ህወሓት ወደ ስልጣን ከመጣ በኋላ እታገልልሃለሁ ያለውን ህዝብ በመርሳት ወደዘረፋና የራሱን ቡድኖች ወደማደራጀት ነው የገባው፡፡ ከዛን ጊዜ ጀምሮም የህዝቡን ዴሞክራሲያዊ መብት መጠበቅ ጉዳዩም አልነበረም፡፡ ይህ መጥፎ ሀሳቡ ደግሞ ለ27 ዓመታት አብሮት ኖሮ ዛሬም በስሙ በሚነግደው የትግራይ ህዝብ እንዲሁም መላ አገሪቱ በእኩይ ተግባሩ እያመሰና እያተራመሰ፤ አገርንም ለማፍረስ ከጀሌዎቹ ጋር ከፍተኛ የሆነ ስራ እየሰራሰ ነው፡፡
ቡድኑ በሃገር መከላከያ ሰራዊት የሰሜን እዝ ላይ ትንኮሳ ከፈፀመበት ጊዜ ጀምሮም በመከላከያ ሃይልና በክልል ሚሊሺያ አባላት ተገቢውን ቅጣት እያገኘ ይገኛል፡፡ ያም ሆኖ ግን መንግስት ለትግራይ ህዝብ የሰጠውን የእፎይታ ጊዜ በመጠቀም በአዲስ መልክ በመስፋፋት በአማራና በአፋር ክልል ንፁሃን ዜጎችና ንብረት ላይ ከፍተኛ ጉዳት እያደረሰ ይገኛል፡፡
በተለይ ሰሞኑን በአማራ ክልል በርካታ ንፁሃን ዜጎችን በግፍ በመጨፍጨፍ “ከአማራ ህዝብ ጋር ሂሳብ እናወራርዳለን” የሚለውን ቃሉን በተግባር እየገለፀ ይገኛል፡፡ ከዚህም አልፎ የአሜሪካ ተራድኦ ድርጅት መጋዘኖችን በመዝረፍ፣ የግለሰቦችን ንብረት በመዝረፍና ከዚያ ያለፉትንም በማጥፋት ከፍተኛ ጉዳት አድርሷል፡፡ ከነዚህም መካከል በእንስሳትና በሰብል ላይ የፈፀመው የጥፋት ስራ ቡድኑ ምን ያህል ለጥፋት እንደቆመ ማሳያ ነው፡፡
እኛም ቡድኑ እያደረሰ ያለውን ጥፋት መነሻ በማድረግ የቡድኑን የቆየ ባህርይና አጠቃላይ የሃገራችንን ወቅታዊ ሁኔታን በተመለከተ እንዲገልፁልን ከትግራይ ዴሞክራቲክ ፓርቲ የፖለቲካ ጉዳዮች ዘርፍ ምክትል ኃላፊ ከአቶ ተስፋዬ አለማየሁ ጋር ቆይታን አድርገናል፡፡ መልካም ቆይታ፡፡
አዲስ ዘመን ፦ ጁንታው ቡድን አገርን ለማፍረስ እየሄደበት ያለውን ርቀት እንዴት ያዩታል?
አቶ ተስፋዬ ፦ አሁን የጁንታው ተግባር ከአንድ ሽፍታ ከሃዲ የአጥፊዎች ተላላኪ ቡድን የሚጠበቅ ተግባር ነው፡፡ ቡድኑ ከምስረታው ጀምሮ አሁን እስካለበት ጊዜ ድረስ እየሰራ የመጣውን ብናይ ወይም ብናስታውስ አሁን አገሪቱና ህዝቦቿ ላይ በገሀድ ጦርነት አወጀ እንጂ ስራው ከጦርነት ትውልድን ከማምከን የአገርን ታሪክ ከማበላሸት ውጪ አልነበረም፡፡ ይህ ደግሞ የከሃዲነቱ ጥግና ማሳያው ነው፡፡
ህወሓት ከምስረታው ጀምሮ ለህዝቦች አንድነትና ትብብር ያልሰራ በጠቅላላው አገርን ሲከፋፍል እርስ በእርስ ሲያባላ የኖረ በአገሪቱ ላይም ምንም አይነት ፍትህ እኩልነት ነጻነት እንዳይሰፈን ሲሰራ የኖረ ነው፡፡ይህ ደግሞ እርሱን ሊገልጹ ከሚችሉ ባህርይዎቹ በጣም ጥቂቶቹ ናቸው፡፡
ከዚህ የተነሳም ከህወሓት ደግ ነገር መጠበቅ አይችልም፡፡ በነገራችን ላይ እነዚህ ቡድኖች በኢትዮጵያዊ ጨዋነት አለማደጋቸውን የሚያሳይ ብዙ ስራዎች ቢኖሯቸውም አገራቸው ግን የእነሱን ነውር ወደጎን እያለች አቅፋና ደግፋ ለብዙ ቁም ነገሮች ያበቃቻቸው ነበር፡፡ግን እንዲህ ላደረገችላቸው አገራቸው የሚጠቅም ተግባር ካለመፈጸማቸውም በላይ ውለታ ቢስ የእናት ጡት ነካሽነታቸውን በሚያሳይ መልኩ አገራቸው ላይ ጦር ሰበቁ፤ ጦርነት አወጁ፤ ይህ በጣም የሚያሳዝንም የሚያስተዛዝብም ነው፡፡
በመጀመሪያ ደረጃ በረሃ ሲገቡ እውነትም ለህዝብ አስበው አገርን ከጭቆና ለማላቀቅ መስሎን ነበር፤ ነገር ግን ከስማቸው እንኳን ብንነሳ ጫካ ሲሄዱም “ነጻ አውጪ” ፣ ስልጣን ላይም ወጥተው “ነጻ አውጪ ” ፣ አሁንም ተባረው ከወጡ በኋላ “ነጻ አውጪ” ነን ይላሉ፤ ነገር ግን የነጻ አውጪ ባህሪዎች ምንድን ናቸው? ብንል ህወሓት ከያዘው አቋምና ከሚሄድበት መንገድ ፍጹም የተለዩ ናቸው፡፡ እንደውም ህወሓት ለዚህች አገር ነጻነት የማያውቅ “ነጻ አውጪ” ድርጅት ነው የሆነባት ፡፡
ቡድኑ እንዳለው ነጻ አውጪ ቢሆንና ነጻነትን የሚያውቅ ቢሆን ኖሮ በአገሪቱ ያሉ ህግ አውጪ፣ ህግ ተርጓሚ እና ህግ አስፈጻሚ እንዲሁም ሌሎች ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ የሃላፊነት ቦታዎችን በፖለቲካል መንገድ ተቆጣጥሮ አገሪቱን የጥቂት ግለሰቦች ብቻ አድርጎ አይመራም ነበር፡፡ ይህ ሁኔታ ሲቀየርና ሲቋረጥ ደግሞ አኩርፎ ህዝቤ ይበለው እንጂ አንድም ቀን አስቦለት በማያውቀው የትግራይ ህዝብ ጉያ አይሸሸግም፤ በኋላም በአገር ላይ ጦር አይሰብቅም ነበር፡፡
ይህ ቡድን በእውነት አገርና ህዝብን የሚወድ ነጻም ለማውጣት የሚጥር ከሆነ ለውጥ ከመጣም በኋላ ቢሆን እስከ ዛሬ የሰራቸውን ስህተቶች እያረመ ወደፊት እንዳይደገሙ እየጣረ በተለይም የበደላቸውን የኢትዮጵያን ህዝቦች ይቅርታ እየጠየቀ መቀጠል ለምን አቃተው፡፡ ይህንን ማድረግ ያቃተው ድርጅቱ ለራሱና በዙሪያው ላሉ ብቻ የሚሰራ ተሸፍኖ ራሱ ብቻ የሚበላና አገርን የሚበዘብዝ አጭበርባሪ ቡድን ስለሆነ ነው፡፡
በመሆኑም ይህ ድርጅት ነጻነት በፍጹም አያውቅም፤ነጻ ያወጣም አገርም ሆነ ህዝብ የለም፡፡ ለእኔ ህወሓት ማለት ከሀዲ ቅጥረኛ አረመኔ ሽፍታ ነው፡፡
አዲስ ዘመን ፦ ግን እኮ ቡድኑ እስከ ዛሬም ድረስ ለብሔር ብሔረሰቦች አንድነትና እኩልነት እየታገልኩ እየሰራሁ ለውጥ እያመጣሁ ነው ይላል?
አቶ ተስፋዬ፦ እንዴ እነሱማ ይላሉ ለራሳቸው ስም በማውጣት በኩልም የሚያህላቸው የለም፤ ነገር ግን መሬት ላይ ሲታይ ያ የተቆለለው ስማቸው የለም በተግባር የተገለጸ ለህዝቡ የተሰራ ስራ አይታይም ፡፡
እነሱ የራሳቸውን ጉድ በጉያቸው ወሽቀው አሁን እንኳን የለውጡ መንግስት ወደ ስልጣን ከመጣ በኋላ አገሪቱ ላይ አሀዳዊ መንግስት ሊመሰረት ነው በማለት ክስ አይሉት ስሞታ ያቀርባሉ፤ ነገር ግን እስከ ዛሬ ድረስ አሀዳዊ መንግስትን ማነው ሲሰራበት የነበረው? እነሱ እኮ ናቸው፡፡ ምናልባት በብልጣብልጥነት ህዳር ሲመጣ ከየክልል የእራሳቸውን ሰዎች እየሰበሰቡ የብሔር ብሔረሰቦች ቀን እያሉ ይቀላምዳሉ፡፡ ያ ከሆነ እንግዲህ ለብሔር ብሔረሰቦች መብት ቆሜያለሁ ማለት እኔ ብዙ አይገባኝም፡፡ ነገር ግን ብሔር ብሔረሰቦችን እንዳትናገሩ ብሎ አፍኖ አጋር ድርጅቶች እያለ የፖለቲካ ተሳትፏቸውን እየገደበ ባልመረጡት ስለነሱ ምንም በማያውቅ ሰው ክልሎቹ እንዲተዳደሩ እያደረገና ሀብታቸውን እየመዘበረ አሀዳዊ ሆኖ የኖረው አሸባሪው ህወሓት ነው፡፡
እኔ በእድሜዬ እንዲሁም ቀደም ብለው አልፈው ነገር ግን በመጽሀፍ ካነበብኳቸው የኢትዮጵያ ታሪኮች ሁሉ እንደ ህወሓት ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያውያንን በመግደልና በመዝረፍ ክፉ ስራ የሰራ የአገር አስተዳዳሪ አላየሁም፤ አላነበብኩም፡፡
በመሆኑም እነሱ የብሔር ብሔረሰብ መብትና ነጻነት ተሟጋች ነን የሚሉት እንደው ዶሮን ሲያታልሏት በመጫኛ ጣሏት አይነት ነገር ነው፡፡ ይህ አሸባሪ ከሃዲ ቡድን እኮ ብሔር ብሔረሰብ ምን ምን እያለ ያለፉት 30 ዓመታት በአገሪቱ ሀብትና ንብረት ላይ እንዲሁም በህዝቦቿ ላይ እንዲጨፍር ያደረግነው እራሳችን ነን፡፡እኛ ጠንከር ብለን ብንታገለው ኖሮ እዚህ ባልደረሰ ነበር። ለነገሩ ይህንን መሰሪ ቡድንም ግንባር ለግንባር መታገል ቀላል እንዳልሆነ አውቃለሁ። በመታገላቸውም ብዙ ነገራቸውን ያጡም እንዳሉ የአደባባይ ምስጢር ነው፡፡ ነገር ግን በተለይ አሁን ያለንበት ሁኔታ ራሳችንን ለማስከበር አገራችንንም ከአሸባሪ ቡድን መዳፍ ፈልቅቀን ለማውጣት ምቹ ጊዜና ሁኔታ ውስጥ ነን፡፡
አዲስ ዘመን ፦ የትግራይ ህዝብ አሁን ላይ ያለበትን ሁኔታ እርስዎ እንዴት ይገልጹታል?
አቶ ተስፋዬ ፦ የትግራይ ህዝብ ባለፉት 30 ዓመታትም ቢሆን ከህወሓት ጋር ተስማምቶ ተግባብቶ ኖሯል ማለት አይቻልም፤ መናገር አይችልም፤ ከህወሓት ሌላ የሚሰማውም ሆነ የሚያየው ፖለቲካ ፓርቲ የለውም፤ በጠቅላላው እግር ተወርች ታስሮ ግን ደግሞ በስሙ ጥቂት ህወሓታውያን ሲያከብሩበት ነው የኖሩት፤ በሌላ በኩልም የትግራይ ህዝብ ምንም እንኳን ጭቆናና አፈናው እንዲሁም ረሃቡ ችግሩ ቢጠናበትም ምናልባት ከዛሬ ነገ ይሻላል ፤ ነገም ሌላ ቀን ነው በማለት በሆደ ሰፊነት ታግሷቸው ኖሯል፡፡
አሁንም ቢሆን ወጣቱ አምልጧቸው ወጥቶ የራሱን አማራጭ እንዳይከተል ዙሪያውን አጥረውበታል፤ ከዛ አመልጣለሁ ካለ ከትምህርት ቤት ጀምሮ በተዘጋጁ ማጎሪያ (እስር ቤቶች) እንዲገባ ይሆናል፡፡ በመሆኑም የኢትዮጵያን መንግስት ለመርዳት ሙከራ ያደርጋሉ፡፡ ከእኛ ጋር አይደሉም ብለው የጠረጠሯቸውን በመግደል ቂም በቀላቸውን እየተወጡ ነው፡፡ በሌላ በኩል መማር ከቤተሰቦቻቸው ጋር ማደግ የሚገባቸው ሴቶችና ወንድ ታዳጊ ልጆችን አፍነው ወደ ጦር ሜዳ እየላኩ እንዲያልቁ እያደረጉም ያሉ አረመኔዎች ናቸው፡፡ ከዚህ አንጻር የትግራይ ህዝብ እነሱን መደገፉም መቃወሙም ዋጋ እያስከፈለው ከመሆኑም በላይ ትልቅ ሰቆቃ ላይ እንደሆነም ማወቅ ይቻላል፡፡ ይህንን ደግሞ ዓለም እንዲያውቅ እናንተም የበኩላችሁን መስራት አለባችሁ፡፡
አዲስ ዘመን ፦ ህወሓት ከዚህ በፊትም የሚከተለው መንገድ ህዝቦችን በብሔርና በጎጥ መከፋፈል ነበር፤ አሁንም ጦርነቱን ለጥቂት ብሔሮች ብቻ በመስጠት ሌላው ኢትዮጵያዊ አይመለከተውም አይነት ነገር እያደረገ ነውና እንደው ይህንን እንዴት ያዩታል?
አቶ ተስፋዬ ፦ ህዝቡን አሁንም ከዚህ በፊትም መከፋፋሉ ራሱ የመጣበት አመጣጥ ጤናማ ያልሆነና የቅኝ ግዛት የሚመስል ነገር ያለው በመሆኑ ነው፡፡ ሌላው ደግሞ ህዝብን በዚህ መልኩ መከፋፈሉ ከፍተኛ የሆነ ፖለቲካዊ ትርፍ ያስገኝልኛልም ብሎ ስለሚያስብ ነው። በመሆኑም በዚህ መልኩ ከፋፍሎ ወንድምና እህት ህዝቦችን አራርቆ በጠላትነት እያተያየ ካልሆነ በቀር ለወንበሩ ብዙ የሚያሰጉት ነገሮች ስለነበሩ አካሄዱን ተጠቅሞበታል።
ይበጀኛል ወዳለው ጦርነት ሲገባም ጦርነቱን የአንድና የሁለት ክልሎች ለማስመሰል ብዙ ጥረት አድርጓል፤ ይህም አንዱ የፖለቲካዊ ትርፍ አገኝበታለሁ ብሎ የሚያስበው አካሄዱ ነው። ነገር ግን በተለይም አሁን ላይ ይህ አይነቱ አካሄድ የተነቃበት ከመሆኑም በላይ ጊዜው ኢትዮጵያዊነት እያቆጠቆጠ ህዝቡም ከመከፋፈል ይልቅ አንድ ወደመሆን እየመጣ ያለበት በመሆኑ ከዚህ በኋላ ይህ ኋላቀር አካሄዱና ግምቱ የሚያስኬደው አይደለም። ወያኔ ከአሁን በኋላ እንኳን ኢትዮጵያን ትግራዋይን አሳምኖ ክልሉን ማስተዳደር የማይችልበት ቁመና ላይ ደርሷል። ምክንያቱ ደግሞ ትግራይን የወጣቶች የሰቆቃ ምድር አድርጓታል፤ በዚህ ደግሞ እያንዳንዱ ሰው የወንድሜን ገዳይ አይቼዋለሁ ቀን ሲወጣ እንገናኝ እያለ ነው። ከዚህ የተነሳ የተማመኑበት የትግራይ ምድር እንኳን ወደ ስልጣን የሚያወጣቸው ሳይሆን መቀበሪያቸው ይሆናል።
አዲስ ዘመን ፦ አሸባሪው ህወሓትንና የኦነግ ሸኔን የጥፋት ጥምረትስ እንዴት አዩት ?
አቶ ተስፋዬ፦ “መሪያቸው አንካሳ ተከታዮቹ አንካሶች” የሚል የትግረኛ አባባል አለ። ከዚህ ተነስተን ባህርያቸውን ብናይ ኦነግ ሸኔ ከለውጡ በኋላ ወደ አገር ሲገባ በመንግስት ደረጃ አቀባበል ተደርጎለት እርሱም ከዚህ በኋላ ሰላማዊ ትግል ምርጫዬ ነው ካለ በኋላ በዚህ መሰሉ እኩይ ተግባር ላይ ተሰማርቶ መገኘቱ የኦሮሞን የነጻነት ጭላንጭል ለማጥፋት እየጣረ ያለ መሆኑን የሚያሳይ ነው። በሌላ በኩል ደግሞ ይህ አሸባሪ ድርጅት እስከ አሁን የወጣበትን አላማ አንዷን እንኳን ያላሳካ ባለፉት በርካታ ዓመታት በህወሓት ከስሙ ጀምሮ እስከ ምግባሩ ድረስ ሲሰደብ ሲዋረድ ብሎም አሸባሪ ተብሎ ሲፈረጅ የኖረ ድርጅት ከመሆኑ አንጻር እንደዛ ሲያሳድደው ሲያስረው ሲገርፈው እንዲሰወር ሲያደርገው ከነበረ ድርጅት ጋር መጣመሩ እውነት ለመናገር ቆሜለታለሁ የሚለውን የኦሮሞ ህዝብ መካዱን ቁልጭ አድርጎ ያሳየ ተግባር ነው።
በሌላ በኩልም ይህ ጥምረት የሚያሳየው ኦነግ ከዚህ በፊትም ከ40 ያላነሱ ዓመታትን ጫካ ያሳለፈው ለኦሮሞ ህዝብ እኩልነት ሳይሆን ለስልጣን ጥማት መሆንም እንድንረዳ አድርጎናል ።
አሸባሪው ህወሓት የሚከተለው ያው የቅኝ ግዛት አካሄድን ነው፤ በአንደበቱም ኢትዮጵያን ለማፍረስ ከሰይጣን ጋርም ቢሆን እንደሚያብር ነግሮናል፤ በመሆኑም የእነዚህ ሁለት አሸባሪ ቡድኖች ሽርክና ወይም ህብረት አገርን ለማፍረስ የራሳቸውን የስልጣን ጥም ዳር ለማድረስ የተደረገ እንጂ ሁለቱም በሀሰትም ቢሆን ቆመንለታል ለሚሉት ህዝብ ምንም የሚፈይደው ነገር የሌለ መሆኑ ሊታወቅ ይገባል።
ስለዚህ አንድ አይነት ላባ ያላቸው ወፎች አብረው ቢበሩ ምንም የሚደንቅ አይሆንም፤ እነዚህ አካላት ከባህሪያቸው አንጻር ሰብዓዊነት አሳይተዋል ወይ ስንል ሁሉም ሰብዓዊነት ያልፈጠረባቸው ሰውን በዘርና በሃይማኖት እየከፋፈሉ የሚገድሉ ናቸው። በመሆኑም የእነሱ መጣመር ለፖለቲካዊ ንግድና ከዛ ለሚገኝ ትርፍራፊ ነው። ህብረታቸውም ነገ በታሪክ የሚጠየቁበት ይሆናል ።
አዲስ ዘመን፦ እነዚህን ሁለት እኩይ አላማን የተሸከሙ ሀይላትን ጥምረት የትግራይም ሆነ የኦሮሞ ህዝብ እንዴት ባለው ጥበብ ነው ሊያልፈው የሚገባው ይላሉ?
አቶ ተስፋዬ፦ ሁለቱም ጨካኞችና ጥቅመኞች ናቸው፤ አረመኔያዊነትን በተግባር መግለጽ ከተፈለገ እነዚህ ሁለት አሸባሪ ድርጅቶች የሚያደርጉትን ማንሳት ብቻውን በቂ ነው።በመሆኑም አረመኔያዊነት ትክክለኛ ትርጉሙን የሚያገኘው በኦነግ ሸኔና በወያኔ ነው። የኢትዮጵያ ህዝብ አሁን ላይ በእነዚህ ሁለት አረመኔ ድርጅቶች እየተፈተነና የጭካኔን ጥግ እያየ በመሆኑ እያንዳንዳችን ስለየአንዳንዳችን ለመሰዋት ዝግጁ መሆን አለብን። ይህ ደግሞ የኦሮሞንም ሆነ የትግራይን ህዝብ የሚመለከትና የሚያጠቃልል ነው።
በነገራችን ላይ እነዚህ አረመኔዎች ካሉ እንኳን መኖር አሟሟታችንም የማያምር በመሆኑ ትግላችን በተግባር በሃሳብ መገለጽ አለበት። አለበለዚያ ግን ኢትዮጵያውያን በሚያሳፍር ሁኔታ ራሳችንን እናዋርዳለን። አባቶቻችን በዚህ ክብር አቆይተውናል፤ እኛ ደግሞ እነዚህ አሸባሪ ሃይሎች የፈለጉትን እንዲያደርጉ መፍቀድ የእናት አባቶቻችን ደምና አጥንት ቀጥሎም በጭንቅላታችን ላይ እሳት መድፋት በመሆኑ የጀመሩትንም እንዳያሳኩ ባሉበት ሄዶ ማክሸፍ ያስፈልጋል። በመሆኑም እያንዳንዳችን ስለእያንዳንዳችንና ስለ አገራችን ብለን እኔ ልሰዋ እኔ በማለት እሽቅድድም ውስጥ የምንገባበት ጊዜ ቢኖር አሁን ነው። ለምን ስለ አገራችን በክብር ሞተን በክበር መቀበር ያለብን የተከበርን ህዝቦች በመሆናችን።
አዲስ ዘመን ፦ አሸባሪው ህወሓት ሁሌም ቢሆን እንደተጎዳ በተለይም ደግሞ የትግራይ ህዝብ በፌደራል መንግስት ግፍና ስቃይ እየደረሰበት እንደሆነ በተለያዩ መንገዶች ሲጮህ ነውና የሚውለው እንደው እርስዎ በዚህ ላይ ያልዎት አስተያየት ምንድን ነው?
አቶ ተስፋዬ፦ ይህ ሀይል እኮ ይህንን ባይል ነበር የሚደንቀው፤ ውሸታቸው እኮ በጣም ከባድ ነው፤ እስኪ እናንት ጋዜጠኞች ከክምችት ከፍላችሁ እያወጣችሁ በዚህ ጊዜ እውነት ተናግረዋል ብላችሁ አሳዩን። አሁንም ቢሆን የችግሩ ጠንሳሾች እራሳቸው ህዝቡን ችግር ውስጥ ጉዳት ላይ እንዲወድቅ ያደረጉትም ፈልገው ነው፤ የፌደራል መንግስትማ ለህዝቡም ለእነሱም የጥሞና ግዜ ያስፈልጋል ብሎ ሰራዊቱን ይዞ ክልሉን ለቆ ወጣ ፤ነገር ግን ስለ ህዝባችን ብለው ከእኩይ ተግባራቸው አልተቆጠቡም እንደውም አንዴ አማራን ሌላ ጊዜ አፋርን በመተንኮስ በግድ ጦርነት ካልገጠማችሁን አሉ እንጂ ፤ በመሆኑም እነሱ የፌደራል መንግስት ህዝቡን ይህንን አደረገ ያንን ሆነ ቢሉ ምንም የሚገርም ነገር የለውም። ለህዝባቸው ለመሸሸጊያቸው ያላሰቡትና ዘላለም በጦርነት አረር እንዲጠበስ ያደረጉት ራሳቸው ናቸው። ህዝቡ ግን እንደ ህዝብ ያሳዝናል፤ ነገር ግን እሱም ቢሆን መንቃትና ዞር በሉ ከላዬ ላይ ሊላቸው ይገባል።
በነገራችን እነዚህ አሸባሪዎች ህዝቡን እንደ አሁኑ መሳሪያ ይዘው አይግደሉት እንጂ ከዚህ ቀደምም ቢሆን በስሙ ከመነገድ ጀምሮ ለእርሱ ንጹህ የመጠጥ ውሃ እንኳን ሳያቀርቡ ፌደራል መንግስት የሚበጅትለትን በጀት ጥርግ አድርገው እየበሉ በሴፍቲኔት ሲያኖሩት ነበር፤ ምንም አይነት አማራጭ እንዳይኖረው ዝግትግት አድርገው በመቀመጥ ሲጨፈጭፉት፣ ሲያሳቅቁት፣ ሲያሳድዱት ነው የኖሩት።
አዲስ ዘመን ፦ የዓለም አቀፉን ህብረተሰብ ጫና እንዴት ያዩታል ?
አቶ ተስፋዬ፦ አይይ…..! ይህም እኮ የሚገርም አይደለም፤ ተላላኪህን አላኩትም አትልም። ምክንያቱም ልከኸዋላ ፤ ወያኔ እኮ የውጪው ዓለም በተለይም የኢትዮጵያን ልማት በጎነት የማይፈልጉ ሃይላት ቅጥረኛ ተላላኪ ነው።በመሆኑም የእነሱ አጀንዳ እያስፈጸመላቸው እየተላላከላቸው ኢትዮጵያን ለማፍረስ ሌት ተቀን እየሰራላቸው እንዴትና በምን ሁኔታ ነው ሊያወግዙት የሚችሉት?
በሌላ በኩልም አሜሪካ ከቅኝ ግዛት ሰንሰለት እንዴት እንደወጣች ። የሰሜኑና የደቡቡ ክፍል እገነጠላለሁ አትገነጠልም በሚል ያደረጉትን ውጊያ ብታጤነውና የእራሷን ታሪክ ብትመረምር ደስ ይለኝ ነበር። ነገር ግን የአሜሪካን ፖለቲከኞች ታሪካቸውን ረስተዋል።
በመሆኑም ኢትዮጵያውያን የውጭ ሀይሎችንም ይሁን ተላላኪዎቻቸውን ባሉበት መግታት፤ የራሳችንን አንድነት ማጠናከር፤ ከዛም እያንዳንዱ ሰው ጦር ሜዳ በመሄድ እዛ ሄዶ መዋጋት ሁኔታዎች የማይፈቅዱለት ደግሞ በተሰማራበት የስራ መስክ ነጋዴው በስራው ታማኝ በመሆን ህብረተሰቡን በማገልገል ብሎም ለአገሩ የሚገባውን ግብር በወቅቱ በመክፈል አስተማሪው ለሚያፈራው ትውልድ ትኩረትን ቅድሚያ ሰጥቶ በመስራት ሌላውም እንደዛው በማድረግ አገር ከተከፈተባት ዘርፈ ብዙ ችግር መታደግ ብሎም ምዕራባውያንና ተቋማቶቻቸውን ማሳፈር ይገባል።
በሌላ በኩልም ለመከላከያችን ሞራልና ስንቅ በመሆን አጋርነታችንን በመግለጽ አገራችን በሁለት እግሯ ቆማ የምትታይበትን ሁኔታ ማመቻቸት አለብን።
አዲስ ዘመን ፦ ፌደራል መንግስት ሰራዊቱን ከትግራይ ክልል ለማስወጣቱ አንዱና ትልቁ ምክንያት ደጀን ማጣት ነበርና እንደው ከዚህስ በኋላ የትግራይ ህዝብ ለሰራዊቱ ብሎም ለመንግስት በምን መልኩ ነው ደጀንነቱን መግለጽ የሚገባው?
አቶ ተስፋዬ፦ አሁን ላይ የትግራይ ህዝብ ከምን ጊዜውም በላይ ጠላቱን በደንብ የለየ ይመስለኛል፤ ከዚህም በኋላ ሌላ ጦርነት ማስተናገድ የቅኝ ግዛት ኑሮ በሚመስል ሂደት ውስጥ ማለፍ ልጆቹን መገበር ስደት መውጣት መራብ መጠማት ማየት የለበትም፤ የሚፈልግም አይመስለኝም። እስከ አሁንም ችግሩ ሳይገባው ወይንም ደግሞ ለመከላከያው ደጀን መሆን ሳይፈልግ ቀርቶ ሳይሆን የሚያስተባብረው የሚያምነው አካል አጥቶ ነው። በመሆኑም ኢትዮጵያውያን እህት ወንድሞቹ ይህንን ችግሩን ተረድተው በምግብ እርዳታም እየደረሰበት ላለው ስቃይ በማስተዛዘንም ከተባበሩት የትግራይ ህዝብ ጠላቱን በሚገባ ያወቀ ይመስለኛል። ይዋል ይደር እንጂ አሸባሪው ህወሓት ላይ መነሳቱም የማይቀር ነው።
አዲስ ዘመን፦ ለነበረን ቆይታ በጣም አመሰግናለሁ።
አቶ ተስፋዬ ፦ እኔም አመሰግናለሁ።
እፀገነት አክሊሉ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 28/2013