ኢትዮጵያ በምትታወቅበት አትሌቲክስ ስፖርት ባለፈው ሳምንት መጨረሻ በተካሄዱ ውድድሮች ታሪካዊ ድሎችን ማስመዝገብ ተችሏል።በቶኪዮ እየተካሄደ ባለው የፓራሊምፒክ ውድድር ላይ በታሪክ የመጀመሪያ የሆነው የወርቅ ሜዳሊያ ተመዝግቧል።በሌላ በኩል በሰሜን አየርላንድ በተካሄደው የጎዳና ላይ ሩጫ በሴቶች ግማሽ ማራቶን የተሳተፈችው አትሌት ያለምዘርፍ የኋላው የዓለም ክብረወሰንን ከእጇ አስገብታለች።
ኦሊምፒክ ከተጠናቀቀ በኋላ ቀጥሎ በሚካሄደው የፓራሊምፒክ ጨዋታዎች ላይ ኢትዮጵያ መሳተፍ የጀመረችው እአአ በ2012 በተካሄደው የለንደን ኦሊምፒክ ሲሆን፤ በወቅቱ አንድ የብር ሜዳሊያ ነበር የተገኘው።ቀጥሎ በተካሄደው የሪዮ ኦሊምፒክም በተመሳሳይ የብር ሜዳሊያ ሲመዘገብ አበረታች ተሳትፎም ለማድረግ ተችሏል።ለሃገሪቷ ሶስተኛ ተሳትፎ በሆነው የቶኪዮ ኦሊምፒክ ደግሞ አዲስ ታሪክ እንዲጻፍ ያደረገ ወርቃማ ውጤት ተመዝግቧል።
ከመክፈቻው ዕለት ጀምሮ የኢትዮጵያን ባህል በማስተዋወቅ በመልካም ገጽታ እየተመሰገነ የሚገኘው ቡድኑ በውድድሮቹም አስደሳች ውጤት እያስመዘገበ ነው።በየአራት ዓመቱ ከሚካሄደው ኦሊምፒክ እኩል ደረጃ ባለው የፓራሊምፒክ ውድድር ኢትዮጵያ በታሪኳ የመጀመሪያውን የወርቅ ሜዳሊያ ስታስመዘግብ፣ አትሌት ትዕግስት ገዛኸኝ ታሪካዊቷን የወርቅ ሜዳሊያ አጥልቃለች።በዚህ ውድድር ላይ በጭላንጭል አይነስውር 1ሺ500 ሜትር ውድድር የምትሳተፈው ብቸኛዋ ሴት አትሌት በፓራሊምፒክ መክፈቻ ዕለት የሃገሯን ባንዲራ በመያዝ ቡድኑን መምራቷ የሚታወስ ነው።
በአሰልጣኝ ንጋቱ ኃብተማርያም የምትሰለጥነው አትሌቷ ከሁለተኛ ዙር ጀምሮ ውድድሩን በማክረር የሮጠች ሲሆን፤ የመጨረሻው ዙር ላይም ሞሮኳዊት ተፎካካሪዋን በከፍተኛ ርቀት ጥላት በመግባት ለሃገሯ ድል ለማስመዝገብ ችላለች። ድንቅ ብቃት በማሳየት ያሸነፈችው የ21ዓመቷ ወጣት አትሌት ርቀቱን ያጠናቀቀችበት ሰዓትም 4፡23፡24 ሆኖ ተመዝግቦላታል።በዚህ ርቀት በሴቶች የተያዘው ክብረወሰን 4፡05፡27 መሆኑንም መረጃዎች ያመላክታሉ።
በፓራሊምፒክ የሜዳሊያ ብዛት የደረጃ ሰንጠረዡን በመምራት ላይ የምትገኘው ቻይና፤ እስካሁን 119 ሜዳሊያዎችን የግሏ ለማድረግ ችላለች።ተከታይ ሃገር እንግሊዝ 64 ሜዳሊያዎችን ስታስመዘግብ፤ አሜሪካ በበኩሏ በሰበሰበቻቸው 46 ሜዳሊያዎች ሶስተኛዋ ሃገር ሆናለች።አንድ የወርቅ ሜዳሊያ ያላት ኢትዮጵያ ደግሞ 45ኛ ላይ ለመቀመጥ ችላለች።
በሶስት አትሌቶች የተወከለችው ኢትዮጵያ ቀዳሚውን ሜዳሊያ በአትሌት ትዕግስት ስታስመዘግብ፤ በ1500 ሜትር ለፍጻሜ የደረሰው አትሌት አመኑ ገመቹ የዲፕሎማ ባለቤት ለመሆን ችሏል።በእጅ ጉዳት ምድብ የተካፈለው አትሌቱ ውድድሩን ለማጠናቀቅ 03:56:04 የሆነ ሰዓት ፈጅቶበታል።ሌላኛው አትሌት ታምሩ ከፍያለው ዛሬ ሌሊት በ1ሺ500 ሜትር ውድድሩን አድርጓል።ከአምስት ዓመት በፊት በተካሄደው የሪዮ ኦሊምፒክ ተሳታፊ የነበረው አትሌቱ ለኢትዮጵያ ሁለተኛውን የብር ሜዳሊያ ማስመዝገቡ የሚታወስ ነው።
በዓለም አትሌቲክስ ዕውቅና በሚካሄደው የአንትሪም ኮስት የጎዳና ላይ ውድድርም ኢትዮጵያ በክብር የተነሳችበት ሌላኛው ስኬት ሰፍሯል።በአውሮፓዊቷ ሃገር በሚካሄደው በዚህ ውድድር ላይ በግማሽ ማራቶን የተሳተፈችው አትሌት ያለምዘርፍ የኋላው በርቀቱ የዓለም ፈጣኗ ሴት አትሌት የሚያደርጋትን ድል አስመዝግባለች።አትሌቷ ክብረወሰኑን ከእጇ ያስገባችው 18 ሰከንዶችን በማሻሻል ሲሆን፤ 1:03:44 የሆነው ሰዓት አዲስ የገባችበት ነው።
የዓለም ክብረወሰኑ የተመዘገበው ከአምስት ወራት በፊት የሰዓቱ ባለቤት ሩት ቺፕጌቲች ርቀቱን ለማጠናቀቅ የፈጀባት ኬንያዊቷ 1:04:02 ነበር።በወቅቱ በተካሄደው ውድድር ኬንያዊቷን ተከትላ የገባችው ያለምዘርፍ 1:04:40 በሆነ ሰዓት ነበር የገባችው።ከወራት ልዩነት በኋላም የራሷን ሰዓት ከአንድ ደቂቃ በላይ ፈጥና በመግባት ፈጣኗ አትሌት ለመሆን ችላለች።አትሌቷ አስደናቂ በሆነ መልኩ 5ኪሎ ሜትሮችን ያሸፈነችው በ15 ደቂቃ ሲሆን፤ 10 ኪሎ ሜትሩን የሮጠችው ደግሞ በ30 ደቂቃ ነው።ቀጣዩን 15 ኪሎ ሜትር በ45 ደቂቃ ከሮጠች በኋላ ፍጥነቷን በመጨመር 21 ኪሎ ሜትሩን በ1 ሰዓት ከ03 ደቂቃ ከ44 ሰከንድ በመሮጥ የርቀቱን የመጨረሻ መስመር ለመርገጠ ችላለች።
የ22ዓመቷ ወጣት ከሩጫው በኋላ በሰጠችው አስተያየትም ‹‹ይህ ህልሜን እውን ያደረገ ውጤት ነው።ከዚህ ቀደም ሁለት ጊዜ የዓለምን ክብረወሰን ለመስበር ብሮጥም አልተሳካልኝም።አሁን ግን ስለተሳካልኝ ደስተኛ ነኝ›› ብላለች።አትሌቷ ከዚህ ቀደም በተካሄደው የዓለም ግማሽ ማራቶን ቻምፒዮና የነሃስ ሜዳሊያ ተሸላሚ ስትሆን፤ በሪዮ ኦሊምፒክ ሃገሯን በ10ሺ ሜትር ለመወከል ከጫፍ ብትደርስም በማጣሪያው በመበለጧ የቡድኑ አባል ለመሆን አልቻለችም ነበር።
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 25/2013