አብርሃም እንድርያስ በቢዝነስ ማኔጅመንት የመጀመሪያ ዲግሪውን ካገኘ በኋላ የመጀመሪያ ሥራው በአዳማ ዩኒቨርሲቲ መምህር ሆኖ ማገልገል ነበር። የአዳማ ዩኒቨርሲቲ መምህር ሆኖ እያገለገለ ነው ከመምህርነት ስራው ጎን ለጎን ሽንኩርት፣ ቲማቲም እና ጎመንን በማልማት የአትክልት እርሻ ለመጀመር የወሰነው።
አብርሃም ብዙም ሳይቆይ በኢትዮጵያ የእርሻ ስራ መስራት ከባድ መሆኑን ተረዳ። ለግብርና አስፈላጊ ግብዓቶችን (ዘሮችን እና ማዳበሪያዎችን) ወይም የሜካናይዜሽን አገልግሎቶችን ማግኘት አልቻለም። በተጨማሪም የሚያመርታቸው አትክልቶች ዋጋ አንዴ ከፍ ሌላ ጊዜ ዝቅ ይላል። በዚህም ምክንያት በአትክልቶች ልማት ያሳለፈው የሁለት ዓመታት ጉዞው በ2005 ዓ.ም በድንገት በኪሳራ መጠናቀቁን ለሀው ዊ ሜድ ኢት ኢን አፍሪካ በሰጠው አስተያየት ጠቁሟል።
ሆኖም ፣ አንድ ሀሳብ በአዕምሮው ውስጥ ተተክሎ ቀርቶ ነበር። አርሶ አደር መሆን ሳያስፈልገው በግብርና ውስጥ መሳተፍ እንደሚችል አሰበ። ለአነስተኛ አርሶ አደሮች አገልግሎት አቅራቢ መሆን እንደሚችል እና አነስተኛ አርሶ አደሮችም ከእሱ ግብዓቶችን እና አስፈላጊውን ድጋፎች ማግኘት የሚችሉበትን ስርዓት መዘርጋት እንደሚችል ማሰብ መጀመሩን ይናገራል።
በግምት 85 በመቶ የሚሆነው የኢትዮጵያ ህዝብ በአንድም ሆነ በሌላ መንገድ በግብርና ላይ በተለይም አብዛኛው በአነስተኛ እርሻ ላይ የተሰማረ መሆኑን የሚያብራራው አብርሃም፤ ለእነዚህ አርሶ አደሮች ግብርና ገቢ ማግኛ ቢዝነሳቸው ሳይሆን ህይወታቸው እና ባህላቸው ነው ይላል። ከግለሰብ አርሶ አደሮች ጋር በመስራት ትርፋማ እንደማይሆን ቢያውቅም ነገር ግን የአርሶ አደሮች ፍላጎት ተደምሮ ከሆነ እውነተኛ ዕድል እንዳለ ተገነዘበ።
የአትክልቱ እርሻ ሥራ ከከሰረ በኋላ አብርሀም ዝም ብሎ አልተቀመጠም። ይልቁንም ሌላ አዋጪ ያለውን ስራ መጀመር እንዳለበት አሰበ። ከዛም ለሁለት ዓመታት የጽሕፈት መሣሪያዎችን እና የኮምፒውተር መለዋወጫዎችን መሸጥ ቀጠለ። በዚህም በአጭር ጊዜ ውስጥ ገንዘብ የሚያገኝበትን መንገድ ተፈጠረ።
በ2007 አጋማሽ ላይ የተለያዩ የእህል ሰብሎችን ለመሰብሰብ የሚያገለግል ትራክተር እና ኮምባይን ሃርቨስተር ገዛ። በኦሮሚያ ክልል አርሲ እና በባሌ ዞኖች ለሚገኙ አርሶ አደሮች የሜካናይዜሽን ኪራይ አገልግሎት ለመስጠት ግሪን አግሮ ሶሉሽን የተባለውን ኩባንያ አቋቋመ። ከገበሬዎች ጋር በመነጋገር ብዙ ጊዜ ያሳልፍ እንደነበር የሚናገረው አብርሃም፤ ከአርሶ አደሮቹ ጋር ያደርግ የነበረው ተደጋጋሚ ውይይቶች በዘርፉ የሚፈለገውን የንግድ ሞዴል ዓይነት እንዲረዳ እንዳገዘው ይናገራል።
ይህን የገበያ ጥናት ስራ በ2008 እና 2009 ዓ.ም ቀጥሏል። በዚህ ጊዜ ሁሉ ዕቅዱን ወደ ተግባር ለመቀየር ምቹ ቦታን መፈለጉን ቀጥሏል። በዚያው ዓመት ከአዲስ አበባ በስተ ደቡብ አቅጣጫ 190 ኪሎ ሜትር ርቀት በምትገኘው እና በገብስ፣ በስንዴ፣ በድንች፣ በነጭ ሽንኩርት ምርት በምትታወቀው በሳጉሬ ከተማ የእርሻ አገልግሎት ማዕከል አቋቁሞ። ከዛም የመምህርነት ሥራውን ለቅቆ ወጣ።
ማዕከሉ በአካባቢው ለሚገኙ አነስተኛ አርሶ አደሮች ዘር ፣ ማዳበሪያ ፣ የእርሻ መሣሪያ እና ስልጠና መስጠት እንደጀመረ የሚያብራራው አቶ አብርሃም፤ እነዚህ አገልግሎቶች ጥሩ እድገት ያስገኙ ሲሆን በባሌ አካባቢ ሳተላይት ሱቅ በመክፈት ማስፋፋት ጀመረ።
አቶ አብርሃም ግን ብዙም ሳይቆይ ይህንን በተለምዷዊ መንገድ በመላ ሀገሪቱ የተለያዩ ቅርንጫፎችን በማስፋፋት የሚፈልገውን ውጤት ማስመዝገብ እንደማይችል የተገነዘበ ሲሆን በዚህ መልኩ ከቀጠለ የአሰራር ቅልጥፍናን ማሳካት አዳጋች እንደሚሆንበትም ተገነዘበ። “ግብዓቶቹን ከአዲስ አበባ በማምጣት የመስሪያ ቤት መከራየት ፣ የግብርና ባለሙያዎችን መቅጠር ፣ የሎጅስቲክስ ተግዳሮቶችን መቋቋም እንዲሁም በየጊዜው የሚነሳውን የፖለቲካ ሁከት መቋቋም የግድ ነበር። እነዚህ ከባድ ተግዳሮቶች በመሆናቸው በ2010 በዲጂታል መንገድ አገልግሎት ስለመስጠት ማሰብ ጀመርኩ ”ይላል።
የመጀመሪያው እርምጃ በሌሎች አገሮች ውስጥ የግብርና አገልግሎቶችን እና ግብዓቶችን ፍላጎት ካዋሃዱ ከነባር ብዝሃ መድረኮች መማር ነበር። አቶ አብረሃም ወደ ኬንያ ፣ ናይጄሪያ እና ህንድ ከተጓዘ በኋላ የተማረውን ተጠቅሞ በኢትዮጵያ ተግባራዊ አደረገ።
የኢትዮጵያ መንግስት በግብርና ግብዓት ማከፋፈያ እና አርሶ አደሮችን በማማከር አገልግሎት አውራ ተዋናይ መሆኑን የሚያብራረው አቶ አብርሃም፤ በቀበሌ ደረጃ ለልማት ጣቢያዎች የተመደቡ ከ 64 ሺህ በላይ በመንግሥት ተቀጥረው የሚሠሩ የልማት ወኪሎች አሉ፤ እና በእያንዳንዳቸው ቀበሌዎች ውስጥ ወደ አንድ ሺህ የሚጠጉ አነስተኛ ገበሬዎችን ማግኘት ይቻላል።
አቶ አብርሃም እንደሚለው፤ አንድ የልማት ወኪል አርሶ አደሮችን የሚያግዝበት የቴክኖሎጂ እገዛ ሳይኖረው አንድ ሺህ አርሶ አደሮችን የማገልገል ዕድሉ ዝቅተኛ ነው። ህዳር 2011 ዓ.ም በኩባንያቸው ለአርሶ አደሮች የተለያዩ ድጋፎች የሚደረጉበትን ዲጂታል ፕላት ፎርም ይዞ ወደ ግብርና ሚኒስቴር ቀረበ። የፕላት ፎርሙን አዋጭነት በማጥናት ከግብርና ሚኒስቴር ጋር ለመስራትም አጋርነት ፈጠረ።
የጥናቱ ውጤት አርሶ አደሮቹ በሶስት ዋና ዋና መስኮች ድጋፍ እንደሚያስፈልጋቸው እንዳመላከተ የሚያነሳው አቶ አብርሃም፤ የሜካናይዜሽን አገልግሎቶች፣ የእርሻ ግብዓቶች እንዲሁም የአየር ንብረት የምክር አገልግሎቶችን አርሶ አደሮች እንደሚፈልጉ በጥናቱ ተረጋግጧል። እነዚህን ሶስት ምሰሶዎች በአእምሮ ይዞ ኩባንያው ለእርሻ የተሰኘ ዲጂታል መድረክ እና መተግበሪያን ማልማት ጀመረ።
የዲጂታል ቴክኖሎጂው ዓላማ አነስተኛ አርሶ አደሮችን ከግብዓት አቅራቢዎች (እንደ የዘር ኩባንያዎች) እና ከትራክተር ባለቤቶች ጋር ማገናኘት መሆኑን የሚያብራራው አቶ አብርሃም ቴክኖሎጂው የአርሶ አደሮች ፋላጎት እንዲሟላ የሚያስችል ነው። የግብዓት እና ትራክተር አቅራቢዎች ምርቶችን እና አገልግሎቶችን ለማቅረብ ተነሳሽነት እንዲኖራቸው የእነዚህ አርሶ አደሮች ጥያቄ በአንድነት ለማቅረብ የሚያስችል ነው።
ለእርሻ በሽያጭ ላይ ከ5 እስከ 8 በመቶ ኮሚሽን ያገኛል። ግብይቶች በጥሩ ሁኔታ በመተግበሪያው በኩል የሚመቻች ሲሆን ፣ ነገር ግን በገጠር አካባቢዎች ባለው የግንኙነት ውስንነት ፣ በዝቅተኛ የሞባይል እና ቴክኖሎጂ ዕውቀት እጥረት ምክንያት ዲጂታል ቴክኖሎጂ ለአርሶ አደሮች አገልግሎት ማቅረቢያ ብቸኛው መንገድ ሊሆን አይችልም። ስለዚህ ለእርሻ የጥሪ ማእከል ያዘጋጀ ሲሆን በኤስ ኤም ኤስ እና በድምጽ አገልግሎቶችን ይሰጣል።
የታለመውን ተገልጋይ አርሶ አደር በብቃት ለመድረስ እና አገልግሎቶቹን ለማመቻቸት መተግበሪያው፣ የጥሪ ማዕከል እና የኤስ ኤም ኤስ በቂ አልነበረም። ብዙ ገበሬዎች የስልኮች ወይም የኢንተርኔት ዳታ ተደራሽነት ስላልነበራቸው ቴክኖሎጂውን መጠቀም አልቻሉም። በዚህ ምክንያት ለእርሻ ሥራ አጥ የሆኑትን የተማሩ ወጣቶችን ዒላማ በማድረግ ወኪሎችን ማሰልጠን ጀመረ።
እንደ አቶ አብርሃም ማብራሪያ፤ እነዚህ ወጣቶች የሚኖሩት በእነዚህ ማህበረሰቦች ውስጥ በመሆኑ እነሱ ቀድሞውኑ የአርሶ አደሮቹ እምነት አላቸው። ግሪን አግሮ ሶልዩሹን ወጣቶቹን በመቅጠር ፣ ሥልጠና በመስጠት በተለያዩ አካባቢዎች የኩባንያው ወኪሎች ሆኑ በእጃቸው መተግበሪያውን በመያዝ አርሶ አደሮቹ ወዳሉበት አካባቢ በመሄድ ለአርሶ አደሩ በአገልግሎቶቹ ተደራሽ እንዲሆን ማድረግ ቻሉ። ወኪሎቹ አርሶ አደሩን ይመዘግባሉ ግብይቶችን ያመቻቻሉ። በሆነ ምክንያት መተግበሪያው የማይሰራ ከሆነ ወኪሎቹ ወደ ጥሪ ማዕከል ይደውላሉ። እነዚህ ወኪሎች የግብይት ክፍያዎች ይሰበስባሉ።
ክፍያን ለማቃለል ፣ መተግበሪያው ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና ከተንቀሳቃሽ ስልክ የባንክ ስርዓት ሲ ኢ ቢ ኢ ብር እንዲሁም ከኦሮሚያ ህብረት ሥራ ባንክ እና ከአቢሲኒያ ባንክ ጋር የተቀናጀ መሆኑን የሚያብራረው አቶ አብርሃም፤ እያንዳንዱ ለእርሻ ስርዓት ላይ የተመዘገበ ገበሬ ወዲያው ከሦስቱ ባንኮች በአንዱ የሚሰጠውን ኢ- ዋሌት አገልግሎት እንደሚያገኝ አብራርተዋል።
ግሪን አግሮ ሶሉዩሽን የተሰኘው ድርጅቱ እና ለእርሻ የተሰኘው መተግበሪያ 35 ቋሚ ሰራተኞች አሉት። እስካሁን ከ42 ሺህ በላይ አርሶ አደሮች ተመዝግበው 88 ወኪሎች በ 11 ወረዳዎች ተመልምለው ስልጠና ወስደው ወደ ስራ ገብተዋል። በጠቅላላው 172 የሜካናይዜሽን አገልግሎት አቅራቢዎች ተቀናጅተው የሚሰሩበት ሁኔታ ተመቻችቷል። ግለሰቦች ፣ የአርሶ አደር ማህበራት ወይም የትራክተሮች ባለቤት የሆኑ የህብረት ሥራ ማህበራት ፣ የመከና እና ሌሎች የእርሻ መሣሪያዎችም ለኪራይ ዝግጁ ሆነዋል። ዘር የሚመጣው ከኦሮሚያ ዘር ኢንተርፕራይዝ እና ከኢትዮጵያ ዘር ኢንተርፕራይዝ መሆኑንም አቶ አብርሃም ጠቁሟል።
ኩባንያው በመንግስት ተቀጥረው ከሚሠሩ አንድ ሺህ 310 የልማት ወኪሎችም ጋር አብሮ እየሰራ ይገኛል። ለእርሻ ለነዚህ የልማት ወኪሎችም ዲጂታል ቴክኖሎጂውን እንዲጠቀሙ ሁኔታዎችን እያመቻቸ ሲሆን፤በተለይም ስለ አየር ንብረት የምክር አገልግሎቶችን እየሰጠ መሆኑ ተናግሯል። እያንዳንዱ የእርሻ ወኪል ግብዓቶች እና አገልግሎቶች ወደሚከፋፈሉበት በቅርብ ወደሚገኘው የእርሻ አገልግሎት ማዕከል አካባቢ ሆኖ አገልግሎቶችን ይሰጣል።
ኩባንያው ለሚቀጥሉት አራት ዓመታት ትልቅ የእድገት ዕቅዶች እና ከፍተኛ ግቦችን ይዞ እየተንቀሳቀሰ ነው። “በ2017 ኩባንያው በሁሉም የሀገሪቱ ክልሎች 4 ነጥብ 5 ሚሊዮን አነስተኛ ገበሬዎችን በማገልገል የአራት ሺህ 500 ወኪሎችን ወደ ስራ ማስገባት ይፈልጋል። ኩባንያው የተቀጣሪ ብዛት ከጊዜ ወደ ጊዜ ከፍ እያደረገ ነው።
ዕቅዱ ለእያንዳንዱ አንድ ሺህ አነስተኛ ገበሬዎች አንድ ወኪል እንዲኖር ነው። ይህ ማለት ኩባንያው ወደ 500 ሚሊዮን የሚጠጋ የኢትዮጵያ ብር (11 ሚሊዮን ዶላር) ገቢ ማግኘት ይችላል ማለት ነው። ተልዕኳችን ለሁሉም ሰው ግብርናን ቀላል ማድረግ ነው”ይላል አቶ አብርሃም።
መላኩ ኤሮሴ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 25/2013