ ሴራዎች ሊኖሩ ስለሚችሉ ይህን ለመታገል ስለሚያስፈልግ ወጣቱ እየተደራጀ አካባቢውን እየጠበቀ ይገኛል፡፡ የትኛውም ሰው ባለበት ሙያ አካባቢውን እንዲጠብቅ ይደረጋል። ከአዲስ አበባ ፖሊስ ጋር በመተባበር ማታ ማታ በየአካባቢው በመዘዋወር ጥበቃ ይደረጋል፡፡ የማህበሩ አባል ወጣቶች በየአካባቢው ተዘዋውረው ህብረተሰቡ በየበሩ መብራት እንዲያበራ ቅስቀሳ ያደርጋሉ፡፡ ለበጎ ፈቃደኛ ወጣቶች መለያ ልብስ በማሰራት፣ ባጅ በመስጠትና ሌሎች ነገሮችን በማሟላት ከማህበረሰቡ ጋር ውይይት እያደረጉ ሰላምና መረጋጋት እየፈጠሩ ይገኛሉ፡፡ በተጨማሪም ከዋጋ ንረት ጋር በተያያዘ ወጣቱ ከሚመለከተው ክፍል ጋር ትብብር እያደረገ ይገኛል፡፡
አዲስ ዘመን፡- ለሰጠኸን ማብራሪያ እናመሰግናለን፡፡
ወጣት ተከስተ፡- እኔም አመሰግናለሁ፡፡
መርድ ክፍሉ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 28/2013