ህጻኑ በኮልታፋ አንደበቱ የእናት አባቱን ስም ደጋግሞ ይጠራል። አሁንም ልክ እንደ ትናንቱ ከጎኑ መሆናቸውን እያሰበ ነው። ዛሬም እናቱ በፍቅር ዓይን እያየች ከሞሰቡ እንጀራ፣ከጓዳው ወተት እንድትሰጠው ይጠብቃል። ለእሱ በቤቱ የተሰባሰቡት ሀዘንተኞች ትርጉም የሰጡት አይመስልም። ከእንግዶቹ መሀል ወላጆቹን እየፈለገ ድምጻቸውን ይናፍቃል። እንደልጅነቱ ከአባቱ ጉያ መወሸቅ መታቀፍን ይሻል። በዓይኖቹ ከወዲያ ወዲህ እየማተረ ነው።
ሁኔታውን ያስተዋሉ እንግዶች ዕንባቸውን መቆጣጠር ተስኗቸዋል። ህጻኑ ደጋግሞ የሚናገረው እውነት ለብዙዎች የልብ ስብራት ሆኗል። ከቀናት በፊት በእናት አባቱ ሙት አካል መሀል በደም ተለውሶ መገኘቱ ተዓምር እያስባለ ነው።
የእሱ በህይወት መትረፍ ለታሪክ ቢለው እንጂ የወላጆቹን ነፍስ የነጠቁ ክፉዎች ሊተውት አዝነውለት አልነበረም። ህጻኑ የሆነውን ሁሉ መርሳት አልተቻለውም ተደጋጋሚው ‹‹እናንዬን ድው አደረጋት›› ይሉት ንግግር ከጨቅላ አእምሮው ተቀርጾ በየደቂቃው ይሰማል። ‹‹እናንዬን ድው አደረጋት›› አሳዛኝ እውነት የያዘ መራር ታሪክ፣ አይረሴ ሀቅ የቋጠረ ክፉ አሻራ። በህጻኑ አማን ደሴ ጨቅላ አእምሮ በአይሽሬ ቁስል የታተመ አይለቄ ንቅሳት ሆኗል።
ጋይንት ወረዳ ንፋስ መውጫ ከተማ የሚኖሩት ጥንዶች በትዳር ዓመታትን አሳልፈዋል። የአብራካቸው ክፋይ የሆኑ ሶስት ልጆቻቸውን አሳድገው፣ አስተምረው ለወግ ማዕረግ ማብቃት የዘወትር ህልማቸው ነበር። በእነሱ ድካም የልጆቻቸውን ፍሬ ማየት ይሻሉና እንደ ወላጅ ማድረግ ከሚገባቸው ግዴታዎች ታቅበው አያውቁም።
አቶ ደሴና ወይዘሮ ገነት የአሸባሪው ጥቃት ቢያሳስባቸው ከቤት ከግቢያቸው ወጣ ብለው መንገድ ጀምረዋል። ምናልባት ከስፍራው ቢርቁ ሞትን ሊያመልጡት ይችላሉ። በወጉ ያልጠነከረው የሁለት ዓመቱ ህጻን አብሯቸው አለ። ወይዘሮዋ ጨቅላውን በጀርባቸው አዝለው ከባለቤታቸው ጋር ሽሽት ይዘዋል። ራቅ ወዳለው የአማቾቻቸው መንደር።
ጥንዶቹ ከሌሎች ቀደም ብለው መውጣታቸው ነበር። ከኋላቸው ቀሪው ቤተሰብ እንደሚከተል ያውቃሉ። ጥቂት እንደተራመዱ ግን ያልጠበቁት ዱብዕዳ ወረደባቸው። ከፊት ለፊታቸው መሳሪያ ታጥቀው ሲመጡ የተመለከቷቸው የአሸባሪው ህወሓት ቡድኖች በባልና ሚስቱ ጥይት አርከፈከፉባቸው።
አቶ ደሴና ወይዘሮ ገነት እንዳሰቡት ሆኖ ከመንገዳቸው አልደረሱም ። እንደ ምኞታቸው ከሞት አላመለጡም። ትንሹን ልጃቸውን አማንን ከመሀል እንደታቀፉ በግፈኞቹ ጥይት ህይወታቸውን ተነጠቁ። የወይዘሮዋ እናት ተኩስ ሰምተው ከቦታው ሲደርሱ ትንሹ ልጅ በእናት አባቱ መሀል ወድቆ ደም እንደተለወሰ ሲያለቅስ አገኙት።
በዕለቱ ከጥንዶቹ ባለፈ ሶስት የቤተሰቡ አባላት በአሰቃቂ ሁኔታ ተገደሉ። ይሄው ዛሬ ለእሳቸውና ለትንሹ የልጅ ልጃቸው አይረሴ ጠባሳ ተርፏል። አሁን ትናንት በእናት አባታቸው ተስፋ የሚያደርጉት ልጆች ቀን ጨልሞባቸዋል። ደስተኛው ቤተሰብም እጅግ በከፋ ሀዘን ተውጧል።
ትንሹ አማን እንደጨነቀው እንደተከፋ ቀጥሏል። ጨቅላ አእምሮው የሚያዘውን፣ስሜት እየደጋገመ ነው። ‹‹እናንዬን ድው አደረጋት›› ይሉትን ቃል ከመናገር አልታቀበም። መለስ ብሎ ደግሞ ዕንባ ያራሰውን የሴት አያቱን ፊት በእጆቹ ይነካካል። ዓይናቸውን በሀዘኔታ እያየም ‹‹ዥም..ዥም በይ፣ ይላቸዋል። ጭንቀት በዋጠው ፣ሀዘን በያዘው የልጅ አንደበቱ።
የሽብርተኛው የህወሓት ቡድን የጭካኔ ድርሳን ተገልጦ አላለቀም። ሐምሌ 16 ቀን 2013 ዓ.ም ለተለመደው የጥፋት ዓላማ በአዲአርቃይ ከተማ ተገኝቷል። ይህ ሰው በላ ቡድን የሚያዘንበው ከባድ መሳሪያ ተረኛ ያደረገው ተረኞቹን የአንድ ቤተሰብ አባላት ሆኗል።
በዕለቱ በከተማዋ በደረሰው ጥቃት ከአንድ ቤተሰብ አራት ሰዎችን አጥፍቷል። በጥቃቱ ሰለባ ከሆኑት ቤተሰቦች አንዷ ወይዘሮ አገሬ መኮንን ሀዘናቸውን ዕንባ ብቻ አልገለጸውም። በግፈኛው አሸባሪው ቡድን የተነጠቁ ቤተሰቦቻቸውን ሞት እንደዋዛ አምኖ መቀበል ተስኗቸዋል። እሳቸው በጥቃቱ መነኩሴ እናታቸውን፣የግንባታ ባለሙያ ወንድማቸውን፣ ከባለቤቱና ከአምስት ዓመት ሴት ልጁ ጋር ተነጥቀዋል። ይህ ብቻ አይደለም የአሸባሪው የጭካኔ ለበቅ ያረፈባቸው ሁለት ጎረቤቶቻቸውም ከጥቃቱ ማምለጥ አልቻሉም።
ጭራው የተረገጠበት የአሸባሪው ህወሓት ቡድን የክፋት ግብር አሁንም ቀጥሏል። ቡድኑ ደቡብ ጎንደር ዞን ጋይንት ወረዳ በቆየባቸው አስር ቀናት ያቀደውን ጭካኔ ለመፈጸም ያገደው አልነበረም። ቤተሰብ እየነጠለ ፣ቤት ንብረት እየመረጠ በሚፈጽማቸው አሳፋሪ ተልዕኮዎች የበርካቶችን አይን በደም ዕንባ ሞልቷል። ህጻናት ተደፍረዋል፤ ንጹሀን ተገድለዋል።
ከቀናት በአንዱ ዕለት የሽብር ቡድኑ የክፋት ዓይኖች በአንድ የቤተሰብ አባላት ላይ አረፉ። የአሸባሪው መርዛማ ቀስቶችም እንደለመዱት ከአንድ የቤተሰብ አባላት ላይ አነጣጠሩ። ሶስቱ ወንድማማቾች በላይ ጋይንት ወረዳ የነፋስ መውጫ ነዋሪዎች ናቸው። በዕለቱ ዘመድ ጠይቀው ወደቤታቸው እየተመለሱ ነበር።
በድንገት በወንድማማቾቹ ፊት የተጋረጡት የክፋት ቡድኖች ድንገት ‹‹እጅ ወደላይ›› ሲሉ አዘዟቸው። ሶስቱ ወጣቶች መሳሪያ አልታጠቁም ። ተደናግጠው የተባሉትን ለመፈጸም ሞከሩ። ‹‹ተማርካችኋል›› የሚል ድምጽ ከመሰማቱ በሶስቱም ላይ የጥይት ውርጅብኝ ዘነበ። ሁሉም በደም ተነክረው ከጎዳናው ወደቁ። ቡድኑ ይህን ከፈጸመ በኋላ ወደ መኖሪያ ቤታቸው ዘለቀ። ከስፍራው ያገኘውን ሀብትና ንብረትም ዘረፈ።
አሸባሪው ይህ ብቻ አልበቃውም። የሶስቱ ወንድማማቾች አስከሬን ተነስቶ በክብር እንዳያርፍ ለሟቾቹም እንዳይለቀስ በጥብቅ ከለከለ። ለሶስት ቀናትም አስከሬኑ ከወደቀበት እንዳይነሳ አገደ። እንዳለውም ሆነ።
አሁንም የአሸባሪው የህወሓት ቡድን ደም እንደጠማው መክለፍለፉን ቀጥሏል። ተከታዩን የጭካኔ ዓላማ ዕውን ለማድረግም ደብረታቦር ከተማ ደርሷል። ነሀሴ 13 ቀን 2013 ዓ.ም። ይህ ቀን በኦርቶዶክስ ዕምነት ተከታዮች ዘንድ የቡሄ ወይም የደብረታቦር በዓል በመባል ይከበራል። በተለይ ደግሞ በደብረታቦር ከተማ በዓሉ በተለየ ስሜትና ትርጓሜ ይከበራል።
ይህ ቀን ግን ለአቶ ድረሰ ነጋና ቤተሰቦቻቸው አይረሴ የጨለማ ዕለት ሆኖ ውሏል። አቶ ነጋ በዚህ ቀን የፍልሰታን ጾም ለማስቀደስ ወደ ቤተክርስቲያን አቅንተዋል። ሲመለሱ ባለቤታቸው ቤት ያፈራውን አዘጋጅተው ቡና ጸዲቁን አቅርበው ይቆይዋቸዋል። ተወዳጅ ልጆቻቸውም እንደሁልጊዜው ከእሳቸው ጥግ አይርቁም።
አባወራው ቤተክርስቲያን እንዳሉ የከባድ መሳሪያ ድምጽ ከጆሯቸው ደረሰ። ደነገጡ። ወዲያው ቤተሰቦቻቸው ውል አሉባቸው። እየሮጡ ወደቤታቸው ሲቃረቡ ደማቅ እሪታ ሰሙ። እየወደቁ፣እየተነሱ ካሰቡት ደረሱ። ከደቂቃዎች በፊት በሰላም የሸኛቸው መኖሪያ ቤት እንዳልሆነ ሆኗል።
እየጮሁ፣እያለቀሱ ያገኙትን ሁሉ ጠየቁ። ባለቤታቸውና አራት ልጆቻቸው እንደቅጠል ረግፈዋል። ከእነዚህ መሀል የልጃቸው ልጅ የሆነች የአራት ወር ህጻን በከባድ መሳሪያው ሀሩር ህይወቷን አጥታለች።
የአሸባሪው ህወሓት ቡድን የጭካኔ ግብር ከህይወት ማጥፋት አልፎ የሰብአዊ እርዳታዎች እስከመዝረፍና መቀማት ተሻግሯል። በቅርቡ የአሜሪካው ተራድኦ ድርጅት ዩኤስ ኤድ በሰጠው መግለጫም ይህንኑ ሀቅ አረጋግጧል። ድርጅቱ እስከዛሬ ለአሸባሪው የህወሓት ወታደሮች እርዳታን ያቀብላል እየተባለ የሚቀርብበትን ክስም ውድቅ አድርጓል።
በኢትዮጵያ የዩኤስ ኤድ ሚሽን ዳይሬክተር ሾን ጆንስ አሸባሪው ህወሓት የእርዳታ ድርጅቱን ንብረቶችና የእርዳታ ቁሳቁሶች በትክክል ስለመዝረፉ አመኔታቸውን ሰጥተዋል። በዚሁ ምስክርነታቸውም ከፍተኛ ቁጥር ላላቸው ተፈናቃዮች የሚያስፈልግ የምግብ እርዳታን በጊዜው ለማድረስ ድርጅታቸው በቅንነት እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል። ትጥቅ አንግቦ ለሚንቀሳቀስ ቡድንም እርዳታና ድጋፍ አድርጎ እንደማያውቅ ይናገራሉ።
ሀላፊው በእርግጠኝነት ሲገልጹም አሸባሪው ሰርጎ በገባባቸው አካባቢዎች በሙሉ የእርዳታ መጋዘኖችን በመስበር ዝርፊያ ፈጽሟል። በተረጂዎች እጅ የሚገኙ የእርዳታ ምግቦችንም በአስገዳጅነት ነጥቆ ወስዷል። መኪኖችን በመዝረፍ በየመንደሩ አሰቃቂ የሚባሉ ድርጊቶችን ፈጽሟል።
የአሸባሪው አሰቃቂ ድርጊት ከህሊና በላይ ነው። በቀላሉ ተነግሮና ተጽፎ የማያልቅ። ይህንን አሰቃቂ ግፍ ሰብዓዊነት የሚሰማው የሰው ልጅ ሁሉ ሊያወግዘው ይገባል ።
ከአትጠገብ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 27/2013